FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS
Saturday, April 12, 2014
ሒላሪ ክሊንተን ጫማ ተወረወረባቸው
በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ እየተባሉ የሚጠበቁት ሒላሪ ክሊንተን ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ጫማ ተወረወረባቸው፡፡ ጉዳት ባይደርስባቸውም ዜናው ግን የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል፡፡
አሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን በላስ ቬጋስ በተጠራ የመልሶ መጠቀም ኢንዱስትሪዎች (Scrap Recycling Industries) ስብሰባ ላይ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ ከአዳራሹ ጫማ ተወርውሮባቸዋል፡፡
ጫማው ሳይመታቸው ቢቀርም ወርዋሪዋ ግለሰብ አስተካክላ ብትወረውር ግን ክፉኛ ጉዳት ልታደርስባቸው ትችል እንደነበር የቪዲዮው ምስል ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አዳራሹ ጨለምለም ያለ በመሆኑ ክሊንተን ጫማው ከተወረወረ በኋላ ነው ያስተዋሉትና ደበቅ ለማለት የሞከሩት፡፡
ሒላሪ ክሊንተን በጉዳዩ ላይ ቀልድ በማከል አስተያየት የሰጡበት ቢሆንም የስብሰባው ኃላፊዎች ግን ታላቅ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ጫማ ወርዋሪዋ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለች ከመሆኗ በላይ ማንነቷ ገና አልተገለጸም፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ሚስት ሒላሪ ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን ለመቆናጠጥ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት አራት ዓመታት ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ደጋፊዎቻቸው ቢጠቀሱም የጋዳፊ ግድያ ከዚያም ጋር ተያይዞ የተከሰተው የቤንጋዚው ቀውስ እና የአሜሪካው አምባሳደር መገደል፣ በግብጽ የተካሄደው ለውጥና ከዚያም በአሜሪካና ምዕራባውያን ግፊት ለውጡ መቀልበሱ፣ በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን ላይ የወሰዱት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በአፍሪካ እንደነ መለስ ካሉ አምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ ግብረሰዶማዊነት እንዲስፋፋ አሜሪካ የተከተለችው ፖሊሲ፣ ወዘተ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሒላሪ ኪሊንተን በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚ/ርነት ዘመናቸው ስላከናወኑት የሚያወሳ “የሚኒስትር ማስታወሻ” በገበያ ላይ ያውላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የዛሬ ስድስት ዓመት አካባቢ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በኢራቅ ከጠ/ሚ/ር ኑሪ አልማላቂ ጋር ንግግር ሲያደርጉ አገሩ በአሜሪካ ወራሪነት መፍረሷ ያናደደው ኢራቃዊ ጋዜጠኛ የጫማ ሚሳኤል ወርውሮባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
http://www.goolgule.com/shoe-thrown-at-hillary-clinton-at-vegas-speech/
Tuesday, April 8, 2014
ኖርዌይ ኢህአዴግ ያሰረባትን ዜጋዋን ጉዳይ እየተከታተለች ነው
ማዕከላዊ እስርቤት ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል በሚል ተሰግቷል
የኢህአዴግን ካዝና የምትሞላዋ ኖርዌይ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙትን ዜጋዋን አስመልክቶ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየሰራች መሆንዋ ታወቀ። በማዕከላዊ እስር ቤት የታሰሩት ዜጋዋ ድብደባና ቶርቸር እንዳይካሄድባቸው በቅርብ ክትትል እያደረገች መሆንዋን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጎልጉል አስታውቀዋል።
ኢህአዴግን ከልጅነቱ ጀምራ ስትደጉም የኖረቸውና አሁን ደግሞ “በልማታዊ መንግሥትነት” መድባ ድጋፏን የምትዘረጋለት ኖርዌይ ዜጋዋን አስመልክቶ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለባት ይታወቃል። በዚሁ መሰረት የኖርዌይ ትልቁ ጋዜጣ ቀደም ሲል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ ይፋ ያደረገውን ዜና የሚያረጋግጥ ዜና አሰራጭቷል።
ደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሃይሎች አሳልፈው ለኢህአዴግ የሰጧቸው የቀድሞ የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦኬሎ አኳይ የኖርዌይ ዜግነት እንዳለቸው በማረጋገጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተለው፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲም ስራውን እየሰራ እንደሆነ አፍተን ፖስት አመልክቷል።
አፍተን ፖስት “የሰብአዊ መብት ተከራካሪ” ሲል በዜናው መክፈቻ የጠቀሳቸውን አቶ ኦኬሎ አኳይን አስመልክቶ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን አማካሪ ስቫይን ሚኬልሰንን ጠቅሶ “አቶ ኦኬሎ የደቡብ ሱዳን የደህንነት ሃይሎች በደቡብ ሱዳንና በዩጋንዳ ድንበር መካከል ይዘዋቸዋል። አንደተያዙም ወደ ጁባ ሳይወሰዱ ተላልፈው ተሰጥተዋል” በማለት የጉዳዩን አካሄድ አመላክቷል።
የኢህአዴግን የገቢ ምንጭ የሆነችው ኖርዌይ በጉዳዩ አቋም በመያዝ ያስታወቀችው ስለመኖሩ ዜናውን የዘገበው አፍተን ፖስት ያለው ነገር የለም። ይሁን አንጂ ድርጊቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኖርዌይ እንደምትቃወመው አልሸሸገም። አቶ አኳይ ለምን ወደ ስፍራው እንደተጓዙ በውል የተገለጸ ነገር እንደሌለ ዜናው ጠቁሟል። “በተመሳሳይ” በማለት ከዜናው ግርጌ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት ክብር እንደሌለው፣ በነጻ ፕሬስና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እያደር የከረረ ርምጃ በመውሰዱ ክፉኛ የሚዘለፍበት ጉዳይ እንደሆነ አጣቅሷል።
ጎልጉል መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓም (March 28, 2014) ቀን ዜናውን ይፋ በማውጣት ቅድሚያ ወስዶ ሲዘገብ አቶ ኦኬሎ ከደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸውን ጠቁመን ነበር። አሁን አዲስ በመጣው መረጃ በዩጋንዳና በደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ተያዙ መባሉ ምን አልባትም ኢህአዴግ ሊመሰርትባቸው ላሰበው ክስ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሚሆን ጥርጣሬ አለ። የዜናው ምንጭ አቶ ኦኬሎ ከጁባ በሄሊኮፕትር መወሰዳቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
በመለስ ዜናዊ ውሳኔና ትዕዛዝ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት፣ አድርጉ ተብለው የታዘዙትን ባለመቀበል አገር ጥለው የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያገባናል በሚሉ “አክቲቪስቶች”፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና፣ ማህበራት ዘንድ ዋንኛ ርዕስ ያለመሆናቸው ምክንያት አስገራሚ እንደሆነባቸው የሚጠቁሙ ዲያስፖራዎች ጥቂት አይደሉም። ከዚያም አልፎ አሁንም የመታሰራቸው እና እርሳቸውን ለማስፈታት በሚደረገው ሁኔታ ላይ የተፈጠረው ዝምታ አጠያያቂ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
አቶ ኦኬሎ ማዕከላዊ እስር ቤት እንደሚገኙና፣ በዚያም በከፍተኛ ደረጃ ቶርቸር ይደረጋሉ በሚል ስጋት ሁኔታውን ለሚመለከታቸው በማሳወቅ በኩል አንዳንድ ወገኖች እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል። ኢህአዴግ እስካሁን ፍርድ ቤት ያላቀረባቸው አቶ ኦኬሎ “አሁን ስለሚገኙበት የጤና ሁኔታ የኖርዌይ ኤምባሲ የጉብኝት ሪፖርት ይጠበቃል” ሲሉ እኚሁ ክፍሎች አመላክተዋል።
ከቤተሰባቸው ተነጥለው በስደት ከሚኖሩበት ኖርዌይ ወደ ደቡብ ሱዳን ያመሩት የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ደቡብ ሱዳን በህወሃት ሙሉ ቁጥጥርና ፈቃድ የምትንቀሳቀስ አገር መሆኗን እያወቁ ወደዚያ ማቅናታቸውን “ታላቅ ጥፋት” መባሉን መዘገባችን ይታወሳል። ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አሁንም አልተሳካም። ጋምቤላ የአኙዋኮች ጭፍጨፋ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ኦሞት ኦባንግ በቅርቡ መኮብለላቸውና በብዙዎች ዘንድ አውሮጳ እንዳሉ ቢነገርም በትክክል ያሉበት አገር በይፋ አለመታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም።
http://www.goolgule.com/norway-following-up-okellos-arrest/
Sunday, April 6, 2014
በደሴ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ
አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ መፈክር በተለያዩ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ ባሳወቀው መሰረት ዛሬ በደሴ ከተማ ብዙ ሺህ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ሲያሰማ ውሏል።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ከተስተጋቡት መፈክሮች ውስጥ ጥቂቶቹ፣
- መሬት ከካድሬው ወደ ህዝቡ ይመለስ
- አንድነት ኃይል ነው
- የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ
- መሬት ለህዝብ ይመለስ
- ጭቆና በቃን
- ድል የህዝብ ነው
- በግፍ የታሰሩ ይፈቱ
በሰላማዊ ሰልፉ ማብቂያ ላይ የአንድነት ፓርቲ ተ/ም/ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌ በቀለ፣ የአንድነት ፓርቲ ውጪ ጉዳይ ኃላፊ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ የደሴ ሰብሳቢ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በህወሃት/ኢህአዴግ ማስፈራሪያ ሳይሸበር አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ያሰማውን የደሴና አካባቢውን ህዝብ አመስግነዋል።
Saturday, April 5, 2014
የማለዳ ወግ… በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል… (ነብዩ ሲራክ)
ግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ! (ነብዩ ሲራክ፣ ከሳውዲ አረብያ ውህኒ ቤት)
እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቼ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግማሽ እድሜዬን ህግና ስርአቷን አክብሬ የኖርኩባትን የሳውዲ አረቢያን ህግ ተላልፌ አይደለም! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላዬ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሴረውና እየተሴረ ካለው እገታ ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። … ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!
አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቼ እሰማው የነበረውን የወገኖቼ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እየሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !
ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና “አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል” ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ።… አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !
በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቼ ጎን ሆናችሁ አለኝታነታችሁን ለገለጻችሁልኝ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቼ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርበው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናዬ አይለያችሁ!
ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !
በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው …
ሰላም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11664/
Friday, April 4, 2014
ህግን ተላልፈን ከህገወጦች ጋር አንተባበርም! (ከአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት የተሰጠ መግለጫ)
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የእሪታ ቀን በሚል መሪቃል በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስመልክቶ በተለይም ከተማዋን ወደ ማህበራዊ ቀውስ እየመሯት የሆኑትን የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍ ህዝቡ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ለማካሄድ ያቀደውን ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ አስመልክቶ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ካደረግንበት ቀን ጀምሮ የሚጠበቅብንን ህጋዊ የማሣወቅ ሥራዎችን ስንሠራ የቆየን መሆኑና መድረስ ለሚገባው አካል ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጥሪው ለሕዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከተው የሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በህግ የተቋቋመበትን ኃላፊነት በመዘንጋት ለጠየቅነው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ህግ በመተላለፍ ክልከላ አዘል ደብዳቤ ልኳል፡፡ ሆኖም የአንድነት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል የላከው ደብዳቤ በአዋጅ ከተደነገገ ህግ ጋር የሚጣረስና የዜጎችን መብት የሚያፍን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአንድነት ምክር ቤት ግንዛቤ በመያዝ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በማውጣት ለመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአቋም መግለጫው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሠላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ፓርቲያችን መጋቢት 15 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ላስገባለት የሠላማዊ ሠልፍ እውቅና መጠየቂያ ደብዳቤ መጋቢት 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በሠጠው ምላሽ የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄውን አለመቀበሉን ማሳታወቁንና ለዚህ ደብዳቤ የላክንለትን መልስ አልቀበልም በማለት የወጣ ነው፡፡
1. የሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ለሚቀርብለት የሠላማዊ ሠልፍ የእውቅና ጥያቄ ህገ መንገሥቱንና አዋጅን በሚቃረን መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ቢሆንም በማን አለብኝነት አዋጁን በጣሰ መልኩ ምላሽ መስጠቱን አልተቀበልነውም፡፡
2. ህዝብን በተለይም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ህጋዊ እውቅና ካገኘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚቀርብለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱም ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ግለሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ወስነናል፡፡
3. ለህግና ህገ መንግሥታዊነት ጥብቅና ለመቆም ቃል የገቡት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ህግን አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ፓርቲያችን ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
4. አዋጁን ያፀደቀው ፖርላማ ለሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄያችን የተሰጠን ምላሽ ህገ ወጥ መሆኑን እንዲመለከት አባሪ በማድረግ ለላክንለት ደበዳቤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
5. ለመጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም የጠራነው ‹‹የእሪታ ቀን›› ሠላማዊ ሠልፍ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የቀረበ በመሆኑና በህገ ወጥ አሰራር ሊታጠፍ ስለማይችል ምክር ቤታችን ሙሉ እውቅና ሰጥቶታል፡፡
6. በሠላማዊ ሠልፍ ለሚደርስ ማናቸውም አይነት ኪሳራዎች፣ ጉዳቶችና መጉላላቶች ተጠያቂው ህጋዊ ቢሮ ይዞ ህገ ወጥ አሰራር የሚከተለው አካል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
7. አሁን የገጠመን የመሠረታዊ አገልግሎቶች ችግር የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ የገጠመውን ስቃይ እሪ በማለት እንዲያሰማ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መድረኩን ያዘጋጀ ስለሆነ ጥያቄያችሁን ለመንግሥት እንድታስተላልፉ የአዲስ አበባ አንድነት ም/ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የቅስቀሳ ስራ ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ የሚጀመር መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ የዘመቻ ስራ ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ ውጭ በቅስቀሳው ስራላይ ለሚገጥመን ህገወጥ ችግር መንግሥት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ እንገልፃለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11657/
ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ!
መጠላለፍ ወደየትኛው ገደል እየመራን ነው?
የአዲስ አበባን መኪናዎች በተለይም በጫት የሚሽከረከሩት ታክሲዎችን በማንኛውም መስቀልኛ መንገድ ላይ ለአምስት ደቂቃ ቆሞ የተመለከተ ሰው በቀላሉ እንደሚረዳው “እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም!” በሚል መመሪያ መኪናዎቹ ተቆላልፈው እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤ እንደሚመስለኝ የአባቶቻችንን ዕዳ እየከፈልን ነው፤ ዱሮ በደጉ ዘመን ሁለት ኢትዮጵያውያን መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲገናኙ አንተ-እለፍ አንተ-እለፍ እየተባባሉ የሰማዕታቱንና የቅዱሳኑን ስም እየጠሩ ይገባበዙ ነበር! ይህ ባህል በጠንካራ የሥልጣኔ ላጲስ ተደምስሶ ጠፍቶ በምትኩ እኔ ካላለፍሁ ማንም አያልፍም መንገዱን ሁሉ መቆላለፍ አዲስ የመጠላለፍ ባህል እየተተከለ ነው፤ የመጠላለፍ ባህል የሚታየው በባቡር መንገዶች ላይ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ነገር መጠላለፍ ባህል እየሆነ ነው! የዚህ ዝንባሌ መጨረሻው አሸናፊ የሌለበት ሙሉ ጥፋት ነው።
በመንገዶች ላይ ጥቂት በጫት የሚነዱ መኪናዎች በመቶ የሚቆጠሩ መኪናዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ይችላሉ፤ ሲያደርጉም በየቀኑ እየታየ ነው፤ በማኅበረሰባዊና በፖሊቲካ ግንኙነትም አንድ ሰው የሚዘራው መርዝ የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት ፍጥነት የማኅበረሰቡን አባላት ያዳርሳል፤ እንቆቅልሹ እንደሚለው ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ! ማለት መርዝ፣ እሳት፣ ተላላፊ በሽታ በሕዝቡ ላይ ማሰራጨት ከአምስትና ከአሥር ዓመታት በኋላ ውጤቱ ምን እንደሚሆን መገመት አያቅትም።
ድብብቆሽ አይጠቅምም፤ሁለት ነገሮችን በግልጽ ማውጣት አለብን፤አንደኛ በአሜሪካና በአውሮፓ መሽጎ ፍርሃቱንና ሽቁጥቁጥነቱን ለመሸሸግ መርዙን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚረጨው ለምንድን ነው? አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ነው፤ ከአገዛዙ ጋር በሚደረግ ትግል ከታች ሆነው ከሥልጣን ውጭ የሆኑ ዜጎች በሥልጣን ላይ ከተቀመጡት ጋር እየተቆራቆዙና እየተጋጩ ናቸው፤ ይህንን እኔ የላይና-የታች ግጭት (vertical conflict) የምለው ነው፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ጋር የሚደረገው ትግል ይህ ነው፤ ይህንን ለማክሸፍ ወያኔ/ኢሕአዴግ ትግሉን ከላይና-ታች አውጥቶ ወደጎን-ለጎን ግጭት (horizontal conflict) ሊለውጠው ይፈልጋል፤ ከወያኔ/ኢሕአዴግም ውጭ በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት የደነዘዙ ሰዎችም ትግሉን ጎን-ለጎን ሊያደርጉት እየሞከሩ ናቸው።
የፖሊቲካ ትግልን የሚመሩ ሰዎች በጎሠኛነትና በሃይማኖት አክራሪነት ስሜት እየተሳቡ ትግሉን የላይና-የታችነቱን ጠብቀው በተደራቢነት የጎን-ለጎን ትግሉን ይጨምሩበታል፤ ይህ ሲሆን ሀሳብ፣ ጉልበትና ሀብት ይከፋፈላል፤ ይበታተናል፤ ወደዓላማ ለመድረስም ያስቸግራል፤ ወያኔ ወደመጨረሻው ላይ ኢሕአዴግ ብሎ የሰየመውን ቀፎ አስቲፈጥር ድረስ በስሙ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያነሣ ነገር አልነበረውም፤ ወያኔን ለድል ያበቃው የማታለያ ስሙ እንደሆነ በበኩሌ አልጠራጠርም፤ ከሃያ ሁለት ዓመታት የጎሣ ሥርዓት በኋላ ኢትዮጵያ ቆስላለች እንጂ አልሞተችም፤ የአሐዝ ማስረጃ ለማቅረብ ባልችልም በብዙ ጎሣዎች መሀከል ጋብቻ እንደዱሮው እየቀጠለ ነው፤ ይህንን የቆየ የዝምድና ሰንሰለት ለመበጠስ የሚጥሩም አሉ።
ኒው ዮርክ ተቀምጦ ትኩስ ውሻ (ሆት ዶግ!) እየበላ ለእስላም ኦሮሞዎች የመገዳደያ መመሪያ የሚሰጥ ሰው የመንፈስ ጤንነቱን እጠራጠራለሁ፤ ይህንን የኒው ዮርክ ቀረርቶ ተከትሎ ሌላ የመጠላለፍ አዋጅ ሰማን፤ ቴዎድሮስ ካሣሁን ለአጼ ምኒልክ ስለዘፈነ ከበዴሌ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለማስታወቂያ የገባው ውል ሥራ ላይ ከዋለ የበዴሌን ቢራ አንጠጣም ተባለና ማስታወቂያው ተሰረዘ ይመስለኛል፤ ማን እንዳሸነፈ ወደፊት ጊዜ ይነግረናል፤ አሁን ደግሞ ሌላ ማዘዣ ሰማሁ፤ “የስ” በሚለው ውሀ ጠርሙስ ላይ እንስራ የተሸከመችው ኮረዳ መስቀል አድርጋ ነበር፤ ልጅቱ ከነመስቀልዋ የምትታይበትን ውሀ እስላሞች አንገዛም ስላሉ ነጋዴዎቹ መስቀሉን አወለቁባት! ይህንን ማዘዣ ላወጣው አክራሪ እስላም ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለሁ፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ጊዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መግለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! መስቀል የናዚ ምልክትም ሆኖ ነበር! ለማናቸውም የዚህ ዓይነቱን መጠላለፊያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገምዱ ሰዎች ዓላማቸው ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ፍቅርንና ሰላምን ለማደፍረስ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት ክፉን በክፉ አትመልሱ ነውና ለተበጠሰው መስቀል አጸፋውን ለመመለስ ማሰብ አይገባም።
ከኒው ዮርክ የተሰማው ቀረርቶም ሆነ የመስቀል ማስወለቁ ጉዳይ የተከሰተበትን ጊዜ ልብ ልንለው ይገባል፤ እስላሞች ስለነጻነት የሚያደርጉት ንቅናቄ በጣም እየጋለ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቲያኖችም የዜግነት ግዳጃቸው አድርገውት ድጋፋቸውን በሚሰጡበት ጊዜ ነበር፤ ይህ መሆኑ ጥርጣሬን ይጋብዛል፤ የገጠመውን የእስላሞችና የክርስቲያኖች ሰልፍ በማደፍረስ ወይም በመክፈል የሚጠቀም ማን ነው? የሚጎዳውስ ማን ነው? ሁሉም የትግል አጋፋሪዎች ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልገውን ክብደት ቢሰጡት ትግሉ በጎን-ለጎን እንዳይሄድና እንዳይዳከም ይረዳል፤ ከዚያም በላይ አክራሪነት የሚባለውና የሚያስከትለውም ሽብርተኛነት የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፤ እግዚአብሔር ከዚያ ያውጣን!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2006
መጋቢት 2006
(ምንጭ: Mesfin Woldemariam Blog)
http://www.goolgule.com/small-fire-burns-down-the-whole-country/
Subscribe to:
Posts (Atom)