Posted by The Ethiopia Observatory
ኢትዮጵያ በሕወሃት ዘመነ አመራር የታወቀችባቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ብዙ “እንዴ!”የሚያሰኙ ጥሩ ሀሳቦችም ፈልቀዋል – አፈጻጸማቸው እትየለሌ ቢሆንም። ከነዚህም መካከል መሠረተ ልማት፡ በጤናና በትምህርት መስኮች መሻሻሎች መታየታቸው ወዘተ መልካም ይነገርላቸዋል – የቢል ጌትስን የራስ ተጠቃሚነትና ኢምፓየር ግንባታ ወደጎን ትተን! በዕጦት ደረጃም በሀገራችን የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር፣ የፍትህ አለመኖርና ለአብዛኛው ሕዝባችን የምግብ ዕጦት ዋና ዋና ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።
ለምሳሌም ያህል፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 30 ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግንና መንግስትን መቃወምን ግልጽ ቢያደርግም፡ እሁድ ዕለት የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ለመሰጠት ለመቃወም: ለሚመለተው አሳውቀው ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት ተፍ ተፍ ሲሉ የአዘጋጁ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ጎንደር ውስጥ ተይዘው ታስረዋል። በተመሳሳይ መንገድ ትግራይ ውስጥም የአረና አመራሮች ሕዝቡን ቀሰቀሳችሁ በሚል ውንጀላ አዲግራት ውስጥ አመራሩና አባሎቹ ክፉኛ ተደብድበዋል – ጉዳት የደረሰባቸውም ሕክምና ለመሻት ተገደዋል። ይህንኑ አስመልክቶ፡ አንዱ ተደብዳቢ መምህር አብርሃ ደስታ የሚከተለውን ጽፏል፡
- “ህወሓቶች በተግባራቸው ሊያዝኑ ይገባል። ህዝብን ፖለቲካ እንዲያውቅና ራሱ ከጭቆና እንዲከላከል ለማገዝ በምንሞክርበት ግዜ መንግስት ወደ ተራ የሽፍትነት ተግባር መሰማራቱ የሚያስደምም ነው … እኛ ለህዝብ ነፃነት ነው የምንታገለው። ትግላችን ሰለማዊ ነው። ወታደርና ፖሊስም የለንም። እኛ ያለን ህይወት ነው። ያለችንን ህይወት ለህዝብ ደህንነት ስንል መስዋእት አድርገናል። በህዝብ ፊት ተደብድበናል። በፖሊስና አስተዳዳሪዎች ፊት ተደብድበናል። እኛ መክፈል ያለብን ህይወትን ነው።”
ይህ በግልጽ የሚታየው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የስብዓዊ መብቶች አንጸባራቂ ሥዕል ነው። ይህ ሁኔታ በየቀኑ በተለያየ መልኩ ሀግሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለ የመንግሥት ሕገ ወጥነት ነው!
በኤኮኖሚው መስክ ያለው ችግር ግዙፍ ነው። ድህነት ከመቀረፍ ይልቅ፡ ሥር እየስደደ መሆኑን ብዙዎች ያማርራሉ። ለጥቂቶች ግን ሀገሪቱ ምድራዊ ገነት ሆናለች። ሕዝቡ እየተደበደበም፡ በየቀኑ አልዋጥ ባይ ፕሮፓጋንዳ በግድ እየተጋተ ነው!
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ለብዙዎቹ የአዲስ አበባ መሽቀርቀር እንደአጠቃላይ የሃገሪቱ የልማትና ዕድገት መለኪያ ተደርጎ እንዲወሰድ የተቀነባበረ ጥረት የሚድረገው። የምርጫ ዘመን በመቃረቡ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቅርቡ ስንዴ ለውጭ ገብያ ሻጭ ልትሆን ነው በማለት ጥር 18፣ 2014 አርሲ ሆነው ማስማታቸው ልብ ሊባል ይገባል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በልማት ገና ሀ ሁ … ላይ ናት – በምግብ 40 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን በቀን ሶስቴ ሳይሆን፡ አንዴም መመገብ ያልቻለች አገር ናት! ይህ በመሆኑ አይደል እንዴ የምዕራቡ ዓለም፡ በቋሚነት ከ10 በመቶ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ክዓመት ዓመት በዓለም አቀፍ እህል ዕርዳታ ሕይወት በመስጠት ላይ ያለው?
ከሁሉም ጎልቶ የሚነገርለትና የሕወሃት ሰዎችም ቶሎ የሚስፈነጠሩበት የአገሪቱ ከትላልቅ ጦርነቶች መላቀቋ ነው። ስለዚህም የሕወሃት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው በመመጻደቅ ሲናገሩ መስማቱ የተለመደ ሆኖአል። በዚህም መነሻነት፡ እንዲህ ይላሉ: ባለፉት 20 ዓመታት፡ ሕወሃት ለረዥም ዘመናት አገሪቱን ያደሙትን ጦርነቶች አቁሞ ልማት ላይ እንድታተኩር አደረገ የሚባለው በብዛት ይሰማል። የሕወሃት ስዎችም ይህ በተደጋጋሚ እንዲነገርላቸው ብዙ ጥረቶች አድርገዋል፡ እያደረጉም ነው። እራሳቸውም በተደጋጋሚ እራሳቸውን በዚህ ሲያሞካሹ ይሰማል፤ ለውጭ የፕሮፓጋንዳ ድርጅቶችም ይህንን እንዲያስተጋቡላቸው፡ ከፍተኛ ክፍያዎችን በየጊዜው ፈጽመዋል።
እስከዛሬ አጥጋቢ ግንዛቤ ያላገኘው ግን፡ ድሮም ሆነ ዛሬ የጦርነቶች አጋጋይ ሕወሃት መሆኑ ነው። የኤርትራንና የትግራይን መገንጠል ጉዞ በተግባር ሲተረጉም ኖረ። ቀኑ ደርሶ ጅብሃ ሲገነጠል፡ ሕወሃት ባዶ የሥልጣን ወንበር ስለታየው፡ ኢትዮጵያዊነትን መረጠ። በትግል አጋሩ ጅብሃ ዘንድ ይህ እንደክህደት እንዳይታበት – በሰላም ሂዱ፡ ኢትዮጵያ ከእናነተ ሰላም እንጂ ሌላው ቀርቶ የባህር በር እንኳ አያስፈልጋትም አለ። ይህንን አስመልክቶ፡ በየካቲት ወር 1994 ስብሃት ነጋ ለዓለምሰገድ አባይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የሕወሃት ቀደምት ፓሊሲ መገንጠል ሆኖ እስከ 1985 መቆየቱን ያረጋግጣሉ። ከቃለ መጠይቁ ውስጥ በጣም አስገራሚው ነገር ግን፡ ብዙ የሕወሃት ተዋጊዎች ኢትዮጵያዊነትን ገና ድሮ አሽቀንጥረው የጣሉ በመሆናቸው፡ ዛሬም ቢሆን በተለይ ከአማራ ጋር ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኝትን በሙል ልብ አለመቀበላቸውን ነው ያመላከቱት [See Identity Jilted: Re-imagined Identity (1998)]።
ያለፈው አልበቃ ብሎ፡ ዛሬም ሕወሃት ሀገሪቱ ውስጥ ሽብርና ፍርሃት በማንገስ የውስጥ ግጭቶችን በመተንኮስ: የተለያዩ ብሄረስቦችን አባሎች በማፈናቀልና ችግሮችን በማባባስ ተጠቃሚ ለመሆን ሲምክር ይታያል – ድ/ር ቴድሮስ ፍጹም “እኔ ያለሁበት ፓርቲ ውስጥ ይህ አይደረግም!” ብለው ዝናቸውን አጋልጠው ቢገዘቱም። ነገሩ ግን፡ ዛሬም በምሥራቅ በተለያያዩ የኦሮም ክፍሎችና ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች መካከል፡ በደቡብም እንዲሁ በተለያዩ ጎሣዎች መካከል፡ አማራንና ኦርሞችን በማጋጭት፡ ጥላቻና መቃቃርን በዜጎች መካከል ለመፍጠር ብዙ ሲሞክር ቆይቷል። አንዳንድ ቦታዎችም፡ ለምሳሌ ቦረና፡ ተሳክቶለት ስሞኑን የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል፤ ሕይወትም ተቀጥፏል። ቤት ንብረቶችም ተደምስሰዋል። ሌላው ቀርቶ፡ የሕክምና ባለሙያ የነበሩት የአገር አስተዳደር ሚኒስትሩ – የዛሬው የሃይማኖትች ጉዳይና የጸረሽብር ኤክስፐርቱ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም – ኬንያ በሥጋቷ ምክንያት (2012ን በማስታወስ) ልተቀስቅሳቸው ብትሞክርም፡ ነገሩ አውቆ የተኛ ቢነቀንቁት አይሰማ ሆኖ እሳችውም እንደክረምት ድብ ክፉኛ አሸልበዋል።
ለማንኛውም፡ በዓለም ላይ እንደሕወሃት የተሳካለት የለም – ዕድሉን ሃገራችንን ለማሻሻል በሚገባ አልተጠቀመበትም እንጂ! ስለሆነም ክሥራ ይልቅ ፕሮፓጋንዳ፡ ዕውነትን ተናግሮ ችግሮችን በጋራ ከመፍታት ይልቅ፡ ሁሉንም ስው ማሞኘት እንችላለን በሚል ትዕቢት ብዙ የሚያሳፍሩ ተግባሮች ሲያከናወን ይታያል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ በበጎነታችው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደጉን የሚመኙ የውጭዎቹ የፖለቲካ፡ የዲፕሎማሲና ኅብረተስባዊ መሻሻሎችን አራማጆች ይህንን የሕውሃትን የሰላም ማስፈን የዋህ መስል ቅጽል በአመኔታ የሚጋሩት በሁለት ተክፈለው ይታያሉ፡ –
(ሀ) በእውነትም ጦርነትና የንጹሃን ዕልቂት መቆሙን፡ ኢትዮጵያ ክድህነት ተላቅቃ ማየት የሚሹ ወገኖች፤
(ለ) ጊዘው የበለጸጉት ሃገሮች ወደታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ዘልቀው በመስፋፋትና በኢኮኖሚ ትብብር ስም የራሳቸውን ኤኮኖሚያዊ፡ የበላይነት ማቆየት የሚሹበት፡ ፖለቲካዊና ስትራተጂካዊ ጥቅሞቻቸውን የሚያበራክቱበት በመሆኑ፡ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተዳብረው፡ የሕወሃትን ገድል መተረኩ፡ ለሚሹት ዓላማ አንድ ጥቅም ትስስሮሽ መፍጠር የሚያስችል መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት ወገኖችም እዚሀ ውስጥ ተስልፈዋል።
ከላይ የተመለከቱት ከተለያየ አግጣጫ ተነስተው ሁለቱም አንድ የሚገናኙበት መጋጠሚያ፡ ስለኢትዮጵያ በጎ ነገር እንዲስተጋባ ማድረጋቸው ነው። በተለይም በሁለተኝው ክፍል የሚገኙት፡ በተቻለ መጠን ስለኢትዮጵያ በጎውን በማጋነን፡ የሕወሃትን የስብዓዊ መብቶች ጽልመት፡ ጎስኝነት፡ ሙሰኝነት የሚሸፋፍን አመለካከት በምዕራባውያንም ሆነ ምሥራቃዊ ሚዲያዎች ላይ በጊዜው ያስደስኮሩላቸዋል።
በተጨማሪም፡ እነዚህ ሀገሮች ለኢትዮጵያ ግዙፍ ዕርዳታ መፍሰሱን ይደግፋሉ። ነገር ግን ይህ ዕርዳታ በብዙ መስኮች – በተለይም በግብርናው – መስክ የሀገሪቱን ችግሮች፡ በምግብ ምርት እራስን ከማስቻል ይዘት ስሌለው፡ ትኩረታችውም ሆነ ጥረታቸው – በዘለቄታ ሀገሪቱን ከምግብ ዕርዳታ ተመጽዋች ነጻ ለማድረግ አላስቻለም። በመሆኑም፡ እየተደረገ ያለው፡ ትላንት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያ አንድ ሶስተኛ መንግሥታዊ በጀቷን በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ተመጽዋችነት ላይ የተመሰረተ ሆኖ የውስጥና የውጭ ፖሊሲዋን በማክራየት እንድትቀጥል አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮባታል።
በአሁኑ ወቅት፡ በተለያዩ ምክንያቶች (የስብዓዊ መብቶች አለመከበር ችግር፡ የየራሳቸው የሀገሮቹ የኢኮኖሚ ችግሮች) መንስኤነት፡ ከለጋሽ ሀገሮች በቀጥታ የሚገኝው ዕርዳታ በክፍተኛ ድረጃ ቀንሷል (ክአሜሪካና እንግሊዝ በስተቀር)። በዚህም ምክንያት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚስጠውን ብዙውን የዕርዳታና ብድር ጫና ድርሻ ተሸካሚ ሆኖአል።
ለምሳሌ፡ ሌላው ቀርቶ ስብዓዊ ዕርዳታን እንኳ በተመለከተ፡ 12 የአውሮፓ ኅብረት ሀገሮች (እንግሊዝን አይጭምርም) በ2012 ለኢትዮጵያ በባይላተራል መንገድ ለዕርዳታ ያዋጡት €24 ሚልዮን ሲሆን፡ በ2013 ይህ መዋጮ ወደ €12.4 ሚልዮን ወርዷል። ከነዚህም መካከል ትልቁን ቅናሽ ያደረገችው ጀርመን ናት – ከ€8.2 ሚልዮን ወ €4.2 ሚልዮን ዝቅ በማድረግ። በመሆኑም፡ከዚህም ከዚያም አስባስቦ የበጀት ምንጮች በማስባስብና ተጨማሪ ምክንያቶች በመፍጠር (ነፍስ ወክፈ መልሶ ማቋቋም) በ2013 እንዳደረገው፡ የአወሮፓ ኮሚሽን በ 2011-2013 12 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለመርዳት እንዲቻል €130 ሚልዮን ለግሷል።
አሁን ለሁሉም ለጋሾች ከባድ የሆነው “የልማት” ዕርዳታውም እንዲሁ በበዙ ጥያቄዎች ላይ መውደቁ መሆኑ ይሰማል።
በዓለም ዙሪይ ያለፉው ሩብ ምዕተ ዓመት የልማት ጊዜ በመሆኑ፡ ብዙ ታዳጊ አገሮች ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆነዋል። ኢትዮጵያ ይህ ዕድል ቢገጥማትም፡ መሣሪያ ያነገቡት የሕወሃት ሰዎችና አጫፍሪዎቻቸው ግንባር ቀድም ተጠቃሚዎች የሆኑበት ሥርዓት በመዘርጋቱ፡ የትላንቱ ጦረኞችና የዛሬዎቹ የስላም ደጋፊ-መስል የአንድ ብኄረስብ ሰዎች፡ ሆን ብለው ዕኩልነትን የሚጻረር የፖለቲካ፡ የኤኮኖሚ፡ የደህንነትና ማኅበራዊ ፓሊስዎችን በኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ግን ዘላቂ መሠረት ስሌለው፡ ዛሬ የኤኮኖሚው የጥንድ ዕድገት ውደሳው ጋብ ብሎ፡ ሀገራችን የመንግሥት ብልግናና የሃስት ፕሮፓጋንዳ ከሚመገቡት መካክል ወድቃለች። በዚሁም ምክንያት (ሽፋኑ የውሃ ዕጥርረት፡ ድርቀት፡ የሃይማኖትና የብኄረቦች አለመቻቻልና ግጭቶች ላይ ቢመካኝም)፡ ተደጋጋሚ ዓለም አቅፍ ጥናቶችኢትዮጵያ ከሚወድቁት የአፍሪቃአገሮች (Failed States) መካከል ተደምራ፡ የወደፊት ጽዋዋ አስፈሪ እንደሚሆን ቀንደኛ ደጋፊዎቿ ድምዳሜ ላይ መሆናቸውን በግልጽ የምንሰማበት ዘመን ላይ ደርስናል።
ድሮስ ቢሆን፡ የሕዝብ ዓመኔታ ያጣ መንግሥት፡ መሣሪያውን ደግኖ በኅይል ለመግዛት ከመሞከር ውጭ ምን አማራጭ አለው? ጊዜው የጥላቻ፡ የክፋትና የቂም በቀል በመሆኑ፡ በአንድ በኩል፡ የሕወሃት ስዎች ዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፡ በሌላ በኩል ደግሞ፡ የኢትዮጵያውያንን ስብዓዊ መብቶች በመግፈፍና መርገጣቸውን በማባባስ፡ ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ጎዳን እየገፉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ዕድገት ይኖራል?
እንዲያውም፡ የራሱን የአገዛዝ ዘመን ለማራዘም ሲል፡ የኢትዪጵያ ሕዝብ ፍላጎትና አመለካከት ሳይጠየቅ ኤርትራን በፊርማው እንድትገነጥል ያደረገ፡ አገሪቱን የባሀር በር ለማሳጣት የደፈረ የመንግሥታዊ ባህልና ኃላፊነትና ግንዛቤ የሌለው ሕወሃት፡ ለሱዳን የኢትዮጵያን መሬት ቆርጦ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑ ሕዝቡን በቃ! የሚል ድምዳሜ ላይ ማድረሱ አያጠራጥርም!
በዓለም ታሪክ ውስጥም ሕወሃት “ታዋቂ” የሚሆነው፡ ራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት፡ የሀገርን ልኡላዊነትና መሬት ቆርሶ ለጎረቤት ሀገርና ለከፍተኛ ብድር ስጭና ገንዘብ ለዋጭ አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ ነው።
ዛሬም ሆነ ነገ፡ ለሀገራችን ዘላቂው መፍትሄ ግን መንግሥት የሕዝብን ፍላጎት ለማክበር መቻሉና ለዚህም ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት መዘርጋቱ ነው። ይህንን ለማድረግ፡ አሁንም ትንሽ የተስፋ መስኮት አለ – የሕውውሃት ስዎች ኃላፊነት የሚስማቸው ቢሁን። ይህ ለሕወሃትና ግብረአበሮቹ ተቀባይ ሳይሆን ቢቀር፡ ቀሪው ምርጫ ሕዝቡ እየተረገጠ መቀጠል፡ ወይንም እነርሱ ከመድረኩ መወገድ ነው።
እስካሁን በዚህ ድህረ ገጽ ይህንን አሳብ አላራመድንም ነበር። የሁኔታው አስከፊነት ግን አሁን የወቅቱ አስፈላጊ እርምጃ አድርጎታል!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10852/
No comments:
Post a Comment