FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, December 27, 2014

“መንግሥት ከደላሎች ጋር አይደራደርም” ኃይለማርያም

ኢህአዴግ ከኤጀንሲዎች ጋር “ሽያጩን” አጠናክሯል

Ethiopian-house-maids


ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት መንግስት በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ በኢትዮጵያውያን ላይ የተከሰተውን ስቃይ እና በደል ተከትሎ ለስራ ወደ አረብ ሀገራት በሚደረግ ጉዞ ላይ እገዳ መጣሉ ይታወሳል። በተለይ ያለአንዳች የህይወት ዋስትና ወደ ተጠቀሱት ሃገራት በኮንትራት የሚሄድ ሰራተኞችን ከገጠር እስከ ከተማ በዘለቀ ድለላ ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው ዜጎችን እያጋዙ የነበሩ የአሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤት ቢሮዎች መዘጋታቸው አይዘነጋም። ዘግይቶም ቢሆን መንግስት በወቅቱ ወሰደ በተባለው እርምጃ የአያሌ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ከአስከፊው የአረብ ዓለም ስቃይ  መታደግ ቢችልም ከግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቻችንን ህይወት ስላለበት ሁኔታ የተጠቀሱትን የኤጀንሲ ባለቤቶች በህግ ለመሞገት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ቴድሮስ አድሃኖም የገቡትን ቃል መተግበር አለመቻላቸው ብዙዎችን አሳዝኖል።
ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን በዚህ ዙሪያ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበው ረቂቅ  ተስፋ ተጥሎበት የነበረውን የዜጎች ደህነነት የማስጠበቅ እርምጃ መቅኔ አስጥቶት መንግስት ከኤጀንሲ ባለቤቶች ጋር በሌላ አቅጣጫ እየደረገ ያለው ድርድር በስረዓቱ በባለስልጣናት ዘንድ በዚህ ዙሪያ አንድ አቋም  አለመኖሩ  ይነገራል። ከዚህ ቀደም በሁለት ሃገራት መካከል ስምምነትና በቂ ዝግጅት ሳይደረግ በሳውዲ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋ ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ኤጀንሲዎች በየገጠር ከተሞች ተግዘው “ያሉበትን ይዞታ እንዲህ ነው” ብሎ መረጃ መስጠት ቀርቶ፣ የትና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ የሚያውቅ ኤጀንሲም ሆነ የመንግስት ተወካይ በሌለበት መንግስት  ከተጠቀሱት ወንጀለኞች ጋር በዜጎች ህይወት መደራደሩ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
ሰሞኑንን ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠ/ሚ/ር ሐይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው ከደላሎች ጋር እንደማይዋዋል ቢያረጋግጡም እነዚህ ወገኖች በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ሰርገው በመግባት የአንዳንድ ደካማ ባለስልጣናት  እጅ በመጠምዘዝ መንግስት ከደላሎች ጋር እንዲደራደር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። አብዛኛዎቹ የኤጀንሲ ባለቤቶች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጭምር  በጥቅም የተቆራኙ ከመሆናቸውም በላይ ከልማት ማህበራት አንስቶ የኢህአዴግ አባል መሆን የሚያስችላቸውን መታወቂያ ካርድ በመውሰድ በህዝብ ሰም እየማሉ የአዞ እንባ በማንባት ከልካይ በሌለበት እነሱ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት ስርአት ውስጥ በዜጎቻችን ህይወት መክበራቸው ይታወቃል።
በዋንኛነት መቀመጫቸውን ሳውዲ አረቢያ ጅድ እና ሪያድ ከተማ ያደረጉ እነዚህ ወገኖች ከዲፕሎማቱ ጋር ባላቸው የእከክለኝ ልከክለህ ወዳጅነት ሲሻቸው በቆንስላው ቢሮ በመፈንጨት መብቴ ይከበርልኝ ያለውን ዜጋ ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በመፈረጅ ምንም አይነት ስለነሱ ምንም እንዳይተነፍስ በማስፈራራት ሲሻቸው በህገወጥ የሃዋላ ንግድ በፈረጠመው ጡንቻቸው በጠራራ ጸሃይ የሃይል ጥቃት ለመፈጸም ይቃጣቸዋል።  የአሰሪ እና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶችን ያስከፋው ሰሞነኛው የጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም መግለጫ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውሩ በተለይ ወጣቶች የተሳሳተ መረጃ ተስፋ ሰንቀው እዚያ ላይ ተሰማርቼ ማጨድ አለብኝ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑን አውስተው አንዳንድ ሰዎች ይህ ፍልሰት የበዛው ወደ አንዳንድ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚደረገው ጉዞ በመከልከሉ ምክንያት ነው የሚለውን ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመሞገት ዜጎች በህጋዊ መንገድ መጓዝ በአውሮፕላን ሆነ እንጂ ከዚያኛው የሕገወጥ ጉዞ አንደማይሻል  አስረድተዋል። ጠ/ሚ/ሩ በማያያዝ ሃሳብቸውን ሲያጠናክሩ የዜጎች ህይወት በአስተማማኝ መልኩ ሊጠበቅ የሚችለው ከደላሎች ጋር በመደራደር ሳይሆን ከመንግሥታት ጋር ስምምነት ሲኖር ብቻ መሆኑን ደግመው አረጋግጠዋል፡፡
እስካሁን እልባት ባላገኘው የአረብ ሃገር ኮንትራት ሰራተኞች ጉዞ የህይወት ዋስትና ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያቶች በኢህአዴግ ባለስልጣናት ዘንድ የሚሰጠው መግለጫ እርስ በእርሱ የተጣረዘ መሆኑን የሚናገሩ ታዛቢዎች የሰራተኛ እና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲ ባለቤቶች እንደወትሮው ቢሮቻቸውን ከፈተው በዜጎች ንግድ ላይ ለመሰማራት በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ይህ ይጨመር አሊያም ይቀነስ በማለት እየተዋዋሉ ባሉበት ሁኔታ መንግስቴ ከደላሎች ጋር አይደራደረም  የሚለው የጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ ግልጽነት የሌለው እና አብዛኛውን ወገን ግራ ያጋባ መሆኑ ይነገራል።
Ethiopian Hagere Jed Bewadi ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የላኩት
http://www.goolgule.com/conflicting-reply-from-eprdf-about-contract-workers/

No comments:

Post a Comment