FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Friday, October 31, 2014

“ይህ አገዛዝ በቃው! አንፈልገውም! 27 ዓመት + 1 አንቀበልም!”

ቡርኪናፋሶ ከአምባገነን ወደ አምባገነን?

burkina-faso-1


ቡርኪናፋሶን ያለገደብ ሲመሩ የነበሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ ለተጨማሪ ዓመታት ሥልጣናቸውን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ በመክሸፉ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ገለጹ፤ ለአንድ ዓመት የመሸጋገሪያ መንግሥት ተመስርቶ ምርጫ እስከሚደረግ በሥልጣን እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡ ሕዝቡና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን ይህንን የሚቀበሉበት ትከሻ እንደሌላቸውና የኮምፓዎሬ አገዛዝ አሁኑኑ መውረድ እንዳለበት በተቃውሟቸው እየገለጹ ነው፡፡ ከ27ዓመት አምባገነናዊ ሥርዓት በኋላ ቡርኪናፋሶ ወደ ሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ልትሄድ እንደምትች ተጠቆመ፡፡
በቀድሞው ፕሬዚዳንት ቶማስ ሳንካራ ዘመን የመንግሥት ባለሥልጣንና የሳንካራ ወዳጅ የነበሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ፤ ቶማስ ሳንካራ ባልታወቀ ሁኔታ በመፈንቅለ መንግሥት ከተገደሉ ከዛሬ 27ዓመት ጀምሮ ቡርኪናፋሶን መግዛት ጀመሩ፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን በመምራት የተሳተፉት ኮምፓዎሬ የሳንካራን መገደል በወቅቱ “ድንገተኛ” በማለት ከመጥቀስ በስተቀር ምርመራ እንዲካሄድ አላዘዙም፤ ምስጢሩም እንዳይወጣ ተደርጎ ቆይቷል፡፡
ቶማስ ሳንካራን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ ለሦስት ዓስርተ ዓመታት ያህል የዘለቀውን አገዛዛቸውን የጀመሩት ኮምፓዎሬ እኤአ በ1990ዎቹ በተደጋጋሚ የተመረጡት ሲሆን የአገሪቱ ሕገመንግሥት ከተሻሻለ በኋላ በሁለት ሺዎቹም ሁለት ጊዜ ተመርጠዋል፡፡
burkina-faso-blaise1
ብሌዝ ኮምፓዎሬ
በአገዛዝ በቆዩበት ዘመን ሁሉ የአውሮጳውያንና የአሜሪካ ወዳጅ በመሆን ሥልጣናቸው ሳይደፈር በአምባገነንነት ለመቆየት ችለዋል፡፡ አክራሪ እስላማዊነትን እዋጋለሁ በማለት የአሜሪካ ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩት ኮምፓዎሬ በላይቤሪያና ሴራሊዮን እጅግ አስከፊ ጭፍጨፋ ያካሄዱትን እና በአሁኑ ወቅት 50ዓመት እስራት የተበየነባቸው የቀድሞው የላይቤሪያ መሪ ቻርልስ ቴለር የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ ሳንካራን ለመገልበጥና ለመግደል የቴይለር ጦር እንደተሳተፈና በምላሹ ኮምፓዎሬለቴይለር ወደ ሥልጣን መምጣትና ከዚያ ጋር ተያይዞ ለተፈጸመው ወንጀል ተባባሪ ናቸው በማለት ሁኔታዎችን የሚያገናኙ ወገኖች አሉ፡፡
በአገራቸው የሚነሱ ተቃውሞዎችን ስልታዊ በሆነ መንገድና በምዕራባውያን ድጋፍ ሲያከሽፉ የኖሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ በአካባቢው አገራት ዘንድ የሰላም ዘንባባ አቅራቢ፣ አስታራቂ፣ አስማሚ፣ ሸምጋይ፣ … ሆነው ምስላቸውን እና ማንነታቸውን ሲገነቡ ቆይተዋል፡፡ በአምባገነንነት በቆዩባቸው ዓመታት በሙስና በተለይም ከአልማዝ ሽያጭ ከሚገኘው ገንዘብ ያላቸው ተሳታፊነት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በቀጣዩ የአውሮጳውያን ዓመት 2015 ሥልጣናቸው የሚያበቃው ኮምፓዎሬ “ደህና ሁኑ” ብለው ለመሄድ የተዘጋጁ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን ሕገመንግሥት በማሻሻል እንደገና ለመመረጥ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፤ ፓርላማቸውን አሰብስበው ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል በማድረግ ሂደት ላይ እያሉ ሕዝቡ “በቃኝ” አለ፡፡
የ27 ዓመታት አገዛዝ የመረራቸው ዜጎች ሐሙስ ዕለት ፓርላማውን ጥሰው በመግባት ድምጽ እንዳይሰጥ ከማድረግ አልፈው በእሣት አጋዩት፡፡ ተቃውሞ በየቦታው ፈነዳ፡፡ ቡርኪናፋሶ መጋየት ጀመረች፡፡ ሁኔታው ያላማራቸው ኮምፓዎሬ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ፡፤ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡ ሕዝቡ “ይህንን አገዛዝ አንፈልግም፣ በቃን” አለ፡፡ ሕዝባዊ ዓመጽ በየቦታው ተቀጣጠለ፡፡ በተለይ ዋና ከተማዋ ዖጋዱጉ የዓመጹ ዋና ማዕከል ሆነች፡፡
መንግሥት ሥራ አቆመ፣ ፓርላማውም ፈረሰ፡፡ ድህነት ያስመረራቸው ዜጎች አሁንም ተቃውሟቸውን ቀጥሉ፡፡ ኮምፓዎሬን ማየትም ሆነ መስማት በጭራሽ አይፈልጉም፡፡ ወታደሮች በየአካባቢው ሥነሥርዓት ለማስጠበቅ እየጣሩ ቢሆንም ዓመጹ ግን ቀጥሏል፡፡ ንብረት እየወደመ ነው፤ ባንኮችምተዘርፈዋል፡፡
ዛሬ አርብ ዳግም ለመመረጥ ሲመኙ የነበሩት ኮምፓዎሬ ሥልጣን በቃኝ፤ መንግሥት ፈርሷል፤ ፓርላማውም አይሰራም፤ ከሥልጣኔ እለቃለሁ ነገር ግን በ2015 ምርጫ እስከሚካሄድ የሽግግር አስተዳደር ተመስርቶ ሁሉም ነገር መረጋጋት አለበት በማለት አስቀድሞ በተቀዳ የቴሌቪዥን መልዕክት ቢያስተላልፉም ሰቆቃ የመረራቸው፣ ኑሮ ያቃጠላቸው፣ ነጻነት የጠማቸው ዜጎች ግን አሁንም “አንሰማም” ብለው ተቃውሟቸውን በመቀጠል ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡
ሰላሳ አራት የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ቅደመ ሁኔታ አንቀበልም ብለዋል፡፡ ለኮምፓዎሬ ምላሽ ሲሰጡም “አንድ የምንቀበለው አጭርና ግልጽ ቅድመ ሁኔታ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ብሌዝ ኮምፓዎሬ ከሥልጣን እንዲለቁ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡
ጦሩ ሥልጣኑን የተረከበ እንደሆነ እየተጠቆመ ሲሆን አገሪቱን በበቂ ሁኔታ ለማረጋጋት እንዳልቻለ ከዋና ከተማዋ የሚመጡ ዜናዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሕዝቡ ዓመጽም ወደ ሌሎች ከተሞች እየተዛመተ መሆኑን ከተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እየተሰማ ነው፡፡
burkina generalsበአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ከአረብ ጸደይ ቀጥሎ የተጀመረ “የአፍሪካ ጸደይ” ሊሆን ይችላል በማለት ግምት የሰጡበት የቡርኪናፋሶ ሕዝባዊ አመጽ ተመልሶ በአምባገነናዊ አገዛዝ እንዳይወድቅ ስጋት አላቸው፡፡ ለዚህም ጠንካራ ተቋማት መመሥረት አስፈላጊነትን ያሰምሩበታል፡፡ በተለይ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ሕዝባዊ ሥርዓት በሚደረግ ጉዞ በቅድሚያ የሚደረጉ መሰናዶዎች ሳይከናወኑ በጭፍን አምባገነኖችን ከሥልጣን እንዲወርዱ ማድረግ በበርካታ አገራት እንደተደረገው መልኩን የቀየረ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመመሥረት እንደሚጋብዝ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የሕዝብ ንቃተ ኅሊና መዳበር፣ የእርሰበርስ ውይይት መጀመር፣ የተቋማት መመሥረት፣ … ወሳኝነት ያላቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንደሆኑ ያሰምሩበታል፡፡
*********************
ይህንን ዘገባ ካጠናቀርን በኋላ ከቢቢሲ የተገኘው ዜና እንደሚያመለክተው ከሆነ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን ጥለው ከአገር እየወጡ እንደሆነ የጦሩጄኔራል ዖኖሬ ትራዖሬ በሕገመንግሥቱ መሰረት አገሪቷን እየመሩ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ቦታ ባዶ እንደሆነና በ90 ቀናት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ መነገሩን ቢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ብሌዝ ኮምፓዎሬ አሁን ያሉበት ቦታ ባይታወቅም በአቅራቢያ ባለ አገር አቋርጠው ወደ አንድ አውሮፓ ምናልባትም ፈረንሳይ የስደት ህይወታቸውን መምራት ይጀምራሉ የሚል ግምት እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡
http://www.goolgule.com/it-is-over-for-this-regime-burkinafaso/

No comments:

Post a Comment