FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, June 5, 2015

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ “ሰላይ” ነው – ዲና ሙፍቲ

“ከአገር የሚሰደዱት ገጠሬ ወጣቶች ናቸው”
spyvsspy
* “አቶ መለስ በጣም ይናፍቁናል”

አሸባሪነት በኢትዮጵያ ሊስፋፋ ያልቻለው ሕዝቡ በሙሉ ሰላይ መሆኑን ዲና ሙፍቲ አስታወቁ፡፡ ከአገር ተሰድደው የሚውጡት አብዛኛዎቹ ገጠሬ ወጣቶች እንደሆኑና ሟቹ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዳሴ አባት በጣም እንደሚናፍቋቸው ተናገሩ፡፡

ቀድሞ በቃል አቀባይነት ሲሰሩ የነበሩት በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኬኒያ ተወካይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ ስታንዳርድ ዲጂታል ከተባለ የኬኒያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ድርጅታቸውን በመወከል  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአልሸባብና መሰል ታጣቂዎች የአሸባሪነት ተግባር በኢትዮጵያ ለማድረስ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድርነው ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ሕዝቡ ሰላይ እንዲሆን የሰለጠነ መሆኑን በመጥቀስ ማንኛውንም ተጠርጣሪ ድርጊት ህዝቡ ሲያይ ሪፖርት እንደሚያደር ተናግረዋል፡፡ ሠራዊቱም እስኪበቃው ድረስ በዚህ ትምህርት አእምሮው የተሞላና የተጠመቀ በመሆኑ ጥቃቱ ሊኖር እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእስልምና ትምህርት ወደ አክራሪነት እንዳይሄድ ኢህአዴግ በየመድረሳው ከሚገኙ የሃይማኖት አስተማሪዎች በየጊዜው የሥራ ራፖር የሚያገኝ መሆኑን እንደተጨማሪ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው እየወጡ በኬኒያ አድርገው ወደ ሊቢያና ሌሎች አገራት ይሰደዳሉ፤ በርካታዎቹ ይሞታሉ፤ በአይሲስ ይታረዳሉ፤ … በማለት ጋዜጠኛው ጥያቄውን ሳይጨርስ አቶ ዲና ፈጠን ብለው እንዲህ አሉ፤ “ወደ ሌሎች አገራት ሲሄዱ የተያዙት አብዛኛዎቹ በሰው አዘዋዋሪዎች እየተባበሉና እየተታለሉ ከአገር የወጡ ናቸው፤ በርካታዎቹ ገጠሬ ወጣቶች ናቸው፤ ከዚህ ሌላ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥ ባለው ዕድል ተደስተው እየኖሩ ነው፤ ኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የምታካሂድ ዴሞክራሲያዊት አገር ናት እንጂ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ያለች አይደለም” ብለዋል፡፡

ወደ ኬኒያ ስለሚኮበልሉት ጋዜጠኞች ጉዳይ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ስድስት ታዋቂ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ ስለመሆናቸው ለተጠየቁት ዲና ሙፍቲ አሁንም ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነጻነት ገና በዕድገት ላይ ያለ መሆኑ ያስረዱት አቶ ዲና በጋዜጠኝነት ሽፋን ህዝብን ከህዝብ ጋር ማጋጨትና ለግጭት ማነሳሳት ኢህአዴግ የማይቀበለው መሆኑን በመግለጽ አሁን በኬኒያ በስደት ያሉት እውነተኛ ጋዜጠኞች እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ በእስር ስላሉት ደግሞ የህጉ ጉዳይ ሳያልቅ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ገልጸዋል፡፡

“መለስ ይናፍቃችኋል?” ተብለው ሲጠየቁ ዲና ሙፍቲ ለሁሉም የኢህአዴግ ሰዎች መለስ በጣም እንደሚናፈቃቸውና የመለስ ራዕይ እስካሁንም እያበበ እንደሆነ አስረድተዋል፤ ሲቀጥሉም “ከአፍሪካ መሪዎች የራሱ መኪናም ሆነ ቤት ሳይኖረው የሞተ ብቸኛ መሪ መለስ ነበር፤ መለስ የመዋቅር ሰው ነበር እንጂ የራሱን ስብዕና ወይም አምልኮተ መለስ (ፐርሰናሊቲ ከልት) የገነባ አለልነበረም” ሲሉ ለቀድሞው አለቃቸው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም በአዲስ አበባ የተዘረጋው የከተማ ባቡር መንገድ ሥራ ከዛሬ ሶስት ወር በፊት የሙከራ አገልግሎቱን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በአዲስ አበባ የትራፊክ መጨናነቅ በሚያስገርም ሁኔታ መቀነሱ ራሳቸውን ምስክር አድርገው አቶ ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ከዚህ የባቡር ዝርጋታ ልምድ ኬኒያ ብዙ ልትማር እንደምትችልና የናይሮቢን ከተማ ከተመሳሳይ ችግር ማላቀቅ እንደማያስቸግር አስረድተዋል፡፡

http://www.goolgule.com/every-ethiopian-citizen-is-a-spy/