FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, January 29, 2013

ከግብርና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከግማሽ በታች ቀነሰ


ጥር ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በግብርና ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት የሆልቲካልቸር፣ሥጋና የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ገቢ
በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን አቶ ተፈራ ደርበው የግብርና ሚኒስትር ዛሬ ለፓርላማው ያቀረቡት ሪፖርት
ጠቆመ፡፡

በ2005 የኢትዮጵያ የበጀት ቀመር የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከሥጋና ከቁም እንስሳት ከወጪ
ንግድ(ኤክስፖርት) 299 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው ከግማሽ በታች
ማለትም 130 ሚሊየን ወይም የዕቅዱን 44 በመቶ ያህል ነው፡፡ከዚህ ገቢ ውስጥ 71 በመቶ የቁም እንስሳት
ድርሻ ሲሆን ቀሪው 29በመቶ ከሥጋ ኤክስፖርት የተገኘ ነው፡፡

በሆልቲካልቸር(አበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ) ዘርፍም በስድስቱ ወራት ከኤክስፖርት 105 ሚሊየን ዶላር የተገኘ
ሲሆን ይህም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ 46 በመቶ ነው፡፡

የኤክስፖርት ገቢው በምን ምክንያት እንደቀነሰ ሚኒስትሩ ለፓርላማው በንባብ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ
የጠቀሱት ነገር የለም፡፡

በአምስት ዓመቱ የመንግስት መርሃግብርን የተለጠጠ ዕቅድ ለማሳካት በሚል ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት
የተለጠጠና ሊፈጸም የማይችል ዕቅድ ከመያዛቸው ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የኤክስፖርት
ገቢው ከዕቅዱ አንጻር ሲመዘን በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል እየታየበት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው
ምንጮች በተደጋጋሚ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

በዚህ ደካማ መንግስታዊ አፈጻጸምም ሶስተኛ ዓመቱን የያዘው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን
ዕቅድ የመሳካቱ ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱም በመታየት ላይ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተ ደረጃ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል። ችግሩ
በዚሁ ከቀጠለ መለስተኛ መሻሻል አሳይቶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ቀድሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሊመልሰው
ይችላል የሚል ፍርሀት አለ።


ምርጫ ቦርድ እንደተጠበቀው ተጨማሪ የመመዝገቢያ ቀን ሰጠ


ጥር ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በተመዝጋቢዎች ድርቅ የተመታው መጪው የወረዳና የአካባቢ ምርጫ ምዝገባ ለሁለት ቀናት የተራዘመ ሲሆን፣ የኢህአዴግ ካድሬዎች በዩኒቨርስቲዎች ሳይቀር እየገቡ፣ ግለሰቦች እንዲመዘገቡ ካልሆነ ግን ችግር እንደሚደርስባቸው እየገለጡ ነው።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት ካድሬዎቹ በዩኒቨርስቲዎች እየዞሩ ሰራተኞችን ተመዝግባችሁዋል አልተመዘገባችሁም እያሉ ሲጠይቁ ውለዋል።
የኢህአዴግ ካድሬዎች በምርጫው ያልተመዘገቡትን ” ከእኛ ጎን ናችሁ ወይስ ከአሸባሪዎች ” በማለት እያስፈራሩ እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገራቸው በርካታ ሰዎች መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
33 የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለኢህአዴግ ምርጫ አጃቢዎች አንሆንም በማለት ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢህአዴግ በበኩሉ ተቃዋሚዎች በምርጫው የማይሳተፉት ጥቅም ስለማያገኙበት ነው በማለት ተቃዋሚዎች ለወሰዱት እርምጃ መልስ ሰጥቷል።
ምርጫ ቦርድ የተመዝጋቢዎች ቁጥር በእቅዱ የተቀመጠውን ያሟላ ነው በማለት ቢገልጽም ፣ ኢሳት ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን የተመዘገበው ህዝብ ከታቀደውም ከግማሽ በታች ነው።

ሕወሐት ለሁለት ተሰነጠቀ፤ ወረቀት ለአባለት ተበተነ


Tigray People Liberation Front Split

ከኢየሩሳሌም አርአያ
ዛሬ በመቀሌ ለአባላትና አልፎም ለህዝቡ በተበተነ የትግርኛ ፅሁፍ እነ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሐዬ፣ ፀጋዬ በርሔ ከነባለቤታቸው እንዲሁም ሌሎች ከድርጅቱ እንዲባረሩ በተበተነው መግለጫ ተጠቁሞዋል። በመግለጫው፥ ከጀርባ አሉ የተባሉትና « የዚህ መኅንዲስ» ተብለው የተፈረጁት ስብሃት ነጋ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከተባሉት መካከል በዋነኛነት ተፈርጀዋል። እነ ቴውድሮስ ሃጎስ፣አዜብ መስፍንና በረከት እጃቸው እንዳለበት የተነገረለት ይኸው መግለጫ ተከታዩን ይመስላል፤
«ተቆርቋሪ ለሆናችሁ የትግራይ ተወላጆ በሙሉ፤
«ድርጅትህ ሕወሐት እስከ ዛሬ ታግላ እዚህ ደረጃ አድርሰሃለች። በተለይም የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ የነበረው ባለ ራዕይው መሪህ በቅርብ ጊዜ አጥተኽል።
ዛሬ እነዚህን ደካማ ጐኖች ተጠቅመው ለጠላት አሳልፈው ሊሰጡህ የሚፈልጉ ያውም ደግሞ የእኔ የምትላቸው ጅቦች ተነስተውብህ ይገኛሉ። ይህንን ግልፅ ለማቅድረግ አሁን በቅርብ ጊዜ በመቀሌ የድርጅቱ ማ/ኰሚቴ ስብሰባ አካሄደን ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ነው እንግዲህ ተከታዩ ነገር የተነሳው። ይኽውም፥ እነ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሐዬ፣ ፀጋዬ ከሚስቱ ጋርና ሌሎችም ያሉበት ይህን አሉ፤
«ድርጅታችን ጨርሶ ተዳክሞዋል። እኛ የኢትዮጲያ ሕዝብ ትግል መስራች ሆነን ሳለ ወደኋላ ተገፍትረን በአንፃሩ ሌሎች ከእኛ ኋላ የተፈጠሩና ራሳችን ያሳደግናቸው ሲጠናከሩ ድርጅታችን ግን እየተዳከመ በመሄድ ላይ ነው። ባዛው መጠን ሕዝባችን እየተጎዳ ነው። ስለዚህ አሁን ካጋጠመን አደጋ መውጣት ካለብን ከድርጅቱ -የተወገዱትን ግን በመጥፎ ጎዳና ያልተሰማሩትን መልሰን ወደ ፓርቲው ማስገባት አለብን። ይህ ካልሆነ ግን የሕዝብ ትግል አውላላ ሜዳ ላይ ጅብ በልቶት ሊቀር ነው።» በማለት ከጠላቶቻችን ጋር እንታረቅ እያሉን ነው።
“ሕዝባችን አስተውል። በዚህ አይነት ዳግመኛ በድርጅታችን ተኃድሶ እንደሚያስፈልገን ነው የተገነዘብነው። በሚቀጥለው የካቲት ወር በሚካሄደው ጉባኤያችን ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶና አጥርቶ (ውሳኔ አሳልፎ) እንደሚወጣና እነዚህንና መሰሎቻቸው ከሚያራምዱት አቋም ጋር ጠራርጐ እንደሚያስወግድልን ተስፋ እናደርጋለን። በዚህም እያንዳንዱ እንደከዚህ ቀደሙ የተለመደ አስተዋፅኦ (ሚና) እንደሚያበረክት አንጠራጠርም።
በተጨማሪ ከጀርባ ሆኖ የዚህ አፍራሽ ዋና ቀያሽ መሃንዲስ ስብሃት ነጋ መሆኑን ደርሰንበታል።”
ከመቀሌ…

በኢትዮጵያ “ሴክስ ቱሪዝም” ያውም እስከ ሰዶማዊነት ድረስ?


 የ”International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA“ ቅድመ ጉባኤ ምክንያት ሚዲያዎች እና ጦማሪዎች ሐሳባቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ “የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ” የተባለው በአገራችን የሚገኙ ዋና ዋና ቤተ እምነቶች በጋራ የሚሳተፉበት ጥምረትም ተቃውሞውን ገልጿል። ይሁን እንጂ የ ICASAን ጉባኤ በዋነኝነት የሚያዘጋጀው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉባኤው ጋዜጣዊ መግለጫውን ከሚሰጥበት ሥፍራ ሚኒስትሩን በመላክ መግለጫ እንዳይሰጥ አድርጓል። በወቅቱ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ፎቶግራፎችም በፖሊሶች እንደ ተደመሰሱ ሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች የጡመራ መድረኮች ዘግበዋል።

ወደ ዝርዝሩ ከመግባታችን በፊት ነገሩ ምን እንደሆነ በአጭሩ እናቅርበው። ነገሩ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሲሆን 16ኛው “ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የአባላዘር በሽታዎች ጉባኤ በአፍሪካ” (16th International Conference on AIDS and STLs in Africa – ICASA) ይባላል። አለመግባባቱን የፈጠረው ግን ይህ ጉባኤ አይደለም። አለመግባባቱን የፈጠረው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሊደረግ የታሰበው “የአፍሪካ ግብረ ሰዶማውያን የቅድመ ኮንፈረንስ ማነቃቂያ ስብሰባ” ነው። ይህንን የግብረ ሰዶማውያን ጉባኤ በመቃወም መግለጫ ለመስጠት የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ቢሰበሰቡም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በቦታው ተገኝተው ከልክለዋል። ጥያቄው ከዚህ ይጀምራል።
1. አዲስ አበባ አፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ለቁጥር የሚታክቱ ስብሰባዎች የሚደረጉባት ከተማ እንደሆነች የታወቀ ነው። (ከዜናው 90% ስብሰባ የሚዘግበው ምስክሩ ኢቲቪ ነው።) ስለዚህ ከተማዪቱ ብዙ ስብሰባ ባዘጋጀች ቁጥር ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጥሩ ገቢ እንደሚያገኙ እና አገርም ሕዝብም እንደሚጠቀም እናውቃለን። ስለዚህ በተቻለ መጠን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በናይሮቢ እና በሌሎች ተቀናቃኝ ከተሞች ከሚደረጉ ይልቅ በአዲስ አበባ ቢደረጉ ተጠቃሚዎች ስለምንሆን ጤና ጥበቃ ጉባኤውን ለማድረግ መጣሩ ተገቢ ነው። ነገር ግን ይህ ጥረቱ የሕዝብን ሃይማኖታዊ መሠረተ እምነት እስከመጣስ ድረስ መሆን የለበትም።
2. ግብረ ሰዶማዊነትን ክርስትናም ሆነ እስልምና አጥብቆ ይቃወመዋል። በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሰዶማዊነት ኃጢአት ነው። ይህ ሃይማኖት ነው። ቤተ እምነቶቹ ደግሞ ምእመኖቻቸው ከግብረ ሰዶማዊነት እንዲጠበቁ ማስተማር ግዴታቸው ነው። ግብረ ሰዶማዊነትን ለማስፋፋት እና ሰዶማውያንን ለማበረታታት ጤና ጥበቃ ጉባኤ እንዲደረግ መድረኩን እንዳመቻቸው እና እንደተጋው ሁሉ እነዚህ ቤተ እምነቶችም ሰዶማዊነት ኃጢአት መሆኑን አጥበቀው መናገራቸውን መከልከል አይገባም። ይህ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው። መንግሥት በቀጥታ በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞችንም መብት በመጣስ ያነሷቸው ፎቶግራፎች በፖሊሶች እንዲደመሰሱ መደረጋቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦልናል። እንዴት ነው ነገሩ?
3. ጤና ጥበቃ ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መደረጉ ለአገር ኢኮኖሚ ይጠቅማል ብሎ ከሆነ በሌላ አማርኛ “ሴክስ ቱሪዝም”ን እያስፋፋ ነው ማለት ነው። ከአገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላዩ ወጣት እና ሥራ አጥ በሆነባት አገር ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ለሴክስ ቱሪዝም እንዲጎርፉባትና አገሪቱ ካለባት ቅጥ ያጣ ችግር በላይ እንዲህ ዓይነቱ የባህል ወረራ እንዲካሄድባት መንግሥታዊ ማበረታቻ መስጠት ስሕተት ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው። በሌላው ዓለም ቢሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ለማቋረጥ ከመሔድ ይልቅ ከሕዝብ ሊያገኙት የሚገባቸውን እምነት ስላጎደሉ ሥልጣናቸውን ወደ መልቀቅ ይሄዱ ነበር።  አገሩ ኢትዮጵያ ስለሆነ አንድ ሚኒስትር የሃይማኖት መሪዎች ያዘጋጁትን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማስተጓጎል ቻለ።
4. ድርጊቱ ኢትዮጵያውያን እንዲሸማቀቁ፣ እንዲያፍሩ፣ ራሳቸውን እንዲጠሉ የታሰበበት ያስመስለዋል። መንግሥት እርሱ ከፈቀደው ሐሳብ ውጪ ያሉ ሐሳቦችን ሁሉ በመጨፍለቅ እስከ ሃይማኖታችን ድረስ መድረሱ አስደንጋጭ ነው። ሰዶማዊነት ኃጢአት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን ይህንን ነው። ጤና ጥበቃ የጣሰው ይህንን መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ነው።
5. ከዚህ አንጻር ሕዝቡ በሃይማኖቱ የማይቀበለውን ነገር መቃወሙ ተገቢ ስለሆነ መንግሥት የራሱን አስተሳሰብ ለመጫን መሞከር የለበትም። ሕዝቡ ስብሰባው እንዲሰረዝ ለማድረግ አቅሙ ባይኖረውም እንኳን እንደማይቀበለው ለመናገር መታገድ የለበትም። ከውጪ አገር የሚመጡ የተወሰኑ የጤና ጥበቃ እንግዶችን ለማስደሰት በሚሊዮኖች የሚቆጠረው ሕዝብ እምነት መዳጥ አይገባውም። ነውር ነው። ነውር ነው። በጣም ነውር ነው። አደራ ይህንንም “ፖለቲካ ነው” እንዳትሉን እነ እንቶኔ።

Monday, January 28, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ (የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)


ሻማ ማብራት ፣ ኤምባሲ መውረር
በአብዛኛው የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ሻማና ጧፍ ማብራት፣ በሰላማዊ ሰልፍ መጮህ፣ ፒቴሽን መፈራረም፣ በተለያዩ ማህበራዊ አውታሮችና ድሮች መሳደብና የመሳሰሉት ናቸው። ባለፈው ሳምንት የኤርትራ ተወላጆች ሎንዶን የሚገኘውን የኢሳያስ ኤምባሲ ጥሰው በመግባት የፈጸሙት የተቃውሞ ተግባር ከፍተኛ የሚዲያ ትኩረት ስቧል።
“ኤምባሲው የእኛ ነው። ከኤምባሲያችን ወደ የትም አንሄድም” ያሉት የኤርትራ ተወላጆች የሚፈሩትን ኢሳያስን ያገኙ ያህል ፎቷቸውን ከግድግዳ በማውረድ መሬት ላይ በመከስከስ ረጋግጠው ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ራሳቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስና ዓለም ተመልክቷል። ይህ ታላቅ የተቃውሞ መልዕክት ለሁሉም ባለስልጣናት መልዕክት ሲሆን በተለይም ስደት ልዩ መለያው ለሆነው የኤርትራ ህዝብ ባንድነት ይነሳሳ ዘንድ የሚቀሰቅስ ተግባር ሆኖ ተገኝቷል። የእኛ አገር ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎችስ? ሻማና ጧፍ በማብራት እንቀጥላለን ወይስ ተቃውሞውን አንድ ደረጃ እናሳድገዋለን?
መለስ አልታደሉም
ጎል ካስቆጠሩ በኋላ አቶ መለስ የተለጠፉበትን ካኒቴራ በማሳየት ደስታቸውን እንዲገልጹ የታዘዙት የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች የተባሉትን ማድረግ አቅቷቸዋል። ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበሩ አሽሟጣጮች ትዕዛዙ ጎል ስናገባ ሳይሆን ጎል ሲገባብን የመለስን ፎቶ የሚያሳየውን ቲሸርት በማሳየት ሃዘንን መግለጽ ቢሆን ኖሮ አቶ መለስ በቡርኪናፋሶ ጨዋታ ወቅት አራት ጊዜ በሃዘን የመታወስ እድል ያገኙ ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።
እነዚሁ ተረበኞች በናይጀሪያ ጨዋታ ላይ ትዕዛዙ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ መክረዋል። ቡድኑ ሜዳ ሲገባ በመጀመሪያ መለስ ያሉበትን ቲሸርት እንዲለብስ፣ ጨዋታው ሊጀመር ሲል ዳኛውን በማስፈቀድ የናይጄሪያ ተጨዋቾችም ቲሸርቱን ከውስጥ እንዲለብሱ እንዲያስገድዱላቸው ጥያቄ ማቅረብ፣ ከዚያም እኛ ካላገባን እንኳ ናይጀሪያዎች ሲያገቡ የመለስን ቲሸርት በማሳየት ደስታቸውን እንዲገልጹ፣ ይህንን ካደረጉ አላሙዲ እንደሚሸልሙ አስቀድሞ ለተጨዋቾቹ ማስታወቅ የሚሉትን ሃሳቦች ያቀረቡት ሸርዳጆች ሁሉም ተደርጎ ካልተሳካ መለስን በኳስ ሜዳ የማስታወሱ ጉዳይ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ይተገበር ዘንድ በአምስቱ ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ እንዲያዝና ውድድሩን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጀው በማድረግ ለስኬቱ መታገል እንደሚቻል መክረዋል። አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት ስለ ስታዲየም ግንባታ ተጠይቀው “እኔን የሚያሳስበን ማዳበሪያ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
በባንዲራ ብዛት የተሞሸረ ብሄራዊ ቡድን
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ላይ ለክብሩ የቀረበለት የባንዲራ ብዛት በሪኮርድነት ተመዝግቧል። ምናልባትም ይህ የዕድሜ ልክ ሪኮርድ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። አሁን ያለው ባለኮከቡ ባንዲራ፣ የቀድሞው ሰንደቅ ዓለማ፣ የኦሮሚያ መለያ፣ የሞአንበሳ ባለ አንበሳው ባንዲራ፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ባንዲራ፣ የኢህአዴግ አርማ …
ቡድኑን ለመደገፍ ወደ ስታዲየም የመጡት ደጋፊዎች ያሳዩት የተለያ ባንዲራ ሁሉም ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቢሆንም የፖለቲካ መልዕክት ከማስተላለፍ አኳያ ሆን ተብሎ የተደረገ በመሆኑ አገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት አመላካች ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ለወደፊቱ ቡድኑ የሚጫወትበት መለያ የሁሉንም ባንዲራ የሚወክል እንዲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊያስብበት ይገባል። ሁሉንም ብሄሮችና የነጻነት ጥያቄ ያላቸውን ክፍሎች መለያ እንዲያካትት ተደርጎ አዲስ መለያ ከተዘጋጀ ሁሉም የየራሳቸውን ባንዲራና አርማ ከመጎተት ይልቅ አዲሱን ማሊያ በመልበስ ውክልናቸውን ያሳያሉ። በመሆኑም አዲሱ የመጫወቻ ሹራብ ክንዱ የኦነግን አርማ፣ አንገቱ የኢህአዴግን፣ ጀርባው የቀድሞውን ባንዲራ፣ ፊትለፊቱ የኦብነግን፣ ቁምጣው የብአዴንን፣ ኪሱ የስልጤ፣ የእግር ሹራቡ የህወሃትን፣ አልበቃ ካለ ኮፊያና ስካርፕ አድርገው የተለያዩ ብሄሮችን እንዲወክሉና ሜዳ እንዲገቡ ቢደረግ የተሻለ ሳይሆን ይቀራል?
ብሄራዊ ቡድን ሬኮርድ ሰበረ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ ውድድር ብዙ የገባበት ቡድን በመሆን ሬኮርድ ተመዝግቦበታል። ቡድኑ ቡርኪና ፋሶ አስር ሰው ሆነው ቢጫወቱም አጋጣሚውን መጠቀም አልቻለም። በጉዳት የወጣው አዳነ ግርማ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ቶሎ እንደማያገግም የቡድኑ ዶክተር አስታውቀዋል።
ከሰላሳ አንድ ኣመት በኋላ አፍሪካ ዋንጫ የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ቡድን መርሃ ግብሩን የሚያጠናቅቅበት የመጨረሻ ጨዋታውን ከናይጀሪያ ጋር ያከናውናል። ያለፈው ዓመት ባለድል ዛምቢያ ከቡርኪናፋሶ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ከተሸነፈች ወይም እኩል ከወጣችና ኢትዮጵያ ናይጀሪያን ማሸነፍ ከቻለች ወደ ሁለተኛው ዙር ታልፋለች። አሁን ባለው የነጥብ ድምር ውጤት መሰረት ቡርኪና ፋሶ አራት፣ ዛምቢያ ሁለት፣ ናይጀሪያና ዛምቢያ ሁለት፣ ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አላቸው።
ሰውነት ቢሻው ተወቀሱ
“በቀጣይ ያልተጠቀምኩባቸውን አሰልፋለሁ”
በቡርኪና ፋሶ አራት ለባዶ የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተወቀሱ ነው። ሽንፈቱን አስመልከቶ የህዝብ አስተያየት ያሰባሰበው ኢቲቪ “በጨዋታው የአሰልጣኙ ደካማ ብቃት ተስተውሏል፣ እንቅስቃሴው ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱ አልገባኝም። አሰልጣኙ አሰላለፍ ላይና አቀያየር ላይ ስህተት ሰርተዋል። አምስት ተመላላሽ ተጨዋቾችን አሰልፏል…” የሚሉ ነቀፌታዎች አሳይቷል።
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን “በድሉ” በማለት የሚጠሯቸውና በቅርብ የሚያውቋቸው ተጨዋቾች አሰልጣኙ አሁንም ችግሩ አልገባቸውም እያሉ ነው። “በራሳችን ሜዳ ኳስ በብዛት ማንከባለላችን ጎድቶናል” በማለት አቶ ሰውነት የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የተሰጠው አስተያየት በናይጀሪያው ጨዋታ አሰልጣኙ ረጅም ኳስ የመጫወት እቅድ እንዳላቸው አመላካች ነው። ይበልጥ እንዳንከስር እንፈራለን ብለዋል። ምን ይደረግ? ለተባሉት ኳስ ይዞ ባላጋራን በመቁረጥና አማካዩን ክፍል ኳስ ለሚችሉ ልጆች በመፍቀድ እንዲጫወቱ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል። የባዮሎጂ መምህር የነበሩት ሰውነት ቢሻው ወኔ በማነሳሳት እንደሚታወቁ የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች በዚህም በኩል ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ ተጨዋቾቹ ሰክነው እንዲጫወቱ መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ።
ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኪራይ ሰብሰቢ ተባሉ
መንግስት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጣቸው የሚነገርላቸው የጥቃቅን አነስተኛ ተቋማት በኪራይ ሰብሳቢነት ተፈረጁ። ኢንተርፕራይዞቹ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የተግባር ማነቆ እንዳለባቸው ይፋ ያደረገው ኮንስትራክሽን ሚኒስትር እንደሆነ የዘገበው ሪፖርተር ነው።
የተበደሩትን ገንዘብ መመለስ እንዳልቻሉ ሪፖርት የቀረበባቸው ተቋማት በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር እዳ መክፈል ሲገባቸው 575 ሚሊዮን ብር ብቻ መክፈላቸው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የተጠናወታቸው አስብሏቸዋል።1.1 ቢሊዮን ብር መቆጠብ ሲገባቸው ተቋማቱ 540 ሚሊዮን ብር ብቻ ተቀማጭ ማድረጋቸው ሌላው ችግር እንደሆነ ሪፖርተር የጠቀሰው ዘገባ ያስረዳል።
“ትርፍም ኪሳራም የለውም”
ከአካባቢ ምርጫ ራሳቸውን ያገለሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉት ጫና እንደሌለ ተሰማ። የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የህዝብ አደረጃጀት ሃላፊ የሆኑትን አቶ ሬድዋንን ፎቶ በማስቀደም አዲስ አድማስና ሪፖርትር እንዳስነበቡት በኢህአዴግ እምነት “ትርፍም ኪሳራም የለም”።
አቶ ሬድዋን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አለመሳተፋቸው “ለኢህአዴግ ትርፍም ኪሳራም የለውም” በማለት በሰጡት መግለጫ እንደተለመደው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ዘልፈዋል። ለአካባቢ ምርጫ ደንታ ቢስ አድርገው ስለዋቸዋል። ኢህአዴግ ያቋቋማቸውና ተወዳዳሪ ሊሆኑ የማይችሉ ፓርቲዎች ምርጫውን በማድመቅና ኢህአዴግን በማጀብ የተለመደ ተግባራቸውን እንደሚጫወቱ በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወሳል።
source : www.goolgule.com

ESAT Daliy News Amsterdam Jan 28 2013 Ethiopia


የከምሴ ነዋሪዎች የሀይማኖት መሪያችንን አናስወስድም በማለት ተቃውሞአቸውን ገለጡ


ጥር ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢሉባቦር ዞን ከመቱ ከተማ 15 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ከምሴ  ቀበሌ ፖሊሶች  ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር የተባሉትን የእስልምና ሀይማኖት መሪ ለመውሰድ በሄዱበት ወቅት ህዝቡ ግለሰቡን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ችግር መፈጠሩ ታውቋል።
ሼህ ሳሊህ አብዱልቃድር ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት ተከሰው 8 ወራት ከታሰሩ በኋላ መረጃ አልተገኘባቸውም በሚል በነጻ ተለቀው ነበር። ባለፈው ሳምንት ፖሊሶች እንደገና ወደ አካባቢው በመሄድ የእርሳቸውን ጓደኛ ያሰሩ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ሼኩን ለማሰር ወደ ቀበሌው ሲሄዱ ህዝቡ በነቂስ በመውጣትና ተክቢራ በማለት በመቃወሙ በህዝቡና በፖሊስ መካከል ፍጥጫ ተከስቶ ነበር። የህዝቡን ስሜት የተረዱት ፖሊሶች በቀጥታ ወደ ግጭት ከማምራት ይልቅ ከህዝቡ ተወካዮች ጋር ለመነጋጋር መምረጣቸ      ው ታውቋል።
በሽማግሌዎችና በፖሊስ መካከል ያለው ውይይት ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ እንደቀጠለ ነው።
በሌላ ዜና ደግሞ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ  መጡበት አካባቢ የተመለሱ ከ700 የማያንሱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፣ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ትምህርት ለመጀመር እንደሚቸገሩ እየገለጹ ነው። ኢሳት ያነጋገራቸው ተማሪዎች እንደሚሉት በዩኒቨርስቲው በሙስሊም ተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጭቆና የሚጀምረው ” ወደ ግቢ ለመግባት በሚደረገው ፍተሻ  ነው”
በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን በትምህርት ሚኒስቴር በመገኘት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል። ይሁን እንጂ በተማሪዎች እና በመንግስት መካከል ስለነበረው ውይይት ለማወቅ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ሙስሊም ሴቶች ኒቃብ እንዳይለብሱ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጋራ በግቢው ውስጥ ስግደት ወይም ማንኛውም ሀይማኖታዊ ስነስርአት እንዳያካሂዱ ያወጣው መመሪያ እንደማይለወጥ አስታውቋል።