አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - 53ኛ!!
በዓለማችን የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን በማወዳደር ደረጃ የሚያወጣው (4 International Colleges & Universities (4icu)) የአፍሪካ ምርጥ የተባሉትን ዩኒቨርሲቲዎችን ዝርዝር ከጥቂት ሳምንታት በፊት አውጥቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በርካታ መረጃዎችን በመሰብሰብ እንዲሁም ለማንም ወገን ያላዳላ ጠለቅ ያለ ሒሳባዊ ትንታኔ በማድረግ ደረጃውን እንደሚያወጣ በድረገጹ ላይ ጠቁሟል፡፡
ከአንድ እስከ ሃያ ባሉት ዝርዝር ውስጥ የደቡብ አፍሪካና የግብጽ ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃውን በብዛት ተቀራምተውታል፡፡ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ዩጋንዳ፣ ቦትስዋና እና ኬኒያ እስከ ሃያ ባለው ደረጃ በመግባት የአገራቸውን የትምህርት ተቋማት ብቃት አስመስክረዋል፡፡
ከተመሠረተ 60ዓመታት ያለፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (በቀድሞ ስሙ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) እስከ መቶ ባሉት ዝርዝር ውስጥ የ53ኛ “ክብር” ተጎናጽፎዋል፡፡ ከተመሠረቱ ጥቂት ዓመታት በሆናቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተበልጦ ለዚህ የበቃው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀደምት ዓመታት የበርካታ አፍሪካውያን ኩራት ነበር፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ሎሌዎቹን ከየቦታው ሰብስቦ ሥልጣን በያዘ ማግስት መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስተማረቻቸውን 42 ምሁራን በሁለት መስመር ደብዳቤ ማባረር ነበር፡፡ በአቶ መለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ዶ/ር ዱሪ መሐመድ ያባረሯቸው እነዚህ ምርጥ ምሁራን እንደ ምሁርነታቸው በነጻ በማሰባቸውና ተማሪዎችንም እንደዚያው እንዲያስቡ በማድረጋቸው እንጂ በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው ተፈላጊ ባለመሆናቸው እንዳልነበር የታወቀ ነው፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በየቦታው የፈለፈላቸው የካድሬ ማምረቻ “ዩኒቨርሲቲዎች” ስሙን ከመያዝ በስተቀር እስከ 100 ባሉት ዝርዝር አንዳቸውም ለመገኘት አለመብቃታቸው የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳይ ነው፡፡
“ስንዋጋ ከረምን፣ በረሃ መድፍ ስናገላብጥ ነበር፣ … እያሉ የሚምሉት የወያኔ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ሲገቡ ከመለስ ጀምሮ በብርሃን ፍጥነት የከፍተኛ ዲግሪ ባለቤቶች ሆኑ፡፡ ከዚያም አልፎ በበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የሚገኘው የፒኤችዲ ዲግሪ ሲሻቸው “በክብር” ካልሆነም “አገር እያስተዳደሩ ከምትተርፋቸው ጥቂት ጊዜ በመቆጠብ” እየተምነሸነሹበት ነው” በማለት የምሬት አስተያየታቸውን አንድ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ምሩቅ ይገልጻሉ፡፡ የሚያስመርቁትን ተማሪ ሥራ ማስያዝ ሲያቅታቸው ደግሞ “ኮብል ስቶን” የማንጠፍ ዲግሪ ነው የሰጠናችሁ በማለት የድንጋይ አንጣፊነት “የሥራ ዕድል” መክፈታቸውን በአደባባይ ይለፍፋሉ ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ከሌሎች በየመንደሩ ከተፈለፈሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረተው ተመራቂ ለካድሬነትና ለሆዱ እንዲያድር የሚደረግ መሆኑ በተመራቂዎቹ “የእውቀት ጥራት” እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑን የወጣው የ“4icu” ደረጃ መለኪያም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
በአሜሪካ በሚገኝ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራ እያከናውኑ የሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊ ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “እኔ ባለሁበት ዩኒቨርሲቲ በርካታ ነጻ የትምህርት ዕድሎች ይመጣሉ፤ አብረውኝ ያሉ መምህራንም ካገርህ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወገኖችህን ጋብዝ ይሉኛል፡፡ አብዛኛዎቹ ዕድሉን የምልክላቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ቢሆኑም በቅጡ የማመልከቻ ፎርም ለመሙላት በጣም የሚቸገሩ፣ እንግሊዝኛ በትክክል አሳክተው አንድ አንቀጽ የማመልከቻ ደብዳቤ መጻፍ በጣም የሚቸግራቸው ሆነው በማግኘቴ በተደጋጋሚ አንገቴን ደፍቻለሁ” ብለዋል፡፡ ውድድሩ ለከፍተኛ ትምህርት በመሆኑ መሠረታዊ የሚባሉትን መስፈርቶች ማሟላት የግድ እንደሆነ የጠቀሱት እኚሁ ሰው፤ አሁንም ግን ተስፋ እንዳልቆረጡና በየጊዜው እንደሚሞክሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ልጆች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተከፈለላቸው በአውሮጳና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ይሰማራሉ፡፡ ዓላማው ወደፊት አማራጭ በሌለው መልኩ ከኢትዮጵያ ልጆች አብላጫውን ይዞ በመገኘት የማንኛውንም ክፍለኢኮኖሚና አመራር ለመቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው ሌላው የበይ ተመልካች ሆኖ ዕድሜ ልኩን ይኖራል በሚል አስተሳሰብ እንደሆነ የትግራይ ነጻ አውጪው ህወሃት ዕቅድ ነው፡፡
ለህወሃት አሽከር በመሆን ታላቅ “ሹመት” ያገኙትና በቅርቡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣቸው የቀድሞ ትምህርት ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህ የከፍተኛ ተቋማት መለኪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለዚህ “ክብር” ማብቃታቸው ሌላ “ዲግሪ” እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ነው በማለት በአውሮጳ የሚገኙ ሌላ ምሁር ሃዘናቸውን በምጸት ገልጸዋል፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ማሃይምም ቢሆን የኢህአዴግን አቋም እስከተከተለ ድረስ ለሚኒስትርነት እንሾማለን ማለታቸው ለትምህርት ያላቸውን ጥላቻ ብቻ ሳይሆን በካድሬዎቻቸው “ሊቁ፣ ምሁሩ፣ …” ተብለው ቢጠሩም መለስ አላቸው የተባለው ዕውቀት በሙሉ ጥራዝ ነጠቅና ከአፍ ብልጠት የማያልፍ ዕውቀት ብቻ እንደነበር ደጋግሞ ያስመሰከረ ነው፤ ውጤቱን ይኸው እያየነው ነው በማለት እኚሁ ሰው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በቅርቡ ከዕንቁ መጽሔት ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ዩኒቨርሲቲው 53ኛ መውጣቱ “ይገባዋል” የሚያሰኝ ደረጃ ደጋፊ ሃሳብ መሰንዘራቸው ይታወቃል፡፡ በቃለምልልሱ ዶ/ር ዳኛቸው ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብም ሆነ ከፖለቲካ አመራሩ ክፍል የሚመጣ ሃሳብ የሚፈትሽበት፤ ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአስተዳደር ክፍሉ ገንቢ አስተያየቶችንና አመለካከቶችን የሚቀርቡበት ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በተገላቢጦሹ ሃሳብና ምክር ይፈልቅበታል በሚባለው ተቋም ሹመኞች በተለያየ ምክንያት እየመጡ አስተማሪዎችን እየሰበሰቡ የሃሳብና የምክር አቅራቢነት ሚና መጫወታቸው በጣም ያስገርማል፡፡ በተለያየ ጊዜ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እየሰበሰቡ ከኃይማኖት እስከ ልማት፣ ከዕድገት እስከ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ … ወዘተ “አሰልጣኞች” ተመድበው “ሥልጠና” ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት በቅርቡ አቶ ብርሃኑ አስረስ ከጻፉት መጽሐፍ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከታህሳሱ ግርግር በኋላ ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ ተይዘው ፍርድቤት በቀረበቡበት ወቅት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ “የተናቀ መንደር ‘በምንትስ’ ይወረራል” ብለው የተረቱት ተረት ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሠልጣኝ የመንግሥት ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ግቢ ሆኗል፡፡”
http://www.goolgule.com/100-best-universities-of-africa/
No comments:
Post a Comment