FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, July 25, 2013

(Breaking News) ሰርካለም አዲስ ኢትዮጰያን ጥላ ተሰደደች!

Awramba Times (Phoenix, Arizona) – Serkalem Fasil, award-winning Ethiopian journalist and former co-publisher of the weekly newspapers Asqual, Menilik, and Satenaw has left Ethiopia with her son yesterday.
According to our confidential sources, Serkalem has already departed to the United states and detail has not been given on the matter.
In November 2005, Serkalem was arrested along with thirteen newspaper editors including her husband, Award winning blogger, Eskinder Nega. Eskinder has been jailed seven times by the Ethiopian government and is still in prison under the nation’s sweeping anti-terror legislation. He has been convicted and sentenced to 18 years in June 2012 on trumped up terrorism and treason charges. Amnesty International, Human Rights Watch and CPJ have condemned the ruling as baseless and politically motivated.
Serkalem Fasil won a “Courage in Journalism Award” from the International Women’s Media Foundation in 2007

Tuesday, July 23, 2013

ሰበር ዜና፣ አዲስ አበባ ከተማ በግድግዳ ጽሁፎች (ግራፊቲ) ተሸፍና አደረች


ድምፃችን ይሰማ
ሰኞ ሐምሌ 15/2005
እሁድ ምሽት ለሰኞ አጥቢያ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቦታዎች የሙስሊሙን ህብረተሰብ ጥያቄዎች በሚያንጸባርቁ ጥቅሶች ተጽፎባቸው አደሩ፡፡ በከተማዋ የተለያዩ መንገዶች፣ የመንገድ አካፋዮች እና አጥሮች ላይ መንግስት ሕገ መንግሰቱን እንዲያከብርና በእምነት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም የሚጠይቁ ጽሁፎች በትላልቅ ቁመት ለህዝብ በሚታይ መልኩ ተጽፈው የተገኙ ሲሆን ይህ በተጻፈባቸው ቦታዎችም ሰዎች ሁኔታውን በትኩረትና በግርምት ሲመለከቱ እንደነበር ታውቋል፡፡Ethiopian Muslims protest, Addis Ababa1
በካዛንቺስ፣ በጦርሀይሎች በውንጌት አስኮ መንገድ እንዲሁም ገና በውል ባልታወቁ ቦታዎች ደምጻችን ይሰማ፣ ኮሚቴው ይፈታ፣ ሕገ መንግስቱ ይከበር፣ ጥያቄያችን ይመለስ፣ በእምነታችን ጣልቃ አትግቡብን የሚሉ ጽሁፎች ተጽፈው የታዩ ሲሆን በካባቢው የሚገኙ የወረዳ አስተዳደሮችም በተፈጠረው ነገር በመደናገጥ ጽሁፎቹን ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ ይገኛል፡፡ የጎዳና እና የግድግዳ ጽሁፎች በአለም የታወቁ የመቃወሚያ ዘዴዎች በመሆናቸው ህብረተሰቡ መልእክቱን ለሚመለከተው አካል ለማድረስ የሚጠቀምባቸው ናቸው፡፡
ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎቹን አግባብ ባለው መልኩ ለመንግስት ሲያቀርብ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን አሁንም በዚህ እርምጃው በመቀጠልና ወደ ሌላ ሂደትም በመሸጋገር መንግስት ለሚወስዳቸው ማንኛውም እርምጃዎች እጅ እንደማይሰጥ በማሳየት ላይ የሚገኝ መሆኑን ይህ የዛሬ ክስተት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ሙስሊሙን በአክራነትና አሸባሪነት በመፈረጅ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሙስሊሙ ህብረተሰብ በተገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ድምጹን ለማሰማትና መንግስት ምላሹን እንዲሰጥ ለማድረግ ጥረቶች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ አይነቱ ስልትም ሆነ በሌሎች ሰላማዊ መንገዶችና የመታገያ ስልቶች የሙስሊሙን ህብረተሰብ ሕጋዊ ጥቄዎች ብቻ የሚያንጸባርቁና ከትግሉ መንፈስ ያልወጡ መልእክቶች ሊተላለፉበት እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡
አላሁ አክበር!
Ethiopian Muslims protest, Addis Ababa2
Ethiopian Muslims protest, Addis Ababa3

ከ “ድርጅታዊ ምዝበራ መጽሃፍ” ላይ የተወሰደ ማስታወሻ


በገለታው ዘለቀ
በቅርቡ ለንባብ የበቃው “ድርጅታዊ ምዝበራ” የተሰኘው  መጽሃፍ ደራሲ ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ ጎንደር ተማሪ በነበሩበት ወቅት በኣንድ ነገር ተመስጠው ነበር። ይህ ምናባቸውን የገዛው ነገር በጎንደር ውስጥ እድሜው የትየለሌ የሆነ የኣንድ የዋርካ ዛፍ ተፈጥሮ ነበር። ይህን ዋርካ ባዩት ቁጥር ምናባቸው ተዛምዶን ይፈጥራል። ግዙፉ ዋርካ ዙሪያውን ያሉትን ቅርንጫፎችና ቅጠሎች ይዞ ዝንት ዓለም ይኖራል። ከምድሪቱ የሚያገኘውን ኣስፈላጊ ነገር እያመላለሰ ልጆቹን ያስተናግዳል። ቅጠሎቹም የራሳቸውን ድርሻ ይወጣሉ። ብዙ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች እያሉ ግን ኣንድ ዋርካ ይባላሉ። ብዙ ሆነው እንደ ኣንድ ደሞ ኣንድ ሆነው እንደ ብዙ ናቸው። የበቀለባት ምድር ደግሞ እናት ትሆናለች። ዶክተር ኣክሎግ በዚህ ዋርካ ተፈጥሮ እየተደመሙ የኢትዮጵያን ብዙህ ተፈጥሮና ኣንድነት ያመሳስላሉ። ያን ዋርካ እያሰቡ ብዙሃዊትን ኢትዮጵያ በዚህ መጽሃፋቸው “ኢትዮጵያ ዋርካ ናት” ይሏታል። በዚህ በኢትዮጵያ ብዙህነትና ኣንድነት እምነታቸው ላይ የጸና ኣቋም እንዳላቸው  ከጽሁፋቸው በሚገባ የልባቸውን መረዳት ይቻላል። ይህ የጸና ኣቋማቸው ደሞ የጎሳ ተኮር ፌደራሊዝምን እና ኢፍትሃዊ እድገትን ኣምርረው እንዲታገሉት ያደረጋቸው ይመስላል። በዚህ መጽሃፋቸው የዚህችን ብዙህ ኣንዲት ኢትዮጵያን  ኣጠቃላይ ይዞታዋን ጥልቀት ባለው ሁኔታና በስፋት ይተነትናሉ፣ህመሟን ጉዳቷን ሁሉ ይመረምራሉ፤ መፍትሄውንም ይጠቁማሉ ኣማራጭ የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችን በጠቆም ህክምናውንም ያሳያሉ።Review of Dr. Aklog Birara's new book in Amharic
“ድርጅታዊ ምዝበራ” ይዞት የተነሳው ጭብጥ ኣንድ ብቻ ኣይደለም። የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ(political economy) ጉዳይ እንደ ዋና ማጠንጠኛ ኣድርጎ የሰብኣዊ መብት ኣያያዟን፣ ታሪኳን፣ ኣጠቃላይ ማህበራዊ ጎኗን ሁሉ ይዳስሳል። ጸሃፊው ዶክተር ኣክሎግ የተለያዩ ጭብጦችን ይዘው  ሲጓዙ ኣምርረው የሚከራከሩላቸው ዋና ዋና ሁለት ጉዳዩች ግን ይታዩናል። እነዚህ የዚህ መጽሃፍ ምሰሶዎች  የሰብኣዊ ልማት(Human Development) ጉዳይና የፍትሃዊ እድገት ጉዳይ ናቸው። ፍትሃዊ እድገት ለዋናው እምነታቸው ለሰብኣዊ እድገት ዋና መንገድ(means) በመሆኑ እንደ ኣንድ ዋና ጭብጥ ኣጥብቀው ይዘውት ይታያል። በመጽሃፉ ውስጥ በሃይል የተተቹት የጎሳ ፌደራሊዝም ጉዳይ፣ የሙስና ጉዳይ የ ኣድሎና ሌሎች ጉዳዩች ሁሉ ለነዚህ መጽሃፉን ውስጥ ውስጡን ለሚከነክኑት  ሁለት የመጽሃፉ ወገኖች እንቅፋት ወይም ኣሜኬላ ተደርገው በመታየታቸው ነው።
ዶክተር ኣክሎግ በዚህ መጽሃፋቸው ውስጥ ሁለት ኣይነት የኣቀራረብ ቴክኒክ ያላቸው ሲሆን ኣንደኛው ኢትዮጵያን ከውጭ ሆነው ወደ ውስጥ የሚያዩበት መነጽር ነው። በዚህ ኣቀራረባቸው የኢትዮያን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ደረጃዎች(status) ከሌሎች ኣገሮች ጋር እያወዳደሩ ነው የሚያቀርቡት። በቅርብ ርቀት ለውድድር ካቀረቧቸው መካከል ጋና፣ ቦትስዋና፣ ታንዛኒያ ኬንያ እና ሌሎችም ሃገራት ናቸው። ከዚህ ወጣ ብለውም ከኣጠቃላዩ ኣለም ጋርም እያወዳደሯት ያላትን ኣጠቃላይ ቁመና በሚገባ ያሳያሉ።በተለይ ከጋና ጋር ጊዜ ወስደው ሰፋ ኣድርገው የሁለቱን ኣገሮች ልዩነት ያሳያሉ። ጋና ከሌሎች የኣፍረካ ሃገራትና  ከራሷ መጥፎ የፖለቲካ ተመክሮዎች ተምራ ሁሉን ኣቀፍ ኣሳታፊ የሆነ ስርዓት በመገንባት ላይ ያለች ኣገር መሆኗ ጥሩ ምሳሌ ኣድርጓታል። በኢኮኖሚው መስክ በ2003  ወደ ሃያ ፐርሰንት የሚሆን ዶመስቲክ ሴቪንግ ኣላት፣ በኣንጻሩ የኢትዮጵያ ዶመስቲክ ሴቪንግ 27 በመቶ ወደታች(negative) ነው።ጋና ከውጭ እዳ ነጻ ስትሆን ኢትዮጵያ ወደ 12 ቢሊየን የደረሰ እዳ ኣለባት። የጋና የመብራት ሃይል ፖሊሲ የዛሬ ስምንት ኣመት ሁሉም ጋናዊያን የመብራት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ሲሆን ኢትዮጵያ ሃይል ወደ ውጭ ለመሸጥ ትቋምጣለች:: ጋና ዴሞክራቲክ ተቋሞችን እየገነባች ተከታታይ ፍትሃዊ ምርጫ ያደረገች ኣገር ስትሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ተቋማት እያደጉ ሲሄዱ ኣይታይም።
ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ በኣለም ባንክ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ከሰላሳ ኣመት በላይ መስራታቸው የኣለምን ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ በጥልቀት እንዲያውቁ ስላገዛቸው ኢትዮጵያን በትኩስና ተኣማኒነት ባላቸው ብዙ ማስረጃዎች ለማሳየት ቀላል እንደሆነላቸው መረዳት ይቻላል። የዚህ መጽሃፍ ዋናው ኣንዱ ጥንካሬ በብዙ መረጃዎች የታጀበ መሆኑ ነው።
ከፍ ሲል እንዳልነው መጽሃፉ ሽንጡን ገትሮ የሚሟገትለት የዚህ የሰብኣዊ ልማትን ጉዳይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያነሳ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይጓዛል። በሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ የማያሳይን እድገት ግንጥል ጌጥ ያደርገዋል። በራሳቸው በዶክተር ኣክሎግ ቢራራ ኣገላለጽ “ብልጭልጭ እድገት” ነው ማለት ነው።። ጸሃፊው ኣይቮሪኮስትን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። ኣይቮሪኮስት ውስጥ ከባድ ያልተመጣጠነ እድገት ተከስቶ ብዙ ህንጻዎችና ግንባታዎች ቢሰሩም ኣብዛኛውን ሜዳ ላይ የጣለ እድገት በመሆኑ ኋላ ላይ ለመፈራረስ በቅቷል።
መጽሃፍ ኢትዮጵያን በ1967 በኣሩሻ ታንዛኒያ የተፈረመውን   “የአንድን አገር ልማት የሚወስነው ሕዝቡ ነው። እድገቱ ስለ ህዝብ ኑሮ መሻሻል ነው። ስለገንዘብ (ኪራይ ሰብሳቢነት)( Political elite extraction of rent from society)) አይደለም።”የሚለውን ስምምነት ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያ በዚህ የሰብኣዊ ልማት መለኪያ ከኣጠቃላይ በኣላም ላይ ካሉ 187 ኣገሮች 174ኛ መውጣቷ በርግጥ የሰብኣዊ ልማት ይዞታዋ ምን ያህል ኣስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እንደዘቀጠ ያሳያል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስለ ያልተመጣጠነ እድገት ሲያነሱበት ይህ የሃብት ልዩነት በኣዳጊ ኣገሮች የሚታይና የሚጠበቅ ኣድርጎ ያቀርበዋል። እንደሱ እምነት ኣገርን የሚያሳድጉት ጥቂት ግለሰቦችና ቤተሰቦች ናቸው። የዚህ ኣይነቱ ዝንባሌ በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካና ማህበራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ኣንጻር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው። ከሁሉም በላይ ይህ ኣይነት የእድገት ኣቅጣጫ መገንጠል ዋስትና ነው በተባለበት ኣገር፣ የጎሳ ፌደራሊዝም በሰፈነበት ኣገር፣ ጎሳዎች የየራሳቸው የንግድ ድርጅት ባቋቋሙበት ኣገር ከፍተኛ እምቅ ችግር ሊሆን እነደሚችል ይታመናል። ህዝቦችም ይህ የተጠራቀመ ሃብት ወደኛ ኣንድ ቀን ይንቆረቆራል (wealth trickle down)ብለው በእምነት እንዲጠብቁ የሚያደርግ ከባቢና ዋስትና የላቸውም። ኢትዮጵያ በኣጠቃላይ ሁኔታ ለዚህ የሃብት ክፍፍል (wealth distribution) የማይመች ሁኔታ ላይ ስትሆን ራሱ ሳይንሱ ግን  ጨካኝ ኣይደለም። ኣሜሪካ ስትመሰረት ዶክተር ኣክሎግ እንደሚያስረዱን እነ ፎርድ፣ ቤተልሄም ብረታብረት እና ሌሎችም ሃብታም ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ ኣዳዲስ ፈጠራዎችን በማምጣት፣ የስራ እድል በመክፈት ከፍተኛ የመካከለኛ መደብ የማስፋፋት ስራ ሰርተዋል::  ሩቅ ሳንሄድ እኛው ኣህጉር ውስጥ ጋና በ 2012 በ 14.6 በመቶ ኣድጋ የነበረ ሲሆን ይህ እድገቷም በብዙ መቶ ሺህ የሚሆኑ ህዝቦቿን ወደ መካከለኛ ገቢ ስቧቸዋል። በኣንጻሩ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንትና ዘጠኝ ኣመታት በተከታታይ በጥንድ ቁጥር እያደገች የመካከለኛ መደብ የማስፋፋት ስራ ኣይታይም። ኢህኣዴግ ከመጣ 20 ኣመታት በሗላ፣ ከስምንትና ዘጠኝ ኣመት ጥንድ ቁጥር እድገት በኋላ 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የቀን ገቢው ከ 2 ዶላር በታች ነው።76 በመቶ የሚሆነው ኣምራቹ ክፍል ወጣቱ ከሃገር ብን ብሎ መጥፋትን ይመኛል።ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው የማምረት ኣቅም ያለው ወጣት ስራ ኣጥቶ በየሱቁ ስር ይቆማል።ጉልበት በጣም ይባክናል። ቢያንስ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የለጋሾችን የምግብ ርዳታ ተስፋ ኣድርገው ይኖራሉ። በ2011 ኢትዮጵያ በጤና ጥበቃ ኣገልግሎት ከኣለም 109ኛ ስትሆን በንጹህ ውሃ ኣቅርቦት የመጨረሻ ናት።  ምግብ በማጣት እድገታቸው የተሰናከለ (malnourished children) ህጻናት ቁጥር ሰላሳ አምስት ከመቶ ደርሷል። 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖረው በቀን ከ $1.25  በታች ነው። 0.22 ሃኪም ለኣንድ ሺህ ኢትዮጵያዊ ነው።ኢንተርኔት ሃያ ኣራት በመቶ ብቻ ነው። የሲቪል ሰራተኛው ሪል ኢንካም እየቀነሰ ነው የመጣው:: የዋጋ ግሽበት በ 2011 ሃምሳ በመቶ ነበር:: እነዚህ እውነቶች የሚያጋልጡት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሃብት መንቆርቆር (wealth trickle down) ጉዳይ “ላም ኣለኝ በሰማይ ወተቷንም ኣላይ” መሆኑን ነው። ያ የጥንድ ቁጥር እድገት ምናልባትም የኤፈርት እድገት  ይሆናል።
ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ የጎሳ ፌደራሊዝምን ተከትሎ ስለመጣው ኢፍትሃው እድገት ሲገልጹ።
ከፖለቲካ ውጭ ለመበልጸግ ሳይሆን ኑሮን ለማሸነፍ የራስ ዳሸንን ተራራ የመውጣት ያህል ነው። ይላሉ::
ቦትስዋና በ1966 ነጻነቷን ስታገኝ በእጇ ያገኘቻቸው የተማሩ ሰዎች 22 ብቻ ነበሩ። ዛሬ ከኣፍሪካ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት ብዙ ምሁራንን ያፈራች ኣገር ናት።ለዚህ ፈጣን እድገቷ ትልቁን ሚና የተጫወተው የተረጋጋ ፖለቲካና ፍትህ በመኖሩ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ  ህግ ኣውጪውና ህግ ኣስፈጻሚው ነጻ ስላልሆነ Check and balance ኣይኖርም:: በህግ  የበላይነት ጥራት መለኪያ ኣሜሪካ  91.8% ያስመዘገበች ሲሆን ኢትዮጵያ 16.4% ኣስመዝግባለች::  በኢትዮጵያ ውስጥ በርግጥም ይህ የጎሳ ፖለቲካ ከመጣ ወዲህ የኢትዮጵያዊያን ዋና የልብ ጥያቄ የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ ሳይሆን የፍትህ ጥያቄ ሆኖ ይታያል። ዋናው ጥያቄ ቢያንስ ቤታችን ያፈራውን፣ ያለችንን ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንካፈል የሚል ይመስላል። ይህ እውነት ነው። ዋናው የመንግስት መኖር ኣስፈላጊነት ለፍትህ መስፈንና የእድገት ኣቅጣጫዎችን ለመቀየስ ነው። መቼም መንግስት ኣያርስም ኣይቆፍርም። የመንግስት ኣስፈላጊነት ዋናው እና ትልቁ ጉዳይ ይሄ ነው። ድሆችን እየነጠቁ ሃብታም የሚሆኑበት ኣገር መንግስት ኣለ ማለት ያስቸግራል። ኣሁን ያለው ኢፍትሃዊ እድገት መንግስት ባይኖረንም ሊከሰት ይችላል። ጉልበተኞች ድሃውን እየነጠቁ ሃብታም በመሆን እንዲህ ኣይነት ልዩነት ይመጣል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ኣዲስ የሚነሱ ሃብታሞች ከታች ህዝቡ ደግፏቸው፣ ከመካከለኛ ገቢ ወደ ከፍተኛ የሚያድጉ ሳይሆን ኣንድ ሃብታም የሚወለደው ብዙ ድሆችን በመጨመር ነው። የብዙ ድሆችን ቤት እየዘጉ በፍጥነት ሃብታም መሆን ህገ ኣራዊት ነው። ትልቁ የማስተዳደር ጥበብ የሚፈተነው ፍትሃዊ እድገት በማምጣት ነው።በኢትዩጵያ ውስጥ በተለይ በነዚህ ኣርባ ኣመታት መንግስት የሚባለው ትልቅ የህብረተሰብ ተቋም በፓርቲ ተውጦ ነው የሚታየው። ፓርቲው መንግስትን መዋጡን የሚያሳየው ኣንደኛ የተቋማት ነጻ ኣለመሆን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሁሉ በራሱ በፓርቲው የውስጥ ኣሰራር መቅረጹ ነው። የግምገማው ስልት፣ ከዘበኛ ጀምሮ የኣባልነት ፎርም ማስሞላት፣ ኣዲስ የሚቀጠሩ የመንግስት ሰራተኞች ኣባል ካልሆኑ ያላመቀጠራቸው ጉዳይ፣ ስኮላርሺፕ ኣንዱ መለኪያ በኣባልነት የመሆኑ ጉዳይ የሚይሳየው መንግስትን እያጠፉ ኣገሪቱን በፓርቲ መዋጣቸውን ነው የሚያሳየው። እንዲህ ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ የኣንድ ፓርቲ ኣባል እንዲሆን ከተገደደ እንዴት ሆኖ ነው በምርጫ ሌላ መንግስት የሚመሰረተው?::  ስልጣን የያዘ ፓርቲ ልማትን ማፋጠን(accelerate ማድረግ) ስራው የነበረ ቢሆንም መንግስትን ማጥፋቱ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ችግር ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣድርጓል።
ዶክተር ኣክሎግ የሰባዊ መብት ጥያቄም ኣንዱ የተመጣጠነ እድገት የማምጫ መሳሪያ ኣድርገው ያዩታል። ኣጽንዖት ሰጥተው ሲገልጹትም
ለኣገር መክሸፍ ዋናው ምክንያት የሰባዊ መብቶች መታፈን ነው። ጎሳ ተኮር ፌደራሊዝም ብሄራዊ ማንነትን ኣብሮ ማደግን ቀብሮታል
በኢትዮጵያ ውስጥ ያላግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ፣ ግፍ እየተፈጸመባቸው ስላሉት ወገኖች ጉዳይ ኣጠቃላይ ስላለው የሰባዊ መብት ኣያያዝ በሰፊው መጽሃፉ ይዘረዝራል።በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጽዳት ኣለማቀፍ ወንጀል በሚገባ ለታሪክ ኣስቀምጠውታል። ስደትን በተመለከተ ስምንት በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ ተሰዶ ይኖራል። ከ 1941-1974 ድረስ በኣጠቃላይ ለትምህርትና ለተለያዩ ጉዳዩች የተሰደዱ 20  ሺህ ሲሆኑ በኣሁኑ ሰኣት የታወቁት ብቻ ስድስት ሚሊየን ደርሰዋል።ለዚህ ስደት ከሚያበቃቸው ጉዳዩች መካከል ሙሰኛ የሆነው የጎሳ ፖለቲካ የኢኮኖሚ እድላቸውን ስለዘጋው፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በፖለቲካ ኣመለካከትና በጎሳ ተጽእኖ ነው።
ዶክተር ኣክሎግ ከፍ ሲል እንዳልነው የኢትዮጵያን ኣቋቋም የሚመዝኑት ከላይ ሆነው፣ ከውጭ ወደ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ በየ ሴክተሩ እየዞሩ ጓዳ ጎድጓዳዋን በባትሪ ያሳያሉ። ውስጥ ውስጡን ያለውን የሙስና ጉድ በሃቀኝነት ኣጋልጠዋል። የመጽሃፋቸውን ርእስ ለምን “ድርጅታዊ ምዝበራ” እንዳሉት የሚገባን ኋላ ላይ ለሙስና የሰጡትን ሰፊ ትርጉም ስንረዳ ነው። በዚህ መጽሃፍ ሙስና የታየበት መነጽር ከቁሳቁስና ከገንዘብ ዝርፊያ በላይ ኣድልዎ የሞላበትን ፖሊሲና የጎሳ ፖለቲካን ሁሉ ይጠቀልላል። ለዶክተር ኣክሎግ 99.6 በመቶ ፓርላማውን መቆጣጠር ራሱ ሙስና ነው። በሃገሪቱ የሚታየውን ኢፍትሃዊ እድገት፣ የመብት ረገጣ የተንሻፈፈ ፖለቲካ ሁሉ የሞሰሰ ስርዓት ውጤት ኣድርገው ነው የሚያዩዋቸው። ከዚህ ኣንጻር ኣጠቃላይ የመጽሃፉ ርእስ የተነሱትን ጭብጦች ጠርንፎ የያዘ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ሙስና የመጀመሪያው ቤቱ ኣእምሮ ውስጥ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የሞሰሰ ኣይምሮ የሚያወጣው ፖሊሲና የሚያቆመው ፖለቲካ ለሙስና ትልቅ በርን እየከፈተ ኣገር ያጠፋል።ይሁን እንጂ እንዲህ ለድሆች የተሰጠን ርዳታ ሳይቀር በቢሊዩን የሚቆጠር ዘረፋ እየተካሄደ፣ ለጋሾች የሚሰጡት ገንዘብ ለሰባዊ መብት መጣሻ መሳሪያ እየሆነ ሳለ ለጋሹ ኣለም ስለምን ችላ ኣለ? የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታ ተቀባይ ከሆኑት መካከል ከኣለም ሶስተኛ ደረጃ ያላት ሲሆን ይህም ያለ እነዚህ ለጋሾች ድጋፍ መንግስት ሊቆም እንደማይችል ከፍተኛ የሆነ የሰባዊ ልማት እንደሚያስፈልግ ያሳያል። ታዲያ በርግጥ እነዚህ ለጋሽ ኣገራት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ሙሉ በሙሉ ኣያውቁም ማለት ሳይሆን እኛ ባየነውና በገባን ልክ ኣያውቁም። የዚህ መንግስት ኣንዱ “ጥንካሬ” በከፍተኛ ሁኔታ ማስመሰል መቻሉ ነው። እነዚህ ብልጭልጭ እድገቶች ሁሉ ማሳያዎችና ለጋሾችን ማደናገሪያዎች ናቸው። የሰባዊ ልማቱን በመረጃ ማጭበርበርም ስለሚኖር ይሄን ያህል ትኩረት የሰጡት ኣይመስልም።ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ኣንዴ በእርዳታ መልክ የሰጡትን ገንዘብ የት ኣደረሳችሁት ብለው ለመጠየቅ የሚያፍሩና  የሞራል ጉዳይም የሚያነሱ ይመስላል። ደፍረው ገንዘቡ የዋለበትን ለመጠየቅ፣ ኦዲት ለማድረግ ኣይደፍሩም። እውነቱ ግን ለድሆች የተለገሰ ገንዘብ ለመጨቆኛ ሲሆን ከዚህ የበለጠ ግፍ ስለሌለ ኣይን ኣውጥተው ጥልቅ ኦዲት ሊያደርጉ ይገባል። ኣንዱ ይሄ ነው:: ሌላው ደግሞ በኣፍሪካ ቀንድ ኣካባቢ የኢትዮጵያ መንግስት በጦር ሃይል የበላይነት ለማሳየት ባደረገው ጥረት በዚያ ቀጣና መረጋጋትን ሊያመጣ ይችላል ከሚል እምነት የጣሉ ሲሆን ይህ እምነታቸው በውስጥ ያለውን የዴሞክራሲና የሰባዊ መብት ይዞታ ጉዳይ በደንብ እንዳያዩ ኣድርጓቸዋል። ነገር ግን ህዝቡን እያሰቃየ ለራሱ ህዝብ ኣሸባሪ የሆነ መንግስት ኣንድ ቀን ድርምስ ቢል የዚያ ቀጣና መረጋጋት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባል። ዛሬ ኢትዮጵያ በጎሳ የተከፋፈለች ስለሆነችና የመገንጠል ጥያቄ ይዘው ነፍጥ ያነሱ ወገኖች ባሉባት ሃገር የሚመጣው ኣለመረጋጋት እጅግ የከፋ ይሆናል።
ሌላው ደራሲው ዶክተር ኣክሎግ የሚሞግቱለትና ጥብቅና የቆሙለት  ጉዳይ የመሬት ነጠቃውን ጉዳይ ነው። ከ90 ሚሊዮን ህዝብ 88 በመቶ የሚሆነው ህዝብ እርሻን ተመክቶ በሚኖርባት ኣገር ባለፉት ኣንድ ኣስርት ኣመታት ኢትዮጵያ ፈረንሳይን የሚያህል የእርሻ መሬት ከሳውዲና ከሌሎች ኣገሮች ለመጡ ኢንቨስተሮች ኣስረክባለች። በዚህ ንጥቂያ የተፈናቀለው ህዝብ ኣንድ ሚሊዮን ኣምስት መቶ ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ኦሞ ሸለቆን ሳይጨምር ነው።በየኣመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ እየተራበባት የስንዴ እርዳታ ከውጭ እየለመነች በሌላ በኩል እዚያው ኣገር ውስጥ እየተመረተ ከፍተኛ መጠን ያለው ሩዝና ስንዴ እየተጫነ ይወጣል። ገና ለሳውዲዎች በጋምቤላ ብቻ 290,000 ሺህ ሄክታር እንደሚሰጥ መንግስት ተስማምቷል።  በነገራችን ላይ ሳውዲ ከዚህ በፊት የከርሰ ምድር ውሃዋን እየተጠቀመች ስንዴ ማምረት ጀምራ ለተወሰነ ኣመታት ኣለምን ኣስደንቃ ነበር። ይሁን እንጂ በኣሁኑ ሰኣት የከርሰ ምድር ውሃዋ በማለቁ ነው ከጅሎች ኣገር ሞፈር ልትቆርጥ የወጣችው።
ስለ መሬትና ውሃ ሙስና ሲነሳ ብዙ ሰው እንደሚለው ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ኣለ ። በእርዳታ የምትኖር ኢትዮጵያ ሳውዲን ከመሬቴ ድርሽ እንዳትይ እንድትል ኣይደለም የሚጠበቀው። ነገር ግን ግልጽ በሆነ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ኢትዮጵያዊያንና ሳውዲዎች ኣብረው ሊጠቀሙ ይገባል። ፖሊሲው ርህራሄን፣ መከባበርን፣ሶሊዳሪቲን እና የሃላፊነት ስሜትን ያገናዘበ መሆን ኣለበት። ዛሬ ኢትዮጵያ ከዚህ ፈረንሳይን ከሚያህል ከሰጠችው መሬት ምን እንደምትጠቀም ኣይታወቅም። ሙስና ስላለ ዜጎች ስለዚህ ግዙፍ መሬት ውል ኣያውቁም። የስራ እድል እንዳይባል የስራ እድል የሚፈጥረው በሄክታር 0.005% ብቻ መሆኑን መጽሃፉ ያሳየናል ።
ከዚህ የመሬት ነጠቃ ኣንዱ የመንግስት ስሌት  የታወቀ ነው። እነዚህ መሬት ነጣቂዎች ኣንዱ ያሳሰባቸው ጉዳይ የኣለም ህዝብ ብዛት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ ይህም በኣላም የምግብ ዋስትና ላይ ጥላ  ይፈጥራል በሚል ስጋት ነው። በዚህ መጽሃፍ ላይ እንደተጠቀሰው የኣለም ህዝብ ብዛት ከኣርባ ኣመት በኋላ ዘጠኝ ቢሊዮን ስለሚሆን ቶሎ ቶሎ የድሆችን መሬት እየነጠቁ ነው። እነዚህ ኢንቨስተሮች መሬት የሚወስዱት ለኣሁኑ ሳይሆን ለሚመጣው ትውልድ ይዞ ለማቆየት ብለው ነው ማለት ነው። ይህ ሞቲቭ መሬታቸውን ላጡ ህዝቦች በብዙ መንገድ እንዲሰጉ ያደርጋቸዋል። ኣንደኛው እቅዳቸው የረጅም ጊዜ በመሆኑ የያዙትን መሬት እንደያዙ ለመቆየት ከሚያስችላቸው ዘዴ መካከል ኣንዱ ይህንን መሬት የሸለማቸውን መንግስት በስልጣን ላይ እንዲቆይላቸው መታገል ነው። እነዚህ ሃብታሞች በሃብታቸው የሃገሪቱን ፖለቲካ በማወሳሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይታመናል። ቢያስተውሉት ግን ለጋራ ጥቅም በሚደረግ የእርሻ ኢንቨስትመንት ውስጥ ቢገቡና በሩቁ ቢያስቡ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ያለ ስጋት ይሰራሉ።ለውጥን ያልተረዳ እቅስቃሴ ጦሱ ለልጅ ልጆችም ይተርፋል።
በሌላ በኩል ያሉንን እሴቶች መንከባከብ እንዳለብን መጽሃፉ ይመክራል። ማህበራዊ ካፒታልን(Social capital) ወደ ምርት መለወጥ ጠቃሚ ነውም ይላል። በኣጠቃላይ ነጻነት የህግ የበላይነት መኖር እንዳለበት ያሰምራል። ከሁሉ በላይ ኣጠቃላይ ሲስተሙን ያረከሰውን የጎሳ ፖለቲካ ማስወገድ ለፍትዊ እድገት መሰረት መሆኑን ኣጥብቆ ይመክራል። የውጭ መንግስታትም የሚሰጡትን እርዳታ እንዲቆጣጠሩ ይመክራል። የተለያዩ የፖሊሲ ኣቅጣጫዎችንም ይዘረዝራል።ሌላው የዚህ መጽሃፍ ትልቅ ጥራት(quality) በሁሉም ደረጃ ላሉ ሰዎች መጣኝ መሆኑ ነው። በኣጠቃላይ መጽሃፉ ትኩስ መረጃዎችን ይዞ ኢትዮጵያ ኣሁን ያለችበትን ሁኔታ ቁልጭ ኣድርጎ የሚያሳይ ሲሆን ለወደፊቱ ደግሞ ቅርስና ታሪከ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እኔን እና ይህንን ሀሳቤን የሚጋሩትን የሀገርህ ልጆችን ላንዳፍታ ጊዜ ስጥተህ አድምጠን!


ብሩክ ሲሳይ
ለረጅም አመታት በተለያዩ የአለም ክፍሎች እየተዘዋወርክ በመሮጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ማድረግህን አንዘነጋውም። በነዚያ ወርቃማ የሩጫ ዘመኖችህ ባገኘሃቸው ድሎች አንተም ተደስተህ እኛንም ብዙ ጊዜ ያስደሰትከን መሆኑን አንረሳውም። ሀገራችንን የምትወክለውን ሰንደቅ አላማ ይዘህ በመሮጥህ ብቻ ሀገርህን እና ህዝብህን ትወዳለህ ማለት አይቻልም። አዎ ሀገርህን መውደድ መገለጫው ብዙ ነው፤ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩን ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና ልማድ፣ አለባበስ ይወዳል፣ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩን ህዝብ ይወዳል፣ ሀገሩን የሚወድ ሰው የሀገሩ ማህበረሰብ የተገነባበትን ሞራላዊ እና ስነምግባራዊ እሴቶች ያንፀባርቃል።Haile Gebrselassie is an Ethiopian long-distance track and road running athlete.
በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራ ወገኖቻችን ልጆቻቸው የሀገራቸውን ቋንቋ እና ባህል እንዲያውቁ ጥረት ያደርጋሉ ልጆቻቸውም በሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩና ባህላቸውን ሲያንፀባርቁ እናያለን ነገር ግን አትሌት ኃይሌ በኢትዮጵያ እምብርት የሚኖሩት ያንተ ልጆች የራሳቸውን ቋንቋ መናገር ሲሳናቸው እና ባህላቸውን ረስተው የምዕራባውያንን የህይወት ዘይቤ ሲያንፀባርቁ በቴሌቪዥን መስኮት ሳይ ያፈርኩትም የፈረድኩትም በአንተ ነው። አዎ ልጆቹማ ምን ያድርጉ የሰጧቸውን ነው የሚቀበሉት፣ ያሳዩቸውን ነው የምያደርጉት እንዲያውም በግጥምም እኮ እንዲህ ይባላል።
ከማንም ከምንም ከሁሉም በላጩ፥
ለልጆች ሥርዐት ቤተሰብ ነው ምንጩ
ባህልንና ቋንቋን መውደድ አንዱ የሀገር ፍቅር ማሳያ እና መግለጫ ነው። አትሌት ኃይሌ ለሀገርህ ያለህን አመለካከት ምን አይነት እንደሆነ በትንሹም ቢሆን ይች ታሳያለች።
አንድ ጓደኛየ ከጥቂት አመታት በፊት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ እኮ ባህርዳር ላይ ትምህርት ቤት አለው ብሎ ሲያጫውተኝ፤ ትምህርት ቤቱ በበጎ አድራጎት መልክ ለወላጅ አልባና ድሀ ቤተሰብ ላላቸው ህፃናት ማስተማሪያ የሚውል መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነገሩን ጠበቅ አድርጌ ጓደኛየን ስጠይቀው የከበርቴ ልጆችን ታሳቢ አድርጎ ለቢዝነስ የተሰራ ትምህርት ቤት እንደሆነ በመንገር ግምቴን ናደው። ለነገሩ ስህተቱ የኔ ግምት ነው፣ አትሌት ኃይሌ እስኪ ላንዳፍታ አስበው እኛን የማያውቁን እንደ የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ሮጄር ፌደር አይነት የሩቅ ሀገር ባዕዳን ሰዎች ሰብአዊነት ተሰምቷቸው ለአሳዛኝ ህፃናት ወገኖቻችን የሚያገለግል ት/ት ቤት ያሰራሉ፣ ህፃናቱን በሀገራቸው እየተማሩ እንዲያድጉ ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋሉ። የኛው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ደግሞ የእነዚህ ህፃናት ቤተሰቦችን መሬታቸውን እንዲያጡ ከመንግስት ጋር እየተሞዳሞድክ በኢንቨስትመንት ስም ብዙ ሺህ ሄክታር መሬት እየተቀበለክ ከትራክ ሩጫ ወደ ቢዝነስ የሩጫ ውድድር መግባትህን ሳይ በመጀመሪያ አዝናለሁ ቀጥየ ደግሞ ይሄ ሰው ግን ኢትዮጵያዊ ነውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ ምክንያቱም የቤተሰቦቻችን እና የማህበረሰባችን በአጠቃላይ ያደግንባቸው የሀገራችን ስነምግባራዊ እና ሞራላዊ እሴቶች እንዲህ አይነት ፍፁም ስግብግብ ባህርይ ያለው ግለሰብ እንዲፈጠር ምቹ አይደለም ብዬ ስለማስብ ነው።
አትሌት ኃይሌ እስኪ ከጓደኛህ ከኬንያዊዩ ፖልቴርጋት ሰብአዊነት ምን እንደሆነ ተማር፤ የሚገርመው ደግሞ ይህን ስግብግብ ባህርይህን ለሰው መርዳት ጥሩ አይደለም፣ እርዳታ ሰነፍ ነው የሚያደርገው፣ እኔ በጥረት ነው እዚህ የደረስኩት እያልክ በአስመሳይ ቃላት ስትሸፍንና ምክንያታዊ ለመሆን ስትጥር ሳይ ታበሽቀኛለህ። ያንተን ጥንካሬ አደንቃለሁ ነገር ግን ወላጅ የሌለውን ህፃን ማስተማርና ማሳደግ፤ የሚበላው ያጣን ህፃን ምግብ ማብላት፣ ደብተር እና እስክርቢቶ ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ እንዴት ነው ህፃናቱን ሰነፍ የሚያደርጋቸው?? አትሌት ኃይሌ እርዳታ ለማድረግ እኮ ከአንተ ኪስ አይጠበቅም በውነቱ አንተ ሰብአዊ ልቦና እና ጊዜህን ለመልካም ነገር ብታውለው ስምህ ብቻ ይበቃ ነበር፤ በስምህ ብቻ አለምአቀፍ እርዳታወችን ታሰባስብበት ነበር ልክ እንደ ጓደኞችህ፤ እሺ ይሄንም ተወው ቢያንስ እስኪ አንተ መስጠት እንደማትወደው ሁሉ ደሀን እያፈናቀልክ መሬት በርካሽ ዋጋ አሊያም በነፃ መቀበሉን ከመንግስት አቁም። ባለፈው ሰሞን መንግስት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ይዘዋል ወይም ደግሞ መሬት ዘርፈዋል ካላቸው ከፍተኛ ከበርቴዎች ውስጥ አንተ መኖርህን ስሰማ በጣም ነው ያፈርኩት
በባለፈው ሰሞን መምህራን ኑሮው ከብዶናል ወርሀዊ ምንዳ ይጨመረን ብለው ቢጠይቁ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ይህን የጠየቁትን መምህራኖች ብቃት የሌላቸው ናቸው ብለው አሳፋሪና የማይገናኝ መልስ ያውም በፓርላማ ሲሰጡ፣ ብዙዎቻችን ሰውየው እየሳቱ ነው አሊያም ደግሞ አሞቸዋል ብለን ነበር ነገር ግን በጣም ያዘንኩት አንተ እነኚህን መምህራን ሰነፍ ስለሆኑ ነው ደመወዝ ይጨመረን ያሉት ብለህ የሟቹን ጠቅላይ ሚኒስተር አሳፋሪ እና በሬ ወለደ ንግግር ስትደግመው አፈርኩብህ። ማን ያውቃል ከዚች ንግግር በኋላ ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር ሃሳባቸውን ስለደገፍክ ብዙ ሄክታር የደሀውን ህዝብ መሬት በዳረጎት መልክ አሰጥተውህ ሊሆን ይችላል።
አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ባገኘሀው ዝና እንዲሁም ባካበትከው ሀብት ምክንያት በዙሪያህ ብዙ ሰወች ይከተሉህ ወይም ይከቡህ ይሆናል፣ ጌታየ አቤት ወዴት የሚሉ ብዙ ሰዎች በዙሪያህ ሊኖሩ ይችላሉ፣ ከአፍህ የሚወጣውን ንግግርክን እየጠበቁ ባያስቅም እንኳ የሚፈነድቁልህ ብዙ ይኖራሉ፣ ኃይሌ አንተ እኮ ምርጥ እና ለየት ያልክ ሰው ነህ እያሉ የሚክቡህ ብዙ ሺህ ሰወች በዙሪያህ ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመሆኑም አንተ የምታስበው ሁሉ ትክክል እንደሆነና እና ካንተ በላይ አዋቂ ኢትዮጵያዊ የሌለ እየመሰለህ ራስክን ክበህ እና ቆልለህ በየቦታው እና ሜዲያው እየተገኘህ የምታደርጋቸውን አሳፋሪ ንግግሮችን መስማትና ማድመጥ ሰልችቶናል እባክህ ዝም በልልን። በነዚህ አሳፋሪ ንግግሮችህ እንዲሁም የግል እና የንግድ ህይወትህ ግን ምን ያክል ህዝብ እንደሚጠላህ የምታውቅ አይመስለኝም፤ ለዚያም ነው መሰለኝ ደግሞ ፖለቲከኛ እሆናለሁ እያልክ የምትቀባጥረው። ቆይ ግን ኢህአዴግን የሚቃወም ፖለቲከኛ ነው መሆን የምትፈልገው ወይስ የኢህአዴግ ካድሬ? ነው ወይስ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ደጋፊ ነጋዴወች ማህበር ማለቴ አንተን ጨምሮ እነ አብነት ገ/መስቀል ያሉበት አጎብዳጅ የዘራፊ ነጋዴዎች ስብስብ እጩ አድርጎህ ይሆን?
ምናልባት የአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የቢዝነስ ሰራውን ስለተቆጣጠሩት እና የቢዝነስ ውድድሩን በያዙት ስልጣን ተጠቅመው በቀላሉ እያሸነፉህ ተቸግረህ ይሆን ወደ ፖለቲካው ለመምጣት ያሰብከው? ምናልባት ሳትሮጥ እና ከላይ ከታች ሳትል በቀላሉ እንደ ሴቷ ጠቅላይ ሚኒስተራችን ቢሊየነር ለመሆን አቅደህ ይሆን ፖለቲካ ያማረህ? ብቻ ዕቅድክን አንተው ታውቀዋለህ ነገርግን አትሌት ኃይሌ እኛ እኮ ነጋዴ እና ስግብግብ ፖለቲከኛ አላጣንም ይሄው 23 ዓመት ይዘውን የለ እንዴ፤ ዝም ብለህ የለመድከው ንግድህ አይሻልህም ወይ ለነገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ሳይሆን ማጭበርበር እና ዝርፊያ ነው ያለው።
ለማኛውም ወግና መንገድ አይከለከልም ይባል የለ ፖለቲከኛ የመሆን ፍላጎት አለኝ ብለህ የማውራት መብት አለህ ነገርግን ህዝብ የሚወድህና ለአገር የምትጠቅም ፖለቲከኛ ለመሆን በቅድሚያ ኢትዮጵያዊ የማያስመስሉህ ስነምግባሮችህን ቀይራቸው፣ በመቀጠል አስፈላጊውን እውቀት ከታሪክ ጀምሮ በመመርመር ተረዳ። ከዚያም ለዝርፊያ ብለህ ከተጠጋህበት ከኢህአዴግ ጉያ ወጥተህ ህዝብን ወግነህ ለህዝብ በመቆም የሚደርስብህን ችግር ልክ እንደነ አንዱአለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ ስትጋፈጥና ለኢህአዴግ በማጎብደድ ያበላሸሀውን ስብዕናህን ስትፍቅ እኛም አትሌት ኃይሌ የትራኩ ንጉስ ሆይ ምንሊክ ቤተመንግስት ውስጥም ንገስ እንላለን።

Monday, July 22, 2013

ይድረስ ለክቡር ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም


በዘውገ ፋንታ
Seattle, U.S.A
በዚህ ሐምሌ ወር (2005 ዓ/ም) የጻፉትን እንደተለመደው በጉጉት ማንበብ ጀምሬ በመንሰፍሰፍ ጨርሻለሁ። መልዕክቶችዎ ብዙ ዘመን የሸፈናቸውን ትዝታዎች እንዳስታውስና ብዙ ትውስቶችን እንዳሰላስል አድርጎኛል። ብዙ ሆድ የሚያባቡ ሃሳቦች ነበሩ። የአብዘኽኘው ሰው ስሜት እንዴት እንደሆነ ባላውቅም፣ ሁላችንም ያለንበት ጀልባ አንድ፣ ያለንበት ባሕር አንድ፣ ጉዞአችንና አቅጣቻችን እንዲሁ አንድ ነው ብየ ስለማምን ያንዱ ስሜት የጋራ ነው ብዬ ገምቻለሁ። ሆኖም በዚያ የተነሳ ይህን ጽሑፍ ስጽፍ የግል ስሜቴ እንዳይለውጠው ጥንቃቄ አድርጌአለሁ። የቀረ እንክርዳድ ሃሳብ ምንጊዜም ስለማይጠፋ፣ ስለሱ አስቀድሜ አንባቢን ይቅርታ እጠይቃለሁ። በ”መንሰፍሰፍ” ያልኩት ቃል ለየት ያለ ይመስል ይሆናል። ክቡርነትዎ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች የሚያስፈሩ፣ የሚያባቡና የሚያርበተብቱ ይሁኑ አይሁኑ ለይቸ ለማወቅ ተስኖኛል። ፍራቻና መባባቱም ቅጥ አጥቷል። ሆኖም ግን፣ አሜርካ ውስጥ ስለምኖር በዕርግጥ ፍራቻ አላውቅም። ስለ ሀገራችን መውደቅና መጥፋት ሳስብ የምለውና የማስበው ዝብርቅርቅ ያለ ይሆናል። ለሞት ስንቅ ቢኖረው የኔንና የሌላውን ከምሬ ነበር።
የክቡርነትዎ ጽሑፍ ብዙ አሮጌ ዐመቶች የሽፈኗቸውን የጥንት አጋጣሚዎች አስታውሶኛል። ከታወሱኝ መካከል  አንዱ ጎልቶ የታወሰኝ ይህ ነበር። በእንግሊዝ ሀገር ስኖር፣ በለንደን ከተማ ወጣ ባለች ቤተመንግሥት የልዑል መሥፍን አለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም የተቀመጠበትን ቦታ እንድጎበኝ አንድ እንግሊዛዊ ሰው ወሰደኝ። በዚያን ጊዜ የተሰማኝን ደስታ በትክክል ለመግለጽ ቃል ያጥረኛል። ከዚያ በፊት አባቱ አፄ ቴዎድሮስ የቆሙባትን ቦታ መቅደላን አይቸ ነበር። ንጉሡ በተንጓለሉበት ቦታ ላይ ቁሜ በታሪክ ያነበብኩትን እያስታወስኩ ሳስብ የተሰማኝ ስሜትና የልጃቸው አፅም ባረፈበት ቦታ ላይ ቆሜ  ሳሰላስል የተሰማኝ ስሜት እጅግ የተለያየ ነበር። የልዑል መሥፍን አለማየሁ ፎትግራፍ በእንግሊዝ ነገሥታት ፎቶግራፎች መካከል ተቀምጦ ሳይ የተሰማኝ ኩራት ወደር የሌለው ነበር። ፎቶግራፉን አይቸ የማልጠግበው እንደሆነብኝ ትዝ ይለኛል። ደስታየን እንድካፈል እንደኔ የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ባጠገቤ ባለመኖሩ አወራጭቶኝ ነበር። ልዑል መሥፍን አለማየሁ አድጎ ምን እንደሚመስል ማወቄ እራሱ ጉድ ታሪክ ሆነብኝ። ግን ብዙ ሳልቆይ እበሳጭ ጀመርኩ። ስለ እሱ የተጻፉትን ታሪኮች እየተጠያየኩ መሰብሰብ ጀመርኩ። የታላቁ ንጉሥ ልጅ አፅም በባዕድ ሀገር መኖሩ ጥያቄ አሳደረብኝ። እስከመቸስ በባዕድ ሀገር ተቀብሮ ይኖራል እያልኩ ለረጅም ጊዜ ሳሰላስል ቆይቻለሁ። የልዑል መሥፍን አለማየሁን ብዙ ውጣ ውረድ፣ መንገላታት፣ ብቸኝነትና በመጨረሻም አሟሟቱን አንብቦ የማያለቅስ፣ የማይጸጸትና የማይበሳጭ ኢትዮጵያ ይኖራል ብዬ አላምንም። እንዲህ ማለቴ ከአርባ ዓመት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ሰው ልቦና አንጻር ነው።  ልዑል መሥፍን አለማየሁ ብዙ ነገሮችን ናፍቆና አምሮት እንደሞተ ግልጽ ነበር። ስለ እሱ የተጻፉት ታሪኮች አንድንዶቹ የዕውነቱ-ደበና ቢሆኑም አለመታደሉን ያስረዳሉ። የሀገሩ እሸት፣ ቋንጣ፣ ቆሎ፣ ዳቦ፣ ፍትፍቱ፣ ቅራሪና ብርዙ፣ የለመደው ምግብና መጠጥ ሁሉ ናፍቆት መሞቱ አያጠራጥርም። ከዚያም በላይ መጫወቻ ግቢው፣ ሜዳው፣ አየሩ፣ እንስሳው፣ መንደሩን እና ያገሩን ሰው እየናፈቀ እንደሞተ ወይም ናፍቆት እንደገደለው ለመረዳት አይከብድም። በልዑል መሥፍን አለማየሁ ቴዎድሮስ ከደረሰው ግፍ፣ በኢትዮጵያኖች ላይ አሁን ባለንበት ወቅት ባገራቸውና በባዕድ አገሮችም እየተካሄደ እንደሆነ እያንዳንዳችን ምስክር ነን።
ሌላው ትዝታ ብዙ ነገሮችን ያፈራርቃል። ክቡርነትዎ ደሴ መጥተው የሁለተኛ ደረጃ ማለፊያ ፈተና ሲያካሂዱ አንዱ ተፈታኝ ነበርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርስዎን አውቄአለሁ። ከዚያም ካርታ ድርጅት ሰሰራ፣ ወዳጆችዎ፣ ክቡር አምባሳደር ኃይሉ ወልደማርያምና ክቡር አቶ ታየ ረታ፣ “መስፍን ካርታዎች ይፈልጋልና ሂድህ የሚፈልገውን ጠይቅና ሰርተህ ስጠው” እየተባልኩ፣ ከእርስዎ ቢሮ እየመጣሁ ብዙ የተለያዩ ካርታዎች በተለያዩ ጊዜ እያዘጋጀሁ ሰጥቸዎታለሁ። ቢሮዎንም አስታውሳለሁ። እንደተባለው በር ይኑርና አይኑረው የማይታወቅና ዝው ተብሎ የሚገባበት ነበር። እርስዎን በውስጧ ላላየ ሰው፣ የዕርስዎን ቢሮ (አዕምሮ እንደሚገምተው አይነት) ሲፈልግ ውሎ ይመሻል እንጂ አያገኛትም ነበር። የት ነው ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ግን መልሱ “ምን ሁነሀል? ወደዚያ ሂድ፣ ታገኘዋለህ!” የሚል ነበር። መጽሐፉና የተጠቀለለው ወረቀት መደርደሪያውዎቹን ሞልቶ በዕግርዎ ስር ተከምሮ ነበር። ይኽ በጥንት ጊዜ ከአርባ ዓመት በፊት የነበረውን የሚገልጽ እንጂ ከዚያ በኋላ ትንሽ ቤተመንግሥት የሆነውን የሚያመለክት አይደለም።  የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ከተማ በብዙ ቀለም የተሰራ ካርታ አሳትሜ ስለነበር ለእርስዎና ከእርስዎ ቢሮ ብዙ ጊዜ ቆመው ለማያቸው ፕሮፌሰር (ስማቸውን ዘነጋሁ) ስሰጣችሁ፣ ሁለታችሁም አድንቃችሁ በጣም ጥሩ በርታ ብላችሁኝ ነበር። ከዚያ በኋል አላየሆትም፤ ተቻኩየ አገር ጥየ ወጣሁ።
ቀጥየ፣ እርስዎ የሚጽፉትን፣ የሚናገሩትንና ስለእርስዎ የሚነገረውን የኢትዮጵያ ታሪክ አካል የሆነውን በታላቅ ስሜት እከታተል እንደነበር ለማመልከት እፈልጋለሁ። በዚያን ወቅት በተማሪዎችና በሰራተኞች ደምቀውና ጎልተው ከሚዘወተሩት ቡና ቤቶች አካባቢ የሚነፍሱ ብዙ ፌዞች ነበሩ። አንድ ድርጊት ሲፈጠር፣ በሚቀጥሉት ቀኖችና ወሮች ጉዳዩ መሰረቱን ስቶና ተለውጦ በአስቂኝ ፌዝ ተደለባብሶ ይነገራል። አሁን ሳስበው፣ አዲስ አበባ የዓለም ፌዝ  መናገሻ መባል ይገባት ነበር እላለሁ። ለፌዘኞች የሹም-ሽረት ወቅት ትልቅ ዓመትበዐላቸው ነበር። በአንድ ሹም-ሽረት ወቅት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለምን ፕ/ር መስፍንን የአንዱ ምንስትሪ ምንስትር አልሆኑም እያለ ይጠይቅና ያወሳ ነበር። በ’ሹም-ሽረት” ዋዜማ ሕዝብ የሚሾመውንና የሚሻረውን አስቀድሞ(የራሱን ምርጫ ይሆናል)ማናፈስ ይጀምራል። ብዙው ትችት የፖለቲካ ‘አሳስኔሽን’(ግድያ) ቢባል ተገቢ ነበር። በማግስቱ ደግሞ“ተሻረ” ወይም “ተሾመ” የተባለው ሳይሆን “ተረሳ” ወይም “ተረሱ” የተባሉት ሰዎች ስም ነበር የሚወሳው። በዚያ ጉዳይ ቆሽታቸው የተነካ ወይም የቆሰለውን የሚያውቁ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በዲ.ሲ ከተማ በህይዎት እንዳሉ እገምታለሁ። ኢትዮጵያኖች ንጉሡ ለምን ፕ/ር መስፍንን የትምሕርት ምንስትር ወይም ሌላ ከፍተኛ ስልጣን አልሰጧቸውም እያሉ የሚጠይቁ ብዙ ቅን ሰዎች ነበሩ። ለዚያ ጥያቄ መልስ የሚነገረው ብዙ ነበር። አንድ መጥቀስ የምሻው አለኝ። እሱም ስለ አማርኛ ቋንቋ ጥልቀትና የአዲስ አበባን ሰው እንደ አቅሙ አቻችሎ ያኖረ የምንግሥቱ ሕጎች ሳይሆኑ የአማርኛ ቋንቋ ነብር ብዬ አምናለሁ። አሁኑ ተበልዞ ጣዕሙን ያጣውን ደረቅ ዐይነት አይደለም። ስገምተው አሁን ሕዝብ መግባቢያ ቃሎቹ “እምቢ! አላውቅም!እንጃ! እንደፈለግህ!” ይመስሉኛል። በዚያን ጊዜ የሚነገረው አማርኛ፣ ሕዝብ እንዲሳሳቅ፣ አንዱ ሌላውን እንዲያስገርም፣ ሰለልተኛው እንዲነቃና እንዲያሰላስል የሚያደርግ ነበር ብየ ብናገር፣ በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድ ምስክሬ ይሆናል ብዬ  እተማመናለሁ። ክቡርነትዎ ለምን እንዳልተሾሙ ይወራ የነበረው ምክንያት ከጥሩ አፍ እንደሰማሁት፣ እርስዎን ለማሾም ንጉሡ ፈቃዳቸው እንዲሆን ሲጠየቁ፣ ንጉሡ “እኛ እሱን አንሾምም!” በማለት እምቢ ስላሉ ነው ተብሏል። “ባይሆን የትምህርት ምንስትር  እንዲሆኑ ግርማዊነትዎ ይፍቀዱ” ብለው ሲማለዱ፣ ንጉሡ “ለሱ ሹመት ወይስ ሽረት? የቱን አስባችሁ ነው?” የሚል መልስ ሰጧቸው ይባላል። በምንሊክ ቤ/መ  አካባቢ በይበልጥ በአንዳንድ ቦታዎች የሚነገር እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህን የሚያውቁ ወይም የሰሙ “አዎ፣ ተብሏል” የሚሉ ከዚህ በዲ.ሲ በአዲስ አበባም እንደ አሉ አምናለሁ፤ እግዜአብሔር ያቆያቸውና ይመሰክራሉ። የንጉሡ ንግግር አስተርጓሚ ወይም ማብራሪያ በተለይ ለቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚያስፈልጋቸው ይነገር ነበር። ንጉሡ “እኛ እሱን አንሾምም!” ያሉበትን ምክንያት አዋቂዎች ሲያብራሩት፣ የርስዎ ቢሮ ያልተደነገገችና መስፈርት ያልተደረገላት ስልጣን ናት ማለታቸው ነበር ተብሏል። ቀጥለውም ነጉሡ “ሹመት ወይስ ሽረት?” በማለት የጠየቁት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ የነበርዎትን ሰፊ ስልጣን አሰመልክቶ ነው ተብሏል። የተባለውን ቃል በቃል ለማንጸባረቅ ጥሬአለሁ። በሌላ መስካሪዎች ቃሎቹ ተሻሽለው ቢቀርቡ አሚን ብየ እቀበላለሁ።
መጀመሪያ አዲስ አበባ ስመጣ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ፣ ብዙ ያስደንቁኝን ሁሉ ከዚህ ባላሰፍርም፣ ትቂት አስገራሚ ሆነው የታዩኝን ለመግለጽ፣ የአቡነ ጴጥሮስና የምንሊክ ኃውልቶች ዋናዎቹ ነበሩ። ቀኑን ሙሉ ከሀውልቱ ግርጌ ቁጭ ብየ እያንጋጠጥኩ እያየሁ ብውል የምጠግበው አልነበረም። የአዲስ አበባ የሰፈር ስም ብዛት እያስገረመኝ እንደ ኢትዮጵያ ‘ጂዖግራፊ’ ማጥናት ጀምሬ ነበር። የአዲስ አበባን ካርታ ስሰራ ያጠናኋቸው ስሞች ረድተውኛል ብል ትክክል ነው። ኋውልቶቹ፣ የመንገዶቹ፣ የአደባባዩና የሰፈሮቹ ስሞች በኢትዮጵያ ታላላቅ ጀግኖችና ንጉሦች ስመ የተሰየሙ ስለሆኑ፣ አዲስ አበባ የታሪክ ገጾች ሆኖ ትታየኝ ነበር። ወደር የማይገኝላቸው የነዚያ ታላላቅ ጀግኖችና ሰማዕታት ስምና ታሪክ አብሮን የሚኖር በየቀኑ የሚታወሱ አድርጓቸዋል ቢባል ከዕውነት የራቀ አይሆንም። የሁሉም ጀግኖች ኃውልቶች በየሰፈሩና አደባባዮች ቁመው ቢታዩ የአዲስ አበባ ገጽ እንዴት በይበልጥ ባማረ! የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነቱን መልሶ ሲቀዳጅና መንበረ መንግሥቱን በእጁ ሲይዝ ለጀግኖቹ ውለታ ብቻ ሳይሆን፣ ለራሱ ክብር ሲል ማስታወሻ ኃውልታቸውን እንደሚያዎም አልጠራጠርም።
በኢትዮጵያኖች ላይ የደረሰው ግፍ፣ በማናቸውም ሕዝብ በቀላሉ ሊፈጸም የማይችል ነው። የዓለም ሕዝብ ሊቀበለው የማይችል፣ ለዚያም በላይ ለሰብዐዊ መብት ሲል ተገዶ የሚወስደው ዕርምጃ ነበር። አለመሆኑ፣ “ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ” የሚባለውን እስስር ሁኔታ በግልጽ አሳይቶናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያውቀው ረቂቅ ሴራ ወራሪን የሚቋቋምለትንና ከተገዥነት የሚያድነውን አካል እንዲያጣ ተደረገ። የሀገርና የሕዝብ ሰንሰለቶች በረቀቀ የሴራ ስልት ተበጣጠሱ። ከታች እስክላይ የነበረው የአስተዳደር ድርብርብ በዘዴ ተናደ። የተረፈው ዳግም እንዳይነሳ በተቀደደለት በር ወደ ውጭ ጎርፎ እንዲወጣ ተደረገ። ለማዳን ከተባለ ይሁን። እስራኤልም የተፎከረበትን የአማራ ሰው ለማዳን ጎትታ አውጥታለች። ኢትዮጵያ ወገኗን በህይዎት ልትጠበቅ ስላልቻለች፣ የቀረው ለመኖር ሲል በዓለም ዙሪያ ተሰደደ። ያረገጠው ምድር የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመኑ እስራኤሎች (አይሁዶች) ሆነዋል። ምክንያቱና መነሻው አንድና ተመሳሳይ ነው። የተሰደዱት ኢትዮጵያኖች ባረፉበት ምድር ሁሉ ሌላ ፈተና እንደሚገጥማቸው ግልጽ ነበር። ገዳይን ቢሸሹ ከሌላ መከራ አራቁም። ብዙዎቹ ለአስከፊ ግፍ ተዳርገዋል። በውጭ የሚኖርቱ ከናት ሀገራቸው ጋር ያለውን  የባህል፣ የቋንቋና የኃይማኖት እስስር እንዳይቋረጥ በያሉበት በአላቸው አቅም እየሞክሩ ነው። ግን፣ በሄዱበት ተከትሎ የሚሄድ ጣጣ አለ፣ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያን የሚገዛው ጨቋኝ ኃይል፣ ስደተኞችን እየተከታተለ ባሉበት ሀገር ኑሮአቸው እንዲናጋ ለማድረግ የሚፈጽመው ሴራ ሊላ እጅግ አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል። ብዙ የተንገላታ ሰው በቆየ ህመም በድንገተኛ ሞት እየተቀጨ የሚያልቀው ቁጥር ብዙ ነው። አንድ ሰው የዕድሜውን መጨረሻ ሲረዳ፣ አገሩ እንዲቀበር ምኞቱን ይገልጻል። ወይም ወዳጆችና ጎደኞች አስበው ሬሳው በውድ ሀገሩ እንዲያርፍ ያደርጋሉ። ሆኖም በአረፈበት ሀገር መቅበር እየተለመደ ነው። ኢትዮጵያኖች ሲሰደዱ በወንዝና በባህር ውስጥ ሰምጠው፣ በበርሃ ሲጓዙ ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታመውና በአውሬ ተበልተው ያለቁ መቃብር ቀርቶ ያልተለቀሰላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። የጠፉት ሰወች አባቶች/እናቶችና አያቶች በቆረቆሯቸው ከተሞች ውስጥ እንዳይኖሩ ሲባረሩ፣  የአረመኔዎቹ መሪ ይህ በማይባል ልቅሶና ዳንኪራ ተቀብሯል። የት? ከአያቶቻቸው ጎን! እንደውም በዚችው መናገሻ ከተማ ኃውልቱ እንዲቆም ታስቧል!
ክቡር ፕ/ር መስፍን፣ ሸሽተናል፣ ሀገር ጥለን ሄደናል። ሆኖም በህይዎት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለመኖር የማይመኝ ሰው ካለ ጣት ይቁጠረው። በውጭ የሚኖር ሰው ሬሳው በሀግሩ እንዲያርፍ መጠየቁ ይህን ምኞቱን ያመለክታል። ሕዝብ ታሪክ የሆነውን ምግባርና ድርጊት አመዛዝኖ ያውቃል። አንድ ሰው የራሱን ኑሮና ህይወት ሰውቶ ለወገኑና ለሀገሩ ጥቅም ታላቅ ምግባር ሲፈጽም፣ ሕዝብ በበኩሉ ለታሪክና ለትውልድ ጥቅም ሲል የጀግኖችን ስምና ታሪክ ወርሶ የሀገሪቱ ቅርስ ያደርጋል።

ግዙፉ የጀሞ ኮንዶሚኒየም ዘምሟል

የ10/90፤ 20/80 እና 40/60 ችብቸባው ቀጥሏል
jemo


አጠገብ ያሉ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ እንዲለቁ ተነገራቸው
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ለማድረግ ስምምነት ሊያደርግ ነው
በግዙፉ የጀሞ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች መንደር ውስጥ በአንድ በኩል በመስመጥ ላይ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ግራና ቀኝ የሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከሕንፃው እንዲለቁ ተነገራቸው፡፡
በሁለቱ ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ከሕንፃዎቹ እንዲለቁ የተጠየቁት በክፍለ ከተማው የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት አማካይነት መሆኑን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የውሳኔው መነሻ ወደ አንድ ጐን በማዘንበል ላይ የሚገኘው ሕንፃ አጠገብ ያሉት ሁለት ሕንፃዎች ተመሳሳይ ችግር አለባቸው በሚል ቢሆንም፣ በሕንፃዎቹ ላይ በዓይን የሚታይ ችግር መኖሩን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ሕንፃዎች ተመሳሳይ መሰነጣጠቅ በውስጥ አካላቸው ቢኖርም፣ መሰነጣጠቁ መቼ እንደተፈጠረ በእርግጠኝነት መናገር የሕንፃዎቹ ነዋሪዎች አይችሉም፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሣ ወንድሙ ተጠይቀው፣ ስለተጠቀሱት ሕንፃ ነዋሪዎች የሰሙት ነገር እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ነዋሪዎቹ በክፍለ ከተማው እንዲለቁና ተለዋጭ መኖሪያ ቤት እንዲወስዱ እንደተነገራቸው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ችግር በታየበት ሕንፃ ላይ ይኖሩ የነበሩ ሁሉም ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት  ተለዋጭ ቤት እንደተሰጣቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በሕንፃው ላይ የተፈጠረው ችግር እንዲጠና በዚህ ሳምንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል እንደሚፈረም ያስረዱት አቶ ካሣ፣ ጥናቱ የጂኦ ቴክኒካል፣ የኮንትራክሽንና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን እንደሚያካትት አረጋግጠዋል፡፡
ጥናቱ ችግር ባለበት አንድ ሕንፃ ላይ ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በጠቅላላ የጋራ መንደሩ ላይ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡ (ሪፖርተር)

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት እና የአንድነት መሪዎች እንደ ጋንዲ!


ግርማ ሞገስ (girmamoges1@gmail.com)
ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነጻነት የሚለው ስትራተጂካዊ ዘመቻ ግቡ ምን እንደሆነ እና እድሜው ሶስት ወሮች እንደሚሆን አንድነት ፓርቲ ግልጽ አድርጓል። ከመግለጫው እንደተረዳሁት አንድነት ፓርቲ ጊዜ ወስዶ ብዙ አውጥቶ እና አውርዶ ያሰላው ለነፃነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ ዘመቻ ነው። አንድ ነገር ግልጽ መሆን የጀመረ ይመስለኛል። ከንዋዮች መንግስት ፍንቀላ ጀምሮ ኢትዮጵያችን ለ50 አመቶች ያህል ብዙ ህይወት እየከፈለች በፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ትግል ጎዳና ስትወድቅ እና ስትነሳ ከርማ ዛሬ ትክክለኛውን ወደ ዴሞክራሲMillions of voices for freedom - UDJ የሚያደርሳትን ጎዳና ያገኘችው መሰለኝ። ወደፊትም መውደቅ መነሳት ሊኖር ይችላል። መንገዱም አልጋ ባልጋ አይሆንም። ይሁን እንጂ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ ኢትዮጵያ ትክክለኛውን ጎዳና ማግኘቷን አብስሯል። የዚህ ዘመቻ ስሌት የፖለቲካ ትግል ባህላችንን እድገት ያመለክታል። የስልጣኔም ምልክት ነው። የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ በርቀት ብርሃን አሳይቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ ክፍሎች ያሉት ጽሑፍ በማቅረብ የተሰማኝን ለአንባቢ አጋራለሁ። ክፍል ሁለት በሽብር ህግ እና በሽብርተኛነት በታሰሩት የሰላማዊ ትግል ሐዋርያት ዙሪያ ያተኩራል። ክፍል ሶስት ደግሞ ዛሬ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት ዘመቻ እና ወደፊት የሚካሄዱ ተመሳሳይ ዘመቻዎችን ከብክለት እና ከውድቀት ለመጠበቅ ይረዳሉ የምላቸውን ምክሮች አንድ ሁለት እያልኩ ለአንባቢ አቀርባለሁ። ክፍል አንድ ግን የፖለቲካ ትግል ባህል ሽግግር በማድረግ ላይ መሆናችንን እንደሚከተለው ያቀርባል።
የትናንቱ እንደሚከተለው ነበር። የገደልን እኛ (The People)። የሞትን እኛ (The People)። የትግሉ እና የድሉ ባለቤት ግን እርስ በርስ ካጫራሱን ቡድኖች ውስጥ በጦርነቱ የቀናው ቡድን ሲሆን የመሰረተው መንግስት ደግሞ የጋራ አገራችንን የግል የጓሮ እርሻው ያደረገ እና ከቀድሞው የከፋ ሽብርተኛ አምባገነን ነው የሚል ነበር የትናንት የፖለቲካ ትግላችን ታሪክ። የትናንቱ የፖለቲካ ለውጥ ትግል ጎዳና በጦርነት የተሞላ ነበር። ብዙ ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል። መንገዶች ወድመዋል። የጦር ካምፖች እና የጦር መኪናዎች ጋይተዋል። ያ ሁሉ የኛ ንብረት ነበር። በህዝባችንም መካከል መቃቃር እና ክፍፍል እያደገ እንዲሄድ በማድረጉ የተወሰኑት ጥለውን እንዲሄዱ እና ከቀረነው ውስጥም ወደ ውጭ የሚመለከቱ እንዲፈጠሩ አድርጎ አንድነታችንን ክፉኛ አዳክሟል የትናንቱ የፖለቲካ መንገዳችን። አዲሱን አምባገነን መንግስት አብዣኛው የአገሪቱ ዜጎች ህጋዊ አድርገው ስለማይቆጥሩት እሱ ስልጣን የጨበጠበትን የመጨራረስ አዙሪት ጉዞ እንድንደግም የሚሰብኩን አዳዲስ ቡድኖች ተፈጥረዋል። የፖለቲካ ትግል ባህላችንም ቢሆን በመገዳደል ደም የተጨማለቀ በመሆኑ የመንግስት ስልጣን የጨበጡት ግለሰቦች ስብዕናቸው የተሟጠጠ ነው። ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ደግሞ በስልጣን ላይ የሚገኙት መሪዎች ፖለቲካ ባህል ከደም መጽዳት እና ስብዕናቸው የተሟላ መሆን ወሳኝ ነው። ባጭሩ ከሶስት ሺ አመቶች በላይ አብሮን የቆየው የፖለቲካ ትግል ባህላችን ከዴሞክራሲ ጋር ጸበኛ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ ግን ህዝባችን የትናንቱን ደም አፋሳሽ የፖለቲካ ትግል ባህል አዙሪት ሰብሮ በመውጣት አዲስ የፖለቲካ ትግል ባህል ጀምሯል። ይኽ አዲስ ክስተት በትልቁ እውቅና እና ድጋፍ ሊለገሰው የሚገባ የፖለቲካ ትግል ባህል እድገት ምልክት ነው። ስልጣኔም ነው። የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከአንድ አመት በላይ በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ያካሄዳቸው እና ዛሬም የሚያካሂዳቸው በድስፕሊን የታነጹ እንከን የለሽ ሰላማዊ የመብት ትግሎች የፖለቲካ ትግል ባህላችን ማደጉን ያመለክታሉ። መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ ጫና ለማድረግ ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን በአዲስ አበባ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ አጀማመር እና አፈጻጸም የፖለቲካ ትግል ባህላችን ሰላማዊነትን እንደመረጠ ይጠቁማል። በተለይ ‘የሚሊዮኖች ድምጽች ለነፃነት‘ በሚል ቀዳሚ መርህ አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያን ሽብር ህግ እዲሰረዝ እና የህጉ ሰለባ የሆኑት የሰላማዊ ትግል ባህል ሐዋሪያት እንዲፈቱ በመንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ሐምሌ 7 ቀን በጎንደር እና በደሴ ከተሞች ያካሄዳቸው ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የፖለቲካ ትግል ባህላችን መብሰሉን እና መሰልጠኑን ያመለክታል።
በተጨማሪ ሐሙስ ሐምሌ 12 ደግሞ አንድነት ፓርቲ ከሐምሌ 21 እስከ መስከረም 5 ቀን 2006 ዓመተ ምህረት የሚዘልቁ አዲስ የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ ስምሪቶች ይፋ አድርጓል። እነሱም፥ በወላይታ ሶዶ፣ በመቀሌ፣ በድሬ ደዋ፣ በአዋሳ፣ በአምቦ፣ በደብረ ማርቆስ እና በአዲስ አበባ ያቀዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች እና በባህር ዳር፣ በጅንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአዳማ፣ በባሌ፣ በወሊሶ፣ በፍቼ፣ በአምቦ፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ እና በአዲስ አበባ ያቀዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች ናቸው። እያንዳንዱ ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን እራሳችንን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሰራዊት አባል አድርገን የምንቆጥር በሙሉ የተቻለንን ያህል ተሳትፎ ማድረግ አለብን።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የአደባባይ ተቃውሞ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በተካሄዱት ሰላማዊ ትግሎች እርስ በርስ አልተላለቅንም እኛ (The People)። ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ፋብሪካ አልፈረሰም። ስራ አልተቋረጠም። የአንድነት ፓርቲ መሪዎች ሳይቀሩ በአደባባይ ከህዝብ ጎን ቆመው ሲታገሉ፣ ከህዝብ ጋር ሲታሰሩ እና ሲፈቱ አስተውለናል። አንድነት ፓርቲ አንድ የፓርላማ አባል (ግርማ ሰይፉ) ብቻ ቢኖረውም ካለምንም ስስት እሱንም በደሴው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አሰማርቶት ነበር። እንግዲህ በአለማችን ታዋቂዎቹ የሰላም ትግል መሪዎች እነ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ሌሎችም ሌላ ምን አደረጉ? ያደረጉት ይኽንኑ ነበር። ከህዝባቸው ጋር እየታሰሩ እና እየተፍቱ መታገል። የሰላማዊ ትግል መሪዎች ከትግሉ ሂደት ውጭ አይሆኑም። ግባቸው እራሳቸውን መረማመጃ አድርገው ህዝቡን የአገሩ እና የስልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ይኽ የሰላማዊ ትግል ባህል ህዝብን ከማቀራረብ አልፎ የትግል እና የድል ፍሬ ባለቤት ያደርገዋል። ህዝብ መሪዎቹን በቀርብ እንዲያውቃቸው ያደርጋል። እንደ ትጥቅ ትግል የእውቀታቸው እና የአዕምሮዋቸው ጤንነት ደረጃ የማይታወቁ ካለ ህዝብ ተሳትፎ ብድግ ብለው አገር የሚያፈርሱ እንደ መለስ ዜናዊ አይነት መሃይም እና ንክ (እብድ) የትጥቅ ትግል መሪዎች ገዢዎቹ አይሆኑም። አዎ! መሐይም። አዎ! ጥራዝ ነጠቅ ነበር። የአልቤንያ እና የሲቪየት ህብረት አምባገነኖች የጻፉትን የፖለቲካ መመሪያ ቃል በቃል ገልብጦ ኢትዮጵያ ላይ በመድፋት የኢትዮጵያ ህዝብ በሽብር አስፈራርቶ አመራሩን እንዲቀበል ማድረግ አዋቂ መሪ አያደርግም። በአውሮፓ ከተሞች ስለ አየር ጸባይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ መናገርም ብቻውን አዋቂ መሪ አያደርግህም። ተሳዳቢነት እና አጭበርባሪነትም አዋቂ አያደርግህም። የአዋቂ መሪ መስፈርቱ ሌላ ነው። የራስን አገር ህዝብ ታሪክ ሳትንቅ በጥልቀት አጥንተህ እና አውቀህ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ የአመራር አሳብ አመንጭተህ፣ ከተቃዋሚዎችህ ጋር አብረህ መስራት ችለህ፣ ቀደም ባለው ታሪካችን የተፈጸሙ ስህተቶችን አርመህ፣ ህዝብን አግባብተህ እና አቀራርበህ ፊቱን ወደ ዴሞክራሲ እና እድገት እንዲመልስ ማድረግ ከቻልክ ብቻ ነው ምናልባት አዋቂ መሪ የምትባለው። መለስ ዜናዊ ግን ችግራችንን አባብሶ ሄደ። የሆነው ሆኖ በጎንደር እና በደሴ እንዳስተዋልነው የአንድነት ፓርቲ መሪዎች እንደ ጋንዲ በህዝባቸው መካከል ሆነው መብት እንዲከበር ታግለዋል። ይኽ ሁኔታ ህዝባዊ ስብዕናቸው እንዲያድግ እንጂ እንዲሟጠጥ አያደርግም። የፖለቲካ ባህላቸውም ከገዳይነት ደም የጸዳ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ አይነት የትግልም ሆነ የድል ባለቤት የሚሆነው እራሱ ህዝቡ ነው። ማለትም በምርጫ የመንግስት ስልጣን ባለቤት የሚሆነው እራሱ ህዝቡ ነው። ስለዚህ ሰላማዊ ትግል እና ዲሞክራሲ የማይነጣጠል ዝምድና አላቸው።
ወሳኙ የውስጥ ትግላችን ነው። ዜናዎች እንደሚያመለክቱት የአውሮፓ ህብረት፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ በኢትዮጵያ ውስጥ መብት ለማስከበር እየተካሄደ ባለው በሳል እና እንከን አልባ ሰላማዊ ትግል ተደንቀዋል። ድጋፋቸውን ለግሰዋል። እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ትግሉ የሚያገኘው ድጋፍ እንደሚጨምር አትጠራጠሩ። እንግሊዝ እና አሜሪካም ለምነውን የሚደጉን ቀን ቅርብ ነው። ወሳኙ የውስጥ ትግላችን መጠናከር እንደሆነ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን እንዳንዘነጋ።
ስለዚኽ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የምንኖር የሰላም ትግል ሰራዊት እና የዴሞክራሲ አርበኞች ኢትዮጵያውያን በመካሄድ ላይ ያለውን አገር አቀፍ የሚሊዮኖች-ድምጽ-ለነፃነት ዘመቻ በሙሉ ልብ መደገፍ እና መሳተፍ አለብን። እያንዳንዱን ዘመቻ ለማደራጀት (ለማዘጋጀት እና ለማኪያሄድ) ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። የገንዘብ እርዳታ በማድረግ የዚህ ታላቅ የፖለቲካ ባህል ለውጥ ታሪክ አካል እንሁን! ነፃነት ገፋፊው የሽብር ህግ እንዲሰረዝ እና የህጉ ሰለባ የሆኑት የሰላማዊ ትግል ሐዋሪያት እንዲፈቱ በመንግስት ላይ ጫና ለማድረግ በተጀመረው ዘመቻ ካለ ምንም ስስት እንሳተፍ። በአሳብ ወይንም በገንዘብ! በተለይ በውጭ ያለን ዜጎች ዘመቻውን በገንዘብ በመርዳት ኢትዮጵያ በመስራት ላይ ባለቸው ታሪክ ላይ ማህተማችንን እናስቀምጥ!
በክፍል ሁለት እንገናኝ።