FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, August 31, 2013

ተመስገን እላለሁም ፣ አልልምም !


temesgen


በሰላም አውሎ ላሳደረኝ ፈጣሪ ስተኛም ሆነ ስነሳ ” ተመስገን ፈጣሪየ! ” የምትለዋን ምስጋና ከማቅረብ ተቆጥቤ አላውቅም ። ቸርነቱ የማያልቅበት ፈጣሪ አምላኬ አጉድሎብኝ አያውቅም! ጤና ስጠኝ ስለው ጤናውን ፣ ጥበብ መላ ላጣሁለት መላ ስጠኝ ስለው መላ ብልሃቱን ፣ ጉልበቴን አበርታው ስለው ብርታቱን ፣ ቅን ልቦና ስጠኝ ስለው ርህራሔውን እና የፈለግኩትን ሁሉ አያጓድልብኝም! እናም ዘወትር ተመስገን እለዋለሁ !
ገና ከአልጋየ ሳልነሳ ከአፊ ውስጥ አንድ ቃል ይመላለሳል ፣ ቃሉ ወደ አረፍተ ነገር ሺር በሎ ተቀየረ ! በጨለማ የማያይ አይኔን ወደ ድቅድቁ ጨለማ የመኝታ ክፍል ጣራ አፍጥጦ በምናብ አነበንበዋለሁ … በጀርባየ ተኝቸ ወደ ጣራ ካፈጠጥኩበት ወደ ጎን ግልበጥ እልና እጆቸን ጭንቅላቴ ስር ወሸቅ አድርጌ ከአፊ የማወጣውን አረፍተ ነገር ደጋገምኩ ” ተመስገን ተመስገን ተመስገን አልልም !” … እል ይዣለሁ!
የጋዜጠኛ ተመስገን ድብደባ ሰሞነኛው መነጋገሪያ …
ለምጀዋለሁና እንደቀሩት ቀናት በአርቡ የሳውዲ የእረፍት ቀን መዳረሻ በድቅድቁ ጨለማ ሌሊት ላይ ነቅቸ የሚነበብ የሚታይ ካለ ዳሰስ ዳሰስ አደረግኩ። የሚሞነጫጨር የማለዳ ወግ መነሻ የሚሆነኝ ጉዳይ ከአንድ የፊስ ቡክ ወዳጀ በኩል በውስጥ መልዕክት ደርሶኛል ። ይህው መልዕክት የደረሰኝ የኢቲቪ ዜና አንባቢ ጋዜጠኛ ተመስገን በየነ ተደበደበ በተባለ ቅጽበት ነበር ። መረጃው ሲሰራጭ እኔም በጅዳ ቆንስል ከድብደባ ያላነሰ ግፍ ተፈጽሞብኝ ነበር ። በደል እየተፈጸማቸው ፡ እየታመሙና እያበዱ ስላሉ ወገኖቸ ጉዳይ መፍትሔ ፍለጋና ምክክር ስብሰባ “አትሰበሰብም ፣አትመክርም!” ተብየ የታገድኩበት አጋጣሚ ነበርና የሰማሁትም የሆነብኝም አበሳጭቶኝ አዘንኩ ! የቆንስሉን እገዳ መረጃ በጻፈ እጀ በተመስገን ላይ የተቃጣውን ድብደባ የተሰማኝን ስሜት ሳላንዛዛ በተሰራጨው መረጃ ስር አስተያየቴን እንዲህ በማለት አስቀመጥኩ ” እርምጃው በማንም ይወሰድ በማን ፣ አላስደሰተኝም! ” በማለት …
ይህ ከሆነ በኋላ በውስጥ መልዕክት መቀበያ ሳጥኔ ብዙ የተቃውሞና ድጋፍ መልዕክት ደረሰኝ! የለመድኩት ነበርና ሁሉንም በጥንቃቄ እያነበብኩ አለፍኩት ። ከትናነት በስቲያ ከደረሱኝ መካከል ከላይ የጠቀስኩት መልዕክት እንዲህ ይላል” ሰላም ነብዩ በኢባሲ የደረሰብህ በጣም አሳዝኖኛል አሁን የሰማሁት መረጃክ ስለተመስገን መደብ እጅግ አዝኛለው አንተም ሀቅን እንናገር ስላልክ ከኢባሲክ ከተከለከልክ እደተመስገን አንዳያደርጉህ ተጠንቀቅ ” ይላል መልስ የሚያሻው አስተያየት!… እርግጥ ነው ባለኝ ትርፍ ሰአት መረጃ በማቀበሌ እና ሃሳቤን ባንሸራሸርኩ ፣ ከተቃዋሚ ጽንፈኛ ተብየ እስከ መንግስት ጽንፈኛ ደጋፊዎች የሚሰነዘርብኝ የማስፈራሪያ የዛቻና የ”እንገድልሃለን !” ፉከራ እኔ ለምጀው ባልፍም ብዙዎቹን ያሳስባቸዋል! ከእኒህ ወዳጆቸ መካከል ምክር ለለገሱኝ ወዳጀ ምስጋና ካቀረብኩ በኋላ በሰጠሁት ምላሽ ከጋጠዎጦች ባልተናነሰ እኔንም ሆነ የዜጎች መብት መገፈፍ ያገባናል የምንልን ወገኖች መብት የማያከብሩ ፣ ሰላም የነሱን ፣ መብት ማስከበሩ ቀርቶ የሚገፉን የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ናቸው የሚል መልሴን ሰጠሁ … በዚህ ዙሪያና በተመስገን በምንም ሚዛን ተቀባይነት የሌለው ድብደባ ዙሪያ የማለዳ ወግ አምዴ ልሞነጫጭር ባስብም ድካም የመጻፍ ፍላጎቴን ጎድቶት እንቢ አለኝ !
ዛሬ ሌሊት ….
በድቅድቁ ጨለማ በነቃሁ ሰአት ይህንን እያሰላሰልኩ መረጃዎችን መፈተሽ ይዣለሁ … በኢቲቪ ጋዜጠኛ በተመስገን በየነ ላይ ደረሰበት የተባለውን ድብደባ ተከትሎ የቅርብ ወዳጆቹ ፣ አድናቂዎቹና የኢቲቪ ጋዜጠኞች የሰጧቸው አስተያየቶች ተበራክተዋል ። ይህን ሁሉ ቃኝቸ ተመልሸ ገደም እንደልኩ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ !
በማለዳው ግን ተነሳሁ … እናም ሰሞነኛው ተመስገን አልለቀቀኝም “ተመስገን አልልም ” እያስባለ ያሚያንሰላስለኝን ሃሳብ ከተጋደምኩበት ቀና ብየ መጻፍ ጀመርኩ ! ግጥም ሆነ …
ተመስገን ማለቱ ክፉ ነው ባልልም
ስጋቱ ተገፎ ስላላየሁ ዛሬም
ተመስገን ተመስገን ተመስገን አልልም !
የቱ ነው እውነቱ የዝብርቅርቁ አለም ?
ሰው ያለ ሃጢያቱ ከቶ አይወነጀልም ?
ወህኒ አይወረወር አይደበደብም ?
ፍትህን ተነፍጎ ከቶ አይገደለም ?
ለዚህ የሚያስደስት ዛሬ መልስ የለኝም!
ስል በስሜት መነጫጨርሙ … ቀጠልኩ …
ተመስገን ተመስገን ተመስገን ባልልም
ድብደባ ግድያን ፍጹም አልደግፍም !
… አልኩና አንገቴን አቅንቸ በኩራት ተሞልቸ ተመስገን ተመስገን አልልም ስል የቅርብ ሩቁን ፣ ግራ ቀኙን የነፍስ ማጥፋት እኩይ ምግባር አጠየቅኩ … ምክርም መክሬ ፍላጎት ምኞቴን እንካችሁ አልኩ …
በጠራራ ጸሃይ በሚንቀለቀለው
“ኢትዮጵያዊ ክብሬ” ስላለ ቢከፋው
ቆፍጣናውን መምህር ያን አሰፋ ማሩን ከቶ ማን ገደለው ?
ያንን ጋዜጠኛ ተስፋየ ታደሰን ማነው ያጋደመው?
በምሽት ጨረቃ ድምቅ ፍንትው ባለው ?
ጀኔራል ሃየሎም ማነው የደፈረው ?
በጥይቱ ባሩድ ከእኛ የለያየው ?
ማለዳው ጸሃይ ጸጥ ረጭ ባለው
የደህንነቱን ሰው ክንፈን ገብረ ማን አጠፋው ?
አመት እንኳ ቀርቶ መንፈቅ ባልደፈነው
ወሎ ሰማይ ስር ረግቶ በሚታየው
በምሽት ጨረቃ ሸሁን በጭካኔ ማነው ገዳያቸው?
አልኩና ውጋት ህመም የምለውን ፣ ምክር ዝክር ይሆናል የምለውን ገጣጠምኩትን ! ከሙሉው ግጥም ግጥሜን በቀነጨብኳት ስንኝ ውጌን ልቋጭ …
ችግሩን ለማጥፋት ከሆነ የምናልም
ለድብደባ ፣ እስራት ፣ ለተበራከተው የሰው ልጅ ግድያም
መፍትሄ ፍለጋ ከሆነ ምንሻው እንዳይደጋገም
“ምንድነው ሰበቡ ” ብሎ ማጠየቁ ሳይጠቅም አይቀርም !
ህግ ባለበት ሃገር ግፉ ተበራክቶ ፣ ልዩነቱ ከሰፋ
ችግሩን እንመርምር ያለ መቁረጥ ተስፋ
ፍርድን አናዛባ ፣ ግፉንም አናብዛ ሰውን አናስከፋ
ሃገር አናሰድብ ሰሟን አናስጠፋ
ሰላምን አናውርድ ልዩነቱ ይጥበብ እንድንኖር በተስፋ
ይህን ሳናሟላ ፣ በልዩነት ሰበብ ሰውን አንበድለው
ሰው ከሃገሩ በምድሩ ክብሩን አናሳጣው
መብት በጠየቀ አሸባሪ አንበለው !
ይህን ካደረግ ሰውን ካከበርነው
ማግለልን ካቆምን በዘር በቀለሙ ብሎም በእሳቤው
ያኔ ነው ቀናችን ድብደባ ግድያ የሚጠፋውማ
ያኔ ነው ቀናችን ተመስገን መባያው
እልል የሚባለው ሰለም የሚኖረው!
ጥላቻን አጥፍተን ፣በእርቅ በይቅርታ ደምቀን ስንታይ ነው
ተመስገን ፣ ተመስገን ፣ ተመስገን የምንለው !
ከእንቅልፍ አንቅቶ ያብተከተከኝን ሙሉ የስንኝ ቋጠሮ በወግ አሰናድቸ እስካቀርበው ለዛሬ የማለዳ ወግ ይህችን ታክል ካወጋን አይከፋም ! ለእናንተ ለወዳጆቸ መልካም ቀንን ተመኝቸ አንድየን አመስግኘ እንለያይ ! ፈጣሪ ሆይ አንተን አልፋና ኦሜጋ እናመሰግንሃለን ! ተመስገን !
ሰላም
ነቢዩ ሲራክ
ከወይና ደጋው ሳውዲ በአንዷ ከተማ

No comments:

Post a Comment