FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Wednesday, January 1, 2014

ማቆሚያና ገደብ ያጣው የፖለቲካ እስረኞቹ ስቃይ!

በዛሬው አጭር ፅሁፌ ላተኩረው የምፈልገው በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ስቃይ ላይ ነው። ገዢዎቻችን ምንም አይነት የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ምን ያህል እውነት ነው የሚለውን ለአንባቢዎቼ እተወዋለሁ። የቃሊቲ ወህኒ ቤት ማረሚያነቱ ምን ላይ እንደሆነ ስላልገባኝና ስላልታየኝ ጭምር ወህኒ ቤት ለማለት ተገድጃለሁ። ስለዚህም የቃሊቲ ወህኒ ቤት የሚለውን ቃል እጠቀማለሁ።
የፖለቲካ እስረኛ የሆኑት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳን ባደረባቸው ህመም ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ሪፈር ተፅፎላቸው በቃሊቲ ወህኒ ቤት ይገኛሉ። ሆኖም በቃሊቲ ወህኒ ቤት በኩል ተገቢውን ትብብር እየተደረገላቸው እንዳልሆነ የእስረኛ ቤተሰቦች አስታውቀዋል። ከጅምሩም የፖለቲካ እስረኞቹን ወደ ዝዋይ ማዘዋወር ያስፈለገው ቤተሰቦቻቸው ፣ ወዳጆቻቸውና አድናቂዎቻቸው እንደልብ እንዳይጠይቋቸው በማድረግ የፖለቲካ እስረኞቹ ላይ የሞራል ስብራት ለማድረስ ነው። ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ የፖለቲካ እስረኞቹ ተገቢውን ህክምና እንዳያገኙ እየተደረገ ይገኛል። የትኛውም እስረኛ  ህክምና የማግኘት መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም እስረኛው የፖለቲካ እስረኛ ከሆነ ግን ይህ መበቱን ይነፈጋል። ለዚህ ደግሞ ተጨባጭ ማስረጃ ካስፈለገ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን እና አቶ ክንፈሚካኤል አበበን (አበበ ቀስቶ) ሁኔታ ማንሳት ይቻላል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ሪፈር ተፅፎለት ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ቢዛወርም የቃሊቲ ወህኒ ቤት ምንም ህክምና ሳያደርግለት ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት እንዲመለስ ወስኗል። ውበሸት ባልታወቀ ምክንያት ያንኑ ዕለት ምሽት ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት እንዲመለስ መደረጉን እና ተመልሶ የመጣበት ምክንያት እንደማይታወቅ  የውብሸት ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለኢትዮ-ምኀዳር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስታውቃለች። ይህን ሁላ ማጉላላት ለምን አስፈለገ? የዝዋይ ማረሚያ ቤት ሪፈር ፅፎለት የቃሊቲ ወህኒ ቤትስ ለምን ህክምናውን ሊነፍገው ፈለገ? እኮ ለምን? የከፋ ነገር ቢመጣስ  ተጠያቂነቱን ማን ሊወስድ ነው? እነዚህ ሁላ አፋጣኝ መልስ የሚሹ ጥያቄ ናቸው።
የቃሊቲ ወህኒ ቤት ወደር የለሽ ግፉን መፈፀሙን በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ብቻ አላበቃም። በመኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ክንፈሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ላይም በተመሳሳይ ግፍ ተፈፅሟል። ፓርቲው እና ቤተሰቦቻቸው ለኢትዮ-ምኀዳር ጋዜጣ አቶ ክንፈ ሚካኤል በጠና ታመው ህክምና አለማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ሁላ እየተደረገ የሚገኘው በቃሊቲ ወህኒ ቤት አስተዳዳሪዎች ነው። ይህ ድርጊት ከማንአለብኝነትና ከእብሪት የሚመነጭ ነው። ከዛም ባለፈ የእኛም ድርሻ አለበት። ይህ ሁላ ግፍ እየተፈፀመ ሰምተን እንዳልሰማን ፣ በእኛ ወይ በእኔ ላይ ካልደረሰ ምን አገባኝ ስለምንል መሆኑን መርሳት የለብንም። እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ የእኛን ድምፅ ይሻሉ። ድምፃችንን ከፍ አድርገን ልናሰማ ይገባል!
Kinfe Michael Abebe (Abebe kesto)

No comments:

Post a Comment