በአዕምሮ ሁከት የተለከፈችው እህት በጅዳ!
አንድ ወዳጄ መሃመድያ ተብሎ በሚጠራው የጅዳ ከፍል ከኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት አካባቢ ይህችን በፎቶው ላይ የምታዩዋትን እህት አግኝቶ ሊያነጋግራት ቢሞክርም ፈቃደኛ አልነበረችም። ከየት ነው የመጣሽው? ስትባል”ከመቀለ” ከማለት ባለፈ
ስሟንና የሆነችውን አትናገርም። ብዙ ሊያግባባት ሞክሮ ያልተሳካለት ይህ ወዳጀ ይህች እህት ያደፈና የተቀደደ ጥቁር “አባያ” ለብሳና መናኛ ነጠላ ጫማ የተጫማችው እህት የአዕምሮ ሁከት እንዳለባት የተረዳው ብዙ ለማነጋገር ሞክሮ በሰጠችው አንዳንድ ምላሽ እንደሆነ ገልጾልኛል!
ልጁን ትምህርት ቤት ሊያስመዘግብ በሔደበት አጋጣሚ በጠራራው ሜዳ ስትንከራተት በማየቱና ምንም መርዳት ባለመቻሉ ያዘነው ወዳጄን መረጃ ይዤ የጅዳን ቆንስል ሃላፊዎች ስልክ በመደወል ይህችን እህት በመጠለያው አምጥተው ሌላው ቢቀር ካሉት የአዕምሮ በሽተኞች ጋር ቀላቅለው ከመኪና እና ከመሳሰሉት አደጋዎች አንዳትጋለጥ ይሰበስቧት ዘንድ ለማሳወቅ ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካም!
አንድ ሌላ ወዳጄ ከትላንት በስቲያ የዚህችን እህት አሁን ድረስ በአካባቢው መኖርና ዝም ብላ እንደምትዞር ነገረኝና ወዳለችበት አካባቢ ሔጄ በአካል ለማነጋገር ሞክሬ ነበር። በጠራራው ጸሃይ የውሃ ፕላስቲክ ባንድ እጇ፤ በሌላ እጇ ፊስታል አንጠልጥላ እየሳቀች እና እየተኮሳተረች ክው ክው እያለች የምትራመደው እህት አገኘኋት። ብዙ ከተከትልኳት በኋላ አረፍ ስትል ጠብቄ አማርኛ ትችያለሸ? አልኳት “ግደፈኒ” አለችኝ ፊቷን ዘወር እያደረገች! ለማግባባትና ለማቅረብ ሞከርኩ ፣ ልታስቀርበኝ አልቻለችም! ብዙ ተከተልኳት! … ትዞራለች … ትዞራለች … ሲደክማት ታርፈና አሁንም ትዞራለች! በቃ! እንዲህ ሆናለች …
ዛሬም እዚያው አካባቢ እየዞረች እንደምትገኝ ወደ ትምህርት ቤት ለጉዳዩ የሔደ ወንድም አግኝቷት በስልክ ገልጾልኛል። ስትንከራተት አይቶ ሊረዳት የፈለገው ይህ ወንድም እሱም ሆነ ያየውን የዚህች እህት አበሳ ያሳያቸው የትምህርት ቤቱ ሴት ኢትዮጵያውያን መምህራን ተከትለው ሊያነጋግሯትና ሊረዷት ቢፈልጉም ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምንም ማድረግ እንዳልቻለ እያዘን ካነሳው ፎቶ ጭምር ልኮልኛል! ዛሬም ይህን መረጃ ለማቀበል ወደ ጅዳ ቆንስል ሃላፊ ወደ ቆንስል ጀኔራል ዘነበ ከበደ እና ቆንስል ሙንትሃ ስልክ ደውዬ የነበረ ቢሆንም ሊመልሱልኝ ግን አልቻሉም! ይህ በእንዲህ እንዳለ በተፈናቃይ ሰራተኞች ዙሪያ ጥናት ለማድረግ በአምባሳደር ውብሸት የተመራ ቡድን ዛሬም በጅዳ ከቆንስል ሃላፊዎች ጋር በመምከር ላይ መሆኑን ታውቋል።
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment