በወያኔ ውስጥ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው ብሎ ነበር አሉ ባለ ራዕዩ የወያኔው መሪ። ባለስልጣኖች በስልጣናቸው ቢባልጉ በወያኔ መንደር በታወቀው የግምገማ ጁዶ አማካኝነት እንዘርራቸዋለን ለማለት ይመስላል የባለራዕዩ ጎጠኛው መለስ ንግግር። የሚደንቀውና ይህን ጉዳይ አሳሳቢ የሚያደርገው ግን ልክ አሁን በወያኔ መንድር እንደሚታየው ባለጌው ከጨዋው አጅግ በዝቶ በሚታይበት ጊዜ ምን ይደረጋል የሚለው ነው። ሙሰኛው ከሀቀኛው፣ ልግመኛው ከሰራተኛው፣ አስመሳዩ ከደህነኛው በተለይም መሪው ከተመሪው በዝቶ እጅግም ገዝፎ በሚታይበት ጊዜ እራስን ፈጽሞ ከመለወጥ የተሻለ አዋጭ ዘዴ በወያኔ መንደር ምን ይሆን? ለዚህም ቢሆን ግን ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነው ወያኔ መላ ያጣ አይመስልም፤ የወያኔ የግምገማ ወንፊት ለወያኔዎች ተቃርኖ የሌላት (woyane friendly) ናትና። ድሮም ቢሆን በወያኔ ውስጥ ግምገማ ምልክት ማሳያ አቅጣጫ ጠቋሚና መስመር ሰጭ እንጅ ቀጭ አልነበረችም ሆናም አታውቅም የወያኔ ተፈጥሮ ለዚህ የተመቻቸ ስላልሆነ። ምንም እንኳ ሌባ ብንሆን፣ ምንም ያክል ሕዝብን ብንበድል፣ ያሻንን ያክል የሀገር ሃብት ብናወድም፣ በሕዝብ ሃብት ብንበለጽግ የወያኔን አለቃነት እስካወቅን ድረስና ወያኔ እንደ ዓይኑ ብሌን በሚጠነቀቅላት ስልጣኑ እስካልመጣንበት ድረስ የወያኔ ግምገማ ጓደኛችን ነች። በስልጣን ላይ ስልጣን፣ በሃብት ላይ ሃብት በአምባገነንነት ላይ አጉራ ዘለልነትን እየጨመርን እንሄዳለን እንጅ በወያኔ ግምገማ ምክንያት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ብሎ ነገር የለም። ታዲያ ይሄ ለወያኔዎች እንጅ ለእውነተኛ ኢትዮጵያዊያን አይሰራም።
አነሳሴ እንኳ ስለ ወያኔ ግምገማ መተረክ አልነበረም ለዚያማ እነሱ ምን የዘው፤ ይልቅስ ከግምገማ ጋር የተያያዘ ስለሚመስልና ሰሞኑን በወያኔ መንደር ስለተፈጸመ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነ ድራማ አንዳንድ ለማለት እንጅ። ጉዳዩ እንዲህ ነው ጄ/ል መሓመድ ሲነሳ ጄ/ል ሞላ ተመለሰ አሉ ጋዜጠኛ አርአያ እንዳለው። ሲጀመርስ ጄ/ል ሞላ ለምን ተነሳ ብሎ መጠየቅ መችም ችግር ያለው አይመስለኝም። እውነት ግን ለምን ተነሳ? ለነገሩ ላንድ የስራ ቦታ ወያኔያዊ ትስስር እንጅ አግባብነት ያለው የትምህርት ደረጃና በቂ የሆነ ተዛማጅ የስራ ልምድ ለማይጠይቀው ወያኔ እንዲህ ያለው ጥያቄ ምናልባት የሌሊት ቅዠት ለሆን ይችላል። ከዚያ ይልቅ የሚያስደንቀው ትላንትና ተነሳ የተባለው ዛሬ ተመለሰ መባሉ ነው። ምክንያቱም እንደ ወያኔ ላለው ከ 38 ዓመት በላይ ድርጅታዊ አሰራር ልምድ አለኝ ለሚል ድርጅት አንድን ጄኔራል ትላንትና አንስቶ ዛሬ ይመልሳል ብሎ ለማመን ስለከበደኝ ነው። አሃሃሃ ይቅርታ ለካ ያች ጉደኛ ግምገማ የሚሏትና ሚስጥር ተጋሪ ቁርጠኛ የልብ ጋደኛ ማስመቻ ግለ ሂስ የምትባል ቀልድ አለችና ለካ። ሁሉም ቅድም እንዳልኩት ነው፤ የወያኔ ግምገማ ለወገኖቿ (ለወያኔዎች) ብርቱ አይደለችም። ታስደነግጣለች፣ ምልክት ታሳያለች አቅጣጫ ትጠቁምና መልሳ አስተማምና ወደ ቀድሞ ቦታ ወይም ለተሻለ አለቅነት ታበቃለች። ይኸው ነው በቃ።
በዚሁ አጋጣሚ በነካ እጄ ግን፤ የሰሞኑ የወያኔ ዓይን ያዥ እንቅስቃሴ ምን የሚያሳይ ይመስላችሗል? መችም በውቅያኖስ ውስጥ አንዳች ነገር ሳይፈጠር ሱናሚ አይነሳም። ይህ የሰሞኑ የተሳከረ የወያኔ እጀብ እጀብም ባካባቢያቸው አንዳች ነገር እንዳለ ጠቋሚ ነው። ባላጋራ ሲገፋ ወዳጅ ይጎትታል አይደል የሚባለው። በወያኔ በራሱ ውስጥም እንኳ ቢሆን እንዲህ ያለው መሳሳብ የተለመደ ነው ምክንያቱም ጥበትና ጎጠኝነት ደንበር የላቸውምና ነው። በነዚህ ጄኔራሎች ሹም ሽርም ያየነው ዋና ጉዳይ ይህንኑ ነው፤ በጄኔራል ሞላና በጄኔራል መሓመድ ቡድኖች መካከል ያለው ለመሳሳብ የሚደረግ ፍጥጫና ፍትጊያ። በዚህ የተነሳም በወያኔ ውስጥ ከላይ እስከ ታች ድረስ እየተዛመተ ያለው አለመተማመንና መቧደን እያየለ
መምጣቱ፤ መጨረሻው አጓጓኝ። በራሳችን አቅምና ልምድ ብቻ የምንቀሳቀስባት ኢትዮጵያ ናፈቀችኝ። በራሳችን አቅምና ልምድ ብቻ የምንቀሳቀስባት ኢትዮጵያ ናፈቀችኝ።
No comments:
Post a Comment