FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, May 29, 2014

40 – 23 የኢህአዴግ የጎሳና የመጥበብ ሰረገላ ሐዲዱ ላይ ነውን?

“ኢትዮጵያን በጎሳ ሳጥን ቆልፎ የሚጓዘው ህወሃትና ድግሱ”

40 - 23


ህወሃት በነጻ አውጪ ስም ታግሎ ኢትዮጵያን መግዛት የጀመረበትን 23ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው። ወዳጆቹና መሪዎቹ ባስቀመጡት እቅድ መሰረት ኢትዮጵያን “በመተካካትና በተሃድሶ” ስም ራሱን እያገላበጠ ለመግዛት የቆረጠው ጊዜ በትንሹ 40 ዓመታት እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ባለው የሰረገላው ጉዞ ኢህአዴግ ከ40 – 23 ከመቀነሱ ውጪ አሰበበት ስለመድረሱ መገመት የሚያስችል ምልክት የለም። እንደውም ስጋት እንጂ።
ሲጀመር “የገበሬ ተሟጋች” ነኝ በማለት ራሱን የአርሶ አደሩ ወኪል አድርጎ የተነሳው ህወሃት፣ ኢህአዴግ ሆኖ አገር መግዛት ሲጀምር ያስቀደመው የብሄር ብሄረሰቦችን የመብት ጥያቄ እንደ ውዳሴ ጸሎት በመደጋገም ነበር። በዚሁ በጎሳ ላይ ተመስርቶ በቋንቋ የተቆለፈው የአገዛዝ ስልት ሲጀመር ማስጠንቀቂያ የሰጡ፣ ለመታገል የሞከሩ፣ የታገሉ፣ ያስተባበሩ፣ ያደራጁ የህወሃት የ40 ዓመት ጉዞ ጸር ተደርገው ተወሰዱ። ስለ ኢትዮጵያ ጥቅምና ኢትዮጵያዊነት ያሳሰቡ ጠላት ተደርገው ተፈረጁ። በስውር በአፈና፣ በግልጽ ህግ እየተጠቀሰባቸው ከጫወታና ከመኖር ተገለሉ። ብዙዎች እንደሚሉት “የጉዳቱን መጠን ህወሃትና የተጎዱት ቤተሰቦች ይቁጠሩት”!
ግንቦት ሃያ “የህዝብ የድል ክቡር ቀን ነው” በሚሉና “የህዝብና የአገር ውድቀት የታወጀበት የክፉ ቀኖች ሁሉ ድምር” ሲሉ በሚሰይሙት መካከል ሰፊ መከራከሪያ አለ። የመንገድ ግንባታ፣ የህንጻ ግንባታ፣ የኮሌጅና የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የግድቦች ግንባታና የአባይ ወንዝ ልማት ወዘተ ጉዳዮች የግንቦት 20 ጣፋጭ ፍሬዎች ስለመሆናቸው “የቀኑ ወዳጆች” ይከራከራሉ። የቀኑ “ባሮችም” ይህንኑ ውዳሴ በማቀንቀን ታማኝነታቸውን ይገልጻሉ። በጥቅም የተደለሉ ሎሌዎች ስለሆኑ ይህንን ድል ለማስጠበቅ በግልጽና በህቡዕ አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ።
በተጠቀሱት የልማት ስራዎች ላይ ተቃውሞ የማያነሱ የቀኑ “ሰለባዎች” ሰላምና መረጋጋት እንዳለ የሚሰብክ አስተዳደር ልማትን ከመስራት ሌላ ተግባር እንደሌለው ይገልጻሉ። አያይዘውም ጣሊያንም በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ መንገድና ድልድዮችን መገንባቱን ያጣቅሳሉ። ከሁሉም በላይ ግን ኢህአዴግ በሚገዛት አገርና ሕዝብ ስም የተበደረውን የገንዘብ መጠን “ከተዘረፈው ውጪ” በማለት ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “መንገድ መስራትና ህንጻ ማቆም የመብት ጥያቄን በጥይት ለመመለስና በደም ለመጨማለቅ ዋስትና ሊሆን አይችልም” በማለት ስርዓቱን አጥብቀው ይኮንኑታል።
በሌላም ወገን የተሰሩትን ህንጻዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች በማንሳት “የግንቦት 20 ፍሬዎች” ሲሉ ይሰይሟቸዋል። ሲያብራሩም “የነዚህ ሁሉ ሃብቶች መነሻና ባለቤቶች ህወሃትና ህወሃት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ባለሟሎች ናቸው። የህዝብ አይደሉም። ሕዝብም አያምንባቸውም” በማለት ጥርስ ይነክሱባቸዋል። በዝርፊያ ሃብት የሚያግበሰብሰውን ኤፈርት ኢትዮጵያን “ንብረቶችሽን ባደራ ላስቀምጥ” የሚል እስከሚመስል የንግድ ኢምፓየሩን ማስፋቱን አብዝተው ይኮንናሉ።
የግንቦት 20፣ የቀኑ ወዳጆች ኤፈርት ላይ የሚቀርበውን ጥያቄ አያስተባብሉትም። ይልቁኑም ድርጅቱ ጓዳና ካዝናው የተለጎመ መሆኑ ያብከነክናቸዋል። አለው የሚባለው ሃብት ሁሉ የትኛው ቋት እንደሚቀበር ስለማይረዱ “የተሸውደናል” ስሜት አላቸው። ለዚህም ይመስላል የህወሃት ወዳጆች “ኤፈርትን ያየህ ወዲህ በለኝ” ሲሉ የሚደመጡት። በግልጽ አነጋገር ኤፈርት ፊት ለፊት ከሚያሳየው ሃብቱ ይልቅ፣ የማይታው ጉዱ ስለሚያመዝን በህወሃት ወዳጆች ሳይቀር አልሞ ተኳሽ (ስናይፐር) የተደቀነበት ነው።
አፈናው፣ ግድያው፣ እስሩ፣ ዝርፊያው፣ ከላይ ከተገለጸው በተቃራኒ አርሶ አደሩ ላይ የሚፈጸመው የመሬት ቅሚያ ሌላው የግንቦት 20 የጨነገፈ ፍሬ ተደርጎ ይወሰዳል የሚሉ አሉ። በተለይም ራሱ ህወሃት ሁሉንም በራሱ ደረጃ ለማሳነስ ሲል ያዋቀረው የቋንቋና ጎሳን ተገን ያደረገ የአገዛዝ ስልት ዛሬ ግንቦት 20ን እድሜውን ወደ ማሳጠር እያደረሱት ነው ሲሉ ያክላሉ። በዚህ አስተሳሰብ ላይ የሚተቹ ሰሞኑን አጠንክረው እንደገለጸት “የግንቦት 20 ወዳጆች ኢትዮጵያዊነት ከውስጣቸው እንዲወልቅ ተደርጎ በተዘጋጀላቸው የትምህርት እቅድ፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ … መሰረት ወደ ጎሳ እየጠበቡ የግንቦት 20 ድል ‘ሰረገላው’ መድረስ የፈለገበት ቦታ ሳደርስ ሃዲዱን ሊያወላልቀው ይችላል”፡፡
40 – 23 ዓመት ላይ ያለው ኢህአዴግ ህወሃትን እያጀበና እየሞሸረ ወደ “መንገሻው” ለማድረስ የተሰሩበት የጎሳ ኬሚስትሪ እንደሚከለክላቸው የሚናገሩ ክፍሎች “የግንቦት 20 ድል እየተከበረ 40 ዓመት መዝለቅ ምናልባትም ከተረትም የወረደ ሟርት ነው” ባይ ናቸው። ህወሃት ለጊዜው ብሎ የዘራው የበቀል ዘርና በጎሳ ሳጥን ውስጥ ከቶ ያሳደጋቸው ወዳጆቹና በጊዜ የታሰረ ቦንብ እንደሚሆኑበት ምልክቶቹ ከበቂ በላይ እንደሆኑም ይናገራሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት “ህወሃትን የሚበሉት ራሱ ያመረታቸው ፈንጂዎቹ ናቸው” በመሆኑም የዘንድሮው ግንቦት 20 አንጸባራቂ ጥቅስ “ለመጥበብ ብሎ ህወሃት የወጠነው የጎሳ መዋቅርና አስተምህሮት የህወሃት ፉርጎ የሚሄድበትን ሃዲድ እያወላለቀው ነው” የሚለው ይሆናል – “ጉድጓድ የሚምስ ራሱ ይወቅድበታልና”፡፡
http://www.goolgule.com/23-years-of-40-and-eprdfs-mess/

የቅድመ ምርጫ አፈናው በውይይት እንዲተካ እንጠይቃለን!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

እንደሚታወቀው የግንቦት 2ዐን 23ኛ ዓመት ለማክበር ጉድ ጉድ እያለ የሚገኘው ገዥ ፓርቲ ወደ ጠቅላይ አምባገነን ፓርቲነት ከተለወጠ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ከመቆጣጠራቸው በፊት በርካቶች ስለ ነፃነት፣ እኩልነት፣ ሰብአዊ መብት መከበርና ዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን ክቡር ህይወታቸውን እንዲገብሩ ተደርጎ በተገኘ የዜጎቻችን መስዋእትነት መንበረ ሥልጣኑን ቢጨብጡም በተግባር ዋጋ የተከፈለበትን ዓላማ ለማሳካት አልቻሉም፡፡ እንዲሁም የህዝቦችን ነፃነት በጉልበት በመቀማት፣ ሰብአዊ መብትን በመጋፋት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማስመሰያነት በንድፈ ሃሳብ አስፍረው በተግባር በዜጎችዋ ግፍ በመፈፀም ነፃነውን ፕሬስ እንደጠላት በማየት፣ ተቀናቃኝ ኃይሎችንና የፖለቲካ መሪዎችን በማሰርና በማፈን፤ በነፃነት የመደራጀት መብትን በመጨፍለቅ በአጠቃላይ ፍፁም አምባገነን የሆነ ስርዓት በመዘርጋት ላይ ነው፡፡

UDJ/Andinet party logo
ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመሻሻልና የሁነቶች የመማሪያ ባህሪ ሊኖረው አልቻለም፡፡ ይልቁንም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ውጭ የሆኑትን በጅምላ በመፈረጅና በተናጠል ግለሰቦችን ከፖለቲካው አውድ በማስወገድ የእድሜ ልክ ገዢ የመሆን ሕልም ውስጥ ወድቋል፡፡
ፓርቲያችን አንድነትም ለሀገራችን የሚጠቅመው ይህ ያለመቻቻልና የጥፋት ጎዳና ሳይሆን የመነጋገር፤ እንዲሁም አሸናፊ የሆነው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያኝና የዜጎች መብት ለስልጣን ሲባል ሳይሸራረፍ እንዲከበር በሠላማዊ ትግል አቅጣጫ መግፋት ተገቢ መሆኑን በጽናት ያምናል፡፡ የአመራር አባሎቻችንም ሳይገድሉ እየሞቱ፤ ሳይደበድቡ እየተደበደቡ፤ ሳያስሩ እያታሰሩ ለህዝቡ የሚገባው ነገር እንዲደረግ ያለመታከት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አንድነት ህጋዊ መስመር በመከተልና በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥም ቢሆን ዓላማውንና ግቡን ፍፁም ሠላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ለህዝቡ ማድረስ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንዳለም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በህዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነትም እጅግ ጨምሯል፡፡ ነገር ግን ተቀባይነታችን በጨመረ ቁጥር በስጋት ባህር የሚዋኘው ገዢ ፓርቲ በአመራሮቻችንና አባሎቻችን ላይ እየፈፀመ ያለው ግልጽ በደልና በማናለብኝነት በጠራራ ፀሐይ ለመደብደብ የሞራል ችግር በሌለባቸው የደህንነት ሠራተኞችና ሆድ አደር ግለሰቦችን በማሰማራት እየተፈፀመ ያለው ግፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር የሆኑት የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ስዩም በጠራራ ፀሀይ ታፍነው እንቅስቃሴያቸውን የማያቆሙ ከሆነ እንደሚገደሉ የተነገራቸው ሲሆን፤ የአዲስ አበባ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በጠራራ ፀሐይ ወደቤታቸው ሲገቡ ከኋላቸው በድንጋይ ተመትተው ሲወድቁ ሞቱ ብለው ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡ እንዲሁም የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የመሀል ቀጠና አደራጅ አቶ ደረጀ ጣሰውን የማይታወቁ ግለሰቦች እንፈልግሀለን በማለት በመኪና አፍነው ለመውሰድ ትግል ሲያደርጉ ባሰሙት ጩኸት ህዝቡ ያስጣላቸው ቢሆንም አይናቸውን በቦክስ በመመታታቸው በከፍተኛ ህክምና ሊተርፉ ችለዋል፡፡ አንድነት ላይ እየተፈፀመ ያለው የአደባባይ አፈና በዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡ በቅርቡ አንድነትን የተቀላቀሉት አቶ አስራት አብረሃምም በኦሮሚያ ፖሊሲ ታፍነው እስካሁን ያሉበት አይታወቅም፡፡ ይህ በአዲስ አበባ አመራሮች የተፈፀመ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ አባሎቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን አፈናና እስራት ለመዘርዘር ከባድ ነው፡፡ ለአብነትም በወላይታ ሰዶ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በሆኑት የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና ምክትል ኃላፊው አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም የዞኑ የምክር ቤት አባላት፣ በደሴ ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ በአቶ አዕምሮ አወቀ ላይ የተፈፀመው ውንብድና፣ ድብደባ እስራትና አፈና ጠቋሚ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
በአመራሮችና አባላት ላይ ከሚፈፀመው አፈናና ክትትል በተጨማሪ የፓርቲውን ስም ለማጥፋትና ተቀባይነት ለማሳጣት አይጋ-ፎረምን የመሳሰሉ የሥርዓቱ ቀላጤ ሚዲያዎች ፀረ-ሠላም ከሚሏቸው ኃይሎችና አሸባሪ ብለው ከፈረጁአቸው አካላት ጋር ግንኙነት እንዳለን የሚያስመስል የልቦለድ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ፓርቲያችን ጠንክሮ መውጣቱን ሲሆን ከዚህ በኋላ በአፈና፣ በድብደባና በእስር እንዲሁም በፍረጃ አንድነትን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይችል ለማረጋገጥም እንወዳለን፡፡
ይልቁንም ገዢው ፓርቲ ካለፈው ስህተቱ በመማር፣ ከስለላ፣ ከፍረጃና ከአፈና በመላቀቅ ወደ ውይይት እንዲምጣ አሁንም ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአፈናና በጉልበት አሁንም ቀጣዩን ምርጫ ለመቀልበስ መሯሯጥ ባለዕዳ የሚያደርገው ገዢውን አካል መሆኑን ለማስገንዘብም እንወዳለን፡፡
የ23ት አመቱ የግንቦት 2ዐ ፍሬ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ቢኖር ይህ አስከፊ ስርዓት ያነበረው ጭቆናና በደል እስር እንግልትና በተጽእኖ ከሀገር መሰደድ ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ የተገነባው አብሮነት አደጋ ላይ መውደቁ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ የነፃነት ቀን ነው በሚሉት በግንቦት 2ዐ ዋዜማ እንኳ የዞን 9 ጦማሪዎች በማእከላዊ መከራ እየተቀበሉ ሲሆን የእስር እርምጃው ቀጥሎ ደራሲ አስራት አብርሃም ታፍኖ ከመሰወሩ ባሻገር የዕንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በተጨማሪ ወደ እስር ተግዟል፡፡ ይህም የግንቦት 2ዐ ፍሬ መሆኑ ነው፡፡
ምን አልባትም ሥርዓቱ የምርጫ 97 ሽንፈትን ተከትሎ በግብታዊነት ወደ መሰረተ ልማት ማስፋፋት በማተኮር አንዳንድ ቁሳዊ ልማት ለማሳየት ቢጣደፍም ማህበራዊ ልማትን ቀብሮ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን እረግጦ፤ ልማት አስመዝግቤአለሁ እያሉ አገዛዝን በኃይል ለማስቀጠል መሞከር የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ፓርቲያችን ዛሬም የዚችን ሀገር ዘርፈ ብዙ ችግር በኃይል ለማዳፈን ከመሞከር ወደ ውይይት እና ብሔራዊ መግባባት ማዘንበል ጠቃሚ መሆኑን አበክሮ ይገልፃል፡፡
ድል የሕዝብ ነው!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ግንቦት 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/12404/

የኢትዮጵያ ህዝብ ይወቅልኝ!

እታገኝ መኮንን ካሣ - በግፍ የሚሰቃዩ እናት

etagegn


እኔ ወ/ሮ እታገኝ መኮንን ካሣ አድራሻ፡- አዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 09 የቤት ቁጥር 760/ሀ ነዋሪ ነኝ፡፡ በአሁኑ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 09 ከላይ ቁጥሩ በተገለፀበት ቤት ከ40 ዓመት በላይ ተከ ራይቼ ስኖር በ1990 ዓ.ም በኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ መያዜን አወኩ፡፡
ቤቴንም ሆነ ልጆቼን እንዲጠብቅልኝና እንዲረዳኝ በማለት ከ1994-1997ዓ.ም ድረስ በውክልና ሰጥቸው የነበረ ሲሆን ከ97 በኋላ ግን ውክልናውን ትቶ የራሱን ቤት ሰርቶ ሄዷል፡፡ ቤቱ እስከታሸገበት ጥር 12 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ለአቶ ደረጄ ጎዳና ከመንግስት ተከራይ በማስመሰል በቤት ቁጥር 760/ሐ በአቶ ደረጄ ስም የአንድ አመት (በ1998 ዓ.ም) የቤት ኪራይ በስማቸው ቀበሌ ሂዶ ከፍሏል በማለት እኔ ደካማና በሽተኛዋን የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው በማለት ቤቴን ጥር 12 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በመድኃኒቴ እና በንብረቴ ላይ በማሸግ በእኔም ሆነ ቤተሰቦቼን ከፍተኛ ችግር ደርሶብናል፡፡
ሆኖም መጋቢት 24 ቀን 2006 ዓ.ም እኛን በፖሊስና በመሣሪያ ኃይል ከግቢ ውስጥ አስወጥተው ንብረቴን በሌለሁበት አውጥተውብኝ እኔ ስምንት ቤተሰቤን ይዤ ዕቃ ቤት እንድኖርና ግማሹ ንብረቴን ውጭ ተጥሎ ለዝናብምና ለፀኃይ እንዲጋለጥ በማድረግ ከፍተኛ ውድመት እንዲደርስብኝ አድርገዋል፡፡
በየደረጃው ላሉት የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ አቤት ብልም ቤቱን ለፈለጉት ሠው ለመስጠት ሲሉ ያላደረኩትን አድራጎት እያቀረቡ ጥፋተኛ ነሽ በማለት ለረዥም ወራት እያንከራተቱኝ መሄጃው ጠፍቶብኝ እገኛለሁ፡፡
ሁከት ስለፈጠሩብኝ ይወገድልኝ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ባቀርብም የወረዳ 09 ቤቶች ልማት ፅህፈት ቤት የሀሰት ማስረጃ እያቀረቡ ሁከት አልፈጠረም በማለት ውሳኔ ተሰጠብኝ፡፡ በበኩሌ በ2005ዓ.ም ይግባኝ ብልም ወረዳውን መጥራት ሳያስፈልገኝ የተሠጠው ውሳኔ ትክክል መሆኑን አረጋግጭአለሁ፤ መልስ ሰጪውን መጥራት አያስፈልግምብሎ መዝገቡን ዘግቶብኛል፡፡
እንዲሁም ሠው ሁልጊዜ ከማስችገር በማለት ትንሽዬ የሸራ መጠለያ አድርጌ ከሰል ቸርችሬ የማድርባትን መጠለያ የደረጄ ነው በማለት ግቢው ውስጥ ሁለት ክፍል አድርገው ቀምተው ሰኔ 16/2004 ዓ.ም ለአስቴር መለስና ለጌታቸው መለስ የልማት ተነሺ ናቸው በማለት ሰጥተውብኛል፡፡ አሁን ደግሞ የምኖርበትን ከመንግስት በየአመቱ የምዋዋልበትን ቤት ለኃይልና ለውኃ ልማት በፃፉት ደብዳቤ ቤቴ መሆኑን በማመልከቻ ላይ ገልጸውልኛል፡፡
እኔ እታገኝ መኮንን በየካ ክ/ከተማ በወረዳ 09 መንግስት ቤት ቁጥር 760ነዋሪ መሆኔን በ26 ዝውውር 2006 እስከ ዛሬ እኖርበት የነበረውን መኖሪያ ቤት ለልማት ተነሺዎች የተሰጠ መሆኑን በደብዳቤያቸው አረጋግጠዋል፡፡
እኔ የ63 አመት አዛውንት የሙት ልጆች ይዤ ብርድና ፀሀይ እየተፈራረቀብኝ እገኛለሁ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ እላለሁ! (ምንጭ: – ነገረ ኢትዮጵያ)
http://www.goolgule.com/the-misery-of-etagegn-mekonnen/

Sunday, May 25, 2014

ያለ በቂ ማስረጃ በሕገ ወጥ መንገድ ከአራት ሳምንት በፌት ከተያዙት ስድስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በተጨማሪ በአንድ ጦማሪ አባል መኖሪያ ቤት ላይ ፖሊስ ለ7 ሰአት የቆየ ብርበራ አካሄደ

Zone9

ያለ በቂ ማስረጃ በሕገ ወጥ መንገድ ከአራት ሳምንት በፌት ከተያዙት ስድስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በተጨማሪ በአንድ ጦማሪ አባል መኖሪያ ቤት ላይ ፖሊስ ለ7 ሰአት የቆየ ብርበራ አካሄደ፡፡Zone 9 bloggers
በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ በዞን ዘጠኝ ጦማሪና መስራች ሶልያና ሽመልስ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ፖሊስ ብርበራ ያካሄደ ሲሆን የጸረ-ሽብር ሕጉ ይፈቅድልናል የሚል ምክንያት ሰጥተው ያለ ፍርድ ቤት የብረበራ ማዘዣ ከካሜራ ቀራጭ ጋር የተገኙት ሰባት ፖሊሶች በጦማሪዋ ክፍል እና ሌሎች አስፈላጊ ነው ባሉዋቸው ክፍሎች ሲያካሂዱ ነበረውን ብርበራ ጨርሰው ይጠቅመናል ያሉትን የዶ/ር መረራ ጉዲና የመጨረሻ መጽሀፍ እና ሌሎች ወረቀቶች ወስደው ቤት ውስጥ የነበሩትን የጦማሪዋን ወላጅ እናት አስፈርመው ከጠዋቱ 4 ሰአት አካባቢ ቤቱን ለቀው ወጥተው ነበር፡፡ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመልሰው በመምጣት ተጨማሪ ፍተሻ በዋናው መኖሪያ ቤት መካሄድ እንፈልጋለን ብለው ሁለተኛ ዙር ብርበራ በምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ እናካሂዳከን በሚል ሰበብ ትንሹ ክፍል ውስጥ የጦማሪዋን እናት እነዲወጡ በማግለል ከማቀዝቀዛውን አንቀሳቅሰው አፍታም ሳይቆዩ 19 ገጽ የግንቦት ሰባት ፕሮግራም አግኝቻለሁ ሲል አንዱ ፈታሽ ተናግሯል፡።
የጦማሪዋን ወላጅ እናት እነዲፈርሙ ያግባቡ ቢሆንም ወላጅ እናትዋ ከክፍሏ እና ሌላም ቦታ በመፈተሽ ስታገኙ ያየሁት ወረቀት ላይ ፈርሜያለሁ ይህ ግን ምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ያልነበረ እና እዚህ ያልተገኘ ሌላ ወረቀት ነው ሲገኝም አላየሁም በማለት አልፈርምም ብለዋቸዋል፡፡ በመሆኑም ፈታሾች ተጨማሪ የሰው ሃይል ደውለው በማስጠራት ለማግባባት ቢሞክሩም ስላልተሳካላቸው ይዘዋቸው የመጡትን የራሳቸውን ሁለት ምስክሮች ብቻ አስፈርመው ባለቤትዋ ለመፈረም ፍቃደኛ አይደሉም ብለው ቤቱን ለቀው ሄደዋል፡፡ ከፓሊስ ጋር የመጡት ምስክሮች አንደኛው አድራሻቸው በብርበራ ምስክርነት ዶክመንቱ ላይ ያልተጻፈ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል ፡፡
በብርበራው ወቅት በነበራቸው የ7 ሰአት ቆይታ የጦማሪዋን መጸሃፍት የጉዞ ትኬቶች የስልጠና ማንዋል እና የመሳሰሉትን ጥቃቅን ወረቀቶች የወሰዱ ሲሆን ማብሰያ ክፍል ከፍሪጅ ጀርባ አገኘነው ካሉት ወረቀት ግን ቤት ውስጥ ያልነበረና ፓሊሶች ራሳቸው ያመጡት በመሆኑ እናትዋ ተናግረዋል፡፡
የዞን ዘጠኝ ጦማሪ አባላት ከየትኛውም በፓርላማ በአሸባሪነት ከተፈረጀ የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑና ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው እነዲሁም አነዚህ ድርጅቶች ላይ በተለያየ አጋጣሚ ትችቶቻቸውን ሲያቀርቡና ሲቃወሙ የሚታወቁ ቢሆንም ሲሆን በተያዙት አባሎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው አስገድዶ ለሃሰተኛ መረጃ እንዲፈርሙ የማድረግ ተግባር ሳያንስ ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ለማያያዝ ማስረጃን እንደተገኘ አድርጎ የማቅረቡ ተግባር መንግሰት ይታማበት የነበረውን የፓለቲካ ውንጀላን በሽብር የመቀየር ክስ በተግባር እንድናይ ያስቻለን ነው ፡።
በመሆኑም አሁንም ቢሆነ ጦማሪ ጓደኞቻችን ሃሳባቸውን በነጻነት ከመግለጻቸው ውጪ ምንም አይነት የወንጀልም ሆነ ሽብር ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው እያስታወስን መንግስት ያሰራቸውን ጦማርያን እና ጋዜጠኞች አንዲፈታ አሁንም አንጠይቃለን፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/12355/

Thursday, May 15, 2014

ደቡብ ሱዳን – የሰላም ድርድር ወይስ ቁማር?

“ካልፈረማችሁ ለICC አሳልፈን እንሰጣችኋለን” ሃይለማርያም

Ethiopia South Sudan


የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ስምምነቱን የማይፈርሙ ከሆነ ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ለዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (ICC) አሳልፈው እንደሚሰጧቸው መግለጻቸውን በጁባ የጎልጉል ምንጭ አስታወቁ፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ ስምምነቱ የማይፈረም ከሆነ እስር እንደሚጠብቃቸው ሃይለማርያም ለሳልቫ ኪር መናገራቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አርብ የተፈጸመው የስምምነት ፊርማ ገና ሳይደርቅ ሁለቱም ኃይላት ወደ እርስበርስ ውጊያው ተመልሰው በመግባት እየተካሰሱ ነው፡፡
እጅግ ደም አፋሳሽ በሆነውና ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የደቡብ ሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ በፊርማ ሲጸድቅ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ሆኖም ስምምነቱ ከተጽዕኖ ባለፈ መልኩ በዕለቱ በፊርማ ካልጸደቀ ሳልቫ ኪርንም ሆነ ሬክ ማቻርን ሃይለማርያም ደሳለኝ ለዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አሳልፈው እንደሚሰጧቸው የተነገራቸው መሆኑን የጎልጉል ምንጭ ከጁባ አስረድተዋል፡፡ ሳልቫ ኪር ወደ ጁባ ከተመለሱ በኋላ ከካቢኔያቸውና ቅርብ አማካሪዎቻቸው ጋር በተነጋገሩ ወቅት በስምምነቱ ወቅት የነበረውን ሁኔታ ባስረዱበት ወቅት መናገራቸውን የመረጃው አቀባይ ለጎልጉልአስታውቀዋል፡፡ ሁኔታው ለደቡብ ሱዳን እጅግ አሳፋሪ ከመሆኑ የተነሳ ደቡብ ሱዳን አምባሳደሯን ከኢትዮጵያ እስከማስወጣት እንዳሳሰባት ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡
በበርካታ ወንጀሎች የሚጠየቁት ኪርና ማቻር ማስፈራራሪያውን በቀላሉ እንደማይመለከቱት መገመት የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ኢህአዴግ ወንጀል በመሥራትና በማሰራት አገር ውስጥ የለመደውን የማጠልሸት ዘዴ በጎረቤት አገሮችም ላይ በመጠቀም የበላይነቱን መግለጹ ስምምነቱን “የሰላም ድርድር ወይስ ቁማር?” ተብሎ እንዲጠየቅ የሚያስገድድ መሆኑን አንዳንድ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡
ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ ሳልቫ ኪርን ጠቅሶ እንደዘገበው ስምምነቱ በማስፈራራትና በተጽዕኖ የተካሄደ መሆኑን ዘግቧል፡፡ “ጠ/ሚ/ሩ ለሬክ ሲነግረው ስምምነቱን ዛሬ ሳትፈርሙ ከዚህ አትወጡም ብሎት ነበር ለእኔ ደግሞ ሰነዱን ካልፈረምክ አስርሃለሁ” በማለት አስፈራርተዋቸው እንደነበር ሳልቫ ኪር መናገራቸውን ዘግቧል፡፡ ሳልቫ ኪር ከሬክ ማቻር ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ምንም ዓይነት ውይይት ሳያደርጉ ለፊርማ ብቻ መተያየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ssudan1
የሃይለማርያም ደሳለኝ እውነተኛ ባለሥልጣንነትና ተጽዕኖ አድራጊነት የታየበት ይህ ስምምነት በኢህአዴግ ውስጥ በምን ዓይነት መልኩ እንደሚቀጥል የሚያወያይ እንደሆነ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ አስተያየቱን ከሰጡ መካከል እንዳሉት “ሃይለማርያም ይህንን ማስፈራሪያ ሲሰጡ በአጠገባቸው የነበሩት የህወሃት ባለሥልጣናት እነማን ይሆኑ በማለት በዓይነ ልቦናዬ ሳስብ ነበር፡፡ እነ በረከት፣ ደብረጽዮን፣ … ሳልኳቸው” የሚሉት አስተያየት ሰጪ ሲቀጥሉ “ጠ/ሚ/ሩ በነካ እጃቸው የሕዝብን ድምጽ የሚያፍኑትን፣ ኦሮሞውን በየቦታው እየገደሉ ደሙን የሚጠጡትን፣ አማራውን ለዘመናት ከኖረበት እያፈናቀሉ መሄጃ ያሳጡትን፣ አኙዋኮችን ያረዱትን፣ ኦጋዴኖችን ያጋዩትን፣ ተናገራችሁ፣ ጻፋችሁ በማለት እስርቤት እስኪጠብ ሃሳቡ የገለጸውን ሁሉ ለስቃይና ስደት የዳረጉትን፣ … ወንጀለኞች እንዲሁ ግፋችሁን ካላቆማችሁ ቃሊቲ ወይም ዝዋይ ወይም … እወረውርሃለሁ ብለው አንዴ እንኳን በማስፈራራት ጠ/ሚ/ር መሆናቸውን ቢያሳዩን ብዬ ተመኘሁ” ብለዋል፡፡
በተጽዕኖና ማስፈራሪያ የተፈረመው የደቡብ ሱዳን ስምምነት ፊርማ ገና ሳደርቅ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ አቁሙን ጥሰው ፍልሚያቸውን ቀጥለዋል፡፡ እርስበርስም እየተካሰሱ ይገኛሉ፡፡ እሁድ ዕለት የሳልቫ ኪር ኃይሎች በከባድ መሣሪያ የታገዘ የምድር ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው የማቻር ኃይሎች ይናገራሉ፡፡ የኪር መንግሥት በበኩሉ ማቻር ስምምነቱን ላለመፈረም በመፈለግ ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረ ነው በማለት ዶ/ር ሬክ ማቻርን ይከስሳሉ፡፡
ማቆሚያ የሌለው የሚመስለውና እስካሁን በሺዎች የሚቀቆጠር ህይወትን የቀጠፈውና ለ1.2 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት ወደ ሰላም የመድረሱ ምኞት እየራቀ የሄደ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ ማስፈራሪያ፣ ዛቻ፣ ቁማር፣ … ቢጠቀምም ህልሙ ቅዠት ሆኖበታል፡፡
http://www.goolgule.com/south-sudan-peace-deal-signed-under-pressure/