FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, August 20, 2014

ከላይ ሆነን ስናይ

(ገለታው ዘለቀ)

above


በቅርቡ የኣሜሪካ ፌደራል ኣቪየሽን ኣስተዳደር (FAA) በዓለም ላይ ለበረራ ኣደገኛ የሆኑትን መስመሮች በካርታው ላይ ከቦ ኣስጠንቅቆ የነበረ ሲሆን በሪፖርቱ ላይ እንደሚታየው እነዚህን ኣደገኛ ቦታዎች በሁለት ከፍሏቸዋል። ኣንደኛው መስመር ኣደገኛነት ያለው ክልል (potentially hostile region) ሲሆን ሁለተኛው ክልል ግን በረራን ጨርሶ የከለከለ(Flight prohibited) ክልል ነው። ኣደገኛነት ኣላቸው ተብለው ኣብራሪዎች ከግምት እንዲያስገቡ የተመከሩባቸው ክልሎች ኬንያ፣ ኣፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ ማሊ፣ የመን፣ ኮንጎና ግብጽ ሲናይ ናቸው። የበረራ መስመር የተከለከለባቸው ኣካባቢዎች ደግሞ ዩክሬን ውስጥ ድኒፕሮፐትሮቭስክ (ይህ ኣካባቢ በሶቪየት ዮኒየን ጊዜ የኒውክሌር ማምረቻ ተቋም የነበረበትና በኣሁኑ ሰዓት ደግሞ በራሽያ የሚደገፉ ገንጣዮች የሚንቀሳቀሱበት ክልል ነው)፣ የክራይሚያ  ክልል፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ኢራቅ፣ ሰሜን ኮርያና ሰሜናዊ ኢትዮጵያ (ትግራይ) ናቸው።
የፌደራል ኣቪየሽን ኣስተዳደር መግለጫውን ካወጣ በሁዋላ በተለይ ለበረራ የተከለከሉትን ክልሎች ስናይ ብዙም ጥያቄ ያልፈጠረብን ቢሆንም የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ግን ተለይቶ ከነዚህ ኣደገኛ ኣካባቢዎች  ጋር እንዴት ሊመደብ ቻለ? የሚለው ጉዳይ በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ የመወያያ ጉዳይ የሆነ ይመስላል። የኣሜሪካ መንግስት ምን ኣይቶ ነው? ምን መረጃ ኣገኘ? የሚሉት ጥያቄዎች በጣም ያጓጉንም ይመስላል። ይህ ጉዳይ መወያያ ከሆነ ወዲህ ብዙ ሰው መላ የመታው የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ለመዋጋት እቅድ ስላለውና የኣሜሪካ መንግስትም ይህንን ስለተረዳ በኣካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስለሚታይ ቦታውን ከኣደገኛ ኣካባቢ ሊያስመድበው ችሎኣል የሚል ነው።ሙያው ባይኖረኝምና  ለዛሬ ጽሁፌ ዋና ጭብጥ ይህ ጉዳይ ባይሆንም በዚህ ላይ እኔም እንደ ግለሰብ የግል ኣስተያየቴን መስጠት እፈልጋለሁ።
FAAበእኔ ግምት የፌደራል የበረራ ኣስተዳደርን ወደዚህ ከፍተኛ ውሳኔ ያመጣው መረጃ ኤርትራና ኢትዮጵያ ወደፊት ወይም በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ጦርነት ሊያደርጉ በዝግጅት ላይ ከመሆናቸው ጋር በጥብቅ የተያያዘ ኣይመስለኝም። የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ለመዋጋት ማሰቡ በራሱ የትግራይን ክልል ኣደገኛ ሊያሰኘው ኣይችልም። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ለማድረግ ዝግጅት ካለም ይህ የመጀመሪያ ኣይደለም። ከ1998 እስከ 2000 ድረስ ሰባ ሽህ ሰው ያለቀበትን ውጊያ ባደረጉበት ጊዜ ኣሜሪካ ይህ የበረራ መስመር እንዲህ ኣሳስቧት ኣታውቅም። ከዚህም በላይ ጉዳዩ የሁለቱ ወገኖች ጦርነት የማስነሳት ፍላጎት ማሳየት ለኣሜሪካ በረራ ኣስጊ ነው ከተባለ የኤርትራ የኣየር ክልል ኣብሮ ለምን ኣልተዘጋም? ብለን እንጠይቃለን:: ቢያንስ-ቢያንስ Potentially hostile region በሚለው ማሳስቢያ ውስጥ እንኳን ኣልገባም። ይልቁን መረጃው የሚያስጠነቅቀው የኢትዮጵያ ሃይላት ኣልፈው ኬንያ  ማንዴራ ኣየር ማረፊያ ላይ ሳይቀር ኣውሮፕላኖች ሲነሱም ሆነ ሲያርፉ ከኢትዮጵያ ሃይላት ሊተኮስባቸው እንደሚችል ነው። በካርታው ላይ እንደሚታየው ኤርትራ በኣደገኛ ክልል እንኳን ያልተፈረጀች ሲሆን ሌላው የኢትዮጵያ ክፍልም በሁለተኛ ደረጃ ኣደገኛ እንኳን ኣልተባለም። ኤርትራም ሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል ንጹህ የበረራ ክልል ሆነው ነው የሚታየው። ሌላው ደግሞ ሌሎች ሃገሮች ማለትም የጦርነት ቀጣና የሆኑ ሱዳኖችን ጨምሮ በኣስተዳደሩ በኣደገኛነት ያልተፈረጁ መሆኑ የሚያሳየው ኢትዩጵያና ኤርትራ ለመዋጋት ኣቅደዋልና በረራ እንሰርዛለን ወደሚል ከፍተኛ ውሳኔ እንደማያመጣ ነው።
ከሁሉ በላይ ግን ኣስተዳደሩን ያሰጋው የጦርነት ቀጣና መሆን ያለመሆን ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከኣሸባሪነት ጋር የተያያዘ ስጋት ነው። ስጋቱ ልክ ዩክሬን ውስጥ እንደሆነው ሲቪል ተጓዦችን ሳይቀር ሊያነጣጥርና ሊጎዳ የሚችል የሽብር ስራ ሊደረግባቸው የሚችልባቸውን ቦታዎች ነቅሶ ከማውጣት ጋር የተያያዘ ነው።ታዲያ የኣሜሪካ መንግስት መደዚህ ከፍተኛ ርምጃ ሲመጣ ኣንዱ የሃገራችን ክፍል በዚህ ክብ ውስጥ ወድቆኣልና ይህ ክፍል ትኩረት ውስጥ መግባቱ ለእኔ ያሳየኝን እንደሚከተለው ኣንድ ሁለት ልበል።
1. ትግራይ ውስጥ የከፍተኛ ሮኬቶችና ሚሳየሎች ክምችት ኣለ ማለት ነው።
2. መሳሪያ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ኣሜሪካ እምነት ያጣችበት ኣደገኛ ቡድን በዚህ ክልል ይንቀሳቀሳል ማለት ነው:: ያ ቡድን ማን ሊሆን ይችላል?
በቅርቡ ዪክሬን ውስጥ ተመቶ የወደቀው የማሌዢያ ኣውሮፕላን ሲመታ ኣንዱ የተፈጠረው ጥያቄ የዩክሬን ገንጣይ ቡድን ይህን ኣውሮፕላን በዚያ ከፍታ ላይ መቶ ሊጥል የሚችል ሚሳየል ከየት ኣመጣው? የሚል ነበር። የብዙዎች መላ ምት የነበረው ራሺያ ቡድኑን ስለምትደግፍ ከሱዋ የተገኘ ድጋፍ መሆን ኣለበት የሚል ነበር።
ታዲያ በዚህ የኢትዮጵያ ክልል በልዮ ስሙ ትግራይ ውስጥ እንዲህ ከፍተኛ ሮኬት ሊኖረው የሚችል ለኣሜሪካ ኣውሮፕላን ስጋት የሚሆን ቡድን ማን ሊኖር ይችላል? ብለን እንድንጠይቅ ያደርጋል። ኣልፎ ኣልፎ እንደምንሰማው በዚያ ኣካባቢ ኣለመረጋጋት ካለ ያቺ የውስጥ ኣለመረጋጋት ከክላሽንኮቭ በጣም ከዘለለ ደግሞ ከላውንቸር የበለጠ ኣቅም ያለው ተቃዋሚ ቡድን ኣይኖርም። በመሆኑም በዚህ ቀጣና ከፍተኛ ሮኬቶችንና ሚሳየሎችን ሊያከማች የሚችለው ብቸኛ ቡድን ወያኔ (TPLF) ብቻ ስለሆነ ይህ ቡድን ነው በኣሜሪካ የበረራ ኣስተዳደር በኣደገኛነት የተፈረጀው ለማለት ይቻላል። ይህ ቡድን ብቻ ነው ኣቅም ያለውና። ወያኔ ትግራይን ለምን የከፍተኛ ሮኬቶችና ሚሳየሎች መደበቂያ ኣደረጋት ለሚለው ምላሹ ከኤርትራ ጋር ለምታደርገው ጦርነት ብቻ ተብሎ ሊወሰድ ኣይችልም። ኢትዮጵያ በሶማሊያ በኩል በሱዳን በኩልም ስጋቶች ኣሉባት። በከፍተኛ ሁኔታ ወያኔ በሚስጥር ትግራይ ውስጥ መሳሪያዎችን መደበቁ ድሮም ቢሆን ለብዙዎች ሲሸት የነበረ ጉዳይ ነው። ወያኔ ህዝባዊ ኣመጽ ሲነሳ የመጨረሻው መደበቂያየ ብሎ የሚያምነው ትግራይን በመሆኑ መሳሪያ ሲደብቅ መሰንበቱ ኣይገርምም።
ያለበት ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ መሳሪያ ሰብስቦ ኣይጠግብም። ጥያቄው ታዲያ ይህን ከፍተኛ መሳሪያ ከየት ያመጣዋል? ካልን ምንጮቹ ኣሸባሪነትን ከሚደግፉ፣ ለዩክሬን ገንጣይ ቡድን ራሽያ ታግዛለች እንደሚባለው በሚስጥር ከደጋፊዎቹ የሚሰበስበው ነው። ባለፈው ጊዜ ደቡብ ኮርያ ውስጥ ጥገኝነት የጠየቁ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ሰራተኞች እንደገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ሰሜን ኮርያ ውስጥ በምስጢር ገብቶ የጦር መሳሪያ ጭኖ እንደተመለሰ ነው።ህወሃት ያልተረዳው ነገር ሚሳየል መሰብሰብ ከምንም ሊያድነው እንደማይችል ነው። ይልቁን ኣሁን ኣሜሪካ እንዳደረገችው ኣለም እየተረዳው መጥቶ ለኣለም ስጋትነቱ ስለሚጋለጥ መጥፊያው ይሆናል።malaysianplane
ከዚህ በፊት የወያኔ መንግስት በኣፍሪካ ቀንድ ላይ ኣሸባሪ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ኣሁን ደግሞ የኣሜሪካ የበረራ ኣስተዳደር ትግራይን ለይቶ በካርታው ላይ መክበቡ በተለይ የትግራይ ነጻ ኣውጪ ላይ ያለውን እምነት ማጣት ብቻ ሳይሆን ወያኔ ለራሷ ለኣሜሪካ ስጋት ነው ወደሚል ድምዳሜ እንዳመጣቸው ያሳያል። እውነትም ነው።
ይህ መረጃ በተለይም የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ ወገኖች ጠቀሜታው ከመጉላቱም በላይ የሃገራችንን የትግል ኣቅጣጫና ሊመጡ የሚችሉ ተለዋዋጮችን እንድናይ ይረዳናል። ወያኔ በዚያ ክልል መሳሪያ መሰብሰቡ በኤርትራ በኩል ሊመጡ የሚችሉትን ሃይሎች ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲል እንዳልኩት ሁኔታው ከገፋና ኣመጾች ከበረቱ ትግራይ ውስጥ መሽጌ ኣገር መበጥበጤን እገፋለሁ የሚል በመሆኑ ይህንን ባህርዩን ከመቼውም በላይ በመገንዝብ  ተቃዋሚዎች  በትግል ካልኩሌሽናቸው ኣንድ ደረጃና ሁለት ደረጃ ከፍ ብለው መገኘት ኣለባቸው። ይቺን ካልኩኝ በሁዋላ በኢትዮጵያ የነጻነት ትግል ኣሰላለፍ ዙሪያ ጥቂት ወንድማዊ ኣሳቤንና ስጋቴንም ጭምር እንደሚከተለው ልጻፍ።
በሃገራችን የነጻነት ትግል እንዳያብብ ኣብቦም እንዳያፈራ ካደረጉት ችግሮች መካከል ኣንዱ የነጻነት ትግሉ ኣጠቃላይ ቅርጹ ወዲያና ወዲህ የተጠመደ መሆኑ ነው። ኣንዱ በብሄር ላይ የተመሰረተ ሌላው ደግሞ ብሄራዊ በሆነ ኣቋም ላይ የተመሰረተ ኣንዱ ደግሞ ለዘብተኛ ነኝ የሚል በመሆኑ ትግሉ እንዳያሸንፍ ኣሸንፎ ስልጣን ቢይዝም ነጻነት እንዳያፈራ ያደርጋል።
የቅርብ ጊዜውን ታሪክ ስናይ እንኳን ህወሃት የብሄር ኣርማ ኣንግቦ ትጥቅ ትግል ከጀመረ በሁዋላ ሌሎች ብሄራዊ ኣቋም ያላቸውን ቡድኖችን ኣብረን እንታገል በማለት ይቀሰቅስ ነበር። በተለይ ኢህዴን ኣንዱ ለህወሃት ከፍተኛ ኣስተዋጾ ያደረገ ድርጅት ነው።
እነዚህ ሁለት ቡድኖች ማለትም ኢህዴንና ህወሃት ከመርህ ኣንጻር ከሳይንስ ኣንጻር የማይደባለቅ ምንነት ይዘው ደርግን መጣል ታላቅ ግብ በማድረግ ብቻ ተጣምረው ታገሉ። ህወሃት ትንሽ ብልጠት ስላለው ኢህኣዴግ የሚባል የማንነት ማደናገሪያ ለጠፍ ኣርጎ ቀጠለ። በትግሉም ወቅት ሆነ ከትግሉ በሁዋላ ህወሃት ወታደራዊ የበላይነቱን እንደጠበቀ የቆየ ሲሆን ሁኔታዎች ሲረጋጉ፣ መንግስት ተመስርቶ ኣገር የሚባለውን ነገር የምር የማስተዳደሩ ጉዳይ ሲመጣ ህወሃት ኢህዼንን እንደገና ኣተኩሮ ያየው ይመስላል። እኔ የትግራይ ነጻ ኣውጪ ነኝ፣ ኦህዴድም የኦሮሞ ሆኖ ተሰልፎኣል፣ ኣንተ ምንድነህ? በሚል ኣይነት ኣፍጦ ካየው በሁዋላ ወደ ብሄር ቡድንነት ዝቅ እንዲል ስሙንም ኣርማውንም እንዲያስተካክል ተፈረደበት። ህወሃት ወታደራዊ የበላይነቱን ይዞታልና ኢህዼን ምንም ኣላለም።
ኢህዴን በኣማራ ተወላጆች ብቻ ኣልነበረም የተሞላው። የተለያዩ ብሄሮች ያሉበት ኣገራዊ ኣሳብ የነበረው ድርጅት ቢሆንም ብዓዴን በመባል የኣማራ ድርጅት እንዲሆን ተፈረደበት። ኣሁን የምናያቸው ኣማራ ያልሆኑ መሪዎች የኣማራ ስም ለጥፈው ብዓዴን የሚባል ኣስገራሚ ድርጅት ፈጥረው ቁጭ ኣሉ።የሚገርመው ኣማራውም ደንታ ሳይሰጠው ዝም ብሏቸው ሰነበተ።
ይህ የማንነት ጥያቄና የመጣመድ ጥያቄ ቀድሞ በትግሉ ጊዜ ቢመጣ ሚናቸውን በሚገባ ቀድመው ቢረዱ የተለየ መልክ ሊኖረው የሚችል ሲሆን ከድል በሁዋላ ህወሃት ወታደራዊውንና ደህንነቱን በሙሉ ከተቆጣጠረ በሁውላ በመሆኑ እነ ኢህዴን ሃይል ኣልነበራቸውምና የተሰጣቸውን ስም ተሸክመው፣ ያልሞቱለትን፣ የህወሃትን ዓላማ ያራምዱ ዘንድ ቀጠሉ። ህወሃት ከመነሻው ደርግን ለመጣል ከሚገባው በላይ የጓጓ በመሆኑ የማይጣመደው ኣልነበረም። ከኤርትራ ነጻ ኣውጪ ጋር ተስማምቶ ታግሏል፣ ከሱዳን በኩል የሚነሳ ቢኖር ኖሮም ኣብሮ ይታገላል ብቻ ከማንም ጋር ታግሎ ደርግን መጣል የመጨረሻው ኣላማው ነበር። ኢህዼንም ቢሆን ደርግን መጣል እንደ መጨረሻ ግብ በማየቱና ይህ ግብ ዋናውን የሃገሪቱን መሰረታዊ የነጻነትና የኣስተዳደር ጉዳዮች ለማየት ኣይኑን በመጋራዱ ከማይጣመደው የቡድን ነጻ ኣውጪ ጋር ተጣምዶ እያረሰ ኣዲስ ኣበባ ገባ:: ህወሃትን ለድል ኣብቅቶ ሲጨርስም እንደ ህወሃት እንዲሆን የህወሃትን ኣምሳል ሆኖ እንደገና እንዲፈጠር ተደርጎ ቁጭ ኣለ።
በሃገራችን በተለይም በሰሜኑ ክፍል የገና በዓል ሲመጣ የገና ጨዋታ ይደረጋል። በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ ይሳተፋሉ። ታዲያ በዚህ ጨዋታ ጊዜ ከየቀበሌው ወይም ጎጡ የመጡት ሰዎች ጥንጓን (ሩሯን) ሲቆረቁሱ “ሚናህን ለይ!” የሚባል ነገር ኣለ። ሚና ያለየበት የገና ጨዋታ የሚያስታውቀው ሩሯ ርቃ ኣትሄድም። በሚገባ ሚና የለየለት ጨዋታ ግን ወደ ኣሸናፊው ያደላና ድል ኣድራጊና ተደራጊ በጊዜ ይለያል።
የሃገራችን የነጻነት ትግል ከህወሃትና ኢህዴን ትግል ጀምሮ ኣሁን ድረስም በቡድነኝነትና በብሄራዊ ታጋይነት ሚናው ቅጡ የጠፋበት ነው። የዚህ የብሄር የነጻነት ጥያቄ ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ መስመሩን ሁሉ ስቶ ግልጽነት የጎደለው እንዴውም ኣደገኛ ኣሰላለፍ ሆኖ እናያለን። በመጀመሪያ ደረጃ በብሄር ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ትግል የሚያስፈልገው ለመገንጠል ነው። ለምሳሌ የ ኤርትራን ትግል ካየን እንደግፈውም ኣንደግፈውም ለመገንጠል ታገሉ እንዳሉትም ተገነጠሉ። እንደ ህወሃት ኣይነቱ ግን ፍላጎቱም ኣይታወቅም። የብሄር ጥያቄ ይዞ ተነሳ ትግራይን ኣልፎ ኣዲስ ኣበባ ገባ። ከገባም በሁዋላ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ጀምሮ ሃያ ኣመት ከቆየ በሁዋላ እንኳን ተምሮ ኣቋሙን የማይቀይር ኣስቸጋሪ ድርጅት ነው።
በኣንድነት እያመኑ በብሄር የፖለቲካ ጥላ ስሮ መቆም ፈጽሞ ኣብሮ ኣይሄድም። የሃገራችን የፖለቲካ ግጭትም ይሄ ነው። በመሆኑም ኣሁንም ለነጻነት ቆመናል የሚሉ ድርጅቶች ጥያቄያቸው ለመገንጠል ካልሆነና የነጻነት ጥያቄ ከሆነ ኣገራቸውን ነጻ ለማውጣት ከዚህ ግልጽነት ከጎደለው የትግል መስመር ወጥተው ህብረ ብሄራዊ መልክ መያዝ ኣለባቸው። የለም እኛ በኢትዮጵያ ኣንድነት ላይ ጥያቄ የለንም ነገር ግን በብሄር ላይ ቆመናል የሚባል ነገር ሚናው ያልለየ በመሆኑ የሃገራችንን የነጻነት ትግል ከማወሳሰቡም በላይ ማንንም ነጻ ኣያወጣም። በብሄር ላይ የተደራጁ ወገኖቼ ሊረዱት የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር በዚህ የትግል ስልት ለማሸነፍ ኣይችሉም ቢያሸንፉም ቡድናቸውንም ሆነ ሃገራችንን ነጻ ሊያወጡ ኣይችሉም። ይህንን ከነ ህወሃት መማር ያስፈልጋል። ህወሃት ኢትዮጵያንም ነጻ ማውጣት ኣልቻለም ቆሜለታለሁ ላለው የትግራይ ህዝብም ነጻነትን ሊያመጣ ኣልቻለም። ኢትዮጵያ ብዙ ናት ብሎ ያመነ ታጋይ፣ ብዙህነቱዋን ያመነ ነጻ ኣውጪ ብዙነቱዋን የያዘ የነጻነት ሰራዊት ነው ነጻ ሊያወጣት የሚችለው ብሎ ያምናል።
በኣሁኑ ሰዓት በትጥቅ ትግሉ ኣካባቢ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችም ቢሆኑ ይህንን ሃቅ መረዳትና በመርህ ላይ የተመሰረተ መቀናጀት ሊያደርጉ ይገባቸዋል። እንደ ትግራይ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (TPDM) ያሉ የህዝብ ብሶት ኣስነስቶናል የሚሉ ታጋዮችም ከወያኔ መማር ኣለባቸው።
እውነቱን ንገረን ካላችሁኝ ከመርህ ኣንጻር ለእኔ ህወሃትም ሆነ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዴምህት) ሁለቱም ኣንድ ናቸው። ልዩነታቸው ህወሃትን ስልጣን ላይ ሆኖ ብዙ በደል ሲፈጽም ያየሁት ሲሆን ዴምህትን ኣላየሁትም። ህወሃት ወንጀለኛ ሲሆን ዴምህት እንደማንኛውም የጎሳ ድርጅት ነው የሚታየኝ። በቃ። መነሳት ያለበት የመርህ ጥያቄ እንጂ የህወሃት ኣመራሮች በግለሰብ ደረጃ ክፉዎች ናቸው የዴምህት(TPDM) ኣመራሮች ግን ጥሩ ዴሞክራት ይመስላሉ የሚለው ኣይሰራም። የመርህ ጥያቄ መነሳት ያለበት ሲሆን እነዚህ ቡድኖችም ሆኑ ሌሎች በብሄር ላይ የቆሙ ሁሉ በመርህ ደረጃ ኣንድ መሆናቸውን ማስተዋል ተገቢ ነው። በግለሰቦች ጥሩነት ከሆነ የህወሃት ሰዎችም በትግሉ ጊዜ በጣም ጥሩ ይመስሉ ነበር። ሌሎች ህብረ ብሄራዊ የሆኑ ድርጅቶች ደግሞ በብሄር ላይ ከተመሰረቱ ጋር በመጣመድ ኣብረን እንታገላለን ማለት የለባቸውም። በተለይም በትጥቅ ትግል ጎራ ያሉ ከሆነ ይህ መንግስት ቢወድቅም በእንደዚህ ዓይነት የትግል ስልት የተመራ ትግል ኣንዱ የብሄር ቡድን እንደ ህወሃት ወታደራዊ የበላይነቱን ይዞ እንደ ህወሃት ኣይነት ስርዓት ላለመቀጠሉ ዋስትና የለንም። በተለይ በጣም ስስ የሆነው ወታደሩና ደህንነቱ በኣንድ የብሄር ቡድን እጅ ሲወድቅ ነጻነት ኣያፈራምና ከእንዲህ ዓይነት የትግል መጣመድ ሚና መለየት ያስፈልጋል።የጨከነ በመርህና በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሚናውን የለየ የትግል ኣቅጣጫ ያስፈልጋል ማለቴ ነው።ራሱ ወያኔ እንደ መጨረሻ ኣማራጭ (worst case scenario) እንደሚሉት  የተለያዩ ተቃዋሚ የሚመስሉ ድርጅቶችን በመፈልፈልና የሰለጠኑ ደህንነቶቹን በዚያ በመሰግሰግ ገዢነቱን (status quo) ለመጠበቅ ስለሚጥር ህብረ ብሄራዊ የትግል ስልት መኖሩ እንዲህ ዓይነቶቹን ኣስመሳዮች ለመዋጥ ይጠቅማል። ዋናው ግን ሁሉን ለመጠርጠር ሳይሆን ጥበብ የተሞላበት ሚና የመለየት ስራ መስራት ኣሰፈላጊነቱን ለማስመር ነው።
tpdmዴምህት እንደዚህ ኣስቦ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ህወሃት ከትግራይ የተነሳ በመሆኑና ኣሁን ያለው የኣስተዳደር ብልሹነት ስላበሳጫቸውና ስላሳፈራቸው እኛው ያመጣነውን እኛው እንመልሳለን የሚል ስሜት ያየለበት ቁጭት ኣስነስቱዋቸው ሊሆን ይችላል። ለነዚህ ወገኖቼ መልእክት ኣለኝ። ኣይዞኣችሁ ህወሃትን ያመጣችሁት እናንተ ብቻ ኣይደላችሁም። እነ ኢህዴን፣ የጎንደር ህዝብ፣ የወሎ ህዝብ፣ የኦሮሞ ህዝብ፣ የሰሜን ሸዋ ህዝብ የኤርትራ ነጻ ኣውጪው ተባብረው ነው ኣዲስ ኣበባ ያስገቡት። የትግራይ ህዝብ ለዚህ መንግስት ለብቻው ተጠያቂ ኣይደለም። ሁላችን ተጠያቂዎች ነን።የደርግ ጭቆና ስላንገፈገፈንና የደርግ መውደቅ ጉዳይ ዋና ግብ መስሎ ስለታየን የህወሃትን ተፈጥሮ ሳንመረምር፣ ስምህ ህወሃት ሆኖ እንዴት ወደ ኣዲስ ኣበባ ትገሰግሳለህ ብለን ኣጥብቀን ሳንጠይቅ ሁላችን ገፍተን ነው ኣዲስ ኣበባ ያስገባነው። ኣበባ ይዘን የተቀበልነው ። በብልጠት ህወሃት ለጠፍ ያደረጋት ኢህኣዴግ የምትባል ስያሜንም ኣልመረመርንም።ጥፋቱ የሁላችን ነው። የትግራይ ህዝብ ለብቻው ተጠያቂ ኣይሆንም። በመሆኑም ሁላችን በጋራ ታግለን ነው ይህንን ኣሳፋሪ ታሪክ የምንቀለብሰው። የትግራይ ህዝብ በታሪኩ ከሌሎች ወንድም ወገኖቹ ጋር እኩል ኣስተዋጾ ሲያደርግ የኖረ፣ ክፉንና ደጉን ኣብሮ ያሳለፈ ለኢትዮጵያዊነቱ ምንም የማይወጣለት ነው። በመሆኑም ከኣሁን በሁዋላ በዚህ ህዝብ ስም ምንም ኣይነት የትግል እንቅስቃሴ ኣይፈልግም። ህወሃት የጎዳው ይበቃዋል። ይህ ወንድማዊ ኣሳብ ነፍጥ ላነሱ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ለሚታገሉ በብሄር ላይ ለተመሰረቱ ወገኖች ሁሉ ነው። ኣረና ትግራይ፣ ኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የመሳሰሉት ድርጅቶችም ከማንነት ፖለቲካ ወጥተው ህብረ ብሄራዊ መልክ እስካልያዙ ድረስ ትግላችን ኣያፈራም።
በቅርቡ ኣረና ትግራይ ለውህደት መነሳቱን በውህደት ላይ ኣዎንታዊ ኣቋም መያዙ የሚደነቅ ሲሆን ይህን ኣቋሙን ቶሎ ብሎ ወደ ተግባር ቢለውጥ ትልቅ የመንፈስ መፈታትን በትግራይ ኣካባቢና በሌሎች ወገኖች ዘንድ ያመጣል የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ከሌሎች ቡድኖች ጋር ኣብሮ ታግሎ ሃገሩን ነጻ ማውጣት ነው። ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም የትጋራይ ነጻ ኣውጪ የሚባል ኣዲስ ቡድን ነጻ እንዲያወጣው ኣይፈልግም። ሁላችን እኩል የተሳተፍንበት ትግልና ድል ነው የሚያዛልቀን። የኦሮሞው ወገናችንም ጥያቄ እንደዚሁ ነው። ያልበላውን ለማከክ ከመሞከር ይልቅ ተቃዋሚ ሃይላት ተባብረው ዴሞክራሲን መልካም ኣስተዳደርን ቢያሰፍኑለት ያ ነው ጥማቱ። የኣማራውም ጥያቄ ይሄ ነው። ለብቻው የዓማራ ቡድን ተቁዋቁሞ እነንደ ህወሃት የዓማራ የበላይነት እንዲመጣለት ኣይደለም። የደቡቡም የምስራቁም ህዝብ የጋራ ችግር በውነቱ ይሄ ኣይደለም።
ሌሂቃን በዚህ ችግርተኛ ህዝብ ህይወት ላይ ባይጫወቱ ጥሩ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ኣስር በመቶ የሚሆነው ህዝብ በየኣመቱ ርዳታ ጠባቂ ነው። ሰባ በመቶ የሚሆነው ህዝብ ድሃ ነው። በዚህች ምድር ላይ ከኒጀር ቀጥለን የመጨረሻውን የድህነት ኑሮ የምንገፋ ህዝቦች ነን። ይህ ድህነት የሚገለጸው በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በመላ ህይወታችን ነው። ወደ ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ህዝብ ማንበብና መጻፍ እንኳን ኣይችልም። በሃያ ኣንደኛው ክፍለ ዘመን ሃያ ሰባት ሚሊየን የሚሆን ህዝብ ስሙን እንኳን መጻፍ በማችልባት ኣገር ኣርባ ኣመት ሙሉ በማንነት ጥያቄ መደናቆር በሚሊየኖች ህይወት መቀለድ ይባላል።
እንደ ዴምህት ኣይነቱ ድርጅት ህወሃትን ያመጣነው እኛ ነንና እኛው እንዳመጣን እኛው እንመልሰው ብለዋል ጥሩ ሰዎች ናቸው ብሎ ወታደራዊውን የበላይነት ማስረከብና በእንዲህ ኣይነት መርህ በሌለው የትግል ስልት መጣመድ ለብሄራዊ ታጋዮች ተገቢ ኣይደለም ብቻ ሳይሆን መርህ የጎደለው ማስተዋል የጎደለው ኣካሄድ ነው።። በቆራጥነት በመርህ ላይ የተመሰረተ ሚናው በደንብ የለየለት የትግል መስመር ያስፈልጋል። ህወሃት፣ ኢህዴን፣ የኤርትራ ነጻነት ግንባር ደርግን ማሸነፍ የመጨረሻ ግብ ኣድርገው ታግለው ሲያበቁ ኢትዮጵያ በኣንድ የብሄር ቡድን ወታደራዊ የበላይነት ስር ወደቀች:: ወታደራዊ ተቋም ደግሞ በቀላሉ ደህንነቱን ይቆጣጠርና የዚያች ኣገር የፍትህና የዴምክራሲ ጥያቄዎች ዳዋ እንዲበላው ያደርጋሉ። ከኣሁን በሁዋላ ኢትዮጵያን የኣንድ ብሄር የበላይነት ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ኣያወጣትም ብቻ ሳይሆን ኣደገኛ መሆኑንም መገንዘብ ኣለብን። ለኦነግ ወገኖቼ፣ ለኣማራ ነጻ ኣውጪ ወገኖቼ፣ ለጋምቤላ ነጻ ኣውጪ ወገኖቼ፣ ለኦብነግ ወገኖቼ፣ ለሲዳማ ነጻ ኣውጪ ወገኖቼና ለሌሎችም የምመክረው ምክር ኣጭር ነው። ወንድሜ ኦባንግ ያለው ነገር ኣለ።
“ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ መሆን አይችልም!”obang metho
ኦባንግ ሜቶ
ታላቅ ኣባባል ነው። የቡድን ጥያቄ ይዘን ቡድናችንንም ሆነ ኣገራችንን ነጻ ልናወጣ ኣንችልም።  ሌላው ስለ ሚና ስናነሳ የርእዮቱን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ተቃዋሚ የመሰሉ ኢህዓዴግ የመሰረታቸው ወይም የሱ መጫወቻ የሆኑትን እነሱንም የመለየት ስራንም ይመለከታል:: እነዚህን በይፋ የመለየትና የማውገዝ ስራ ካልተሰራ ኣሁንም ኣይናፋር ታጋዮች ሆነን ሚናው ያለየለት ትግል ውስጥ ስለምንቆይ ትግላችን ቶሎ ኣያፈራም።
በመሆኑም የነጻነት ታጋዮች በኣንድ በኩል ውህደትንና ህብረትን እያጠናከሩ በሌላ በኩል ደግሞ የሚና መለየቱን ጉዳይ በቆራጥነት ሊመሩት ይገባል። ኣንድ ሰው በኣንድ ኣስተዳደራዊ ጥያቄ ዙሪያ ኣርባ ኣመት መጨቃጨቅ የለበትም። ኣለም ጥሎት በመጣ፣ በኣንድ ወቅት ብልጭ ባለ ግልጽነት በጎደለው የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ተኮልኩለን ድሃውን ማሰቃየት የለብንም። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሄራዊ የሆኑትን እንቅስቃሴዎች እንደግፍ። እናንተ ኢትዮጵያን በሙሉ ማንነቱዋ የምታዩ ነጻ ኣውጪዎች ደግሞ ሚና የመለየት ስራ እየሰራችሁ ወደ ህብረት ኑና ኣገራችንን ታደጉ። ዛሬ ህዝቡ እየጠየቀ ነው። ኧረ እንደዚህ ኣድርጉ በሉን፣ ምሩን…. ለመታገል ዝግጁ ነን…… የት ናችሁ? የት ደረሳችሁ? ኣየ…. የጨነቀው ህዝብ….።  የሚያሳዝነው ግን በተግባር የሚታይ ነገር የለም። ይህ መንግስት በኣመጽ ነው የሚወድቀው። ይህንን ደግሞ ለመምራት ሚናቸውን በሚገባ የለዩ ነጥረው የወጡ የእውነተኛ ፓርቲዎች ህብረትና ኣመራር ሰጪነትን ይጠይቃል።  በቃ!…. ያለፈው ይብቃንና ወደ ፍጻሜ እንምጣ።ለነዚህ በብሄር ላይ ለቆሙ ወገኖቼ በመጨረሻም የምመክረው ይህንን ነው። ችግሮቻችን የሚፈቱት ከላይ ሆነን ስናይ ነው። ከላይ ከኣፍረካ ህብረት፣ ከላይ ከግሎባላይዜሽን፣ ከላይ ከኢትዮጵያ ኣንድነት ላይ ሆነን ስናይ ውስጥ ለውስጥ የሚነሱ የባህላዊ ቡድን ማንነት ጉዳዮች የትግላችንን መስመር ኣያሰምሩልንም። ከላይ ኣሁን የሰው ልጅ ከደረሰበት ማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ የግንዛቤ ደረጃ ላይ ሆነን ስናይ ከማንነት ፖለቲካ ጋር የተያያዙብን ጥያቄዎች ገዝፈው ኣይታዩንም።ይልቁን ከፍ ባለ ዴሞክራሲና መልካም ኣስተዳደር ላይ ኣይናችን ኣርፎ በዚያ ይህን የተቸገረ ህዝብ ለመርዳት መቆም ይገባናል ለማለት ነው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
http://www.goolgule.com/when-seen-from-above/

No comments:

Post a Comment