ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ የዓለም አቀፍ ወንጀል ሕግ ባለሙያና መምህር
ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም 50ኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የመጀመርያ ዙር ተመራቂ ናቸው፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አሜሪካ ከሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ያገኙ ሲሆን፣ የፒኤችዲ ዲግሪም ያገኙት እዚያው አሜሪካ ነው፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በቀይ ሽብር ምክንያት ከአገር ከመሰደዳቸው በፊት በሕግ አማካሪነትና በጠበቃነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሜሪካ ከ20 ዓመታት በላይ በማስተማር ሥራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ፍርድ ቤት ሩዋንዳ ውስጥ በዓቃቤ ሕግነት ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ወደ ማስተማር ሥራቸው ተመልሰው ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በተመድ ግብዣ በናይጄሪያና በካሜሩን መካከል የነበረውን የወሰን ክርክር ለማየት ተቀጥረው ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በአብዛኛው በሰው እንዲታወቁ ያደረጋቸውን የቅንጅት ጥምረት የ1997 ዓ.ም. የምርጫ እንቅስቃሴና ተዛማጅ ውጤቶች አካል ለመሆን የወሰኑት ይህን ሥራቸውን አቋርጠው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በምርጫ 97 ለፓርላማ ተወዳድረው ቢያሸንፉም እንዳብዛኛዎቹ የቅንጅት አባላት ሁሉ ፓርላማ አልገቡም፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ ከግል ሥራቸው ውጪ በትርፍ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ሲሆን፣ በዋነኛነት ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግን ያስተምራሉ፡፡ ሰለሞን ጐሹ እየተካረረ የመጣውን የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትና የአፍሪካ ኅብረትን ውዝግብ አስመልክቶ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በዓለም አቀፍ የወንጀል የሕግ ሥርዓት ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው? ፍርድ ቤቱን ለማቋቋምስ ያነሳሳው ምክንያት ምንድን ነው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ዘ ሄግ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤትን የማቋቋም ሒደት ወደ 80 ዓመት የወሰደ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሙከራ የተደረገው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እንደተደመደመ ነው፡፡ በቬርሳይል ስምምነት መሠረት የጀርመን የጦር ወንጀለኞችን ለመዳኘት ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ገና ሥራውን ሳይጀምር ጦርነቱን ቀስቅሰው የነበሩት የጀርመን ንጉሠ ነገሥት ስፔን ሄደው የስፔን መንግሥት ለፍርድ ቤቱ ሊያስረክባቸው ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ሥራውን አቋረጠ፡፡ ሁለተኛው መኩራ ደግሞ በኑረንበርግና በቶኪዮ የናዚ የጦር ወንጀለኞችን ለመዳኘት ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም ነበር፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች በጣም የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግንና ሥርዓትን አስፋፍተዋል፡፡ ቋሚ የሆነ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለማቋቋም ጥሩ ጠቋሚ ነበሩ፡፡ ሦስተኛው ሙከራ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመዳኘት የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ያቋቋመው ፍርድ ቤትና በዩጎዝላቪያም በተመሳሳይ በፀጥታው ምክር ቤት የተቋቋመው ፍርድ ቤት የያዙትን ጉዳይ አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቃቸው ነው፡፡
ፍትሕ በመስጠትና ጥፋተኞቹን በመቅጣት የተዋጣለት ሥራ ስለሠሩ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ አሁን ቋሚ የሆነ ፍርድ ቤት ማቋቋም አለብን ብሎ ተነሳ፡፡ የተመድ አባል አገሮች ሮም ላይ የፍርድ ቤቱን ማቋቋሚያ አርቅቀው እ.ኤ.አ በ1998 ፍርድ ቤቱ የተቋቋመው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በዓለም አቀፍ የወንጀል ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ያለውን ሥልጣን ካየን የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጀል፣ በሰው ዘር ላይ በሚሠራ ወንጀልና የጠብ አጫሪነትን ወንጀል (Aggression) የማየት ሥልጣን አለው፡፡ ፍርድ ቤቱን ያቋቋሙ አባል አገሮች በጦር ትንኮሳ ምንነት ላይ ስምምነት ላይ ስላልደረሱ ትርጉሙ በሮም ሕግ ውስጥ አልተካተተም፡፡ እስካሁንም ድረስ በዚህ ወንጀል የተከሰሰ የለም፡፡ ፍርድ ቤቱ በወንጀሉ ላይ ክስ አይቀበልም፡፡ ነገር ግን አባል አገሮቹና የፀጥታው ምክር ቤት የፍርድ ቤቱን ሥልጣን ሊያስፋፉት ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቱ ሲቋቋም የበርካታ የአፍሪካ አገሮችን ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት ግን አፍሪካና አይሲሲ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን መርጠዋል፡፡ ፍርድ ቤቱንና አፍሪካን አላግባባ ያለው ችግር መነሻው ምንድን ነው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የፍርድ ቤቱ ሥልጣን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስተናገድን ይጨምራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥሰቶች በአብዛኛው የሚከሰቱት በአፍሪካ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም አይታይም፡፡ የጦር ወንጀልም ቢሆን አይታሰብም፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ግን የተለመደ ነው፡፡ ሌላ ቦታ በሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ አይተኮስም፡፡ ምናልባት በእስያ እንደ ማይናማር ያሉ አምባገነን መንግሥታት ይኖሩ ይሆናል፡፡ አፍሪካን የሚስተካከል ግን የለም፡፡ እንደሚባለው ፍርድ ቤቱ የተጠመደው በአፍሪካ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እርግጥ እስካዛሬ ድረስ ፍርድ ቤት የቀረቡት አፍሪካውያን ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም በመዝገቡ ብዙ አፍሪካዊ ያልሆኑ በተለይ የእስያ አገሮችን ዜጎች የሚመለከቱ ምርመራዎች አሉ፡፡ መረጃ በማጠናቀር ላይ የሚገኙ አፍሪካዊ ያልሆኑ ብዙ አገሮች አሉ፡፡ አፍሪካውያኑ አዲስ ቅኝ ግዛት ለመመሥረት ያለመ ፍርድ ቤት ነው ሲሉ ግርም ነው የሚለኝ፡፡ ወደ ፍርድ ቤቱ የቀረቡ የአፍሪካውያን ጉዳዮች እኮ የተመሩት በራሳቸው በአፍሪካውያኑ መንግሥታት ነው፡፡ የኡጋንዳ፣ የኮንጎና የኬንያ መንግሥታት ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ያላደረገች አገር ሱዳን ብቻ ናት፡፡ ከሰን ልናስቀጣ አልቻልንም፣ አቅሙም የለንም፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ይርዳን ብለው ነው ጉዳያቸውን ያቀረቡት፡፡
ሪፖርተር፡- የአፍሪካ አገሮች ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤቱ ቢመሩትም ይህ በከፍተኛ ተፅዕኖና ጉትጎታ የተከናወነ እንደሆነ ማስረጃዎች ይቀርባሉ፡፡ የኬንያና የኡጋንዳ መንግሥታት የሐሳብ ለውጥንም ለዚህ ማሳያነት ይጠቅሱታል፡፡ ይህ እርስ በርሱ አይጋጭም ወይ?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔ ምንም የሚጋጭ ነገር አይታየኝም፡፡ አንደኛ ነገር ማስረጃ ካለ ያ ሰው የግድ መከሰስ አለበት፡፡ አለበለዚያ ከፍትሕ ተጠያቂነት ማምለጥ ነው የሚሆነው፡፡ ማስረጃ የለም ካሉ መጀመርያውንም አለማቅረብ ነበር፡፡ ማስረጃ ቀርቦ ዓቃቤ ሕጉ የሚያዋጣ መሆኑን ካመነ በኋላ ክሱን ሊያቋርጥ አይችልም፡፡ በአስተያየት ወይም የፖለቲካ ጥቅም ያመጣል በሚል መዝለል አይቻልም፡፡ የአፍሪካ አገሮች ለምሳሌ የሱዳኑን ፕሬዚዳንት አል በሽር መክሰስ ተገቢ አይደለም በሚል ይከራከራሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የሰላሙን ድርድር ያበላሸዋል የሚል ነው፡፡ ሰላም ሊገኝ የሚችለው በቅድሚያ ፍትሕ ሲገኝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የአፍሪካ ልሂቃን የአፍሪካ የፍትሕ አረዳድ ከምዕራባውያን የፍትሕ ሥርዓት ጋር አንድ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ መደበኛ ያልሆነ የፍትሕ ሥርዓትና ማኅበረሰብ አቀፍ መፍትሔዎች የአፍሪካ መለያ እንደሆኑ በመጥቀስ የሚከራከሩም አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ከፍትሕ ይልቅ ሰላም ይስፈን የሚሉ አካላት ተጨባጭ ነጥብ የላቸውም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ፍትሕ ከሌለህ ሰላም ሊኖርህ አይችልም፡፡ አንተም ተው አንቺም ተይ ተብሎ ወንጀል ሊቀር አይችልም፡፡ ቅጣቱ እኮ ሊዘለልም ይችላል፡፡ ማኅበረሰቡም ይቅርታ ሊያደርግለት ይችላል፡፡ ዋናው ቅጣቱ ሳይሆን ተጠያቂነቱ ነው፡፡ በአካባቢው እርቅና ሰላም እንዲወርድ ከተፈለገ ቅጣቱን መዝለል ወይም በይቅርታ ማለፍ ይቻላል፡፡ ተጠያቂነትን ግን በምንም ዓይነት መንገድ መዝለል አይገባም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለአፍሪካ የተለየ ዓይነት ፍትሕ አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ አፍሪካ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የተለየ እሴት እንዳለውም ይከራከራሉ፡፡ የፍትሕ አሰጣጡ ሒደት ከአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊስተካከል ይገባል በማለት ያስረዳሉ፡፡ አውሮፓም፣ አሜሪካም ሆነ አፍሪካም ያለው ሰው ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍትሕ ይፈልጋል፡፡ ፍትሕ ደግሞ ሁሌም አንድ ዓይነት ነው፡፡ ፍትሕ ሁሉን አቀፍ የሆነ መብት ነው፡፡ አፍሪካ የተለየ ፍትሕ የለውም፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ተመሳሳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አይሲሲ ብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶችን በቅድሚያ አሟጦ መጠቀምን ያበረታታል፡፡ የአፍሪካውያን አገሮች ብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶች ከአቅምና ከፖለቲካ ጫና ጋር በተያያዘ ችግር ስላለባቸው ይህ ዕድል በጥንቃቄ መታየት አለበት የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አይሲሲ ጉዳዮችን እያየ ያለው ለአፍሪካ ብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶች በቂ ዕድል ሳይሰጥ እንደሆነ ይተቻሉ፡፡ ለምሳሌ ኬንያ የኡሁሩ ኬንያታን ጉዳይ ራሷ እንድታይ አፍሪካ ኅብረት ጠይቋል፡፡
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አይሲሲ ሲቋቋም የነበረው ትልቁ ጥያቄ ሉዓላዊነትን የተመለከተ ነበር፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ፍርድ ቤቱን ያልተቀበሉት ሉዓላዊነታችንን በሌላ አካል አናስደፍርም በሚል ነው፡፡ ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሲባል በቅድሚያ ዕድል የሚሰጠው ለየአገሮቹ የሕግ ሥርዓት ነው፡፡ የአገሮቹ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ፍትሕ ከተሟጠጠ በኋላ ነው ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚኬደው፡፡ የአይሲሲ ሕግ የሚለው የአገሮቹ ፍርድ ቤት ፍትሕ ሊሰጥ የማይችል ከሆነ፣ ፈቃደኛ ካልሆነ ወይም አቅም ከሌለው፣ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሊያስተናግድ እንደሚችል ነው፡፡ በአፍሪካ ይህን ነገር ስናይ አንደኛ ድክመትም እያላቸው ለሉዓላዊነት ሲባል የማስተናገድ ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከመሩ በኋላ መልሰው እናስተናግድ ማለታቸው በጣም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ የሚወክሉ አገሮች የፍርድ ቤቱ አባል አይደሉም፡፡ ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት መካከል አሜሪካ፣ ቻይናና ሩሲያ አባል አይደሉም፡፡ ይህ የፍርድ ቤቱን ተቀባይነት ምን ያህል ይጎዳል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ችግሩ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አሜሪካውያን በሉዓላዊነት ጉዳይ በጣም በቀላሉ ነው ስሜታቸው የሚነካው፡፡ ከተመድ አባልነት ሁሉ መውጣት አለብን በማለት የሚከራከሩ ብዙ አሜሪካውያን አሉ፡፡ በቡድን ተደራጅተው ይህን የሚያንቀሳቅሱ አሉ፡፡ ሉዓላዊነታቸውን ለአንድ የዓለም አቀፍ ድርጅት መስጠት አይፈልጉም፡፡ ሌላው አባል ያልሆኑበት ምክንያት አሜሪካውያን በዓለም ጉዳይ ሁሉ እጃቸውን አስገብተዋል፡፡ ወታደሮቻቸውም ሆነ ዜጎቻቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አይፈልጉም፡፡ ሆኖም አሜሪካውያን ፍርድ ቤቱን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች ሲደግፉት ደግሞ ይታያል፡፡ በተጨማሪም አባል ካልሆኑት ከቻይናና ከሩሲያ ጋር በመሆን በፀጥታው ምክር ቤት አማካይነት ፍርድ ቤቱን የተመለከቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ይሰጣሉ፡፡ ይኼ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡
ለምሳሌ ቡሽና ብሌር ብዙ ጊዜ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት መቅረብ አለባቸው እየተባለ ይወራል፡፡ ምናልባትም ይገባቸው ይሆናል፡፡ ቡሽ ያለፀጥታው ምክር ቤት ፈቃድ ነው ኢራቅን የደበደበው፡፡ አሜሪካ ግን ለፍርድ ቤቱ አብዛኛውን በጀት ትመድባለች፡፡ በሌላ በኩል ከእያንዳንዱ አገር ጋር በተናጠል ባደረጉት ስምምነት የአሜሪካ ዜጋን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዳያቀርቡ አስፈርመዋል፡፡ ይህን የአሜሪካ ስምምነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ አገሮች ፈርመዋል፡፡ እነዚህን ኃያላን አገሮች ፍርድ ቤቱ ጥቅማቸውን ካልነካ በስተቀር ይፈልጉታል፡፡ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ አድኖ እስከመስጠት ድረስ እኮ ትብብር ያደርጋሉ፡፡ ይህ መቶ በመቶ ተቀባይነቱን ባያጠፋውም ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቱ ከፀጥታው ምክር ቤት ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት አለው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የፍርድ ቤቱ አባል አይደሉም፡፡ ነገር ግን ራሳቸው የማይገዙበትን ተቋም ሌሎች እንዲቀበሉት የማዘዝ ሥልጣን መስጠት በፍትሕ ላይ እንደ መቀለድ አይሆንም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- ይኼ እውነትም በፍትሕ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ራሳቸው የማይገዙበትን ሕግ በሌላው ላይ መጫን ቀልድ ነው፡፡ ነገር ግን የዓለም አቀፍ ሕግና ፖለቲካ የሚነዳው በኃይል ነው፡፡ ጉልበት፣ ኃይልና ሀብት ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በሌላው ሕዝብ ላይ ኃያላኑ የመጫን አቅም አላቸው፡፡ ይኼ ፍትሐዊ አካሄድ አይደለም፡፡ የአሜሪካ እውነታ የዓለም እውነታ የሚሆንበት የዓለም ሥርዓት ነው ያለው፡፡ አሜሪካና ሌሎች ኃያላን አገሮች እኮ ዓለም አቀፍ ሕግን እንደፈለጉት ነው እየጣሱ ያሉት፡፡ እንደ አማራጭ እየቀረበ ያለው ነገር አፍሪካ ውስጥ ራሱን የቻለ የአፍሪካ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋም ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ደረጃ ተቋቁሟል፡፡ በታንዛኒያ አሩሻ ቢሮ ከፍቷል፡፡ እስከዛሬ ድረስ አንድም ጉዳይ ግን አላስተናገደም፡፡ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ፍትሕ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ በአንድ ወቅት አፍሪካዊ ፍርድ ቤት የማቋቋምን ሐሳብ ያነሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአሩሻውን ቢሮ ጎብኝቼዋለሁ፡፡ በቂ የሰው ኃይል አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቱ የአሜሪካን የፖለቲካ ፍላጎት እየተከተለ እንደሚሠራ ይታማል፡፡ ከአሜሪካ ተፅዕኖ ተላቆ ነፃና ፍትሐዊ አሠራር ለመከተል ዕድል ይኖረዋል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ከአሜሪካ ተፅዕኖ መላቀቅ የሚችለው ዓለም በሙሉ ከአሜሪካ ተፅዕኖ ሲላቀቅ ነው፡፡ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ኃይል ሰፊ ነው፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኗቸው ሰፊ ነው፡፡ በጀት በመመደብ አሜሪካ ቀዳሚ ነች፡፡ አፍሪካውያን ለፍርድ ቤቱ አይከፍሉም ማለት ይቻላል፡፡ ገንዘብ የሚመድቡ ናቸው ደፍረው የሚናገሩት፡፡ ይኼ ከዓለም የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ተመድ ራሱ ከዚህ የዓለም ሁኔታ ተገንጥሎ አይታይም፡፡
ሪፖርተር፡- የቀድሞው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዦን ፒንግ የቀድሞውን ዋና ዓቃቤ ሕግ ሞሪኖ አካምፖን ከፍርድ ቤቱ ነጥለው በዘረኝነት ከሰዋቸው ነበር፡፡ አዲሷ ዋና ዓቃቤ ሕግ ቤንሱዳ ጋምቢያዊ መሆኗ ለውጥ ያመጣል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አፍሪካዊ በመተካቱ የፍርድ ቤቱ ሚና ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በኦካምፖ ላይም የተሰነዘረውን ወቀሳ ይኼን ያህል አክብጄ አላየውም፡፡ ፒንግ ይናገር የነበረው የአፍሪካ መሪዎችን ስሜት ነበር፡፡ የአፍሪካ መሪዎችም ሲመቻቸው ፍርድ ቤቱን ይፈልጉታል፡፡ ሳይመቻቸው ሲቀር ደግሞ አይፈልጉትም፡፡ ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ ከባድና አሰቃቂ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አሁን አንድ አፍሪካዊ መሪ ከባድ ወንጀል ለመፈጸም ሲያስብ የፍርድ ቤቱን ህልውና ያስታውሳል፡፡ አሁን ማንም መሪ የትም ይሁን የት አሰቃቂ ወንጀል ከፈጸመ ዘ ሄግ የመሄድ ዕድል አለው፡፡ የሮም ስምምነትን ያላፀደቀ አገር ዜጋ እንኳን ከዚህ አያመልጥም፡፡
ሪፖርተር፡- ባልፈረሙት ሕግ የመገዛት አሠራር ከዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ አይደለም?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እኔ ይኼ አሠራር ትክክል ይመስለኛል፡፡ የሰው ዘር የማጥፋት ወንጀል በሩዋንዳ ቢፈጸምም የሚያመጣው ጥፋት በሩዋንዳ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ አንድን ዘር እስከነጭራሹ ከዓለም ያጠፋል ወይም ለማጥፋት ጥረት ያደርጋል፡፡ ዓለም የአንድ ዘር ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት በመደምሰሱ ይጎዳል፡፡ የሚጎዳው ያ ዘር ብቻ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከፍርድ ቤቱ አወቃቀር መካከል በብዛት ጥያቄ የሚነሳበት የዓቃቤ ሕጉ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ሥልጣንና ተጠያቂነቱ ላይ ቅሬታ ይቀርባል፡፡ አወቃቀሩ ላይ ያለው ችግር ምንድን ነው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አወቃቀሩ ላይ የሚታየኝ ችግር የለም፡፡ ከአንድ አካባቢ ብቻ ዓቃቤ ሕጉን መምረጥ ትክክል አይደለም፡፡ አኅጉራቱና አገሮቹ መወከል አለባቸው፡፡ ዓቃቤ ሕጉ ችሎታው፣ ታማኝነቱ፣ ሀቀኝነቱና የፍርድ ዕውቀቱ ተመርምሮ ነው የሚመረጠው፡፡ የመጀመርያው ጣሊያናዊ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ጋምቢያዊት ናት፡፡ በሠራው ሥራ ወይም ሊሠራ ሲገባው በዘለለው ሥራ ተጠያቂ የሚሆንበት ሥርዓት የለም የሚል ቅሬታ ይቀርባል፡፡ ይኼ በዳኞቹም ላይ በተመሳሳይ ይቀርባል፡፡ ሁሉንም ነገር በተጠያቂነት ማካሄድ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡- የአውሮፓ አገሮች ከአሜሪካ ያልተናነሰ ተፅዕኖ በፍርድ ቤቱ ላይ እንደሚያሳርፉ ይነገራል፡፡ አንዳንድ አፍሪካውያን እንዲያውም ዳግም ቅኝ ግዛትን ለማወጅ ፍርድ ቤቱን እየተጠቀሙ ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ፍርድ ቤቱን የአውሮፓ ፍርድ ቤት በማለት ይጠሩታል፡፡ አውሮፓ አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ እየፈጠረች ነው ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- አውሮፓ አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ እየፈጠረች ነው ለማለት አልችልም፡፡ አውሮፓውያን እኮ ማንም ዜጋ የሰብዓዊ መብቱ ተጠብቆ እንዲኖር የሚያደርግ የራሳቸው ፍርድ ቤት አላቸው፡፡ እንዲያውም ይህ ፍርድ ቤት ለአውሮፓውያን አያስፈልጋቸውም፡፡ ጫና ለመፍጠርም እየተጠቀሙበት ነው ለማለት አልችልም፡፡ ፍርድ ቤቱ የራሱ ጉድለቶች አሉበት፡፡ ነገር ግን አፍሪካውያኑ አብረው በመሥራት ማስተካከል አለባቸው፡፡ የአፍሪካውያን ቅሬታ ከፍትሕ ሳይሆን ከፖለቲካ አመለካከታቸው የሚመነጭ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጉዳዮቹን ለፍርድ ቤት የመምራት መብት ለአገሮች ብቻ ሳይሆን ለግለሰብና ለድርጅቶች ጭምር የተሰጠ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ከግለሰቦችና ከድርጅቶች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ጥቆማዎች ቢቀርቡለትም ቅድሚያ ሰጥቶ የሚከታተለው ከአገሮች የሚመሩ ጉዳዮችን ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በአገሮች የሚመሩ ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጣቸው አንደኛ ማስረጃ በቀላሉ መሰብሰብ ስለሚቻል ነው፡፡ አገሩ ራሱ ስለሚስማማ ያንን ማስረጃ ለማቅረብ ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት የሚያቀርበው ክስ በአገሮች ተቃውሞ ሊቀርብበት ስለሚችል ነው፡፡ መንግሥት ካልተባበረ ማስረጃ ማግኘት ቀላል አይሆንም፡፡ መንግሥታቱ ራሳቸው የሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ለፍትሕ የበለጠ አመቺ ናቸው፡፡ አባል ያልሆነም አገር ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ሥር ከወደቀ ወደ ፍርድ ቤቱ ሊወስድ የሚችልበትም አሠራር አለ፡፡
ሪፖርተር፡- በአፍሪካ ላይ የተደረገው ትኩረት ከወንጀሎቹ ክብደት አኳያ እንደሆነ በአንድ በኩል ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል በኢራቅ፣ በጋዛ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያና በባህሬን ከአፍሪካ በባሰ ሁኔታ አሰቃቂ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ በመጠቆም የፍርድ ቤቱን አድሎአዊነት እንደሚያሳይ የሚቀርብ ክርክር አለ፡፡ በእርግጥ ከባድ ወንጀሎች በአፍሪካ ብቻ ነው የሚፈጸሙት ለማለት ይቻላል?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ለፍርድ ቤቱ ሳያቀርቡ ቀርተው አይደለም፡፡ አፍሪካ ውስጥ በጣም ያነሱ ወንጀሎች ወደ ፍርድ ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ልዩነቱ የማስረጃ ጉዳይ ነው፡፡ በሌሎቹ አገሮች ማስረጃ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በተጨማሪ ጉዳዮቹ ከሃይማኖትም ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ሃይማኖት ለፍትሕና ለክርክር የሚያመች አይሆንም፡፡ ሌሎቹ አገሮች ከአፍሪካ በተለየ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤቱ የማይመሩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በእነኚህ አገሮች የጦር ወንጀል መኖሩ ምንም አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ምዕራባውያን እስልምናን ለማጥፋት ይሠራሉ ስለሚባል ጉዳዮቹን በጥንቃቄ ነው የሚያዩዋቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተባብራ የመሥራት ታሪክ አላት፡፡ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል አገር አይደለችም፡፡ ዋነኛ ምክንያቷ ምንድን ነው?
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የኢትዮጵያ አቋም የሚያሳዝንም የሚያሳፍርም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመቀበል በአፍሪካ ውስጥ ቀዳሚነት ነበራት፡፡ የሮምን ስምምነት ኢትዮጵያ በጉጉት መቀበል ነበረባት፡፡ እንደ ወንበዴ መንግሥታት ይህን ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ አልቀበልም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ተጠያቂ ላለመሆን ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍትሕ ሥርዓት ትልቅ ከበሬታ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ያቀረበችው እኮ የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፍርድ ቤቱን ችግር ቀድማ በመረዳት ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ነው አባል ያልሆነችው የሚል ክርክር የሚያቀርቡ አካላት አሉ፡፡ ኢትዮጵያ አባል ሆና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆን የአፍሪካን የወቅቱ ጥያቄ ለማስተናገድ ትቸገራለች የሚል ሐሳብም ይቀርባል፡፡ የአጋሮቿ የአሜሪካና የቻይና አባል አለመሆንም እንደተጨማሪ ምክንያት ይነሳል፡፡
ዶ/ር ያዕቆብ፡- እነዚህ ሁሉ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከፍትሕ በላይ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ልማትም ሆነ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ከፍትሕ በኋላ ነው፡፡ መረሳት የሌለበት ነገር አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የፍርድ ቤቱ አባል ናቸው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቱን በመቃወም ቀዳሚ ሥፍራ እየያዘች ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ‘የራሳችን የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋም አለብን’፣ ‘ይኼ ፍርድ ቤት ዋጋ የለውም’፣ ‘ሰላም ከፍትሕ ይቀድማል’ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህንኑ እየደገሙት ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- አፍሪካና ፍርድ ቤቱ የተሻለ ግንኙነት ለመመሥረት ምን ሊያደርጉ ይገባል? ፍርድ ቤቱ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አማካይነት በይፋ ‘ዘረኛ’ ተብሏል፡፡
ዶ/ር ያዕቆብ፡- የአፍሪካ አገሮች የዲሞክራሲ ይዞታቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል፡፡ የውስጥ አስተዳደራቸው በዲሞክራሲ ሲታነጽ ፍትሕን ይቀበላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ በተመድ ውስጥ የፍርድ ቤቱና የአፍሪካ አገናኝ ቢሮ ለመክፈት አቅዶ ተመድም በጀት ለመመደብ ተስማምቶ ነበር፡፡ አፍሪካውያን ሐሳቡን ያልተቀበሉት ሌሎቹ አኅጉሮች ሳይኖራቸው ለምን አፍሪካ ብቻ ይኖረዋል በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ችግራቸውን ለመቅረፍ የተሻለ ተቀራርበው መሥራት አለባቸው፡፡ (ምንጭ ሪፖርተር)
No comments:
Post a Comment