ኮንትራቱስ ይቁም፣ የቀሩትን ዜጎች መብት ማን ያስከብር?
ሳውዲዎች ከኢትዮጵያ ከኬንያና ከኢንዶኖዥያ የቤት ሰራተኛ ቅጥር ካቆሙ ሰነባበተ! ይህነኑ ተከትሎ የቤት ሰራተኛ እጥረት የሳውዲዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ባለጸጎቹ የሳውዲ ዜጎች በያዝነው የረመዳን ወር ብቻ 32 ቢሊዮን ሪያል የሚገመት ገንዘብ በሃገር ውስጥ ገበያ ልውውጥ ላይ እንደዋሉ በሰማን መባቻ የሳውዲዎች ችግር ሆኖ በመነገር ላይ ያለው የቤት የሰራተኛ አቅርቦቱን ጉዳይ ነው። ይህንንም የሃገሪቱ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው በመዘገብ ላይ ናቸው ። በሰራተኛ አያያዝ በኩል አለም አቀፍ ውግዘት ተለይቷቸው የማያውቁት ሳውዲዎች እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ለዜጎቹ መብት ተከራካሪ የሌላቸውን ዜጎችን ጩኽት መስማት ተስኗቸዋል። “ስብአዊ መብት ገፈፋ ደረስብን!” ሲሉ የዝሆን ጀሮ ይስጠኝ ብለው ይስተዋላሉ ፣ ይህም የሚጠፋው ጥፋት እንደዳይታረም አድርጎታል። የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ክብር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ከሳውዲዎች ጋር በህግ ማዕቀፍ ሳይስማሙ መንገዱን ከከፈቱት ወዲህ ባለፉት ሶስት አመታት ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በኮንትራት ስራ ስም ወደ ሳውዲ ገብተዋል። ሳውዲዎች ከዛሬ ከሶስት አመት በኋላ በአያያዝ ጉድለት ጥፋትና ወንጀል ሲከተል ጤናቸው ተሟልቶ የተቀበሏቸውን ዜጎች በሽተኛ ላካችሁብን እስከሚል ቧልት ተሻግረዋል። ዜጎች ባለፉት አመታት ህጋዊ ተብለው እየመጡ ህገ ወጥ የመብት ገፈፋ ይፈጸምባቸዋል።
ለዚህ ሁሉ በደል ግን ሳውዲዎችን ብቻ መውቀስ ሚዛናዊ አያደርግም ባይ ነኝ! ይህን የምልበት ዋንኛ ምክንያት ከኢትዮጵያ በኩል የሚላኩት ሰራተኞች ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅትና ህጋዊ የሁለቱ ሃገራት የኮንትራት ውል ካለመላካቸው ባሻገር ስለመጡበት ስራ ፣ ስለመጡበት ሃገር፣ አረብኛ ቀርቶ የሃገራችን ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ መናገር የማይችሉ ከገጠሩቱ የሃገራችን ክፍል ተግዘው የመጡ መገኘታቸውን አውቃለሁና ነው! ለ ስራ ያልደረሱ ታዳጊዎች እንደሚላኩ አይቻለሁና ነው! በዚህ መሰል መንገድ የመጡት ዜጎች የት እንደሚገቡ? የት እንደሚድርሱና ምን እንደሚፈጸምባቸው አለመታወቁ ሳውዲ ሲገቡ ክትትል ተደርጎ አይመዘገቡምና ነው! በተባራሪ የምናየው የመብት ገፈፋ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንደጨው በየ ሳውዲው ገጠር ከተማ ተበትነው ሊደርስባቸው የሚችለውን አደጋና ተደራሽ አለመሆናቸውን በግልጽ ያሳይ ይመስለኛል። ይህን ስል ሰብአዊ መብታቸው ተጠብቆ በሰላም መስራት የቻሉ በሽዎች የሚቆጠሩ መኖራቸውን ጭምር በመጠቆም ነው። ስለሚደርሰው በደል ስናወራ ግን ከላይ እንዳስቀመጥኩት ለዚህ የመብት ጥሰት ዋና ተጠያቂ አሰሪዎች ቢሆኑም የኢትዮጵያ መግስት ተወካዮች ለተሰየሙበት የዜጎች መብት ጥበቃ ዋና አላማ ትግበራ ዳተኛ መሆናቸው በተጠያቂነቱ ረድፍ ያሰልፋቸዋል። ይህ ዳተኝነትም ችግሩ ከመቀነስ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል!
ለስራ በመጡ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰው መብት ረገጣ ውሎ ባደረ ቁጥር ዜጎች ራሳቸውን ከማጥፋት ጀምሮ ለሚደርስባቸው በደል የአሰሪዎችን ቤተሰቦች በበቀል እስከማጥቃት ያደረሰ የአእምሮ መታወክ ገጥሟቸው አይተናል፣ ይህ እርምጃም ባይተዋሮች ግራ እንደተጋቡ “የአተርፍ ባይ አጉዳይ!” ሆነው ዘብጥያ ወርደዋል! ለምን ይህን ጥፋት ፈጸሙ? ምን ገጥሟቸው ለዚህ ወሳኔ ደረሱ? ብሎ የሚያማክር፣ ለመብታቸው መከበር የሚቆም ተወካይ አጥተናል ! እህቶች ወንጀል ፈጸሙ ተብሎ ህግ ፊት ቀረቡ ሲባል የሚያስተረጉምላቸው ተወካይ አጥተው በአረቡ መገናኛ ብዙሃን ስማችን ሲጎድፍ ያየንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው! እንደ ዜጋ ዜጎች ግፍና ወንጀል ሲሰራብን፣ ስንሰደብ፣ ስንደበደብ፣ ስንደፈር እና ስንገደል ጠያቂ የለንምና የእኛ ጉዳይ ለአረብ መገናኛ ብዙሃን ጉዳያቸው አይደለምና አይገንም! በአንጻሩ ጥቂት ዜጎቻችን በሚፈጥርባቸው ጫና ተነሳስተው ፈጸሙት ብለን በምንገምተው ተቀባይነት የሌለው አስቃቂ ወንጀል እየተደጋገመ ከተነገረንና ስማችን ካጎደፈው በኋላ ሳውዲ ከኢትዮጵያ የቤት ሰራተኛ የመቅጠር ውል ማቋረጧን በይፋ አስታውቃለች! ከኢትዮጵያ የቤት ሰራተኛ የማምጣት ውል መቋረጥ ተከትሎ ከፍተኛ የሰው ሃይል እጥረት ተከስቷል። ይህንኑ ክፍተት ለመሸፈንም የሳውዲ ቀጣሪዎች ፊታቸውን ወደ ቀድሞዋ የሶብየት ግዛቶች አዙረዋል!
ኢትየጵያን ጨምሮ ከኬንያና ከኢንዶኖዥያ ጋር የቆመውን ውል ለመሸፈን የድሃ አረብ ሃገራትን ዜጎች ለማስመጣት ያደረጉት ሙከራ “በአወቅኩሸ ናቅኩሽ!” ይሁን ሳውዲዎች በሚሰጡት ከዚህ የተለየ ምክንያት የሚሳካ አልሆነም! ሳውዲዎች ችግሩ ለመፍታት የሚሄዱበት መንገድ ለውጥ ያመጣል በሎ መገመት አይቻልም፣ ትናንት ፊሊፒኖች ተረኛ ነበሩ፣ ትናት ሲሪላንካ እና ኢንዶኔዥያ ተረኞች ነበሩ፣ ውሉ ሲሰረዝ ደግሞ እንደተለመደው “በአሰሪዎቻቸው ቤተሰቦች ወንጀል ፈጽመዋል!” የሚለውን ሙግት አስነስቶ ተከላካይ ተወካዮቻቸው የስራ ውላቸውን አገዱት! ሳውዲዎች ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ አቀኑ! የኬንያ መንግስት ተወካዮች በዜጎች የሚደርሰውን እንግልት ተመልክተው ወራት ሳይቆይ የስራ ውሉን ካች አምና ሰረዙት! እኛ ብቻ ያለ መብት ተከራካሪ ቀርተን ለአሁኑ ውርደት ተዳረግን! ያም መጣ ይሄ ሄድ የሳውዲ መንግስት ዜጎቻቸው መሰረታዊ የሰው ልጆችን መሰረታዊ መብት እንዲያከብሩና የአያያዝ ይዞታው እንዲያስተካክሉ ካላደረገ ነገም አዲሶቹን ተቀጣሪ የሩስያ ድሆች ከእኛው የጎደፈ ስም ረድፍ እንደሚያሰልፋቸው አያጠራጥርም!
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የተጣለውን እገዳ ተከትሎ ሰራተኛ ማስመጣቱ ለበርካታ ወራት እንደሚቋረጥ ሲጠቆም በስራ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያንን ከሃገር የማባረር እርምጃ እንደማይወሰድ አንድ የሰራተኛ ሚኒስትር ሃላፊ ገልጸዋል! በስራ ላይ ያሉትን ዜጎች የመብት ጥበቃ ጉዳይ በሚመለከት ግን አሁንም ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ቀጥሏል! በቅርቡ በማህበራዊ ገጾች የተሰራጨውን አንዲት ራሷን የሳተች እህት በሳውዲ አንቡላንስ የጤና ረዳት ሰራተኞች ጋር አይኗን አፍጥጣ ስትታገል የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል እና ራሷን በማቀዝቀዣ መስኮት ስር በኮረንቲ ራሷን አንቃ የገደለችውን ዜጋ ምስል ተመልክቶ ልቡ ያልተሰበረ አለ አልልም! በቅርቡ ያገኘሁት መረጃ ደግሞ ሊሰሙት እንኳ አሰቃቂ ነው። ከወራት በፊት እዚህ ጅዳ ከተማ ውስጥ በጩቤ መላ አካሏ ተወግታ በአሰሪዎችዋ ቤት ሞታ የተገኘችው እህት ጉዳይ አሳዛኝ ሆኖ እናገኘዋለን። ገዳይዋ ለፍርድ መቅረብ ሳይችል በድኗ እየተቆራረሰ ለሳውዲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መማሪያ ሲሆን መባጀቱን በቂ የምስል መረጃ የያዘው ወንድም የተሰፋፋውን የዚያች ምስኪን አካል አስከፍኖ እንደቀበረ ሲናገረው ሰው መሆን ያስጠላል! ይህ ሁሉ ሲሆን የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች አያውቁም አይባልም! ይህ ወንድም እንገለጸልኝ መረጃውን ከማቀበል አልፎ ሬሳውን ለማስቀበር ውክልና ይዞ ከቆንሰሉ ፍቃድ ለማውጣት ቢሔድም ፈተና ተጋርጦበት እንደነበር የሚያመውን መረጃ አቀብሎኛል! . . .
ከዚህ መሰሉ መረጃ ጋር ተዳምሮ ራሳቸውን ያልሳቱት፣ ትንሽ ቀለም ቢጤ የቀሰሙት፣ ስልጡን የሆኑት እህቶች ቀዳዳ እየፈለጉ ችግራቸውን ከመናገር አልቦዘኑም! አድራሻየን ፈላልገው በተንቀሳቃሽ ስልኬ እየደወሉ የችግር ጭንቅ በደል ድምጻቸውን እንዳሰማላቸው የሚጠይቁኝ እህቶች እንባ ሰላም ነስቶኛል! በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ ለማቀበል ወደ ሪያድ ኢንባሲና ጅዳ ቆንስል ተደጋጋሚ ስልክ ብደውልም ሃላፊዎችን ስልካቸውን አይመልሱም! ያን ሰሞን በምስራቅ የሳውዲ ክፍል በደማም በአሰሪዎቿ ቤተሰቦች በደል እየደረሰባት አደሆነ ያጫዎትኳችሁ እህት ውሎ አዳርም ከቀን ቀን እየከፋ መምጣቱን ገልጻልኛለች “አንዱ ልጅ ሊደፍረኝ ከኋላየ መጥቶ ተናነቀኝ፣ አምርሬ ሳለቅስና ታግየ ስመነጨቀው ተወኝ፣ እናት ለምን ታለቅሻለሽ ብላ በስድብ አመናጭቃ ተቀበለችኝ ፣ ምን ላድርግ ብቻየን ሰቅሰቅ ብየ አለቀስኩ!” ስትል ትናንት ምሽት ስልክ ደውላ አጫውታኛለች! የዚህችን እህት ጉዳይ ያሳዘናቸው ወገኖች ከደማም ኮሚኒቲ ሃላፊዎች ጋር አገናኝተውኝ ሙሉ መረጃውን ሰጥቻቸዋለሁ! ለትብብራቸው ምስጋናየ ይድረስ! የሪያድ ኢንባሲ ሃላፊዎችም ተመሳሳይ ትብብር ታደርጉ ዘንድ ከአደራ ጋር እማጸናችኋለሁ! ልድገመው! ሳውዲው ሃላፊ እንዲህ አሉ . . .” ቅጥሩ ቢያቆምም በስራ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ አይባረሩም! “እኔም ይህንን አከልኩበት . . . ለዜጎች የሚቆረቆሩ የመንግስት ተወካዮችን አፋልጉኝ! በማለት . . . ኮንትራቱስ ይቁም፣ የቀሩትን ዜጎች መብት ማን ያስከብር? ስል ቢጨንቀኝ የዛሬ የማለዳ ወጌ መነሻ መድረሻ ወግ አድረግኩት!
የሚሰማኝ ባገኝ . . .!
ቸር ያሰማን!
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment