FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, June 27, 2013

ኢሳት (በደረጀ ሀብተወልድ)

ደረጀ ሀብተወልድ
ከሁለት ሣምንት በፊት ሲቪሊቲ ፓልቶክ ባዘጋጀው የጋዜጠኞችና የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ውይይት ላይ ኢሣትን በመወከል ተሳትፌ ነበር። በክፍሉ ታዳሚ ከነበሩት ከ 500 በላይ ተሳታፊዎች መካከል በጣም የሚበዙት የኢሳት ደጋፊዎች መሆናቸውን ሳይ ደስታ ሳይሰማኝ አልቀረም። ከደስታው ባሻገር የተሰማኝ ሌላ ስሜት ግን፦” ሰው እንደዚህ ሲደግፋችሁ፤ የበለጠ በርትቻችሁና ጠንክራችሁ  መሥራት አለባችሁ” የሚል አደራዊ ሸክም ነው።
ደጋፊዎቻችን የመብዛታቸውን ያህል ታዲያ ከጥቂት ሰዎችም ቢሆን  ቅሬታ አዘል ጥያቄዎች መሰንዘራቸው አልቀረም።ኢሳትን በተመለከተ የተሰነዘሩት እነዚህ ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች ሲጨመቁ፦” ኢሳት የግንቦት 7 ነው፣ ግንቦት 7 እና መሪዎቹ  ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ያገኛሉ፣ ጭራሽ የሚዲያ ሽፋን የማትሰጧቸው ፓርቲዎች አሉ” የሚሉ ናቸው።
ለሦስቱም ጥያቄዎች ለመስጠት የሞከርኩትን መልስ ነው እዚህ  በመልኩ ለማስቀመጥ የሞከርኩት፦
1-      ኢሳት የግንቦት 7 ነው የሚለውን በተመለከተ፦
ይህ ጥያቄ መነሳት የጀመረው ከኢሳት ምስረታ ጊዜ አንስቶ መሆኑ ይታወቃል።በወቅቱ ይህን ወሬ ከሰሙት መካከል  አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ አንዱ ነበር። ታማኝ  የኢሳት 1ኛ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲ ሲከበር ለጥያቄው መልስ የሰጠው፦” አይደለም እንጂ ቢኾንስ !?”በማለት ነበር። ቀደም ባሉት ዓመታትም ራዕይ ያላቸው አገር ወዳድ ዜጎች የቤት ካርታቸውን ሳይቀር እያስያዙ ከባንክ በተበደሩት ገንዘብ ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ(ኢቲኤን) ይሰኝ የነበረው ተወዳጅ   የቴሌቪዥን ጣቢያ “አንዴ የ ሲ. አይ. ኤ ነው ሌላ ጊዜ የ እነ እገሌ ነው” ከሚል ሀሜት ሊያመልጥ ያለመቻሉን ታማኝ በማውሳት፤ ሰው እየወጣ ለሚናገርበትና ሀሳቡን ለሚገልጽበት  ጣቢያ ህልውና-  የድጋፍ ጥያቄ ሲቀርብለት ምላሽ ባለመስጠቱና የጣቢያውን ህልውና ማስቀጠል ከነዛ ጥቂት ሰዎች አቅም በላይ በመሆኑ ሊዘጋ መቻሉን አብራርቷል።Ethiopian Satellite Television, ESAT TV
“በጣም የሚያሳዝነው ኢ.ቲ.ኤን ተዘጋ ሲባሉ  እሠይ! ደግ ሆኑ!” ያሉ ሰዎች መሰማቱ  ነው።”ሲልም ታማኝ አክሏል።አዎ!ጣቢያው መዘጋቱ የሁሉም መናገሪያ አፍ መዘጋቱ ቢሆንም፤ በዚህ የተደሰቱ  <<ሰዎች>> እንደነበሩ ታማኝ ልምዱን አካፍሎናል።
በወቅቱ ኢሳት በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ መሆኑን የገለጸው ታማኝ፤ ይህን እውነት የማይቀበሉ- የማንም ይሁን የማን የባለቤትነቱ ጉዳይ ሊጨንቃቸው እንደማይገባ፣ ኢሳትን ሊጠይቁትና ሊተቹት የሚገባው እየሠራው ባለው ሥራ ሊሆን እንደሚገባው፣ የዚህ ዓይነት ሥራ የሚሠራ ሚዲያ አይደለም ግንቦት 7- ኢህአዴግም ቢሆን ካቋቋመ ሊመሰገን እንጅ ሊነቀፍ  እንደማይገባው በመንገር ነበር ምላሹን የቋጨው።
-የዩኒቲ ኮሌጅ ባለቤትና ፕሬዚዳንት በነበሩት በዶክተር ፍስሀ እሸቱ “ዕለታዊ አዲስ” የተሰኘ ዘወትር የሚታተም ጋዜጣ ሲቋቋም በፕሬስ ተቋሙ ታቅፈው ከሠሩት ጋዜጠኞች መካከል- ይህ ፀሀፊ አንዱ ነበር። ያኔ ዕለታዊ አዲስ ይታማ የነበረው “ሲ.አይ.ኤ ያቋቋመው ነው” እየተባለ ነበር። ጋዜጣው በርዕሰ-አንቀጹ  በሰጠው ምላሽም ፦”አረ በፍፁም! የሲ.አይ. ኤ አይደለሁም”የሚል ሙግት ውስጥ አልነበረም የገባው-ይልቁንም፦ “ሲ.አይ. ኤ ይህን ጋዜጣ፤ እየሠራ ላለው ተግባር አቋቁሞ ከሰጠ ሊመሰገን ይገባዋል” የሚል ነበር ምላሹ።ሁሌም አዲስና ተልቅ ነገር ከትችት  ሊያመልጥ እንደማይችል ያለፉ ልምዶቻችን ሁሉ ምስክሮች ናቸው።
በኢሳት ዙሪያ ለተነሳው ተመሣሳይ ጥያቄም በበኩሌ ከዚህ ውጪ ምላሽ የለኝም። ኢሳት በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ነፃ ሚዲያ መሆኑን እረዳለሁ።  እኔ የምናገረው፤ የማውቀውን ያህል ነው። ይህን ስነግረው <“አይ ተሣስተሀል ፤ኢሣት የግንቦት 7 ነው”  የሚለኝ ካለ ምላሼ፦”እና? ቢሆንስ?” የሚል ነው።ግንቦት 7ቶች ራሳቸውን የሚተቿቸው ሰዎች ሰይቀሩ በተደጋጋሚ  የሚስተናገዱበትን ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ ካቋቋሙ በእውነት  ልናደንቃቸው ይገባል። አዎ!እንደሚወራው ኢሳት የግንቦት 7 ነው ብለን የምናምን ከሆነ፤ የግንቦት 7 መሪዎች ዲሞክራቶች መሆናቸውን በተግባር ከማስረገጥ ውጭ ሌላ የሚሰጠን ትርጉም ሊኖር አይችልም።
2-ግንቦት 7 እና መሪዎቹ በኢሳት የተለየ ሽፋን ያገኛሉ የሚለውን በተመለከተ፦
ይህ አባባል  በመረጃ ላይ ሳይሆን በግምት የተወሰደ ድምዳሜ እንደሆነ ተረድቻለሁ።ግምት ሁልጊዜ ህሊናዊ(ሰብጀክቲቭ) ነው። ይሆናል ብለን የገመትነው ነገር በመረጃ ሲመረመር ከግምታችን ውጪ የሚሆንበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። ግንቦት 7 ሰፊ ሽፋን ያገኛል የሚለውን ወሬ ለመጀመሪያ ጊዜ  የሰማን ሰሞን ለማወቅ ያህል ” ለየትኛው ፓርቲ ብዙ ሽፋን ሰጥተናል?” በሚል -ዜናና ፕሮግራም ቆጠራ ድረስ ገብተናል።ያኔ አንድነት ፓርቲ ጥሩና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ጊዜ ነበር(እነ አንዷለም ሳይታሰሩ ማለቴ ነው)  በወቅቱ ባደረግነው ቆጠራ ሰፊ ሽፋን አግኝቶ የነበረው አንድነት ፓርቲ ነው። ዶክተር ነጋሶ፣ አቶ አንዷለም፣አቶ አስራት ጣሴ… ሌሎችም  የአንድነት አመራሮች በተደጋጋሚ ቃለ-ምልልስ የሰጡበትና ያወጧቸው የነበሩት መግለጫዎች በሙሉ ሽፋን ያገኙበት ጊዜ ነበር።
-ግንቦት 7 በነጀነራል ከማል ገልቹ ከሚመራው የኦነግ አንድኛው ክንፍ ጋር ትብብር በመሰረተ ሰሞን ደግሞ- ከፍ  ያለ ሽፋን አግኝቶ ነበር።
-የሙስሊሞች መብታችን ይከበር ጥያቄ የተነሳ ሰሞን ደግሞ ጉዳዩ ከሁሉም የበለጠ ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ ነበር።
-የዋልድባም እንደ ችግሩ መጠን ሰፊ ሽፋን አግኝቷል።
-ከሳምንታት በፊት ሰማያዊ ፓርቲም እንዲሁ  ትርጉም ያለውና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምር ሰፋ ያለ ሽፋን አግኝቷል። ወዘተ..
-በግለሰብ ደረጃም የዓባይ ወንዝ ግድብ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እነ ዶክተር ጌታቸው በጋሻው እንዲሁም በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ የ ኢሳት ገቢ ማሰባሰቢያ ሲያካሂዱ እነ  ታማኝ በየነ፣ በተለያዩ ጉዳዩች ፖለቲካዊ ትንታኔያቸውን እንዲያጋሩን ስንፈልግ  ደግሞ እነ ጃዋር መሀመድ… ወዘተ በተደጋጋሚ በኢሳት ላይ ቀርበዋል። ይህ ማለት ጋዜጠኞቹ ለምንሠራቸው ዘገባዎችና ቃለምልልሶች  በአመዛኙ እየተመራን ያለነው በክስተቶች (Events) ነው ማለት ነው።
አንዳንዶቻችን ግን ይህን አልተገነዘብንም ወይም ላለመገንዘብ አስቀድመን የራሳችንን መስመር አስምረናል። ከተጠቀሱት ድርጅቶችና ግለሰቦች ጎልቶ ሚታየን፤ እነ ዶክተር ብርሀኑ ኢሳት ላይ መናገራቸው ብቻ ነው።እደግመዋለሁ ሁላችንም ሳንሆን አንዳንዶቻችን።
ስለዚህ በዚህ ዙሪያ የምንወቀስበት ነገር ካለ ወቀሳው መቅረብ ያለበት ከላይ በአብነት  እንደተጠቀሱት ያሉ  ትኩረት ሳቢ(የዜና ዋጋ ያላቸውን) እንቅስቃሴዎች አድርጎ ሽፋን ያልሰጠንለት ድርጅት ካለ፤ ያን በማሳየት  ቢሆን ይመረጣል። “ጥሩ አንቀሰቃሴ(የዜና ዋጋ ያለው) አደርጌ ሽፋን አልሰጣች ኝም”የሚል ድርጅት ካለ በተጫባጭ በማሳየት ሊወቅሰንም፣ በአደባባይ ሊከሰንም ይችላል።ያ ሲሆን እኛም ያላየናቸውን ስህተቶች ዐይተን ለማስተካከል ዕድል ይኖረናል።እስካሁን ባለው ሂደት በማንም ይደረጉ በማን፤ ያየናቸውን ክስተቶች በሙሉ ያለምንም አድሎ ባለን አቅምና የሰው ሀይል ለመሸፈን ሞክረናል።ከዚህም አልፎ(ብዙዎቹ መረጃ ለመ ጠት ፈቃደኛ አይሁኑ እንጂ) በተለያዩ ጉዳዩት ዙሪያ የመንግስትን  ሀላፊዎች ለማነጋገር ብዙ ጊዜ ሙከራ ተደርጓል።
ይህን ስል  የተሟላ ሥራ እየሠራን ነው እያልኩ አይደለም።ብዙ በሚሠራ ተቋም አልፎ አልፎ ለስህተት መዳረጉ የሚጠበቅ እስከሆነ ድረስ ፤ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ ራሳችን የምናያቸውና የምንነጋገርባቸውም ነገሮች አሉ።በየጊዜው ግን ድክመቶቻችንን ለማሻሻል ጥረት እያደረግን ነው። አሁንም የምለው ነገር ቢኖር፤  በዚህ ረገድ ድክመቶች ተስተውለውብን ከሆነ፤ልንመከርና ልናስተካክል ዝግጁ ነን።
በ3ተኛ ደረጃ የተነሳውን ጥያቄ የማየውም ከዚሁ አንፃር ነው። እስከዛሬ የሚዲያ ሽፋን ያላገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ይኖራሉ። ያ የሆነው ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በአመዛኙ በክስተቶች እየተመራን በመሥራታችን እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም። ወደፊት እነዚህን ጉዳዮች በዕቅዳችን በማካተት ያሉብን ጉድለቶች ለማሻሻል እንጥራለን። ኢሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐይንና ጆሮ ነው የምንለው ለመፈክር ብቻ አይደለም። ከልብ በማመን ነው።
በመጨረሻም፦
ሰሞኑን  በፌስ ቡክ በተሰራጨው የዶክተር ብርሀኑ ንግግር ዙሪያ አስተያየት እንድሰጥ የጠየቃችሁኝ በርካታ ናችሁ።የተሟላና የጠራ መረጃ ባላገኘሁበት ሁኔታ አስተያዬት መስጠት ስላልፈለግኩ ነበር ዝም ያልኩት። አንዳንዶቻችሁ ግፊታችሁን ባለማቆማችሁ በአጭሩ የምለውን ልበል፦
ዶክተር ብርሀኑ በንግግራቸው የጠቀሷቸው ሁለት ተቋማት አሉ-ግንቦት 7 እና ኢሳት። በሚመለከተኝ በኢሳት ጉዳይ ላይ  ባ’ጭሩ የምለው ነገር ቢኖር ፦የኢሣትን ህልውና  ለማረጋገጥና ቢያንስ አሁን በሚያደርገው መጠን ስርጭቱን ለማስቀጠል  ከተፈለገ ፤ ዲሞክራሲ በአገሬ እንዲያብብ እሻለሁ የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ሁሉ ኢሣትን የመርዳት ሀላፊነት ጭምር አለባቸው የሚል ነው። ኢሣት ከምስረታው ድረስ እስካሁን ድረስ “እባካችሁ እርዱኝ” እያለ እንደሚገኝ  በግልጽ የሚታወቅ ነው ።  ይሁንና እንደ ኢሣት ያለን -ከነ ኢቲቪ የተለየ ድምጽን የመጠበቅ  ሀላፊነቱ- የግለሰቦችና የድርጅቶች ብቻ አይደለም።  ስላልታደልን ነው እንጂ በዋነኝነት ኢሣትን  ሊረዳ የሚገባው የኢትዮጵያ መንግስት ነበር።
እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ዋነኛ ጥያቄ፦” ኢሳት ከግለሰቦችም ሆነ ከተለያዩ አካላት የሚያገኘው ድጋፍ የኢዲቶሪያል ነፃነቱን አያሳጠውም ወይ?” የሚል መሆን ነው ያለበት። አዎ! የገንዘብ ድጋፍ መቀበልን- የሚዲያን ነፃነትና ገለልተኝነት አሳልፎ ከመስጠት ጋር በማያያዝ ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ተገቢ ስጋት ነው።
ይሁንና ኢሣት የተመሰረተበት ጊዜ፣ ቦታ(በስደት)፣ዓላማ፣ የተቋሙ አወቃቀር፣የሚገኝበት ሁኔታ ወዘተ..ለተጠቀሰው ስጋት የሚያጋልጠው አይደለም። ይነስም ይብዛም በተለይ በውጪ አገር የሚገኙ በርካታ  ኢትዮጵያውያን  በቋሚነት ሳይቀር ኢሣትን እየደገፉ ይገኛሉ። እነዚህ ወገኖች ኢሳትን እየደገፉ ያሉት ለራሳቸውና ላ’ገራቸው ሲሉ ነው። የድጋፍ መነሻቸውም ይህ አመለካከታቸው ነው። ሰዎቹ ኢሳትን በቋሚነት ስለሚደግፉ በግላቸው ያገኙት ወይም የተደረገላቸው ነገር የለም።ሊኖርም አይችልም። ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችም ጉዳይ  ከዚህ በተለየ መልኩ ሊታይ አይችልም።አንድ ድርጅት ኢሳትን ሊረዳ የሚገባው የኢሳት መኖር ለማደርገው (ለሚደረገው) ዲሞክራሲን የማምጣት ትግል ጠቃሚ ነው በሚል አመለካከት እንጂ- ባደረገው ድጋፍ ምክንያት በተለየ መልኩ በሚዲያው ለመስተናገድ በማሰብ  አይደለም። ግንቦት 7ትም አንደተበለው አሣትን ደግፎ ከሆነ  ከዚህ እሣቤ ውጪ  ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አልገምትም።  “በታገልነው ልክ የስልጣን ደመወዝ ይገባናል “ የሚሉ ገዥዎችን አምርረው የሚኮንኑ ሰዎች ይህን ያስባሉ ማለት በጣም ይከብዳል።     እስካሁን ያሉት የኢሣት አሠራሮችም ይህን አያመለክቱም።
ላብራራ፦  በኢሣት ጋዜጠኞች የኤዲቶሪያል ስብሰባ ላይ አንድም ቀን ከሌሎች በተለየ መልኩ ለእገሌ ፓርቲ ወይም ድርጅት  ይሄ ይሠራለት የተባለበት ጊዜ  ፈጽሞ የለም-ሊኖርም አይችልም።እስካሁን ድረስ የኢዲቶሪያል ነፃነታችን  የተጠበቀ እንደሆነ በድፍረት መናገር እችላለሁ። አልዋሸሁም።ይህን ፅሁፍ  ጓደኞቼ ሊያነቡት እንደሚችሉ አውቃለሁና ቢያንስ እነሱ እንዲታዘቡኝ አልፈልግም።ከዚያም በላይ ህሊና አለ። ማንም ጣልቃ የማይገባበት የኤዲቶሪያል ነፃነት አለን። ሥራችንን እና እንግዶቻችንን የምንወስነው  በኤዲቶሪያል ስብሰባችን  በነፃነት እየተነጋገርን፣እየተከራከርን፣እየተሟገተን ነው።   በምን ምክንያት  ካ’ገራችን ተሰደድን?  …… <<አሳልፈን አንሰጥም!>> በማለታችን ምክንያት ለእስር እና ለስደት የተዳረግንበትንና ስንት ያየንበትን መክሊታችንን/ሀብታችንን/ ነፃነታችንን፤ እዚህ ለምን ብለን የምንጥለው ይመስላችሁዋል? ለገንዘብ? ለጥቅም? ወይስ ለዝና?  በፍጹም!!!  እንዳትሣሳቱ።  ቢያንስ ለራሳችን ክብር  አለን።               ሀቁ ይኸው ነው፦  ነፃና ገለልተኛ የሆነ የኤዲቶሪያል ነፃነት አለን። አምላክ ዕድሜና ጤናውን ይስጠን እንጂ – ይህ ሙያዊ ነፃነታችን ተጠብቆ እስከቀጠለ ድረስ ከኢሣት ጋር እንቀጥላለን።እደግመዋለሁ፦ደመወዝ እስከተከፈለን ድረስ ሳይሆን ፤አሁን ያለን ሙያዊ ነፃነት እስከተጠበቀ ድረስ።    በዚህ አጋጣሚ  እንዲህ ያለ ሙያዊ ነፃነቱ የተጠበቀ የሚዲያ ተቋም ለመሰረቱ ሰዎች ያለኝን ታላቅ አክብሮት ሳልገልጽ ባልፍ፤ ንፉግ እሆናለሁ።
እናም… አስተያዬቴን የጠየቃችሁኝ ሰዎች፣ እንደተባለው ግንቦት 7- ለኢሳት ድጋፍ አድርጎ ከሆነ፤ የግንቦት 7 መሪዎችን- በባልደረቦቼና በኢሳት ወዳጆች ስም ከልብ አመሰግናለሁ ከማለት ውጪ ሌላ ምን ልል እችላለሁ?ሌላ ማለት ካለብኝ ልል የምችለው፦  “ ሌሎችም ድርጅቶች ሆናችሁ ግለሰቦች በምትችሉት አቅም በልጅነት ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ኢሳትን በመርዳት በአገራችን  ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ታግዙ ዘንድ አደራ!” ነው ።
ኢሣት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንደበት፣ ዓይን እና ጆሮ ነው!!!

No comments:

Post a Comment