አገዛዙ ሰሞኑን በቅርብ ጊዜ ታሪኩ የከፋ የተለዩ ድምጾችን ያለመታገስ ባህርይ አሳይቷል፡፡ ስድስት የዞን ናይን ብሎገሮችን እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ታምራትን በአንድ ወገን፣ የሠማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ቀስቃሾችን በሌላ ወገን ሰብስቦ ከማይሞላው ማጎሪያው ከቷቸዋል፡፡ በፕሬስ ላይ የሚደረግ አፈና እና በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርስ ውክቢያ ከስርዓቱ የሚጠበቁ ባህርያትነት አልፈው የማንነቱ መገለጫ በመሆናቸው እርምጃው ብዙም ግርምትን አልፈጠረም፡፡
ይሁን እንጂ ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ በነፃ ሐሳብ አቀንቃኞችና በተቃዋሚዎች ላይ ይህን መሠል መጠነ-ሰፊ የእስር እርምጃ ሲወሰድ ይህ በከፍተኝነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገዛዝ ዘመን ይህን መሳይ እርምጃዎች የተለመዱ የነበሩ ቢሆንም የአፈጻጸም ስልታቸው የተለየ መሆኑ ስለገዢው ፓርቲ ወቅታዊ ውስጣዊ የፓወር ዳይናሚክስ ጥቂት የሚያስገነዝበን ነገሮች አሉት፡፡
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገዛዝ ዘመን ይህን መሠል የማወከብ ዘመቻ ለማድረግ ሲወሰን አስቀድሞ ዋነኛው ሰውዬ ወደ ምክር ቤታቸው ሪፖርት በማቅረብ ሰበብ ቀርበው አሊያም ወደ ሚዲያ አውታሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በመስጠት ሰበብ ብቅ ብለው አሰልቺውን “የህገ-መንግስታዊና ኢ-ህገመስታዊነት” ማብራሪያ ካቀረቡ በኋላ መንግስታቸው ስለአንዳንድ ተቃዋሚዎችና የነጻ ሚዲያ አባላት ኢ-ህገመስታዊ እንቅስቃሴ “አንድ ቶን መረጃ” እንዳለውና መንግስት ወደ እርምጃ ከመግባቱ በፊት “የጥፋት ዕጆቻቸውን እንዲሰበስቡ” በሃይለ ቃል የታጀበ ማስጠንቀቂያ ያሰማሉ፡፡ የዚህ ስልት ዋነኛ ዓላማ ህዝቡንና ዓለማቀፍ ማኅበረሰቡን ለቀጣዩ እርምጃ ማዘጋጀት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በማስጠንቀቂያው ተደናግጦ ስደትን ወይም አፉን ለጉሞ መቀመጥን ምርጫው የሚያደርግ ተቃዋሚ ወይም የነፃ ፕሬስ አባል ካለ ከጨዋታው ሜዳ ገልል እንዲል ማድረግም በሁለተኛ ደረጃ ዓላማነት ይቀመጣል፡፡
የሰሞኑ ፀረ-ተቃዋሚ እና ነፃ ሐሳብ ዘመቻ ግን በአፈፀፀም ስልቱ ለየት ይላል፡፡ ከእርምጃው ሁለት ቀናት በፊት በምክር ቤታቸው የተገኙት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በወቅቱ ያቀረቡት ሪፖርት “ከወትሮው የተቃዋሚዎች ውንጀላ ነፃ ስለመሆኑ” ከብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ከተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ ሙገሳ የተቸረው ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አንዳችም አሁን የተወሰደውን እርምጃ መምጣት የሚያመላክት ስሜታዊም ሆነ ቃላዊ ምልክት አላሳዩም፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ሪፖርት ሁለት ቀናት በኋላ ግን የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ስርዓቱ እጅግ የጠበበውን የፖለቲካም ሆነ የሚዲያ ምህዳር የማስፋት አንዳችም ፍላጎትም ሆነ ተነሳሽነት እንደሌለው በአደባባይ አሳየ፡፡
እዚህ ላይ የሚነሳው ዋነኛ ጥያቄ ግን ከወትሮው በተለየ ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው መጪውን እርምጃ አመላካች አንዳችም ፍንጭ እንዴት ሳያሳዩ ቀሩ? የሚለው ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው የስልት ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት ይህን መሳይ የስልት ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልግበት አንዳችም ምክንያት መመልከት አይቻልም፡፡
ይልቁንም ሚዛን የሚደፋው፣ ጠ/ሚኒስትሩ ይህን መሳይ ዋነኛ ውሳኔ ከሚያሳልፈው እውነተኛው (De facto) የአገዛዙ የአመራር ክበብ (leadership circle) ውጪ መሆናቸውን ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከቀዳሚያቸው በተለየ ከመጋረጃ ጀርባ ዋነኛ ውሳኔ ለሚያስተላልፈው የአመራር ክበብ ውሳኔዎች ቅቡልነት ከማስገኘትና ውጫዊ የስልጣን ስርጭት ምስል ከመፍጠር ባሻገር ሁነኛ ውሳኔዎችን በግላቸው፣ አሊያም ከሌሎች ጋር ለማሳለፍ የማይችሉ ከመሆናቸውም ባሻገር በአገዛዙ ጠረጴዛ ላይ ያሉትን አጀንዳዎች ምንነት በተመለከተም ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ክስተቱ አስገንዝቦን አልፏል፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/12013/
No comments:
Post a Comment