FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, April 8, 2015

በስዊድን የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር ራሱን አስተዋወቀ

semayawi sweden
የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ማኅበር በስዊድን ተመስርቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለጽ፤ የድጋፍ ማኅበሩ ቅዳሜ አፕሪል 4 ቀን 2015 ዓ.ም. (ግንቦት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.) ራሱን አስተዋውቋል። በዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ተግባርን ጥሪ ለተደረገላቸው ተሰብሳቢዎች ያስረዱት አቶ ሰለሞን ጌታነህ የድጋፍ ማኅበሩ ሰብሳቢ ናቸው።
አቶ ሰለሞን በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በተደረገው የማስተዋወቁ ሥነሥርዓት ላይ ስለሰማያዊ ፓርቲ ሲያስረዱ፤ ሰማያዊ ፓርቲ በወጣት አባላት የተመሰረተና የሚመራ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ብልጫ ያለው እንደሆነና የወጣቱም ድጋፍ ሰማያዊ ፓርቲን እንዳልተለየው አሳውቀዋል። አያይዘውም ሰማያዊ ፓርቲ የዓላማ ጽናቱ የበረታ በመሆኑና በሀገር ውስጥ የሚያደርገውም እንቅስቃሴ እጅግ የጎላ ስለሆነ ፓርቲውን ሁላችንም መደገፍ ይገባናል ብለዋል።
የፓርቲው አመራሮች
የፓርቲው አመራሮች
በስብሰባው ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን መግለጫውን ከሰሙ በኋላ ልዩ ልዩ ገንቢ ሃሳቦችን ሰጥተዋል። ተሰብሳቢዎቹ ለፓርቲው ከሰጡት ሃሳቦች ውስጥ፣ “ሰማያዊ ፓርቲ በሀገር ቤት እንደሚያደርገው ሁሉ በዚህም የድጋፍ ማኅበሩ ከሌሎች የሰላማዊ ትግል ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር በመገናኘት ራሱን ማዳበር ይገባዋል” የሚለው ይገኝበታል።
ተሰብሳቢዎቹ የመጀመሪያ ጥሪ መሆኑን አስታውሰው በዕለቱ የተገኘው የህዝበ ቁጥር አነስተኛ ነው ተብሎ እንደማይገመት በመግለጽ፣ “ፓርቲው የበለጠ በሰራ ቁጥር ብዙ አባላትና ደጋፊ ማፍራት እንደምትችሉ ካለው ሁኔታ መረዳት ይችላል” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። ስብሰባውን ለመዘገብ በስፍራው የነበረው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጽዋል።
ቀጥሎም ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ዓላማና ሥራ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል ለተሰብሳቢው ቀርቧል። በመጨረሻም የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በስልክ ቀርበው ሰብሳቢዎቹንና ተሰብሳቢውን በማመስገን በሀገር ቤት ያለውን ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክተው፤ በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያቸው አባላትና በሳቸውም ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል የበረታ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ከዚህ የከፋ ችግር ሊገጥመን ቢችልም ፓርቲዬም ሆነ እኔ በጽናት ቆመን ትግሉን እንገፋለን በማለት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስረድተዋል። ከኢንጂነር ይልቃል አጭር የስልክ መልክት በኋላ ስብሰባው ተጠናቋል። 

(ዘጋቢ: ወለላዬ ከስዊድን)

http://www.goolgule.com/semayawi-party-support-group-introduced-in-sweden/

የት ሂዱ ነው?

"ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም"
Prof_Mesfin1
ዓለም ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን “የሙጢኝ!” ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን “የሙጢኝ!” እንላለን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞት ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባሎች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የአያቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

http://www.goolgule.com/i-live-and-die-here-in-my-own-home-land/