FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, June 5, 2015

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ “ሰላይ” ነው – ዲና ሙፍቲ

“ከአገር የሚሰደዱት ገጠሬ ወጣቶች ናቸው”
spyvsspy
* “አቶ መለስ በጣም ይናፍቁናል”

አሸባሪነት በኢትዮጵያ ሊስፋፋ ያልቻለው ሕዝቡ በሙሉ ሰላይ መሆኑን ዲና ሙፍቲ አስታወቁ፡፡ ከአገር ተሰድደው የሚውጡት አብዛኛዎቹ ገጠሬ ወጣቶች እንደሆኑና ሟቹ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዳሴ አባት በጣም እንደሚናፍቋቸው ተናገሩ፡፡

ቀድሞ በቃል አቀባይነት ሲሰሩ የነበሩት በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኬኒያ ተወካይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ ስታንዳርድ ዲጂታል ከተባለ የኬኒያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ድርጅታቸውን በመወከል  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአልሸባብና መሰል ታጣቂዎች የአሸባሪነት ተግባር በኢትዮጵያ ለማድረስ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድርነው ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ሕዝቡ ሰላይ እንዲሆን የሰለጠነ መሆኑን በመጥቀስ ማንኛውንም ተጠርጣሪ ድርጊት ህዝቡ ሲያይ ሪፖርት እንደሚያደር ተናግረዋል፡፡ ሠራዊቱም እስኪበቃው ድረስ በዚህ ትምህርት አእምሮው የተሞላና የተጠመቀ በመሆኑ ጥቃቱ ሊኖር እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእስልምና ትምህርት ወደ አክራሪነት እንዳይሄድ ኢህአዴግ በየመድረሳው ከሚገኙ የሃይማኖት አስተማሪዎች በየጊዜው የሥራ ራፖር የሚያገኝ መሆኑን እንደተጨማሪ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው እየወጡ በኬኒያ አድርገው ወደ ሊቢያና ሌሎች አገራት ይሰደዳሉ፤ በርካታዎቹ ይሞታሉ፤ በአይሲስ ይታረዳሉ፤ … በማለት ጋዜጠኛው ጥያቄውን ሳይጨርስ አቶ ዲና ፈጠን ብለው እንዲህ አሉ፤ “ወደ ሌሎች አገራት ሲሄዱ የተያዙት አብዛኛዎቹ በሰው አዘዋዋሪዎች እየተባበሉና እየተታለሉ ከአገር የወጡ ናቸው፤ በርካታዎቹ ገጠሬ ወጣቶች ናቸው፤ ከዚህ ሌላ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥ ባለው ዕድል ተደስተው እየኖሩ ነው፤ ኢትዮጵያ በየአምስት አመቱ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የምታካሂድ ዴሞክራሲያዊት አገር ናት እንጂ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ያለች አይደለም” ብለዋል፡፡

ወደ ኬኒያ ስለሚኮበልሉት ጋዜጠኞች ጉዳይ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ስድስት ታዋቂ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች በእስር ላይ ስለመሆናቸው ለተጠየቁት ዲና ሙፍቲ አሁንም ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነጻነት ገና በዕድገት ላይ ያለ መሆኑ ያስረዱት አቶ ዲና በጋዜጠኝነት ሽፋን ህዝብን ከህዝብ ጋር ማጋጨትና ለግጭት ማነሳሳት ኢህአዴግ የማይቀበለው መሆኑን በመግለጽ አሁን በኬኒያ በስደት ያሉት እውነተኛ ጋዜጠኞች እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ በእስር ስላሉት ደግሞ የህጉ ጉዳይ ሳያልቅ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ገልጸዋል፡፡

“መለስ ይናፍቃችኋል?” ተብለው ሲጠየቁ ዲና ሙፍቲ ለሁሉም የኢህአዴግ ሰዎች መለስ በጣም እንደሚናፈቃቸውና የመለስ ራዕይ እስካሁንም እያበበ እንደሆነ አስረድተዋል፤ ሲቀጥሉም “ከአፍሪካ መሪዎች የራሱ መኪናም ሆነ ቤት ሳይኖረው የሞተ ብቸኛ መሪ መለስ ነበር፤ መለስ የመዋቅር ሰው ነበር እንጂ የራሱን ስብዕና ወይም አምልኮተ መለስ (ፐርሰናሊቲ ከልት) የገነባ አለልነበረም” ሲሉ ለቀድሞው አለቃቸው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም በአዲስ አበባ የተዘረጋው የከተማ ባቡር መንገድ ሥራ ከዛሬ ሶስት ወር በፊት የሙከራ አገልግሎቱን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በአዲስ አበባ የትራፊክ መጨናነቅ በሚያስገርም ሁኔታ መቀነሱ ራሳቸውን ምስክር አድርገው አቶ ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ከዚህ የባቡር ዝርጋታ ልምድ ኬኒያ ብዙ ልትማር እንደምትችልና የናይሮቢን ከተማ ከተመሳሳይ ችግር ማላቀቅ እንደማያስቸግር አስረድተዋል፡፡

http://www.goolgule.com/every-ethiopian-citizen-is-a-spy/

Thursday, May 14, 2015

በየመን የሚታየው ምስቅልቅል እየሰፋ ስለመጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጥረት ምን ያስተምረናል?

(አክሊሉ ወንድአፈረው)
yemen crisis
በተለያዩ ሀገሮች የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ያለፉባቸውን ጥምዝምዞች፣ የገጠማቸውን ደጋፊና አደናቃፊ ሂደቶች መመርመር በአንድ ሀገር ውስጥ ለሚካሄደው ትግል ታላቅ ጠቀሜታ አለው። በዚህ አንጻር በ2011 የአረብ ስፕሪንግ ከአምባገነናዊ ስርአት ወደ ዴሞክራሲ ልትሸጋገር ነው ተብላ ተስፋ የተጣለባት የመን፣ እነሆ ዛሬ በእርስ በርስ ጦርነት ተናውጣ እንኳንስ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ልትሸጋገር ከራሷም አልፋ አካባቢውን ለማመስ የቻለ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ መመርመር ለሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ትግልም ሆነ በአካባቢው መረጋጋት ላይ ሊኖረው ለሚችለው እንደምታ ታላቅ ትምህርት ይሰጣል።

በዚህ አኳያ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የየመንን ተመክሮ በመመርመር ለኢትዮጵያ ሁኔታ የሚኖረውን ትምህርት አመለክታለሁ። በርግጥ ይህ ጽሁፍ ሰፊ የሆነውን የሁለቱን ሀገሮች ውስብስብ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ ወዘተ እውነታ ሙሉ ለሙሉ በዝርዝር መሽፈን እንደማይችል ግልጽ ቢሆንም፣ ለቀጣይ ገንቢ ውይይት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።

የየመን ምስቅልቅል መሰረቶች

ለ150 አመታት ያክል ለሁለት ተከፍላ የቆየችው የመን በ1990 እንደገና ተዋሀደች ። ምንም እንኳ የተዋሀደችው የመን ህገመንግስት የብዙሀን ፖርቲዎች ስርአትን እንደሚቀበል የደነገገ ቢሆንም፣ የመን ከውህደት ቀኗ ጀምሮ አብደላሂ ሳሊህ ከስልጣን እስከተወገዱበት ጊዜ በእርሳቸው ፕሬዚደንትነት እና በፓርቲያቸው በየመን አጠቃላይ ህዝባዊ ኮንግረስ ፓርቲ (The General People’s Congress) የበላይነት ነው ስትገዛ የኖረችው።

አብዲላህ ሳሊህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደስልጣን የወጡት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በጁላይ 17፣1978 በዚያን ጊዜዋ ሰሜን የመን ሲሆን የመሪነት ምሳሌነታቸውን ሀ ብለው የጀመሩትም ስልጣን ከያዙ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 30 የሰራዊቱ ባለስልጣኖችን እንዲገደሉ ትእዛዝ በመስጠት ነበር። የሟቾቹም ጥፋት “ስልጣኔን ለመጋፋት አሲረዋል” የሚል ነበር። ይህ ሁኔታ ያመላከተውና በቀጣይም የተረጋገጠው የአብዲላሂ ሳሊህ ራእይ ተቃዉሞን ጨፍልቆ ስልጣንን ለብቻ ጠቅልሎ መኖር እንደሆነ ነበር። መልእክቱ ገና ከጠዋቱ ግልጽ ነበር፡፡

ውህዷ የመን በመጀመሪያው ጥቂት አመታት ከየመን ሲሻሊስት ፓርቲ እስከ እስላማዊው ኢስላህ (Islaah) ፓርቲ ድረስ ያሉት ሁሉ የተሳተፉበት የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተሰተናገዱበት ህገመንግስት በሜይ 1991 አጸደቀች፡፡ በ1993 በተካሄደ ምርጫም ሕዝባዊ ኮንግረስ 143 ፣ የየመን ሶሻሊስት ፓርቲ 69 ኢስላህ የተሰኝው የእስልምና ፓርቲ 63 የባአዝ አመለካከት ተከታይ ፓርቲ 6፣ የናስር ርእዮትን የሚከተለው ፓርቲ 2፣ አል ሀቅ 2 እና ከምንም ፓርቲ ያልወገኑ ግለሰቦች 15 ወንበር ይዘው ነበር፡፡
በዚህ ምርጫ ምንም እንኳ መሰረቱ በዋናነት የቀድሞዋ ደቡብ የመን የሆነው ሶሻሊስት ፓርቲው ሁለተኛውን ብዛት ያለውን የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፈ ቢሆንም ባዲሱ የትብብር መንግስት ውስጥ ግን፣ ህዝብ በብዛት ከሌለበት አካባቢን የሚወክል ነው በማለት፣ የሚገባውን ቦታ ሳያገኝ በምትኩ የእስላማዊው ፓርቲ (ኢስላህ) መሪ አብዲላሂ ቢን ሁኔይን ከአሊ አብዲላህ ሳሊህ እና በፓርቲያቸው በየመን አጠቃላይ ህዝባዊ ኮንግረስ ፓርቲ ጋር የጋራ መንግስቱን እንዲመሰርቱ ተደርጎ አብዲላሂ ቢን ሁኔይን የፓርላማው አፈ ጉባኤ ሆነው ተመረጡ። ይህ ጉዳይ የደቡብ የመንን ህዝብ እና የሶሻሊስቱን ፓርቲ ቅሬታ እንዲገባቸው ማድረግ ጀመረ።

በመቀጠልም ሀድረመውት (Hadhramaut) እየተባለ በሚጠራው ደቡብ የመን ክፍል ሰፊ የነዳጅ ዘይት ማምረት ሲጀመር፤ መሬታችንንና ሀብታችንን ያላግባብ በሰሜናውያኑ ተዘረፈ የሚል ከፍተኛ የቅሬታ ስሜት በደቡቡ ነዋሪዎች መሀል ተቀሰቀሰ።
በመቀጠልም በትብብሩ መንግስት ውስጥ የበለጠ ቅሬታና መፍረክረክ የተከተለው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የመናውያን፣ መንግስታችሁ የገልፉን ጦርነት እልደገፈም በማለት ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ድንገት ወደየመን ሲመለሱ ነበር። እነዚህ እጅግ ብዙ ገንዘብ ወደሀገራቸው በመላክ የሀገሪቱን እኮኖሚ ያግዙ የነበሩ ሰዎች ድንገት ከሳውዲ ሲባረሩ ወደሀገሪቱ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ ባንድ ጊዜ ደረቀ። ለተመላሾቹም ቤት፣ ስራ ወዘተ ማመቻቸት ለመንግስቱ እጅግ ከባድ ሆነ።

ይህ ሁኔታ የፈጠረው ጫና በትብብሩ መንግስቱ ውስጥ አለመግባባትና ቅራኔውን አፋፋመው። ቀጥሎም፣ የሀገሪቱ ምከትል ፕሬዚደንት አሊ ሳሊም አል በይደር ስልጣናቸውን ለቀው ወደ ደቡቧ ከተማ ወደ ኤደን ተሰደዱ። የቀድሞው የደቡብ የመን ፕሬዚደንት የውህዷ የመን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሁነው ቢቀጥሉም በአጠቃላይ በተለያዩ ፓርቲዎች ውስጥ በተፈጠረው አለመተማመን እና ንትርክ ምክንያት ፕሬዚደንቱ ስልጣናቸው ዋጋ ቢስ ሆነ።

በዚህ ሁሉ መሀል ጎሳ ነክ የሆኑ አመለካከትን የሚያራምዱ ድርጅቶች በሰሜንም በደቡብም የሀገሪቱ ክፍል ራሳቸውን ማጠናከሩን ቀጠሉበት እያደርም በተለያየ የፖለቲካ ክፍሎች መሀል የሚታየው አለመግባባትና ግጭት እየሰፋ ሄደ። ሁኔታው ተባብሶም በሜይ 21፣ 1994 ደቡብ የመን ተገንጥላ የየመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ብላ ራሷን እንደ ነጻ ሀገርና መንግስት አወጀች።

ይህች አዲስ ሀገር በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅናን ያላገኘች ሲሆን፣ ባብዛኛው በሰሜን የመን ባለስልጣኖችን ያካተተው መንግስትም የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ አካሂዶ በጁን 7፣1994 ኤደንን ተቆጣጠረ። ደቡቡና ሰሜኑ ሲዋሀዱ ቀደም ሲል በሁለቱም በኩል የነበረው ሰራዊት ሙሉ ለሙሉ ስላልተዋሀደ በድርጅቶች መሀል አለመግባባት ሲፈጠር በሁለቱም በኩል ያለው ሰራዊት በገለልተኛነት ቆሞ ሀገራዊ የማረጋጋት ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ፣ ከየክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ወግኖ ግጭቱን እጅግ ወደመረረ ደም መፋሰስ አናረው። ሁለቱም የውህዷ የመን አካሎች (ሰሜኑም ደቡቡም) ቀደም ሲል እንደመንግስት የተደራጀ ሰራዊት ስለነበራቸው የደቡብ አማጽያንና በዋናነት ከሰሜን የመን በመጣው የመንግስት ሰራዊት መሀል የተካሄደው ውጊያው በታንክ እና ባይሮፕላን ጭምር ነበር።
የሰሜኑ ጦር ኤደንን መቆጣጠሩን ተከትሎም በሽዎች የሚቆጠሩ የደቡብ የመን የፖለቲካ ሰዎችና ወታደሮች ሀገር ለቀው ተሰደዱ። የደቡብ የመን ህዝብ እምርሮ በሰሜኑ ነዋሪዎች ተረግጠናል፣ የሚለው ሰሜት እጅግ እየሰፋ ሄደ። ከሰሜኑ የመን ተገንጥሎ ነጻ የደቡብ የመን መንግስትን ለመመስረት የሚደረገው ትግልም ከፖለቲካ ተቃውሞ እስከ ትጥቅ ትግል ደረሰ። ይህ ሁኔታ በዚሁ በደቡብ የመን ውስጥ ተጠናክሮ ለቀጠለው አልቃይዳም አመች ሁኔታን ፈጥሮለታል።

ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ አብድላሄ ሳላህ የስልጣን ተቀናቃኝ የበዛባቸው የያዙትን ስልጣን መደላድል የሚያጠናክር ህገመንግስታዊ ማሻሻያ በተከታታይ በመውሰድ ስልጣናቸውን ለማንም ሳያካፍሉ እርሳቸው ቤተሰቦቻቸው እና ድርጅታቸው በዘላቂነት ለመግዛት የሚያስችላቸው እርምጃወችን ይወስዱ ስለነበረ ነው፡፡ ለምሳሌ በ2000 አመተ ምህረት ልጃቸውን የስልጣናቸው ወራሽ ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ የቅርብ አጋሮቻቸው ሳይቀሩ እንዲርቋቸው አድርጓል። በዚህም ምክንያት የቅርብ አጋሮቻቸው ሳይቀሩ ከ2009 ጀምሮ አብድላሄ ሳላህ ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው በግልጥ ይናገሩ ነበር።

አብደላሂ ሳላህ የውህዷ የመን ፕሬዚደንት ከሆኑ በኋላ በደቡብ የመን የነበረውን የመገንጠል ስሜት ሊያስወግዱ ባለማቻላቸው ብዙዎችን የመሪነት ብቃታቸውን እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል፡፡ እንዲሁም በሰሜን በኩል እያደር የመጣውን የሁቴዎችን እንቅስቃሴ ሊገቱ ባለመቻላቸው የሺዓዎችን መጠናከር እና የኢራንን ጣልቃ ገብነት የሚፈሩ ሁሉ አብድላሄ ሳላህ ላይ ታላቅ ቅሬታ እንዲያድርባቸው ሆኗል።

በመቀጠልም በማርች 18፣ 2011 51 ሰላማዊ ሰልፈኞች በጸጥታ ሀይሎች ከተገደሉ በኋላ እጅግ የቅርብ ወዳጆቻቸው ሳይቀሩ ፕሬዚደንት ሳላህ ከስልጣን መውረድ እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር፡ (Charles Schmitz, Yemen’s National Dialogue ፣ a policy paper serious, PP 8 , Middle east Institute, February 2015.)
ይህ ሁሉ ሲሆንም ቀስ በቀስ ባንድ ወቅት በመካከለኛው ምሰራቅ በዴሞክራሲያዊ ጅምሯ ውዳሴን ያገኝችው የመን፤ ህዝቧ ከማዕከላዊም መንግስት ጋር ሆድና ጀርባ እየሆነ መጣ። በዚህ ውስብስብ የቅራኔ ሂደት ውስጥ የአልቃይዳ ተዛማጅ የሆነው እንቅስቃሴም ስር እየሰደዱ የቅራኔው አደገኛነቱም እየጨመረ ነበር የመጣው።
ለማጠቃለል የየመን የፖለቲካ ምስቅልቅል መስረቶች
  • እያደር እየጠበበ በመጣው የፖለቲካ ምህዳር ምክንያት በስርአቱ ውስጥ ሀሳብን በነጻ ማራመድ አይቻልም የሚለው አመለካከት በተቃዋሚውም በህዝቡም አመለካክት ውስጥ በመስረጹ
  • ስርአቱ በተለያየ ማጭበርበሪያ በመጥቀም ለውጥን ለማገትና ራሱን ዘላለማዊ ገዥ ለማድረግ በመሞክሩ የተለየ ራዕይ ያላችው በህጋዊነት በመታገሉ ላይ ተስፉ መቁረጣቸው
  • ስርአቱ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚነሱ ጥያቈዎች አና ግጭቶች መፍትሄ ሊሰጥ ስላልቻለ በአንድ በኩል ችግሩን ለመፍታት ቅንነት የለውም በሌላ በኩል ችሎታ/ብቃት የለውም የሚለው አስተሳሰብ መስፈኑ
  • የስራ አጥነት መጠን አጅግ ክፍ ብሎ በወጣቱ ላይ ያሳደረው ተስፋ መቁረጥ
  • በጎሳ ላይ ያተኮረ ማህበራዊ ግንኝነትን ትልቅ ቦታ የሚስጥው የህብረተሰብ አደረጃጀት የገዥውን ቡድን አግላይነት በቀላሉ የጎሳ ትርጕም በመስጥት እኛ እና እነሱ ለሚለው አደገኛ አመለካለት ስፊ አድል በመክፈቱ
  • ደቡብ አና ስሜን የመን ሲዋሀዱ ሰራዊቱ በጊዜ ከአንድ አካባቢ ወይም ድርጅት ታማኝነት አንዲወጣና በሀገራዊ ራዕይ አንዲዋሀድ ባለመደረጉ።(ሌሎችም የታጠቁ ሀይሎች እንዲሁ ወደሀገራዊ ሰራዊትነት እንዲቀላቀሉ ሳይደረግ የፖለቲካ ድርጅቶች መሀል ግጭት ሲከሰትም ከሀገሪቱ ይልቅ ለየጎሳው ወግኖ እንዲነሳ ተመቻችቶ መገኘቱ)
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ አብደላሂ ሳሊህ እና ድርጅታቸው በተለያየ ደረጃ መቻቻልን እንዲያሰፍኑ፤ ስልጣንን እንዲያጋሩ፣ ንቅዘትን እንዲያሰወግዱ መብት እንዲያከብሩ፣ እርቅ አንዲያወርዱ ቢለመኑም ነገሩን ሁሉ በማሳነስ በውጭ ድጋፍ ላይ እጅግ በመመካት በትምክህት የተፈጠረውን እድል ሁሉ ሊጠቀሙበት አለመቻሉ
ጥቂቶቹ ነበሩ።
የጸደይ አብዩት በየመን (አረብ ሰፕሪንግ)ና የዲሞክራሲ ሀይሎች ንቅናቄ
የአብድላሂ ሳሊህ እና ፓርቲያቸው ህዝባዊ ኮንግረስ ፓርቲ (The General People’s Congress) በሚያካሂደው ያላቋረጠ የመብት ረገጣ የተነሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከህዝብ እየተነጠሉ፣ አዳዲስ ተቃዋሚወችንም በሰፊው እያፈራ በውስጡም እየተፍረከረከ ነው የተጓዘው፡፡ ባንድ ወቅት ተከፋፍላ ለነበረችው ሰሜንና ደቡብ የመን መዋሀድ ባለውለታ በመሆኑ የተወሰነም ቢሆን አክብሮት የነበራቸው አሊ አብዲላህ ሳሊህ እና ፓርቲያቸው አጠቃላይ ህዝባዊ ኮንግረስ ፓርቲ (The General People’s Congress) ቀስ በቀስ በሕዝብ አክ እንትፍ ተባሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 ሰሜን አፍሪካንና መካከለኘው ምስራቅን ያናወጠው ሕዝባዊ አመጽ ወደ የመን የደረሰው ብዙም ሳይዘገይ ነበር። እንደ ቱኒዝያና ግብጽ፣ በየመንም ህዝብ በየከተማው በነቂስ በመውጣት አሊ አብዲላህ ሳሊህና ፓርቲያቸው የያዙትን መንግስት ከስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ።

የአጠቃላይ የህዝባዊ እንቅስቃሴ ሞተር በመሆን ይህን ሕዝባዊ አመጽ የመሩት ወጣቶች ስርአቱን አስወግዶ በምትኩ መቻቻል የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲያዊት የመንን እውን ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡ የየመን ወጣቶች እንቅስቃሴ “civil state,” በማለት የሰየሙት ስርአት እንዲመሰረት ነበር ትኩረት አድርገው የሚጠይቁት። ይህ ሲቪክ መንግስት (civil state) በወጣቶቹ አገላለጥ በህግ የሚገዛ፣ ባስተዳደር ችሎታ ቴክኒካዊ ብቃት ያላቸውን ያቀፈ እና ከሙስና የጸዳ ስርአት ነው። ባጭሩ፣ የለውጥ ፈላጊወቹ ወጣቶቹ ፍላጎት ገዥውን ቡድን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በምትኩ የዴሞክራቲክ ስርአትን መመስረትም ነበር

ትግሉ እየጠነከረ የተቃዋሚው ጎራም እየሰፋ ቢመጣም አሊ አብዲላህ ሳሊህ እና ፓርቲያቸው ግን ቀደም ባሉት አመታት እንዳደረጉት ሁሉ ይህንንም ተቃውሞ ጨፍልቆ ማለፍ ይቻላል በሚል ግምት ስልጣንን የሙጥኝ ብለው ተቀመጡ።
ይህም በመሆኑ በአሊ አብዲላህ ሳሊህ እና ፓርቲያቸው ላይ ተጽእኖ ለማድረግ እና ትግሉን ለማፋፋም፤ ከተለያየ ህብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት በኦገስት 2011 ተመሰረተ። ይህ ብሄራዊ የምክክር ካውንስል (the National Council) ተብሎ የተሰየመው አካል 143 አባላት ያሉት ነበር። ይህ ትብብር የተለያየ የፖለቲካ አቋም እና ፍላጎት የነበራቸውን ድርጅቶች ወደአንድ መግባቢያ እንዲደርሱ በማድረግ በተፍረከረከችው ሀገራቸው ህዝብ ላይ እንደገና የተስፋ ብርሀን ብልጭ እንዲል አደረገ።
በፎቶው ላይ የሚታዩት ከመሀል መሀመድ ባሲንደዋህ (Mohammed Basindwah) አዲስ የተመሰረተው የተቃዋሚወች ትብብር ፕሬዚደንት፡ በግራ በኩል አብደል ዋሂብ አል አነሲ (Abdul Wahab Al-Anesi) የ እስላማዊው ኢስላህ ፓርቲ (Islah Party) ዋና ጸሀፊ በቀኝ በኩል ደግሞ የየመን ሶሻሊስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ያሲን ሰኢድ ኑማን (Yasin Said Numan) ናቸው።
በፎቶው ላይ የሚታዩት ከመሀል መሀመድ ባሲንደዋህ (Mohammed Basindwah) አዲስ የተመሰረተው የተቃዋሚወች ትብብር ፕሬዚደንት፡ በግራ በኩል አብደል ዋሂብ አል አነሲ (Abdul Wahab Al-Anesi) የ እስላማዊው ኢስላህ ፓርቲ (Islah Party) ዋና ጸሀፊ በቀኝ በኩል ደግሞ የየመን ሶሻሊስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ያሲን ሰኢድ ኑማን (Yasin Said Numan) ናቸው።

ተቃዋሚው ራሱን አሰባስቦ ተከታታይ ሰላማዊ ግፊትን በማድረግ አሊ አብዲላህ ሳሊህ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ጥሪውን ቀጠለ። ከፖለቲካ ድርጅቶች እና የወጣቱ መሪዎች በተጨማሪም ብዙ ታዋቂ ግለሰቦችም በህዝባዊው እንቅስቃሴው አሊ አብዲላህ ሳሊህን ከስልጣን በማስወገድ በምትካቸውም ሁሉን አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመመሰረት ለሚደረገው ትግል ድጋፋቸውን ሰጥተው ነበር። ከነዚህም ውስጥ ከዚህ በታች ምስላቸው የሚታየው በ2012 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ተዋኩል ካርማን (Tawakul Karman) አንዷ ናቸው።

የየመን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል እጅግ በሚያሰገርም መረጋጋት ትግሉን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ቢያካሂድም ፣ ጽንፈኛ የሆነው የአልቃይዳ እና ከእሱም ጋር የተባበሩ ታጣቂዎች በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ አየተቀላቀሉ አልፎ አልፎ ንቅናቄውን የመሳሪያ ሀይል የተጨመረበት ሲያደርጉት ታይቷል።
የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ተዋኩል ካርማን
የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ተዋኩል ካርማን
በወቅቱ አሜሪካኖች “ተቃዋሚውን ከሳላህ መንግስት ጋር በመሆን በኃይል ያጠቃሉ” እየተባለ ይነገር ለነበረው ተቃውሞ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካን ባለስልጣን ሁኔታውን እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል “የአልቃይዳ ስርጎገቦች ከሌሎች ጸረ መንግስት ሀይሎች ጋር ተቀላቀቅለው ስለሚንቀሳቀሱ አሜሪካን በየመን የሚገኙ ያልቃይዳ አማጽያን ላይ የሚወሰደው የሀይል እርምጃ ለመንግስቱ የወገነች ሳትመስል መንቀሳቀስ እጅግ ከባድ ነው።”

የሳላህ መንግስትና የሀያላኑ ግንኙነት

የመን ከምእራቡ ሀገር በተለይም ከአሜሪካን እና ከሳውዲ አረብያ ጋር የቅርብ ግንኑነት ያላት ሀገር ናት። ያሜሪካን ዋና ትኩረት በየመን ውስጥ መሽጎ የሚገኘውን የአልቃይዳ ድርጅት መደምሰስ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሳውዲ አረብያ (እንዲሁም የሌሎቹ የገልፍ ሀገሮች) ዋና ፍላጎት ደግሞ በየመን ሺዓ ሙስሊሞች በኩል ሊደርስብኝ ይችላል ብላ የምትሰጋበትን የኢራን መንግስት ግፊት መቋቋም ነው። የኢራን የኃይማኖት መሪዎች ለሳውዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ ፍቅር እንደሌላቸው ብቻ ሳይሆን ስራቸው ሁሉ ከእስልምና ህግጋት ጋር የተጻረረ ስለሆነ መወገድ አለባቸው ብለው በይፋ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ኢራኖች በተለይም የሺዓ እምነት ተከታይ የሆኑትን የሁቱ ነገድ ሙስሊሞችን ተከታታይ የመነሳሳት እንቅስቃሴ ስለሚደግፉ ይህ እንቅስቃሴ እንዳያድግ እና እናዳይጠናከር ሳውዲዎችም ሆኑ ሌሎች የገልፍ መንግስታት አጥብቀው ይጥራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በየመን ውስጥ እነሱ የሚቆጣጠሩት ወይም ለነሱ ታማኝ ያልሆነ መንግስት እንዳይመሰረት እጅግ ይሰጋሉ። የመን ከሳውዲ ጋር ባላት የድንበር አዋሳኝነት የተነሳ በየመን ውስጥ የሚደረግ ነገር ሁሉ ሳውዲን ይነካል ብለው ስለሚሰጉ፣ የሳውዲ ባለስልጣኖች የመንን ባይነቁራኛ መመልከት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ አካሄዷን ለመቆጣጠር ሁልጊዜም ይጥራሉ።

የሳላህ መንግስት ለአሜሪካንም ይሁን ለሳውዲ የነበረው ታማኝነት 100% በላይ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህም በመሆኑ ህዝበዊ ትግሉ እጅግ በተፋፋመበት እና በለውጥ ፈላጊው የዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ላይ ስርአቱ ታላቅ ጭፍጨፋ ያካሂድ በነበረበት በ2011 መጨረሻ ሳይቀር አሜሪካ ለሳላህ መንግስት የ120 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ባብዛኛው ወታደራዊ ሰጥቶ ነበር።
በማርች 2012 ዘ ኔሽን በተሰኝው ጋዜጣ ላይ የቀረበ አንድ ሪፖርት እንዳለውም በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1980ቹ ከተጀመረው ሶቭየት ህብርትና ከአፍጋኒስታን የማስወጣት ጦርነት ጀምሮ ከዚያም የ9/11 ን ሽብር ተከትሎ የሳላህ መንግስት አልቃይዳንና ጸረ ሽብርተኛነትን እንደማሰፈራሪያ በመጠቀም ካሜሪካኖች እና ከሳውዲ አረብያ ስልጣኑን ለማጠናከር እና ተቃዋሚወቹንም ለማዳከም የሚያስችለው ከፍተኛ ድጋፍን አካብተውበታል

በውጭ ግንኙነት ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰ አንድ ድርጅት (ካዉንስል ፎር ፎሬን ሪሌሽን) በቅርቡ እንደዘገበው አሜሪካ ለፕሬዚዳንት አሊ ሳሊህ መንግስት ያደረገችው እርዳታ ከአመት ወደ አመት እጅግ ፈጣን በሆነ መልክ ሲያድግ ነበር የቆየው።

የምእራቡ አለም እና ያካባቢው መንግስታት ነጠላ ጥቅም ላይ ያተኮረ አካሄድ በዴሞካራሲ እንቅስቃሴው ላይ ያሳደረው እንደምታ

የየመን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እያደገ ቢመጣም አሜሪካኖች ከሳላህ በኋላስ ምን ይሆናል ለሚለው በቂ ዝግጅት አላደረጉም ነበር። ሳውዲዎችና የገልፍ መንግስታትም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። ከሳላህ በኋላ የሚመጣው መንግስት ከቁጥጥራቸው ውጭ ቢሆንስ የሚለው እጅግ አሰጨቋቸው ነበር።

በተቃዋሚው እና በምእራቡ መንግስታት መካከል የተወሰነ ግንኙነት ቢደረግም፣ የአብዳላሂ ሳላህ ቢወገዱ ባልቃይዳ ላይ ለሚያካሂዱት ጥቃት ተቃዋሚው ሙሉ በሙሉ ድጋፍ ይስጥ ይሆናል ወይ ለሚለው ጥያቂ ባሜሪካኖች በኩል በተወሰነ ደረጃ እርግጠኞች አልነበሩም። ተቃዋሚው የብዙሀን ፓርቲ ስርአትን፣ የምእራቡን የሚመስል ዴሞክራሲ፣ አሰፍናለሁ ቢልም ላሜሪካኞች ይህ ቅድሚያ የሚሰጡት አልሆነም፡፡ ስለዚህ ሙሉ በሙሉ የስርአት ለውጥን ከመደገፍ ይልቅ ሳላህን አስወግዶ ስርአቱን ግን ማስቀጠሉን ስራዬ ብለው ተያያዙት።

የሳውዲ አረብያና ሌሎችም የጎልፍ መንግስታትም በተመሳሳይ መንገድ ያቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አብደላሂ ሳላህን አስወግዶ በቦታው ምክትል ፕሬዚደንቱን አብዱ ረቡ ማንሱር ሃዲ (Abdu Rabbu Mansour HadI) ወደ ስልጣን ማምጣት ነበር።
በዚህም መሰረት ያሜሪካውኑ ፕሬዚደንት የተከበሩት ባራክ ኦባማ የጸረ ሽብር አማካሪና በኋላም የሲአይኤ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጆን ብረናን (John Brennan), ፕሬዚደንት ሳላህን በሳውዲ አረብያ ከሚገኙበት ሆስፒታል ከጎበኙዋቸው በኋላ ስልጣናቸውን እንዲለቁና ለምክትል ፕሬዝደንቱ እንዲያስተላልፉ ነገሯቸው፡፡

የተቃዋሚዎች ህብረትም ሆነ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ይህንን የሳውዲና ያሜሪካ እቅድ ፈጽሞ አልተቀበሉትም የህዝቡን እንቅስቃሴ ለማምከን የሚደረግ ሴራ ሲሉ ነበር ያወገዙት።
ተቃዋሚው በስርአቱ ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት አበክሮ ቢያሳሰብም የገልፍ መንግስታትም ሆኑ አሜሪካ አልደገፉትም። የሽግግር እቅድ ተብሎ ባሜሪካና በገልፍ መንግስታት (ሳውዲ፣ ኳታር፣ ባህሬን) የቀረበውም ሁሉን አቀፍ መንግስት መመስተረትንም ሆነ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወዲያውኑ ማካሄድን ያካተተ አልነበረም። የተፈለገው የሳሊህን ምክትል ወደ ፕሬዚደንትንት አምጥቶ መቀጠል ነበር።

ይህ ከህዝቡና ከአክቲቭስቶች ፍላጎት ጋር የተቃረነና ዴሞክራሲያዊ አካሄድን የሳተ ቢሆንም በወቅቱ ያሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሰራቅ ሀላፊ የነበሩት ሚስተር ጀፍሪ ፌልትማን (Jeffrey Feltman, the Assistant Secretary of State for Near Eastern Affairs) ይህንኑ እቅድ እንደሚደግፉ አስታወቁ።
ያሜሪካን መንግስት የወሰደውን አቋም እንዲያስተካክል የኖቤል ሽልማት አሽናፊዋ የመናዊት ተዋኩል ካርማን (Tawakul Karman) እንዲህ ሲሉ ተማጸኑ “ዩናትድ ስቴትስ አሜሪካንን በሽብርትኛነት ላይ ያላትን ጭንቅ እንገነዘባለን። ያሜሪካን ደህንነት ለመጠበቅ ከየመን ጋር አሜሪካ ያላትን ስምምነት ማክበርን በተመለከተ ምንም ችግር የለንም። እኛ የምንጠይቀው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መለኪያወችን እንድትከተሉና የየመንንም ህዝብ ለነጻነት፣ ለስብአዊ መብቱና፣ ለፍትህ መስፈን ያለውን ፍላጉቱን እንድታከብሩለት ብቻ ነው። በሸዎች በሚቆጠሩ የየመን ወጣቶች ስም ከእናንተ ጋር በሙሉ ሽሪክነት አብረናችሁ ለመቆም ዝግጁነታችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ከእናንተ ጋር በጋራ፣ ሆነን ጽንፈኛነት እንዳይቀፈቀፍ አመች ሁኔታ የሚፈጥረውን መደላድሎች፣ ልማትን ተጋባራዊ በማድረግ እና ነጻ የሲቪክ ማህበራትን በመመስረት እናስወግዳለን፣፡ መረጋጋትንም እውን እናደረጋለን። ለዚህም ለውጥ ፈላጊወችን እንድትደግፉና ከሽብርተኞች ይልቅ ንጹሀን የመናውያንን የሚገድለውን ስርአት መደገፍ እንድታቆሙ እማጸናለሁ”፡፡

ያም ሆኖ ግን ሰሚ አላገኙም። በወቅቱ የለውጥ ፈላጊዎቹ ወጣቶች መሪ ከነበሩት ውስጥ አንዱ ኻሊድ አለ አኒስ (Khaled al-Anesi) ትግላችን እና አብዮቱ ከጀርባ ነው በጩቤ የተወጋው ነበር ያለው “This revolution has been stabbed in the back.”
ባሜሪካን ነዋሪ የሆኑ ትውልደ የመኖችም ተመሳሳይ የለውጥ ፍላጎታቸውን ለአሜሪካ ባለስልጣናት አሰምተው ነበር።
አብዱላሂ ሳላሀ አርፈውበት በነበረው በኒውዮርክ ሪትዝ ካርልተን (Ritz-Carlton ) ሆቴል ፌት ለፌት የተቃውሞ ስልፍ ካካሄዱት ውስጥ ጥቂቶቹ (ፎቶ ከኒው ዮርክ ታይምስ 2012)
አብዱላሂ ሳላሀ አርፈውበት በነበረው በኒውዮርክ ሪትዝ ካርልተን (Ritz-Carlton ) ሆቴል ፌት ለፌት የተቃውሞ ስልፍ ካካሄዱት ውስጥ ጥቂቶቹ (ፎቶ ከኒው ዮርክ ታይምስ 2012)
ይህ ሁሉ የህዝብ ተቃውሞ እያለ በተጻራሪው መንገድ እንዲጓዝ በመደረጉ ህዝባዊ ንቅናቄው በተጀመረው መልክ ቢቀጥል የሚፈለገው ነጻነት፣ የመብት መከበር፣ ዴሞክራሲ ወዘተ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል የሚለው አመለካከት በጥርጣሬ መታየት ጀመረ። ሌሎች አማራጮችንም የመመርመር ጉዳይ ትልቅ ቦታ ያዘ።

አቡበከር አልሸማሂ የተባለ አንድ በትውልደ የመናዊ የሆነ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ የምእራቡ አለም የስርአት ለውጥ እና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴውን በመደገፍ በዋናነት የሚፈሩትን አላቃይዳን ለማዳከም እንደሚቻል ይህ ሳይሀን ቢቀር ግን ቀጣዩ ሁኔታ ለየመንም ላካባቢውም መልካም ነገርን እንደማያመጣ ልብ ያለው ልብ ይበል ሲል የማስጠንቀቂያ ደወል አስምቶ ነበር
የዚህ ወጣት ጥሪ፣ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዋ፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ህብረትም ሆነ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ድምጽ ግን አድማጭ አላገኘም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው አልቃይዳና ሌሎችም ኃይሎች “ብለናችሁ ነበር፣ የምንፈልገውን ለማገኝት የራሳችንን ጉዞ መጀመር ነው የሚያዋጣን” በማለት ወጣቱን ከሰላማዊ የትግል ጎዳናው ወጥቶ ለሚፈልጉት ግብ እንዲሰለፍ ሰፊ የመመልመያ መሳሪያ ያገኙት።

የየመን ህዝባዊ ትግል መደናቀፍና ለየት ያለ ተቃውሞው መበራከት

የዴሞክራቲክ ሂደቱ መደናቀፍ የሳላሀ መንግስት ደጋፊወች፣ ምእራባውያንና የገልፍ መንግስታት እንደተመኝት ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ መንኮታኮት ለፕሬዚደንቱ ስደት፣ በየመን ውስጥ ላክራሪዎችና ለቀጣይ ምስቅልቅል የተመቻቸ ሁኔታን ነው የፈጠረው።
በቅርቡ የቀረበ ጥናት እንዳሳየውም፣ ሀገሪቱ ምስቅልቅል ውስጥ መግባት አልቃይዳን ተጠቃሚ አድርጎታል።
ባሜሪካን ጸረሽብር ሀይሎች እና በሰው አልባ አይሮፕላን ጥቃት በተከታታይ በደረሰበት ጥቃት እጅግ ተዳክሞ የነበረው አልቃይዳ በ ኤፕሪል 2015 ሙላካ (Mukallah) በተሰኘችው ከተማ የሚገኝ እስር ቤት ሰብሮ በመግባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹን አስለቅቋል። በመቀጠልም በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ኬላዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
የሀሽድ (Hashid) ጎሳ ተዋጊወች በሰንአ (Sanaa) ከተማ ውስጥ ጎዳናወችን ሲቆጣጠሩ (ፎቶ በ ካሊድ አብደላሂ፣ ሮይተር፣ ዲሰምበር 2011)
የሀሽድ (Hashid) ጎሳ ተዋጊወች በሰንአ (Sanaa) ከተማ ውስጥ ጎዳናወችን ሲቆጣጠሩ (ፎቶ በ ካሊድ አብደላሂ፣ ሮይተር፣ ዲሰምበር 2011)
በኤፕሪል 17፣ 2015 እንደተዘገበውም፣ በሀገሪቱ ምስራቃዊ ግዛት የሚገኝ የመንግስት ኃይል አሸንፎ፣ እጅግ ሰፊ የሆነ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ተቆጣጥሯል።

መሰረቱን ጎሳ ያደረገው የየመን ፖለቲካ አሁንም ተጠናክሮ ሀገሪቱን ወደተወሳሰበ አሳዛኝ ክፍፍል ይዟት በመጓዝ ላይ ይገኛል።አሊ ሳላህን፣ የተኳቸው ፕሬዚደንት ሃዲና ፓርቲያቸው ከስልጣን ተባረው እነሆ ዛሬ የስደት ፕሬዚደንት ሆነዋል።
አፍቃሪ ኢራን የሆኑት የሁቴ አማጽያን ሰንአ (Sanaa) ከተማን ከተቆጣጠሩ በሐላ በሳውዲ አረቢያ የሚመራውና ባሜሪካ የሚደረፈው የአየር ጥቃት  እንደማይበግራቸው በሰልፍ ሲገልጽ ( ፎቶ በሀና ሞመመድ፣ ዐሶሽየትድ ፐረስ 2015)
አፍቃሪ ኢራን የሆኑት የሁቴ አማጽያን ሰንአ (Sanaa) ከተማን ከተቆጣጠሩ በሐላ በሳውዲ አረቢያ የሚመራውና ባሜሪካ የሚደረፈው የአየር ጥቃት እንደማይበግራቸው በሰልፍ ሲገልጽ (ፎቶ በሀና ሞመመድ፣ ዐሶሽየትድ ፐረስ 2015)
ባጠቃላይ የፕሬዚደንት አሊ ሳላህ መንግስት የዲሞክራሲ እንቅስቃሴውን ለማጨናገፍ ቀና ደፋ ሲል እና ባለው ኃይል ሁሉ ሲሯሯጥ አልቃይዳ፣ የሁቲ አካራሪዎችና ሌሎችም ጎሳ ነክ ኃይሎች እጅግ ተጠናከሩ። የፕሬዚደንቱ የስልጣን ጥም፣ ግትርነትና እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ብሎ ድርቅ ማለት መጨረሻው የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች መዳከም፣ የስርአቱ ሀገሪቱን ሊገዛ አለመቻል፣ የሀገሪቱ አንድነት መናጋት፤ የአልቃይዳ መጠናከር፣ የተገንጣዮች እንቅስቃሴ መጠናከር፣ ሀገሪቱ የሰፊ ጦርነት አውድማ መሆን እና ከራሷም አልፋ ላካባቢው ሁሉ አደጋን መጋረጧ ጥቂቶቹ ናቸው።

እኛስ?

የየመን ሁኔታ የህዝብን መብት ረግጦ፣ ሌሎችን አግልሎ፣ ተለጣፊ ድርጅቶችን ሰብስቦ መግዛት ይዋል ይደር አንጂ በዘላቂነት ሊቀጥል እንደማይችል በርግጠኛነት ያሳያል። የውጭ መንግስታት ድጋፍ፤ ጊዚያዊ ጥንካሬን አንጂ ዘለቄታ ያለው በህዝብ ዘንድ ከበሬታን እና ፍቅርን ሊያሰገኝ እንደማይችልም ያመለክታል፡ በጎሳ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መዘዙ እጅግ ሰፊ እንደሆነም ያሳያል።
በሀገራችን ፖለቲካ መድረኩን ለብቻ ሙጭጭ ብሎ መያዙ፤ የመብት ረገጣው፣ ህዝብን ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ እየተሟጠጠ መምጣቱን ከገዥው ወያኔ/ኢህአዴግ በስተቀር የሚክድ የለም። በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው ውጥረትም የተለያየ መልክ እየያዘ፣ እጅግ እየተካረረ እንጂ እየረገበ መፍትሄም እያገኘ አይደለም የመጣው።

በገዥው ቡድን በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱትን ፖለቲካ ድረጅቶችንም ሆነ የሲቪክ ድርጅቶች ሰበብ እየፈለገ በፍጹም እነዳይንቀሳቀሱ እያደረገ ስለመጣ፤ በዚች ሀገር ውስጥ በዚህ ስርአት ውስጥ መብትን በህግ ስር ሆኖ ለማስከበር መሞከር ከንቱ ሙከራ ነው የሚለው ስሜት እጅግ ፈጣን በሆነ መልክ እየተስፋፋ ይገኛል።

የምእራብ መንግስታትን በተመለከተም በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ታላቅ ድጋፍ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ግንዛቤ ቢኖርም፣ በተግባር እንደታየው ግን ዴሞክራሲን፣ እኩልነትን፣ ፍትህን ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ለእነርሱ በዋነኛነት ቅድሚያ የሚሰጡት እንዳልሆነ ነው።

ሀገራችን ሁሉን አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ከሚፈልጉ ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መቀጠል የለባትም እስከሚሉ ድርጅቶች የተለያየ አይነት ትግል በውስጥም በውጭም የሚያካሂዱባት ሀገር ነች። የጎሳ መርዝ እጅግ ስር ሰዷል፡ በሰራዊቱም በፖሊሱም ውስጥ የጎሳ ቅኝት ሰፊ ነው። ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ እንደሻቢያ ያሉ እና ሌሎችም ጠላቶች ኢትዮጵያን ከበዋት ይገኛሉ። በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልቃይዳ፣ አሁን ደግሞ ኢሰላሚክ ስቴት በአይነ ቁራኛ ከሚያዩዋቸው ሀገሮች አንዷ ለመሆኗ በየጊዜው በአልሸባብ የተነገረውን እና በኤፕሪል ወር ደግሞ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን አንገት መቅላት እና በጥይት ደብድቦ መግደል ማገናዘቡ ይበቃል።
የየመን ምስቅልቅል ሰለባ፤ በደም የተነከረ የወገኑን ልብስ ሲያሳይ (ፎቶ በ ቢቢሲ አፕሪል 2015)
የየመን ምስቅልቅል ሰለባ፤ በደም የተነከረ የወገኑን ልብስ ሲያሳይ (ፎቶ በ ቢቢሲ አፕሪል 2015)

ይህ ሁሉ የሀገራችንን አደጋ እጅግ ሰፊና ውስብስብ እንደሆነ ያሳያል። በሀገሪቱ የሚታየው ውጥረት ገንፍሎ እንደሚፈነዳ በርግጠኛነት መናገር ይቻላል፤ ጥያቄው መቼ እና በምን መልክ የሚለው ብቻ ይሆናል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉትን አደጋዎች ለማስወገድ ካልተቻለም ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት የሚለው እጅግ አስቸኳይ መፍትሄን የሚሻ ሁሉንም ሊያስጨንቅ ሊያስጠብብ የሚገባ ጉዳይ ነው።

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎቿ ሀገር ነች። ለኢትዮጵያ አንድነት አንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ ዜጎች ያሰባሉ፡ ለብሄር ብሄረሰቦችም እኩልነት እንዲሁ። በዚህ አኳያ የሁሉም አመለካከከት በክብር ሊስተናደግ የሚችልበት በጠንካራ እሴቶቻችን ላይ በማተኮር በኢትዮጵያዊነት በጋራ የመኩራት ሂደት ተጠናክሮ የሚወጣበትን መደላድል መፍጠር ግድ ይላል።
የተለያዩ ቅሬታዎችና አዳዲስ አመለካከቶች በሰላማዊ መንገድ በሙሉ ቅንነት ሊስተናገዱ የሚችሉበት መድረክ ሊፈጠር ይገባል። ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ ሁሉም ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው በባሌም በቦሌም እንዲሰደዱ የሚያደርጓቸው የፍትህ መጥፋት፣ የህግ የበላይነት መጥፋት፣ የተስፋ ማጣት ወዘተ ሁኔታዎች ሊስተካከሉ የሚችሉበት ስርአት እውን መሆን አለበት። ለዚህም ችግሩን በጋራ በቅንነት ለመፍታት በቁርጠኛነት መነሳት ያሰፈልጋል።

የፖለቲካ ድርጅቶች የማምንበትን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ ከውጭ ጠላትም ጋር ቢሆን እሰለፋለሁ የሚያሰኛቸው የፖለቲካ ድባብ እንዲወገድ የሚያስችል መተማመን፣ መፈጠር ይኖርበታል። በስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲካ መሪዎች መጨረሻቸው፣ እስርቤት፣ ስደት ወይም ክብር የሌለው ሞት የሆነበትን ስርአት እንዲያከትም ማድረግ የግድ ነው። በምትኩም በፖለቲካ ራእይ ልዩነት የተነሳ እንደጠላት መተያየት የሚወገድበትን መሰረት መጣል፣ ያመጽ አዙሪትን መሰረት ማፍረስ ያሰፈልጋል። ለዚህም አሳታፊ፣ እውነተኛ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ስርአት መስረት መጣል የግድ ይላል።

ባለንብረቶች አንዱ ፖለቲካ ፓርቲ ከስልጣን ሲወርድ ንብረታቸው የሚነጠቅበት፣ የጦር መኮንኖች እና ሌሎች ባለስልጣኖች የውርደት ኑሮ እንዲኖሩ የሚገደዱበት ስርአት ማብቃት አለበት።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ መመካከር የግድ ነው፡፡ የተቃዋሚው ባስቸኳይ ማበር አስፈላጊ ነው። የብሄራዊ መግባባትና እርቅ መሰረትን መጣል የግድ ነው። የዚህ ጉዳይ ተግባራዊ መሆን የረፈደ ቢመስልም እጅግ ሳይዘገይ አሁኑኑ ሊሆን ይገባዋል።
የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ መንግስታትም ሆኑ በዚች ሀገር ደህንነት ተጠቃሚ ነን የሚሉ ሁሉ ለዚህ ተግባር መደናቀፍ ሳይሆን መሳካት ነው ድጋፍ ሊሰጡ የሚገባው። የነርሱም ጥቅም በዘላቂነት የሚጠበቀው በተረጋጋ፣ ህግ በሰፈነበት፣ መብት በተረጋገጠበት መቻቻልና ነጻነት በሰፈነበት ስርአት ውስጥ ብቻ እንደሆነ የመን ምስክር ነች።

ቀደም ብየ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የጠቀስኩት አቡበከር አልሸማሂ የተባለው የየመን ትውልድ ያለው እንግሊዛዊ ወጣት በ 2011 ሀገሩን በተመለከተ ካሰማውን የአደጋ ደውል እና ካቀረበው ጥሪ ጋር የሚመሳሰል መልእክት እኔም ለማሰማት እፈልጋለሁ።
የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አሳሰቢያ እጅግ ፈታኛና አጣዳፊ መፍትሄን የሚሻ ነው። በሀገሪቱ ላይ ጥቁር ደመና አንዣቧል። ጭንቀት ሰፍኗል። ውጥረት በዝቷል። ተስፋ ማጣት ተስፋፍቷል። አሁንም ቢሆን ይህን ጭንቅ ለማስወገድ አደጋውን ለማስወገድ የተወሰነ እድል አለ፡፡ ይህ ደግሞ ደፈር ያለ አዲስ እርምጃን ይጠይቃል። ይህን እውነታ በመካድ ወይም በማድበስበስ ለማለፍ መሞከር ለኢትዮጵያም ለአካባቢውም መልካም ነገርን እንደማያመጣ ልብ ያለው ልብ ይበል።

ሜይ 5፣ 2015
ላስተያየት ethioandenet@bell.net

http://www.goolgule.com/lessons-from-yemen-to-mitigate-conflict-in-ethiopia/

Wednesday, April 8, 2015

በስዊድን የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ራሱን አስተዋወቀ

semayawi sweden
የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር በስዊድን ተመስርቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለጽ፤ የድጋፍ ማኅበሩ ቅዳሜ አፕሪል 4 ቀን 2015 ዓ.ም. (ግንቦት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.) ራሱን አስተዋውቋል። በዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ተግባርን ጥሪ ለተደረገላቸው ተሰብሳቢዎች ያስረዱት አቶ ሰለሞን ጌታነህ የድጋፍ ማኅበሩ ሰብሳቢ ናቸው።
አቶ ሰለሞን በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በተደረገው የማስተዋወቁ ሥነሥርዓት ላይ ስለሰማያዊ ፓርቲ ሲያስረዱ፤ ሰማያዊ ፓርቲ በወጣት አባላት የተመሰረተና የሚመራ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ብልጫ ያለው እንደሆነና የወጣቱም ድጋፍ ሰማያዊ ፓርቲን እንዳልተለየው አሳውቀዋል። አያይዘውም ሰማያዊ ፓርቲ የዓላማ ጽናቱ የበረታ በመሆኑና በሀገር ውስጥ የሚያደርገውም እንቅስቃሴ እጅግ የጎላ ስለሆነ ፓርቲውን ሁላችንም መደገፍ ይገባናል ብለዋል።
የፓርቲው አመራሮች
የፓርቲው አመራሮች
በስብሰባው ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን መግለጫውን ከሰሙ በኋላ ልዩ ልዩ ገንቢ ሃሳቦችን ሰጥተዋል። ተሰብሳቢዎቹ ለፓርቲው ከሰጡት ሃሳቦች ውስጥ፣ “ሰማያዊ ፓርቲ በሀገር ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ በዚህም የድጋፍ ማኅበሩ ከሌሎች የሰላማዊ ትግል ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር በመገናኘት ራሱን ማዳበር ይገባዋል” የሚለው ይገኝበታል።
ተሰብሳቢዎቹ የመጀመሪያ ጥሪ መሆኑን አስታውሰው በዕለቱ የተገኘው የህዝበ ቁጥር አነስተኛ ነው ተብሎ እንደማይገመት በመግለጽ፣ “ፓርቲው የበለጠ በሰራ ቁጥር ብዙ አባላትና ደጋፊ ማፍራት እንደምትችሉ ካለው ሁኔታ መረዳት ይችላል” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። ስብሰባውን ለመዘገብ በስፍራው የነበረው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጽዋል።
ቀጥሎም ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ሥራ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ለተሰብሳቢው ቀርቧል። በመጨረሻም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በስልክ ቀርበው ሰብሳቢዎቹንና ተሰብሳቢውን በማመስገን በሀገር ቤት ያለውን ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክተው፤ በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያቸው አባላትና በሳቸውም ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል የበረታ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ከዚህ የከፋ ችግር ሊገጥመን ቢችልም ፓርቲዬም ሆነ እኔ በጽናት ቆመን ትግሉን እንገፋለን በማለት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል። ከኢንጂነር ይልቃል አጭር የስልክ መልክት በኋላ ስብሰባው ተጠናቋል። 

(ዘጋቢ: ወለላዬ ከስዊድን)

http://www.goolgule.com/semayawi-party-support-group-introduced-in-sweden/

የት ሂዱ ነው?

"ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም"
Prof_Mesfin1
ዓለም ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን “የሙጢኝ!” ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን “የሙጢኝ!” እንላለን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞት ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባሎች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የአያቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

http://www.goolgule.com/i-live-and-die-here-in-my-own-home-land/

Wednesday, March 11, 2015

የወያኔ ጥላቻ ፍሬ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።
ወያኔ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ትግሬ ሁሉ ዕዳ አለበት ማለት እንደወያኔ ማሰብ ነው፤ ወንጀል በዘር አይተላለፍም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳል፤ ጊዜው ሲደርስ ውጤቱንም ለመቀበል ይገደዳል፤ ይህ የሚሆነው ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ኃይል በጎ መንፈስ አድሮበት፣ አእምሮው በትምህርት ተገርቶ በትክክል ማሰብ ሲችል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በአለበት ሁኔታ በጎ መንፈስ የራቀው ይመስላል፤ አእምሮም ጭራሹኑ በእኩይ መንፈስና በጥላቻ እየዛገ ነው፤ ስለዚህ ያስፈራል፤ በደቡብ ሱዳን ሁለት መቶ ሰዎች በዘር ተለይተው ታረዱ ሲባል ያስፈራል፤ በናይጂርያ፣ በኮንጎ የሚካሄደውን የዘርና የሃይማኖት እልቂት ስንሰማ ያስፈራል፤ በ1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊና አዲሱ ለገሰ እንዳስታወሱን የሩዋንዳ የጎሣ እልቂት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፤ የቅርብ ተኳሽ የሆነው የአግዓዚ ጦርም አድፍጦ መጠበቅ ያስፈራል፤ ሌላውም ይህንን አውቆ አድፍጦ መጠበቁ ያስፈራል፤ ሰማይ ጠቀስ የሠሩት፣ የሥልጣን ኃላፊነትን ችላ ብለው በሥልጣን የሚነግዱና የሚከብሩት፣ የማይኖሩበትን ሕንጻ የሚክቡት፣ ከሕዝብ ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት ኑሮ ያስፈራል፤ አቶ አስገደ ወያኔ መደንገጡን ይነግረናል፤ መደንገጥ የማይቆጣጠሩት ፍርሃት ነውና አደጋ ያመጣል፤ አደጋው አደጋን ይጠራል፤ ይህም ያስፈራል።
በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።
ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ጥላቻ ወደንዴት፣ ንዴት ወደቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደአውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።
ሌላ አገር እንዲህ አልሆነም፤ እዚያ አገር እንዲህ አልሆነም፤ የሚባል ነገር የለም፤ እኛ ዘንድ ሌላ ነው፤ የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው!
ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፤ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል፤በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቁጣም ድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳትእንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም፤ ሰው በቀኙ በኩልይነቅላል፤ ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ እያንዳንዱምየ ክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ …ኢሳይያስ 9/18-21
ትንቢተ ኢሳይያስ ለሩዋንዳውያን ብቻ አይደለም፤ ጥላቻና ክፋት በተዘራበት ቦታ ሁሉ ውጤቱ ጥፋት ነው፤ ምናሴ ኤፍሬምን በልቶ አይቀርም፤ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላዋል።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/14596/

Wednesday, February 25, 2015

ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው!

ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም

haile china



የጎረቤት ኬንያ ዳኛ ለኬንያ መንግሥት አስፈጻሚው ክፍል ልኩን ነገረው፤ ሕገ መንግሥቱን በመርፌ አስተኝተህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ሕግ ለማውጣት አትችልም፤ ስለዚህም የሰነዘርኸውን የጉልበት ሕግ አንሣ፤ አለው፤ ዳኛ አይጥፋ! ሌላ ቢቀር ከጎረቤት ዳኝነትን እንስማ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር ስንት ጋዜጠኛ፣ ስንት የሃይማኖትና ስንት የፖሊቲካ መሪዎች ከየወህኒ ቤቱ ይወጡ ነበር! ሁላችንም እንደልባችን ሳንፈራ፣ ሳንፈራራ በሙሉ ነጻነት ችግሮቻችንን የወያኔን ጭቆና ጨምሮ ለመወያየትና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የምንችልበት መድረክ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖረን ነበር፤ ስንት ሰው ሥራ ያገኝ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ በየመንገዱ ጠመንጃ የያዘ ሊያስፈራራን የሚሞክር ሆድአደር እያየን፣ እንደዚሁም በየጫካው ያሉትን እያሰብን ሰላማችንን ከምናጣ አበባውን ትተን፣ ሩዙን ትተን፣ የተወደደልንን ጤፋችንን እያመረትን አዲስ ኑሮ ብንጀምር የተሻለ ነበር፡፡
ግን አንድ እንቅፋት አለብን፤ እነዚህ ከየኪዮስኩ እውቀት ገዝተን አዋቂዎች ሆነናል የሚሉት እንትኖች መጀመሪያ ችግሩ እንዲገባቸው፣ ሁለተኛ መፍትሔው እንዲገባቸው፣ ሦስተኛ ጉልበትና እውቀት አንድ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በጉልበት እውቀት የማይገኝ መሆኑን ማሳመን በረዶ እየወረደ የስሜን ተራራን መውጣት ነው፤ በረዶ ሳይኖር ወጥቼዋለሁ!
እነዚህን የጉልበት አዋቂዎች — ስለሽማግሌዎችና አሮጊቶች ሳያስቡ፣ ስለመብራት ኃይል ሳያስቡ፣ ስለውሀ ሳያስቡ ሁሉም በጉልበት ፎቅ ይውጣ የሚሉ! ይባስ ብለው ለእስረኛውም ፎቅ እየሠሩለት ውጣ! ሊሉት ነው!
እነዚህ የጉልበት አዋቂዎች የአበሻ ኑሮ፣ ቡናው፣ ሙቀጫው፣ ምጣዱ፣ በርበሬው፣ ቁሌቱ፣ ቄጤማው፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ ኧረ ስንቱ! ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው! እናውቃለን ስለሚሉ እንዴትስ ይማራሉ? በእውነት ለመማር ቢፈልጉስ ስንት ዓመት ሊያስፈልጋቸው ነው!
እግዚአብሔር እነሱንም እኛንም በምሕረቱ ይጎብኘን! የሚያስተምር ጎረቤት አያሳጣን! (ምንጭ: ከፕ/ር መስፍን ፌስቡክ ገጽ)
http://www.goolgule.com/forgetting-what-they-have-learned-and-taught-by-the-chinese/

“መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ”

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን አስታወቁ

dark



በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡
የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች “መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ” እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ነገረ ኢትዮጵያ ፌስቡክ ገጽ)
http://www.goolgule.com/opposition-party-leaders-under-severe-interrogation-and-torture/