(ርዕሰ አንቀጽ)
ደረጃ ምደባ ለሸቀጥ ወይም ለአንድ ምርት የሚወጣ ማነጻጸሪያ፣ መለያ፣ መተመኛ፣ የጥራት መጠን መለኪያ … ነው። የደረጃ ምደባ ሲከናወን እንደ አቅሚቲም ቢሆን አስፈላጊ የሚባሉ የመመርመሪያ መሳሪያዎች፣ ቤተ መመርመሪያ፣ መርማሪ ባለሙያና ተመርማሪው ሸቀጥ አስፈላጊ ናቸው። የወጉ አሰራር ካለ ማለት ነው።
“እኛ” ሲባል ባጭሩ ከአንድ በላይ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር አንድ ብቻውን “እኛ” ሊባልም ሆነ እኛ ብሎ ራሱን ሊጠራ አይቻለውም። ስለዚህ “እኛ” የወል፣ የስብስብ ወይም የጋራነት መለያ ከሆነ፣ አንድ ሆኖ “እኛ” የሚል ተቀባይነት የለውም። አሁንም ባጭሩ የከሸፈ አስተሳሰብ ነው። የከሸፈ ብቻ ሳይሆን የሚያከሽፍም ነው። በነጠላነት ውስጥ ያለው “እኛ” ነት በርካቶችን አክሽፏል፤ አሸማቋል። አሁን ባለው አያያዝ ጉዳቱ ወደ “ውድቀት ህዳሴ” እያንደረደረ ነው። ግን ፍሬን ሊያዝበትና እንድርድሩ ሊገታ ይችላል።
ኢህአዴግ የሚባለው አገዛዝ፣ አብዛኞች ተቃዋሚዎች “መንግሥት” እያሉ የሚጠሩት፣ እኔ ያላቀድኩት፣ እኔ ያልተለምኩት፣ እኔ ያላወጅኩት ሁሉ “ቀሳፊ ተስቦ ነው” በሚል መስማት ከተሳነው 23 ዓመት ሆኖታል። ጆሮው ስለተዘጋና ልቡናው “ያለ እኔ” በሚል የእብሪት ስብ ስለተደፈነ “ወደብ ያስፈልግሃል” እንኳን ሲባል ላለመስማት ደንቁሮ ነበር። ዛሬ ወደብ ላላቸው አገር ጥሪት እያባከነና ሰግዶ እያሰገደን ያለው ኢህአዴግ እሱ ያላለማው ልማት ውድመት ነው። እሱ ያልተዋጋው ጦርነት ሁሉ ጭፍጨፋ ነው። እሱ ያላቦካው ዳቦና እንጀራ አይሆንም። እሱ እውቅና ያልሰጠው ህዝብ ህዝብ አይደለም። እሱ ያልባረከው ሚዲያ ጸረ ህዝብ ነው። እሱ ያላካለለው ወሰን የአድሃሪያን ትምክህት ነው። ይህ ለእርሱና ለሚያሳድራቸው ቢሆን አይገርምም። የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው እሱ የሁሉም ነገር አባት፣ መሪና ፈጣሪ መሆኑንን የመቃወም የልዩነት ተፈጥሮ መብት እንኳን አይፈቅድም። የሚቃወሙት ሁሉ አሸባሪ እንዲባሉ በዲዳው ሸንጎ ማስወሰኑ ሌላው ቅሌት ነው። ግብዓት በሌለበት ደረጃ ምደባ!! ክሽፈት ማለት ይህ ነው።
በተቃዋሚ ሰፈርም ተመሳሳይነት አለ። ያገር ቤቱን እንኳ ብንተወው ነጻነት አለበት በሚባልበት አገር ያለው ሚዲያ መረጃ ለማሰራጨት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታና ድጋፍ የሚያሻው ቢሆንም የሚጠበቅበትን እየሰራ ነው ለማለት አይቻልም። እኛን ጨምሮ። ተሸብበናል፤ ፈርተናል። በርካታ የሚያነጋግሩና ህዝብ በነጻነት የሚወያይባቸው ጉዳዮች እያሉ ቀድቶ በመለጠፍ (ኮፒ/ፔስት) ሥራ ተወጥረናል፤ ይህ ለሰው ሥራ ዕውቅና ሳይሰጡ የሚፈጸም ተግባር ሙያዊ ጋዜጠኝነት ሳይሆን “የዘረፋ ጋዜጠኛነት” ነው። ከመርህ አንጻር መደገፍና፣ ለሚደግፉት ሃሳብ ልዩ ትኩረት መስጠት አግባብ ቢሆንም ብዙም የተኬደበት ግን አይደለም። በግል የጎልጉል ድረገጽ ጋዜጣ በመርህ ደረጃ ከሚያራምደው ዓላማ አንጻር በተደጋጋሚ ወቀሳ ደርሶብናል። ይህ የተደረገው በግልጽ ዓላማችንን በማስቀደማችን ለማስጠንቅቅም ጭምር ነው።
ወቀሳዎቹ ከላይ እንዳልነው “እኛ” ሲሉ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ የመወከል ስልጣን ለራሳቸው የሰጡ የሚሰነዝሩት ነው። እንደ ኢህአዴግ “ዲዳው ሸንጎ” በስብሰባ ያስወስኑት መቼና የት እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም “እኛ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ” በሚል የማግለል አሠራር ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ቅልጥ ያለ ወያኔ ተደርጎ ተወስዷል። ፍትህን ለሚያጎናጽፍ የእርቅ ሃሳብና እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉና በይፋ ድጋፍ መስጠታችን “የወያኔን እድሜ አራዛሚዎች” በሚል እንድንዘለፍ አድርጎናል።
ከመርሃችን አፋፍ ላይ ቆመን ለምናወጣቸው ዘገባዎችም ሆነ በስማቸው ባደባባይ አስተያየት የሚልኩልንን ስናስተናግድ ሃሳቡ ላይ “እኛ” ሳይባል “እኔ እንደሚመስለኝ” በማለት መሟገት ሲቻል፣ ባልተሰጠ ማንነት “እኛ … ዘራፍ” ማለት ዋጋው አይገባንም። ሰዎች ሃሳባቸውን “እኔ” እያሉ ሲገልጹ፣ “እኛ” በማለት መመለስ ለማስፈራራት የሚደረግ ከንቱ ሙከራ ሆኖ ይሰማናል። “እኛ የዲያስፖራው ማህበረሰብ” በማለት በህግም ይሁን ባገር ሽማግሌዎች ባልተሰጠ ሹመት አንድ ሰው ራሱን በራሱ ሹመኛ አድርጎ የአዋጅ ይዘት ያለው አስተያየት ሲሰጥ ያመናል፤ ይዘገንነናል። “እኛ” ሲባል በ“እኛ” ውስጥ ያልተቆጠሩትስ? ለምሳሌ እኛ ራሳችንስ? በዚሁ በፍርሃቻ ተሸብበው እንደ ከሸፈ ባሩድ ያደፈጡት አብዛኞችስ? ብዙ ብዙ … ዎችስ?!!!
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማንም ለማንም የሚለግሰው “ቦነስ” ወይም ገድቦ የሚሰጠው አይደለም። ሃሳባችንን አራግፈውና አብጠርጥረው ለሚተቹን፣ ለሚወቅሱን፣ ለሚያስተምሩን … ወዘተ ሁልጊዜም በራችን ክፍት ነው። የሳይበር ሚዲያውን የተቀላቀልነውም ለዚሁ ነው። በጨዋነት ሃሳብ ላይ መከሳከስ ይቻላል ስንል ባልተሰጠ ውክልና “እኛ” በማለት ደረጃ የመመደብ ሃላፊነትን ተላብሰው “ሊሰፍሩን” የሚፈልጉትን ግን “ኦ! ኦ! ወራጅ አለ እንላለን”። ምክንያቱም አካሄዱ የመናገር፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ … ብቻ ሳይሆን የማሰብን ነጻነት ይጋፋል፡፡ ሰውን በራሱ ሃሳብ እንዲፈራና እንዲሸማቀቅ የሚያደርግ እርኩስ ነገር ስለሆነ እንጸየፈዋለን፡፡
አሁንም ደግመን ደጋግመን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የእኛ ሳይሆን የናንተ መሆኑንን እንገልጻለን። ፍትህን ሊያመጣ የሚችል እርቅ አሁንም በመርህ ደረጃ የምንደገፈው፣ ማንም የማይሸልመን፣ ማንም የማይወሰድብን ፈርጥ ሃሳባችን መሆኑንን አበክረን እናስታውቃለን። ማንም በ“እኛ አልደገፍነውም” የማግለያ ማስፈራሪያ ሊነጥቀን የማይችል ዕንቋችን ነው፡፡ ሃሳብን በሃሳብ የመጣላትና የመማማር ልምድ እንዲመጣ እንመኛለን። በሃሳብ መከራከር ጠላትነት እንዳልሆነ ከሚያምኑ ጋር በህብረት እንሰራለን። በሃሳብ ተለያይቶ በመከባበር አብሮ መስራት የሚችል ትውልድ እንዲነሳ የበኩላችንን እናበረክታለን። ከጎናችን ሁኑ። ጻፉ፣ ተናገሩ፣ አስተያየት ስጡ፣ “እኛ” ግን አትበሉ። እኛ ለመሆን ተደራጁና በድርጅት ስም ተንፍሱ!! አለበለዚያ “እናንተ እነማን ናችሁ” ይመጣልና!!
http://www.goolgule.com/who-is-us-and-who-sets-the-standards/
No comments:
Post a Comment