FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, December 31, 2013

በ”ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ”ና በሁለት ተጨማሪ መጽሀፎች ላይ የቀረበ አጭር አስተያየት

ፋሲል የኔዓለም

በፖለቲካው ዓለም ጉልህ ስፍራ ያላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የጻፉትን አዲስ መጽሃፍ ያነበብኩት ዘግይቼ ነው ፤ ለመዘግየቴ ሶስት መሰራታዊ ምክንያቶች ነበሩኝ፣ አንዱና ዋናው ዶ/ሩ በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አመለካከት በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ስላቀረቡ በመጽሀፉ ውስጥ እምብዛም አዲስ ነገር ያቀርባሉ የሚል እምነት ስላልነበረኝ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዶ/ሩ ራሳቸው በከፊል የጠቀሱት ነው፣ “ በአገሪቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለ የተቃዋሚ ድርጅት አመራር አባል መሆኑን ሲመለከት፣ ከቅንጦትም ባሻገር በተወሰነ ደረጃ “ የስራ ፈትነት” ወይንም የበለጠ ጠርጣራ ( cynic) ለሆነ ሰው “ በተግባር ስራ ለመስራት ካለመቻል “ የመጣ፤ ተግባራዊ ድክመትን ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ ሊመስል ይችላል” የሚለው ነው። ሶስተኛው ምክንያቴ ደግሞ ፣ ፋሽን በሚመስል መልኩ በአገር ቤት የሚኖሩ ፖለቲከኞች በተከታታይ መጽሃፎችን በማሳተማቸው ለእነሱ ቅድሚያ ለመስጠት በመፈለግ ነው።Ethiopian books review
ዶ/ር ብርሃኑን ያነበብኩት ሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች -ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ” እንዲሁም ኢ/ር ሃይሉ ሻውል “ ሕይወቴ እና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚሉ ርዕሶች ያሳተሙዋቸውን መጽሃፎች ካነበብኩ በሁዋላ በመሆኑ፣ በሶስቱም ስራዎች ላይ መጠነኛ ንጽጽር ለማድረግ አስችሎኛል።
ዶ/ር መረራ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ዛሬ ያለውን የአገራችንን ፖለቲካ ግሩም በሆነ መንገድ አቅርበዋል፤ መጽሃፉ ብዙ አስቂኝ ገጠመኞች የተካተቱበት በመሆኑ ፣ በቋንቋና በዓርትዖት በኩል የሚታይበትን ጉልህ ችግር አይተን እንዳላየን እንድናልፈው ያስገድደናል። መጽሀፉ በጥሩ ዓርታዒ እንደገና ቢታረምና ቢታተም “ የተዋጣላቸው” ከሚባሉት የአገራችን መጽሀፎች ተርታ የመመደቡ እድል ከፍተኛ ነው። ዶ/ር መረራ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ የመጣውን፣ በ1960ዎቹ ተዘርቶ በእነ አቶ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ተኮትኮቶ ያደገውን የብሄር ፖለቲካ መነሻ ፣ ያመጣውን ግሳንግስ እና የግሳንግሱን ማራገፊያ መፍትሄ አስቀምጠዋል። መፍትሄ ብለው ያስቀመጡትም በመጽሀፉ የመጨረሻ ገጽ እንደሚከተለው ሰፍሯል፣ “ …ለታሪክም ለህዝብም አስቀምጬ (ማለፍ) የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ ፣ አብዛኛው የትግራይ ሊሂቃን “ ስልጣን ወይም ሞት” ብሎ ስልጣን ላይ የሙጥኝ እስካለ ድረስ ፣ አብዛኛው የአማራ ሊህቃን በአጼዎች ዘመን የነበረውን የበላይነትን መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፣ ብዙሃኑ የኦሮሞ ሊህቃን ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተወ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠና የምትወጣ አይመስለኝም። በሌላ ቋንቋ ለነዚህ መሰረታዊ በሽታዎቻችን መድሃኒት እስካላገኘን ድረስ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ፈጽሞ የምታገኝ አይመስለኝም።” ( ገጽ 264)። ምንም እንኳ “አብዛኛው” የሚለው ቃል አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል ቢሰማኝም ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው ሳላስታውስ አላልፍም፤ በተለይ” እነዚህ የሶስቱ ብሄሮች ሊህቃን ህልማቸውን እንዲተው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለው ጥያቄ ለእኔ ቁልፍ ይመስለኛል። ዶ/ር መረራ በዚህ ዙሪያ የተብራራ መልስ ቢሰጡ ኖሮ መጽሃፋቸውን የበለጠ ሙሉ ማደረግ ይችሉ ነበር እላለሁ።
የኢንጂነር ሃይሉ መጽሀፍ የአገራችንን የፖለቲካ ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋይ ያያዘው በመሆኑ ብዙም ክብደት የሚሰጠው ሆኖ አላገኘሁትም፤ ንድፈሃሳባዊ ትንተናዎች ይጎድሉታል፣ የተዓማኒነት ችግሮችም አሉበት( በተለይ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ስለነበረው የሽምግልና ሂደትና ከዚያ በሁዋላ ስለተፈጠሩት ኩነቶች) ፤ ለተተኪው ትውልድ የሚሰጠው ትምህርት ስለመኖሩም በእጅጉ እጠራጠራለሁ፤ በእርግጥ ኢ/ር ሃይሉ ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው እስካሁን በህይወት ለመቆየት መቻላቸው እድለኛ ሰው እንደሆኑ በመጽሃፋ ለማየት ችለናል፣ አገራቸውን የሚወዱ ሰው መሆናቸውንም አስገንዝቦናል። ኢ/ር ሃይሉ የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን መንገድ በመከተል መጽሀፉን በሌላ ሰው በማስጻፋቸው ስለጸሃፊነት ችሎታቸው አስተያየት ለመስጠት አያስችልም ።
የዶ/ር ብርሀኑ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” የሚለው ርዕስ ዘጊ ወይም ለማንበብ የማይጋብዝ ነው፤ በትምህርቱ አለም የዘለቁና የጥናትና ምርምር ወረቀቶችን ለማንበብ ፍላጎት ያላቸው ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር፣ እንደ እኔ አይነቱ ተራ አንባቢ በርዕሱ ማልሎ መጽሀፉን ለማንበብ ስለመነሳሳቱ እጠራጠራለሁ። መጽሀፉ ውጫዊ ገጽታው ባያማልልም ውስጣዊ ይዘቱ ግን ድንቅ ነው። እንደምንም የጀመርኩትን መጽሀፍ እየተጨነቁና እየፈራሁ፣ እያዘንኩና ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ፣ እግረ-መንገዴንም የጸፊውን እይታ፣ የትንታኔ እና የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታ እያደነቁኩ ጨርሸዋለሁ። መጽሀፉን እንደጨረስኩ የተናደድኩበት ነገር ቢኖር ጻሃፊው የኢትዮጵያን ችግሮች እንዲያ አድርገው ካቀረቡ በሁዋላ መፍትሄውን በይደር በመተዋቸው ነው።
ከዚህ ቀደም የአገራችንን ሁለተናዊ ችግሮች ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የተፈጥሮና የህዝብ ብዛትን በአንድነት አጣምሮ፣ በአገራችን ህልውና ላይ የደቀኑትን ፈተናዎች ቅልብጭ አድርጎ ያሳየ ከገብረህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሁዋላ የተጻፈ መጽሀፍ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ ይህን ስል ሌሎች ድንቅ የፖለቲካ መጽሃፎች አልተጻፉም እያልኩ አይደለም፤ የዶ/ር ብርሃኑን መጽሀፍ ለየት የሚያደርገው የተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችን ለይተው በማውጣት እርስበርስ ያላቸውን ትስስር ከግሩም ትንተና ጋር ሁሉም ሊረዳውና ሊጠቀምበት በሚችለው መንገድ ማቅረባቸው ነው ። (የምጣኔ ሀብት ትምህርት ( economics) የማይገባው ሰው እንኳ ቢሆን፣ መጽሀፉን አንብቦ ስለአገራችን ኢኮኖሚ ለመረዳት አይሳነውም።) መጽሃፉ የባራክ ኦባማን The Audacity of Hope እንዳስታወሰኝ ብገልጽ ያጋነንኩ አይመስለኝም፣ አጋነኸዋል የምትሉኝ ካላችሁም ” አንብቡትና ሞግቱኝ።
የዚህ መጽሀፍ ትልቁ መልእክት፣ ለእኔ እንደገባኝ፣ “የአገራችን ችግር ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት ይፈታል” የሚለው አስተሳሰብ እንደሚታሰበው ቀላል አለመሆኑንና ከአሁኑ መፍትሄ ካልተበጀለት በሁዋላ ላይ ይዞት የሚመጣው ችግር ቀላል አለመሆኑን ማሳየት ነው ። የብሄር ፖለቲካው በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ፣ በአገራችን ልማትን ለማምጣት የሚገጥሙ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ችግሮች፣ ከአካባቢ ውድመትና ከህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ በመጽሀፉ በዝርዝር ቀርቧል። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየታየ ያለውን የገቢ አለመመጣጠንም 1500 ብር የሚያወጣውን የአንድ መለኪያ ውስኪ ግብዣ በምሳሌነት በማንሳት በደቡብ አፍሪካ እንደታየው በአገራችንም ለወደፊቱ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ጣጣ ጸሀፊው በደንብ አሳይተውናል።
መጽሀፉ የውጩ ፖለቲካ በአገራችን ፖለቲካ ላይ የሚያሳርፈውን ተጽዕኖ እንዲሁም የአለማቀፉ የንግድ ስርዓት በኢትዮጵያ እድገት ላይ ያለውን ተጽእኖ ቢያካትት ኖሮ የበለጠ ድንቅ ይሆን እንደነበር አስባለሁ ። ከዚያ በተረፈ ግን መፍትሄዎቹ በሌላ ክፍል እንደሚቀርቡ መገለጹ በመጽሀፉ ላይ በቂ ክርክር እንዳይነሳ ያደረገው ይመስለኛል። በመጽሀፉ በቀረቡት ችግሮች እና ትንተናዎች ላይ ተቃውሞ የሚኖረው ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፣ ተቃውሞ የሚነሳው ችግሮችን ለመፍታት በሚቀርቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ እንደሚሆን በመገመት ቀጣዩ መጽሃፍ አወያይ ( አካራካሪ) ይሆናል እላለሁ።
ስለአገራቸው እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ሁሉ መጽሀፉን እንዲያነቡት እመክራለሁ ( የዶ/ር መረራንም ጨምሮ)። በተለይ በሰላማዊው የትግል ሜዳ ለመፋለም የሚያስቡ ጀማሪም ሆኑ ነባር ፖለቲከኞች የብርሀኑን መጽሀፍ በማንበብና በምርጫ ክርክር ወቅት ይዞ በመቅረብ ( የመፍትሄው መጽሀፍ ቶሎ እንደሚደረስ በመገመት) ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፤ ስልጣኑን ይረከባሉ ብዬ ባላስብም።

Monday, December 30, 2013

በጀግኖች አባቶቻችን ደም የተቦካው ሉአላዊ ግዛታችን ላይ የሚደረገውን ስውር ሴራ ያለማወላወል በፅናት እንታገለዋለን (ሰማያዊ ፓርቲ)

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. (December 30, 2013)
የኢትዮጵያንና የሱዳንን ድንበር የማካለሉ ሥራ ከመስከረም 29 ቀን 2002 ዓ.ም. (October 9, 2009) ጀምሮ እየተከናወነ እንደሆነ፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው ዕለታዊ የሱዳን ጋዜጣ ሱዳን ትሪቢውን (Sudan Tribune) በመስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም. (September 18, 2009) መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ጉዳይ ያንገበገባቸው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩት ዜጎቻችንም ራሳቸውን በተለያዩ “ኮሚቴዎች” እና “ግብረ ሃይሎች” በማደራጀት ለጉዳዩ ክፈተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ፓርቲያችን (ሰማያዊ)፣ ለነዚህ ሀገር ወዳድ ዜጎች ያለውን ከፍተኛ አክብሮት ለመግለጽ ይወዳል፡፡Statement from Semayawi party of Ethiopia, regarding Nile issue.
ሆኖም፣ የነዚህን ሀገር ወዳድ ዜጎችና አፍቃሪ-ኢትዮጵያውያን ጥሪና መግለጫዎች ከቁብም ካለመቁጠር፣ በሥልጣን ላይ ያለው የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ሥውር የሥልጣን ማራዘሚያ ደባዎችን እየሸረበ እንደሚገኝ አጋልጠዋል። ወያኔ ራሱ ያቋቋመው “የኢትዮጵያና የሱዳን ድንበር ኮሚቴ” አባላት ራሳቸው በተለያዩ ቃለ-ምልልሶች እንዳጋለጡት፣ ወያኔ በአባቶቻችን ደም ተላቁጦ ለተቦካውና የበርካታ ሰማዕታትን ህይወት ላስከፈለው የኢትዮጵያ ድንበርና የግዛት ሉዓላዊነት ግዴለሽነቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያንም ሉዓላዊ ግዛትና ድንበር “በጫካ ውሎችና ስምምነቶች” እያመካኘ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ መስጠቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
ይህንንም ከፍተኛ የሆነ የሃገር ክህደትና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ለማስተባበል በመገንዘብ፣ የወያኔ-ኢህአዲግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ-ገጹ ላይ በመስከረም 2002 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አንድ የማደናገሪያ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ከዚህም የማደናገሪያ መግለጫ ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት(3) አበይት ጉዳዮች መገንዘብ ይቻላል። እነርሱም፦
1ኛ. የኢትዮጵያና ሱዳን የፖለቲካ ኮሚቴ (Ethio-Sudan Political Committee) ተብሎ የሚጠራ ከፍተኛ አካል መኖሩንና የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚቴም (Ethio-Sudan Joint Boundary Committee) በፖለቲካው ኮሚቴ ሥር እንደሚሠራ አረጋግጧል፤ የዚህ የኮሚቴ መዋቀርና የአሰራር ሂደቱም ለረጅም ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አይንና ተደብቆ የቆየ እንደሆነና፣ ወያኔ-ኢህአዲግም በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ክትትል መጋለጡን ሲያውቅ ተጨንቆ ያወጣው ምስጢር ነበር።
2ኛ. የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚቴም (Ethio-Sudan Joint Boundary Committee) ከጥቅምት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. (October 15, 2009) እስከ ግንቦት 2002 ዓ.ም.(May 2010) ድረስ የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርንና አካባቢውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይስና ቅኝት እንደሚያደርግም ገልጾ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ወያኔ ሲጋለጥ ያወጣው ሌላው ምስጢር ሲሆን፣ (ሱዳን ትሪቢውን ያወጣውን ዜና የሚያጎለምስ) እና የሱዳን ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ድንበሩን ለማካለል የሚያደርገውን ዝግጅት የሚያስተጋባ ነው።
3ኛ. የድንበር ክለላው ከግንቦት 2002 ዓ.ም. ( May 2010) በኋላ እንደሚደረግና ከዚህም ጋር አያይዞ ወያኔ-ኢህአዲግ ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት አምነው የተቀበሉት የድንበር ክልል እንዳለ አስምስሎ ለማቅረብም ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በመሆኑም፣ ወያኔ-ኢህአዲግ አሁን የሚያካሂደው “የድንበር-ክለላ ሂደት” ዳግም ድንበርን የመከለል ተግባር ( re-demarcation ) እንደሆነ መግለጹ ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ ይህ ማደናገሪያና ተራ ልፈፋ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማወናበድና ግዛቱን በጫካ ውሎችና ስምምነቶች አማካይነት አሳልፎ ከመስጠት የዘለለ ኢምንት እውነታ የለውም፡፡ ይሄንን በተመለከተም ያጠኑት ሊቃውንትንና በግዛቱ ላይ የሚኖሩትን ዜጎች ምስክርነት ሊያገኝ አልቻለም፤ አይችልምም፡፡
የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት “ያለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት የተቀበሉት የድንበር ክልል” የሚለው ሀተታ፤ ሜጀር (ሻለቃ) ጉዊን የተባለው የእንግሊዝ ጦር መኮንን በ1902 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) “አስምሬአለሁ” የሚለውን የወሰን ክልል ነው። ይሁንና አንድ በእንግሊዝ የቅኝ-ገዥነት አባዜ የሰከረ ሻለቃ ያሰመረውን መስመር መሠረት አድርጎ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ሉዓላዊነትን የወያኔ-ኢህአዲግ ገዢ ቡድን “ለሱዳን ይገባታል” ብሎ መሟገቱ የፖለቲካ ቅጥፈት እንጂ ታሪካዊ ማስረጃ የለውም፡፡ የሚከተሉትም ታሪካዊ ዳራዎች የወያኔን ሙግት ውድቅ ያደርጉታል፦
1ኛ.ሻለቃ ጉዊን መሬቱን አካልያለሁ ሲልና በወረቀት ሲያሰምር፤ በኢትዮጵያ በኩል አንድም ተወካይ ስለአልነበረ የጉዊን የድንበር ማካለል ተግባር ከቅኝ ገዢዎች ማንአለብኝነት ተለይቶ የማይታይና የውል አፈጻጸም ሥርዓት የማይከተል በመሆኑ የተነሳ ተቀባይነት የለውም፡፡
2ኛ. የ1896 ዓ.ም.(እ.አ.አ.) የአድዋ ጦርነት ድል በቅኝ ገዥዎች ላይ በፈጠረው ከፍተኛ መደናገጥ ምክንያት 1902 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) አካባቢ እንግሊዝና ጣሊያን በጋራ በመመሳጠር የሰሜንና የምዕራብ ኢትዮጵያን ድንበር ለመግፋት የፈፀሙት ሴራ ስለሆነ፣ የሻለቃ ጉዊን ተልዕኮም ከዚያ ሴራ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ ስለሆነም ተቀባይነት የለውም፡፡
3ኛ. ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በፊትም ይሁን ከዚያ በኋላ፣ ይህ ሻለቃ ጉዊን ከለለው የሚባለው መሬት ምን ጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያ ይዞታ ውጭ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይባስ ብሎም፣ በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ግዛት አሁን ሱዳን ተብሎ ከሚጠራው ሃገር በጣም ወደ ውስጥ የገባ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ የግዛት ጥያቄ ሲነሳ የይገባኛል ታሪካዊ መሠረት ያላት ኢትዮጵያ መሆኗን ለማስተባበል አዳጋች ነው፡፡
4.አሁን የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት በመጋቢት 22/2006 ዓ.ም ገደማ March 30, 2014 ለሱዳን ለመስጠት ቅድመ-ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ግልጽነትና ተጠያቂነትን መርሆው ያላደረገው የወያኔ-ኢህአዲግ መንግሥት ግን አንዳችም መረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያገኝ የተለመደ አፈናውን ገፍቶበታል፡፡ በመሆኑም፣ በእልፍ-አዕላፍ ድንበር ጠባቂ ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት ተጠብቆ የኖረውን ዳር ድንበር፣ ወያኔ በተለመደ “የደጃዝማቾች ፈረስ መጠጫና ጉግዝ መጫወቻ ነው” በሚል ንፍገት አሳልፎ ለሱዳን ሊሰጠው ተዘጋጅቷል፡፡ ይህ የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሰፊ ውሃ-ገብና ለም ሉዓላዊ መሬት፣ የታሪክ ማስረጃዎችንና የኢትዮጵያውያንን መስዋዕትነት በማናናቅ ለባዕዳን ሊሠጥ አይችልም፡፡
ስለዚህ ከላይ በተጠቀሱት ማስረጃዎችና በዓለም-አቀፍ የአሠራር ደንብ መሠረት፤ ወያኔ-ኢህአዲግ ከሱዳን ጋር የሚያደርገው የድንበር ክለላ ስምምነት ህገ-ወጥ ነው። ከዚህም ባሻገር፤ ከዋናው ባለጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በስተጀርባ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት ይሁን የድንበር ክለላ ተግባር ምንም ዓይነት ተቀባይነት አይኖረውም።
ከዚህም ሌላ፣ ወያኔ-ኢህአዲግ የተወሰኑ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት ቆርሶ በመስጠት ሥልጣኑን በጎረቤት አገር ሱዳን ለማስባረክ ብሎ የሚያደርገው ሽር-ጉድ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ውጤቱም “ታግዬላቸዋለሁ የሚላቸውን ብሄሮችና ብሔረሰቦች” ከማዳከምና ብሎም ለማፈራረስ የተጠቀመበተ ዘዴ የቅኝ ገዢዎች ለራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ ያሰመሩትን የድንበር መስመር በመቀበልና የቅኝ ገዢ ጠበብትን እንደ ምስክር በመጠቀም ነው። ይህም ተግባሩ፣ቀድሞውንም በቋፍ የነበረውን የወያኔ-ኢህአዲግን መንግሥት የፖለቲካ ቅቡልነት የሚያሳጣው መሆኑን ለማስታወስ እንፈልጋለን፡፡ አልፎ-ተርፎም በዚህ ተግባሩም ዛሬም የቅጥረኛ ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ህዝቡ እንዲያውቀው እንፈልጋለን፡፡
ይህ የወያኔ-ኢህአዲግ ገዢ ቡድን ተግባር የሃገራችን ኢትዮጵያን ዓለም-አቀፍአዊ ክብር የሚጎዳ ስለሆነ ከተግባሩ እንዲታቀብ እናሳስባለን፡፡ በተጨማሪም፣ ለጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ ዝርዝር መረጃና ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበትም ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ይህን ሳያደርግ ቢቀር ግን፣ ፓርቲያችን የተጣለበትን የአባቶቻችንን ክብርና የሀገራችንን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት መቼም ቢሆን ያለምንም ማወላወል የምንወጣ መሆናችንን ለጉዳዩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ኅዝብ በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡
ሰላም፣ ተስፋ፣ ፍትህና እኩልነት በዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በተከበሩባት ኢትዮጵያ ዕውን ይሆናል!!!

በአዲስ አበባ የቅርብ ጊዜ የጅምላ መቃብር ተገኘ

ሁኔ አቢሲኒያዊ

ነገሩ የተከሰተው አርብ እና ቅዳሜ እለት ነው ከስድት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የጃንሜዳ ጦር ካምፕ(በቀድሞ ስሙ ሦስተኛ ሻለቃ) ግቢ ውስጥ በትንሹ ወደ 6 የሚጠጉ አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተገኝተዋል! አስከሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት ለመንገድ ስራ የጦር ካምፑ ግቢ አጥር ወደ ውስጥ ፈርሶ መቆፈር ነበረበት፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ነው እንግዲህ በስካቫተር ሲቆፈር በመጀመሪያ ሁለት አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተንከባለሉ፡፡ በዚህ የተደናገጡት ሰራተኞች ለጊዜው ስራቸን ያቋረጡ ሲሆን በበነጋው ቅዳሜ እለት ረፋዱ ላይ በሌላ አቅጣጫ ቁፋሮ ሲያደርጉ በዛም በኩል እዲሁ በብርድ ልብስ የተጠቀለሉ አራት አስከሬኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ከአፈሩ ዉስጥ ተገኙ፡፡A mass grave in Addis Ababa, Ethiopia
በዚህ መሃል ከጦር ካምፑ አካባቢ የተወሰኑ መኮንኖችና ከፍተኛ ማዕረግ(ጄነራሎች)በትከሻቸው ላይ ያለባቸው ሰዎች ወደ ቦታው በመምጣት ስራው እንዲቆም ትእዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን በአካባቢው የነበረውንም ሰው ከቦታው አባረው በትነዋል፡፡ በስፋራው ተገኝተው ሁኔታውን ሲከታተሉ እና በስራው ላይም ተሳታፊ የነበሩ ለሰማያዊ ፓርቲ ቅርብ የነበሩ ሰዎች ፎቶ ለማንሳት ጥረት ቢያደርጉም በወታደሮቹ ተመናጭቀዉ ክልከላ ደርሶባቸዋል፡፡ እንደምንጮቻችን እና የምስል ማስረጃዎች ከሆነ አስከሬኖቹ የተጠቀለሉበት ብርድልብስ አንዳችም ሳይቀደድና ሳይበሰብስ ከነአዲስነቱ መገኘቱ ጅምላ ግድያው በቅርቡ የተፈፀመ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬን አሳድሯል! በጉዳዩ ላይ ማጣራት ለማድረግ ሙከራ ያደረጉት የሰማያዊ ፓርቲ አባሎችንም ፊት እንደተነሳቸውና ለማናገርም ፈቃደኛ የሆነ ሰው አለማግኘታቸዉንም እንዳዉም ቦታውን ባስቸኳይ እንዲለቁ ከሀይለ ቃል ጋር መታዘዛቸውንም ጨምረውተናግረዋል፡፡
ከወታደሮቹ መሀከል የሆነ አንድ ስምና ሀላፊነቱ ለጊዜው ያልታወቀ ምናልባትም የግቢው አዛዥ ሊሆን የሚችል ሰው ይህ ግቢ ሶስት ስርዓቶችን ያገለገለ በመሆኑ የማናቸው እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም ሰዎች በመሆናቸው ክቡር ናቸውና አፈር አልብሷቸው ብሎ ትእዛዝ ሲሰጥ የሰሙ የአይን ምስክሮች ለምንጫችን ስለሁኔታው አስረድተዋል! በሁኔታው በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በእጅጉ ያዘኑና የተደናገጡ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላትና መንግስት ይህን ጉዳይ አጣርተው ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አስተያየት ሲሰጡም ተደምጠዋል! በአሁኑ ሰዓት በስፍራው ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ አካባቢውም በቆርቆሮ ተከልሏል፡፡
ተጨማሪ ብርድልብሱ ደብረ ብርሃን ሲሆን ዲዛይኑ በኢህአዲግ ዘመን በቅርብ የተጀመረው ነው!
ሁኔ አቢሲኒያዊ
ከፒተርቦሮው ዩ.ኬ

Sunday, December 29, 2013

ከቴዲ አፍሮ የተሰጠ መግለጫ “ለሙዚቃ አፍቃሪዎቼ በሙሉ”


Ethiopian Artist Teddy Afroከጥቂት ሳምንት በፊት የዳግማዊ ሚኒሊክን መቶኛ አመት የሞት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ በእንቁ መጽሔት ተጋብዤ ቃለ ምልልስ አድርጌአለሁኝ። ይኸዉ ዉይይታችን በ “አመጣጡን ያየ አካሄዱን ያዉቃል” እርዕስ ስር ለህዝብ እንደቀረበ አዉቃለሁ። ከዚህ ዉጪ እኔ በማላዉቀዉ ሁኔታ መጽሔቱ በሰራዉ ስህተት ፎቶዬን በሌላ አነጋገር አጅቦ ያወጣዉን ከኔ እምነትም ሆን ጉዞ ጋር የሚራመድ ጉዳይ አይደለም። ይህንኑ ለማረጋገጥ “አመጣጡን ያየ አካሄዱን ያዉቃል” በሚል ርዕስ ስር በወጣዉ መጽሔት መልክቶቼን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል። ያም ሆኖ መጽሔቱ በሰራዉ ስህተት እርምት አድርጎ ይቅርታም ጠይቆናል። ጉዞዬ የፍቅር የአንድነት እና የይቅር ባይነት ነዉና ይህንንም ጉዳይ በዚሁ ስሜት ውስጥ እናስተናግደዋለን።
ፍቅር ያሽንፋል
ቴዎድሮስ ካሳሁን


Friday, December 27, 2013

የጁነዲን ባለቤት በድርድር ተፈቱ !!/ከኢየሩሳሌም አርአያ/

የቀድሞ የኦህዴድ/ኢህአዴግ አመራር አባልና ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት በውስጥ በተደረገ ድርድር ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን የቅርብ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ገለጹ። « ከሳኡዲ ኤንባሲ ገንዘብ ተቀብለው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል» በሚል በሽብርተኝነት ወንጀል እንዲከሰሱ የተደረጉትና ለአንድ አመት የታሰሩት የአቶ ጁነዲን ባለቤት ወ/ሮ ሃቢባ መሐመድ ከሕወሐት መሪዎች በተላለፈ ቀጭን ትእዛዝ እንዲፈቱ መደረጉን የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም ይህ ሊሆን የቻለው በስደት ከሚገኙት አቶ ጁነዲን ሳዶ ጋር በተደረገ ምስጢራዊ ድርድር ላይ “መንግስት ከዚህ ቀደም በወሰዳቸው እርምጃዎች፣ ፖለቲካዊ ምስጢራዊ ጉዳዮችና ገዢውን ፓርቲ የሚመለከቱ ማንኛውም ነገሮች በየትኛውም ቦታ ላለማጋለጥ፣ ላለመናገር፣..” ከጁነዲን ጋር ከስምምነት ከደረሱ በኋላ ባለቤታቸው እንዲፈቱ መደረጉን አስታውቀዋል። በሙስና የተጨማለቁት አባዱላ ገመዳ እንዲሁም ደ/ፂዮንና ፀጋዬ በርሄ ከጁነዲን ጋር እንደተደራደሩ ምንጮቹ አያይዘው ገልፀዋል። መጀመሪያም ወ/ሮ ሃቢባ የሰሩት ወንጀል ኖሮ አይደለም የታሰሩት ያሉት ምንጮቹ አቶ ጁነዲን ከስልጣን ለማንሳት ሲባል ብቻ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል። ጁነዲን ባለቤታቸው ከታሰሩ በኋላ በስልጣን ላይ እያሉ እንዲያውም ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ሚሚ ስብሃቱ በምታዘጋጀው ራዲዮ ጣቢያ « ጁነዲን መታሰር አለባቸው፤ መንግስት እስከ አሁን እርምጃ የማይወስደው ምንድነው?..ባለቤታቸው አሸባሪ ናት» በማለት የፍ/ቤትን ነፃነት ጭምር በሚጋፋ መልኩ ቅስቀሳ ይካሄድ እንደነበረ ምንጮቹ አስታውሰዋል። 
አቶ ጁነዲን ከአገር ከወጡ በኋላ እውነቱን እያወቁ መደራደራቸውና ባለቤታቸውን በማስፈታት ሌሎች ንጹሃን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች ላይ በተዘዋዋሪ በመፍረድ የኢህአዴግና ካንጋሮው ፍ/ቤት ተባባሪ መሆናቸው አሳዛኝ ነው ብለዋል ምንጮቹ። አቶ ጁነዲን ምናልባትም « ባለቤቴ በፍ/ቤት ነፃ ተባለች» በሚል በኢትዮጲያ የፍትህና የፍ/ቤት ነፃነት እንዳለ አስመስለው ሊናገሩ እንደሚችሉ ማረጋገጫ የለም ያሉት ምንጮቹ አክለውም ጁነዲን ምንም አሉ ምን በስልጣን እያሉ ለፈፀሙት ወንጀል መጠየቃቸው እንደማይቀር መታወቅ አለበት ብለዋል።
source: www.harartubes.com

በከፊቾ ዞን የጽላት ዝርፊያና ቀበኞቹ

"ባለሃብቶች በእድሳት ስም ቤተ መቅደስ ዘልቀው ጽላት ይቀይራሉ"

tabot


በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በከፊቾ ዞን በጥንታዊ አድባራት ጽላት መዘረፉን እናውቃለን ያሉ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ገለጹ። የዜናው ምንጮች የዞኑ አገረ ስብከት በዞኑ በሚገኙ አድባራት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል። ዝርፊያውን የሚያካሂዱት “ባለሃብቶች” መቀመጫቸውን አዲስ አበባና ጅማ ከተማ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ነዋሪነታቸው ቦንጋና ጊምቦ እንደሆነ የሚገልጹት የዜናው ምንጮች “ቀበኞች” በማለት የሚጠሯቸውን የጽላት ዘራፊዎች የዝርፊያ ስልት ተናግረዋል። በመጀመሪያ እድሜ ጠገብ የሆኑትን አድባራት ይለያሉ። በቃፊሮቻቸው አማካይነት መረባቸውን ዘርግተው ሰዎችን ያጠምዳሉ። ህዝበ ክርስቲያን በሚሰበሰብበት ወቅትና ዓመታዊ የበዓላትን ቀን መርጠው በርዳታና በእድሳት ስም ውዳሴ ይቀበላሉ።
በዞኑ የሚገኙት አቢያተ ክርስቲያናት እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በርካታ ጥንታዊ ቅርስም እንዳላቸው የሚጠቁሙት ክፍሎች “ያረጁትን አድባራት እናድሳለን በማለት ጥቁር ለምዳቸውን ለብሰው መቅደስ ውስጥ ይዘልቃሉ” በማለት የዝርፊያው ድራማ እንዴት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
ለሃይማኖታቸው የቀኑና የታመኑ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ሲያጋጥሟቸው መቅደስ ውስጥ ተመላልሰው በሚሰበስቡት መረጃ መሰረት አብረቅራቂ ሃሰተኛ ጽላት በመተካት ዝርፊያ እንደሚካሂዱ፣ ለዝርፊያ የሚመችና ስብናው የወደቀ አገልጋይ ሲያገኙም በግልጽ ያሻቸውን አድርገው ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ።
ድርጊቱ የቆየና ሰዎቹም የሚታወቁ እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ “ቀበኞቹ” ካላቸው የገንዘብ አቅም አንጻር እጃቸው ከወቅቱ ጉልበተኞችና የቤተ ክህነት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት በላይ አመላክተዋል። በዚህ ተነሳ “እንፈራለን፤ ፊት ለፊት ለመግጠምም እንቸገራለን” በማለት ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምስጢራቸው እንዲጠበቅ አስጠንቅቀው መረጃውን ለመስጠት ችለዋል።
“ይህንን ዜና ጥቅማቸው የሚነካና ችግር ያለባቸው አካላት ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞች ሊያስተባብሉት ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ዜናው የሚያስደነግጣቸው ክፍሎች የሚወስዱትን የመጀመሪያ ርምጃ ያመላከቱት ተቆርቋሪዎች፣ “የእኛ ጥያቄ ግን ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እውነታው እንዲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የዞኑ አገረ ስብከት ዛሬ ነገ ሳይል በተቀደሱ የማምለኪያ አድባራት ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት ያሳሰቡት ክፍሎች፣ ቀበኞቹ በርዳታ ስም እድሳት ባካሄዱባቸው አድባራት ላይ የሙከራ ምርመራ ቢደረግ ጥቆማው ምላሽ እንደሚያገኝም በርግጠኛነት ተናግረዋል።
በእድሳትና በርዳታ ስም መቅደስ በመዝለቅ ከሚከናወነው ዝርፊያ በተለየ በድርድር የሚካሄዱም ዝርፊያዎች ስለመኖራቸው ያመለከቱት ክፍሎች “ጉዳዩ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ስምና ቦታን ለይተን ለመጠቆም እንቸገራለን” ብለዋል። “መልዕክቱ ለቀበኞቹ፣ ለተባባሪዎቻቸውና የሚሰማ ተቆጣጣሪ አካል ካለ ለነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል። በዞኑ ያሉ የህዝብ ወኪል እንደራሴዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ወስደው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
“የቃል ኪዳን ጽላት ዘርፎ ከማነከስና ሰልሎ ከመሞት ውጪ ሌላ ዕድል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ተቆርቋሪ አዛውንቶች በ2005 መገባደጃ ላይ ዋሻ ውስጥ ተገኘ የተባለ ጽላት የት እንደገባ እንደማይታወቅ አመልክተዋል። ዜናው የመገናኛ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ደርሶ እንደነበር፣ ነገር ግን በማይታወቅ ሁኔታ ተዳፍኖ መቅረቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላትን እስካሁን እንደሚከነክናቸው አመልክተዋል።
ከዝግጅት ክፍሉ
ይህ ዜና ከመታተሙ በፊት ከጥቆማው በተጨማሪ ሰዎችን ለማነጋገር ተሞክሯል። የዞኑን አገረ ስብከት ለማግኘትም ተሞክሯል። ከዜናው ባህሪ በመነሳት ጉዳዩ ሳይጣራ ግለሰቦችን የሚያመላክቱ መገለጫዎችን ከመጠቀም ተቆጥበናል። በተጠቀሰው ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ በርካታ ቦታዎች ነዋያትና ጥንታዊ ቅርሶች እንደሚዘረፉና ለዝርፊያው ተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉት የድንበር ጠባቂዎች መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማ እውነት በመሆኑ ተጨማሪ ጥቆማ ለምታቀርቡልን መድረኩ ክፍት ነው። ከቦንጋና አካባቢው፣ እንዲሁም ከጅማ ነዋሪዎች ለደረሰን ጥቆማ እናመሰግናለን። በዜናው ላይ ቅሬታም ሆነ ተቃውሞ ካለ እናስተናግዳለን።

Thursday, December 26, 2013

ረቡዕ ምሽት በመንፉሃ ዙሪያ መጠነ ሰፊ ጥብቅ ፍተሻ ተጀመረ!

(ነቢዩ ሲራክ ከሳውዲ አረቢያ)

eth embassy saudi 1


በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተጀመረውን ፍተሻ በማረጋገጥ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ዜጎች በሰላማዊ መንገድ በአስቸኳይ ለጸጥታ አስከባሪዎች እጅ በመስጠት ወደ መጠለያ በመግባት ወደ ሃገር እንዲገቡ ማምሻውን ባወጣው ማስታወቂያ አሳስቧል። ካለፉት ሳምንታት ወዲህ በሪያድ መንፉሃ በኤምባሲውና በሃገር ሽማግሌዎች የተቋቋሙ የመረጋጋት ኮሚቴ አባላት ወደ መንፉሃና ኢትዮጵያውያን በሚበዙባቸው መንደሮች በመንቀሳቀስ ዜጎች ያለ ምንም ጉዳት እጃቸውን ሰጥተው ወደ ሃገር ለመግባት እንዲዘጋጁ የመከረ ቢሆንም ጥረቱ አልተሳካም ነበር ።  የሪያድ ኤምባሲ የሽማግሌዎች ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ቅስቀሳ ወደ ሃገር ለመግባት ባልተጨበጠ ተስፋ የተዘናጉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ያልያዙ ወደ ሃገር በመግባቱ ላይ እንዳያቅማሙ መምከራቸው ይጠቀሳል!
eth embassy saudi 1አሁን በተጀመረው የመንፉሃ ፍተሻ ማዋከብ የለበትም። ህጋዊ መኖርያ ፍቃድ የሌለውን ብቻ እንደሚይዙና ከአሰሪው (ከከፊሉ) ጋር ይሰራል አይሰራም የሚባል ማጣራትም ሲካሔድ አልተስተዋለም ተብሏል።
ከአሰሪው ጋር የማይሰራ እንደ ህገ ወጥ እንደሚቆጠር የሳውዲ ህግ በግልጽ ያሳወቀ ሲሆን የጅዳና የሪያድ ኢምባሲ ይህ ህግ እንደሚጸና ተደጋጋሚ ማስታወቂያ በማውጣት “በሰላም ወደ ሃገራችሁ ግቡ!” በማለት ሲመክሩና ሲወተውቱ ሰንብተዋል።
በቀጣዩ መጠነ ሰፊ የማጣራት ዘመቻም ከአሰሪው (ከከፊሉ) ጋር የማይሰራ እንደ ህጋዊ ስለሚቆጠር የሳውዲ መንግስት በፈቃደኝነት እጃቸውን የሚሰጡት ወገኖች ወደ ሃገር መስደድ እንደተጠናቀቀ አንወጣም ባሉት ላይ ፍተሻ በማድረግ በእስራትና በገንዘብ እንደሚቀጣ በኢምባሲና በቆንስል መስሪያ ቤቶች በኩል ባስተላለፈው ማስጠንቀቂያ አስታውቋል ።
ቁጥራቸው በሽዎች የሚገመቱ ዜጎች እስካሁንም ድረስ ወደ ሃገር ግቡ የሚለውን ጥሪ ባለመቀበል የተዘናጉበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ካለፉት ሁለት ቀናት ወዲህ መንቀሳቀስ  ያልጀመረው የጅዳ አካባቢ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ሃገር ቤት ለመግባት ወደ ተዘጋጀው መጠለያ በመግባት ላይ ናቸው። ከአሰሪያቸው ጋር ስለማይሰሩ ህገ ወጥ የተባሉት ግን አሁንም እንቅስቃሴ አለማሳየታቸው ይመለከታል።
የጅዳ ቆንስልና የወገን ለወገን ደራሽ ኮሚቴውም አውቶቡስን በአፋጣኝ እንዲቀርብ በማድረጉ ረገድ ከቆንሰሉ ሃላፊዎች ጋር በመተባበር ለነዋሪው ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ህጋዊ ሰነድ የሌላችሁ አስፈላጊውን ውሳኔ መውሰድና በእድሉ መጠቀም ይጠበቅችኋል። እድሉን መጠቀም መቻል ብልህነት ነው!

የፍርሃት ባህልን እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ

አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ

one two


ክፍል አንድ
ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫ ስለሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚኖረውን ገጽታ እና ትርጓሜ ማስቀመጥ ያስቸግራል። አንዱ ሰው የሚፈራውን ነገር ሌላው ላይፈራው ስለሚችል ፍርሃት እንደ የግለሰቡ ባህሪ እና ጥንካሬ ወይም ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ የተለያየ መልክ ይኖረዋል። ይሁንና በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚጋሩት ባህልና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እንደመኖሩ ሁሉ የሚጋሩትም ፍርሃት ወይም ደስታ ወይም ሃዘን ወይም ድፍረት ወይም ሌሎች ባህሪያት ይኖራል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዋዊ ባህሪያት ለአንድ ማህበረሰብ ወይም ለበርካታ ሰዎች የወል መገለጫ ተደርጎ ሲገለጽ ይስተዋላል። ‘የዚህ አካባቢ ሰዎች ጀግኖች ወይም ጸብ ፈሪዎች ወይም እሩህ ሩህዎች ወይም ጨካኞች ወይም ቂመኞች ወይም ገራገሮች ወይም ተንኮለኖች ወይም ጎጠኞች ወይም ሌላ ባህሪ ያላቸው ናቸው’ የሚል አገላለጽ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ አነጋገር ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ባይሆንም በአካባቢው ላይ ጎላ ብለው በሚታዩ ሰዎች ላይ ተደጋግሞና ተዘውትረው የሚታዩ ተመሳሳይ ባህሪያት የአካባቢው ሰው ሁሉ መገለጫ ተደርገው ስለሚወሰዱ ድምዳሜው ለስህተት የተጋለጠ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት በዚህ ጥልቅ ጥናት ባላካሄድኩበት ነገር ግን ደጋግሜ ሳብሰለስለው በቆየሁት የፍርሃት ባህል እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ዙሪያ ያለኝን ምልከታ ለአንባቢያን ለማካፈልና በጉዳዩም ላይ ለመወያየት ወሰንኩ።
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን እና ከዚያም አልፎ ባህል እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስና በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ገጽታ በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በስነ-ልቦና ጠበብቶች ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የፍርሃት ምንጮች መካከል፤ ነፃነትን ማጣት፣ ነገ የሚሆነውን ማወቅ አለመቻል፣ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ፣ የማያቋርጥ ብስጭት ወይም ንዴት፣ ድህነት በሚያስከትለው ስቃይ ውስጥ መማቀቅ፣ አጋር እና አለኝታ ማጣት፣ በሌሎች ክፉኛ መነቀፍ፣ መንጓጠጥ፣ መጠላት እና መገለል፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ማጣት፣ የሞት አደጋን ማሰብ፣ ሽንፈት ወይም ስኬት አልባ ሆኖ መቆየት፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከእነኝህ መክንያቶች ውስጥ የአንዱ መከሰት አንድን ሰው ወደ ፍርሃት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። እነኝህ ምክንያቶች ተደራርበውና በአንድ ጊዜ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ሲከሰቱና ዕልባት ሳያገኙ እረዘም ላለ ጊዜ ሲቆዩ ደግሞ አደጋቸው የከፋ ነው የሚሆነው። ከዚህም በመነሳት ወደ እኛ ማህበረሰ ስንመለስ በግላችንም ሆነ በጋራ ህይወታችን ከላይ ከተጠቀሱት የፍርሃት መንሰዔዎች መካከል ስንቶቹ በህይወታችን ውስጥ ተከስተዋል፣ ስንቶቹን በአሸናፊነት አለፍናቸዋል፣ ስንቶቹስ ዛሬም ድረስ አብረውን ይኖራሉ፤ የሚሊቱን ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንዲጠይቅ እየተውኩ በወል በምንጋራቸው ጥቂት የፍርሃት መንሰዔዎች ላይ ላተኩር።
የነፃነት ማጣት
ሰብአዊ መብቶች በገፍ በሚጣሱበት እና ዜጎች የሰውነት ክብራቸው ተገፎ፣ ተዋርደውና ነፃነታቸውን ተነጥቀው በሚኖሩበት አገር ሁሉ ፍርሃት ትልቁ ገዢ ኃይል ነው። በእንዲህ ያለው ማህበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ሰለባ የሆኑት እና ነፃነት አልባ ሕይወትን የሚገፉት ተጨቋኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ጨቋኞቹም ጭምር ናቸው። ተጨቋኖቹ በግፍ ልንገደል፣ ልንታሰር፣ የስቃይ ሰለባ ልንሆን፣ ታፍነን ልንሰወር፣ ከሃገር ልንሰደድ፣ ከሥራ ልንባረር፣ ንብረታችን ሊወረስ፣ በግዞት ከቦታ ቦታ ልንዛወር፣ ከቅያችን ልንፈናቀል፣ በሃሰት ክስ ልንወነጀል፣ ደሞዛችንን ልንነጠቅ፣ ከሥራ ደረጃችን ልንቀነስ፣ ወዘት … እያሉ አደጋዎችን እያሰቡ በሽብርና በፍርሃት ቆፈን ተይዘው ‘ጎመን በጤና’ በሚል የማፈግፈጊያ ስልት መብቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠት የግፍ እንቆቋቸውን እየተጎነጩ መራራ ሕይወታቸውን ይመራሉ። ጨቋኞቹም ይህን በነፍጥ እና በሕግ አንበርክከው ነፃነቱን የነጠቁትና ለስቃይ የዳረጉት ሕዝብ በአንድ አይነት ተአምር በቁጣ ገንፍሎ ከተነሳ አንድም ቀን እንደማያሳድራቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እያንዳንዱን ደቂቃና ሰዓታት ልክ እንደ ተጨቋኙ በፍርሃት እና በሽብር ነው የሚያሳልፉት። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱም፣ የእለት ሥራቸውንም ሲያከናውኑ፣ ሲተኙም ሆነ ሲዝናኑ በሠራዊትና በመሣሪያዎች ጋጋታ ታጅበው ነው። ምናልባትም ከተጨቋኞቹም በባሰ ፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ያጤንን እንደሆነ ገዢና ተገዢ እርስ በእርስ የሚፈራሩበት፤ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ተቃዋሚዎች መንግሥትን የሚፈሩበትና አንዱ ሌላውን የማያምንበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የመንግሥት ፍርሃት ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች አልፎ የሲቪክ ማኅበረሰቡን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ ነጋዴውን፣ ምሁራኑን፣ ገበሬውን፣ ወጣቱን እና ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ የሚፈራበትና በቁራኛ የሚከታተልበት፤ እነሱም መንግስትን እንደ ተናካሽ አውሬ የሚፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በመንግሥትና በሕዝቡ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በመንግሥት፣ በሕዝቡና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ካለመተማመን የመነጨው ይህ ጥልቅ ፍርሃት በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቁር ደመናን ጋርዷል። በገዢው ኃይል በኩል ያለውን የፍርሃት ድባብ ለመመልከት በየጊዜው መንግሥት የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች፣ የሚያወጣቸውን የማፈኛ ሕጎች፣ እያጠናከረ የሄደውን የሥለላና የአፈና መዋቅር፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጫቸውን ሕግን ያልተከተሉ እና በሽብር መንፈስ የተዋጡ መግለጫና ዘገባዎችን መመልከት በቂ ነው። በተለይም የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ ያስደነበረው የወያኔ መንግሥት ከላይ የጠቀስኳቸውን እና አጥብቆ የሚፈራቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀፍድዶ ለመያዝና እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመገደብ ባወጣቸው የጸረ-ሽብር፣ የሲቪክ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መተዳደሪያ፣ የፕሬስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ፣ የፀረ-ሙስና እና ሌሎች አዋጆች ሥርዓቱ የአፈና  እና የመብት እረገጣ ተግባሩን ሕጋዊ ወደማድረግ ሂደት የተሸጋገረ መሆኑን ያሳያሉ። ፍጹም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ፤ አቅመ ደካሞችን እንኳን ሳይለይ ‘የፈሪ በትሩን’ ሲያሳርፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
ባለፉት ሃያ አመታት የአገዛዝ ሥርዓቱ የፈሪ በትሩን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሳርፏል። ብዕርና ወረቀት በያዙ ከከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ አንደኛ ደረጃ ትመህርት ቤት ሕፃናት ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት ተላትሟል። በርካቶችን ገድሏል፣ አስሮ አሰቃይቷል፣ ደብድቧል፣ ከትምህርት ገበታቸው ላይ አፈናቅሏል፣ ከአገር አሰድዷል፣ በሃሰት ወንጅሎ አስፈርዷል። በእምነት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ከአማኞች፣ ከመንፈሳዊ አባቶች እና ይህን አለም ሸሽተው በገዳም ከከተሙ መነኮሳት ጋር ሳይቀር ተላትሟል። የኃይማኖት ተቋማት እንዲከፋፈሉና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ምእመናን በመስጊዶችና በቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በታጠቁ ኃይሎች ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተዋርደዋል። ቀሳውስት ጥምጥማቸውን እንዲያወልቁ እና መስቀላቸውን እንዲጥሉ ተደርጎ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞቻቸውል። ኢማሞች ጺማቸው እየተጎተተ ተወስደው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ይህ ሕዝብን የማዋረድ እና የማሸበር ተግባር የመነጨው እንደ እኔ እምነት የገዢው ኃይል እየተባባሰበት ከመጣው የፍርሃት እና የመሸበር ስሜት የተነሳ በራስ የመተማመን ስሜቱ እየተቦረቦረ በመሄዱ ነው። ዛሬ ሥርዓቱ የገዛ ጥላውንም የሚፈራበት፣ አባላቱ ላይ እንኳን እምነት ያጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለእዚህም አንዱ ማሳያው በነጋ በጠባ ቁጥር ማቆሚያ በሌለው የግምገማ ስብሰባ አባላቱን ሲያስጨንቅ መታየቱ እና ለዚሁ የሚያባክነው ጌዜ እና የሕዝብ ገንዘብ፣ የባለሥልጣናት ተደጋጋሚ  ሹም ሽር እና ከአገር ከድተው የሚወጡ ባለሥልጣናት እና የወያኔ አባላት ቁጥር መጨመሩ ነው።
ይህ የገዢው ኃይል የሕግን ልጓም በመበጣጠስ የፈረጠመ ክንዱን ይቀናቀኑኛል ባላቸው ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሙያ ማኅበራትና አባላቶቻቸው ላይ ሁሉ ማሳረፉ ቀሪውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እንዲደነብርና በፍርሃት ቆፈን እንዲሸማቀቅ አድርጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚነካ ቢሆንም የጥቂቶች ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥቂት የሲቪክ ማኅበራት፣ ጥቂት ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በጠአት የሚቆጠሩ ግለሰቦ ብቻ ናቸው ባላቸው ውሱን ጉልበት እና አቅም ሲወያዩ፣ የምንግሥትን መጥፎ ተግባራት ሲቃወሙ፣ ለዜጎች መብት ሲሟገቱ እና ባደባባይ ሲጮሁ የሚስተዋለው።
በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መቆየት
ሌላው እና ትልቁ የፍርሃት ምንጭ በከፋ ድህነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ እየማቀቁ መቆየት እና ድህነቱ ባስከተለው የስቃይ ህይወት አካላዊና መንፈሳው አቅም ተሸርሽሮ ክፉኛ መጎዳት እና መዳከም ነው። ሕዝብን በድህነት ውስጥ አምቆ በማቆየት ለሰው ልጅ ከሚገባው ክብር ወርዶና ከእንስሳ ያልተሻለ ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ቅስሙን መስበር የአምባገነኖች አንዱ የሥልጣን እድሜአቸውን ማራዘሚያ ሥልት ነው። የድህነት ክፋቱ ኪስን ብቻ ሳይሆን የሚያራቁተው ክብርንም ጭምር ነው። አንድ ሰው በመንገድ ላይ ቆሞና እራሱን ከመጽዋቾቹ ሥር ዝቅ አድርጎ ቁራሽ ምግብ ወይም ቤሳ ሲለምንና ሲማጸን በኩራትና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አይደለም። እያፈረ እና እየተሸማቀቀ በተሸናፊነትና በዝቅተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው። ይህ ክስተት በሙሉ ጤንነት እና በወጣትነት ወይም በጉልምስና እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ውስጥ ሲሆን ደግሞ ያለው የውስጥ ሕመም እና የሕሊና ቁስል እጅግ የከፋ ነው። የድህነት ክፋቱ ያፈሩትን ቅሪት ብቻ ሳይሆን የሚያሳጣው ወይም ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅምን ብቻ ሳይሆን የሚሸረሽረው መንፋሳዊ ወኔንም ጭምር ነው ከላያችን ገፎ የሚወስደው። ከሰውነት ደረጃ ላይ የሚያቆመንን መንፈሳዊ ልዕልና ካጣን በኋላ ቁሳዊ ድህነቱን ብናሸንፈው እንኳን መንፈሳዊ ድህነቱ ይከተለናል። እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ነገር ድሃ ሁሉ ፈሪ ነው ወይም በፍርሃት ቆፈን የተተበተበ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ ነው። በከፋ የኢኮኖሚ ድህነት ውስጥ እየኖሩ ክብራቸውን አስጠብቀውና እና በላቀ የመንፈሳዊ ወኔያቸው እራሳቸውንና አገራቸውን አስከብረው ያለፉ ድሃ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ማሰብ የግድ ይላል። ዛሬም የገንዘብ እጦትና ድህነት ያላላሸዋቸውና መንፈሳዊ ልዕልናቸውን አስጠብቀው በክብር የሚሞቱ ወገኖች አሉን፤ ትቂቶች ቢሆኑም።
የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊ  ማንነታቸው ውስጥ ድህነትና ፍርሃት ተረባርበው ወይም ከሁለቱ በአንዱ ተጠልፈው ስብእናቸው ፈተና ውስጥ የወደቀባቸውን ሰዎች የሚመለከት ነው። በተለይም በዚህ ግለኝነት በነገሠበት እና ገንዘብ በሚመለክበት የአለም ወቅታዊ  ሁኔታ ውስጥ መናጢ ድሃ ሆኖ ለዘመናት መቆየት መዘዙ ብዙ ነው። ብዙዎች ከዚህ መቋጫው ከጠፋው የድህነት አረንቋ ለማምለጥ ስደትን አማራጭ አድርገው በተለያዩ አቅጣጫዎች አገሪቷን ለቀው ለአረብ አገራት ባርነት ተሰደዋል። ቀሪዎች ደግሞ የአገዛዝ ሥርዓቱ ሎሌ በመሆን ነፃነታቸው በቤሳ መሸቀጥን ቀጥለዋል። ለሁለቱም እድሉን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ደግሞ በየጎዳናው ላይ ተበትነው ዝናብ፣ ውርጭና ፀሃይ እየተፈራረቁባቸው የመጽዋቾቻቸው ደጅ ጠኞች ሆነዋል።
ከተወሰኑ አሥርት አመታት በፊት አንድ ሰው በድህነቱ ምክንያት እራሱንና ልጆቹ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ መሰረታዊ የሆን አልባሳትና መጠለያ ጎጆ ባለቤት ለማድረግ የሚገጥመው ፈተና ቢኖርም ይህን ያህል የመረረ አልነበረም። ዜጎች በወር ከሁለት ብር አንስቶ እንደ የአቅማቸው የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶችን ቤቶች ተከራይተው የመጠለያ ችግራቸውን ይቀርፉ ነበር። በአገሪቷ ውስጥ የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ከመመዝገቢያ ያልዘለለ አነስተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ተማሪዎችን በነጻ ያስተናግዱ ነበር። ብዙ ምሁራንንም አፍርተዋል። በየቀበሌው ከተደራጁ ጤና ጣቢያዎች አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዜጎች በነፃና እጅግ ተመጣታኝ በሆነ ክፍያ ጥሩ ሕክምና የማግኘት እድል ነበራቸው። በአንድ ብር በሚገዛው አስር ትንንሽ ዳቦ ወላጆች ልጆቻቸውን አብልተው ያሳድሩ ነበር። ዛሬ አገሪቱ በልማት እየገስገሰች እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ዜጎች በኑሮ ውድነትና ዋስትና ማጣት በጨለማ  ህይወት ውስጥ እየተደናበሩ ይገኛሉ።
መንግሥት በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ያሻውን ቢያደርግ  በሕዝብ በኩል መላሹ ዝምታ ሆኗል። አብዛኛው ሕዝብ ከተዘፈቀበት የድህነት አረንቋ ሳይወጣ በርካታ ነገሮች ተቀይረዋል። በመቶና በሁለት መቶ ይገዛ የነበር ጤፍ በሺዎች ሲያወጣ ምላሹ ዝምታ ሆኗል። ቲማቲም እንኳን ባቅሟ በኪሎ ከሁለት ብር ወደ ሃያ ብር ስትጠጋ አንዳንዴም ስትዘል ዝምታ፣ የቤት ኪራይ ከመቶዎች ወደ ሺዎች ሲንር ዝምታ፣ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው ሲያሻቅብ ዝምታ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በሰአታት፣ ከዚያም ለቀናት አንዳንዴም በተወሰኑ ቦታዎች ለሳምንታት ሲጠፉ ዝምታ፣ መነኮሳት እና አድባራት ሲዘረፉና ሲዋረዱ ዝምታ፣ መስጊዶች እና ኢማሞች ሲዋክቡና ሲታሰሩ ዝምታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ሲሳደዱ ዝምታ፣ የንግዱ ማኅበረሰቡ ሲዋክብና ሲጉላላ ዝምታ፣ ገበሬዎች በማዳበሪያ እዳ ንብረታቸውን ሲነጠቁና ከዛም አልፎ ከትውልድ ትውልድ ያቆዩትን ይዞታቸውን እየተነጠቀ ለውጪ ቱጃሮች ሲቸበቸብ ዝምታ፣ ወንዶች ሚስቶቻቸውና ሴት ልጆቻቸው እፊታቸው ሲደፈሩና ሲጠቁ እያዩ ዝምታ፣ እናቶች ልጆቻቸውና ባሎቻቸው በየወጡበት ሲቀሩ እያዩ ዝምታ፣ በየከተማው የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ እየተደረገ ከነልጆቻቸ በየሜዳው ተበትነው ይዞታቸው ለስግብግብ ባለሃብቶች ሲሰጥ ዝምታ፣ የሙያ ማኅበራት ሲጠቁ ዝምታ፣ መምህራኖች ሲዋከቡ ዝምታ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ‘በድህነት ቅነሳ እስትራቴጂ’ ስም ሲፈናቀሉና ለርሃብ ሲዳረጉ ዝምታ፣ ባለሥልጣናት የከፋ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ሲንቦጫረቁ ዝምታ፣ ሕፃናት ሳይቀሩ በየአደባባዩ ግንባራቸው በጥይት እየተቦደሰ ሲረሸኑ ዝምታ፣ የአገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ክፉኛ አቆልቁሎ ትውልድን ወደማክሰም ደረጃ ላይ ሲደርስ እየተመለከትን ዝምታ፣ መንግሥት ድህነትን ሸሽተው ከሃገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው እያለና ገንዘብ እየቃረመ ለዘመናዊው ባርነት እያዘጋጀ ፓስፖርት ሰጥቶ ሲያሰድድ ዝምታ፣ በየጎዳናው የወደቁ  ሕፃናቶችን በጉዲፈቻ ስም መንግስት ለውጪ ዜጎች በብዙ ሺ ዶላር ሲቸበችብ እያየን ዝም፣ መንግስት የራሱን ሕገ-መንግስት እየናደ የፈቀደውን ሁሉ በዜጎች ላይ ሲፈጽም የህዝብ ምላሽ ዝምታ፣ ዝምታ፣ ዝምታ…..። ስንቱ ተጠቅሶ ይቻላል?
አንድ ሕዝብ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ያለፋታ ሲዥጎደጎድበት እና መገለጫ የሌልውን ግፍ እና ጭቆና በጫንቃው ላይ ሲጫንበት ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ፣ እያለቀሰና ልቡ እየደማ እንዴት ነህ ሲሉት ደህንነቱን ለመግለጽ ‘እግዚያብሄር/ አላህ ይመስገን’ እያለ የውሸት ሳቅ እየሳቀ እንዲኖር ያስገደደው ምንድን ነው? መንፈሱና አካሉ በቁሙ ተሸርሽረው እያለቁ ባልሞትኩም ባይነት የአያቶቹን ገድል በህሊናው እያመነዥከ በዘመኑ ለተጋረጡበት ፈተናዎች፤ በተለይም ድህነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጭቆዎችና በገዛ አገሩ ተዋርዶ መኖርን ለመሸሽ ስደትን ወይም ልመናን ወይም ሕሊናን ቀብሮ ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆንን ከማን ተማረ? ይህ ጥልቅ የሆነው ዝምታችን የፍርሃት? ወይስ የትእግስት? ወይስ በፍርሃትና በትእግስተኛነት መካከል ሌላ ደሴት ወይም መንጠልጠያ ስፍራ አለ? እራሳችንን እንጠይቅ!
(ክፍል ሁለት)onetwo
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያሰፈነ ስላለው የፍርሃት ባህል ቀደም ሲል ባሰራጨሁት የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ባለሙያዎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ለፍርሃት ባህል መስፈን መንሰዔዎች ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝሬ ነበር። በክፍል አንድ ጽሑፌ መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት ምንም እንኳን ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫዎች መካከል አንዱ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በወል የምንጋራቸውና በማኅበረሰብ ደረጃም በሚንጸባረቁት የፍርሃት ምልክቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። በመሆኑም በዚህ ክፍል ውስጥ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ የሚፈጥረውን የፍርሃት ቆፈንና የሚያስከትለውን መዘዝ በመቃኘት ፅሑፌን ልደምድም።
በአለማችን ታሪክ ከሰው ልጅ አዕምሮ ተፍቀው የማይወጡና እጅግ አሰቃቂ በመሆናቸው ሲታወሱ የሚኖሩ በርካታ ጦርነቶችና የእርስ በርስ እልቂቶች ተከስተዋል። የመጀመሪያውና የሁለተኛው የአለም ጦርነቶች፣ የኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ፣ የአፓርታይድ የግፍ አገዛዝ፣ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት እልቂት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የተከሰቱትና የሚሊዪኖችን ሕይወት የቀጠፉት እልቂቶች በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። እነኚህ በክፉ ክስተትነታቸው በታሪክ የሚወሱት አጋጣሚዎች ካስከተሉት እልቆ መሳፍርት የሌለው ሰብአዊ ቀውስ እና የንብረት ውድመት ባሻገር ከትውልድ ትውልድ የሚወራረስ ትምህርትንም አስተምረው አልፈዋል። በተለይም የምዕራቡ አለም በራሱም ሆነ በርቀት በሌሎች ላይም የተፈጸሙትን እነዚህን መሰል መጥፎ ክስተቶች በአግባቡ በመመርመር፣ መረጃዎችን ሰብስቦና አደራጅቶ በማስቀመጥ፣ በመጽሐፍ ከትቦና እና በፊልም ቀርጾ በማኖር ቀጣዩ ትውልድ እነኚህን መሰል አደጋዎችን ከሚያስከትሉ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ኢኮኖሚያው ቀውሶችና ቅራኔዎች እራሱን በማራቅ ችግሮችን እጅግ በሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ችለዋል። ዛሬ ላይ ያለው ትውልዳቸውም እነ ናዚ እና ሌሎች አንባገነኖች በታሪካቸው ውስጥ ያደረሱትን ሰቆቃና ግፍ እያሰብ የሚሸማቀቅ ወይም በፍርሃት የሚርድ ሳይሆን ታሪክን በታሪክነቱ ትቶ ሙሉ አቅሙንና ጊዜውን ከሳይንስና ተክኖሎጂ ጋር አዋህዶ በዚህ ምድር ላይ ያሻውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
ወደ አገራችን ስንመለስ ኢትዮጵያም ዛሬ ያለችበትን ጂዮግራፊያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ገጽታዎች ለመላበስ ያበቋት እጅግ በርካታ ክፉ እና በጎ ተበለው የሚጠቀሱ የታሪክ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ምንም እንኳን ከላይ ከተጠቀሱት የአለማችን አሰቃቂ ታሪኮች ጋር ባይወዳደርም አገራችንም ከውጭ ወራሪዎች በተሰነዘረባት ጥቃትም ሆነ በልጆቿ መካከል በተከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውድ ልጆቿን አጥታለች። ድህነትን ጠራርጎ ሊያስወግድ ይችል ከነበረው አቅም በላይ በብዙ እጥፍ የሚገመት አንጡራ ሃብቷን በጦርነቶች፣ በግጭቶችና በዘራፊዎች ተነጥቃለች። ይህ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ተደራርበው አገሪቱን ከድሃም ድሃ ተብለው ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ አሰልፈዋታል። እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ እኛስ እንደ ሌላው ዓለም ሕዝብ አገራችን ካለፈችበት የረዥም ዘመን ታሪክ እና በየወቅቱ ከተከሰቱ መጥፎና በጎ የታሪክ ክስተቶች ምን ተማርን? ተምረንስ ለዛሬ እኛነታችን ምን አተረፍን? በአያቶቻችን እና በእኛ መካከል በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ተክለ አቋማችንም ሆነ አመለካከታችን ዙሪያ ለውጦች አሉ ወይ? ለውጣችን ቁልቁል ወይስ ካለፉት ወገኖቻችን የህይወት ተመክሮ ትምህርት ወስደን የደረስንበት የላቀ የአስተሳሰብና የኑሮ ደረጃ አለ? የታሪክ መዛግብቶቻችንስ ያለፉ ነገስታቶችን እና የጦር አበጋዞቻቸውን ከማወደስና ገድላቸውን ከመተረክ ባለፈ በቀጣዩ ትውልድ ሕይወት የጎላ ሚና ሊኖራቸ በሚችል መልኩ ተዘጋጅተዋል ወይ? ወይስ ‘እኔ የገሌ ዘር’ እያለ እንዲያዜምና በአያቶቹ ገድል እንዲያቅራራ ብቻ ተደርገው ነው የተዘከሩት? እንደ እኔ እምነት ከምዕራቡ አለም እኛንና ብዙዎች የአፍሪቃ አገራትን ከሚለዩን ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ከነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚመነጩ ይመስለኛል።
የዛሬ መቶ እና ሁለት መቶ አመት በፊት የተፈጠሩ የታሪክ ክስተቶችን ፍጹም በተዛባ መልኩ እያጣቀስን ልክ የእኛ የልፋት ውጤት አስመስለን እስኪያልበን የምንፎክርና የምንጨፍር እኛ ነን። ታሪክን እና ጀግኖችን ማወደስ ተገቢ ቢሆንም የኛን ድርሻ እነሱን በማወደስ ብቻ ስንገታው አደጋ ላይ ይጥለናል። እንደ አያቶቻችን ታሪክን መስራት ሲያቅተን ታሪክ ሰሪዎችን በማውሳትና በዜማና በግጥም ማወደስ ብቻ ብንኮፈስ የዛሬውን ማንነታችንን አይሸፍነውም። ይህ በአያቶቻችን ታሪክ ውስጥ ተደብቀን ‘በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ’ እያሉ ማዜም፣ መፎከር፣ ማቅራራትና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ዛሬ ከተጣቡን የድህነት፣ የፖለቲካ ጭቆና እና ማኅበራዊ ቀውስ የማያስጥለን እና ነፃ የማያወጣን እሰከ ሆነ ድረስ ኩራታችን ከድንፋታ አያልፍም። አገሬን እወዳልሁ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ እያሉ ባንዲራ ለብሶ ማቅራራት በተግባር ካልታገዘ የውሸት ወይም ባዶ ኩራት (false pride) ነው የሚሆነው። እውነተኛ ኩራት የሚመነጨው ከራስ ነው፤ የራስን ማንነትን በማወቅና በመቀበል ላይ የሚመሰረት ነው። ማንነትን አምኖ መቀበል አቅማችንንም አብረን እንድፈትሽ ይረዳል። የዛሬ ባዶነታችንን በአያቶቻችን የታሪክ ገድል እንድንሞላ ወደሚያስገድድ የሞራል ክስረት ውስጥም እንዳንገባ ይረዳናል። የዛሬ ውርደታችንን በአድዋ ድል እና በሌሎች የአያቶቻችን ተጋድሎዎች በተገኙ ስኬቶችን ልንሸፍነው ከመጣር ይልቅ ታሪክ እንድንሰራ ብርታት ይሆነናል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ያሳቀፉንን የዘረኝነት መርዝ እያራባን በታሪክ ተፈጽመዋል የተባሉ አንዳንድ ክስተቶችን እየመነዘርን ‘ያንተ ቅም ቅም አያትህ የእኔን ቅም ቅም አይታቶች በድሎ ነበር፤ ስለዚህ በቅም ቅም አያቶቼ ላይ ያንተ ዘሮች ላደረሱት በደል ኃላፊነቱን አንተ ትወስዳለህ እያልን ድርጊቱን ዛሬ ላይ እንደተፈጠረ በመቁጠር የምንጋጭና ለመነጣጠል እንቅልፍ አጥተን የምናድርም አለን። እራስን እንደተበዳይ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ በዳይ በመቁጥርና የተዛባን ታሪክ በመተንተን ለዛሬው በዘረኝነት መርዝ ለተለወሰው የፖለቲካ አጀንዳቸው ማሳኪያነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካፈር የሚለውሱ ኢትዮጵያዊያኖችም (እነሱ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ቢሉም) ልብ ሊገዙ ይገባል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጎሣዎች በገዛ አገራቸው እኩል መብትና ጥቅም እንዲረጋገጥላቸውና የሁሉም አገር እንድትሆን ከመጣር ይልቅ በዘረኝነት ስሜት ውስጥ ተወጥሮ ኢትዮጵያዊነትን መካድና ከራስ ጎሣ ውጭ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ጠላት መቁጠር መዘዙ ብዙ ነው። ይህን ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልገውም። በቅርባችን ካለችው ከሩዋንዳ ትምህርት መውሰድ ይቻላል። ይህን የዘረኝነት እሳት እየተቀባበሉ የፖለቲካ መታገያቸው ያደረጉ ኃይሎችም ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በስሙ የሚነግዱበት ሕዝብ ሊያወግዛቸው ይገባል።
እርቀን ሳንሄድ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኳን ብንፈትሽ ዛሬ ለምንገኝባቸው እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ ችግሮች መንስዔ የሆኑትን ነገሮች በቀላሉ ልንገነዘብ እንችላለን። የችግሮቻችንን ምንጮች እና ያስከተሉብንን መዘዝ በቅጡ መረዳት ከቻልን ከተዘፈቅንበት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ጊዜ ላይወስድብ ይችላል። መወጣጫውም ላይርቀን ይችላል። ትልቁ ጥያቄ ችግሮቻችንን ከመዘርዘር ባለፈ ምንስዔዎቻቸውንም በቅጡ ተረድተነዋል ወይ? እንደ አንድ አገር ሕዝብ በችግሮቻችን እና በችግሮቹ ምንጭ ዙሪያ የጠራ የጋራ ግንዛቤ አለን ወይ? በፖለቲካ እና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስንደራጅስ ከነዚህ ግንዛቤዎች ተነስተን ነው ወይ? የጋራ የሆኑ ችግሮች ሰዎችን ያስባስባሉ፣ ለድርጅቶች መፈጠርም መንስዔ ይሆናሉ፣ ችግሮቹንም ለመቋቋም እና ለማስወገድ “ከአንድ ብርቱ …” እንደሚባለው ኃይልን ይፈጥራሉ። ይሁንና ስብስቡ ወይም የተደራጀው ኃይል ፊት ለፊት ከተጋረጡት ችግሮች ጋር ከመፋለም ባለፈ በድጋሚ እንዳይከሰቱ ምንጮቻቸውን ለማድረቅ የሚያስችል እይታ ከሌለው እና አቅሙንም በዚያ ደረጃ ካላሳደገ ይህ አይነቱ ማኅበረሰብ ሁሌም ለተመሳሳይ አደጋዎች የተጋለጥ ነው። የችግሩን መንሰዔ አጥንቶ ምንጩን ለማንጠፍ ከሚያወጣው ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ የበለጠ አዳዲስ ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ከተኛበት እየባነነ ተነስቶ ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችሉ ድርጅቶችን ለመፍጠርና ለማፍረስ የሚያወጣው ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት እጅግ የላቀ ነው። በእንዲህ አይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ጠንካራ የሆኑና ልምድ ያካበቱ ድርጅቶችን መፍጠር አይቻልም። ብዙዎቹ ድርጅቶች ሳይጎረምሱ፣ ሳይጎለምሱ እና ሳያረጁ በጨቅላነታቸው ይሞታሉ ወይም ደንዝዘው ስማቸውን ብቻ ይዘው ይቀራሉ። ይህ አይነቱ ማህበረሰብ አውራ የሚሆኑና በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉም የፖለቲካ፣ የኃይማኖት እና የማኅበራዊ ህይወት መሪዎችን የመፍጠር አቅም የለውም፤ አይፈጥርምም፤ በራሳቸው ጥረት ቢፈጠሩም ጎልተው እንዲታዩ እድሉን አይሰጥም። ትላንት ያነገሳቸውን በማግስቱ አፈር ከድሜ ሲደባልቃቸው ምንም አመክንዮ አይፈልግም። ሲያከብርም፣ ሲሾምም፣ ሲያዋርድም ሆነ ሲኮንን በስሜት ነው። በተለይም እንደኛ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተተብትቦ ግራ ለተጋባ ማኅበረሰብ ልምድና በእውቀት የጎለበቱና የሕዝብ አመኔታን ያገኙ ባለ ዕራይ ድርጅቶችና ግለሰቦች መኖር እጅግ ወሳኝ ነው።
የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶቻችንን የምንይዝበት መንገድ ሊፈተሽ ይገባዋል። የቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ማብቂያን ተከትሎ የፈረሰውና ጀርመንን ለሁለት ከፍሏት የነበረው ግንብ ሲናድ ምስራቅና ምዕራቡን ወደ አንድ አገር ከመለወጥ ባለፈ መላው አውሮፓን አንድ ያደረገ ክስተትን ፈጥሯል። የሰብአዊ መብቶች እና የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳቦች የልዩነት ማጦዣ ምክንያቶች ከመሆን ወጥተው ጀርመንን ብቻ ሳይሆን አውሮፓን ያዋሃዱ ተጨባጭ እውነታዎችን ፈጥረዋል። ይህን ተከትሎም ከታሪክ ለመማር ዝግጁ በሆኑ በበርካታ የአለማችን አገራት በመሬት የተገነቡም ሆነ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የተካቡ የልዩነት ግንቦች ሁሉ ፈርሰው ዜጎች ለጋራ ራዕይ በጋራ የመቆም ጽናትን አሳይተዋል። ሕዝባቸውንም ነጻ አውጥተዋል። ሌሎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ አገሮች (አብላጫዎቹ የአፍሪቃ አገራት) የልዩነቶቻቸውን ግንቦች አጠንክረውና አዳዲስ ግንቦችን በአይምሯቸው ውስጥም ገንብተው የተሰበጣጠረና የሚፈራራ የኅብረተሰብ ክፍልን በመፍጠር ጉዞዋቸውን ቀጥለዋል። የጎሣ ግንቦች፣ የሥልጣን ግንቦች፣ የኃይማኖት ልዩነት ግንቦች፣ የድሃና የሃብታም ግንቦች፣ የጨቋንና የተጭቋኝ ግንቦች፣ ሌሎች ማኅበረሰቡን በአንድ ላይ እንዳይቆም እና ድህነትና አንባገነንነትን አሽቀንጥሮ እንዳይጥል አቅም የሚያሳጡ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተገንብተዋል።
ድርጅቶችን እና መሪ የሚሆኑ ግለሰቦችን እየፈጠርንና መልሰን እየደፈጠጥን የመጣንበትን የ50 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንቃኝ ይህንን እውነታ ያረጋግጥልናል። ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ የፖለቲካ፣ የሙያና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮሩ ድርጅቶች ተፈጥረው ብዙዎች ካለሙበት ሳይደርሱ ከስመዋል። ጥቂቶችም ባልሞት ባይ ተጋዳይነት በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆነው ቀጥለዋል። በከሰሙትም እግር ሌሎች በርካቶች ተተክተው በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ወድቀው የኅብረተሰቡን ቀልብ ለመሳብ ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላል። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በዚህ ዘመን ውስጥ ብቅ ብለው በከሰሙትም፣ ተውተርትረው ቆይተው በተዳከሙትም፣ አዳዲስ ስም እየያዙ በተፈጠሩትም ድርጅቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮቹና የድርጅቶቹ ፈጣሪዎችም ሆኑ አጥፊዎቹ አንድ አይነት ሰዎች መሆናቸው ነው። ትላንት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ሌሎችን እንደ ጠላት ይፈርጁ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የብዙ ድርጅቶች ፈጣሪዎች ሆነዋል። ትላንት በጠላትነት የሚፈራረጁ ድርጅቶች አባል የነበሩ ሰዎች ቂማቸውን እንዳረገዙ ዛሬ በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር የተሰባሰቡበትንም ሁኔታ እናያለን። በድርጅቶቹ መካከል እጅግ ጠባብ የሆኑ የርዕዮታለም ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ አብዛኛዎቹ የመጨረሻ ግባቸው አንድ እና አንድ ነው። ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ የሕግ ልዕልና የተረጋገጠባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት እና ድህነትን ያሸነፈች ኢትዮጵያን ማየት፣ መፍጠር ነው። በነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚለያዩ ድርጅቶች ያሉ አይመስለኝም፤ ሊኖርም አይችልም። ልዩነቱ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ድርጅቶቹ በሚከተሉት አቅጣጫና መንገድ ቅየሳ ላይ ነው።
በዚህ የ50 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሽብር መንፈስና በነውጥ ተግባራት የተሞላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በድርጅቶች መካከል እርስ በርስ አለመተማመንንና መካካድን ፈጥሯል። ይህም አለመግባባቶቹ ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አልፈው እልቂትን አስከትለዋል። በዚያም የተነሳ አገሪቷ በፍርሃት እንድትዋጥና ሕዝቧም በስጋት እንዲኖር፤ የፍርሃት ባህልም እንዲጎለብት ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። ዛሬ በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪክ ማኅበራት፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከልም የበርሊን ግንብ አይነት ግዙፍ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። የዛሬዎቹ ኃይሎች ከገዢው ፓርቲ በስተቀር በትጥቅ የተደራጁ ስላልሆኑ ነው እንጂ ለመጠፋፋት ቅርብ ናቸው። ትልቁና እያንዳንዳችን እራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን፤ እነዚህን ግንቦች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ንደን እና በላያቸው ላይ ተረማምደን ልብ ለልብ እንዋሃዳልን? እንዴት እንደ አንድ ሕዝብ የጋራ ዕራይ፣ የጋራ መዝሙር፣ የጋራ ህልም፣ የጋራ መፈክር፣ የጋራ መድረክና የጋራ አገር እንፈጥራለን? እንዴት ከቂም፣ ከበቀልና ከቁርሾ ሽረን ከታይታና ከቧልት ፖለቲካ ወደ እውነተኛ የፖለቲካ ሕይወት እንመለሳለን?
ለማጠቃለል ያህል በእኔ እምነት ከተተበተብንበት ውስብስብ ችግሮችና ከተጫነን የፍርሃት ድባብ ለመላቀቅ፤ አልፎም ጤናማ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚከተሉት ተግዳሮቶች ቢቀድሙ ይበጃል እላለሁ::
  • ዛሬ ለፖለቲካ ንትርክና  እርስ በርስ መፈራራት እንደ ምክንያት የሚነሱት የታሪካችን ክፍሎች ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት እና ከሌሎች ወገንተኝነት ነጻ በሆኑ ምሁራን በአግባቡ የሚጠኑበት ማዕከል ቢኖረን። የመወዛገቢያ ነጥብ የሆኑትም ታሪካዊ ኩነቶችን በአግባቡ ቢጠኑ እና በተለያዩ መንገዶችም ተደግፈው ለማስተማሪያነት ቢውሉ በድንቁርና ላይ ከተመሰረቱት ታሪክ ጠቀስ የሆኑና በጥላቻ መንፈስ የተሞሉ ክርክሮች ወጥተን እውቀትን በዋጁ ውይይቶች ላይ እናተኩራልን።
  • የሩቁን ለታሪክ ምሁራን እንተወና ባለፉት አምሣ ዓመታት ከ1960 ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ኃይሎች ዛሬም በአገሪቷ የለት ተዕለት የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በግራና በቀኝ ሆነው እና በመቶ ድርጅቶች ጉያ ውስጥ መሽገው በአገሪቷና በድሃው ሕዝብ እጣፈንታ ላይ ወሳኞች ሆነው ቀጥለዋል። በተለይም ‘ያ ትውልድ’ በሚል የሚታወቀው የኅብረተሰብ ክፍል ከልጅነት እስከ አዋቂነት ክቡር ሕይወቱን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና እውቀቱን ያለምንም ስስት የዛችን አገር እጣ ፈንታ ለማቅናት መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል፤ ዛሬም ዋነኛ ተዋናይና አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ትውልድ ትላንትናም ሆነ ዛሬ በገዢና በነጻ አውጪዎቻች ቡድኖች ተፈራርጆ እርስ በርሱ ተጨራርሷል፣ ቂምና ቁርሾም ተጋብቷል፣ ተሰዷል አሰድዷል። ዛሬም በልቡ ቂም ይዞና በቀልን አርግዞ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ መሽጎ የጎሪጥ ይተያያል። ባገኘው አጋጣሚም ሆሉ ይናቆራል። ‘ቂም ተይዞ ጉዞ’ እንዲሉ ትላንት በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው በጠላትነት ይፈራረጁና ሊገዳደሉ ይፍላለጉ የነበሩ ሰዎች ይህን ሸክማቸውን በንስሃ እና በይቅር ባይነት ከላያቸው ላይ ሳያራግፉ ውስጥ ውስጡን እየተብሰከሰኩና እየተፈራሩ ገሚሶቹ በልጅነታቸው በቆረቡባቸው ድርጅቶች እየማሉ ቀሪዎቹም ዘመኑ በወለዳቸው አዳዲስ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው የለበጣ ውህደት እየመሰረቱ በዋዜማው ይፈረካከሳሉ። እንደ እኔ እምነት ከዚህ የእርስ በርስ መፈራረጅ፣ መፈራራትና የቆየ ቂምና ጥላቻ ሳንሽር የምንክበው ካብ ሁሉ የእምቧ ካብ ነው የሚሆነው። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ከዚህ አዙሪት ወጥተንና ከቂም ተላቀን የጋራ ራዕይ እንዲኖረን እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱን ለይቅርታ ማዘጋጀት አለበት። ከልብ የበደላቸውን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅርታ ለመቀበል። ከድርጅታዊ ወገንተኝነትም እራሱን ነጻ አውጥቶ በሱና በድርጅቱ ላይ የተፈጸመውን በደል ብቻ ሳይሆን እሱም ጠላት ብሎ በፈረጃቸው ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል ለመናዘዝና ለደረሰውም ሁሉ አቀፍ ጥፋት ድርሻቸውን በድፍረት በማንሳት የተጠታቂነት ባህልን ‘ሀ’ ብለው ሊጀምር ይገባዋል።
  • ይህ ሁኔታም የደረሰውን የጉዳት መጠን በቅጡ እንድናውቅ ከማድረጉም ባሻገር እርስ በርስ የመወነጃጀሉን ታሪክ እንድንገታውና ልባችንንም በፖለቲካ ንስሃ አንጽተን የሚነገርለትን ያህል የተሳካ ባይሆንም እንኳ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪቃው ‘በእውነት’ ላይ ወደ ተመሰረተ የእርቅ እና የሰላም መድረክ እንድቀርብ እድል ይፈጥርልናል።
  • የልጆቹን እርስ በርስ መጨራረስ እየተመለከት ፓለቲካ እንዲህ ከሆነ አርፎ መቀመጥ ይበጃል፤ እርም የፖለቲካ ነገር በሚል አይምሮውን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ የለት ጉርሱን ብቻ እየቃረመ የአገሩን የፖለቲካ እጣፈንታ ለእዝጌሩ ትቶ ደግ ቀንና መልካም አስተዳደርን እንደመና ከሰማይ እንዲወርድለት የሚጠባበቀውም የኅብረተሰብ ክፍል አይኑን ይገልጣል፤ ከመጠፋፋት ወደ ሰለጠነ የውይይት ባህል በሚሻገረው የፓለቲካ ኃይልም ላይ እምነት ያሳድራል፤ እራሱንም ከፍርሃት ነጻ አውጥቶ በሙሉ ልብ በአገሩ ጉዳይ ባለቤት ይሆናል።
  • ስለዚህም የገዢው ኃይል ወያኔ ካለበት ጥልቅ ፍርሃት እና የሥልጣን ጥም የተነሳ ለእንዲህ ያለው ለውጥም ሆነ የሰላምና የእርቅ ጎዳና ገና ዝግጁ ባይሆንም የተቀሩት የፖለቲካ ሃይሎች መንገዱን በመጀመር ለዘመናት በመካከላቸው የቆየውን ቁርሾና ቂም ከአዕምሯቸው በማውጣት ከልብ የመነጨ እርቅ በማድረግ የልዩነት ግንቦችን ማፈራረስ ይጠበቅባቸውል። የሰላም፣ የእርቅ እና የእውነት አፈላላፉ ጉባዔ ያስፈልገናል።
በእውነት ላይ ተመስርተው ተቃዋሚዎች በቅል ልቦና ከታረቁ አብረው ከሠሩ በኢትዮጵያዊና በኢትዮጵያዊያን ላይ ለዘመናት እንደ መዥገር ተጣብቀው ደማችንን የሚመጡትን፣ ክብራችንን ገፈው እርቃን ያስቀሩንን፤ ድኅነት፣ እርዛት፣ አንባገነናዊ ሥርዓትና ጭቆና፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ድንቁርና፣ ጨለምተኝነት፣ ፍርሃት፣ ሙስና እና ጥላቻን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለን መጣል እንችላለን። ቅን ልቦና ይኑረን! ለዘመናት የተጫነንን ሸክማችንንም እናራግፍ። ያኔ ለፍቅር በፍቅር፣ ለሰላም በሰላም፣ ለነጻነት በነጻነት፣ ለአንድነታችን በአንድነት የምንሰራበትና ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሰሪ የምንሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ቸር እንሰንብት!
ያሬድ ኃይለማርያም ከብራስልስ

Wednesday, December 25, 2013

ፖለቲካና ሃይማኖተኝነት የሚያቃርናቸው ነገር አለን?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

politics and religion


ፖለቲካ የሚለው ቃል የባዕድ ቃል ነው እምነተ-አሥተዳደር ማለት ነው፡፡ ከባዕድ ከመምጣቱም ቃሉንና ተግባሩን በመልካም ጎኑ ቀምሰን ሳናጣጥመው ወዲያውኑ ምሬቱን ስላሳየን ለቃሉና ለተግባሩ መልካም ስሜት የለንም፡፡ አንድ አባባልም ፈጥረንለት ከሥነ-ቃሎቻችን ቀላቅለንለታል ‹‹ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ ነው›› የሚል፡፡ በእርግጥ ግን ፖለቲካን ርቆ መራቅ ይቻላል? ለዚህ ቃልና ለተግባሩ ባለን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት የተነሣ ፖለቲካ ያለውን የሀገርንና የሕዝብን እጣ ፈንታ የመወሰንን ያህል ግዙፍ አቅምና ሚና ዘንግተን ፖለቲካንና ፖለቲከኛነትን ጭንቅላታችን ውስጥ የጭራቅ ምስል ሥለን በመፍራት በመጥላትና በመሸሽ በዜግነታችን ለሀገራችን ልናበረክተው የሚገባንን ተግባርና አገልግሎት እንዳናበረክትና ሀገሪቱም በፖለቲካ ምክንያት ከሚከሰቱ ትብትብ ችግሮች እንዳትወጣ አድርጓታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ ማለትም ሕዝቡ ፖለቲካን መጥላቱ ከፖለቲካ መራቁ መገለሉ ገዥዎች በመድረኩ ላይ ያለጠያቂ እንደፈለጉ እንዲፋንኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝቡን ለፖለቲካ በሚሰጠው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊያስጨብጠው ከሚችሉት ልፈፋዎች (propaganda) ከሚፈጠር ፍርሐት የተነሣ በርከት ያሉ የመገለያ ሰበቦችን እንዲፈጥር አስገድዶታል፡፡
ሕዝባችን አሁን ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ማየት ለዚህ በቂ ምሥክር ነው፡፡ ሕዝቡ ሀብታም ከድሀ ሳይለይ የግፍ አገዛዙ ከልክ በላይ ያንገፈገፈው ቢሆንም ሊከፍለው የሚገባውን ዋጋ ከፍሎ የተነጠቀውን ነጻነት በእጁ ለመጨበጥ ያለው ቁርጠኝነት እጅግ ደካማ ሆኗል፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝምታ ግፍን ተንጋሎ መጋት የመረጠ አስመስሎታል፡፡  ይህ ግምት የተጋነነ መስሎ የሚታየው ዜጋ ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ይህ ሁኔታ እንዳለ ያምንና ለድካማችን ለስንፍናችን ለፍርሐታችን ለዳተኝነታችን ምክንያት የእናታችንን ቀሚስ የምንጠቅስ ነን፡፡ ይሄንን ጉዳይ ተጨባጭነት ባለው ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፡፡
እኔ ለአቅመ አዳም ከመድረሴ በፊት ጀምሮ ማለትም ገና የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ባቅሜ ግፍና በደልን በመቃዎም ትግል ያለፈ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮች አሉ እንደኔና እኔን እንደመሰሉ ሁሉ የሚፈጸሙ ግፍና በደሎችን እነሱም ይቃወሙ ዘንድ ከምንጠይቃቸው ወገኖች ከፊሎቹ “አይ እኔ ፈሪ ነኝ፣ ራስ ወዳድ ነኝ፣ የግል ጥቅሜን አሳዳጅ ነኝ የሌላው አይገደኝም ” ላለማለት ዘወትር የሚናገሩት ነገር ነበር አለም፡፡ ‹‹አይ ይሄ ፖለቲካ ነው አያገባኝም›› የሚል በተለይ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉትና ሃይማኖተኛነትን በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ሰዎች፡፡ ይመስለኛል በሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችም ዘንድ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡
እነኝህ ሰዎች በደሉን ያደረሱት ፖለቲከኞች እንደሆኑና በደሉም የደረሰው በቤተክርስቲያን ላይ ሆኖም እንኳ እያለ ያንን በደል መቃወም እንዴት ፖለቲካ ሆኖ እንደሚታያቸው አስገራሚ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ችግር የሚፈጠረው አንደኛው ከላይ እንዳልኩት ራስን ከኃላፊነት ለማሸሽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካላመረዳትም ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማንኛውም ዜጋ ወዶም ይሁን ተገዶ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፖለቲካዊ ጉዳይ ይመለከተዋል ይገደዋል፡፡ ፖለቲካ ነው አያገባኝም ብሎ ማለት በሌላ አማርኛ እኔ ዜጋ አይደለሁም ሀገርንም ሆነ ሕዝብን እራሱን ጨምሮ እንደፈለጉ እንዳሻቸው ቢያደርጉ አይመለከተኝም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ብሎ የሚል ሰው ደግሞ በዜግነቱ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ወይም የሚገባውን ማለትም የመሥራት፣ የመማር፣ የመኖር ወዘተ መብቶች ለእኔ አይገቡኝም አልጠይቅም ማለቱ እንደሆነ ያለመረዳትን ያህል ድንቁርና የተጫነው አባባልና አስተሳሰብም ነው፡፡
አንድ ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ሰው ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ዜጋም ነው፡፡ ሃይማኖተኛነቱ ዜጋነቱን አይከለክለውም ዜጋነቱም ሃይማኖተኛነቱን አይከለክለውም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በተለይ በኢትዮጵያ ሲሆን ደግሞ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስና በፍልስፍና መጸሐፍትም ጭምር ሀገረ እግዚአብሔርነቷ እንደመመስከሩ ተጣጥመው ያሉ እንጅ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው ሊወጣቸው የሚገባቸው ሁለት የማንነት መገለጫዎች አሉት ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ሰው ቢሆንም እንደዜጋነቱ ደግሞ ሀገሪቱ እንዲያደርግላትና እንዲወጣላት ከሱ የምትጠብቀው ብዙ ግዴታዎች ደግሞ አሉ፡፡ ይሄም ስለገባቸው ነው አባቶቻችን ለሀገራቸው ታቦት ተሸክመው ጦርነት ይወጡ ይዋደቁ ይሞቱላትም የነበሩትና የሀገራችንን ነጻነት ሉዓላዊነትና ክብር አስጠብቀው ሊቆዩ የቻሉት፡፡
ከሁለት ሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ስደተኛውን ሲኖዶስ ለመመለስ ወይም ሀገር ቤት ካሉ አባቶች ጋር ለማስታረቅ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ በነበረበት ጊዜ በመሀሉ አባ ጳውሎስ ዐረፉ፡፡ አይ አግዚአብሔር ባወቀ ነገሩን አስተካከለው ተብሎ ሲታሰብ የሀገር ቤቶቹ አጋጣሚው የፈጠረው ነገር አልተመቻቸው ሆኖ የእርቅ ድርድሩን ለማሰናከል አንድ ሰበብ ፈጠሩ በመግለጫም ስደተኞቹን አባቶች ከቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት የሌለውን ፖለቲካዊ ጉዳይ ያነሣሉ ስለሆነም የእርቅ ድርድሩ መሰናክል ገጥሞታል ወይም ወደፊት ማስቀጠል አልቻልንም አሉ ፡፡
በወቅቱ ይህ መግለጫ እጅግ ካስቆጣቸውና ካሳዘናቸው ወገኖች አንዱ ነበርኩና ወዲያውኑ በመጽሔት፣ በመካነ ድሮች ይሄንን የተሳሳተና ሸፍጥ ያዘለ ፍረጃ የሀገር ቤቶቹ አባቶች የዘነጉትን የታሪክ እማኝነት በማንሣት እርቃኑን ያስቀረ ጽሑፍ ለንባብ አበቃሁ፡፡ ለራሳቸው ለስደተኛው ሲኖዶስም በመካነ ድራቸው በኩል እንዲደርሳቸው በማድረግ እነዚህ የዛሬዎቹ ‹‹አባቶች›› ፖለቲካ ብለው ያሉት ነገር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባለባት ታሪካዊ ኃላፊነት ወይም ባለ አደራነት ከኦሪት ጀምራ ከዚያም በፊት ከሕገ ልቡና ጀምራ ስትወጣው ስትከውነው የኖረችው የተቀደሰ ተግባር መሆኑን፣ ነገሥታትን በዕውቀትና በጥበብ በሥነ-ምግባር አሳድጋ ቀብታ ስታነግሥ የኖረች መሆኗን ወደ ኋላ ደግሞ ማለትም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሦ መንግሥት ተሰጥቷት እስከ ቅርብ ጊዜ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቆይቶ ለየት ባለ መልኩ ሀገሪቷ በፈተናዎች የተዋጠች ብትሆንም፤ ከሀገሪቱ ነጻነት እስከ ሥልጣኔዋ የማይተካ ቁልፍ ሚና የተጫወተች ኃላፊነቷን በሚገባ የተወጣች መሆኗን፤ አሁን በስደት ላይ ያሉ አባቶችን የሀገር ጉዳይ በማንሣታቸው ፖለቲከኞች ብለው የሚነቅፏቸው የሚኮንኗቸው ከሆነ እየነቀፉ ያሉት እነሱን ብቻ ሳይሆን በስንክሳሩ የሚዘከሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን፣ የቤተክርስቲያኗን ተጋድሎ እና ታሪክ መሆኑን “ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” ብሎ ስለ ተበደሉ ፍትሕ ስለተነፈጉ ወገኖች መጮህ መሟገት አምላካዊ ኃላፊነትን መወጣትና ሐዋርያዊ ግዴታ መሆኑን፣ ከሐዋርያት ሕይዎትና ከክርስቶስ ቃል ጋር በማመሳከር ለዚያ የደነቆረ ፍረጃና ነቀፋ አጥጋቢ ምላሽ እንደሰጠሁ ብዙ ሳይቆዩ ማለትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ፖለቲከኛ ሲሏቸው ይሸማቀቁና በዜግነታቸው የሚሰማቸውን ሁሉ አፋቸውን ሞልተው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመናገር ይሳቀቁ የነበሩ ስደተኞቹ አባቶች የጽሑፌን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ በማካተት እንዲህ እንዲህ በማለታችን ፖለቲከኞች ተባልን፤ እንዲህ እንዲህ ማለት ፖለቲከኛነት ሳይሆን ሐዋርያነት ነው የሚል መግለጫ አወጡና ለብዙኃን መገናኛዎች ለቀቁ፡፡ እኔም በእውነት እንዲያ ብዙ ስደክምለት የኖርኩትን አስተሳሰብ ያውም በሲኖዶስ ደረጃ ሲንጸባረቅ የተሰማኝ ደስታ የላቀ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላማ እንዲያውም በተለይ ከሀገር ውጭ ያሉ ሰባክያን ይሄንን አስተሳሰብ በደንብ እያንጸባረቁት እንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር እየሰማናቸው ነው፡፡ ጎሽ እንዲያ ነው ከዚህ በኋላ ፈሪውና ራስ ወዳዱ ለዳተኝነቱ የዜግነት ኃላፊነቱን ላለመወጣቱ የሚጠቅሰው ሌላ ምክንያት ምን እንደሆነ እንግዲህ ደሞ እንሰማለን፡፡
በእርግጥ እነኝህ አባቶች ይሄንን እውነታ አተውት ወይም ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ልቦናቸው ይሄንን ሀቅ ስለሚያውቅማ ነው በቂም ባይሆን አምነውበት ለመተግበር ሲሞክሩ የቆዩት፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ፖለቲካን ወይም ሀገራዊ ጉዳይን ከዜግነት ግዴታና ከቤተክርስቲያን ለመነጠል ከፋሽስት ጣሊያን ጀምሮ በደርግ በተለይም ደግሞ በወያኔ የተሰበከው ማወናበጃና ማምታቻ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ላይ እንዳጠላ ሁሉ ይህ ሁኔታ ከባድ ጫና ፈጥሮባቸው በዜግነታቸው ለሀገራችን ልናበረክት ይገባል ብለው የያዙትን ቀናና ትክክለኛ አስተሳሰባቸው ከልብ ወጥቶ ወደ አንደበት ስላልደረሰ ነበር በሀገራዊ ወይም በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በሚጠሩና በሚከወኑ መድረኮች ተገኝተው ያለ ሀፍረትና መሸማቀቅ እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የቅርብ የሆኑትንም ማንሣት እንችላለን እንደ አርበኛው አቡነ ጴጥሮስ ሁሉ በግንባር ቀደምትነት በወኔና በስሜት ምላት መናገር ያለባቸውን ለመናገር ተሳትፏቸውንም ለማበርከት ይቸገሩ የነበሩት፡፡ አሁንም ቢሆን ገና ይቀራል ይቀራል፡፡ እንደ ሐዋርያትና ሠማዕታት ሁሉ ባለ 30,60,100 ፍሬ ባለ አዝመራ መሆን የፈለገ አባት ወይም የሃይማኖት ሰው ቢኖር መንገዱ ይሄው ነው ሌላ የለምና ያለ ማመንታት በልበ ሙሉነትና በወኔ ውጡ ተሳተፉ ተጋደሉ፡፡
ከዚሁ አካባቢ ካሉ ሰዎች ከሕዝቡም ቢሆን የሚነሣው ሌላኛው ሰበብ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ያመጣውን ምን ማድረግ ይቻላል እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ዝም ብለን መቀበል ነው እንጅ›› የሚል ነው፡፡ ለአሁኑ ባጭሩ ለመመለስ አንደኛ ነገር ‹‹ማንም ሲፈተን  በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች፡፡ ያዕ. 1÷13-15 ተብሎ መጻፉን ልብ ይሏል፡፡ ሁለተኛ ስኬት የሚገኘው ከጥረት ከግረት ከልፋት መሆኑን አዳምን ጥረህ ግረህ በግንባርህ ወዝ ብላ እደር ዘፍ. 3÷19 ባለውና ሊሠራ የማይወድ አይብላ  2ኛተሰ. 3÷8-13 ባለው ቃል እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ብሎ በማየት የሚገኝ ነገር እንደሌለ እንቅጩን ተናግሯል፡፡ በዚህም ላይ የሚሠሩ እጆችና እግሮች የሚያስብ ጭንቅላት የሰጠን የሚበጀንን ነገር እንደወደድን እንድናደርግበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
እስከዛሬም ድረስ በዓለም ታሪክ ያለውን ብንመለከት ሰዎች በጥረታቸው አንዱ አንዱን ይጥላል አንዱ አንዱን ያነሣል እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ እናንተ ይበቃቹሀል ወግዱ እናንተ ተቀመጡ ብሎ አያውቅም፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ነገር ላይ የእርሱ ፈቃድ እንዳለበትና አድራጊውም ሥራውን በርትቶ እየሠራ በሚሠራው ነገር ሁሉ የእሱ ፈቃድና እረድኤት እንዲኖርበት መለመን መጠየቅ ማሳሰብ እንዳለበት እሙን ነው፡፡
የሀገራችንንም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብናይ ያለው እውነታ ይሄው ነው፡፡ ደርግን የሸኘው እግዚአብሔር መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ይሁን እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ ደርግን ከመንበሩ አውርዶ ወያኔን ደግሞ ና ተቀመጥ ብሎ አስቀምጦ አይደለም፡፡ ወያኔን ምክንያት አድርጎ ደርግን ሸኘው እንጅ፡፡
በደርግ የተማረሩ ወያኔዎች ወተው ባይታገሉ ኖሮ ለነገሩ ወያኔ ብቻም አልነበረም ምርኩዙ መጠቀሚያው የሆኑ ሌሎችም ነበሩ አሉም፡፡ ለማንኛውም እነሱ ‹‹አይ እግዚአብሔር ያመጣውን እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? ›› ብለው እጅ እግራቸውን አጣምረው ቁጭ ቢሉ ኖሮ ደርግን ታግለው ለመጣልና ሥልጣን ለመጨበጥ ለመቆናጠጥ መቻላቸው የማይታሰብ በሆነ ነበር፡፡ በይነ ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) ሥርዓት ኖሮ ተመርጠው ለሥልጣን ካልበቁ በስተቀር፡፡ በመሆኑም ቁጭ ብሎ ዓይንን በማቁለጭለጭ የሚገኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ሰው ማግኘት የፈለገውን ነገር የእግዚአብሔር ፍቃድ ታክሎበት በልፋት በጥረት ይገኛል እንጅ እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ካሉበት ከሰማይ ዱብ የሚል ነገር ጨርሶ የለም፡፡ ስትቃዥ ኖረህ እንደቃዥህ አፈር ትገባታለህ እንጅ፡፡
ይህ ዑደት እስካሁን እንደነበረ ሁሉ ወደፊትም ይቀጥላል በወያኔ የተማረረ ሕዝብ ወያኔ እንዲወገድና ነጻነቱን በእጅ መጨበጥ ማስገባት ከፈለገ ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉ ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው ተራ ሰበብና ምክንያትን ነቅሎ ጥሎ፣ የፍርሐትንና የራስ ወዳድነትን ማቅ አውልቆ ጥሎ፣ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቶ፣ ቆረጥ ቆፍጠን ጨከን ብለህ እከሌስ ለምን? እከሌ… ሳትልና ሳትተያይ በዜግነትህ ማድረግ ስላለብህ እንደምታደርገው ብቻ አምነህና ዐውቀህ መታገል ብቻ፡፡
ሦስተኛው የሰበበኞች ሰበብ ደግሞ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ከሁለተኛው ጋራ ተመሳሳይ ሆኖ ነገር ግን ብልጠት አይሉት ድንቁርና የተሞላበት አስገራሚ ሰበብ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 13÷1-7 ያለውን ይጠቅሱና ሰጥ ለበጥ ብለን የመገዛት አምላካዊ ግዴታ አለብን ይላሉ፡፡ እጅግ አሳፋሪና ነውረኛነትም ነው፡፡ ቃሉን እንይ “ ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች ይገዛ ፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለ ሥልጣንን  የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል የሚቃወሙትንም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ፡፡ ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚደርጉት የሚያስፈሩ አይደሉምና ፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል፡፡ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡
ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ ” ይላል ቃሉ እንግዲህ ይሄንን ቅዱስ ቃል እንዴት ለፍላጎታቸው አጣመው እንደተጠቀሙበት አያቹህ? ቃሉ ምንም በማያሻማና ጥርት ባለ መልኩ ነው የቀረበው፡፡ ቁጥር 3-4 ያለውን ቃል ልብ ብለው ቢመለከቱት ቅዱስ ጳውሎስ ስለ የትኞቹ ባለ ሥልጣኖች እየተናገረ እንደሆነ በተረዱ ነበር፡፡ “ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል” ይሄንን ቃል በሚገባ መረዳት እንድንችል አሁን ካለንበት ሥርዓት ሥራ ጋር እንይ ፡፡ ቃሉ እንዳለው ‹‹ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና›› በሚለው ቃል ግልጽ ባለ መልኩ ስለ የትኞቹ ገዥዎች እንደተናገረ አሳይቷል፡፡
በዘመንኛ አገላለጽ ለፍትሕ ለቆሙ ወይም ዲሞክራት ለሆኑ ማለቱ እንጅ እጃቸውን በንጹሐን ደም ለሚያጥቡ ግፈኞች ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ምክንያቱም ‹‹መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና›› ብሏልና ለፍትሕ የቆሙ ወይም ዲሞክራት መሪዎች መልካም ለሚያደርጉት ማለትም ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ ለሰብአዊ መብቶች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ደሀ ተበደለ እያሉ ስለተበደሉትና መብታቸውን ስለተነፈጉት ለሚጮሁት፣ ግፉና ጭቆናን ለሚቃወሙት ለሚሟገቱት የሚያስፈሩ አይደሉምና ብሏልና፡፡ እንኳን ሊያስፈሩ ይሄንን በማድረጋቸው ማለትም መልካም ሥራ በመሥራታቸው ፍትሕ እንዲሰፍን በመታገላቸው እንዲያውም ከእነሱም ምስጋና ይሆንልሀል፡፡ በማለት እያወራላቸው ያላቸው ባልሥልጣናት ስለ የትኞቹ ዓይነቶች እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡
ይሄንን ጉዳይ በሀገራችን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብናየው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን ምክንያቱም የኛ ባለሥልጣናት የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉት ማለትም ሰብአዊ መብትን ለሚረግጡት ፍርድ ለሚያጓድሉት፣ ለሚጨቁኑት፣ ግፍ ለሚያበዙት፣ ለሚመዘብሩት፣ በደል ለሚያደርሱት፣ ፍትሕ ለሚነፍጉት፣ ለሚያንገላቱት ሳይሆን ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ የፍትሕ ያለሕ፣ የመንግሥት ያለህ፣ የዳኛ ያለህ፣ የሕግ ያለህ ለሚሉት ለተጨቆኑት የሰብአዊ መብት እረገጣ ለደረሰባቸው ወገኖች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ ለሚሉት፣ ግፉና በደል ስለ ደረሰባቸው ምስኪኖች ለሚጮሁት፣ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ነጻነት ለሚታገሉት፣ እውነት ለሚናገሩት እንደሆነ አእምሮ ላለው ሁሉ ግልጽ ነው፡፡
በመሆኑም እራሳቸው ክፉ አድራጊዎችና መልካም የሚያደርጉትንም የሚያመሰግኑ ሳይሆኑ የሚሳድዱ የገቡበትም ገብተው ድራሻቸውን የሚያጠፉ መሆናቸው ግልጽ ነው በመሆኑም ይህ የአገዛዝ ሥርዓት ቃሉ ከሚልላቸው ባለሥልጣናት ዓይነቶቹ በተቃራኒ ያለ መሆኑ ግልጽ ነውና ይሄንን ቃል ለሚጠቅሱ አባዮችና እራሳቸውን ለሚያታልሉ የዋሀን በቃሉ የሚያምኑ ከሆነ ጥቅሱ ላይ በቁትር 4 ላይ ያለውን ማለትም ‹‹ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና›› እንዳለ ሁሉ በሀገርና በሕዝብ በቤተክርስቲያንም ላይ ክፉ የሚያደርገውን በመበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ለመባል እንዲተጉ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እናም ቃሉ ምንም የሚያምታታ ነገር የሌለበት ጥርት ባለ መልኩ እንዳስቀመጠው ቅን ፈራጅ ለሆኑት ለሕዝብ ልብ በሉ “ለሕዝብ” ሁለንተናዊ ደኅንነት ሰላምና ጤና ለቆሙት ባለሥልጣናት ማለቱ እንጅ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ፣ መክስምያኖስ በሀገራችን ደግሞ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ መሐመድ፣ በወረራ መጥቶ ለነበረው ለፋሺስት ጣሊያን ዓይነቶች ሁሉ ተገዙ ማለቱ አይደለም፡፡ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ እንኳን ልንገዛላቸውና ክብር ልንሰጣቸው የእግዚአብሔር ሰላምታ እንኳን እንዳንሰጣቸው ሐዋርት በበርካታ ቦታዎች ላይ እያለቀሱም ጭምር አበክረው አስጠንቅቀዋል፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ ነገሩን ግልጽ እንዳደረኩት ቸር ይግጠመን፡፡
amsalugkidan@gmail.com

ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ?

ማስተዋል ደሳለው

ላለፉት 8 እና ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ አያደገ ነው ሲባል እንሰማለን፤  የእድገት ፍጥነቱ  ላይ የሚነሱ በርካታ ጥያቄውች  ቢኖሩም መንግስት  የመንገድ ግንባታ ፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታወችን እና መሰል ነገሮችን  በመጥቀስ እድገት እንዳለ አስረግጦ ይከራከራል::  በሌላ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱ ተመዘገበ በሚባልባቸው ዓመታት በዋጋ ንረት የህዝቡ ኑሮ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ  እንደሆነ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው:: ታዲያ  የኢኮኖሚ እድገት አለ በተባለባቸው ዓመታት የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ? ይህን ጥያቄ ከ 7 ዓመት በፊት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ  ተጠይቀው የሰጡት መልስ የዋጋ ንረቱን የኢኮኖሚ እድገቱ እራሱ የፈጠረው ጉዳይ ነው ነገር ግን ቀስ በቀስ እድገቱ ሲቀጥል ራሱ እድገቱ ችግሩን ይፈታዋል ብለው ነበር፤ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በዃላም እንኩአን ሊሻሻል  የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰበት ሂዷል::  ችግሩ የተለያዩ  ምንጮች ቢኖሩትም በዋናነት በ 2 ከፍሎ ማየት ይቻላል::
፩. የኢኮኖሚ እድገቱ ምንጭ
፪. የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር
የኢኮኖሚ እድገት ማለት በአጭሩ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨማሪ ሀብት መፍጠር ማለት ነው::  በመጀምሪያ ላለፉት 8  እና ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ  የተፈጠሩት ተጨማሪ ሀብቶች ምንድን ናቸው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ፤  በአብዛኛዉ ሀገሪቱ ዉስጥ የተፈጠሩት ሀብቶች ከመንገድ ፣ ከሕንፃ እና ከ ከኃይል ማመንጫ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ናቸው:: በመቀጠልም የዚህ ሀብት የገንዝብ ምንጭ ምንድን ነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል፤ የገንዘቡ ምንጭ በዋናነት ከብድር እና እርዳታ የተገኘ ሀብት ነው ፣ በተለይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 1998 ዓም ጀምሮ በሶማሊያ በመጀመሪያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት በመቀጠልም የአልሻባብ እንቅስቃሴ መጠናከር ለኢትዮጵያ ትልቅ ሲሳይ ይዞ ነው የመጣው:: በሶማሊያ ያለዉን ሁኔታ  ለመቆጣጠር ምዕራባዉያኑ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ  በዋና አጋርነት የተሰለፈችዉ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንት ዓመታት በየዓመቱ በቢልየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከምዕራብ ሃገራት እንድታገኝ አድርጓታል:: ይህም ማለት ሀገሪቱ ዉስጥ የጎላ  የኢኮኖሚያዊ መዋቅር ፣ የአሰራር ስርዓት  እና የቴክኖሎጅ ለውጥ ሳይኖር ከፍተኛ ገንዘብ ወደኢኮኖሚው ፈሰስ እንዲሆን አድርጓል:: በሌላ አገላለፅ  የቆየው የሀገሪቱ  ኢኮኖሚ የጎላ የምርት ጭማሪ ሳይኖረው ከዉጭ የተገኘ ብድር እና እርዳታ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨመረ እና የኢኮኖሚዉ መጠን አደገ ማለት ነው::  ስለዚህ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ሊያሻሽል የሚችል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የጎላ  ለዉጥ ሳይታይ ለመሠረት ልማት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ፈሰስ የተደረገው ገንዝብ የገንዘብ አቅርቦትን (Money Supply) በመጨመር እና  የአገልግሎት ዘርፉ ( Service sector) ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተነጥሎ እንዲለጠጥ እንዲሁም ዋጋ እንዲንር በማድረግ አብዛኛዉን ሕዝብ ለችግር አጋለጠ ::
ከብድር እና እርዳታ የተገኘው ገንዘብ መሰረተ ልማት ላይ ሲዉል ከላይ የተገለፀው ችግር ቢኖርበትም በአንፃሩ የመሰረተ ልማት መስፋፋት የማምረቻ ወጭ ( cost of production) እንዲቀንስ በማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም አለ ፤ በተጨማሪም ገንዘብ ገንዘብን ይፈጥራል “ money creats money” በሚለው የኢኮኖምክስ  መርህ መሰረት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ የተረጨው ገንዘብ በአብዛኛዉ አገልግሎት ዘርፉ ላይ የፈጠረው ተጨማሪ ሀብት አለ:: ነገር ግን ይህ የተፈጠረ ተጨማሪ ሀብት በጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ስላልተመራ ወደጥቂት ሰወች እጅ እንዲገባ ሁኗል::  ሃብቱ እጃቸው የገባ ሰወችም የኢኮኖሚዉን መዋቅር ሊለዉጡ የሚችሉ እንደኢንዱስትሪ አይነት ዘርፎች ላይ ከመሰማራት ይልቅ ከሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለዉን የከተማ ቦታ በኢንቨስትመንት እና በሊዝ ስም በመዉሰድ ህንፃ በመገንባት እየተለጠጠ ላለው የአገልግሎት ዘርፍ በማከራየት በአቁአራጭ ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ ተጠቀሙበት::
በሌላ በኩል የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ስርዓት በሙስና የተጨማለቀ እና ወጥ ስላሆነና አዳዲስ ብቅ ለሚሉ ባለሀብቶች መሬት ማግኘት ከባድ ስለሆነ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ወሳኝ ሀብት (strategic resource) የሆነዉን የከተማ ቦታ ቀድመው የያዙ ባለሀብቶች የገቢያ ዉድድሩን ሚዛናዊ እንዳይሆን በማድረግ አዲስ የሚፈጠሩ ተወዳዳሪያቸውን በቀላሉ ከገቢያ ያስወጣሉ:: በተጨማሪም እንደነዚህ አይነቶቹ  ባለሀብቶች በአብዛኛው የፖለቲካዉ እና የግዥዉ ፓርቲ ጥገኛ ስለሆኑ የሚጠበቅባቸዉን ያክል  ግብር እና ታክስ አይከፍሉም:: ሥራቸዉን ስለሚያውቁም በሀገሪቱ በረጅም ጊዜ ሊከሰት ይችላል ብለው የሚፈሩትን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ስለሚሰጉ የሚያገኙትን ትርፍ ወደዉጭ ያሽሻሉ ፤ በጎን ሙሰኛ ባለስልጣናትም የሚዘርፉትን ገንዘብ ከሀገር ያሸሻሉ:: ከዚህ ላይ ፋይናንሽያል ትራንስፓረንሲ ኳሊሽን  ያወጣዉንና ኢትዮጵያ በህገወጥ የገንዘብ ፍሰት (illicit financial flow) በፈረንጆቹ ከ 2000 እስከ 2009 ያጣችዉን 11. 7 ቢልየን ዶላር ልብ ይሏል::
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጤናማ ሁኖ እንዲያድግ ከተፈለገ ከላይ የተጠቀሱት  የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መዋቅር ድክመቶች መስተካከል የሚገባቸዉ ሲሆን ፤ በዉጭ ብድር እና እርዳታ ላይ መንጠልጠሉን ቀንሶ ከሀገር ቤት በፍትሃዊነት ከሚሰበሰብ ግብር ሊሆን ይገባል:: ከዉጭ የሚገኘዉን ሀብትም  በብዛት መሰረተ ልማት ላይ ብቻ ማዋሉ የሚያስከትለዉን ችግር ጥልቅ ጥናት በማካሄድ  መመርመር እና  ገንዘቡ ከመሰረተ ልማቱ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪው እና የእርሻዉን ዘርፍ መዋቅር ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማስቻልም መሰራት አለበት:: ከሁሉም በላይ ግን የኢኮኖሚ ነቀርሳ የሆነዉን ሙስና ለማስወገድ ከአንድ ፓርቲ የበላይነት ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መሸጋገር እንዲሁም ተጠያቂነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ እንደገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ፣ የግል መገናኛ ብዙሃን  የመሳሰሉትን ተቋማት መፍጠር ያስፈልጋል:: ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ ሽህ ጊዜ ብታድግ የኢኮኖሚውን ፍሬ ጥቂቶች እየበሉ የአብዛኛዉ ሕዝብ  ኑሮ ማሽቆልቆሉ ይቀጥላል::

ቴዲ አፍሮ እና ጥሬ ጨዋዎች

ሁኔ አቢሲኒያዊ

ፒተርቦሮው ዩ.ኬ
ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በብዙዎች ሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ወጣት ከያኒ ነው፤ በሙዚቃዎቹ በሚያነሳው ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ታሪካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች የተነሳ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት የቻለ ይመስለኛል፡፡ የእርሱን ታላቅነት መግለፅ የዚህ ጹሑፍ ዓላማ፣ ጥያቄም፣ የማወቅም ፍላጎት አይደለም፡፡Ethiopian Artist Teddy Afro
ይልቁንም ለዚህ አጭር መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ከሰሞኑ በአንዳንድ ጥቃቅን እና አነስተኛ ካድሬዎች እንዲሁም መንግስትን ለምን እንደሚቃወሙ እንኳን በማያውቁት እንደ እነ ጃዋር መሀመድ የመሳሰሉ ሰሞንኛ ትችታቸውን በመሰንዘራቸውን ምክንያት እኔም የተሰማኝን ልጨምር በሚል ነው፡፡
እንደምናውቀው ቴዎድሮስ ካሣሁን በዚህች የሙዚቃ ህይወቱ ከዛቻ እስከመታሰር ድረስ የደረሰ መሆኑ እሙን ነው ይህም የደረሰበት የተለየ ሰው ስለሆነ ነው
ቴዲ ሺህ ዘመናት ስልጣኔያችንና ታሪካችን፣ ጥበባችን በፍቅር፣ ፍቅራችን በጥበብ የተገመደበት ውሉ ከየት ተጀምሮ የት እንደተቋረጠ ታሪክን እንጠይቅ ዘንድ እንዲህ ሲል በቅኔው ተመራምሮ ያመራምረናል፡-
ብራናው ይነበብ ተዘርግቶ ባትሮኖሱ ላይ፣
የእነ ፋሲለደስ የእነ ተዋናይ፣
የት ጋር እንደሆነ ይታይ የእኛ ጥበብ መሰረቱ…፡፡
እናም እስቲ ታሪክ ይታይ፣ ይመርመር፣ ዘመናትን ያስረጁና የተሻገሩ ብራናዎቻችን ይውጡ፣የሺህ ዘመን የሃይማኖት፣ የጥበብ፣ የታሪክ፣ የሥልጣኔና የፍልስፍና ድርሳኖቻንን ይታዩይመርመሩ… በአክሱም ስልጣኔ፣ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ትንግርት፣ በጎንደርበእነ ፋሲለደስ የስልጣኔ አየር ዝናዋ የናኘላት፣ እነዛ ፍቅርን በጥበብ አስውበው በቅኔያቸውናበማኅሌታቸው ሰማይ ሰማያትን ሰንጥቀው በመንፈሳቸው ጸባዖት የደረሱ፣ በፍቅር ጧፍ የነደዱበማሕሌታዩ ያሬድ መንፈስ የተነሱ እንደ ተዋናይ ያሉ የቅኔ የጥበብ ጉልላቶች እንደ አጥቢያኮከብ በደመቁባት ምድር ዛሬን ፍቅር የተራብን፣ ጥበብን የተራቆትን፣ ስለ ፍቅር የደከመንምንድነው ምክንያቱ የሚል ይመስለኛል ቴዲ…፡፡
ቴዲ በሙዚቃው ለታሪክ ያለውን ስሱነትና (sensitivity) እውቀትም (Indigenous Knowledge)አሳይቶናል፡፡ ተዋናይን ስንቶቻችን እናውቀዋለን ተብለን ብንጠየቅ የሚያስተዛዝበን ሳይሆን ይቀራል፡፡ በተለይ ደግሞ ለዘመናችን ትውልድ ለአፉም ለልቡም ቅርቦቹ እነ አርሴናል፣ቼልሲ፣ ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ እነ ፊፍቲ ሴንት እነ ቢዮንሴ፣ ወዘተ… የባሕር ማዶዎቹ ዝነኞች ናቸውእንጂ እነ ተዋናይን እነ ቅዱስ ያሬድን፣ እነ አጼ ፋሲልን ሊያስባቸው ወኔው ያለውአይመስልም፣ ኅሊናውንም ይደክመዋል እናስ እንዴት፣ ምን ሲደረግስ ሊያስባቸው ይችላል የኔትውልድ፡፡ በቅኔው የተራቀቀና በመንፈሳዊ እውቀቱ አንቱ ስለተባለው ስለ ተዋናይለመስማትም ሆነ ለማወቅ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ ግድ ይላል፡፡ አሊያም ከቤተክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች እግር ስር ቁጭ ማለት ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
ቴዲ በየትኛው መንገድ የሀገሩንና የቤተ ክርስቲያኑን የጥበብ እና የሥልጣኔ ከዋክብቶችን ሊያውቅ እንደቻለ ባይነገረንም የትናንትናዎቹን የሀገራችንን ባለውለታዎችና የዘመንፈርጦች ማንነት ለማወቅ እና እንዲሁም ታሪኩን ለመመርመር ግን የተጋና የሰላ አእምሮ እንደተቸረው/እንዳለው የግጥሞቹ መልእክቶች ይነግሩናል፡፡ እናም ከታሪካችንና ከስልጣኔያችን መሰረት ከአክሱም ተነስቶ በጊዜና በታሪክ ሃዲድ ላይ አሳፍሮን በትላንት ታሪካችን ውስጥ ራሳችንን እንድንመረምር፤ ራሳችንን እንድናይ ይወተውተናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ይለናል ቴዲ ስለ ፍቅር ዜማው ውብ የግጥሞቹ ስንኞች፡-
. . .የኋለው ከሌለ የለም የፊቱ፣
ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ፣
ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ፡፡
በማለት ከታሪካችን ጋር እጅ ለእጅ በምናብ ሊያጨባብጠንና ሊያስተያየን ይፈልጋል፤ እናምያለ ትላንት ዛሬ የለም፣ ያለ ዛሬ ደግሞ ነገ አይታሰብም በሚል የመጣንበትና የተጓዝንበትንአኩሪና አሳፋሪ የታሪካችንን ምእራፍ ለማገላበጥ ለደከምን ለእራሱ እና ለእኛ ትልቅ ቁም ነገርያለው ምክር ያስተላልፋል፡፡ ይህ የከያኒው የግጥም ስንኝ የሮማውን ታላቅ የሕግ ሊቅ፣ፈላስፋና አስተማሪ የሆነውን የሲስሮን አባባል አስታወሰኝ፡- ‹‹ከመወለዳችን በፊት ያለውንታሪክ ካላወቅን ዕድሜ ልካችንን ሕጻን ሆነን እንቀራለን፡፡›› ታሪካችንን ለመመርመር እናከታሪካችን ለመማር የደከምን እኛ ዛሬም እንደ አዲስ ሰናፈርስ ስንጀምር ከመጀመር ሀ ሁሳንወጣ እንደ ህጻን ባለህበት እረገጥ የሆንበትና ታሪክን እንድንደግም የተፈረደብን ምስጢሩምን ይሆን በማለት ታሪክ ጠያቂ፣ የታሪክ ወዳጅ፣ ከታሪክ የምንማር እንድንሆን ያተጋናል፡፡
ከምንኮራበት ታሪካችንና ስልጣኔያችን ባልተናነሰ አንገት የሚያስደፋ ስማችንና ማንንታችን በዓለም ፊት በቀየረብን በበርካታ የራብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና መበላላት ታሪክ ዘመናትን ውስጥ አልፈናል፡፡ እናም የመጣንበት መንገዱ ረጅም ዘመናቶቻችንም መከራ ሰቆቃና ዋይታ የነገሰባቸው ናቸው ሲል የትናንቱን ታሪክ ለመድገም የተፈረደብን ይመስል ታሪክ ደጋሚዎች እንድንሆን የሆንበትን እውነታ መመርመርና ማየት እንችል ዘንድ ትልቅ ጥያቄ ያጭርብናል፡፡ ዛሬም እግራችን መሄድ ተስኖት ቆመናል የእርሱ ደጋፊዎች እንዳሉ ሁሉ የእርሱ ተቃዋሚዎች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ነው ነገር ግን በአሉባልታ የቴዲን ስራዎች ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ትግል ወይ ቅናት ነው አልያም ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንደሚባለው ይሆናል፡፡
ለእምዬ ምንሊክ ያላቸው ጥላቻ ሰሞኑን ተቀስቅሶባቸው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ከርመዋል አስገራሚው ነገር ምንሊክን ለመሳደብ ቴዲን ሰበብ ማድረጋቸው ነው ሌላው ደግሞ መረጃውን እኔ ለቅቄዋለው ብሎ ማንም ኃለፊነቱን እሰከዚች ሰዐት ድረስ ሳይወስድ እነርሱ ቴዲን እና ምንሊክን መዝለፍ የየእለት ተግባራቸው አድርገውታል፡፡
ምንሊክን ህዝቡ እምዬ ብሎታል ቴዲን ደግሞ የዘመናችን የሙዚቃው ንጉስ ብሎ ሰይሞታል
ደበበ ሰይፉ ጥሬ ጨው በሚለው ግጥሙ እንዲህ ነበር ለነፈዞች የገጠመው
ጥሬ ጨው – ደበበ ሰይፉ
————
መስለውኝ ነበረ ፣
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰው ፍጡሮች ፣
ለካ እነሱ ናቸው ፣
ጥሬ ጨው..ጥሬ ጨው
ጥሬ ጨዋዎች ፣
መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-
መታሸት-መቀየጥ
ገና እሚቀራቸው ፣
“እኔ የለሁበትም !”
ዘወትር ቋንቋቸው ።
ለማንኛውም እኔም እንደ ደበበ ሰይፉ ሰሞንኛ የቴዲ ተቸዎችን ጥሬ ጨው ብዬ ሰይሜያቸዋለው፡
ሁኔ አቢሲኒያዊ
ፒተርቦሮው ዩ.ኬ

Tuesday, December 24, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ በአስቸኳይ የግንፍሌውን ጽ/ቤት እንዲለቅ ትእዛዝ ተሰጠው

ሰማያዊ ፓርቲ ግንፍሌ አከባቢ የሚገኘውን እና በጽ/ቤትነት የሚጠቀምበትን ቢሮ በዛሬው እለት ከሰኣት በኋላ አቶ ሄኖክ የተባሉ አከራዩ ከአራት ትግሪኛ ተናጋሪ ግለሰቦች ጋር በመምጣት ቤቱን ለነዚህ ግለሰቦች ስለሸጥኩላቸው እንድትለቁላቸው ሲል አሳስቧል:፡ “ቤቱን ገዛሁት” የሚለው ትግሪኛ ተናጋሪ ግለሰብ ቤቱን የገዛሁት ስለሆነ በአስቸኳይ እንድትለቁ ካልሆነ የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አመራሮቹ ላይ ዝቷል::
                                       Blue Party office
ይህ ገዛሁት የሚለው ግለሰብ በማይመለከተው ጉዳይ በመግባት ከዚህ በፊት ልቀቁ ተብላችሁ በተደጋጋሚ እንደተነገራችሁ መረጃው አለኝ በማለት በአመራሮቹ ላይ ቁጣ የተቀላቀለበት ዛቻ በመዛት ሄዷል:: በወቅቱ ይዞት የነበረው ተሽከርካሪ ጥቁር የደህነንት መኪና የሆነች ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ሲሆን የታርጋ ቁጥሩም ኮድ 2-89176 የሆነ ነው::
ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ ቀደም በመነን አከባቢ ተከራይቶት የነበረውን ጽ/ቤት ገና ሳይገባበት በዝግጅት ላይ እንዳለ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ፖሊሶች እና ቅጥረኞች ተባብረው በተቀናጀ አፈና ቢሮውን መንጠቃቸው ይታወቃል:: የነጠቁትንም ቢሮ ለካድሬያቸው በመስጠት ፔንሲዎን ከፍቶ እየሰራበት ይገኛል::
ምንጭ፡ ሰማያዊ ፓርቲ ብሎግ

Monday, December 23, 2013

የኢህአዴግ አዲሱ አሰላለፍ ፪ – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

በድህረ-መለስ ኢትዮጵያ የፖለቲካው ሥልጣን በስርዓቱ ልሂቃን መካከል ከሚደረገው የኃይል መተናነቅ አንጻር፣ ዛሬም ከመፈራረቅ ጣጣው የተላቀቀ የማይመስልባቸው ምልክቶች መታየታቸው እንደቀጠለ ነው፡፡ ከአራት ወር በፊት በዚህ መፅሄት ላይ ‹‹አዲሱ የኢህአዴግ አሰላለፍ›› በሚል ባቀረብኩት ፅሁፍ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ተፈጥሮ ከነበረው ክፍፍል የትኛው ቡድን የበለጠ ጉልበት አግኝቶ በአሸናፊነት መውጣት እንደቻለ ከገለፅኩ በኋላ ፅሁፉን የቋጨሁት እንዲህ በማለት ነበር፡- ‹‹የፓርቲው የታሪክ ድርሳን እንደሚነግረን ‹ይሆናሉ› የተባሉት ተቀልብሰው፣ ባልተጠበቁ ሁነቶች (የኃይል መገለባበጥ ተከስቶ) ፖለቲካው የሚመራበት አጋጣሚ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡››
እነሆ በዚህ ፅሁፍ ደግሞ በቅርቡ በተጨባጭ የታዩትን አዳዲስ ኩነቶች እና ይህንኑ ተከትለው ሊመጡ ይችላሉ ብዬ የምገምታቸውን ‹የቢሆን ዕድሎች› (Scenarios) ለማየት እሞክራለሁ፡፡ 
ሰላም የራቀው-ኢህአዴግ 
በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ዛሬም ድረስ ሙሉ በሙሉ የተረጋጋ ፖለቲካ አልሰፈነም፤ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ፣ ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎችን ጠቅልሎ ይዞ በነበረው በቀድሞ ሊቀ-መንበሩ ህልፈት ሳቢያ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት እና እርሱን ሊተካ የሚችል መሪ ማግኘት ባለመቻሉ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከሕግ ይልቅ የጠመንጃ ኃይልና የግለሰብ አምባገነናዊነት በገነነበት ሀገር ‹የማይገመቱ ክስተቶች› (Unpredictable Event) ማምጣታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ በዚህ አጀንዳ ለመመልከት የምሞክረው ጉዳይ፣ በአሁኑ ጊዜ ሀገር እየመራ ያለው ኃይል ለሁለት የተከፈለ ቢሆንም፣ በአንፃራዊነት በጥምር የሚሰራ መሆኑን በማስረገጥ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ቡድኖች የጉልበት ምንጭም የታጠቀውን ኃይል በመቆጣጠር እና የፖለቲካውን ሥልጣን በመያዝ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ይኸውም ሠራዊቱ እና የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ በህወሓት ሰዎች ሲንቀሳቀሱ፣ ፖለቲካውን ደግሞ የብአዴን መሪዎች፣ ከተወሰኑ የኦህዴድና ደህአዴን የአመራር አባላት ጋር ተባብረው መያዛቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸው ነው፡፡
የህወሓት ኃይል
ህወሓት የቀድሞው ፍፁማዊ የበላይነቱን ለመመለስ ዋና ችግር የሆነበት በውስጡ ለተፈጠረው መከፋፈል እስካሁን መፍትሄው ተለይቶ አለመታወቁ ነው፤ ከዚህ ቀደም በዚሁ መፅሄት፣ አንዱ ኃይል የተሻለ ጉልበት በማግኘቱ ሌላኛውን (እነአዜብ መስፍንን ጨምሮ አባይ ወልዱና ቴዎድሮስ ሀጎስን የመሳሰሉ ከፍተኛ ካድሬዎች የተሰባሰቡበትን) በመብለጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንቅስቃሴያቸውን መገደቡ ተሳክቶለት እንደነበረ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ ይህ ክፍፍል ምንም እንኳ እንደ 1993ቱ ከፓርቲ እስከ ማስወጣት የሚደርስ አለመሆኑ ቢታወቅም፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው አሰፋ የተሰለፉበት ቡድን ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኖ መውጣት ችሏል፤ ይህም ሆኖ ውስጥ ውስጡን የሚገመደው ተንኮልም ሆነ ሽኩቻ ገና መቋጫ አለማግኘቱ ግልፅ ነው፡፡
በዚህ ፅሁፍ ጠመንጃ የታጠቀውን ክፍል ‹የህወሓት ኃይል› እያልኩ የምገልፀበት ዓብይ ምክንያት፣ በጄነራል ሳሞራ የኑስ ኤታ ማዦር ሹምነት የሚመራው የመከላከያ ሠራዊት እና በማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌታቸው አሰፋ ስር ያለው የደህንነት ኃይል ለሚደግፉት ቡድን መጠናከር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ ከግምት በመክተት ነው፡፡ ሁለቱም ሰዎች ለመለስ ፍፁም ታማኝ የነበሩ ቢሆንም፣ ከህልፈቱ በኋላ እንደእርሱ ተጭኖ ሊቆጣጠራቸው የሚችል ጉልበታም ህወሓትን ጨምሮ በሁሉም የግንባሩ አባል ፓርቲ ውስጥ አለመኖሩ፣ በፖለቲካው ‹ቼዝ› የ‹ዘመነ መሳፍንቱ›ን ሚካኤል ስሁል አይነት ሚና እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል፤ ሁለቱም ከስራቸው የነበሩትንና ‹ስልጣን ሊጋፉ ይችላሉ› ብለው የጠረጠሯቸውን ባልደረቦቻቸውን አስቀድሞ ገለል ማድረጉ ከሞላ ጎደል የተሳካላቸው ይመስለኛል፡፡
በተለይም ጌታቸው አሰፋ ከራሱ ወንበር አልፎ ከእነአዜብ መስፍንና አባይ ወልዱ ጋር በመተባበር አንድ ቀን በጠቅላላው የመንግስት የሥልጣን እርከን ላይ ‹ናቡቴ ሊሆን ይችላል› የሚል ስጋት ያሳደረበትን እና ‹መለስ ዜናዊ ሞት ባይቀድመው በእርሱ ቦታ ሊተካው ነበር› እየተባለ የሚነገርለትን የመረጃ ኃላፊ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል በሙስና የሚወነጀልበትን መንገድ አመቻችቶ ለእስር ባይዳርገው ኖሮ ‹‹ለቁርስ ያሰቡንን…›› አይነት ታሪክ ራሱን መድገሙ አይቀሬ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
ጄነራል ሳሞራ የኑስ በበኩሉ ተቀናቃኙ አድርጎ ይመለከታቸው የነበረው ሶስቱ ከፍተኛ መኮንኖች እንደ ወልደስላሴ ‹ፍንቀላ መሳይ ነገር ሊሞክሩ ይችላሉ› ተብለው አይደለም፡፡ የእነርሱ የመጀመሪያው ችግር ከወታደራዊ ዲሲፕሊን በማፈንገጥ አለቃቸውን አለማክበራቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሳሞራ ‹በየትኛውም ምክንያት ከኃላፊነቴ ብነሳ የቆየ ፋይል አገላብጠው አደጋ ላይ ሊጥሉኝ ይችላሉ› በሚል ስለሚጠረጥራቸው ነው፡፡ እነዚህ መኮንኖች የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሌፍተናንት ጄነራል ሰዓረ መኮንን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መልካም ግንኙነታቸው እንደቀድሞው እንዳልሆነ የሚነገረው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌፍተናንት ጄነራል አበባው ታደሰ እና የአየር ኃይሉ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሞላ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ እናም ሰዓረ እና አበባው በቀጥታ ሠራዊት ከሚያዙበት ቦታ ተነስተው በመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ በቢሮ ስራ ላይ ሲመደቡ፣ ሞላም ከነበረበት ኃላፊነት አኳያ ብዙም ይመጥነዋል የማይባል የቢሮ ስራ ተሰጥቶታል፤ በእርሱም ቦታ ሜጀር ጄነራል አደም መሀመድ ተተክቷል፡፡ የሳሞራ እና የሞላ ልዩነት በመለስ ዘመንም በአደባባይ የሚታወቅ እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡
ለጉዳዩ ቅርብ ከሆነ የመረጃ ምንጬ እንዳረጋገጥኩት የአስተዳደር ዘይቤውን በማኪያቬሊያዊ አስተሳሰብ (ከፋፍለህ ግዛ) የሚያሳልጠው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ለሞላ ትዕዛዝ የሚሰጠውም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ በተመለከተ የሚያነጋግረው የዕዝ ተዋረዱን ጠብቆ በኤታ ማዦሩ በኩል ሳይሆን፣ በቀጥታ በመገናኘት መሆኑ፣ አየር ኃይሉን ከመከላከያ ሚኒስቴር የተገነጠለ አስመስሎት ነበር፤ ይህ ሁኔታም በሁለቱ መኮንኖች መካከል ያለው ግንኙነት የሥልጣን ተዋረድን የጠበቀ እንዳይሆን በማሰናከሉ በጄነራሉ ላይ ደፍሮ የማይናገረው ቅሬታ ሊያሳድርበት ችሏል፤ ከመለስ ህልፈት በኋላም ሳሞራ ሂደቱን ለማስተካከል መሞከሩ፣ በየግምገማው ላይ እስከ መዘላለፍ አድርሷቸው ነበር (በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ እንደ ጦር ኃይሎች አዛዥነቱ፣ ከጄነራሎቹ ጋር መደበኛ /Official/ በሆነ መንገድ ትውውቅ አላደረገም፤ እነዚህ ሶስት ጄነራሎችም ለዚህ አይነቱ የአሰራር መፋለስ ጥፋተኛ የሚያደርጉት አለቃቸውን ሳሞራ የኑስን ነው፤ ከምንጮቼ እንደሰማሁት ከሆነም ከወራት በፊት ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኘበት ‹ጎልፍ ክለብ› በሚባለው የጄነራሎቹ መዝናኛ በተዘጋጀ ፕሮግራም ማጠናቀቂያ ላይ ሳሞራ አንድ ጠረጴዛ ከበው ወደ ተቀመጡት እነዚህ ጄነራሎች ጋ ሄዶ ‹ኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ላስተዋውቃችሁ› ማለቱን እና እነርሱም በጥያቄው ተበሳጭተው ቢሮ ያላቸው መሆኑን እና ክብራቸውን በሚመጥን መልኩ መተዋወቅ እንደነበረባቸው በኃይለ ቃል መመለሳቸውን ነው)
የሳሞራ የኑስ እና ሰዓረ መኮንን መነቋቆር ከትግሉ ዘመን ጀምሮ የመጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ሳሞራ ከማንም በላይ የሚፎካከረውም ሆነ መበለጥ የማይፈልገው በሟቹ ጄነራል ኃየሎም አርአያ እንደ ነበር የቀድሞ ጓዶቻቸው ያስታውሳሉ፤ ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ በስራ ላይ ያሉ መኮንኖችን ‹የሳሞራ› ወይም ‹የኃየሎም ተከታይ› በማለት መከፋፈሉ በጓዶቻቸው እና በፓርቲው መሪዎች አካባቢ የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለማዕረግ እድገት የተለየ የድጋፍ አስተያየት የሚያገኙት በዛን ዘመን ‹የሳሞራ ተከታይ› የሚባሉት እየተመረጡ እንደነበረ በወሬ ደረጃ ይናፈሳል (በነገራችን ላይ ጄነራል ሳሞራ ከጤንነት ጋር በተያያዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጡረታ ይሰናበታል በተባለበት ጉዳይ ላይ እያንገራገረ እንደሆነ ከመከላከያ አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፤ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ‹ለእኔ በጎ አመለካከት የላቸውም› በሚል የሚጠራጠራቸው ጄነራሎች በሥራ ላይ እያሉ የእሱ ጡረታ መውጣት ከመስሪያ ቤቱ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ያደሩ የሙስና ካርዶች የሚመዘዙበትን ዕድል ያሰፋዋል የሚል ነው፤ በተለይም በግዙፍ የቢዝነስ ሥራዎች ላይ በታላቅ ተፎካካሪነት እየተሳተፈ የሚገኘው ‹መቴክ› ምንም እንኳ ማረጋገጫዎች ባይቀርቡበትም በመከላከያ ሥር ከነበረበት ዘመን እስከ 2002 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከግዥዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ የሙስና ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው፡፡
መቴክ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በአዋጅ የልማት ድርጅት እንዲሆን ቢደረግም፣ ዛሬም ዳይሬክተሩ የሠራዊቱ አባል ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ ሲሆን፣ መከላከያ ደሞዝ የሚከፍላቸው ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞችንም እንዳቀፈ ይታወቃል፡፡ እናም ሳሞራ ሃሳቡ ከተሳካለት ለጥቂት ተጨማሪ ዓመታት በሥልጣኑ ላይ ሲቀጥል፣ አሊያም ‹የወንድ በር› ለማግኘት በትግሉ ዘመን የእርሱ ሰልጣኝ እንደነበረ የሚነገርለትን እና በቅርቡ ብቸኛው ከሜጀር ወደ ሌፍተናት ጄነራል ማዕረግ ያደገው ዮሀንስ ገ/መስቀል እንዲተካው መንገድ ጠረጋውን ማመቻቸቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ ይመስለኛል)
ይህም ሆኖ የተኮረኮርን ያህል የምንስቀው ጄነራል ሳሞራ የኑስ በቅርቡ ለታተመው ‹‹ህብረ ብሔር›› መፅሄት ሙስና ለሠራዊቱ አደገኛ መሆኑን እንዲህ በማለት መግለፁን ስናነብ ነው፡-
‹‹ሙስና ሠራዊቱን ሊያበላሸው ይችላል፡፡ ሙስና ፀረ-ልማት ነው፤ ሠራዊቱን ሊበትነው እና ሕዝባዊ ባህሪውን እንዲያጠፋ ሊያደርገው ይችላል፤ አንድ ሠራዊት ሠራዊት ነው የሚባለው እንደ ወታደር እንደ አንድ አካል ሲያስብ እንጂ ለግሉ ሲያስብ አይደለም፡፡ …በአጠቃላይ (ሠራዊቱ) በዚህ ነው የሚፈርሰው፡፡›› 
መቼም ጄነራሉ ይህንን የተናገረው እራሱን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ መኮንኖች እንደ እንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በተንጣለለ ቪላ ቤት ውስጥ፣ የተቀማጠለ ኑሮ መኖራቸውን ረስቶት አይመስለኝም፤ ‹ይህ የተንዛዛ ወጪያቸውም የሚሸፈነው ከደሞዛቸው በሚያገኙት ገቢ ነው› ብሎ ቧልት መሳይ ክርክር ሊያመጣ አይችልም፡፡ ይሁንና እታች ያለው ጭቁን የኢትዮጵያ ሠራዊት ምንም እንኳ በአለቆቹ ‹ቴክሳስ›ነት ላይ ለመቆጣት ባይደፍርም፣ እንደማንኛውም ዜጋ ለኑሮ ውድነትና አስከፊ ድህነት የተጋለጠ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
የሆነው ሆኖ ተሰሚነታቸው እየተቀዛቀዘ የመጣው አቦይ ስብሃት ነጋ ከወራት በፊት ለ‹‹ውራይና›› መፅሔት ‹‹ህወሓት ትንሳኤ ያስፈልገዋል›› በማለት የሰጡትን ምክር ተከትሎ፣ ጄነራል ሳሞራ እና አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ከድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ጋር በመተባበር ህወሓትን ለማጠናከር እና በፖለቲካ ውስጥ የነበረውን የአንበሳውን ድርሻ ለማስከበር (ጉዳዩን ከለጠጥነው ደግሞ ‹ለማስመለስ›) እየሰሩ እንደሆነ ይነገራል (በነገራችን ላይ የሳሞራና ጌታቸው ተፅእኖ መጨመሩን ለመረዳት፣ መከላከያ ‹አገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን ለመከላከል› በሚል ‹እጅግ ጥብቅ ሚስጢር ብሎ የሰየማቸውን የሰው ኃይል ፕሮፋይል፣ የሒሳብ መዝገቦችና ሰነዶች እና የክፍያ ማስረጃዎች ለማንም አካል እንዳይገለፅ› የሚያስችለውን ስልጣን፣ ደህንነቱ ደግሞ በስራ ላይ የሚፈፅማቸው ማንኛውም ጉዳዮች ወደፊት በህግ እንዳይጠይቅ እስከ መከላከል የሚደርሰውን አዲስ የተዘጋጁትን አዋጆች ማንበቡ በቂ ነው፡፡ በርግጥ እነዚህ ባለሥልጣናት እንዲህ ባለ ተመሳሳይ መንገድ እንዲጓዙ ያስተሳሰራቸው አንዱ ጉዳይ ‹ህወሓት ተዳከመ፣ ተሸነፈ፣ አበቃለት…› የሚለው የካድሬውና ደጋፊው ቁጭት እንጂ ወትሮም መልካም ግንኙነት ኖሯቸው አይመስለኝም)
ለማንኛውም በጥቅሉ ሲታይ የህወሓት ትልቁ ችግር ተብሎ በአመራር አባላቱ የሚጠቀሰው ‹በዚህ ወቅት ወደፊት መምጣት የሚችሉ ጠንካራ ቴክኖክራቶችን አለማፍራቱ፣ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያደርግለትን የታጠቀውን ኃይል ተጠቅሞ የፖለቲካ ልዩነቱን ጨፍልቆ በአሸናፊነት ይዞት መውጣት የሚችል መሪ እንዳይኖረው አደረገ› የሚል ነው፡፡ በርካታ የላይኛ እና የታችኛው ካድሬዎችም ‹ለእንዲህ አይነቱ ክፉ ጊዜ ድርጅቱ የሚያስፈልገው፣ በትግሉ ዘመን ልምድ ያካበተ ታጋይ ብቻ ነው› የሚል አቋም እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ስርዓቱ ከሚያራምደው ርዕዮተ-ዓለም ጋር ጠንካራ ትውውቅ ያሌለውን እና የትግሉን ዘመን በአሜሪካን ሀገር በማሳለፉ ‹የምዕራባውያን ድጋፍ አለው› ለሚባለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚሰጡት ዝቅተኛ አመለካከት መግፍኤም ይኸው ይመስለኛል፡፡
ለነገሩ እርሱም ቢሆን በጠንካራ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ካለመታነፁ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በሚያያዙ ምክንያቶች ለትንፋሽ ጊዜ የማይሰጠውን የድርጅት ሊቀ-መንበርነትንም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ የሚወራውን ያህል ይፈልገዋል ብሎ መደምደሙ አስቸጋሪ ነው ብዬ አስባለሁ፤ ከዚህ ይልቅ በተፈጥሮ ከታደለው የተግባቢነት ባህሪው አኳያ እንደ ሕዝብ ግንኙነት የመሳሰለ ብዙም የማያጨናንቅ ሥራን ይመርጣል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከሰለጠነበት ሙያ ጋር የቀጥታ ተያያዥነት ያለውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በሚመራበት ዘመን፣ ከውጭ ሀገር በርካታ የተቋረጡ ፈንዶችን እንደገና ለማስለቀቅ መቻሉ እንደ ታላቅ ስኬት የሚወራለት፤ አልፎ ተርፎም ‹ወባን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት ብርቱ ትግል አደረገ› ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር እስከ መሸለም የደረሰው እዚህ መስሪያ ቤት እያለ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት አስተዳደር ከህወሓት ሰዎች ትልቁን ስልጣን የያዘው ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከምዕራባውያን ጋር የቆየ ቀረቤታ እንዳለው ሰምቻለሁ፤ እንደሚታወሰው ደብረፅዮን ከክፍፍሉ በፊት (የደህንነት መስሪያ ቤቱ እንዲህ እንደ ዛሬው እጅግ ዘመናዊ በሆነው የቻይና ቴክኖሎጂ ሳይጥለቀለቅ) ከነበረው ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ላይ ተነስቶ፣ ቁልቁል ወርዶ በሁመራ በአንድ ዞን እንዲሰራ የተመደበው (ሁላችንም ስንገምት እንደነበረው) የአንጃው አባል ወይም ደጋፊ ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም የእነስዬ-ተወልደ ቡድን በመባል የሚታወቀው (‹አፈንጋጩ› ኃይል) ደብረፅዮንን በሲ.አይ.ኤ እና ሞሳድ ወኪልነት የመክሰሱ ጉዳይ የድርጅቱን በርካታ አባላት ቀልብ በመሳቡ፣ መለስ ይህንን ተከትሎ ከሚመጣበት አደጋ ራሱን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እስከ 1998 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በሁመራና ራያ አካባቢዎች በዞን ደረጃ ለማገልገል ተገዷል፡፡ እናም እርሱን የምዕራቡ ዓለም ፊት-አውራሪ አሜሪካና ሸሪኮቿ ወዳጅ ነው የሚያስብለው በቀድሞ መስሪያ ቤቱ በኩል በነበረው ግንኙነት ይመስለኛል።
የፖለቲካውን መዘውር የጨበጠው ኃይል
የዚህ ቡድን አምበል እንደ ድርጅት ብአዴን ቢሆንም፣ በቋሚ ተሰላፊነት ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አባዱላ ገመዳ፣ ሙክታር ከድር እና ሬድዋን ሁሴን እንደሚገኙበት ይነገራል፤ ለብአዴን ‹በተሻለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ለመገኘቱ መደላድል ፈጥሮለታል› የሚለውን ሙግት ምክንያታዊ የሚያደርገው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና ጥናት ምርምር አማካሪ በረከት ስምዖን፣ የኢህአዴግን የካድሬ ማሰልጠኛ ማዕከል በዳይሬክተርነት የሚመራው አዲሱ ለገሰ፣ ደርቦ ይዞት የነበረውን የትምህርት ሚኒስትርነት ለሽፈራው ደሳለኝ በመልቀቅ፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ የስራ ጊዜውን በግንባሩ ፅ/ቤት የሚያውለው ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ-ጉባኤው ካሳ ተክለብርሃን የያዙት ሥልጣን ያለውን የፖለቲካ አቅም መመዘኑ ይመስለኛል፡፡ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥም ከሳሞራ አንድ እርከን ዝቅ ባለ ሥልጣን ከሌሎች ሁለት ጄነራሎች ጋር የሚገኘው አበባው ታደሰ እንደ ቀድሞው በዕዝ አዛዥነቱ (በቀጥታ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን ማንቀሳቀስ የሚችልበት) ላይ ቢሆን ኖሮ ጥንካሬውን የተሟላ ማድረጉ አይቀሬ እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡
ከዚህ ሌላ ለእነበረከት ቡድን ተጨማሪ የፖለቲካ ጉልበት እየሆናቸው ያለው የኃይለማርያም ደሳለኝ ቢሮ እና በአባዱላ ገመዳ አፈ-ጉባኤነት የሚመራው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው፡፡ አባዱላ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ለማቅረብም ሆነ ለመታዘዝ ፍቃደኛ ያልሆኑ አንዳንድ ባለስልጣናት፣ በውስጥ መስመር በሚተላለፍለት ‹ጥቅሻ› በምክር ቤቱ በኩል የሚመለከተው የቋሚ ኮሚቴ አባላት አስጠርቶ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚገመግምበት ስልት እየተገበረ ነው፡፡ በአናቱም ምን ጊዜም የሳምንቱን የሥራ መጨረሻ ቀን አርብን ጠብቆ የሚሰበሰበው የሚኒስትሮች ም/ቤትን ከሞላ ጎደል ይህ ቡድን እየጠቀመበት ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ሚኒስትሮቹ በሚገናኙበት አብዛኛውን ሰዓት ሳይግባቡ (በጭቅጭቅ) ማሳለፋቸው ይነገራል፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአቶ መለስ ዘመን ም/ቤቱ የሚሰበሰበው የተለያዩ አጀንዳዎችን ለማቅረብ እና በቀረበው አጀንዳ ላይ ለመከራከር (ለመመካከር) ሳይሆን፣ መለስ ወስኖ የመጣበትን የሥራ ድርሻ ተቀብሎ ለመበተንና ሪፖርት ለመስማት የነበረው አሰራር፣ ዛሬ ተቀይሮ በርካታ የተነቃቁ ሚኒስትሮች የየራሳቸው ሃሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ (ለማንፀባረቅ) የሚታገሉበት መድረክ ወደ መሆን በመሸጋገሩ ነው፡፡ ይህም ሁናቴ ዋናውን የመንግስት ሥራ የመገምገም እና የማስፈፀም አቅምን ሳይቀር ከሚኒስትሮች ም/ቤት ወደ ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አሻግሮታል የሚያስብሉ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይሁንና በዚህስብሰባ ላይም ቢሆን ደፈር ብሎ ከበረከት ስምዖን እና አባይ ፀሀዬ የተሻለ አዳዲስ ሃሳብ የሚያቀርብ ባለሥልጣን እንደሌለ ሰምቻለሁ (በነገራችን ላይ ምክንያቱን ባላውቅም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹የፖሊሲና ጥናት ምርምር አማካሪ› ተደርገው የተሾሙት በረከት ስምዖን፣ አባይ ፀሀዬ፣ ኩማ ደመቅሳ እና ዶ/ር ካሱ ኢላላ የሥራ ቦታቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ሳይሆን መገናኛ አካባቢ በሚገኝ አንድ ህንፃ ላይ ነው፡፡ የተሰጣቸው ኃላፊነት ኃይለማርያምን በቅርብ እንዲያገኙ ከማስገደዱ እና በግልፅ ከሚታወቀው የአማካሪ አስፈላጊነት አኳያ ካየነው ግን ግራ የሚያጋባ ይመስለኛል)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ…
ኃይለማርያም ደሳለኝ ይህንን ቦታ ከያዘ በኋላ፣ ብዙዎች በስልጣኑ የማዘዝ አቅሙ ላይ አመኔታ እንደሌላቸው (አንጋፋ ታጋዮች እንደ ‹አሻንጉሊት› ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ) ደጋግመው መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ በግልባጩ ‹አፈንግጦ ለመውጣት መሞከሩ አይቀሬ ነው› የሚሉ ግምቶች ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ መላ-ምቶች ዛሬም ድረስ እልባት ባያገኙም፣ እዚህ ጋ ያልጠቀስኳቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያሳያቸው ወጣ ያሉ አቋሞቹን ሳስተውል ግን፣ አሁን ያለው አሰላለፍ (የአነበረከት እና አባዱላ ፖለቲካዊ መጠናከር) ለእርሱም የተረፈው ይመስለኛል፡፡ እንዲሁም ከቤንች ማጂ የተባረሩ አማርኛ ተናጋሪዎችን አስመልክቶ በድርጅቱ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ‹አጥፊዎቹ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ› ከማለት አንስቶ (በነገራችን ላይ በአማካሪ ብዛት እንዲከበብ ካደረገው ምክንያት አንዱ ጓዶቹ በዚህ ንግግሩ መበሳጨታቸው ነው) በቅርቡ ህወሓትን ለመሸምገል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ‹ሁኔታዎች እንዲህ እየተካረሩ ከሄዱ ወደ ማሰሩ መግባታችን አይቀርም› በማለት ማስፈራራቱ እና በቴዎድሮስ አድህኖም የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የመቆጣቱ ጉዳይ ድረስ የሚካተቱ እውነታዎች ሰውየው የራሱን መንገድ ለመከተል እየሞከረ መሆኑን ያሳያሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
የሆነው ሆኖ እነዚህ ሁናቴዎች የፖለቲካውን ጉልበት ሙሉ በሙሉ በብአዴንና በተባባሪነት በጠቀስኳቸው የኦህዴድና ደህአዴን የአመራር አባላት አካባቢ ቢያከማቻቸውም፣ በማንኛውም ሰዓት ያሻውን ማድረግ የሚችለው የታጠቀው ኃይል ደግሞ ከህወሓት ጎን እንደተሰለፈ ይገኛል፡፡ መጪውን ጊዜም አዲስ ክስተት እንድንጠብቅ ገፊ ምክንያት ይህ አይነቱ የኃይል አሰላለፍ ይመስለኛል፡፡
ምን እንጠብቅ?
ከረጅሙ የፓርቲ ፖለቲካና መንግስታዊ መንገራገጮች በኋላ፣ የሁለቱንም የኃይል መሰረቶች ጠቅልሎ በመዳፉ ሥር የከተተው መለስ ዜናዊ በሞተ ማግስት ‹የኃይል መገዳደሮች ሊከሰቱ ይችላሉ› የሚለው የብዙዎቹ ግምት ነበር፤ ከወራት በፊት አስነብቤ በነበረው ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍም ግምቶቹ እውን መሆን እንደ ጀመሩ ማሳያዎች ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ራሳቸውን ያቧደኑት ኃይሎች ዋነኛ ግብ ከሥልጣን የሚነሱ ጥቅሞችና አነስተኛ የየራሳቸው ፓርቲ ፍላጎቶች የፈጠሩት በመሆኑ፣ እንደ ሟቹ ደመ-ቀዝቃዛ አምባገነን አይነት በጠንካራ መዳፍ ሥር የሚያሰባስባቸው ባለመገኘቱ በየጊዜው የኃይል መሸጋሸጎች ሊከሰቱ እንዲችሉ አድርጓቸዋል፤ አሁንም እየተስተዋለ ያለው ይኸው እውነታ ነው፡፡ በዚህ አውድ ላይ ቆመን ሊፈጠሩ የሚችሉ የቢሆን ሃሳቦችን ስናስቀምጥም በጠረጴዛው ላይ የምናገኘው ሁለት ዕድሎችን ይመስለኛል፡፡
የመጀመሪያ ሲናሪዮ የሚሆነው ከላይ የጠቀስኩት ቡድንተኝነት እንዳለ ሊቀጥል ይችላል የሚል ነው፤ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ባለኝ መረጃዎች መሰረት የፖለቲካውን መስመር የያዘው ቡድን መሪ አባላት፣ አሁን ያላቸውን መንግስታዊ ሥልጣን ጠብቀው መቆየትን መሰረታዊ መሰባሰቢያ አጀንዳ ማድረጋቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሳሞራና ጌታቸው ጥምረት ህወሓትን ወደ ቀደመው ዘመኑ ለመመለስ ቢሻም፣ ሊሄድበት የሚችልበት መንገድ አደገኛ መሆኑ (ወታደራዊ ላዕላይ መዋቅሩንና የደህንነት ኃይሉን ከመያዙ አኳያ) ሁኔታዎችን ባሉበት ይዞ መቀጠልን በትርፍ-ኪሳራ ስሌት የተሻለ አማራጭ አድርጎ ይወስደዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሁለተኛው የቢሆን ዕድል፣ ዳግመኛ የኃይል መሸጋሸግ ሊፈጠር መቻሉ ነው፤ ሰዎቹ ጥቅመኛ በመሆናቸው የቋንቋ ተናጋሪነት ልዩነቶቻቸውንና የኋላ የመቆራቆስ ታሪኮቻቸውን ተሻግረው፣ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ሌላ መልክ ያለው ስብስብ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል፤ ይህ አይነቱ አዲስ የኃይል አሰላለፍም፣ ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በፊት በማይታወቀው ተሰዊና ሰዊ ሊጠናቀቅም ይችላል፡፡
በመጨረሻም ምንም ይፈጠር ምን፤ እኛን ሊያግባባን የሚገባው ጭብጥ፣ የትኛውም ቡድን በግንባሩ ውስጥ ቢነሳ፣ የማዕከላዊ መንግስቱን ህልውና ወደሚበታትን ሂደት መግባቱ ሊሰካለት አለመቻሉ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ መልኩ ሄዶ የሚጣሉበትን ጠረጴዛ መስበሩ ምን እንደሚያስከትል ያውቁታልና ወደዚህ ምዕራፍ እንደማይሻገሩ አምናለሁ፡፡ ይሁንና ከፓርቲው ዝግነት እና ከፖለቲከኞቹ አቋም የለሽነት አንፃር አሁንም ሆነ በቀጣይ ጊዜያት ከማንም ግምት ውጪ ያሉ ክስተቶች እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት ሳይታሰብ ግንባሩን ሊያተራምሱት ይችላሉ ብሎ መገመቱ አግባብ ይመስለኛል፡ ,,,,,,       / ዘሀበሻ/