FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, February 10, 2014

አንድ ቁምነገር፤ የብሄራዊ ቋንቋ ያለህ…!!! ( አቤ ቶኪቻው)

በነገራችን ላይ ብሄራዊ ቋንቋ የሚባል ነገር የለንምኮ… አማርኛ ለረጅም ጊዚያት የሀገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ ሆኖ አግልግሏል። አሁን ግን አማርኛ በአማራ ክልል እና በፊደራል አስተዳደሮች (አዲስ አበባ እና ድሬደዋ እንዲሁም ይሁንልን ባሉ አንዳንድ ክልሎች) ብቻ ተወስኖ ይኖር ዘንድ ተፈርዶበታል። ሁሉም ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ተማሪዎች በገዛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ። እንዲሁም እንደየ ክልሎቹ ሁኔታ ‘የፌደራሉን’ ቋንቋ (አማርኛ) ከተወሰነ ክፍል በኋላ መማር ይጀምራሉ። (የፌደራል ቋንቋ ስል የፌደራል ፖሊስ ቋንቋ ማለቴ አይደለም ካነሳናቸው አይቀር ግን የእነርሱ ቋንቋ ራሱ መቀየር እንዳለበት ጠቁሞ ማልፉ መልካም ነው እስከመቼ ድረስ ቆመጥ እና ክላሽ ለመግባቢያ ቋንቋ ይጠቀማሉ… ) ሃሃ… ብለን ወደ ቁምነገራችን ስናሳልጥ፤

በኬኒያ የስደት “ኬዝ” ጋገራ
በግሌ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውን አሳምሬ እድግፈዋለሁ። በአፍ መፍቻ ቋንቋ አለመማር አቀበቱ ብዙ ነው። ለምሳሌ፤ አንድ በጉራግኛ አፉን የፈታ ልጅ በሳይንስ ትምህርት ክፍለ ጊዜ በቅጡ በማይርዳው ቋንቋ የእጅ መታጠብ ጥቅም ቢነገረው ቋንቋውን ለምዶ መምህሩ ምን እያለው እንደሆነ እስኪገባው ድርስ ፊቱን ሳይታጠብ ወደ ትምህርት ቤት ሊመጣ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ድሮ አርሰናልን እደግፍ ከነበረው በላይ የምደግፈው ነገር ነው። (እኔ የምለው አርሴ ገሰገሰች…. አሁንም ድጋፌን ልጀምርላት ወይስ አርፌ ሲቲዬን አይዞሽ… ልበል…)
ያም ሆኖ ግን ኢትዮጰያን የመሰለች ሀገር፤ እንዴት ብሔራዊ ቋንቋ አይኖራትም… ይሄን ጊዜ አነስተኛ እና ጥቃቅን የኢህአዴግዬ ካድሬዎች “ኢትዮጵያ የሚባል ብሄር ስለሌለ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ አያስፈልጋትም” ሊሉ እንደሚችሉ ይጠረጠራል ተጠርጥሮ ታድያ እንዴት ዝም ይባላል…
አሁን ‘በስራ’ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት፤ አንቀጽ አራት ላይ የኢትዮጰያ ብሄራዊ መዝሙር፤ በሚለው ርዕስ ስር “የኢትዮጰያ ብሔራዊ መዝሙር የህገ መንግስቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዘቦች በዴሞክራሲ ስርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፤ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል።” ይላል። ይህም ሕግ መንግስቱ ራሱ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መኖሩን ያመለክታል ማለት ነው።  ስለዚህ ኢህአዴግ መስተፋቅር እና መስተ ነዋይ ያስነካቻችሁ በሙሉ “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የለም” ስትሉ ከህገ መንግስቱ ጋር እየተላተማችሁ እንደሆነ ታውቁት ዘንድ ይሁን፤ (መላተም ብርቃችን አይደለም ካላችሁንም እንግዲህ በቴስታ በሉትና የግንባራችሁን ታገኛላችሁ!)
ሀገር በብሔራዊ መዝሙር ብቻ አትኖርም በብሄራዊ ቋንቋም እንጂ… ብለን በአዲስ መስመር ስንቀጥል፤
አሁንም ህግ መንግስቱን ስናየው፤ አንቅጽ አምስት ላይ ስለ ቋንቋ ሲደነግግ፤ “ማናችውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራችዋል” ይላል… እስይ የኔ አንበሳ ብለን ስንወርድው፤ በዚሁ አንቅጽ ቁጥር ሁለት ላይ “አማርኛ የፌድራሉ ቋንቋ ይሆናል” ይላል።  እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የምንቀውጠው፤ (አራዳ “ቀወጠው” ብሎ ሲል፤ አጥብቆ ተከራከረ አለቀም እምቢኝ አለ፣ በጉዳዩ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ  ሲል ተጨቃጨቀ። የሚል ትርጉሜ ይይዛል።)
“አማርኛ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ ይሆናል” ሲል የደነገግውን ሕገ መንግስት አፍ ካለው ይናገር ዘንድ ከሌለውም በተወካይ በኩል እንዲመልስልኝ ሁለት ጥያቄዎችን እጠይቀዋለሁ፤ አንደኛው አማርኛ ብቻውን ምን እዳ አለበት እና ለብቻው የፌደራሉ ቋንቋ ይሆናል… የሚለው ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ፤ ብሄራዊ መግባቢያ ቋንቋችንስ ምንድን ነው… የሚል ይሆናል።
እንደ ሀገር የሚያስትሳስርን የሚያግባባን ሁለትስ፣ ሶስትስ ቋንቋ ቢኖረን የሚጎዳው ማነው… በባቢሎን ዘመን ስራ ፈቶች እግዜርን ላይ ለመድረስ ግንብ ሲገነቡ የልባቸውን ክፋት ያየው አምላክ ቋንቋቸውን ደበላልቀው የሚል ሃይማኖታዊ ትምህርት ሰምቼ አውቃለሁ፤ ታድያ መንግስታችን በልባችን ምንም ክፋት የሌለብንን ዜጎቹን በቅጡ ተግባብተን በቅጡ ተባብረን ትልቅ ሀገር ብንገንባ ምን ይጎድልበታልና ብሔራዊ ቋንቋ አሳጣን…. (የጥያቄ ምልክት በብዛት)
እናም፤ ጆሮ ያለው ይስማ አንድ የሚያደርጉን ቋንቋዎች ያስፈልጉናል። ሶስት እና አራት ቋንቋዎቸን ብብሔራዊ ቋንቋ ደርጃ የሚጠቅሙ ሀገሮች ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱበትም። ስለዚህ እየተግባባን እንድንገነባ ዛሬውኑ ብሔራዊ ቋንቋዎቻችንን አሳውቁን እና  አስተምሩን፤ የዚህ ቁምነገር ፀሀፊ፤ አንጀት ላይ ጠብ በሚሉ አጥጋቢ ምክንያቶች፤ ቢያንስ አማርኛ እና ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ሆነው ግልጋሎት መስጥት እንዲጀምሩ በብርቱ ይወተውታል።
ተቃዋሚዎች ሰምታችኋል!
ኢህአዴግም ሰምተሻል!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10956/

No comments:

Post a Comment