FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, February 4, 2014

ጦሰኛው የዐይን ኩልና መሬት ቅርምት በኢትዮጵያ

ይሄይስ አእምሮ

እንደመነሻ – በዚህች ቅጽበት በኢቲቪ እየተላለፈ የሚገኘውን አንድ የእንግሊዝኛ ፕሮግራም ብትመለከቱ የት እንዳላችሁ ልትገረሙ ትችላላችሁ፡፡ ወጣቷ ሴት ጋዜጠኛ ለፈረንጆችና አዲስ አበባን ከእግር እስከራሷ ለማያውቋት ቄንጠኛ የኢትዮጵያ ወይም የሌላው ዓለም ዜጎች ስለዚህችው ገሃነም ከተማ ቆንጆ ምስል ለመፍጠር እየቃተተች ስሰማት ሚስቴ እስክትታዘበኝ ድረስ ከንፈሬን ጠመም በማድረግ አሽሟጠጥኳት፤ ሳላውቅ በስሜት ነውና ጋዜጠኚት ይቅርታሽን እባክሽ፡፡ ሚስቴን ግን ታዘብኳት – “ሞጥሟጣ” ብላ አትሰድበኝ መሰላችሁ፤ ሆ! ለካንስ “ሰውን የሚሰደበው በሚያውቀው ነው” መባሉ አለነገር አይደለምና – ዳሩ መጽሐፉስ ቀድሞ “አይከብር ነቢይ በብሔሩ” ብሎስ የለም? በጥቂት የሌሊት የመንገድና የዳንስ ቤት መብራቶችና በጥቂት ዘመነኛ ዳንኪራ ረጋጮች፣ በጥቂት ተምነሽናሾና በጥቂት ገንዘብ መንዛሪዎች የሚሊዮኖች እሥር ቤት የሆነችው አዲስ አበባ እንደለማችና እንዳለፈላት የሚቆጠር ከሆነ የኢቲቪ ድካም በርግጥም ዋጋ አገኘ ማለት ነው፡፡ እውነቱ ግን ይህች ጋዜጠኛ እንደምትለው አይደለም፤ በራሱ ርዕስ ስመለስበት እዳስሰዋለሁ፡፡ ግን ግን ስድስት ሚሊዮን አካባቢ ነዋሪ በሚገኝባት አዲሰ አበባ በጥቂቱ አሥር ሺህ ሰዎች ቢቀማጠሉባትና ሌት ተቀን የሰማይን ጣሪያ በኋላ እግሯ ረግጣ እንዳራቀችው በቅሎ አለልክ ጠግበው እየፈነጠዙ ያሻቸውን ቢያደርጉ አዲስ አበባና አዲስ አበቤዎች አልፎላቸዋል ማለት እንዳልሆነ ኢቲቪዎችም ሆኑ የወያኔው መንግሥት ሊሸፋፍኑት እንደማይችሉ ልናስታውሳቸው ይገባል፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ ነው ነገሩ፤ አዲስ አበባ እነሱ እንደሚያሳዩዋት አይደለችም፡፡ አሁን ወደተነሳሁበት ላምራ፡፡
Land grab in Ethiopia
ጋምቤላ፣ ኢትዮጵያ
“ይበጃል ብለው የተቀቡት ኩል ዐይን አጠፋ፡፡” የምንለው ግሩም ሥነ ቃል አለን፡፡ ጦሰኛ የዐይን ኩል ነው፤ ለጌጥ ብለው ቢቀቡት ዐይንን ከነጭርሱ ደርግሞት ዐረፈው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሕይወት ዘመኔ እስካሁን ከታዘብኳቸውና አሁንም ድረስ ከምታዘባቸው በርካታ መንግሥታዊ ዐዋጆችና ደንቦች መካከል ብዙዎቹ ከመንግሥቶቻችን የሚፈልቁ ሣይሆኑ ከውጭ የተኮረጁ ናቸው – እንደዬመንግሥቶቻችን የርዕዮተ ዓለም ቅኝት ከምሥራቁ ወይም ከምዕራቡ፡፡ የሚኮረጅ ነገር ደግሞ አዋጭነቱና ተግባራዊነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ የጦጢት ምሳሌ ቀላል አስረጂ ነው፡፡
ተማሪው ዛፍ ሥር ሆኖ ሲያጠና ቆይቶ ምሳውን በልቶ እስኪመለስ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሚያጠናበት ዛፍ ላይ ሆና የተማሪውን ድርጊት ትከታተል የነበረችዋ ጦጣ ትወርድና ደብተሩን ልክ እሱ ሲያደርግ እንደነበረው አደርጋለሁ ብላ በእስክርቢቶ ትሞነጫጭርበታለች፡፡ ሲመለስ ተበለሻሽቶ ያገኘዋል፡፡ በዚህ ነገር ሁሌ ይበሳጫል፡፡ አንድ ቀን ግን ቢላዎ አምጥቶ በደንደሱ በኩል አንገቱን ይገዘግዝና ደብተሮቹ ላይ በማስቀመጥ ለምሳው ወደቤቱ ይሄዳል፡፡ ሲመለስ ኮራጇ ጦጢት ራሷን በራሷ ገዝግዛ ገድላ አስከሬኗን ተዘርግቶ ያገኘዋል፤ ተገላገለ(ችም)፡፡ ከዚያን በኋላ የሚያናድደው ጦጣ አልነበረም፡፡ በዱሮው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት በአንደኛው የሚገኝ ጥሩ ታሪክ ነው፡፡
ብዙ የአፍሪካ በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥታት ኩረጃ ይወዳሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ከራሳቸው ማመንጨት የማይችሉ ቀፎራሶች ስለሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ በቂ የመንግሥት አመራር ዕውቀትና ችሎታ ስለሌላቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ ከየዘርፉ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸውን ምሁራን ስለማያስጠጉና ከደደቡ ጭንቅላታቸው አሟጠው ሊያወጡት የሚችሉት የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ከሕዝባቸው ሥነ ልቦናዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ሕይወት ጋር ፍጹም ሊስማሙ የማይችሉ ኩረጃዎችን ከሌሎች ሀገራት በተለይም አደጉ ከሚባሉና በስንትና ስንት ተሞክሮ ከተፈተኑ መንግሥታት እንዳለ እየገለበጡ በሀገርና በሕዝብ መቀለድን እንደዋና መዝናኛቸው ያደረጉት ይመስላሉ፤ አለማወቃቸውን ሊያውቁም ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ሶሻሊዝም ግልብጥ ነው፤ የሠፈራ ፕሮግራም ግልብጥ ነው፤ ሕገ መንግሥት ግልብጥ ነው፤ የትምህርት ሥርዓቱና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፓኬጁ ግልብጥ ነው፤ የአስተዳደር መዋቅሩ ግልብጥ ነው፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አወቃቀር ግልብጥ ነው፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ግልብጥ(ቅጂ) ነው፡፡ ያልተገለበጠ ነገር የለም፡፡ እኛም ተገልብጠናል፤ ኢትዮጵያዊነታችን ቀርቶ ሌላ ሌላ ነገር ሆነናል ወይም እየሆንን ነው፡፡ ግልብጥነት ከዚህ በላይ የለም፡፡ ብዙዎቹ ሲገለበጡ ግን ስማቸውና ቅርጻቸው እንጂ ከአንጀት ለሀገር ዕድገትና ልማት ታስቦ አይደለም፡፡
አንዲትም ትንኝ አልገደልኩ፡፡
አንድም አማራ ከሚኖርበት አካባቢ አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ሰው ከቀዬው አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ኢትዮጵያዊ (በሳዑዲ) አልተንገላታም፡፡
አንድም ኢትዮጵያዊ በፖለቲካ ምክንያት አልታሠረም፡፡
አንድም ዜጋ በተቃውሞ ሠልፉ ምክንያት አልተገደለም ወይም ማረሚያ ቤት አልገባም፡፡
አንድም ዜጋ ከእርሻውና ከመኖሪያ ቦታው (ቦታው ለኢንቬስተሮች በሊዝ በመሸጡ ምክንያት) አልተፈናቀለም፡፡
አንድም ሰው አልተራበም፡፡
አንድም ነጋዴ በግብር ብዛት አልተማረረም፡፡
አንድም የመንግሥት ሠራተኛ በኑሮው አልተማረረም፡፡
አንድም ገበሬ ኢሕኣዴግን እጠላለሁ አላለም፡፡
ወዘተ……
ኦ! ኦ! ኦ! ኦ! በጣም፣ በጣም፣ እጅግ በጣም ዕድለኞች ነን፡፡ ብዙ “አንድም”-ኦችን መጥቀስ ይቻላል – የመንግሥት ሰዎቻችን የኛን የሞልቃቃ ዜጎቻቸውን የተደላደለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኑሮ ለሚዲያ ፍጆታና ለዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ለማስረዳት በሚያደርጉት የዘወትር ጥረት የሚናገሩትን ለማስታወስ ነው እነዚህን ጥቂት ምሳሌዎች ያነሳሁት እንጂ ሁሉም ነጭ ውሸቶች ቢጠቀሱ ሰማይ ብራና ውቅያኖሶች ቀለም ቢሆኑ ተጽፈው አያልቁም ፡፡ (ማሳሰቢያ፡ ይህን ጦማር የምጽፈው በታሪክ መዝገብ ቤት የሚቀመጥልኝ በዚህ ጉዳይ ዙሪያም የጮኽሁት አንዳች ነገር እንዲኖረኝ በመሻት እንጂ ወያኔ ሰምቶኝ፣ ከሚያደርገው ነገር ይታቀባል ከሚል ሞኝነት እንዳልሆነ አስፈላጊ ባይሆንም እዚህ ላይ መጠቆም እፈልጋለሁ፤ የተረገመ ቡድን ጊዜውን ጨርሶ በታሪክ ወጀብ እስኪጠራረግ ድረስ የዜጎችን ብሶትና የታላላቆችን ምክር የሚሰማበት ጆሮም ሆነ ትግስት እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ ወያኔዎች በተለይ የሚቃወማቸው የሚመስላቸውን ወገን ‹ጭራ ለማስበቀል› የሚወዳደራቸው የለም፡፡ ጠላቶቻቸውን በማናደድ በምድር አንደኞች ናቸው – የሰማዩን አላውቅም፤ ያው የነሱው ጌታ ሊቀ መላኩ ሣጥጥናኤል ሊሆን እንደሚችል ከመጠርጠር በስተቀር፡፡)
የወያኔን ምግባር የምታስታውስ የአንዲት ሴት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ሴትዮዋ ባሏ ከሚለው በሁሉም ነገር ተቃራኒ ናት፡፡ “እንብላ” ሲላት “እንፍሳ” የምትል በባሕርይዋ ፍጹም ጋግርታም የሆነች የትዳር ላይ ወያኔ ናት፡፡ እኛ የወያኔን ጠባይ ማወቅ አቅቶን በትንሹ 23 ዓመታትን በ“እንካስላንትያ በብጣሽ” “ምናለ በድሪቶ” ዓይነት መደናቆር ስንጃጃልና ወርቃማ ጊዜያችንን በከንቱ ስናባክን ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ እንደዘለቅነው የዚች ሴትዮ ባልም አንዳች መፍትሔ በመፈለግ ወርቃማ ሊያደርገው ይችል የነበረውን የትዳር ሕይወቱን በከንቱ በማባከን ሲደናቆር ባጅቶ በመጨረሻው ያቺ ሴት ጎርፍ ወስዷት ትሞታለች፡፡ መንደርተኛው ተጠራርቶ የዚያችን ሴት ሬሣ ፍለጋ ወደ ወንዝ ይወርዳል፡፡ ባል “ወንድሞቼና እህቶቼ አንደዜ ስሙኝማ!” ይልና እንዲህ ይላቸዋል፡ “ሚስቴ ለኔም ሆነ ለቤተሰቡ ቀና ሆና አታውቅም፤ ነፍሷን ይማረውና ምነዜም ተቃራኒ ነበረች፡፡ ስለዚህ ለጎርፉም ስለማትታዘዘው እንዲህ ሽቅብ ወደላይ እንጂ ወደታች አትሄድለትምና ወደታን ትተን እንዲህ ተወደላይ በኩል እንፈልጋት” በማለት ጎርፉ በሚሄድበት አቅጣጫ ሣይሆን በሚመጣበት አቅጣጫ በኩል እንዲፈልጓት ሃሳብ አቀረበና በጎርፍ ሰውን የመውሰድ ዓለም ውስጥ አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡ ወያኔም ሆን ብሎና እንደሥልት የሚከተለው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚበጅ ሃሳብ ከቀረበ ሁልጊዜም – ከጥቂት በጣት የሚቆጠሩ አብነቶች በስተቀር – ተቃራኒውን መንገድ ነው የሚከተለው፡፡ ያንንም የሚያደርገው ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አጥቶት ሣይሆን ሀገራዊ ስሜት የሌለው በመሆኑና እንደስትራቴጂ የሚከተለው የአገዛዝ ዘይቤ ከቀድሞዎቹ ገዢዎች በተለዬ ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ የሱ የለዬለት ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ሣይሆን የኛ በወሬና በጩኸት ዕድሜያችንን መፍጀታችን ነው፡፡ የበሬው ምናምን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተለው እንደዋለችው ቀበሮ እኛም ወያኔ ሰው ይሆናል ብለን አገዛዙን እንዲያሻሽል ብዙ ብንጮኽም እስካሁን ምንም አልለወጥነውም፤ ወደፊትም ለመቼውም ቢሆን ከዚህ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮው ልንለውጠው አንችልም፡፡ ይልቁንስ እየሣቀብንና የለመደውን የግመሎቹንና የውሾቹን ተረት እየተረተብን ሲዖላዊውን የናቡከደነፆርንና የፈርዖንን አገዛዝ እንዳነገሠብን ይኖራል፡፡ ማርሽ መለወጥ ያለብን እኛው ነን፡፡ ወያኔ ወሬን በማሳመርና በጥናት ጽሑፎች ጋጋታ ወይም በእርግማንና በተቃውሞ ሠልፎች ብዛት ወይም በጋዜጣዊ መግለጫና ኆልቁ መሣፍርት በሌላቸው ፓርቲዎች ምሥረታ ወይም በጎጥና በዘውግ በሚደራጁ ንቅናቄዎችና ግምባሮች ቱማታ … ከሥልጣኑ ሊወገድና እውነተኛ ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም፡፡ ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ጊዜ እጅግ ቢያልፍም አሁንም ቢሆን ችግሮች እየከፉ እንጂ እየተሻሻሉ ባለመሄዳቸው የምናደርገውን የተናጠል እርምጃ ገታ አድርገን ወይም ከተኛንበት ጥልቅ እንቅልፍ ነቅተን በጋራ አንድ ነገር ማድረግ ይገባናል፡፡ ፈረንጆቹ “Better late than never.” እንደሚሉት እየሞተ ላለ ሕዝብ በማንኛውም ሰዓት የሚደርስለት ረድኤት ትልቅ ፀጋና በረከት ነውና ሀገራችንን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት እንተባበር፡፡ መፍትሔው እሱና እሱ ብቻ ነውና፡፡
መሬት ቅርምት ስለሚባለው የወያኔ አንዱ ፋሽን ትንሽ እንነጋገር፡፡ በመሠረቱ ቀደም ሲል እንዳልኩት ወያኔ በተፈጥሮው ዐይንና ጆሮ ስለሌለው እንጂ በዚህ ጉዳይ ያልተባለ የለም፡፡ ፈረንጁም ሀበሻውም ብዙ ተናግሮበታል፤ ብዙም ጽፎበታል፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ከመሄድ በስተቀር የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ለአሁኑ ሰሞኑን ከወጡ ዜናና ሀተታዎች መካከል ከሁለት ምንጮች ያገኘኋቸውን ሁለት ዜናዎችን ተመርኩዤ ጥቂት ላውራና እፎይታ ላግኝ – የከበደኝ ጭንቅላቴም ቀለል ይልልኛል፡፡ እነዚህ ምንጮቼ ሪፖርተርና ኢትዮሚዲያ ናቸው፤ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉት ነገር አለ፡፡
ሪፖርተር “መንግሥት ‹የውጭ ባለሀብቶች የመሬት ቅርምት ኢትዮጵያን አይመለከትም› አለ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ሰሞኑን ለፓርላማ ተብዬው የደናቁርት እንቅልፋሞች ስብስብ የተናገሩትን የስድስት ወር ዘገባ በመጥቀስ ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም እዬዬው የሚሉት እንግዲያውስ የጂቡቲና የሣዑዲ ዐረቢያ የእርሻ መሬቶች ለኢንቬስተሮች ስለተሸጡ ይሆናል፡፡ በአምስቱም በሮች ከአዲስ አበባ ስንወጣ የሚታዬው ለሕዝቡ ከጥፋት በስተቀር ተጨባጭ ዕድገትና ልማት የማያመጣ የአበባ እርሻና የኢንዱስትሪና የሆቴል መናፈሻ ከየት የመጣ መሬት ነው? ጭቁኑ ገበሬ በመናኛ ሣንቲም የካሣ ክፍያ እትብቱ ከተቀበረበት የአያት ቅድመ አያቶቹ ሥፍራ እየተነቀለ አይደለምን ለሀብታም የተሰጠውና እየተሰጠም ያለው? በየክልሉ ለህንድና ለቻይና ኩባንያዎች በነጻ ሊባል በሚችል እጅግ አነስተኛ ዋጋ የተቸበቸበውና እየተቸበቸበ ያለውስ መሬት ገበሬዎች እየተፈናቀሉ አይደለምን? ታዲያ የሚኒስትሮቹና የምክትል ሚኒስትሮቹ ውሸት ይህን ፀሐይ የሞቀው እውነት በምን አቅሙ ነው ሊሸፍነው የሚችለው?
“መሬት የሚሸጠውና የሚለወጠው በኢሕአዴግ ከርሰ መቃብር ላይ ነው” ሲሉ የነበሩትና የገበሬው መጨቆንና መራብ መጠማት የትግላቸው መነሻ እንደሆነ አዘውትረው ይሰብኩ የነበሩት የሕወሓት ታጋዮች ዛሬ ምን ነካቸውና ተገልብጠው በዚህ የዋህ ባላገር ላይ ሊዘምቱበት ቃጡ? ቤት ያፈራውን በፈቃዱ ወድዶ እየሰጠ ወይም እንደዬሁኔታዎች አስገዳጅነት በወያኔው ጉጅሌ በጉልበት እየተነጠቀ ካባና ቀሚስ ሆኖ እንዳይበርደውና እንዳይርበው ሸፋፍኖ ቤተ መንግሥት እንዲገቡ የረዳቸውን ገበሬ ጨረቃ ላይ ያስቀሩት ለምንድነው? የሚታየው ኢፍትሃዊ የመሬት ክፍፍልና የእራሽ መሬት እየጠበበ መሄድ ያመጣው ችግር አነሰና ያቺ ያለቺው መሬት በምን ምክንያት ነው ለባዕድ እየተሸጠ ምርቱም የሀገሪቱ አንጡራ ሀብትም ለውጪዎች የሚሸጠው? መንግሥት የሚባለው ይሄ የወያኔ የጅቦች መንጋ በምኑ እያሰበ ይሆን እንዲህ ያለ የዓለም መንግሥታትን የሚያስደምም የመንግሥት አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የተከለው? ከግዛቱ አንዳች አንዳች እሚያህለውን መሬት እየገነደሰ ለጎረቤት ሀገራት ማደል፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከጭቁን ገበሬዎች እየቀማ ለውጭ ባለሀብቶች ለዚያውም ተጨማሪ ብድር ሳይቀር እየፈቀደና እየሰጠ ማከፋፈል፣ በነዳጅ ቁፋሮ ሰበብ በሺዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ጦርነት ማወጅና እንደዐይጥ መጨፍጨፍ… ምን የሚሉት የሕዝብ አስተዳደር ሣይንስ ነው? ከየትስ ተማሩት ይባላል?
በሪፖርተር ዜና ላይ እንደተመለከተው የ“ፌዴራል ኢትዮጵያ” መንግሥት (ፐ! አይ ቋንቋ! ‹ፌዴራል› ሲባል ተሰምቶ እነዚህ የማያፍሩ ጉዶች ይህን ክቡር ቃል አምጥተው አለቦታው ደነቀሩት፤ ለነገሩማ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ነጻነት ይሉስ የለም፡፡ ብቻ ይህም ከመጥፎ ኩረጃዎች አንዱ ነው [It is a mockery or parody of the real democracy which is said to be practiced in the so called civilized world.]  የግብርና ሚኒስቴር፣ “የውጭ ባለሀብቶች በግብርና ኢንቬስትመንት ላይ ለመሰማራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው እያለሙ እንጂ፣ መሬት ለመቀራመት ብለው ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም” ሲል ማስታወቁ በእግረ መንገድ ሰውዬው የሃሳብ መንጠፍ ብቻ ሣይሆን የቋንቋ ችግርም እንዳለበት ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከማን ወሰዱ የሚለው ግልጽ ስለሆነ እሱን እንተወውና ከማንም ይሁን ከማን መሬቱን መውሰዳቸው በራሱ መቀራመት አይደለም ወይ? ይህን የተናገረው ሰው እስኪ ደግሞ ያጢነው፡፡ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ከጁፒተርና ከማርስ ወርዶ የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ተንሳፍፎ – የገበሬዎችን መሬት ሳይነካ – ለምድረ ዐረብና ህንድ ተቃረጠ እንበል? የኛ ገበሬዎች ከመሬታቸው መፈናቀላቸውንና በፖሊስና በመከላከያ ኃይል ብዙ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ትስስር ካላቸው የመኖሪያና የእርሻ ቦታቸው እንዲወገዱ መደረጉን በአንደኛው አንጎላችን ይዘን በሌላኛው አንጎላችን ደግሞ የኢትዮጵያን የመሬት ወቅታዊ ሥሪት ስናስብ ከሕዝብ ብዛት የተነሣ ለአንድ ገበሬ የሚሰጠው የእርሻ መሬት ስፋት ስንት ነው ብለን እንጠይቅ፡፡ የአብዛኛው ገበሬ የእርሻ መሬት ከኩርማን ያነሰና እንኳንስ ለሽያጭ ሊተርፍ ራስን ለመቀለብ የማያስችል አነስተኛ ምርት የሚመረትበት ነው፡፡ ታዲያ የውጪዎቹ ባለሀብቶች ከየት የመጣ “ሰፋፊ መሬት” ነው የሚሰጣቸው? በምንም መንገድ ያግኙት ይህ ክስተት “የመሬት ቅርምት” ካልተባለ የትኛው ነው ሊባል የሚችል? ግብርና ሚኒስትሮች – እባካችሁን የቋንቋ ትምህርት ቤት ግቡ! አለበለዚያ “የሚሉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እየተባላችሁ የዝንታለም መዘባበቻ እንደሆናችሁ ትቀራላችሁ፡፡ ከደደቢት በረሃ ይዛችሁት የመጣችሁት ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝን እንጂ የእርሻ መሬትን እንዳልሆነ ልትረዱ ይገባል – ተጋደልቲ አኽዋትና!! የሌላችሁን ነገር ነነገር ደግሞ አትሰጡም ወይም አትሸጡም፡፡ እየቸበቸባችሁት ያላችሁት ገበሬውን በማፈናቀልና ዜጎችን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ስደት በመዳረግ የምታግበሰብሱትን የሕዝብ መሬት ነው፡፡ ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል፤ ወያኔም ቀን ወጥቶለት ከጉድጓድ ወጣና መንግሥትም ሆነና የንጹሓን ዜጎችን መሬትና ሀብት ንብረት በጠራራ ፀሐይ እየዘረፈ፣ ባለመብቶችንም እየገደለ መሬታችንን ለባዕዳን ሲሳይ ያደርጋል፡፡
አቶ ተፈራ ደርበው የተባለ አጋሰስ ሆዳም (ሆዳም አጋሰስ? እኔንም አማርኛው ጠፋኝ ልጄ!) ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “መሬት መቀራመት ኢትዮጵያን ጭራሽ አይመለከታትም”፡፡ ይሄም ሰውዬኣችን የቋንቋ ትምህርት ቤት ይግባና በእግረ መንገድም የሎጂክ ትምህርት በዚያው ያጥና፡፡ በል የተባለውን እንደበቀቀን ቃል በቃል እየደገመ ኅሊና ካለው ከኅሊናው ጋር እየተጋጨ የሰው መሣቂያና መሣለቂያ ከመሆን የሚድንበትን ብልሃት ይፈልግ፡፡ ዕድሜ ለቴክሎጂ ሕዝቡም ሆነ መላው ዓለም በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን አንድ በአንድ ያውቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈሳች በሴከንድ ውስጥ ዋሽንግቶንና ኒዮርክ ላይ ትሸታለችና ወያኔዎች እንደልማድና እንደተፈጥሮ ጠባያቸው ልፉ ብሏቸው እንጂ ማንንም ሊያታልሉ አይችሉም፡፡ ዋሹም አልዋሹም ለቅጣት መጥተዋልና እንደዮዲት ጉዲት፣ እንደግራኝ አህመድና እንደመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የመጡበትን ኃጢኣተኛና ተንኮለኛን የመቅጣት ተልእኮ ሣይጨርሱ ንቅንቅ አይሉም፤ “ማንም ሊያነቃንቃቸው አይቻለውም፣ ዘላለማዊያን ናቸው፤” ማለት ግን አይደለም – የቀን ጉዳይ እንጂ ድቡሽት ላይ ቤቱን የሠራው ወያኔ ይቅርና ስንትና ስንት ለሰማይ ለምድር የከበዱ ታላላቅና ኃያላን መንግሥታት ጊዜያቸው ሲደርስ አይሆኑ ሆነው ተንኮታኩተዋል፡፡ የላይኛውም በሉት የታችኛው እስኪያዝ ድረስ ነው፡፡ (ይህችን ሃሳቤን እንኳን ብዙ ሰው እንደሚቃወመኝ አውቃለሁ – የራሴ ብቻ ናትና እለፉኝ! መተላለፍ ተገቢ ነው፡፡ ካልተላለፍን ደግ አይደለም፡፡) በእግረ መንገድ ግን ወደፍቅርና መተሳሰብ መንገድ እንግባ እያልኩ እንደሆነ አፍ አውጥቼ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤ ቀኑ የጨለመብን ፍቅር ስለጎደለንና አንዳችን ለአንዳችን የማንተዛዘን ድንጋይ ልቦች ስለሆንን ነው – ሁላችንም ባንሆን “ጥቂቶቻችን”፡፡ አቤት ፍርሀቴ! አንዳንድ ደመ ፍሉ ሰው ቱግ እንዳይልብኝ እኮ ተጨንቄ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የመሬት ቅርምቱ የገበሬውን የእርሻና የመኖሪያ ቦታዎች በመቀማትና ከንብረቱም ከኑሮውም ሳይሆን ሜዳ ላይ ከነቤተሰቦቹ በትኖ በማስቀረት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በከተሞችም በተለይም በአዲስ አበባና አካባቢዋ እጅግ ብዙ የሚዘገንን የመሬት ዘረፋ እየተካሄደ ነው፡፡ የአምሳና ዐርባ ዓመት ይዞታ ያለውን ሰው አንድ ወያኔ በጨበጣ ይመጣና ያፈናቅለዋል፡፡ ይህ ወያኔ፣ ከሆነ ቦታ ማዘዣ ሊይዝ ይችላል ወይም በፌዴራል ሊያስገድድም ይችላል፡፡ “ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ” በመሆኑ የፈለገውን ለማድረግ፣ ቀልቡ ያረፈበትን መሬት ከዕድለቢስ ምሥኪን ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለመቀማት ብዙም አይቸገርም፡፡ ለድሃ መጣሁ የሚለው ወያኔ በሰውነቱ ውስጥ በተካሄደበት ኬሚካላዊ ለውጥ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የለዬለት ፀረ-ድሃ ሆነና የማይፈጽመው ግፍና በደል የማናየውም የድሆች ብሶት የለም፡፡ ዱሮ በትግሉ ዘመን በዐይኔ ሂዱብኝ እንዳላለ፣ ዛሬ ወያኔ ስኳር ሲቀምስ ድሃ አልይ አለና ከጥቂቶች ጋር በሂልተንና ሼራተን አሼሼ ገዳሜውን ከአዳዲስ ባልንጀራዎቹ ከነአላሙዲንና አብነት ጋር ማጧጧፉን ቀጠለ፡፡ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት የሚሊዮኖች ሲዖል የጥቂቶች ግን ገነት ሆና ሌላው ቀርቶ ከሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት ደህና ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ዛሬ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ደረጃቸው ወርዶ የለዬላቸው ለማኞች ሆነዋል፡፡ የወያኔ መቶ ብር ምንዛሬ የደርግን አምስት ብርና የኃይለሥላሴን ሃምሳ ሣንቲም (ኧረ እንዲያውም ከዚያም በጣም ያንሳል) በሆነበት ሁኔታ የሦስትና አራት ሺህ የተጣራ ደሞዝ ተከፋዮች ይህ ገቢያቸው ከቤት ኪራይና ከጓያ ሽሮ እንዲሁም ከትራንስፖርት አላለፈም፤ እናም ይህ የወያኔዎች መሠረታዊው ድል በመሆኑ ሊኮሩበትና ሊኮፈሱበት ይገባል፡፡ ጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልቡ የሚወዳቸውና ጠብ እርግፍ የሚልላቸውም ለዚህ ድል ስላበቁት ነው፡፡ አዲስ አበቤ ስለሳቀና ‹እኝ› እያለ ጥርሱን ስላገጠጠ ብቻ እየኖረ ያለ ሕዝብ ከመሰለን ስህተት ነው፤ ብዙዎቻችን እያኗኗርን እንጂ እየኖርን አይደለንም፤ አሸር በአሸር በልቶ እንደከብት መኖርን መኖር ካላችሁትም በዚህ ደረጃ የምንኖር በብዛት አለን፤ የለየላቸው ያጡ የነጡ ደግሞ በሥውር የርሀብ ጦርነት አንጀታቸው እርስ በርሱ እየተፋተገ የመሞቻቸውን ጊዜ የሚጠብቁ በየጎዳናውና በየቤቱ ሞልተዋል፡፡ አንዳንድ ጣዕረሞቶች ደግሞ በተፈጥሯቸው አስቸጋሪ ከመሆናቸው የተነሣ የሟቹን የመሞቻ ቅጽበት ለመተንበይ ያስቸግራሉ፡፡ ለዚህም ነው -ለምሳሌ- ለ23 ዓመታት ያጣጣረን አንድ ሰው በየትኛዋ ደቂቃ እስትንፋሱ ልትወጣ እንደምትችል መገመት የሚያቅተን፤ ነግር ግን ይህ ሰው አልሞተም ብሎ መዋሸት አይቻልም፡፡ ሞቱን ሞቷል፤ ችግሩ ዕድሩ አልለፈፈም፤ ለቀስተኛውም አላወቀለትም፡፡ አይደለም እንዴ ጓዶች?
ወደኢትዮሚዲያ እንለፍና ከሚለው ነገር ድረገጹን ያልገበኘንና ያን ዜና ያላየን እንቋደስ፡፡
“Land for Sale” በሚል ርዕስ ሥር ባስነበበን በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ዜና ብዙ ቁም ነገሮች ተጠቅሰዋል፡፡ በምንጭነት የጠቀሰው አልጀዚራ በ“People and Power” ፕሮግራሙ ለሥርጭት ያበቃውን ሀገራችንን የሚመለከት ዝግጅት ነው፡፡ ከጊዜ ዕጥረት አኳያ ዋና ዋና ነጥቦችን ብቻ መርጬ ባጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
ይህ የዜና ዘገባ የሚነሣው ኢትዮጵያ አስደማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት እያመጣች ያለች ሀገር መሆንዋን በመጥቀስ ነው፡፡ ወደዚያ ከገባን መውጫ የለንምና ዕድገታችን ተከድኖ ይብሰል፤ ወደ አንገብጋቢ የመሬት ሽያጭ ማለፉ ይሻላል፡፡
“… ነገር ግን” ይላል ይህ ዜና – ስለኢትዮጵያ አወንታዊ ነገሮችን ከጠቀሰ በኋላ – “ነገር ግን አሉታዊ ዜናዎችም ከዚህ መልካም [የሚመስል] ወሬ ጋር ተጫፍረው ማለፊያውን ዜና ሊያደበዝዙት ሲሞክሩ መታዘባችን አልቀረም፡፡ 87 ሚሊዮን ከሚሆነው የሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ የሚሆነው የትምህርት ዕድልን ካለማግኘት ጀምሮ እስከ የጤና አገልግሎት ሽፋን በበቂ አለመዳረስና በመሳሰሉት በርካታና የተለያዩ ችግሮች እየተሰቃዬ ነው፤ [የአላሙዲንን ሀብት ለአጣሙዲኖች በምናብ የሚያከፋፍለው] የሀገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ በዓመት ከ1500 ዶላር በታች ነው፡፡ ከ30 ሚሊዮን የሚበልጠው ሕዝብም ሥር በሰደደ ጠኔና ርሀብ እየማቀቀ ነው፡፡(ትንሽ ከፍ ሲል ስለአዲስ አበባ ርሀብ የተናገርኩትን እዚህ ላይ ያስታውሷል)፡፡ ከኢኮኖሚው ዕድገት አንጻር እየታዩ ያሉት በጎ ጅምሮች ተስፋ ሰጪነታቸው እንዳለ ሆኖ በቢዝነስና በህጎች ላይ ማሻሻያ ቢደረግ፣ የመንግሥት አግልግሎት ሰጪ ተቋማት በዘርፉ በሠለጠነና በቂ ዕውቀት በቀሰመ የተማረ የሰው ኃይል እየተመሩ የተቀላጠፈና ከሙስና የጸዳ ዘመናዊ አሠራር ቢከተሉ ሀገሪቱ የበለጠ ዕድገት ልታስመዘግብ በቻለች ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከመቶው እኩሌታውን ያህል የሚሸፍነው የግብርናው መስክ እየተነዳ ያለው ከቁጥጥር በወጣ የመሬት ቅርምት ነው፡፡ ይህን የመሬት ቅርምት የሚያካሂዱት ደግሞ መንግሥት የፈቀደላቸውና ሽያጩን ራሱ መንግሥት የሚፈጽምላቸው የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና የግል ኢንቬስተሮች ናቸው፡፡ የሚገዙበት ዋጋ ደግሞ በሊዝ ጨረታ (ሆኖ እጅግ አነስተኛ ገንዘብ) ነው፤ በዚህ ዓይነት የመሬት ሽያጭ በብዙ ሚሊዮን ጋሻ የሚገመት ለም የእርሻ መሬት ለውጪ ባለሀብቶች ይሸጣል፡፡ [የገበሬው መሬት በዚህ መልክ ተቸብችቦ ሊያልቅ የቀረው ጊዜ አንድ ሐሙስ ብቻ ነው፡፡ ህልምና ትርጉም እንደፈቺው ነው - ደግሞ፡፡]
ይህ የመሬት ሽያጭ በመንግሥት ዐይን እንደ ጥሩ ነገር ይታያል፡፡ በሚገኘው ገቢ የገጠሩን ሕዝብ ለማሻሻል የሚረዱ ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ መሠረታዊ የልማት አውታሮችን ለመዘርጋት፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና አዲስ ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት እንደሚውል የግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይገልጻል፡፡ …
ነገር ግን ኦክስፋም፣ ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅትና የኦክላንድ ኢንስቲትዩትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይህን የመንግሥት የመሬት ሽያጭ ድርጊትና የኩባንያዎቹን የመሬት ቅርምት ለሀገሪቱ አደጋ እንደሚያስከትል እያስጠነቀቁ ናቸው፤ መንግሥት ግን ማንኛቸውንም ሊሰማቸው ፈቃደኛ አይደለም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እንደሚሉት የመንግሥት ድርጊት የዓለም አቀፉን የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ ይጥሳል፡፡ ምክንያታቸውን ሲገልጹ መንግሥት በሚሊዮኖች ሄክታርና ጋሻ የሚገመት ለም መሬት ለገዢዎች ለማዘጋጀት ከየትም አያመጣውም፡፡ ሊያደርግ የሚችለው  በዝቅተኛ የካሣ ክፍያ ከገበሬው እየቀማ መሬት መሸጥና ዜጎቹን በኃይል እያፈናቀለ የትሚናቸውን ማባረር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከራሱ ዜጎች ይልቅ ለውጭ ሀገር ቅድሚያ መስጠቱን ያመለክታል፡፡ በዚህ ኢሰብኣዊ ድርጊት የሚፈናቀሉት በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ሰብኣዊ መብታቸው ይገፈፋል፤ ባህላቸውና የአኗኗር ዘይቤያቸው ለአደጋ ስለሚጋለጥ በሥነ ልቦናዊ ችግር ሊጠቁ ይችላሉ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለርሀብና ለበሽታ ስለሚጋለጡ ሁልጊዜም ዕርዳታ ጠባቂዎች ሆነው ሰው እጅ እያዩ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡
ደሳለኝ ራህመቶ የሚባሉ የሥነ ሕዝብ ዕውቀት ባለቤት እንደሚሉት ተፈናቃይ ገበሬዎች በፍንቀላው ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ የሚደርስባቸው ጉዳት የከፋ ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል ገበሬዎቹ መሬታቸው ይወሰድባቸዋል፤ ዘላኖቹ ኢንቬስተሮች መሬቱን ለእርሻ ወይም እነሱ ለሚፈልጉት ነገር ሲያዘጋጁ ሥፍራውን ስለሚመነጥሩትና ደኑን ስለሚያጠፉት የአካባቢያቸው የተፈትሮ ሀብት ይወድምባቸዋል (ቢመለሱ እንኳን አያገኙትም)፤ የተፈጥሮ ሚዛንም ይዛባል፤ መንግሥት እንደሚለው እነዚህ ኩባንያዎች ለአካባቢው መሠረታዊ ልማት ይጠቅማሉ ነው የሚለው፤ እነዚህ ጥቅሞች ግን በሰዎቹ ቸርነትና በጎ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር የኮንትራት ስምምነቱ ላይ አልተገለጹም፡፡ እነዚህ ኢንቬስተር ተብዬዎች ደግሞ የራሳቸውን ፍላጎት ከማሳካት ውጪ ለአካባቢው ልማትና ለገበሬዎች ደንታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በገዙት እርሻ ላይ እነሱ የሚፈልጉትን የእህል ዓይነት እንጂ የአካባቢው ሕዝብ ወይም ሀገሪቷ የምትፈልገውን ምርት ላይሆን ይችላል፡፡ ገበያቸውን የሚመርጡትም እነሱ ናቸው – ‹ይህን እዚያ ወይም ያንን እዚህ ሽጡ፤ እንዲህ ያለ ሰብልም አምርቱ› ብሎ የሚያስገድዳቸው አንድም የህግ አንቀጽ ወይም የስምምነት ሰነድ የለም፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ምርት አምርተው የትም ሊሸጡት ይችላሉ፡፡ እንዲያውም ለሀገር ውስጥ ገበያ ሣይሆን ለውጪ ገበያ ነው የአብዛኛው ምርታቸው ዒላማ(ታርጌት)፡፡ ለምሳሌ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከገበሬዎች ተነጥቆ የተሰጠው አንድ የሣዑዲ ኩባንያ በመሬቱ ላይ ሩዝ አብቅሎ ምርቱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ነው እሚልከው፤ ሩዝ ደግሞ ከዚያ አካባቢ ሕዝብ የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ የለምና ለከብት ካልሆነ ለራሱ አይመገበውም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ኩባያዎችና ባለቤቶቻቸው በዘርም በሃይማኖትም ላልተወለዱትና ላልተዛመዱት ሕዝብ እንዲጨነቁ አይጠበቅም፡፡ ገበሬው የገዛ መንግሥቱ ያላሰበለት ደግሞ ባዕዳኑ እንዲጨነቁለትና እንዲቆረቆሩለት አይጠበቅም፡፡ (“ኩባያዎች” አልኩ እንዴ? ኩባንያ በሉት እባካችሁ)
መንግሥት ከሚያራምዳቸው ፕሮግራሞቹ አንዱ የመንደር ምሥረታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደደርግ ዘመን የመንደር ምሥረታና የሠፈራ ፕሮግራም ሁሉ ጥናት ያልተደረገበትና ምንም ዝግጅት የሌለው በመሆኑ ከልማቱ ጥፋቱ ይበልጣል፡፡ ከትውልደ ትውልድ ጀምረው የኖሩበትን ቀዬ በአንድ አዳር ልቀቁና ውጡ ሲባሉ ዙሪያው ገደል ይሆንባቸዋል፡፡ መንግሥት ሠራሽ ወደሆነ አዲስ መንደርም ሄደው መልመድም ሆነ ሕይወትን እንደገና “ሀ” ብለው መጀመር ይቸግራቸዋል፡፡ ሰማይ ምድሩ ነው የሚደፋባቸው፡፡
እንደዚህ ያለ አሰቃቂ መንግሥት ወለድ መፈናቀል ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል ጋምቤላ ውስጥ የአኙዋክና የኑዌር ጎሣዎች አባላት የሆኑ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ይገኙበታል፡፡ አቶ ሙት የሚባል አንድ አኙዋክ ተፈናቃይ፣ “የመንግሥታችን ተቃዋሚዎች ‹መሬት ቅርምት› በሚሉት ፈሊጥ አንድም ዜጋ አልተፈናቀለም፤ በማንም ያልተያዘ መሬት ነው ለኢንቬስተር በሊዝ የሸጥነው” የሚሉንን የወያኔ ባለሥልጣናት ለማሳጣት እንዲህ ይላል፤ በጥሞና አድምጡት፡፡
“ኢንቬስተሮቹ እንደመጡ ጓዛችሁን ሸክፉ ተባልን፡፡ እምቢ ብንላቸው ንብረታችንን፣ ከብቶቻችንን፣እህላችንንና ቤቶቻችንን ሁሉንም ድምጥማጡን እንደሚያጠፉት እናውቃለን፤ [መግደልና ማሳደድ ለነሱ ብርቃቸው አይደለም፤ በኛ በአኙዋኮች ላይ ደግሞ የለመዱት ተግባር ነው]፡፡ ማካካሻ ስጡን ብለን ብንጮኸም ሰሚ የለንም፡፡ ምክንያቱም ቦታው የኢንቬስተሮቹ እንጂ የናንተ አይደለም ብሎ መንግሥት ቁርጡን ነግሮናል፡፡ ይህ ቦታ ደግሞ አያት ቅድመ አያቶቻችን የኖሩበትና ለየትውልዶቻቸው ሲተላለፍ የኖረ ነው፡፡ በመንግሥት አቋም በጣም ፈራን፡፡ ተበሳጭተህ መሬቴን ተቀማሁ ብትል እሥር ቤት ትጣላለህ፡፡ ለምን ታሰርኩ ብለህ  ብትጠይቅ ይባስ ብለው ይገድሉሃል፡፡ [ጠያቂ የላቸውም፡፡ ሕግም የላቸውም፡፡] መሬቱን ተቀምተናል፤ ከአሁን በኋላ የኛ አይደለም፡፡ እኛንም በፈለጉ ጊዜ ሊገድሉን የሚችሉ [የውሻን ያህል እንኳን ክብር የሌለን] ነን፡፡”
ኢትዮጵያውያንም ሌሎች ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዓለም ዜጎችም በዚህ ጉዳይ ቢጮሁ ቢጮሁ የወያኔው መንግሥት እንደልማዱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ እንዲያውም ችግሩን አባብሶ ቀጥሎበታል፡፡ በኦክላንድ ኢንስቲትዩት የጥናት ዘገባ መሠረት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ እንኳን የወያኔው መንግሥት ለውጪ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በመጣያ ዋጋ የሸጠው የገበሬዎች መሬት አንድ ላይ ቢደመር የፈረንሣይን ሀገር ያክላል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደግሞ የፈረንሣይን የቆዳ ስፋት ከሁለት ዕጥፍ በላይ የሚሆን የእርሻ መሬት ከዚሁ ከፈረደበት ገበሬ እየተነጠቀ ሊሸጥ እንደሆነ እነዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ስለዚህ መሬቱም እኛ ኢትዮጵያውያንም እንዳወጣን በወያኔ ተቸብችበን እስክናልቅ በጉጉት መጠበቅና የመጨረሻውን ለማየት እንድንበቃ ዕድሜን ከፈጣሪ መለመን ነው የሚኖርብን፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፡፡ አሜን፡፡ (ካህኑ እግዚኦ ሲሉ አሁን ከጎረቤት ቤ/ክርስቲያን ይሰማኛል፤ ቅዳሴ እየጨረሱ ነው ማለት ነው፡፡ እኛም በያለንበት እስኪ እግዚኦ እንበል፡፡ እግዚኦታ መጥፎ አይደለም፡፡ ሙስሊሙም፣ አይሁዱም፣ ክርስቲያኑም፣ ሁሉም እንደየእምነቱ ይጸልይ፤ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ የተላኩት ከጥልሚያኮሱ ዓለም (from the underworld/netherworld) በመሆኑ እነሱን ለማስወገድ እንደግንቦት ሰባት እምነትና ውሳኔ እውነትም በተገኘው ዘዴ ሁሉ – ጸሎትንም ጨምሮ ማለቴ እንደሆነ ይሰመርልኝ – አስተሳሰባዊ ዘርማንዘራቸው ለትውልድ ብክለት ሳይተርፍ ወደመጡበት መመለስ ነው፡፡ ወደዚምባብዌ … ማነው ወደ ደደቢት ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚያስ ሊመለሱብን ይችላሉ፡፡ ማስወገድ ከምድረ ገጽ ነው፡፡ ማስወገድ ደግሞ ሥጋን አይደለም – መጥፎ አስተሳሰብን እንጂ፡፡ መጥፎ አስተሳሰብን ለማስወገድ መታጠቅ ከሚገባን የመሣሪያ ዓይነቶች አንዱና ዋናው ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ እነዚህን ሰዎች ፍቅርን ጨምሮ በሁሉም መሣሪያ እንረባረብባቸውና የሀገራችን የጋራ ባለቤቶች እንሁን፡፡ ለሀገርና ለራስ ኅልውና ሲባል በፍቅርም በሠይፍም መዋጋትን እነቅዱስ ዳዊትና ልጁ ሶሎሞን፣ እነሙሤም በተግባር አሳይተውናል፡፡ አሁንም በድጋሚ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፡፡
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10912/

No comments:

Post a Comment