ከአምስት ወር በፊት የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የአዲስ ዓመት የሥራ ዘመን መጀመር አስመልክቶ በጋራ ባአካሂዱት ጉባዔ አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ፕሬዚዳንታዊ የመክፈቻ ንግግር ማድረገቸው የሚታወቅ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ የንግግር ይዘት መንግሥት በ2006 ዓ.ም. ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ተግባሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንቱ ንግግር በሕግ መንግስቱ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት የተደረገ ንግግር ስለመሆኑ የሚያመላክት አንዳችም ነገር አላየሁበትም፤በመሆኑም የፕሬዚዳንቱ ንግግር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢነገር የተሻለ ይሆን ነበር ግን በሁለቱም ቢነገር ውጤቱ ዉሃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ላይ ሊካተቱ የሚገባቸው ነገር ግን ያልተካተቱ፣ እንዲሁም መካተት አልነበረባቸውም ያሏቸውን በመለየት አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄና አስታየት አቀርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ በመገኘት በአቶ ግርማ ነጥቦች ዙሪያ ምልሽ መስጠታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ይሁን እንጂ ምላሻቸው ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ስኬታማ አልነበረም ለዚህም ዋንኛው ምክንያት የመንግስት የአስተዳደር ብሉሹነት ነው ፡፡
የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ከተደረገ እና የመንግስት አቋም በጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ከተገለፀ ስድት ወር ሊሞላው የተወሰኑ ቀናት ይቀረዋል፡፡በሚቀሩት የተወሰነ ቀናት ውስጥ የግማሽ ዓመት ወይም የስድስት ወር የመንግስት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ምን ያኸል ውጤታማ ነበር የሚለውን በመንግስት እይታ ወደፊት የሚገለፅ ቢሆንም ወደ ጉሮሮ ጠብ ያላለ እድገት እና የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች የታፈነበት ወራት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ይህ በእንዲ እንዳለ ለዘህ ፁሁፍ መነሻ የሆነው ዋና አሳብ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከአምስት ወር በፊት በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ ንግግራቸውም ስለተቃውሞ ሠልፍ እና ስለህዝባዊ አብዮት የሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ስለ አብዮት ያላቸው ፍራቻ ከምን እንደመነጨ መገመት ቀላል ቢሆንም ስለ ህዝባዊ ስብሰባና የተቃውሞ ሠልፍ የያዙት ሃሳብ ግን የመንግስታቸው እየታ ጤናማ አለመሆኑ በሚገባ የሚሳይ ነው፡፡
በወቅቱ አቶ ኃይለማርያም እንዲህ ነው ያሉት ‹‹ ሌት ተቀን የጐዳና ላይ ነውጥ አምጥቼ ገዥውን ፓርቲ እቀይራለሁ ብሎ አቅዶ መንቀሳቀስ ወንጀል ነው፤ የጐዳና ላይ ነውጥ በዚች አገር ላይ እንሞክራለን የምትሉትን አቋሙ፡፡ ይህንን ለሕዝቡም ጭምር ነው የምናገርው በቂ መረጃ ስላለን ነው በተግባር ላይ ስላልዋለ ምንም ማድረግ ስለማንችል እንጠብቃለን፡፡ በተግባር ላይ የማዋል ሙከራ ካለ ትክክል ስላልሆነ እርምጃ እንወስዳለን ‹ኳሱ› በእናተ እጅ ነው ››፡፡ በማላት በሰማያዊና በአንድነት ፓርቲ እየተደረጉ ያሉ ሕዝባዊ ስብሰባና የተቃውሞ ሠልፎች መንግስታቸው በምን መልኩ እንቅስቃሴውን እየተከታተለ እንደሆነ እና ሊወሰድ የታሰበውን እርምጃ የሚያመላክት ነው፡፡
የአቶ ኃይለማርያም ማስጠንቀቂያ በቀጥታ የተላለፈው አንደኛ ለህዝብ ሲሆን ሌላው ደግሞ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ንግግር ከተደረገ ወራቶች የተቆጠሩ ቢሆንም መንግስት ከማስጠንቀቅ ባለፈ የተፈራውን ህዝባዊ አብዮት እና የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊገታ የሚያስችል አንድም የመንግስት መልካም አስተዳደር በአገራችን ላይ አልታየም፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም በእያንዳንዱ ሰው ንሮ ላይ የሚታይ ችግር መልሶ መድግም ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፡፡ በተጨማሪ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊያቀዘቅዝ ሳይሆን የበለጠ ሊያነሳሳ የሚያስችል የመንግስት የአስተዳደር ሽባነት ጎልቶ የታየበት ወራት ነው፡፡ በመሆኑም ለእዝብ እና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተላለፈው የመንግስት ማስጠንቀቂያ ተግባራዊነቱ እስከምን ድረስ ነው ? ::
በመንግስት የተፈራው እና ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት አንደኛው ነገር ሕዝባዊ አብዮት ነው፡፡ ሕዝባዊ አብዮት በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በህግ ተፈቅዶ ወይም ቅድመ እውቅና ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር አይደለም፡፡ ዜጎች በመንግስታቸው የሚታየው የአስተዳደር ብልሹነት መሸከም ሲከብዳቸው እና ሸክማቸውን ያበዛባቸውን ደካማ መንግስት ለመለወጥ ወይም ለማውረድ ሲፈለጉ ምርጫና መሰል ነገሮችን ሣይጠብቁ በአደባባይ በመውጣታ ስልጣን የህዝብ መሆኑን በማሳየት ብልሹ የመንግስት ባለስልጣናትን እና ስልጣንን አሽቀንጥሮ የሚጣልበት አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደዚህ አይነቱ አብዮት በተለያዩ አገራት ተግባራዊ ተደርጓል ፤ይሁን እንጂ እስከዛሬ ድረስ የተደረጉ አብዮቶች ሙሉ በሙል ውጤታማ ናቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም አብዛኞቹ አብዮቶች ስኬታማ ነበሩ፡፡ስኬታማ ያልሆኑ አብዮቶች ደግሞ ውጤታቸው የተበላሸ ያደረገው ዜጎች ያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ሣይሆን አብዮቱን ከፊት ሆኖው ሲመሩት የነበሩ መሪዎች አብዮቱን የመምራት እና የማስተባበር እንዲሁም የተገኘውን ውጤት የማስጠበቅ ድከመት ነው፡፡
በመሆኑም በጨቋኝ ሥርዓት መንግስት አስተዳደር ውስጥ ስለአብዮት ተግባራዊነት ይቅርና ስለ አብዮት ማሰብ እዳው ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እነኚ አምባገነን መሪዎች ስልጣናቸው ሕዝብን ለማገልገል ሣይሆን እራሳቸው የሚገለገሉበት ዓይነተኛ መንግድ ነው፤ በመሆኑም ይህን ስልጣናቸው ማጣት ለእነሱ ከባድ ኪሳራ ነው፡፡ ስለዚህ የፈጀውን ይፍጅ በማለት ለተነሱ እና ለሚነሱ አብዮቶች ለማኮላሸት ዘብ ነው የሚቆሙት፡፡ ይሁን እንጂ ህዝባዊ አብዮት በይትኛውም መለኪያ ስዕተትም አጥያትም አይደለም ይህዝብ ጥያቄ እንዴት ስዕተት ሊሆን ይችላል ? በመሆኑም ሕዝባዊ አብዮት በአገራችን ላለመከሰቱ ኳሱ በማን እጅ ነው ? ፡፡ እንዲሁም መንግስት እየታየበት ያለው የአስተዳደር ብሉሽነት ለማረም እና ህዝብን ለማገልገል ካልተቻለው አለመቻሉንም ተገንዝቦ ለሚችሉት እድሉን ካልሰጠ እና ይባስ ብሎ ወደለየለት የአምባገነን ስርአት የሚያመራ ከሆነ ሕዝባዊ አብዮት ምን ይጠብቃል !፡፡
ሌላው እና ዋንኛው ጉዳይ በአገራችን ኢትዮጵያ እታየ ያለው የመንግስት የአስተዳደር ብሉሽነት ለማጋለጥ እና አማራጭ መፍትሔ ለመስጠትና ለማስተዳደር በሰላማዊ መንገድ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነኚኽ ፓርቲዎች በተለይ ሰማያዊና አንድነት የሚያደርጓቸው ማናቸውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመንግስት በኩል የሚሰጠው ምላሽ ድብደባና እስራት ነው፡፡
እርግጥ ነው በሠላማዊ ትግል ሂደት ውስጥ ውጣ ውረዶ የበዛ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ የተካሄዱት ሠላማዊ ትግሎች ውጤት ያስመዘገብት መተኪያ የሌለውን የሰው ልጅ ሕይወትን እስከመንጠቅ በመድረሰ ነው፡፡ሠላማዊ ትግል ማለት ታጋዩ የሚታገልለትን ውጤት ሳይመለከት በትግሉ ሂደት የሚሰዋበት ፅኑ እምነት ነው እስከመባል ይደርሳል፡፡
ይህን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመረዳት ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በህዝቡ ውስጥ ጥሩ መነቃቃትን የፈጠረ ነው፡፡በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ በወጣት አመራሮቹ እና አባላቶቹ በመታገዝ የሚያደርጋቸው ሰላማዊ ተቃውሞ ድርጊቶች እጅግ በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች ባለተከበረበት፣መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ አንድን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት እያጋጨ፣ዜጎች የሚናገሩትን ቋንቋ መሠረት በማድረግ ብቻ ከመሬታቸው የሚፈናቀሉበት፣የኑሩ ውድነት እና እጅግ በጣም ቅጥ ያጣው ሙሰኝነት በተስፋፋበት፣የአገር ሀብት ፍታሃዊ ክፍፍል ባልታየበት እነዚህ እና መሰል ችግሮች ሙሉ በሙሉ ባይሆን እንኳን በከፊል መፍትሔ ባልተገኘባቸው ጉዳዮች ተከታታይ እና ጠንካራ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አለመደረጉ የፓርቲዎቹ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጥያቄን የሚያጭር ነው፡፡
እርግጥ ነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግስት እየደረሰባቸው ያለው ተፅኑ ቀላል የሚባል አይደለም በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ እየደረሰበት ያለው ጫና ስራዎችን የሚሰራበት ቢሮ እስከማስከልከል የደረሰ ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ የተገለፁት እና መስል የመንግስት አስተዳደር ችግሮች እልባት እንዲያገኙ ይህ ባይቻል እንኳን መጠነኛ ማሻሻያ እንዲታይ ምርጫን 2007 እየተጠበቀ ከሆነ ሠላማዊ ወይም አመፅ አልባ ትግል ህዝብን ከምን ሊታደግ ነው ? :: በመሆኑም የመንግስት የአስተዳደር ሃላፊነት ለማግኘት ምርጫን መጠበቅ ግድ ቢልም በመንግስት ላይ እየታየ ያለው የአስተዳደር ችግሮች እንዲታረም እና ማሻሻይ እንዲደረግባቸው ምርጫን መጠበቅ ተገቢ ሆኖ አይታይም፡፡ ስለዚህም በሠላማዊ መንግድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የተለያዩ አመፅ አልባ ትግሎችን በመንደፍ እና በማስተባበር ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል እንቅስቃሴዎቻቸውን በይበልጥ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ እንቅስቃሴ ለገዢው ስርዓት የአስተዳደር ብሉሹነት ዕድል እና ትምህርት ካልሰጠው አሁንስ ኳሱ በማን እጅ ነው ? ::
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10849/
No comments:
Post a Comment