የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የተኳቸው የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ በወጡ በዘጠነኛ ወራቸው ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በመገናኘት፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባለፈው ዓርብ ማለዳ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
“ጥያቄ ለማቅረብና ማብራሪያ በመሻት በመምጣታችሁ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ከዚሁ ቀጥሎ የምትፈልጉትን ጥያቄ እንደትጠይቁ ዕድል እሰጣለሁ፤” በሚል የመግቢያ ንግግር ጋዜጣዊ መግለጫውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ የፈጀ ቆይታ ከጋዜጠኞች ጋር አድርገዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተገኙ ከ20 በላይ ጋዜጠኞች ያገኙትን ዕድል በመጠቀም በአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ በተለይም በቅርብ በተከሰተው የዓባይ ግድብ ውዝግብ፣ በሙስናና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን በማቅረብ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዝርዝር ምላሽ ሰምተዋል፡፡ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ኢኮኖሚያዊና ተያያዥ ጉዳዮች
ከ2005 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የአክሲዮን የንግድ ድርጅቶች ላይ የጣለው የዲቪደንድ ታክስ (የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ላይ የሚጣል ታክስ) ጉዳይ በመጀመሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡
የአገሪቱ የታክስ ሕግ የተጠቀሰውን የታክስ ዓይነት አስመልክቶ በተከፋፈለ የአክሲዮን ድርሻ ትርፍ ላይ የአሥር በመቶ ታክስ የሚጥል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአክሲዮን የተቋቋሙ ድርጅቶች በአጠቃላይ የአሥር በመቶ ታክሱን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል አደረጉም አላደረጉም በአጭር ጊዜ ሊከፍሉ ይገባል በሚል ባወጣው መመርያ፣ የንግዱ ኅብረተሰብን ሲያጉላላና ሲያከራክር ቆይቷል፡፡ ታክስ ባለሥልጣኑ ባወጣው መመርያ መሠረት ድርጅቶቹ የተጠቀሰውን ታክስ ወደኋላ ለአምስት ዓመታት በማስላት እንዲከፍሉ በመወሰኑ የተነሳ፣ ድርጅቶቹ በጉዳዩ ላይ ያነሱት የሕግ ጥያቄ ሳይመለስ ቅጣትን ፍራቻ ክፍያ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ የዚህን ታክስ አግባብነት የተጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም ተከታዩን ብለዋል፡፡
“ከትርፍ ድርሻ የሚከፈል ታክስ የሚጠየቀው የትርፍ ድርሻው ከተከፈለ ብቻ ነው፡፡ የትርፍ ድርሻው ሳይከፋፈል ለኢንቨስትመንት ከዋለ ታክስ አይከፈልበትም፡፡ ይህ የቆየ የመንግሥት አቋም ነው፤” ብለዋል፡፡
በታክስ ባለሥልጣኑና በንግዱ ኅብረተሰብ መካከል የተፈጠረው ክርክር የትርፍ ድርሻው ተመልሶ ለኢንቨስትመንት ውሏል? በሚል ጥያቄ ላይ መሆኑን አቶ ኃይለ ማርያም ከገለጹ በኋላ፣ መጣራት ያለበት የትርፍ ድርሻው ለባለሀብቶች ተከፋፍሏል ወይስ ለኢንቨስትመንት ውሏል የሚለው እንደሆነና ይህ እየተሠራ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ስህተቱን የሠራው መንግሥት መሆኑ ከተረጋገጠ በንግዱ ኅብረተሰብ ላይ ለደረሰው መጉላላትና ጥቅም ማጣት መንግሥት ይቅርታ ይጠይቃል? የሚል ተያያዥ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ “ስህተት መኖሩን ካረጋገጥን ይቅርታ የማንጠይቅበት ምክንያት የለም፤” ብለዋል፡፡
ጉዳዩ አከራካሪ እንደሆነ በመጠቆምም አንዳንዱ ትርፉን ተቀብሎ መክፈል የማይፈልግ መኖሩን፣ ነገር ግን ለኢንቨስትመንት የዋለም እንደሚገኝ እንደሚገነዘቡና ይህንን ማጣራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዕድገት ዙሪያ ከዚህ ቀደም ሲጠራጠሩ የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕድገቱን ወደ መቀበል መምጣታቸውን፣ ነገር ግን እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያሉ ተቋማት አሁንም የሚያወጧቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ለአብነትም ዘንድሮ ይመዘገባል ብለው የገመቱት የኢትዮጵያ ዕድገትና የመንግሥት ግምት አሁንም የተለያዩ መሆናቸውን በተመለከተ፣ መንግሥትም ሌሎች ተቋማትም የሚግባቡበት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ኢንቨስትመንት መኖሩንና በዚህ መሀል የገንዘብ ፖሊሲውን በማጥበቅ የዋጋ ንረትን መዋጋት የሚለው የመንግሥት አቋም ግጭት የለበትም ወይ? እንዲሁም ባለፈው ዓመት የታየው የግብርና ምርት ዝቅተኝነት፣ በተመሳሳይም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ዝቅተኛ አፈጻጸምን ከግምት በማስገባት ባለ ሁለት አኀዝ ዕድገት ዘንድሮ መጠበቅ አይከብድም ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
በሰጡት ምላሽም፣ “ላለፉት 11 ዓመታት በአይኤምኤፍና በኢትዮጵያ መንግሥት የዕድገት ትንበያ ዙሪያ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ወደ ትክክለኛው መረጃ ስንመጣ ግን የእኛን መረጃ ሲያስቀምጡ ነው የኖሩት፡፡ የለመድነው ነገር ዛሬ ቢደገም ምን አዲስ ነገር አለው፤” ብለዋል፡፡ በማከልም፣ “ግምት ግምት ነው ግምቱ ወደ እውነት መጠጋት ግን አለበት፤” በማለት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግምት ሁሌም ወደ እውነት የተጠጋ እንደነበርና አሁንም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 8.5 በመቶ ዕድገት እንዲመዘገብ ምክንያት የሆነው ግብርናው ያሳየው የ4.9 በመቶ ዝቅተኛ አፈጻጸም መሆኑን፣ በዚሁ ዓመት ተስተውሎ የነበረው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም የመነጨው በጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ወደ 13 በመቶ በመውረዱ እንጂ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በ18.6 በመቶ አድጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ያሳየው ዝቅተኛ አፈጻጸም አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ወደኋላ እንደሳበው፣ ነገር ግን መንግሥት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ላይ በወሰደው ዕርምጃ ውጤት በመታየቱ፣ ከዚህ ባለፈም የግብርና ዘርፍ የሰብል ምርት ዕድገት ብቻ ስድስት በመቶ ማደጉንና ከስታስቲክስ ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ከሌሎቹ የግብርና የዘርፍ ዓይነቶች ዕድገት ጋር ሲደመር፣ ቢያንስ የግብርና ዕድገቱ ሰባት በመቶ ስለሚሆን ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያለ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የሚለውን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት፣ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ሁለት ዓይነት አስተሳሰቦች መኖራቸውን በማስቀደም ነበር፡፡
“አንደኛው ዕድገት እያስመዘገቡ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ዕድገትን ገቶ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ይገባል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው አስተሳሰብ በምሥራቅ እስያ አገሮች ልምድ አልሠራም፡፡ ዕድገት እየመጣም የዋጋ ንረትን ተቆጣጥሮ መሄድ ይቻላል የሚለው በተግባር የተረጋገጠ ነው፡፡ በእኛም ሁኔታ ዕድገት እያስቀጠልን የዋጋ ንረትን ማውረድ ችለናል፤” ብለዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት በሰጡት ማብራሪያ ዋናው ነገር የዋጋ ንረቱ ምንጭ እንደየአገሩ የሚለያይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ባደጉ አገሮች ያለው የዋጋ ንረት ምንጭና ግፊት ባላደጉ አገሮች ካለው ጋር ፈጽሞ እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡
“የእኛ መነሻ ምንድን ነው? የእኛ የምግብ ዋጋ ንረት ነው መነሻው፡፡ ዋናውና ትልቁ የግብርና ምርት ላይ ትንሽ ፈቅ ሲባል ዋጋው ይወርዳል፡፡ አርሶ አደሩ ዋጋ ወደቀ ብሎ መንጫጫት ይጀምራል፡፡ ስለዚህ መነሻው እንጂ አጠቃላይ ቲዎሪው አይደለም የሚወስነው፤” ብለዋል፡፡
ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ ሲገባ የሚያመጣው የዋጋ ግሽበትና በአቅርቦት ምክንያት የሚመጣውን ግሽበት መንግሥት ከፋፍሎ መመልከቱን አቶ ኃይለ ማርያም የገለጹ ሲሆን፣ “ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ በሚገባበት ወቅት ግሽበት አይፈጥርም ሳይሆን፣ አቅርቦት በሚጎልበት ወቅት የዋጋ ንረቱ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር አይተናል፡፡ ስለዚህ አቅርቦቱን በማሻሻል የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር ይቻላል፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
በማጠናከርም ግሽበትን ለመፍታት አቅርቦቱን ማሻሻል ማለት በሌላ በኩል ግብርናን ማሳደግ መሆኑንና ይህም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደ መግደል እንሚቆጠር በመግለጽ ይህ ሊሆን የቻለው ከኢኮኖሚያዊ አወቃቀሩ የተነሳ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የግብፅ ጉዳይ
በኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት የኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ስለተከሰተው አለመግባባትና ችግሩን ለመቅረፍ ያለው ዕድል፣ የሁለቱ አገሮች አለመግባባትን ተከትሎ በግብፅ በኩል ስለታየው የጦርነት ጉሰማ አካሄድና የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተፋሰሱን በጋራ የመጠቀም ፅኑ እምነትን አጉልተው አንፀባርቀዋል፡፡
“ፍላጎታችን በጋራ ብልፅግና ላይ የተመሠረተ ትብብር ይኑር የሚል ነው፡፡ ይህ አቋማችን ይቀጥላል፡፡ ይህንን አቋም የዓለም ኅብረተሰብ በአጠቃላይ እየተቀብለው ነው፤” ብለዋል፡፡
ሰጥቶ በመቀበል መደራደር ላይ የተመሠረተ አቋም በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን በመግለጽ፣ የባለሙያዎቹ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት ግድቡ የተፋሰሱን አገሮች ሊጠቅም እንደሚችል ያለማወላዳት እንዳስቀመጠ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ ሪፖርት ሌሎች የሰጣቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መኖራቸውን ከዚህም ውስጥ የግድቡ ዲዛይንን እንደሚመለከት ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ የግድቡ ኮንትራት የኢንጂነሪንግን ግዥና ግንባታን ያጠቃለለ መሆኑን፣ ይህም ማለት የመጀመሪያው ዲዛይን ብቻ ተሠርቶ ቀጣይ ዙር ዲዛይኖች በዚህ ላይ መሠረት ተደርገው እንደሚሠሩ፣ በመሆኑም ቀጣይ ዲዛይኖች ላይ መካተትና ሊተኮርባቸው የሚገባቸውን ሐሳቦች ባለሙያዎች በሪፖርታቸው እንዳቀረቡ ገልጸዋል፡፡
“የእኛ መንግሥት ከቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ እጅግ አብዛኞቹን በአሁኑ የሥራ ወቅት በዲዛይኑ እያካተተ የሄደበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ አስተያየቶቹን ለማካተት ቆም ብለን እንነጋገራለን የሚል ስምምነት ከግብፅ ጋር ተደርሷል፤” ብለዋል፡፡
ሌላው የባለሙያዎቹ ቡድን ግድቡ ሊፈጥር የሚችለው የአካባቢ ተፅዕኖ መጠናት ያለበት መሆኑን እንደጠቆመ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ “ግብፅና ሱዳን በዚህ ረገድ መረጃ ሊሰጡ ፈቃደኛ ስላልነበሩ ባለን መረጃ ላይ ብቻ ተመሥርተን ነው የአካባቢ ተፅዕኖ ጥናቱን ያካሄድነው፤” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይም ተነጋግሮ መሥራት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግብፅ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗ ጥሩ ነገር እንደሆነ ነገር ግን ውጤቱን መተንበይ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ በድርድሩ ወቅትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን፣ “የግድቡ ሥራ የማይቆም መሆኑንና መጠኑ የማይቀንስ መሆኑም መታወቅ አለበት፤” ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡
የግብፅ ፕሬዚዳንት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በግድቡ ዙሪያ በመወያየት በግልጽ በሚዲያ የታየው ኢትዮጵያን የማተራመስ አቋም ሆን ተብሎ ይሆን በስህተት ባይታወቅም፣ ከ120 ዓመታት በፊት ጀምሮ በግብፅ ይራመድ የነበረ አስተሳሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
“በዚህ አስተሳሰብ መመራት ትክክል እንዳልሆነ ለግብፅ መሪ በተደጋጋሚ ገልጫለሁ፡፡ መንግሥታቸው ይህንን አቋም ይዟል የሚል እስካሁን አልሰማንም፤ ይህንን አቋም በያዘ ጊዜ ግን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው፤” ብለዋል፡፡
የሙስና ጉዳይ
በቅርቡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን ተንተርሶ፣ በኢሕአዴግ የፖለቲካ ልዩነት የተነሳ የተወሰደ ዕርምጃ ስለመሆኑና በቀጣይ የመንግሥት ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ላይ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ፣ ዕርምጃው በኢሕአዴግ ጉባዔ እንዲሁም በማዕከላዊና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ ጥልቅ ውይይት ተካሄዶበት የተያዘ አቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ኪራይ ሰብሳብነትን አንዳንዶች እስከሚያሾፉበት ድረስ እየተነገረ ያለ ቃል ነው፡፡ ይህንን ዕውን በማድረግ የድርጅታችን አንድነት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ጠላት መታገል አለብን ብለን ነው ያስቀመጥነው፤” ሲሉ አክለዋል፡፡
የሙስና ሥራ የሰዶ ማሳደድ ሥራ ባለመሆኑ በተጠና መንገድ ሥራ መጀመሩን፣ በዋነኛ ደረጃ ከተለዩት ውስጥ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ በተወሰደ ዕርምጃ ግለሰቦች ተጠያቂ እንደተደረጉ ገልጸዋል፡፡
ሙሰኞችን መቅጣት ብቻ ሙስናን መዋጋት አይደለም፡፡ ሥርዓቱ ለሙስና ምቹ እንዳይሆን ማድረግ ይገባል ከሚል ፅኑ እምነት በመነሳት የመሬት ሥርዓቱን የማስተካከሉ ሥራ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
“በሁለተኛ ደረጃ ታክስ ላይ መጥተናል፡፡ ቢሮክራሲውንም ከፍተኛ አመራሩንና ባለሀብቶችን ተጠያቂ አድርገናል፤” ብለዋል፡፡ “የፖለቲካ ልዩነት ስላለ ነው በሚል ለቀረበው ጥያቄ ይህንን ሊል የሚችል ካለ የፖለቲካ ልዩነት ሳይሆን የመቀራረብ ልዩነት ነው፡፡ ከሙሰኞች ጋር የተቀራረበ ካለ ደስ ሊለው ይችላል ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ ….. ከየቤታቸው በሻንጣ የተከማቸ ገንዘብ እየወጣ እየታየ ምን የፖለቲካ ልዩነት ሊባል ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ቀጣዩ መንግሥት ያተኮረበት የሙስና ምንጭ የመንግሥት ግዥ ዘርፍ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ “ይህ አገር ከፍተኛ የመሠረተ ልማት እያካሄደ ነው፡፡ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ከፍተኛ የኮንትራት ስምምነትና ድርድሮች የሚደረግበት ነው፡፡ በመሆኑም የሙስና ምንጭ ነው፡፡ ስለዚህ በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ዕርምጃ እንወስዳለን፤” ሲሉ ቀጣይ ዘመቻቸውን ጠቁመዋል፡፡