FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, December 11, 2013

“የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ከማንዴላ ጋር መያያዟን እጠራጠራለሁ” ፕሬዚዳንት መንግሥቱ

ለማንዴላ የገንዘብ ድጋፍ ሰጥተናል፣ ታምመው አስታመናል

mengistu-hailemariam


የኔልሰን ማንዴላን ሕልፈት በማስመልከት አውስትራሊያ ከሚገኘው ኤቢኤስ ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ መንግሥቱ ለሬዲዮው በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ በእሳቸው በትረ ሥልጣን ወቅት ማንዴላ የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት ከመጎናፀፈቸውም ባሻገር፣ የአንድ መቶ ሺሕ ዶላር ገንዘብ ተበርክቶለቸዋል፡፡ ይህና ቀሪው ንግግራቸው እንዲህ ቀርቧል፡፡
‹‹ማንዴላና የተወሰኑ ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በስውር መጥተው፣ ወታደራዊ ሥልጠና አግኝተውና እግረ መንገዳቸውን ሞሮኮን ጐብኝተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን ተገንዝቤያለሁ፡፡
‹‹በዚያን ጊዜ አሜሪካኖች በአማካሪነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ፡፡ እስራኤሎችም ነበሩ፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ የማንዴላን ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘትና ወታደራዊ ሥልጠና በመከታተል እግር በእግር እየተከታተሉ መረጃ ሲሰበስቡ ስለሰነበቱ፣ ሰውየው አገራቸው እንደደረሱ ወዲያውኑ እጃቸው ተይዞ ወህኒ ቤት ገብተዋል፡፡
‹‹በሮቢን ደሴት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ ከአንድም፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ጆሃንስበርግ ውስጥ ታስረዋል፡፡ የመጨረሻውና ትልቁ ለ27 ዓመት የታሰሩበት ጊዜ ነው፡፡
‹‹እኔ ማንዴላን በስም እንጂ በገጽ አይቼ አላውቅም፡፡ ልጆች ሆነን በምንሰማው ሁሉ ስለአፓርታይድ ያለንን ጥላቻ በተለያየ መልኩ የምንገልጽ ሰዎች ነበርን፡፡ በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ተለቅቀው በመጀመሪያ ደረጃ ዚምባቡዌ በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ በዚያን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት ጊዜ እሳቸውም የስብሰባው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ጤናቸው በጣም የተጐሳቆለና ብርድ ቢጤም መትቷቸው ታመው ስለነበር እኛ ዘንድ ከአንድ ሳምንት በላይ አስታምመናል፡፡ ጠና ያለ በሽታ ስለነበር ሐኪሞች ተሰባስበው የሚቻለውን ሕክምና ሁሉ አድርገው አስታምመናል፡፡
‹‹ስለታሪካቸው፣ ስለ ወህኒ ቤቱ፣ ስለሌላውም ሁሉ በሰፊው አነጋግሬያቸው አጫውተውኛል፡፡ በመጨረሻም የጠየቁኝ ነገር ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ ከእስር ቤት እንደወጡ ስለዓለም ወቅታዊ መረጃ ያላቸው ግንዛቤ ውስን ስለነበረ እንዴት ሆኖ ነው ሶቪየት ኅብረት እንዲህ ዓይነት ሥራ የሠራው? ለመሆኑ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ አልተደረገም ወይ? አልተነጋገራችሁም ወይ? በዚህ መልኩ እንዴት ነው አብዮት የተቀለበሰው፣ ወዘተ በማለት እነ ጐርባቾቭ ስለሠሩት ሥራ በመጸጸት፣ የእኔ አገር ለሶሻሊዝም በጣም የተመቻቸች (ፈርታይል) ነች፤ የምናራምደው ይኼንኑ ነው አሉኝ፡፡ አይ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ ከመድረስዎ በፊት እስቲ ጊዜውንና ወቅቱን ይዩት፡፡ እርስዎ ዓለምን የሚያውቁበት ሁኔታ በእስር ቤቱ ምክንያት ምን እንደሚመስል ትንሽ ሰንብተው ይመልከቱና የሚወስዱትን ዕርምጃ ቢያመዛዝኑ ይሻላል፡፡ እኔ የምደግፈውና እናንተም ያነሳችሁት መፈክር ‹አንድ ሰው አንድ ድምፅ› (ዋን ማን፣ ዋን ቮት) ባላችሁት መርህ መሠረት የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ነፃነቱን ያግኝና ከዚያ በኋላ የትኛውን የዕድገት አቅጣጫ እንከተል የሚባለውን ነገር ልታዩት ትችላላችሁ አልኳቸው፡፡ ይህን ያህል ነው የተነጋገርነው፡፡
‹‹በእኛ በኩል ምን የምንረዳው ነገር ካለ ብንላቸው ምንም ነገር የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ውሳኔ ነው የተፈታሁት፡፡ ነፃነታችንም በዚሁ መልኩ የተገኘ ስለሆነና ሌላ ትግል የሚጠይቅ ባለመሆኑ ምንም ዕርዳታ አያሻኝም አሉ፡፡ እኔ እንኳ ትጥቅ ወይም ሌላ ያስፈልግ ይሆን በሚል ነው የጠየቅኳቸው፡፡ ለሰውየው ትልቅ ክብር ስላለኝ በመሪ ደረጃ ያን ጊዜ ባይሆኑም አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሸኘኋቸው፡፡ የዚያን ጊዜ ኦሊቨር ታምቦ በፅኑ ታሞ ስለነበር እርሱን ስዊድን ሄጄ ልጠይቅና ህንድ ደርሼ ወደ አገሬ እመለሳለሁ አሉኝ፡፡
‹‹መቼም ከእስር ቤት ነው የወጡት፡፡ ምንም ነገር የላቸውም በሚል ግምት አንድ መቶ ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ቼክ ሰጠኋቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የተገናኘነው ዚምባቡዌ ነው፡፡ ዚምባቡዌ በዚያን ጊዜ የገለልተኛ ንቅናቄን ታስተናግድ ስለነበር በዚያን ጊዜ ነው የተገናኘነው፡፡
mengie and madiba‹‹ብዙ ሰዎች ሰውየውን ለማነጋገር ያስቸግሩ ስለነበርና የነበራቸውም ጊዜ በጣም ውስን ስለበር እኔም በዚያ ላይ ተጨምሬ ማስቸገር አልፈለግሁም፡፡ ማንዴላ እንደ ብርቅ ናቸው፡፡ ግማሹ ቀርቦ ለማነጋገር፣ ምን ዓይነት ሰው ነው፣ ምንስ ይመስላል በሚል ብዙዎች መሪዎች ከፍ ያለ ጉጉት ስለነበራቸውና የማነጋገር ጊዜ ስላነሰ፣ እኔ በዚህ ጊዜ ፕሮቶኮሌን ልኬ ሳነጋግራቸው፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ ሰው ናቸው፡፡ እንጃ ምን ያህል እንደሚያነጋግሩዎት አሉኝ፡፡ አይ እንግዲያውስ እግረ መንገዳችንን ስብሰባው ላይ እንዴት ነዎት? ተሻለዎት? ምን አዲስ ነገር አለ? አልኳቸው፡፡ አመሰግናለሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተደረገልኝ ሁሉ በሚል ተለያየን እንጂ የሰፋ ውይይት አላደረግንም፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ እንደሚታወሰው በከፍተኛ ክብርና ሥርዓት በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያን የክብር ኰርዶን ነው የሸለምናቸው፡፡ ስለተደረገው ትግልና ስለሳቸው ማንነትም ሰፋ ያለ ንግግር አድርጌያለሁኝ፡፡ በዚያው መሠረት እሳቸውም አንፃራዊ መልስ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያውቋት፣ ኢትዮጵያ ብቸኛ የነፃነት ኰከብ ሆና እንደኖረችና ከልጅነት ጀምሮ ኢትዮጵያን ሲያስቡ፣ እንደተስፋ ሲመለከቱ የኖሩ መሆናቸውን፣ በሒደትም ያዩትና የተገነዘቡት ይኼንኑ መሆኑን የሚገልጽ ታሪካቸውን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ተመልሼ መጥቼ መካከላችሁ ስቆም የሚሰማኝ እንደገና የመወለድ ዓይነት ነው በሚል በጣም ልብ የሚነካ ንግግር አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ዚምባቡዌ ከመገናኘታችን በቀር አላገኘኋቸውም፡፡ ከፕሬዚዳንትነት ወርደው ሌሎች ሥራውን በሚመሩበት ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ችግር ይደርስባቸው ስለነበር ኢትዮጵያውያንን አትንኩ፣ አገራቸው ነው፣ ይኑሩ ተንከባከቧቸው ብለው በታቦ ምቤኪ ጊዜ በመናገራቸው ዛሬ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይኼ ነገር በከፍተኛ ደረጃ ይሰማቸዋል፡፡ የሰሞኑም ሐዘን በኢትዮጵያውያን ላይ ልዩ ስሜት እንደሚያሳድርባቸው አልጠራጠርም፡፡ ይኼን ነው የማውቀው፡፡ ሌላው ጽፈዋል፡፡ ‹ረጅሙ ጉዞ› የሚውን መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ እዚያ መጽሐፍ ውስጥ ስለኢትዮጵያ የሚያውቁትን፣ ያዩትንና የተደረገላቸውን ነገር አትተው በአክብሮትና በፍቅር ጽፈዋል፡፡ ይኼንን ነው ስለማንዴላ የማስታውሰው፡፡
በማንዴላ ሕልፈት ምን ተሰማቸው?
እዚህ በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ የምንገኝ ሰዎች የሰውየውን የጤና ሁኔታ እናውቃለን፡፡ በየጊዜውም እንሰማለን፡፡ መሪዎች ወንድሞቼም ሁሉን ነገር ስለሚያውቁ ይነግሩኛል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሰውየው ዕድሜያቸው ውስን እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሆስፒታልም ለመጀመሪያ ጊዜ በረጅሙ መቆየታቸው፣ ልባቸው በከፍተኛ ደረጃ መታወኩ ብሎም መናገር እንደተሳናቸውና እንዳይሞቱ ያህል ይጠበቁ ስለበር፣ ነገ ተነገወዲያ ከማለት ባሻገር ስለሰውየው በቂ ግንዛቤ ስለነበር፣ ሕልፈታቸው እንግዳ ወይም ያልተጠበቀ ነገር አልሆነም፡፡ ያዘንነው ቀድም ብሎ ስለሆነ ሞታቸው ለኔ በግሌ ልዩ ሁኔታ አልፈጠረም፡፡
ወደፊት እንዴት ያስታውሷቸዋል?
እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ስለደቡብ አፍሪካ መተንበይ ያስቸግረኛል፡፡ በውጪው ዓለም በብዙ እንደሚነገረው ለረዥም ጊዜ በእስር መማቀቃቸውና ለነፃነት መታገላቸው ብዙ ብዙ የሚደነቅ፣ የሚወደዱበት፣ የሚከበሩበትና ጀግና የሚያሰኛቸው ሥራ ቢኖርም በሌላ በኩል ደግሞ ውስጥ ያሉ የትግል አጋሮቻቸውንና ጓዶቻቸው በአንዳንድ ችግርና ድክመት ምክንያት ደስተኞች አይደሉም፡፡ ተቃዋሚም አላቸው፡፡ ይኼንን የውጭው ዓለም በውል የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ እስር ቤት በነበሩ ጊዜ ረዥምና ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነው እንለቃችኋለን ነፃነታችሁን ታገኛላችሁ፣ አመራርም ላይ ትቀመጣላችሁ፤ ነገር ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ደቡብ አፍሪካን ልትለውጡ አትችሉም፡፡ የነጩን ኅብረተሰብ ሀብት ንብረት ልትነኩ አትችሉም፤ ወይም የጊዜውን ሶሸሊዝም ወይም ማኅበራዊ ሥርዓት የሚባል ነገር አይታሰብም፡፡ በዚህና በዚያ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር ፈቃዳችሁ ከሆነ ነፃነታችሁን ለመስጠት በሚል መንገድ ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ተፅዕኖ የተደረገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወጥተው ያለውን ሥርዓትና ኢኮኖሚ እንዳለ ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ምድር በጥቁር ሕዝብ ላይ ግፍ ተፈጽሞ እንደሆነ ደቡብ አፍሪካን የሚያክል የለም፡፡
መግደል፣ መግረፍ፣ ማሰቃየት፣ ማሰርና ማስራብ ብቻ ሳይሆን ወይም ኢሰብዓዊ የጉልበት ሥራ ማሠራት ብቻ ሳይሆን ጥቁሮች እንዳይራቡ፣ እንዳይወለዱ በየምክንያቱና በጤና ችግር ወደ ሆስፒታል በሚሄዱበት ጊዜ በሚስጥር እንዳይወልዱ እያመከኑ የኖሩ ናቸው የአፓርታይድ አራማጆች፣ ነጮቹ፡፡ ብዙዎቹ ጥቁሮች ለዚህ ያላቸው ጥላቻ ወሰን የለውም፤ መናገር ያቅታል፡፡ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ከእነሱ ጋር መኖር አለበት ወይ? የሀብት ክፍፍሉና የኑሮ ሁኔታም በእንዲህ ዓይነት መልኩ መቀጠል አለበት ወይ? የሚሉ ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ማንዴላ የሚታሰቡበትና የሚከበሩበት የ27 ዓመት እስር ብሎም ደግሞ ነፃነት የማምጣቱ ጥረት አሁን ያለችውን ደቡብ አፍሪካ የመፍጠሩ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የወደፊቷን ደቡብ አፍሪካ በሚመለከት አዲሱ ትውልድ ያለው ዓላማ ከእነማንዴላ የተለየ ነው፡፡ ዛሬ ነፃነት አለ ብለው ብዙዎች አያምኑም፡፡ የነፃነት ሰንደቅ ዓላማ ነው የምናውለበልበው እንጂ ሁሉም ነገር የነጮች በመሆኑ፡፡ ተወላጁ ቦታ የለውም ተብሎ ስለሚታመንና እውነትም ስለሆነ የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ ከማንዴላ ጋር መያያዟን እጠራጠራለሁ፡፡ (ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment