ብርሃኔ አሰበ አለሁድረስ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ፣መልካም የአየር ፀባይ ያላት፣ህዝቦቿ የራሳችን አኩሪ ባህልና ወግ ያለን፣የራሳችን መልካም መልክዓ ምድራዊና አሰፋፈር ያለን በጋራ ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት በየትኛውም ዘመን ሉአላዊነቷ ያልተደፈረ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ናት። በተለያየ ወቅት የተፈጥሮ ሃብቷን ለመቀራመትና ሉአላዊነቷን ለመዳፈር የሞከሩ ሃገራት ሁሉ፣በውድ ልጆቿ የተባበረ ክንድ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተው ኢትዮጵያን ዳግም እንዳይመኟት የተባረሩበትና የኢትዮጵያን አይበገሬነት በአፍሪካም ሆነ በአለም መድረክ ያስመሰከረች፣ አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ በማቆየት በአለም ታሪካዊ ስፍራ ያላት፣ በቀደምት ውድ ልጆቿ የደም መስዋዕትነት ሀገራችን ሉአላዊነቷ ሳይደፈር ለብዙ ሺ አመታት ቆይታለች።
በአሁኑ ስዓት ኢህአዴግ/ህወሃት ለግልና ለግዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል የኢትዮጵያን አንድነት በማደብዘዝ እንሆ በእኛ ዘመን ለዘመናትተደፍሮ የማያውቀውን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ባለቤት የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሳይወያዩበትና ሳያፀድቁት በጓሮ በር የኢትዮጵያን መሬት ለባዕድ ሃገር/ሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ሽርጉዱን ተያይዞታል። ከአመታት በፊት በምዕራቡ የሃገራችን ክፍል /ድንበር በኩል/ በመሸራረፍ ለም የሰሊጥ ምርት የሚሰጥ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም በማለታችን እንሆ ዛሬ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ ፣ የኢትዮጵያን ቅርጽ የሚያጠፋ ረጅም ርዝመት ያለው ለም መሬት ለሱዳን ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሰማን።
ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን መሰሪ ተግባር አንድነታችንን አጠናክረን መግታት ካልቻልን ነገ ደግሞ በሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ በኩል የኢትዮጵያ መሬትተቆርሶ ለሌሎች አጎራባች ሀገራት ላይሰጥ ምን ዋስትና አለን?
አያቶቻችንና አባቶቻችን ደማቸውን ገብረው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን የሀገር ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ የአሁኑ ትውልድ የታሪክ ግዴታ ነው። ይህን የታሪክ ግዴታችንን ሳንወጣ ችል በማለት በመሰሪው የህወሃት/ ኢህአዴግ አመራር የሃገራችን ሉአላዊነት እየተሸራረፈ ለባዕድ ሀገራት ሲሰጥ በምን አገባኝ ስሜት ዝም ብለን ብንመለከት በ– ዚ–ያ ዘመን ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የውጭ ጠላትጋር የሀገሬን ሉአላዊነት አላስደፍርም በማለት በዱላ፣ በጦርና ጋሻ፣ ዘመናዊ ባልሆነ የጦር መሳሪያ ፣በባዶ እግራቸው በመዝመት ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ሳያስደፍሩያስረከቡን የአባቶቻችን አጥንት እሾህ ሆኖ ይወጋናል።
“የኢትዮጵያ ድንበሮች በኢትዮጵያውያን ደም የራሱ፣ በኢትዮጵያውያን አጥንት የተገነቡ ሲሆኑ ድንበሮቻችንን ለማስከበር ከሁልቆ መሣፍርት፣ ተራ ዜጐች አንስቶ እስከ አንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አንገታቸው ሰጥተዋል፡፡ በዶጋሊ፣ በጉራዓ፣ በጉንዲት፣ በመተማ፣ በአድዋ፣ በወልወል በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሶማሊያና በኤርትራ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም የሌላውን ግዛት በመቋመጥ ሳይሆን ድንበሬን አላስነካም በሚል ነበር፡፡ እንደዛሬው መኪና ወይንም ባቡር ባልኖረበት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ከመሃል አገር ተነስተው በእግር ለወራት በረሃውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ንዳዱን ተቋቁመው፣ ወባውን ደፍረው ከሙስታሂል እስከ ጋምቤላ፣ ከራስ ካሣር እስከ ሞያሌ ዘልቀው ድንበሩን ሰፍረው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አስረክበው ሄዱ፡፡ ይህ ተረካቢ ትውልድ የተረከበውን መሬት ሳይቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል ይሆን—-” ከያዕቆብ ኃይለማሪያም/20 July 2008/።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን አደራ ጠብቆ የሀገሩን ሉአላዊነት ሳይሸራረፍ በማስከበር ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ያለበት መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም ። ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ ህዝብ እውቅና ውጭ በሚስጥር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመጋፋት ዳር ድንበራችንን ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገውን የውል ስምምነት የፖለቲካ ልዩነት፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣አመለካከት ሳይለያየን የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ድርጅቶች፣ ሲቪክስ ማህበራትና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በጋራ ተንቀሳቅሰን አሁኑኑ ማስቆም ካልቻልን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማስደፈርም አልፎ እስከ ወዳኛው ትውልድ ድረስ ብጥብጥና ትርምስን የሚያወርስ ስውር ደባ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት በመጋፋት ለም መሬታችንን ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት አገር ወዳድ የሆንን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጋራ በመንቀሳቀስ በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየ የሃገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፈን አንሰጥም! በሚል መርህ ተግባብተን ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም ግዜ ሳንወስድ በያለንበት ፈጥነን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለባዕድ ሀገር አሳልፎ የመስጠት ታሪክ አልወረስንም!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10768/
No comments:
Post a Comment