FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, April 8, 2015

በስዊድን የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ራሱን አስተዋወቀ

semayawi sweden
የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር በስዊድን ተመስርቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለጽ፤ የድጋፍ ማኅበሩ ቅዳሜ አፕሪል 4 ቀን 2015 ዓ.ም. (ግንቦት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.) ራሱን አስተዋውቋል። በዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ተግባርን ጥሪ ለተደረገላቸው ተሰብሳቢዎች ያስረዱት አቶ ሰለሞን ጌታነህ የድጋፍ ማኅበሩ ሰብሳቢ ናቸው።
አቶ ሰለሞን በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በተደረገው የማስተዋወቁ ሥነሥርዓት ላይ ስለሰማያዊ ፓርቲ ሲያስረዱ፤ ሰማያዊ ፓርቲ በወጣት አባላት የተመሰረተና የሚመራ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ብልጫ ያለው እንደሆነና የወጣቱም ድጋፍ ሰማያዊ ፓርቲን እንዳልተለየው አሳውቀዋል። አያይዘውም ሰማያዊ ፓርቲ የዓላማ ጽናቱ የበረታ በመሆኑና በሀገር ውስጥ የሚያደርገውም እንቅስቃሴ እጅግ የጎላ ስለሆነ ፓርቲውን ሁላችንም መደገፍ ይገባናል ብለዋል።
የፓርቲው አመራሮች
የፓርቲው አመራሮች
በስብሰባው ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን መግለጫውን ከሰሙ በኋላ ልዩ ልዩ ገንቢ ሃሳቦችን ሰጥተዋል። ተሰብሳቢዎቹ ለፓርቲው ከሰጡት ሃሳቦች ውስጥ፣ “ሰማያዊ ፓርቲ በሀገር ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ በዚህም የድጋፍ ማኅበሩ ከሌሎች የሰላማዊ ትግል ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር በመገናኘት ራሱን ማዳበር ይገባዋል” የሚለው ይገኝበታል።
ተሰብሳቢዎቹ የመጀመሪያ ጥሪ መሆኑን አስታውሰው በዕለቱ የተገኘው የህዝበ ቁጥር አነስተኛ ነው ተብሎ እንደማይገመት በመግለጽ፣ “ፓርቲው የበለጠ በሰራ ቁጥር ብዙ አባላትና ደጋፊ ማፍራት እንደምትችሉ ካለው ሁኔታ መረዳት ይችላል” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። ስብሰባውን ለመዘገብ በስፍራው የነበረው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጽዋል።
ቀጥሎም ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ሥራ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ለተሰብሳቢው ቀርቧል። በመጨረሻም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በስልክ ቀርበው ሰብሳቢዎቹንና ተሰብሳቢውን በማመስገን በሀገር ቤት ያለውን ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክተው፤ በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያቸው አባላትና በሳቸውም ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል የበረታ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ከዚህ የከፋ ችግር ሊገጥመን ቢችልም ፓርቲዬም ሆነ እኔ በጽናት ቆመን ትግሉን እንገፋለን በማለት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል። ከኢንጂነር ይልቃል አጭር የስልክ መልክት በኋላ ስብሰባው ተጠናቋል። 

(ዘጋቢ: ወለላዬ ከስዊድን)

http://www.goolgule.com/semayawi-party-support-group-introduced-in-sweden/

የት ሂዱ ነው?

"ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም"
Prof_Mesfin1
ዓለም ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን “የሙጢኝ!” ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን “የሙጢኝ!” እንላለን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞት ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባሎች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የአያቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

http://www.goolgule.com/i-live-and-die-here-in-my-own-home-land/

Wednesday, March 11, 2015

የወያኔ ጥላቻ ፍሬ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።
ወያኔ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ትግሬ ሁሉ ዕዳ አለበት ማለት እንደወያኔ ማሰብ ነው፤ ወንጀል በዘር አይተላለፍም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳል፤ ጊዜው ሲደርስ ውጤቱንም ለመቀበል ይገደዳል፤ ይህ የሚሆነው ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ኃይል በጎ መንፈስ አድሮበት፣ አእምሮው በትምህርት ተገርቶ በትክክል ማሰብ ሲችል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በአለበት ሁኔታ በጎ መንፈስ የራቀው ይመስላል፤ አእምሮም ጭራሹኑ በእኩይ መንፈስና በጥላቻ እየዛገ ነው፤ ስለዚህ ያስፈራል፤ በደቡብ ሱዳን ሁለት መቶ ሰዎች በዘር ተለይተው ታረዱ ሲባል ያስፈራል፤ በናይጂርያ፣ በኮንጎ የሚካሄደውን የዘርና የሃይማኖት እልቂት ስንሰማ ያስፈራል፤ በ1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊና አዲሱ ለገሰ እንዳስታወሱን የሩዋንዳ የጎሣ እልቂት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፤ የቅርብ ተኳሽ የሆነው የአግዓዚ ጦርም አድፍጦ መጠበቅ ያስፈራል፤ ሌላውም ይህንን አውቆ አድፍጦ መጠበቁ ያስፈራል፤ ሰማይ ጠቀስ የሠሩት፣ የሥልጣን ኃላፊነትን ችላ ብለው በሥልጣን የሚነግዱና የሚከብሩት፣ የማይኖሩበትን ሕንጻ የሚክቡት፣ ከሕዝብ ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት ኑሮ ያስፈራል፤ አቶ አስገደ ወያኔ መደንገጡን ይነግረናል፤ መደንገጥ የማይቆጣጠሩት ፍርሃት ነውና አደጋ ያመጣል፤ አደጋው አደጋን ይጠራል፤ ይህም ያስፈራል።
በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።
ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ጥላቻ ወደንዴት፣ ንዴት ወደቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደአውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።
ሌላ አገር እንዲህ አልሆነም፤ እዚያ አገር እንዲህ አልሆነም፤ የሚባል ነገር የለም፤ እኛ ዘንድ ሌላ ነው፤ የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው!
ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፤ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል፤በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቁጣም ድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳትእንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም፤ ሰው በቀኙ በኩልይነቅላል፤ ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ እያንዳንዱምየ ክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ …ኢሳይያስ 9/18-21
ትንቢተ ኢሳይያስ ለሩዋንዳውያን ብቻ አይደለም፤ ጥላቻና ክፋት በተዘራበት ቦታ ሁሉ ውጤቱ ጥፋት ነው፤ ምናሴ ኤፍሬምን በልቶ አይቀርም፤ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላዋል።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/14596/

Wednesday, February 25, 2015

ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው!

ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም

haile china



የጎረቤት ኬንያ ዳኛ ለኬንያ መንግሥት አስፈጻሚው ክፍል ልኩን ነገረው፤ ሕገ መንግሥቱን በመርፌ አስተኝተህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ሕግ ለማውጣት አትችልም፤ ስለዚህም የሰነዘርኸውን የጉልበት ሕግ አንሣ፤ አለው፤ ዳኛ አይጥፋ! ሌላ ቢቀር ከጎረቤት ዳኝነትን እንስማ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር ስንት ጋዜጠኛ፣ ስንት የሃይማኖትና ስንት የፖሊቲካ መሪዎች ከየወህኒ ቤቱ ይወጡ ነበር! ሁላችንም እንደልባችን ሳንፈራ፣ ሳንፈራራ በሙሉ ነጻነት ችግሮቻችንን የወያኔን ጭቆና ጨምሮ ለመወያየትና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የምንችልበት መድረክ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖረን ነበር፤ ስንት ሰው ሥራ ያገኝ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ በየመንገዱ ጠመንጃ የያዘ ሊያስፈራራን የሚሞክር ሆድአደር እያየን፣ እንደዚሁም በየጫካው ያሉትን እያሰብን ሰላማችንን ከምናጣ አበባውን ትተን፣ ሩዙን ትተን፣ የተወደደልንን ጤፋችንን እያመረትን አዲስ ኑሮ ብንጀምር የተሻለ ነበር፡፡
ግን አንድ እንቅፋት አለብን፤ እነዚህ ከየኪዮስኩ እውቀት ገዝተን አዋቂዎች ሆነናል የሚሉት እንትኖች መጀመሪያ ችግሩ እንዲገባቸው፣ ሁለተኛ መፍትሔው እንዲገባቸው፣ ሦስተኛ ጉልበትና እውቀት አንድ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በጉልበት እውቀት የማይገኝ መሆኑን ማሳመን በረዶ እየወረደ የስሜን ተራራን መውጣት ነው፤ በረዶ ሳይኖር ወጥቼዋለሁ!
እነዚህን የጉልበት አዋቂዎች — ስለሽማግሌዎችና አሮጊቶች ሳያስቡ፣ ስለመብራት ኃይል ሳያስቡ፣ ስለውሀ ሳያስቡ ሁሉም በጉልበት ፎቅ ይውጣ የሚሉ! ይባስ ብለው ለእስረኛውም ፎቅ እየሠሩለት ውጣ! ሊሉት ነው!
እነዚህ የጉልበት አዋቂዎች የአበሻ ኑሮ፣ ቡናው፣ ሙቀጫው፣ ምጣዱ፣ በርበሬው፣ ቁሌቱ፣ ቄጤማው፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ ኧረ ስንቱ! ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው! እናውቃለን ስለሚሉ እንዴትስ ይማራሉ? በእውነት ለመማር ቢፈልጉስ ስንት ዓመት ሊያስፈልጋቸው ነው!
እግዚአብሔር እነሱንም እኛንም በምሕረቱ ይጎብኘን! የሚያስተምር ጎረቤት አያሳጣን! (ምንጭ: ከፕ/ር መስፍን ፌስቡክ ገጽ)
http://www.goolgule.com/forgetting-what-they-have-learned-and-taught-by-the-chinese/

“መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ”

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጨለማ ቤት መታሰራቸውን አስታወቁ

dark



በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ የሚገኙት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀጠና/ዞን አመራሮች ለ16 ተከታታይ ቀናት በጨለማ ክፍል መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አስታወቁ፡፡
የካቲት 17 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ (የፓርቲው የጎንደር አደራጅ አቶ አግባው ሰጠኝ)፣ የአንድነት እና መኢአድ የዞን አመራሮች “መረጃ አውጡ፣ የደበቃችሁትን ሁሉ ተናገሩ” እያሉ እንደሚደበድቧቸውና በጨለማ ክፍል እንዳሰሯቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ አሁንም መረጃየን ሰብስቤ አልጨረስኩም በሚል ተጨማሪ 8 ቀናት ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
ተጠርጣዎቹ በማዕከላዊ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ሰቆቃ አስመልክተው ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀረበበትን አቤቱታ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጎንደርና ጎጃም አካባቢዎች የዛሬ አራት ወር ገደማ በፖሊስ ታስረው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ጠበቃቸው በተደረገባቸው ክልከላ ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን ካገኟቸው 2 ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አግባው ሰጠኝ እየተፈጸመበት ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የርሃብ አድማ ላይ መሆኑ የታወቀ ሲሆን አድማውን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት አመራሮቹ የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ነገረ ኢትዮጵያ ፌስቡክ ገጽ)
http://www.goolgule.com/opposition-party-leaders-under-severe-interrogation-and-torture/

Monday, February 9, 2015

ዋ ለረዣዢም በቆሎዎች! (ታሪኩ አባዳማ)


ታሪኩ አባዳማ
ከ1990ዎቹ የቀዝቃዛ ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ የአምባገነኖች ባህሪ እንኳ ተለውጦ እንደ አዲሱ ዘመን ሁሉ እነሱም ስልጣን ላይ የተቀመጡት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያውም በህዝብ ፈቃድ መሆኑን ለማሳየት ተግተው እየሰሩ ነው። በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ይታይ እንደነበረው አይነት ሁሉን ነገር በይፋ ጨፈላልቆ በማን አለብኝነት በብቸኛ ፓርቲ ስልጣን ላይ መቀመጥ የሌጅትመሲ ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ አስተማማኝ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ተገንዝበዋል። በመሆኑም ጨካኝ አምባገነኖች ሳይቀሩ ምርጫ ሲጠሩ ፣ መድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት መፈጠሩንም ሲሰብኩ ማየት እና መስማት እየተለመደ ነው። ለምርጫው ሂደት ፣ ለውድድሩ ድራማ ብሎም ለማይቀረው የመጨረሻ ውጤት አዋጅ የተቀነባበረ አሰራር ቀይሰዋል።Tigray People Liberation Front Split
የምዕራቡ እና ምስራቁ ዓለም ፍጥጫ በረድ ብሎ የፖለቲካው አየር የሚነፍስበት አቀጣጫ ሲቀየር ከወጀቡ ጋር ተቀላቅሎ ከማዝገም ሌላ አማራጭ አልተገኘም። ስለሆነም ከዲሞክራሲያዊ ባህሪያት አንዱ የሆነውን ምርጫ የተቀበሉ ስልጡኖች መሆናቸውን ለለጋሽ የምዕራቡ ዓለም ለማሳየት ደፋ ቀና ብለዋል። ህዝባቸው እንደሚወዳቸው ፣ እንደሚመካባቸው እንደሚመርጣቸውም ደጋግመው ያስተጋባሉ።
አሸነፍን ያሉቱ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ወንበር በተቆጣጠሩበት ፓርላማ ባንድ ጀምበር ህግ አርቅቀው ያውጃሉ ፣ ህጉን ራሳቸው ይፈፅሙታል ወይንም ይጥሱታል… ተሸነፉ የተባሉት ፀባይ አሳምረው ፣ አንገት ደፍተው ካልተቀመጡ ህገ ረቂቅ ይፃፍባቸዋል… አሸባሪ ተብለው ወህኒ ይጋዛሉ… ስለዚህ አምባገነኖች ምርጫ ለመጥራት አይፈሩም ፣ አያፍሩም… እንደሚያሸንፉም አይጠራጠሩም። ምክንያቱም ድል የሚታወጀው በብቸኛው መገናኛ በራሳቸው ራዲዮና ቲቪ ነውና!!
የኢንዶኔዢያው ሱሀርቶ ፣ የዛምቢያው ካውንዳ ፣ የኬንያው ሞይ ዓለም አቀፍ ፖለቲካው ባሳደረው ግፊት ምርጫ ጠርተው ተሸንፈው ስልጣናቸውን ለተመረጡ ዜጎች አስረክበዋል ፤ የግብፁ ሙባረክ እና የቡርኪና ፋሶው ካምፓዎሬ ምርጫ መጥራት ማለት ማሸነፍ ሆኖ ስላገኙት ያለገደብ ስልጣን ላይ ለመቀመጥ የሚያስችል ህግ ከልሶ ለማርቀቅ ሲሰናዱ ህዝብ በቃ ብሎ በቁጣ አስወግዷቸዋል ፣ የዙምባቤው ሙጋቤ የዩጋንዳው ሙሰቬኒ እና ሩዋንዳው ካጋሜ ዛሬም ምርጫ እየጠሩ ተፎካካሪያቸውን በብረት እያደቀቁ በስልጣን ላይ ናቸው – ምርጫ ሳይተጓጎል በየዓምስት አመቱ ሲጠሩ ውነትም ዲሞክረሲ የሰፈነ ይመስላል።የአይቮሪኮስቱ ሎሬት ባግቦ እና የኛዎቹ ወያኔዎች ምርጫ መጥራት ባይታክቱም ተወዳዳሪን በምርጫ ሳጥን ብቻ ሳይሆን በሬሳ ሳጥን መሸኘት ላይ የተካኑ ሆነው ተገኝተዋል።
እነኝህ ሁሉ የድህረ ቀዝቃዛ ጦርነት ዘመን ወጀብ የሚቀዝፉበትን አቅጣጫ እንዲሞርዱ ካስገደዳቸው መካከል ናቸው። ሁሉም በገዛ ህዝባቸው ላይ ሰቆቃ የፈፀሙ ፤ የዘረጉት መንግስታዊ መዋቅር በዘር እና አድልዎ ላይ የተገነባ ፤ ሙስና እስከ አንገታቸው የዋጣቸው ፣ ስልጣንን አላንዳች ተጠያቂነት በመዳፋቸው ጨምድደው ለመዝለቅ ቅንጣት የማያመነቱ ገዢዎች መሆናቸውን ህዝባቸው ፣ አለምም ይመሰክራል።
ኢንዶኔዢያ ከ200 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ፣ ከ250 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባት እና ከ300 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር ናት። ሱሀርቶ ወደ ስልጣን የመጣው በወታደራዊ ሀይል ሲሆን ለ31 ዓመታት ሰልጣን ላይ ቆይቷል – አገዛዙ በየ አምስቱ ዓመት ምርጫ የሚጠራ ሲሆን ሱሀርቶ ለሰባተኛ ጊዜ ለመመረጥ እየተሰናዳ ባለበት ሁኔታ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት በግንቦት 1998 በህዝባዊ እምቢተኝነት ከስልጣን ተወግዷል። የሱሀርቶ አገዛዝ ቃላት ሊገልፁት በማይቻል መጠን የነቀዘ ፣ አፈና አና ግድያ የተንሰራፋበት ሲሆን ከምዕራቡ ጋር በነበረው ቁርኝት በተገኘ ብድር የተገነቡ ፎቆች እና መንገዶች ምክንያት አገሪቱ በርሱ አገዛዝ ዘመን አድጋ ነበር የሚሉ አሉ። የመሬት ልማት በፖለቲካ ጥፋት!!
ሁዋላ ላይ ይፋ እንደ ሆነው የሱዋርቶ አገዛዝ ብልሹነት ተጋልጦ ስልጣኑን እንዲለቅ ሲገደድ በመጨረሻው ሰዓት “I am sorry for my mistakes” ሲል ተመፃድቋል። ስህተቱ በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት ለራሱ እና ለቤተሰቦቹ ማግበስበሱ ፣ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ተቃዋሚ ዜጎች ለሞት እና ስደት መዳረጉ ፣ እጅግ አድርጎ በሙስና የነቀዘ አስተዳደር መሆኑ ነበር።
ዛምቢያ ከቅኝ አገዛዝ እንድትላቀቅ መሪ ሚና የተጫወቱት ካውንዳ ለስልጣናቸው እጅግ አድርገው የሚሳሱ እሳቸው ከሌሉ አገሪቱ ያበቃላት የሚል ዝንባሌ ነበራቸው። የፖለቲካው አየር ሲለወጥ እና ተቀዋሚ ድርጅቶች የለውጥ ጥያቄያቸውን አንግበው ሲነሱ ምርጫ ለመጥራት ተገደዋል። እሳቸው ምርጫ ውድድር ውስጥ ሲገቡ ለነፃነት ያበቃሁት ‘ህዝብ ካለኔ ማንን ሊመርጥ ይችላል?’ የሚል እምነት አድሮባቸው ቆይቷል። ውነትም ሀያ በመቶ ድምፅ ማግኘታቸው ሲታይ አሁንም የሚወዳቸው አለ ያሰኛል። ይሔ ሀያ በመቶ ድምፅ ግን ዘር ግንድ ቆጥሮ የለገሳቸው የራሳቸው ብሔረሰብ ህዝብ ብቻ ነበር። የምርጫው ውጤት በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምስክርነት ይፋ ሲሆን እና መሸነፋቸውን ሲገነዘቡ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከቤተመንግስት ለመውጣት አላንገራገሩም። ከነጭ ቅኝ ግዛት ነፃ ያወጡት ህዝብ ድምፁን ሲነፍጋቸው ህዝቡ ውለታ ቢስ መሆኑን በምሬት ሳይጠቁሙ ግን አላለፉም። በኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ ፣ ህዝብን አምናችሁ ምርጫ የሚባል ጣጣ ውስጥ አትግቡ ብለው ቀሪ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎችን ምክር ከመለገስም አልቦዘኑም። ጉዳዩ ምርጫ ከሆነ ሌላ መላ ፈልጉለት የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
እነሆ ምርጫዎች እየተካሄዱ ነው። በዩጋንዳ ፣ በኬንያ ፣ በደቡብ ሱዳን ፣ በሩዋንዳ፣ በኢትዮጵያ … ምርጫ ይጠራል… ደም ይፈሳል… አምባገነኖቹ ተቃዋሚ ነው ብለው በጠላትነት የፈረጁትን እጃቸው ላይ ባገኙት በማናቸውም የማጥቂያ ዘዴ ተጠቅመው ያምቃሉ። እናም ስልጣን ላይ ይቆያሉ… በምርጫ!!
ዘመኑ የዲሞክራሲ ነዋ! ዲሞክራሲ ደግሞ ‘ሂደት’ ነው ይላሉ። ዛሬ ተዘርቶ ነገ አይበቅልም ይሉናል። ሀያሶስት ዓመትም መብቀል አይችልም… ሀምሌ ላይ ዘርቶ ታህሳስ ላይ እንደሚታጨድ ሰብል ጊዜ ይወስዳል ይሉናል…እንደ ማሳው እንደ አፈሩ ነው። ዲሞክሲ ጎምርቶ የሚታጨደው በስንት ዘመን እንደሆነ ግን የሚነግረን የዲሞክሲ አዝመራ ጠቢብ ሊጠሩልን አልቻሉም… ብቻ ሂደት ነው… ምርጫ ደግሞ በያምስት ዓመቱ ይጠራል… ማን ይፈራል?
በዘረኝነት ቀንበር ጠምደው የከፋፈሉትን ህዝብ በማይጎመራው የዲሞክረሲ ማሳ ላይ እየነዱት ነው። ቀንበሩን ተሸክመው ከሚወላከፉት ዜጎች መካከል የምናውቃቸው የሚያውቁን ብዙ ናቸው።
ከአስር ዓመት በፊት በ1997 ወያኔ ምርጫ ውድድር ይደረግ ብሎ የፖለቲካ ምህዳሩን በመጠኑ ሰፋ ሲያደርግ ፉክክሩን ባሸናፊነት እንደሚወጣ አልተጠራጠረም ነበር። ወያኔ በወቅቱ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መለስ ዜናዊ እንዳረጋገጠው ‘… ሳናጭበረብር ግልፅ በሆነ ምርጫ የምናሸንፍ መሆኑን ይህ ሰልፍ ያራጋግጣል’ ብሎ እንደነበር ያስታውሷል። ባለ ‘ራዕዩ መሪ’ ህዝቡንም ልቡንም ማንበብ አልቻለም። ውድድሩ ተጠናቆ ወያኔ መሸነፉ ሲረጋገጥ ታንክ እና መትረየስ ይዞ መጣ – አዲስ አበባን የጦር ቀጠና አደረጋት። የፈሰሰው ደም ፣ የጎደለው አካል እና የፈረሰው ቤት ጩኸቱ ዛሬ ድረስ ያስተጋባል።
ታዛቢ አይፈሩም ምክንያቱም ማን እንደሚታዘባቸው አስቀድመው የሚወስኑትም እነሱ ናቸው። ከወያኔ የዘርኝነት ቀንበር ነፃ የሆነው ብዙሀኑ ህዝብ ግን ሳይመርጡት በነፃ ይታዘባል ፤ ሸፍጡንም ፣ ኮረጆ ግልበጣውንም ፣ ዱላውንም ፣ ጥይቱንም ፣ ወህኒውንም አይቶ ቀምሶ በዝምታ ይመሰክራል። ማን ተወዳድሮ ማን እንዳሸነፈ ያውቃል ፣ ድምፁን ሲሰርቁበት ግን ሌቦችን ለመታደግ አቅም የለውምና በዝምታ ታዝቦ ፣ አድፍጦ ሌላ ቀን ይጠብቃል።
አምባገነን ገዢዎች በስልጣን መቆየት የሚችሉበትን ሰበብ እያሰላሰልኩ ሳለሁ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ሔሮዶቱስ በማስታወሻው ያሰፈረው ገጠመኝ ትዝ አለኝ።
ጉዳዩ እንዲህ ነበር። ፐርቲንደር የተባለው ንጉስ ኮሪንዝ በተሰኘች ምድር በለጋ ዕድሜው ወደ ዙፋን ይወጣል። ታዲያ ሰልጣኑን ጠብቆ ለማቆየት የሚችልበትን ልምድ ለመቅሰም እንዲረዳው መልዕክተኛውን በስልጣን ለረዢም ዘመናት የቆየ ዝራቡለስ ወደ ተባለ የሚልተስ አምባገነን ገዢ ዘንድ ይልከዋል።
አንጋፋው አምባገነን ዝራቡለስ መልዕክተኛውን በጠዋት ተቀብሎ የመጣበትን ጉዳይ ካጣራ በሁዋላ ፈረሱን አስጭኖ ወደ በቆሎ እርሻ ይዞት ይሄዳል። እዚያም ከማሳው መካከል እየተንጎራደደ ለመልዕክተኛው የሆነ ያልሆነውን እያወራ በያዘው ገጀራ ከሌሎቹ ተክሎች ቀድመው ረዘም ረዘም ያሉትን አንገት እየቀላ ይጥላል። ረዣዢም በቆሎ ካናቱ እየተጎመደ ሲወድቅ ማየቱ ግራ የገባው መልዕክተኛ ወደ መጣበት ተመልሶ የሆነውን ለወጣቱ ንጉስ ፐርቲንደር በዝርዝር ይነግረዋል። ወጣቱ ንጉስ የተላለፈለት መልዕክት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀበትም – ስልጣንህን ለማቆየት ከፈለክ ከሌሎች ሁሉ ቀድመው የነቁ ረዘም ያሉትን እየመረጥክ ሳይቀድሙህ በመቀንደብ ማስወገድ ነው። ይኸው ነው መልዕክቱ –
ጥንትም ዛሬም ረዣዢም ተቀናቃኞችን ሳይቀድሙህ ቅደማቸው… ‘ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው…’ የመንግስቱ ፖሊሲ እንደነበር ሁሉ የመለስ ዜናዊ ‘ጃኬታቸውን አስወልቀን አባረርናቸው…’ የተግባር መመሪያ ነበር – ወያኔ ዛሬ የሚጠቀመው በዚሁ ነው። በተቀዋሚ ሰፈር ረዘም ብሎ የወጣውን እሸት አናቱን ቀንጥሰው ለመጣል ቆርጠው ሲሰሩ ቆይተዋል። ትናንት በቅንጅት ፣ በነ ፕሮፌሰር አስራት እንዲሁም ዛሬ – በአንድነት እና በመኢአድ ላይ የተፈፀመው ይኸው ነው። በወያኔ ዘመን ድንክዬ በቆሎዎች ሲሻቸው መኖር ይፈቀድላቸዋል – የአምባገነኖች ዲሞክረሲ በነሱ አንገት ላይ አይመትርም።
ዋ ለረዣዢም በቆሎዎች!!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/14360/

Saturday, February 7, 2015

የትግራይ ሕዝብንና የኢትዮጵያ ፓሊስን በኢትዮጵያዊያን ለማስጠላት የሚደረገው ጥረት ከሽፏል!


Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracy
ህወሓት ንፁሀንን ለመደብደብ የሚያበቃ በቂ ክፋት ያለው ልዩ ጦር ሲያሰለጥን ቆይቷል። ይህን ልዩ ጦር የፓሊስን መለያ እያለበሰ ነውረኛ ሥራዎችን እንዲሠራ በማድረግ በአንድ በኩል ንፁሀንን የመጉዳት በሌላ በኩል ደግሞ ፓሊስን በሕዝብ የማስጠላት መንታ ግቦችን ለማሳካት ተጠቅሞበታል። ይህ ልዩ ጦር በአለፉት ጥቂት ሳምንታት ባዶ እጃቸው ለተቃውሞ በወጡ ነብሰ ጡር ሴቶች ላይ ሳይቀር ባሳየው ጭካኔ፣ በሰማያዊ እና በአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ባደረሰው ድብደባ መጠን እና ባካሄደው የግለሰብ ንብረቶች ዝርፊያ የሥርዓቱ ባህርይ ፈጽሞ ከሰውኛ ተፈጥሮ እየወጣ እንደሆነ አመላካች ነው። በእነዚህ ድብደባዎች ወቅት በትግራይ ተወላጆች ላይ የተለየ ትኩረት በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው ተደርጓል። በትግራይ ተወላጆች ላይ የተለየ ትኩረት የተደረገው በደብዳቢዎቹ የግል ውሳኔ ሳይሆን ከበላዮቻቸው በተሰጠ ትዕዛዝ ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።
በአርበኞች ግንቦት 7: እምነት መሠረት የፓሊስ ከፍተኛ አዛዦች ህወሓቶች ቢሆኑም አብዛኛው የሠራዊቱ አባል በህወሓት ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ የተማረረ፤ የሥርዓቱ መለወጥ የሚፈልግና ሥርዓቱን ለመለወጥ የሚደረገውን ትግል የሚደግፍ ኃይል ነው። ስለሆነም ህወሓት የተለየ ጦር አሰልጥኖ የፓሊስ ልብስ በማልበስ ነውረኛ ወንጀል በማሠራት ፓሊስን ለማስጠላት የሚያደርገው ሴራ ሊጋለጥ ይገባል ብሎ ያምናል። የፓሊስ ሠራዊት አባላትም በስማቸውና በደንብ ልብሳቸው የሚደረገውን ደባ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንዲያጋልጡ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ህወሓት እንደሚያስበው እና የኢትዮጵያም ሕዝብ እውነት አድርጎ እንዲቀበለው እንደሚፈልገው የትግራይ ሕዝብ በጅምላ የህወሓት አፍቃሪና ደጋፊ አይደለም። እንዲያውም በተፃፃሪው ህወሓት ከትግራይ ተወላጆች ልብ እየተነቀለ ነው። የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትሕዴን/ደምህት) ከትግራይ የበቀለ፤ ህወሓትን በአመጽ ለመፋለም የቆረጠ ኃይል ነው። አርበኞች ግንቦት 7 በትግራይ ውስጥ ብዙ ደጋፊዎች ያሉት መሆኑ የምናውቀው ሀቅ ነው። አረና ትግራይ ህወሓትን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የተነሳ ተሰሚነቱን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ እና አቶ አብርሀ ደስታን የመሰለ ወጣት ኢትዮጵያዊ የፓለቲካ መሪ ያወጣ ድርጅት ነው። ህወሓት አንድነት ፓርቲ ላይ የመረረ አቋም ከወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ በትግራይ ውስጥ ያለው ተቀባይነት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ነው። ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጅምላ ለማጣላት የሚያደርገው ጥረት ማክሸፍ ይኖርብናል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል፤ ለዚህም ተግቶ ይሠራል። አርበኞች ግንቦት 7 ከትግራይ የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር በመተባበር ፀረ ህወሓት ትግል በትግራይ ውስጥ መቀጣጠል ይኖርበታል ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት ትግራይ የህወሓት መቀበሪያ የመሆኗ ጊዜ ሩቅ አይደለም።
በዘንድሮው የ2007 የሴራ ምርጫ አማካይነት ተድበስብሰው የመጡ እነዚህ ሁለት ክፋቶች ማለትም ፓሊስን በሕዝብ ማስጠላት እና የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የዲሞክራሲ ወገንተኞችን ለይቶ ማጥቃት ከበስተጀርባቸው ያዘሉት እኩይ ዓላማ መጋለጡ መንገዳችን ያጠራልናል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። በአንድነትና በመኢአድ የተፈፀው የድርጅትና የንብረት ዘረፋም የዚሁ ፕሮጀክት አካል መሆኝ ግልጽ ነው፤ ነገ ተመሳሳይ ነገር በሰማያዊ ፓርቲም ላይ ይፈጽም ይሆናል።
በመሆኑ ከ2007 የሴራ ምርጫ ትሩፋቶች በትግራይ ሕዝብና በፓሊስ ሠራዊት ጀርባ የሚደረገው ደባ መጋለጡ ነው። ይህ ድል ጽኑ መሠረት እንዲይዝ ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ የመነጠል እና ፓሊስ የሕዝብ አጋር መሆኑን የማረጋገጥ ሥራዎችን አጠናክረን መሥራት እንዳለብን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
http://ecadforum.com/Amharic/archives/14351/