FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, February 10, 2014

አንድነት ከባድ ተግዳራት ይገጥመዋል፤

ታደለ መኩሪያ

የሀገራችንን የፖለቲካ አካሄድ ለአርባ ዓመታት ተከታትያለሁ። ሀገሪቱን የሚመሩት ሆኑ ተቃዋሚዎች በውል የሕዝቡን ችግር የተረዱት አይመስሉም። የሕዝብን ይውንታ ያላገኙ በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ላይ የወጡትም ቢሆኑ፣ እሽ አትበሉን የንጉሥ ዶሮ ነን ባዮች ናቸው። ሕዝቡም የቅኝ ገዥዎችን እየተከላከለ ነፃነቱን አስከብሮ የኖረ ነው። በዚህም ይኩራራል፣ ግን የራሱን ነፃነት እርሱን ከሆነ ሰው ይጠብቃል። በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ላይ የወጡትም በመሣሪያ ኃይል አንገቱን አስደፍተውት አብሮት የተፈጠረውን ነፃነት ቀምተውት እንደወር ቀለብ ሰጪና ነሺ ሆነው ሲያላግጡ ይታያሉ። በቅርቡም አንድ የወያኔ ባለሥልጣን በገሃድ በመገናኛ ብዙሃን እንደገለጸው የገበሬውን ሕብረተሰብ ተኛ ስንለው ይተኛል፣ ተነስ ስንለው ይነሣል፣ ብሎ በድፍረት ተናግሯል።ይህ ሁኔታ በግላጭ ለዩኒቨርሲቲ መምህሩ፣ ለተማሪው፣ለጀነራሉ ፣ ለተራ ወታደሩ፣ ለባንክ ማኔጀሩ ፣ ለተቃዋሚ የፓለቲካ መሪው ፣ ለአባላቱ አይሰራም ማለቱ ይቻል ይሆን? ግመልን ለመጫን እንዲተኛ ይደረጋል ውሻም ጌታው ላይ መጠላጥሉንና ጭራውን መቁላቱን እንዲያቆም እንዲተኛ ይደረጋል። የወያኔው ባለሥልጣንም የነገሩን ይህንኑ ነበር። ከዚህ ሰው መሆናችንን ካልተቀበለ መንግሥት ፍትህን መጠየት እንዴት ይቻላል? ፍትህ የሰው ተፈጥሮ መገለጫው ነው።ሰው በሰውነቱ ነፃነት የተላበሰ ከሆነ የፍትህ ሕሊናና ሰሜትም ተላብሶ የሚመጣ ፍጥረት ነው። ከዚህ ውጪ ሰውን ማሰብ አይቻልም።
Ethiopian Muslims protest 2014
በታህሣሥ 20፡ 2006 ዓ ም የአንድነት ፓርቲ የሥራ አስካጅ አባላቱን ለመምረጥ የተገኘው ተሰብሳቢ ፍትህ!፣ ፍትህ! እያለ በቁጣ እጆቹን ሲያወናጭፍና በእንባ ሲራጭ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቲቪ (ኢሳት) ተመልክቻለሁ። በቤገምድር ክፍለ ሃገር በዳባት ወረዳ በድቅድቅ ጭለማ የወያኔ ታጣቂዎች ከአርሶ አደሩ ቤት ገብተው አባወራውን ገለው፣በዕንቅልፍ ላይ ያለቸውን ሕፃን ቀኝ እጇን በጥይት ክፉኛ አቁስለዋት ስለነበር የተቆረጠውን እጇን ለታዳሚው አሣየችው፤ እንደመብረቅ ጮህ፣ ቁጣውን ገለጸ፣ እንባውን አዘራ፤ ቤተሰብም ይህቺን ሕፃን ይዙ ፍትህ ፍለጋ ነው፤ በሀገሩቱ ፍትህ እንደሌለ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ለማሳየት ነው፤ ተሰብሳቢውስ ቢሆን ፍትህ ፈላጊ ነው።
በሀገራቸን ፍትህ ቀስ በቀሰ እየጠፋ ከመጣ ዓመታት ተቆጠሩ። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ ንግሥ በዘመድ በጋብቻ በጉቦ ሚዛናዊ ፍርድ ይዛባ እንጂ ፍትህ ከሕዝቡ አዕምሮ አሟጦ አልጠፋም። ስለዚህ ሕግ ተጥሷል ብለው ዜጎች ሲያስቡ እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ችሎት ድረስ ዶሲያቸውን አንግበው ይሄዱ ነበር። ከ1966 ዓ.ም ለውጥ በኋላ ሰዎች ያለ ፍርድ ሲገደሉ ፍትህ ፍቺውን እያጣ መምጣቱን ለመረዳት ሕዝቡ ጊዜ አልወሰደበትም።
በ1967 ዓ ም ነበር፤ከአራቱም ማዕዘናት ሕዝቡ ለገበያ መጥቶ ይገበያያል፤ የደርግ አባል የሆነ የለውጥ ሐዋሪያ ስለአብዮቱ መግለጫ ይሰጣሉና ስብሰብ ብላችሁ አዳምጡ ተባለ፤ ሕዝቡ ተሰበሰበ፤ ስለአብዮቱ ተደሰኮረ፤ የለውጥ ሐዋሪያው መፈክር አሰሙ፤ ኢዲዮ ይውደም፣ አቆርቋዠ ይውደም፤ ኢህአፓ ይውደም፣ አዳሃሪ ይውደም፤ሕዝቡ ተዳከመ። አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ገበያተኛ፣ የእርግምን ጋጋታው ምንድነው በማለት አርጎመጎመ፤ ኦሮሞኛ ተናጋሪው ‘ጃኖሆይ አልጋ ቡሰኒ ትውደሚ ኢረ ካየኒ’ ጃኖሆይን አውርደው ትውደምን በዙፋናቸው ላይ አስቀመጧት ብለው ጠየቁ። ደርግም በተግባር ካለሕግ የበላይነት ማውደሙን ቀጠለ። ብዙ ሳይቆይ በአካባቢው አንድ ወጣት ተማሪ በፓሊስ ተገደለ፤ መምህራንና ተማሪዎች ሥራ አቆሙ፤ ገዳዩ ለፍርድ ይቅረብ አሉ፤ የመምህራኑ መሪ በታጣቂዎች ተገደለ፤ ልክ እንደቤገምድሩ ቤተሰቦች የአስተማሪውን አስክሬን በመኪና ተጭኖ የሁለት ወር ሕፃኑን ባለቤቱ ታቅፋ ጓደኞቱ 400 ኪሎ ሜትር ተጉዘው አስከሬኑን ለወላጆቹ አዲስ አበባ አሰረከቡ፤ ለምርመራ ወደ ምኒሊክ ሆስፒታል ተወሰደ። አስከሬኑን አጅበው የሄዱ መምህራን፣ ጉዳዩን ከአስራ አራቱም ክፍለሃገር የመጡ የመምህራን ተወካዮች በስድስት ኪሎው ጽፈት ቤቱ በሰብሰባ ላይ ነበሩና ስለ መምህሩ ግድያ አስረዱ።
ወደያውኑ በሀገራችን ፋሽሽታዊ ተግባር እየነገሰ መምጣቱን አስመረውበት፣ በጅማው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይቀርባል በማለት ውሳኔ ተሰጥቶት አለፈ። ለመምህሩ ቅብር ተወካዮቹ በሙሉ በቀጨኔ መድኃኒዓለም ተገኙ። ዛሬ እነዚያ የመምህራን መሪዎች በሕይወት የሉም፤ ለፍትህ መስዋዕትነትን እየከፈሉ አለፉ።የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበርም ከጅማው ስብሰባ በኋላ በእግሩ ሊቆም አልቻለም።
በአንዲት ሀገር ሕዝቡ ፍትህ የለም ብሎ ካመነ የሀገር ፍቅሩ ይቀንሳል። ስው አይደለህም ተብሎ በሕገ አራዊት መዳኛትን አይፈቅድም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነት የከፈለውን ዋጋ ከራሱ አልፎ የዓለም ሕዝብ ያውቅለታል። ነገር ግን ስለራሱ አበሮት ስለተፈጠረው ነፃነቱ ያለው ግንዛቤ አናሳ ሆኖ ይታያል። በሕግ አራዊት የሚተደደር ሕዝብ መሆኑ አልተገለጠለትም። ዛሬ ሥልጣን ላይ የወጡት ወያኔዎች ቢሆኑም ፍትህ ጠፋ ብለው ለነፃነታቸው ዱር የገቡ እንደሆነ ይነገር ነበር፣ ሆኖም በቅርቡ ከመሥራች መሪዎች በመነገር ያለው ሌላ ነው። የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ለመሰዋዕትነት የገበረው ለፍትህ ሳይሆን የአማራውን ሕዝበና የኦርቶዶክ ሃይማኖትን ለማጥፋት የድርጅቱ መሥራች አባት አቦ ስባት ነጋ በተዘዋዋሪ ይነግሩናል። ‘የአማራውን አከርካሪው ሰብረናል የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አጥፍተናል በማለት በኢፋ ተናግረዋል። ለግራኝ ሙሐመድም ለዩዲትም አልሆነላቸውም፤ የቤቶ ሞሶሎኒን ግን አሳክተዋል፤ የተከበሩ የፓርላማ ተመራጩ የአዋሺ ባንክ መሥራች አቶ ቡልቻ ደመቅሣን ተከታይ አፍርተዋል፣በኦሮመኛ እንዲህ ይተረታል ‘ማንጉዶን ገልገላ መሪቴ፤ ኢጆሌን ገነማን አላን ባቴ፤ አዛውቱ ማታ የመከሩትን ከጠዋቱ ልጆቹ አደባባይ አወጡት ማለት ነው። የአቶ ቡልቻን ምኒሊክን ማውገዝ ተከትሎ በነፃነት እንድንኖር ያደረጉን ንጉሥ ስም በየፓል ቶኩ ሲብጠረጠር እሰማለን፤ ስለምኒሊክ የተዘፈኑ ዘፈኖችም አዳይደመጡ እየተባለ ነው፤ ከአዋሽ ባንክ ገንዘባችሁን አውጥታችሁ ከወጋገን ባንክ አስቀምጡ የሚል ጨዋ ሰው የለም፤፤ አቶ ቡልቻ ግን የሚሉት ያንን ነው። አቶ ስባት ነጋና ስብስባቸው ወያኔ ሩዋንዳ ውስጥ በሁቱና በቱትሲው መካከል የተፈጠረውን የእርስ በእርስ መጫረስ በኦሮሞና በአማርኛ ተናጋሪው መካከል ሊፈጥሩት ያቀዱት አልተሳካም። የቤቶ ሞሶሎኒ እቅድ ከከሸፈ ሰንበት ብሏል፤ ከዘር፣ ከፓለቲካ ፓርቲ፣ ከሃይማኖት፡ ከዜግነት በፊት ሰው ነኝ፣ ማለት ከተጀመረ ቆይቷል፤
ስለዚህ የወያኔን የሕግ አራዊት አራማጅ ቡድን በሕጋዊነት ሕጋዊ ለማድረግ የሚደረገው ሰላማዊ ትግል የሰውን ረቂቅነትና ታላቅነት የሚጠይቅ ነው፤ የሰውነት ሕልውናውን የተገፈፈን ሕዝብ ክብሩን ለማስመለስ ለሚደረግው ትንንቅ ብቃትና ቆራጥነትን የተላበሰ መሪ ግድ ይላል፤ሆኖም በሥልጣን ላይ ያለውን ስብስብ ከአቅም ማነስ ተነስቶ የሚታየውን ሐቅ ደፍጥጦ ሕጋዊ ከማድረግ በፊት ዘለቄታዊ ጥቅሙ መታየት ይኖርበታል። የአንድነት ፓርቲ ከግንቦቱ 97 ዓ ም ምርጫ ይህንን ግንዛቤ ሳያገኝ አይቀርም። ደግም ደጋግሞ አንድን ነገር መሥራት ውጤት እንደማያመጣ ማወቁ ክብደት እንደሌለው ግልጽ ነው፤ ‘ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ’ የሚለውን የግንቦት 1997ዓ ም አበባል ከአዲሱ የአንድነት ሊቀመበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሰለሰማሁት ነው። ከስብሰባው እንደተረዳሁት ‘የፍትህ’ ጥያቄ ነው። ይህ የስውነት ጥያቄ የተቃዋሚዎች በቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ፍትህ የተቀማው ሕዝብ ጥያቄ ነው። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በ እሥር ይማቅቃሉ፣ እንዲታሰሩ ማን ትዕዛዙን እንደሰጠ አይታወቅም፤ በጠራራ ፀሐይ ሰዎች ይገደላሉ ትዕዛዙን ማን እንደሰጠ አይነገርም፣ አንድ የተቃዋሚ ድርጅት በመንገድ ላይ ወይም በቤቱ ይደበደባል ማን ትዕዛዙን እንደሰጠ ሃላፊነት የሚወስድ የለም፤ የወያኔ ጅንራል በሞባይል ስልኪ በቁባቱ ባት ላይ ተቀምጦ ሠራዊቱን ለሞት ወደ ጦር ሜዳ ይልካል፤ በስልክ ወይም በብጣሽ ወረቀት ትዕዛዝ ፍርድ ይዛባል፤ ዜጋ ሲገደል ሲታሰር ይታያል፤ ትዕዛዙን የሰጠውን አልጠየቅንም፤ የሕግ አራዊቱን ሞተር አቀሳቃሹ ማነው? ተጠያነት በሌለው መንግሥት መመራት ራስንም አስጠያቂ ያደርጋል። ዛሬ ባይሆን የልጅ ልጆቻችን ይጠይቁናል። ያም ሆነ ይህ እንደሃገር ነፃነት ለራሳቸው ነፃነት የቆሙ ኢትዮጵያውያን አሉ። በዕርግጥ በተናጠል የሚከፈለው መሰዋዕትነት ፍጣን ውጤት ባያስገኝም ወደ ነፃነቱ በሚወስደው ጎዳና ላይ ናቸው። ይህ የያንዳንዱ ሃላፊነት ለራሱ መብትና ነፃነት መቆም ሲሆን፤ የፓለቲካ መሪዎችም ተግባር ይህን አሰባስቦ በቆራጥነት መምራት ነው፤ የኢትዮጵያ ዕስልምና ተከታይ ወገኖቻችን የፍትህ ጥያቄ አቅጣጫ ወደ ቀድሞው የሃገር ነፃነት አሁን ደግሞ’ የሰው ነኝ’ ነፃነት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው።
የአንድነት ፓርቲ መሪውንና የሥራ አስካጅ ኮሚቴውን በመረጠበት ዕለት የቀረበለት ሰቆቃ ነበር፤ የትግሉን መራራነት ጠቋሚ ነው። አባላቱም የዛችን ሕፃን የተቆረጠ እጇን ሲያይ ስሜቱን መቆጣጠር ተሳነው ‘እኔም ሰው እኮ ነኝ፣ ሕመሟ ተሰማኝ፣ በማለት ነበር ፍትህ! ፍትህ! በማለት ስሜቱን የገለጸው፤ መሪዎቹም ወደፊት የሚገጥማቸው ተግዳራት እንደቀድሞው ወያኔን በማውገዝ፣ ለኢንባሲዎች ደብዳቤ በመጻፍ ወይም በራቸውን በማኳኳት እንዳልሆነ ፍትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፤ ወደ ሕዝቡ ተጠግቶ ነፃነቱን እንዲያስከብር ማስተባበር መሆኑን አመልካች ነው።ይህም ቢሆን እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት የሚጠይቅ ይሆናል።ፍትህ በሌለበት ሕብረተሰብ ሕግ አራዊት በነገሰበት መራጭም ተመራጭም አይኖርም።
በኢትዮጵያ ፍትህ ይንገሥ!
ታደለ መኩሪያ
tadele@shaw.ca
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10952/

No comments:

Post a Comment