FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, August 15, 2013

የሥላሴዎች እርግማን (ሁለት)፤ አደህይቶ ማድከም (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም )


ከታትፎና ለያይቶ በማዳከም ቤቱን አፍርሶና መሬቱን ነጥቆ፣ ከሥራው አፈናቅሎና ሥራ አሳጥቶ ያለርኅራኄ ማደህየት በፕሮግራም የተያዘና በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ ሥራ ነው፡፡
Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam
ለጥቂት ዓመታት በአሜሪካ ቆይቶ የመጣ አንድ ጓደኛዬ ራሱን በሁለት እጆቹ ይዞ ‹‹አዲስ አበባ በመሬት መናወጥ ፈራርሳ በመጠገን ላይ ያለች ከተማ ትመስል የለም እንዴ!›› አለኝ፤የመሬት አይደለም አንጂ የመናወጥ ነገር በእርግጥ አለ፤ የመሬት መናወጥ ባይደርስባትም የአእምሮ መናወጥ የመታት ከተማ ነች አልሁት፤ ቅንጅት ነፍሱን ይማረውና በፖሊቲካው መድረክ ብልጭ ብሎ ድርግም ካለበት ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ ታይቶ የማይታወቅ የማፍረስና የመገንባት ሥራ በአንድ ላይ ጎን ለጎን ሲካሄድ እያየን ነው፤ ከጥንስሱ ጀምሮ የማሰብ ችግር ውላጅ መሆኑ በግልጽ ይታያል፤ ብዙ አገሮች አዳዲስ ከተማዎችን ሠርተዋል፤ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ሕንድ፣ ናይጂርያ፣ ብራዚል አሉበት፤ የወያኔ/ኢሕአዴግ ግን የተለየ ነው፤ አዲስ ከተማ እየሠራ ሳይሆን የጥንቱን እያፈረሰ ነው፤ ደርግ ሲጀምር ከጥንቱ ሥርዓት ጋር በመጣላት ነበር፤ ወያኔ ሲጀምር ግን ከማን ወይም ከምን ጋር ተጣልቶ አንደሆነ በግልጽ ባይታይም በጥላቻ መወራጨቱ ይታይ ነበር፤ ጎልቶ የወጣውም የችግረኛ ጉጉትና ምኞት፣ ሽሚያና ዝርፊያ የወያኔ ዓላማ ከራሱ የማያልፍ መሆኑን ያመለክት ነበር፤ በውጤቱም የሆነለት ያባትህ ቤት ሲዘረፍ እንደሚባለው ሆኖ ከውጭ ባንክ ተርፎ፣ ከአገር ውስጥ ባንክ ተርፎ፣ በጆንያና በጉድጓድ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያስቀመጠ ተደላድሎ እየሳቀ ይዝናናል፤ ያልሆነለትም በየሜዳው ያለቅሳል፤ ከተማው በሙሉ በማፍረስና በመገንባት ይታመሳል፤ ይተራመሳል፤ ዋናው ዓላማ ሕዝቡን ማዳከም ነው፤አዳክሞም ማደህየት ነው፡፡–
. ይህ ሁሉ መንገድ የደሀውን ቤት ሁሉ እየመነጠረ ሲረዝምና ሲሰፋ፣
. የደሀ ቤቶች ተመንጥረው መንገዱ ከረዘመና ከሰፋ በኋላ ባለሥልጣኖች በድንገት ስለባቡር የሚያስታውሳቸው አማካሪ     ሲያገኙ፤
. የድሆች ቤቶች እየተመነጠሩ የሰፋውን መንገድ እያፈረሱ ሲያጠቡት!
.ቤቶች ሲፈርሱና መንገዶች ሲረዝሙ፣ መንገዶች ሲሰፉና ሲጠቡ፣
. መንገዱ ለባቡሮች ሲቆፈርና ሲተራመስ፣
. መንገዱ በደሀዎቹ ቤቶች ፍርስራሽ ተጨናንቆ በደሀ እንባ ሲጨቀይ፣
. ለደሀዎች መኖሪያ ኮንዶሚንየም እየተባለ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲገባና ሲወጣ፣
. የመንገዱና የባቡሩ ወጪ ከኮንዶሚኒየሙ ሥራ ጋር ተዳብሎ በቢልዮን የሚቆጠር ብር እየተተራመሰ ከመንግሥት ኪስ   ሲፈስ፣
.‹‹የመንግሥት ሌቦች›› የሚፈስሰውን እየለቀሙና እየተወዳደሩ ‹‹በምድር ላይ ሳንበተን ስማችንን እናስጠራ›>ብለው ግንበ-   ሰናኦርን ሲክቡ፣
.የሙስና ተከላካዮች ፈራ-ተባ እያሉ በእርሳስ ሲመዘግቡና ግንዱንና ስሩን ሳይነኩ በኢዮባዊ ትእግስትና በሰሎሞናዊ ፍርድ  ቅጠሎቹን እየከረከሙ ሲያረግፉ፣
.ሙስና ስሩ እየጠነከረ ግንዱም እንደግንበ-ሰናኦር ወደሰማይ እያደገ ሲሄድና ቅጠሉም ወዲያው ሲለመልም፤
.ደሀነትም በጌትነት እየተጋጠ በሞትና በሕይወት መሀከል ሆኖ እያቃሰተ ሲያድግ፣
.ለደሀነት መቀነሻ የሚባለው ሁሉ ደሀነትን ለማባባስ ሲውል፣
የደላው ይደሰታል፤ የተጎዳው እንባውን በየመንገዱና በየቤተክርስቲያኑ፣ በየቤተ መስጊዱ ይረጫል፤ የሚታዘብ ያንጎራጉራል፤
በቁንጣን፣ በስካር ጥቂቶች ሲንሩ፣
ብዙዎቹ ደግሞ በረሀብ መንምነው በቁንጫ ሲያርሩ፣
የደሀ እንባ ሲጎርፍ መሬቱ ሲሸበር፣
ዝብርቅርቁ ወጣ፤ ሕይወት ትርጉም አጣ፤
መንገዱ ጠበበ፤ ትርምስምሱ በዛ፤
እሪታው፣ ኡኡታው ቀለጠ እንደዋዛ፤
መሬቱም፣ ዓየሩም በክፋት ጠነዛ፤
ጥላቻና ቂሙ በሰፊው ተነዛ፤
እምቢልታው ሲጣራ ነጋሪት ሲያገሳ፣
የአለው ሁሉ ሞቶ የሞተው ሲነሣ፣
ምጽዓት መድረሱ ነው፤ ሊስተካከል ነው ፍርድ፤
በግና ፍየሉ ሊለዩ በገሀድ!
አፍርሶ መገንባት ዘለቄታ ያለው እድገትና መሻሻል ያስከትላል ብለው የሚያምኑ ከኋላቸውም ከፊታቸውም የሚያዩት ሁሉ ያከሸፋቸውና የከሸፉ ናቸው፤ ወደኋላ እንዳያዩ ታሪክ የላቸውም፤ ወደፊት እንዳያዩ ራእይ የላቸውም፤ የሥላሴዎች እርግማን!

No comments:

Post a Comment