“ካልፈረማችሁ ለICC አሳልፈን እንሰጣችኋለን” ሃይለማርያም
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ስምምነቱን የማይፈርሙ ከሆነ ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ለዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (ICC) አሳልፈው እንደሚሰጧቸው መግለጻቸውን በጁባ የጎልጉል ምንጭ አስታወቁ፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ ስምምነቱ የማይፈረም ከሆነ እስር እንደሚጠብቃቸው ሃይለማርያም ለሳልቫ ኪር መናገራቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አርብ የተፈጸመው የስምምነት ፊርማ ገና ሳይደርቅ ሁለቱም ኃይላት ወደ እርስበርስ ውጊያው ተመልሰው በመግባት እየተካሰሱ ነው፡፡
እጅግ ደም አፋሳሽ በሆነውና ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የደቡብ ሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ በፊርማ ሲጸድቅ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ሆኖም ስምምነቱ ከተጽዕኖ ባለፈ መልኩ በዕለቱ በፊርማ ካልጸደቀ ሳልቫ ኪርንም ሆነ ሬክ ማቻርን ሃይለማርያም ደሳለኝ ለዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አሳልፈው እንደሚሰጧቸው የተነገራቸው መሆኑን የጎልጉል ምንጭ ከጁባ አስረድተዋል፡፡ ሳልቫ ኪር ወደ ጁባ ከተመለሱ በኋላ ከካቢኔያቸውና ቅርብ አማካሪዎቻቸው ጋር በተነጋገሩ ወቅት በስምምነቱ ወቅት የነበረውን ሁኔታ ባስረዱበት ወቅት መናገራቸውን የመረጃው አቀባይ ለጎልጉልአስታውቀዋል፡፡ ሁኔታው ለደቡብ ሱዳን እጅግ አሳፋሪ ከመሆኑ የተነሳ ደቡብ ሱዳን አምባሳደሯን ከኢትዮጵያ እስከማስወጣት እንዳሳሰባት ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡
በበርካታ ወንጀሎች የሚጠየቁት ኪርና ማቻር ማስፈራራሪያውን በቀላሉ እንደማይመለከቱት መገመት የሚቻል ሲሆን በሌላ በኩል ኢህአዴግ ወንጀል በመሥራትና በማሰራት አገር ውስጥ የለመደውን የማጠልሸት ዘዴ በጎረቤት አገሮችም ላይ በመጠቀም የበላይነቱን መግለጹ ስምምነቱን “የሰላም ድርድር ወይስ ቁማር?” ተብሎ እንዲጠየቅ የሚያስገድድ መሆኑን አንዳንድ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡
ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ ሳልቫ ኪርን ጠቅሶ እንደዘገበው ስምምነቱ በማስፈራራትና በተጽዕኖ የተካሄደ መሆኑን ዘግቧል፡፡ “ጠ/ሚ/ሩ ለሬክ ሲነግረው ስምምነቱን ዛሬ ሳትፈርሙ ከዚህ አትወጡም ብሎት ነበር ለእኔ ደግሞ ሰነዱን ካልፈረምክ አስርሃለሁ” በማለት አስፈራርተዋቸው እንደነበር ሳልቫ ኪር መናገራቸውን ዘግቧል፡፡ ሳልቫ ኪር ከሬክ ማቻር ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ምንም ዓይነት ውይይት ሳያደርጉ ለፊርማ ብቻ መተያየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የሃይለማርያም ደሳለኝ እውነተኛ ባለሥልጣንነትና ተጽዕኖ አድራጊነት የታየበት ይህ ስምምነት በኢህአዴግ ውስጥ በምን ዓይነት መልኩ እንደሚቀጥል የሚያወያይ እንደሆነ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ አስተያየቱን ከሰጡ መካከል እንዳሉት “ሃይለማርያም ይህንን ማስፈራሪያ ሲሰጡ በአጠገባቸው የነበሩት የህወሃት ባለሥልጣናት እነማን ይሆኑ በማለት በዓይነ ልቦናዬ ሳስብ ነበር፡፡ እነ በረከት፣ ደብረጽዮን፣ … ሳልኳቸው” የሚሉት አስተያየት ሰጪ ሲቀጥሉ “ጠ/ሚ/ሩ በነካ እጃቸው የሕዝብን ድምጽ የሚያፍኑትን፣ ኦሮሞውን በየቦታው እየገደሉ ደሙን የሚጠጡትን፣ አማራውን ለዘመናት ከኖረበት እያፈናቀሉ መሄጃ ያሳጡትን፣ አኙዋኮችን ያረዱትን፣ ኦጋዴኖችን ያጋዩትን፣ ተናገራችሁ፣ ጻፋችሁ በማለት እስርቤት እስኪጠብ ሃሳቡ የገለጸውን ሁሉ ለስቃይና ስደት የዳረጉትን፣ … ወንጀለኞች እንዲሁ ግፋችሁን ካላቆማችሁ ቃሊቲ ወይም ዝዋይ ወይም … እወረውርሃለሁ ብለው አንዴ እንኳን በማስፈራራት ጠ/ሚ/ር መሆናቸውን ቢያሳዩን ብዬ ተመኘሁ” ብለዋል፡፡
በተጽዕኖና ማስፈራሪያ የተፈረመው የደቡብ ሱዳን ስምምነት ፊርማ ገና ሳደርቅ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ አቁሙን ጥሰው ፍልሚያቸውን ቀጥለዋል፡፡ እርስበርስም እየተካሰሱ ይገኛሉ፡፡ እሁድ ዕለት የሳልቫ ኪር ኃይሎች በከባድ መሣሪያ የታገዘ የምድር ጥቃት እንደሰነዘሩባቸው የማቻር ኃይሎች ይናገራሉ፡፡ የኪር መንግሥት በበኩሉ ማቻር ስምምነቱን ላለመፈረም በመፈለግ ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረ ነው በማለት ዶ/ር ሬክ ማቻርን ይከስሳሉ፡፡
ማቆሚያ የሌለው የሚመስለውና እስካሁን በሺዎች የሚቀቆጠር ህይወትን የቀጠፈውና ለ1.2 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት ወደ ሰላም የመድረሱ ምኞት እየራቀ የሄደ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ ማስፈራሪያ፣ ዛቻ፣ ቁማር፣ … ቢጠቀምም ህልሙ ቅዠት ሆኖበታል፡፡
http://www.goolgule.com/south-sudan-peace-deal-signed-under-pressure/
No comments:
Post a Comment