FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, August 3, 2013

የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ አማረጭ፣ መቼና እንዴት?


ሸንቁጥ አየለ (shenkutayele@yahoo.com)
እድሜዬ ለፖለቲካ ግንዛቤና ትንታኔአዊ ፍች ከደረሰ በሁዋላ አንድ አስገራሚ የስነልቦና ቀዉስ ማህበረሰባችንን ዉጦት አስተዉላለሁ:: ይህም በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የጥላቻን ፖለቲካን በአደባባይ የሚያራምዱ ምሁራንን: ፖለቲከኞችን : ታላላቅ ሰዎችን: የሚዲያ ባለሞያዎችን: የሀይማኖት አባቶችን እና የዉጭ ሀገር ሰዎችን በስፋት ማስተዋል መቻሌ ነው:: የሚገርመዉ ደግሞ የጥላቻ ፖለቲካዉን የሚያራምዱት በኩራትና በእርጋጠኝነት መርህ ላይ ቆመዉ ብሎም ከዚህ የጥላቻ የፖለቲካ ማህጸን የሚወለደዉ አዉሬ እነሱን እንደማይበላቸዉ ተማምነዉ ነዉ:: ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት የጥላቻና የመለያየት ፖለቲካ የሚያናዉዛቸዉ ሰዎች ትናንት የላቸዉም: ነገ የላቸዉም :ዛሬ ብቻ ግን አላቸዉ:: ዛሬ ብቻ የሚለዉ ህሳቤ ዋነኛ የጥላቻ ማጠንጠኛቸዉ መርህና መገልጫቸዉ ነዉ::
የኢትዮጵያዊነት አብሮነት ማንነትን እያነሱና በአሉታዊነቱ ብቻ እያብጠለጠሉ ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ማንነት እንዲሁም የሚያስተሳስሩት የጋራ የአብሮነት ህልዉና የሌለዉ እስኪመስል ድረስ ሀገሪቱም በፍርስራሽ ማንነት ላይ የቆመች እስኪመስል ድረስ ብሎም ወደፊት ህዝቡ እርስ በእርስ ተጠላልቶ እንዲጠፋፋና በመጨርሻም የወላለቀችና የተበጣጠቀች ኢትዮጵያን ለማስተዋል የቆረጡ ታላላቅ ሰዎችን ማስተዋል ችያለሁ:: መቼም ታሪክ በአጋጣሚ ታላቅ ማማ ላይ ካወጣቸዉ ቢያንስ ስለቆሙበት ማማ ስል ታላላቅ ሰዎች ማለት ግድ ሳይሆንብኝ አይቀርም:: በርካታ ኢትዮጵያዉያንም ይሄን በጥላቻ ማዕበል የሚዘወር ፖለቲካዊ ጉዞ ማስተዋል ብቻ ሳይሆን በማዕበሉ ዉስጥ ገብቶ ለመዋኘት ተገደዉ ነገሩን በተገርሞም በፍርሃትም እያስተዋሉ አሉ::
ሀገር የሚያስተዳድር ፖለቲከኛ በድፍረትና በእርግጠኝነት ይሄኛው ህዝብ ለዚህኛዉ ህዝብ ጠላት ነዉና ከዚህኛው ክልል መባረር አለበት እያለ በአደባባይ ሰብኮ ጠላት ያለዉን ህዝብ ከክልሉ አባሮ ሲያበቃ እንደ ሽልማት ወደ ከፍተኛ የስልጣን ማዕረግ ሲወነጨፍና ከክልል ወደ ማዕከል ሲሳብ የምታስተዉሉት በዚህች ስለህገመንግስታዊ መብት በሚወራባት ሀገር ላይ ነዉ:: አንዲት ትልቅ ጋዜጠኛ ብድግ ብላ ይሄኛዉ ህዝብ ዘገምተኛ አእምሮ ያለዉ እና ገና ኢቮሉሽኑን ያልጨረሰ ህዝብ ነው ስትል እየተንቀባረረች ወንጀለኛ ንግግር ስታደርግ እንደ ጀግና ባለስልጣናት ጥላና ከለላ ሲሰጡዋት የምናይበት ሀገር አሁን ያለንባት ኢትዮጵያ ነች::
ይባስ ብላም ይህችዉ ጋዘጠኛ መሰላል ላይ የተሳፈረች ሰዉ ጠላት ብላ ስለፈረጀችዉ ህዝብ በሀገሩ የመኖር መብት አሳንሳና አንኩዋሳ ከመደስኮር ዘላ አንዱ ህዝብ ከገዛ ሀገሩ ማለትም ከአንዱ ክልል ወደ ሌላዉ ክልል መባረሩ አግባብ ነዉ ስትል በዕብሪት ስትናገር የሚደመጠዉ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነዉ:: እሱዋ ራስዋ ግን ማን ክልል ላይ ነዉ ያለሽዉ ብትባልም የጠራ መልስ ስለ ነገም ሆነ ስለትናት መሰረቱዋ የሚያሳስባት ጉዳይ የለም::እንዲህና መሰል አይነት ሀሳቦች እንደ መልካም የሚሰራጩበት ጥላቻዊ ካንሰር የወረረዉ ማህበራዊ ቀዉስ ዉስጥ ከገባን ሰነባብተናል::
የነገን የኢትዮጵያን ሀገራዊ ሸክም የሚሸከም ወጣት ፖለቲከኛና የፖለቲካ ተንታኝ ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጠዉ ወጣት አንድ ሰዉ የዚህ እምነት ተከታይ ካልሆነ የዚህ ብሄር አባል አይደለም በማለት የአንድን ብሄር ማንነት በአንድ እምነት ብቻ ሲያጥረው የምታስተዉሉት በዚህ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ በምትገኘዋ ኢትዮጵያ ነዉ:: ይባስ ብሎም ሳይንሳዊ የፖለቲካ ትንታኔን ከመስጠትና ኢትዮጵያ እንዴት የብዙሃኑን ፍላጎት ማሙዋላት እንዳለባት መፍትሄ ከመጠቆም ይልቅ መራራ ጥላቻን የሚያራምድና በህዝቦች መሃከል አለመተማመንን እንዲሁም የመበቃቀል ስሜትን ለማበረታታት አንዱ ወገን አንዱን ወገን በሜንጫ አንገት አንገቱ ቢለዉ ህጋዊነቱን ለማስረገጥ ደፋ ቀና ሲል የምታስተዉሉት እዚሁ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀዉስ የዋጠዉ ማህበረሰባችን ዉስጥ ነዉ::
በተማርኩባቸዉ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ ምሁራን ነን ብለዉ የተለያዩ ዲግሪዎችን ለማንጠልጠል የሚሽቀዳደሙ ሰዎች ሀገር እንዴት የሁሉን ፍላጎት ልታሙዋላ ይገባል የሚለዉን ጥያቄ አንስተዉ ከመወያዬት ይልቅ በጠባብና በከንቱ የመጠፋፋት ቡድናዊ አባዜ ሲባዝኑ ይስተዋላሉ:: ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ በቡድን ተሰልፈዉ እንዲደባደቡ ሲያበረታቱ አስተዉያለሁ:: ሌላዉ ቀርቶ ማርክ አሰጣጣቸዉ እንኩዋን ጎሳቸዉን መሰረትና ማዕከል ያደረጉ ምሁራን ተብዬ የተቀፈቀፉትም በዚሁ ማህበራዊ ቀዉስ በዋጣት ኢትዮጵያ ነዉ::
ይሄን እዉነት በአለፉት እሩብ ምዕተ አመታት ዉስጥ በዩኒቨርስቲዎቻችን ዉስጥ ያለፈ ዜጋ ሁሉ አስተዉሎታል ወይም በሂደቱ ዉስጥ ተሳትፎአል:: ሆኖም ማንም ወገን አሸናፊ ሲሆን አላስተዋልኩም:: በርካታ ጥላቻዎች ሲሰበኩና ሲነዙ ግን በየቀኑ ተመልክቻለሁ:: አሁንም እየተመለከትሁ ነዉ:: በ እርግጠኝነት በዚህ መሰሉ ሂደት ዉስጥ ማንም አሸናፊ አይሆንም:: ጥላቻ ላሰከራቸዉ ሰዎች ግን ይህን ብትነግራቸዉ ይስቁብሃል:: በጥላቻ ሽምጥ ግልቢያ ላይ ናቸዉና:: ትላንት የላቸዉም ነገም የላቸዉም ዛሬ ብቻ አላቸዉ:: ዛሬአቸዉም በጥላቻ ካንሰር ተበልቶባቸዋል::
በዚህ አይነት ሁኔታ ዉስጥ ያደገ ትዉልድ እንዴት የብዙሃንነት ስሜትን በማንገብ ወደ አደባባይ ሊወጣ እንደሚችል ማሰብ በራሱ አድካሚ ነዉ:: እያንዳንዱ በራሱ የተበደልኩ ባይነት ስሜት ዉስጥ ግብቶ ገና ይብሰለሰላል:: ሌላዉ ቀርቶ አሸንፍኩ ባይ ወገን እንኩዋን ገና ተበድያለሁ ከሚለዉ የመብሰልሰል ስሜት አልወጣም:: ገና ብዙ ቂም : ገና ብዙ ያልተወራረድ ሂሳብ ያብሰለስላል:: ያልገደላቸዉ በርካታ ጠላቶች ከፊቱ ቆመዉ ይታዩታል:: የአባቶቹን ታሪክ ክዶ እንኩዋን ሥለራሱ ክህደት እርግጠኛ አይደለም:: አንዴ መቶ አመት ታሪክ አለኝ ይላል:: ሌላ ጊዜ የሶስት ሽህ አመት ሊያከብር ይሸናከላል:: አሸንፎ እንኩዋን ስለቆመበት መሬትና ታሪክ ምንም እርግጠኛ አይደለም::
ጥላቻ ዛሬዉን እንኩዋን አጥቁሮበታልና:: በአናቱም በርካታ አስመሳዮች በዚህ ሂደት ዉስጥ እዬዋኙ አላዬንም አልሰማንም ሲሉ ታስተዉሉአቸዋላችሁ:: የሀገሪቱ አጠቃላይ ሂደት አያሳስባቸዉም ወይም ደግሞ አንዳያሳስባቸዉ ሆን ብለዉ ልባቸዉን ክርችም አድርገዉ ዘግተዋል:: እነዚህ ወገኖች በዉትወታ ይነቃሉ ብለዉ በማሰብ እነዚህ ወገኖች ላይ የሚጩሁና የስድብ ናዳ የሚያወርዱም ያገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ጥቂት ሀይሎችም አሉ:: ሆኖም ማንም ማንንም አያደምጥም:: የሚያስተሳስራቸዉ ሀግራዊ ራዕይ ሳይኖር አንዱ ወደ ቀኝ ሌላዉ ወደ ግራ ግማሹ ወደፊት ቀሪዉ ደግሞ ወደ ሁዋላ ይፈሳል::
አሁን ከዚህ መአት ማን ያወጣናል? ማንስ ወደ ማን ደፍሮ ይሄዳል? ማንስ ማንን ለማድመጥ ይፈልጋል? የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) ማን ያስተምረናል? እርግጥ ነዉ ማንም ይሄን ጥበብ ለኢትዮጵያዊዉ ትዉልድ ሊያስተምረዉ አይችልም:: የዉጭ ሀይልም ይሄን እዉቀትና ስልት ሊያስታጥቀን አይችልም:: እርግጥ ነዉ ማንም ማንን አስተምሮ ማሳመን አይችልም ወይም ወደ አንድኛዉ አመለካከት ሊስበዉ አይችልም:: እርግጥ ነዉ ማንም ማንንም ለምኖና አባብሎ ሊያሳምነዉ አይችልም:: እርግጥ ነዉ ማንም ማንንም ተዋግቶ ሊያሸንፈዉ አይችልም:: እርግጥ ነዉ ማንም ማንንም አስፈራርቶ ሊያጠፋዉም ሆነ ከምደር ገጽ ሊያስወግደዉ አይችልም::
ግን አንድ እዉነት አለ:: ሁሉ ኢትዮጵያዊ አብሮ በመከራ ዉስጥ የሚያልፍበት መራራ ቀን የመጣበት ዕለት አንድ የጋራ መሰረት መፈለጉና እንዴት እንተባበር መባባሉ አይቀርም:: ያን ቀን ግን አሁን ጎትቶ ወደፊት ማምጣት አይቻልም:: እርግጥ ነዉ በኢትዮጵያዉያን መሃከል ያለዉ ክፍተተ ይሰፋ ዘንድ በተሰራዉ የቤት ስራ የፈረጠመዉ የጥላቻ ጡንቻ መዛሉ ብሎም መተንፈሱ አይቀርም:: ሆኖም ያ ቀን ዛሬ ብዙሃኑ ህዝብ ስለተመኘዉ አይመጣም:: ወይም የተወሰነዉ ወገን ስለ ፍቅር ስለሰበከ ያ ቀን አይመጣም:: እዉነት ላይ ለመድረስ አንዲት አገር በመራራ እዉነት ዉስጥ ማለፍ አለባት:: ዛሬ በጥላቻ ፈረስ ላይ ተቀምጠዉ እየተሳደቡ ያሉም ሆኑ እየተሰደቡ ያሉ ወገኖች : እያባረሩም ያሉ ሆኑ እየተባረሩ ያሉ ወገኖች መራራዉን እዉነት ለማጣጣም በመራራዉ የእዉነት ጎዳና ዉስጥ ማለፍ አለባቸዉ:: ያኔ የጋራ ህልዉናቸዉን ሊገነቡ የሚችሉት በመናናቅና በመጠፋፋት ዉስጥ ሳይሆን በሳይንሳዊ ቀመር በተቀመረ የመቻቻል : የማካተት እና የብዙሃንነት ስርዓተ-መሰረት ላይ ሀገሪቱ ስትቆም ብቻ መሆኑ ይገለጥላቸዋል::
አንዳንድ ወገኖች ዛሬ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ስለሰበኩ በአክራሪ የጥላቻ ስሜት ዉስጥ እየተንቦጫረቁ ያሉ ወገኖች ወደ ማዕከላዊ ህሳቤና ወደ መፋቀር ይመጣሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነዉ:: በርካታ ሀገሮች በበርካታ ዉስብስብ ሂደት ዉስጥ ካለፉ ብሁዋላ ማዕከላዊ የሆነዉን የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) ሊደርሱበት ችለዋል:: ስለሆነም የኢትዮጵያ ጉዳይ የተለዬ የሚመስላቸዉ ኢትዮጵያዉያን አሁን በጥላቻ ስሜት ዉስጥ የሚዳክሩ ወገኖችን በመለማመጥ ወይም በመሳደብ ማዕከላዊ ወደሆነዉ የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) እንዲሁም አቁዋምና አመለካከት መሳብ አይቻልም::
መጽሃፉ እንዳለ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ። ይህ ህሳቤ በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ ለወንድማማችነትና ለፍቅር የሚሰሩ ሀይሎችን በአንድ ዘርፍ ህዝቡን ለመከፋፈልና ለማጫረስ የሚሰሩ ሀይሎችን ደግሞ በሌላ ዘርፍ አቁሞ የሚያሳይ መስታወት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል:: እዉነታው እንዲህ ከሆነ ዘንዳ በጥላቻ ዉስጥ የሚናዉዙት ኢትዮጵያዉያን በጥላቻ ዉስጥ ናዉዘዉ እንዲያበቁ ጊዜም እድልም ስጡዋቸዉ:: ሆኖም ጨርሰዉ ከምድረ ገጽ እንዲያጠፉዋችሁ እድሉን አትስጡዋቸዉ:: በጠሉዋችሁና በሰደቡዋችሁ ቁጥርም አታልቅሱላቸው:: አንድ ነገር ግን ልታረጋግጡላቸዉ የግድ ያስፈልጋል:: ይሄዉም በዚህ ምድር ላይ የምትኖሩት በእነሱ ፈቃድ አለመሆኑን እርግጠኛ ሆነዉ እንዲረዱና እንዲያዉቁ ማድረግ አለባችሁ::
በዚህ ሂደት ዉስጥም የእነሱ ህልዉናም ከእናንተ ህልዉና ጋር በዉዴታ ሳይሆን በግዴታ የተሳሰረ መሆኑን ልታረጋግጡላቸዉ ይገባል:: ይሄን ለማድረግ ግን ሰደብኝ ብሎ እኝኝ ከማለት የዘለለ ስሜትና ህሳቤ ዉስጥ እራሳችሁ ተነክራችሁ መውጣት አለባችሁ:: ይህ ማለት በጥላቻ የናወዙት ሀይሎች ወደዉ ሳይሆን ሳይወዱ የእናንተን ህልዉና እንዲቀበሉ የምታስገድዱበት ደረጃ ላይ መድረስ አለባችሁ:: ያኔ በጥላቻ አባዜ ዉስጥ የሚናዉዙ ሀይሎች ለሁሉም ህልዉና ወሳኝ ወደ ሆነዉ ማዕከላዊ የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) የህላዌአቸዉ ቁልፍ በጋራ ምሰሶሶዉ ላይ እንደተንጠለጠለ እያስተዋሉ ያለ ዉዴታቸዉ ወደናንተ ይሳባሉ:: ያኔም እናንተም እራሳችሁ ያለ ዉዴታችሁ ወደ እነሱ ትሳባላችሁ :: ስልጣኔና እዉቀት በሁላችን ልቦና ሲበራም ሁላችን ወደ ሁላችን እንሳሳባለን:: ያን ጊዜም ከልዩነታችን አንድነታችን ያማልለናል:: ያ ቀን ግን አሁን አይደለም:: በጥላቻ ፈረስ ላይ የወጡት ሀይሎች የእናንተ ህልዉና ከእነሱ ህልዉና ጋር ያለዉ ትሥስር ገና አልታያቸዉምና::
ሂደቱ ግን እዚህ እዉረቀት ላይ እንደሰፈረዉ ቀላል አይደለም:: ማንም በፍጥነት በመሮጥ ያን ቀን ወደ ራሱ የሚጎትተዉ አይደለም:: እንዲሁም ማንም ተኝቶ ስላንቀላፋ ያ ቀን ወደ እርሱ እንዳይደርስ የሚያስቀረዉ አይደለም:: አገር ማዕከላዊ ወደ ሆነዉ የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) ህዝቡዋ አስኪሰባሰብ ድረስ አለሁ ብላ ብታዉጅም እዉነተኛ ህልዉናዋ ገና አልተረጋገጠም:: ሁሉን ነገር እንዲህ ማሰቡ በራሱ ከጥልቅ ፍርሃት በዘለለ ጥልቅ እዉነትን ይፈነጥቃል::የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ አማረጭ ያን ጊዜ በስፋት ይዳሰሳል:: በዚህ ሂደት ዉስጥ ተያይዘን እስክናልፍ ፈጣን የፖለቲካ አማራጮችን የሚያንሰላስሉ ፖለቲከኞች ሊነቀፉ ባይገባም የሚጥሉት የፖለቲካ መሰረት ሁሉ የእንብዋይ ካብ ከመሆን አይዘልም:: ደግሞም ሲሆን እያዬንዉ ነዉ:: ሆኖም ኢትዮጵያዉያን ስለ ሳይንሳዊ የፖለቲካ አማራጮች የሚያወሩበት ቀን በርግጠኝነት ይመጣል:: ሁሉ ለራሱ ሲል አማራጮችን ሳይወድ ያስሳል:: ስለዚህ ዘና በሉ:: በጥላቻ ፖለቲካ እንዳትበረግጉ:: ማንም ማንን ቢጠላ እራሱ እስር ቤት ነዉና በወህኒ ያለ ሰዉ እያሰባችሁ ያ መልካም ቀን እስኪመጣ ፈገግ በሉ:: ከእናንተ በላይ እናንተን የሚጠሉዋችሁ ወገኖች በከፍተኛ የጥላቻ ካንሰር በየቀኑ በዉስጣቸዉ እራሳቸዉን እየገደሉ መሆኑንም አትርሱ:: ከእዉነተኛዉ አካላዊ ካንሰር በከፋ መልኩ የጥላቻ ካንሰርን በዉስጡ የተሸከመ አንድን ሰው አፈንድቶ እንኩዋን ሊያጠፋዉ እንደሚችል እሙን ነዉና::
እኔ በአምላኬ ስም ልባርካችሁና ልለይ:: እንዲህ ብዬ :- ኢየሱስ ክርስቶስ በለምለም ፍቅሩ ጥላ ያኑራችሁ ስል:: እናንተም ከእኔ የተለዬ አምላክ ካላችሁ በአምላካችሁ ስም ባርኩኝ እንጅ አትርገሙኝ:: እንደምናዉቀ በአለም ላይ ማንም የእርግማን አምላክ አይከተልምና ባትወዱኝም ህልዉናዬ ከእናንተ ጋር በአንድ ድር ተሳስሮአልና እኔን ከመመረቅ ዉጭ ምርጫ የላችሁም:: ብትመርቁኝ እራሳችሁን መረቃችሁ:: ብትረግሙኝ ግን እራሳችሁን እረገማችሁ:: በኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚማልለዉን ወገኔን የረገማችሁም ሆነ የመረቃችሁ አጠቃላይ ሚስጥሩ በተመሳሳይ ቁልፍ የታተመ መሆኑ ይሰወራችሁዋል ብዬ አላስብም::
የኢትዮጵያዉያን የፖለቲካ አማራጭ እንዴትና መቼ የሚለዉ ጥያቄ መመለስ የሚጀመረዉ በሁለት ወቅት ነው:: አንዱ በትንሹ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ህልዉና ማክበር ሲጀምርና ለማስከበር ሲንቀሳቀስ ነዉ:: በትልቁ ግን በወዲያኛዉ ወገን የተሰለፈዉ ተቃራኒ ሀይል የራሱ ህልዉና ከሌሎች ህልዉና ጋር የተቆራኘ መሆኑን አዉቆ ስለሌሎች ሲል ፍላጎቱን የተወሰን ትቶ ወደ ጋራ ህሳቤ ማለትም ማዕከላዊ የአካታችነት: የብዙሃንነት እና የጋራ አሸናፊነት ስልት (win-win approach) ወደ እምንለው ቅኝት ሲሳብ ነዉ:: ይህን ላመሰጥርባችሁ ብዬ : ደግሞም ለቅኔ ዘረፋ እንዲያነሳሳችሁ አስቤ : አንድም ከላይ የተወያዬንበት ህሳቤ ምን ያህል እንደተገለጠላችሁ ልፈትናችሁ አቅጄ የአምላኬን ነገር አያይዤ አመጣሁባችሁ::

No comments:

Post a Comment