(ርዕሰ አንቀጽ)
እርቅን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልን ለማውረድ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ቁልፍ ሚና አላቸው። በር ዘግተው ይጸልያሉ። ያስታርቃሉ። ይገስጻሉ። ያስጠነቅቃሉ። እንዲህ አይነት ለሌሎች ብርሃን ለመሆን የሚቃጠሉ የሃይማኖት አባቶች ያሏቸው ምንኛ የታደሉ ናቸው?
በተቃራኒው የአምላክ ባሪያዎች፣ የየእምነታቸው ባሪያዎች፣ የምዕመናን መንፈስ መጋቢዎችና ጠባቂዎች፣ ወዘተ አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚወጡ በይፋ ተነገረን። “በተገንጣይ ነጻ አውጪ” ስም እየተጠራጠረና እየተጸየፈ አገራችንን ከሚመራ ከሃዲ ድርጅት ጎን ለመቆም የሃይማኖት መሪዎች መነሳታቸው ለፈረደባት ኢትዮጵያና ለህዝቧ ከዚህ በላይ ሃፍረት የለም!! ችግሩ በውስጥም በውጭም ያለውን ይመለከታል። ይህንን ስንል ምክንያታችንን ህዝብ ይረዳዋል ብለን እናምናለን።
በሰማያዊውም ሆነ በምድራዊው ዓለም “መተፋት” አለ። የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ከዚህ አስደንጋጭ /ለሚደነግጡት ነው/ የፈጣሪ ቅጣት ይጠበቁ ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ በወጉ ታውቁታላችሁና ዝርዝር ማብራሪያና ስብከት ውስጥ አንገባም። ተግባራችንም አይደለም። ግን ልብ ያለው ልብ ይበል! ለማለት እንወዳለን። ከመተፋትና ከመናቅ፣ ብሎም ተጠቅመው እንደሚጥሉት እቃ ከመጣል ይጠብቃችሁ!!
ሰሞኑን የሃይማኖት መሪዎችን ኢህአዴግ ሰብስቧቸው ድርጅታዊ ሥራ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ሲያሰለጥናቸው ነበር። በግልጽ ቋንቋ “ሃይማኖታዊ ካድሬነትን” ሲያስተምራቸው ሰንብቷል ማለት ነው፡፡ ስልጠናው “ጽንፈኝነትን ተቃወሙ” የሚል ነው። የተማሩትን በተግባር ለመፈጸምና ያላቸውን ልዩ ብቃት ለመገምገም እሁድ የሰርቶ ማሳያ ሰልፍ እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡ በኢህአዴግ ቋንቋ ሰልፉ “ተሞክሮ ማስፋት፣ ማስፋፋት፣ ማስረጽ፣ ማሳለጥ … ” መሆኑ ነው።
ጽንፈኝነትን መቃወምም ሆነ በሃይማኖቶች መካከል ተቻችሎ ለመኖር በህብረት መነሳት ይሁን የሚባልለትና በመርህ ደረጃ ሊደገፍም የሚገባው ጉዳይ ነው። በየትኛውም ደረጃ፣ ማህበር፣ ተቋምና የሃይማኖት ቤቶች ውስጥ የሚጠነሰስን “ጽንፈኛነት” ባግባቡ መቃወም ሃጢያትም የለውም። ዓለም በሙሉ ባንድነት በሰላማዊ ሰልፍ ጽንፈኛነትን ማስወገድ ቢችልና ሰላም ለማውረድ ባንድነት ቢሰሩ ክፋት የለውም። ወደ ኢህአዴግ ሰራሹ የተቃውሞ ሰልፍ ስንመጣ ግን ለሁሉም ወገኖች ጥያቄም፣ ማሳሰቢያም፣ ፍርሃቻም አንዳለን ለመግለጽ እንወዳለን።
የሃይማኖት መሪዎች በሙሉ ኢህአዴግ ራሱ ለፈጠረው በሽታ “ክትባት አለኝና ኑ ልክተባችሁ” ከሚለው ድብቅ አስተሳሰቡ በተለየ እንዴት በነጻ አስተሳሰብ ላይ ይቆማሉ? ብለን ስንጠይቅ መልሳችን ” አይታስብም” የሚል ይሆናል። ምክንያቱን በውጪም በውስጥም ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ነጻና “ፈሪሃ አምላክ” የነገሰባቸው እንዳልሆኑ እንረዳለንና!! ከዚያም በላይ የሁሉም ወገን ስጋት ይኸው የሃይማኖት መሪዎች መገሸብ ይመስለናል። ኢህአዴግም እንዳሻው የሚነዳቸው አፈጣጠራቸውንና ጽናታቸውን ስለሚገነዘብ ነው።
ሃይማኖቶች የሰላምና የፍቅር መስበኪያ ቦታዎች ናቸው ቢባልም አንዳንድ ሰዎች በጣም ሃይማኖታቸውን ከመውደዳቸው የተነሳ ዓለም በሙሉ የእነርሱ ሃይማኖት እንዲወድላቸው ከመፈለግ የተነሳ በፍቅር የጀመሩትን እምነት አክርረው የጥላቻ መነሃሪያ ያደርጉታል፡፡ ይህ ደግሞ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ሲንጸባረቅ የኖረ እውነታ ነው።
ሰሞኑን ኢህአዴግ የሰበሰባቸው የሃይማኖት ድርጅቶችም መስመር ሊወጣ የሚችለውን የአክራሪነት አቋም እንዲያወግዙ ነቅተዋል፤ ሠልጥነዋል፡፡ በጉባዔው ላይ ሼክ ከድር ሙሐመድ “ሃይማኖት ሰላም ነው። አገራችን ሰላም ትፈልጋለች፤ አገራችን ስትታመም መድኃኒቷ እኛ ነን” ብለዋል። ግሩም አባባል ነው።
አቡነ ማትያስ በበኩላቸውም “የኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገት የሚፈታተኑ የሁላችንም ተቃራኒ ናቸው፤ ይህንን የመቋቋም ኃላፊነትና ግዴታ አለብን፤ … የየእምነታችንን ተከታዮች የአገራችሁን ሰላም ጠብቁ ብለን መስበክ የምንችልበት ሰፊ መድረክ አለን” በማለት ሃሳባቸውን በመሰንዘር ሌሎቹም የሃይማኖት ተቋማት ምን ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
ለሃይማኖት መሪዎቹ የምናስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ይህንኑ ለአገር ተቆርቋሪነታችሁን እና ሰላም ወዳድነታችሁን “ያልተጠኑት ገጾች” ላይ አስፍሯቸው ነው፡፡ ላለፉት 22ዓመታት ሰላም ሲነፍግና ህዝብን ሲጨቁን፤ ዜጎችን በግፍ እስርቤት ሲከትና በቃላት ሊነገር በማይቻል ሁኔታ ሲያሰቃይ፤ ሲገድል፣ በጅምላ ሲጨፈጭፍ፣ ከመኖሪ ቦታ ሲያፈናቅል፣ ዜጎቹን ለአረብ አገር ለግርድና ሲሸጥና ሲያሻሽጥ፣ ህጻናትን (ወንድ ህጻናትን ጨምሮ) ለወሲብ ንግድ ሲሸቅጥ፤ የአገር ድንግል መሬትን የተፈጥሮ ደን እየጨፈጨፈ በሳንቲም ሲሸጥ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ፣ … መብትን ሲነፍግ፣ የመናገርና ሃሳብ የመስጠት መብታችን ይከበር ያሉትን ሁሉ እንደ ወራሪ ኃይል ደረትና ግምባራቸውን በጥይት ሲበሳ፣ የኢትዮጵያ እናቶችን ለዘመናት ሲያስለቅስ፣ … የኖረውን ኢህአዴግን በነካ እጃችሁ “ተው ተመከር፤ ይብቃህ፤ እረፍ!” ስትሉና ስትገዝቱት ባለመሰማታችሁ ምመናን አዝነውባኋል። አሁንም ግን ጊዜ አለና በነካ እጃችሁ ኢህአዴግንም አስጠንቅቁ፣ አውግዙ።
የሃይማኖት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይሆን በነጻ አውጪ ስም የመንግሥት ሥልጣን ይዞ አገርን ላለፉት 22ዓመታት ሲያሸብር የኖረውን አክራሪውና ጽንፈኛውን ህወሃትን ራሱን “እስካሁን የረገጥከው ሰብዓዊ መብት ይበቃሃል” በማለት ሃይማኖታዊ ድርሻችሁን ተወጡ፡፡ የሰላም አስጠባቂ፣ የፍትህና የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ካድሬ ሁኑ፡፡ በምድር ላለው ኑሮና ተድላ ሳይሆን ለመጪው ዓለም አማኞች እንዲያስቡ የምትሰብኩትን እስቲ ለአንድ ጊዜ ራሳችሁ ኑሩበትና ይህንን የሕዝብ እሮሮ በማሳወቅ ከዚህ ምድር አስተሳሰብ የላቃችሁ መሆናችሁን አሳዩ፡፡ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ከሆነም ምዕመኖቻችሁን እንዳስተማራችሁት እናንተም ለተግባራዊነቱ በዝግጅት ቁሙ!
እሁድ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የአክራሪነትና ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብቶች ረገጣንም አብራችሁ ተቃወሙ፤ ይህን የማይገኝ ዕድል ተጠቀሙና ድምጻቸው የታፈነውን ዜጎች ድምጽ አሰሙ፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መግለጫ በእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡ አክራሪዎችንና ጽንፈኞችን “እረፉ” በማለት ያውግዛቸው ብሎ እንዳወጀው ሁሉ፣ በዚያውም ህወሃትንና ኢህአዴግን እንዲሁም ተላላኪዎቻቸውንና ጉዳይ አስፈጻሚ አሽከሮቻቸውን “የእስካሁኑ ይበቃችኋል፤ እረፉ፤ በነጻ አውጪ ስም አገርና ወገን ላይ የምታደርሱትን ግፍ አቁሙ” በሏቸው። እስኪ የሃይማኖት አባትነት ወግ አሳዩን!! እስኪ በታሪክ የሚዘከር ተግባር ፈጽሙ። ከኮሚኒስቶች ጉያና ትዕዛዝ ውጡና በምትሰብኩት አምላክ ፊት ስትቆሙ የማታፍሩ ሁኑ። የ”አምላካችሁ ባሮች” ቅድሚያ ለማን እንደምትሰጡ እወቁ። በሰማያዊውም ሆነ በምድራዊው ዓለም በቁም “መተፋትም” አለና!!
No comments:
Post a Comment