FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, February 20, 2014

የማለዳ ወግ … በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ ወዴት እየሔድን ነው ? (ነብዩ ሲራክ)

ከሳምንት በፊት እዚህ ጅዳ ሻረ ሄራ በሚባል አካባቢ የሃበሻን ዘር ያሳዘነ የግድያ ድርጊት መፈጸሙን ሰማሁ ። ትውውቅ ባይኖረንም በአይን የማውቀው ወንድም አብዱ ሁሴን ይማም በጭካኔ መገደሉን የሰማሁት ድርጊቱ በተፈጸመ ከሰአታት በኋላ ከአንድ ወዳጀ በኩል በደረሰኝ የስልክ መልዕክት ነበር። በቀጣይ ቀናት ወጣቱ አብዱ የተቀጠፈበትን የጭካኔ ድርጊት የሚያወግዙ በርካታ መልዕክቶች ማስተናገድ ጀመርኩ። በመካከላችን ባሉ ጥቂት የሰው አውሬዎች እየሆነ ያለው እና ስማችን የመክፋቱ ነገር ያሳሰባቸው በርካታ ወገኖች በግድያው ማዘናቸውን በመግለጽ በርካታ መልዕክቶችን ልከውልኛል። በጭካኔ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ዘልቆ ነፍሱን አስጨንቆ ያሳዘነው አንድ ወንድም የላከልኝ መልዕክት እንዲህ ይላል ….

Nebiyu Sirak
“.ጩኸት ሰሚ ሲያጣ … ሀበሻ የድሮዎቹ የሉም … ወድ የሆነውን የሰውን ደም በከንቱ የሚጠጡ እርኩስ መንፈስ የተጠናውታቸው ውሾች ናቸው .so ሰሞኑን በ ጅዳ አካባቢ ሸር ሄራ አካባቢ የተደረገውን ግፍ ልንገርክ በሀበሾች ጭካኔ የተገደለውን ልጅ በአካል አውቀዋለሁ “አብዱ ሁሴን ይማም”ይባላል … በሳንጃ ገደሉት ! ልብ በል የሳውዲ መንግስት ታዲያ እዴደት አያሳድደን ! እንደነዚህ አይነት እርኩሶች እያሉ እኛ ቤተሰብ እንዴት እንርዳ? ልጅስ እንዴት እናስተምር? ..ነብዩ ሰው እንዴት …የሰውን ነፍስ ያጠፋል? ደግሞም ሳውዲ ? ከተሰራ ለሚገኝ ገንዘብ እጅግ ያሳዝናል ይጎመዝዛል ! ጌታ እውነቱን ይፍረድ ለሀበሻ ጩኸት በቃኝ እኔም ሀበሻ ነኝ!!! ” ይላል !
ሰሞኑን “ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ በላይ በግፍ የግድያ ወንጀል ተፈጸመ !” ወሬው ከጓዳ እስከ አደባባይ ሲናኝ አስከፊውን ሂደት የታዘቡ ወገኖች ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም። ጉዳዩን በቅርብ ከሚያውቁና ከሚከታተሉ የሃገሩ ሰዎችም መልዕክቶችና አስተያየቶች ድርሰውኝ በሃፍረት ለማስተናገድ ተገድጀም ነበር … የሟችን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ ፣ ኢትዮጵያን የሚወዱና ስለኢትዮጵያ የሚጽፉ ፣ አንድ ከፍ ያለ ሃላፊነት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያና ሃያሲ የሃገሩ ሰው አዝነውብን አግኝቻቸዋለሁ ። በቁም ነገር በቢሯቸው አስጠርተው ያሉኝ እንዲህ ነበር ” ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ምንድ ነው እንዲህ የመሰለ የዘቀጠ በሃበሾች ያልተለመደ ጉዳይ ተደጋገመሳ ? ሀበሾች ምን ገባባችሁ? ከአመታት በፊት በሪያድ መንፉሃ ፣ ከወራት በፊት በመዲና በአብሃ እና በዙሪያው ያን ሰሞን ደግሞ በኪሎ ተማንያ እና በዙሪያው በሃበሾች መካከል መጨካከን የተሞላበት ድርጊት ታይቷል። ከሁሉም የሚያሳዝነው የግድያ ምክንያቶቹ ጊዜያዊ ጸብን ፣ ጥቅምንና ጥቃቅን የሰው ህይዎትን በጭካኔ ሊያስጠፉ የማይገባቸው ምክንያቶች ናቸው ። ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ሲል በጥያቄ ላፋጠጡኝ ሳውዲ ወዳጀ የሚሆን መልስ ግን አልነበረኝም !
እርግጥ ነው ፣ ባሳለፍናቸው አመታት በሪያድ መንፉአ አካባቢ አልፎ አልፎም በኢትዮጵያውያኑ መካከል በሚፈጠር ግጭት ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ዜጎች በሰላ ጩቤ አሰቃቂ ጥቃት ተፈጽሞባቸው የመቁሰልና የመገደል አደጋ ምክንያት እንደ ነበር የአይን እማኞች አጫውተውኝ ነበር ። በጩቤ ለመወጋጋቱ ዋንኛ ምክንያትም ደግሞ ተራ ከገንዘብና ከሴት ጋር የተያያዙ እዚህ ግቡ የማይባሉ ምክንያቶች መሆናቸው ማጤን ፣ መገንዘብ ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል …በሳውዲና የመን ድንበር ከተሞች ይህ መሰሉ ወንጀል የከፋ እንደነበር አውቃለሁ። በተለይም በጀዛን ፣ በአብሃና በከሚስ ምሽት በሚባሉ አካባቢዎች በዙሪያው ባሉ የከተማና የገጠር ከተሞች በከተሙ ኢትዮጵያውያን መካከል ተፈጸሞ የምንሰማው ግድያ ፍጹም ጭካኔ ያልተለየው መሆኑ ይጠቀሳል !
ከሶስት አመታት በፊት በየመን ድንበር ከተሞች በቻም ሳይሆን ወደ በአቅራቢያው ባሉ አብሃና ከሚስ ምሸት ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎችበለስራ ባቀናሁባቸው ቀናት በእኛ ዙሪያ እየሆነ ያለውን ለመስማት የከበደ መረጃ አስታውሳለሁ። በህገወጥ መንገድ በሚያመላልሱ ወገኖች በጎሳ ተቧድነውና ብሔርን ለይተው የሚከሰተውን ግጭት ከጩቤ ያለፈ እንደ ነበርም በቦታው ተገኝቸ ታዝቤያለሁ። በግጭቱ ስለተቀጠፈው ህይዎት ፣ ፍርድን ይጠባበቁ ስለነበሩ የእኛ ገዳዮችም የፍርድ ሂደት በቅርብ እከታተል ነበር ። ከሁሉም የሚያሳዝነው የሰውን ልጅ ያህል ታላቅ ፍጡር በስለት የሚጠፋበትን ምክንያት መስማት እንደነበርም ትዝ ይለኛል። ከሃገር ቤት ያለ የዘር ፣ የግል ጥላቻና ጸብን መሰረት ያደረገው የደም መቃባት ፣ በገንዘብ መካካድ ” ጓደኛየን ነጠቀኝ!” ፣ “የሰማንያ ሚስቴን ደፈረ !”፣ በሚሉትና በመሳሰሉት ክሶች የሚያጠነጥነው ብቀላ በፍትህ ሳይሆን በጭካኔ ለመወጣት የሚፈጸም ያረጀ ያፈጀ ይትበሃል ሳውዲ ተከትሎን መጥቶ ስማችን ማርከሱ ደግሞ ከሁሉም በላይ ያማል !
በያዝነው አመት ከጅዳ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው በሙስሊማን ቅዱስ ከተማ በመዲናም መካካድ ያመጣው አምባጓረጀ በቅዱሷ ከተማ ቅዱስ የማይባል ግድያ ለመፈጸሙ ምክንያት ነበር ። ይህም የጭካኔ ወንጀል የተፈጸመበት ኢትዮጵያዊ ፣ ወንጀል ፈጻሚው ኢትዮጵያዊው መሆኑ ደግሞ ጉድ አሰኝቶ አሳፍሮን አልፏል። ከወራት በፊትም እዚሁ ጅዳ በተለያዩ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያን መካከል የተነሰሱ አምባጓሮዎች በተመሳሳይ ጭካኔ በተሞላባቸው የግድያ ድርጊቶች የተከበቡ ወንጀሎች ምክንያት ነበሩ ማለት ይቻላል። እናም ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ….
ባሳለፍነው ሳምንት በጭካኔ የተገደለው ወንድም ወንጀል ተጠርጣሪ ፣ ተጠያቂ የቅርብ ጓደኛ ወዳጁ የነበረው ወንድም በቁጥጥር ስር መዋሉን ሰማን ! አብዱ በማጣታቸው ትልቁ የሃዘን መርግ የወደቀባቸው፣ የሚይዙት የሚጨብጡ ያጡት ፣ ቤታቸው የጨለመባቸው አንዲት ሴት ልጂና የስድስት ወር ነፍሰ ጡር ባለቤቱ ሃዘን የከበደ ነው…ስለአብዱን ቅንነት፣ ሰው አማኝ ትጉህና ታታሪነቱን የሚመሰክሩት ባልንጀሮቹም ሃዘናቸው መሪር ያደረገው የተፈጸመው የጭካኔ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ወንጀሉ ቀዳሚ ተጠርጣሪ የቅርብ ወዳጆቹ በመሆናቸው እርር ድብን ብለው አዝነዋል! ዛሬ የማይሰማ የማያየን አብዱ ሁሴን እድሜ በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ይገኝ እንደነበር በቅርብ ጓኞቹ ጨምረው አጫውተውኛል ። የወንድም አብዱ ሁሴን ይማም የቀብር ስነ-ስርዓት ትናንት ርቡዕ ከቀትር በኋላ በጅዳ ከተማ ተፈጽሟል ! አብዱ የሔደው ሁላችንም ወደ ማንቀርበት የላይኛው ቤት ነው ! ነፍሱን ይማረው ! ” አላህ ይርሃሙ !”
ወንጀሉን በትኩሱ ለማቅረብ በፖሊስ በጥብቅ መያዙ እጀን ባያዘባቸው ቀናት በርካታ አስተያየቶችን ለመሰብሰብ ሞክሬያለሁ ። ዙሬ ዙሬ ግን የደመደምኩት ሳውዲው ሃያሲ ወዳጀ ባሉት ተስማምቸ ነበር፣ ሃበሾች በዚህ መሰል ድርጊት እንደማንታወቅ ተናትነው ከቅርብ አመታት የሰበሰቧቸው መረጃዎች ቢያሳስቧቸው ቆጣ ብለው በንዴት ያጠየቁኝ ታወሰኝ “ግን ምንድን ነው እየሆነ ያለው? ወደ የትስ እየተኬደ ነው? ” ነበር ያሉኝ …እኔም ተጠርተን የማናውቅበት ወንጀል ሲደጋገም አሞኛልና አሳፍሮ መልስ ያጣሁለትን የሃያሲውን ወዳጀ ጥያቄ ላጠይቅ ግድ አለኝ … ግንስ … በጭካኔ እየተገዳደልን ፣ እየተጠላላን ወዴት እየሔድን ነው ? ምንድን ነው እየሆነ ያለው?
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
Abdu Hussan
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11057/

No comments:

Post a Comment