FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, December 25, 2013

ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ?

ማስተዋል ደሳለው

ላለፉት 8 እና ዘጠኝ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ አያደገ ነው ሲባል እንሰማለን፤  የእድገት ፍጥነቱ  ላይ የሚነሱ በርካታ ጥያቄውች  ቢኖሩም መንግስት  የመንገድ ግንባታ ፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታወችን እና መሰል ነገሮችን  በመጥቀስ እድገት እንዳለ አስረግጦ ይከራከራል::  በሌላ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱ ተመዘገበ በሚባልባቸው ዓመታት በዋጋ ንረት የህዝቡ ኑሮ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ  እንደሆነ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው:: ታዲያ  የኢኮኖሚ እድገት አለ በተባለባቸው ዓመታት የህዝቡ ኑሮ ለምን አሽቆለቆለ? ይህን ጥያቄ ከ 7 ዓመት በፊት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ  ተጠይቀው የሰጡት መልስ የዋጋ ንረቱን የኢኮኖሚ እድገቱ እራሱ የፈጠረው ጉዳይ ነው ነገር ግን ቀስ በቀስ እድገቱ ሲቀጥል ራሱ እድገቱ ችግሩን ይፈታዋል ብለው ነበር፤ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በዃላም እንኩአን ሊሻሻል  የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰበት ሂዷል::  ችግሩ የተለያዩ  ምንጮች ቢኖሩትም በዋናነት በ 2 ከፍሎ ማየት ይቻላል::
፩. የኢኮኖሚ እድገቱ ምንጭ
፪. የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር
የኢኮኖሚ እድገት ማለት በአጭሩ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨማሪ ሀብት መፍጠር ማለት ነው::  በመጀምሪያ ላለፉት 8  እና ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ  የተፈጠሩት ተጨማሪ ሀብቶች ምንድን ናቸው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ፤  በአብዛኛዉ ሀገሪቱ ዉስጥ የተፈጠሩት ሀብቶች ከመንገድ ፣ ከሕንፃ እና ከ ከኃይል ማመንጫ ከግንባታ ጋር የተያያዙ ናቸው:: በመቀጠልም የዚህ ሀብት የገንዝብ ምንጭ ምንድን ነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል፤ የገንዘቡ ምንጭ በዋናነት ከብድር እና እርዳታ የተገኘ ሀብት ነው ፣ በተለይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ 1998 ዓም ጀምሮ በሶማሊያ በመጀመሪያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት በመቀጠልም የአልሻባብ እንቅስቃሴ መጠናከር ለኢትዮጵያ ትልቅ ሲሳይ ይዞ ነው የመጣው:: በሶማሊያ ያለዉን ሁኔታ  ለመቆጣጠር ምዕራባዉያኑ የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ  በዋና አጋርነት የተሰለፈችዉ ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንት ዓመታት በየዓመቱ በቢልየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በእርዳታ መልክ ከምዕራብ ሃገራት እንድታገኝ አድርጓታል:: ይህም ማለት ሀገሪቱ ዉስጥ የጎላ  የኢኮኖሚያዊ መዋቅር ፣ የአሰራር ስርዓት  እና የቴክኖሎጅ ለውጥ ሳይኖር ከፍተኛ ገንዘብ ወደኢኮኖሚው ፈሰስ እንዲሆን አድርጓል:: በሌላ አገላለፅ  የቆየው የሀገሪቱ  ኢኮኖሚ የጎላ የምርት ጭማሪ ሳይኖረው ከዉጭ የተገኘ ብድር እና እርዳታ ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ተጨመረ እና የኢኮኖሚዉ መጠን አደገ ማለት ነው::  ስለዚህ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ሊያሻሽል የሚችል የግብርና እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የጎላ  ለዉጥ ሳይታይ ለመሠረት ልማት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ ፈሰስ የተደረገው ገንዝብ የገንዘብ አቅርቦትን (Money Supply) በመጨመር እና  የአገልግሎት ዘርፉ ( Service sector) ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተነጥሎ እንዲለጠጥ እንዲሁም ዋጋ እንዲንር በማድረግ አብዛኛዉን ሕዝብ ለችግር አጋለጠ ::
ከብድር እና እርዳታ የተገኘው ገንዘብ መሰረተ ልማት ላይ ሲዉል ከላይ የተገለፀው ችግር ቢኖርበትም በአንፃሩ የመሰረተ ልማት መስፋፋት የማምረቻ ወጭ ( cost of production) እንዲቀንስ በማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም አለ ፤ በተጨማሪም ገንዘብ ገንዘብን ይፈጥራል “ money creats money” በሚለው የኢኮኖምክስ  መርህ መሰረት ኢኮኖሚዉ ዉስጥ የተረጨው ገንዘብ በአብዛኛዉ አገልግሎት ዘርፉ ላይ የፈጠረው ተጨማሪ ሀብት አለ:: ነገር ግን ይህ የተፈጠረ ተጨማሪ ሀብት በጠንካራ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ስላልተመራ ወደጥቂት ሰወች እጅ እንዲገባ ሁኗል::  ሃብቱ እጃቸው የገባ ሰወችም የኢኮኖሚዉን መዋቅር ሊለዉጡ የሚችሉ እንደኢንዱስትሪ አይነት ዘርፎች ላይ ከመሰማራት ይልቅ ከሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለዉን የከተማ ቦታ በኢንቨስትመንት እና በሊዝ ስም በመዉሰድ ህንፃ በመገንባት እየተለጠጠ ላለው የአገልግሎት ዘርፍ በማከራየት በአቁአራጭ ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ ተጠቀሙበት::
በሌላ በኩል የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ስርዓት በሙስና የተጨማለቀ እና ወጥ ስላሆነና አዳዲስ ብቅ ለሚሉ ባለሀብቶች መሬት ማግኘት ከባድ ስለሆነ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ወሳኝ ሀብት (strategic resource) የሆነዉን የከተማ ቦታ ቀድመው የያዙ ባለሀብቶች የገቢያ ዉድድሩን ሚዛናዊ እንዳይሆን በማድረግ አዲስ የሚፈጠሩ ተወዳዳሪያቸውን በቀላሉ ከገቢያ ያስወጣሉ:: በተጨማሪም እንደነዚህ አይነቶቹ  ባለሀብቶች በአብዛኛው የፖለቲካዉ እና የግዥዉ ፓርቲ ጥገኛ ስለሆኑ የሚጠበቅባቸዉን ያክል  ግብር እና ታክስ አይከፍሉም:: ሥራቸዉን ስለሚያውቁም በሀገሪቱ በረጅም ጊዜ ሊከሰት ይችላል ብለው የሚፈሩትን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ስለሚሰጉ የሚያገኙትን ትርፍ ወደዉጭ ያሽሻሉ ፤ በጎን ሙሰኛ ባለስልጣናትም የሚዘርፉትን ገንዘብ ከሀገር ያሸሻሉ:: ከዚህ ላይ ፋይናንሽያል ትራንስፓረንሲ ኳሊሽን  ያወጣዉንና ኢትዮጵያ በህገወጥ የገንዘብ ፍሰት (illicit financial flow) በፈረንጆቹ ከ 2000 እስከ 2009 ያጣችዉን 11. 7 ቢልየን ዶላር ልብ ይሏል::
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጤናማ ሁኖ እንዲያድግ ከተፈለገ ከላይ የተጠቀሱት  የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መዋቅር ድክመቶች መስተካከል የሚገባቸዉ ሲሆን ፤ በዉጭ ብድር እና እርዳታ ላይ መንጠልጠሉን ቀንሶ ከሀገር ቤት በፍትሃዊነት ከሚሰበሰብ ግብር ሊሆን ይገባል:: ከዉጭ የሚገኘዉን ሀብትም  በብዛት መሰረተ ልማት ላይ ብቻ ማዋሉ የሚያስከትለዉን ችግር ጥልቅ ጥናት በማካሄድ  መመርመር እና  ገንዘቡ ከመሰረተ ልማቱ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪው እና የእርሻዉን ዘርፍ መዋቅር ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማስቻልም መሰራት አለበት:: ከሁሉም በላይ ግን የኢኮኖሚ ነቀርሳ የሆነዉን ሙስና ለማስወገድ ከአንድ ፓርቲ የበላይነት ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መሸጋገር እንዲሁም ተጠያቂነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ እንደገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ፣ የግል መገናኛ ብዙሃን  የመሳሰሉትን ተቋማት መፍጠር ያስፈልጋል:: ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ ሽህ ጊዜ ብታድግ የኢኮኖሚውን ፍሬ ጥቂቶች እየበሉ የአብዛኛዉ ሕዝብ  ኑሮ ማሽቆልቆሉ ይቀጥላል::

No comments:

Post a Comment