FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Thursday, February 13, 2014

የጤፍ ምርትን ለውጭ ገበያ፣ ይቁም ሊባል የሚገባ!

አሰግድ ኣረጋ (ኮለምበስ – ኦሃዮ)

ሰሞኑን ስለጤፍ ምርታችን የባዕዳኑ ብዙሃን መገናኛ አጀብ እያሉን ነው፤ ለዘመናት የተደበቀው የዘሩ ገመና መጋለጡን እየነገሩን ነው፤ ስለያዘው ንጥረ ነገር፣ ስለጤናማነቱ፣ በምዕራቡ ገበያ ስለመፈለጉ፣ ከሁለም በላይ ስለ ውጭ ምንዛሪ ምንጭነቱ። ምግብነቱ ተትረፍርፎ የኢትዮጵያ ህዝብ ማስቀመጫ – ቦታ ያጣ ይመስል፣ የወንዙ ልጆች ጭምር ፣ ጤፍ-የጤፍ ዘር፣ እንጀራ ፣ ብሰኩት፣ ኬክ ሆኖ ምግብ በዝቶበት ለሚቀናጣው ለውጭ ገበያ እንዲነጉድ ከምዕራባውያኑ ጋር አብረን ከበሮ እየደለቅን ነው፤ አደብ ልንገዛ ይገባል።Ethiopian unique grain Teff
ባለሙያዎቹ ወቅታዊና በቂ መረጃ እሰካላስጨበጡን ድረስ፣ በዚህ ፁሁፍ አቅራቢ ዕምነት፣ ምርታማነቱ ባለህበት እርገጥ የሆነውንና – በደሃው ገበሬ ማሳ ዛሬም ሆነ የዛሬ 100 ዓመት በሄክታር ከዘጠኝ ኩንታል ያልዘለለውን ፣ ተገቢ የምርምርና ጥናት እገዛ በዙሪያዉ ያላንዣበበውን ይህን ብቸኛ የኢትዮጵያ ልጅ – ጤፍ ፣ አሁን ባለበት ደረጃ ለዉጭ ገበያ በውጭ ምንዛሪ ምንጭነት በሰፊው ለማቅረብ የተያዘው እንቅስቃሴ የምርቱንም ሆነ የህብረተስቡን የኑሮ ዕውነታ ያላገናዝበ ፣ከፈረሱ ኮርቻው ዓይነት ነው። በምርቱ ህልውናና በሸማቹ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ያልተፈለገ ጦርነት ክተት የማለት ያህል ነው። በመንግስት በኩል ቆም ተብሎ እነደገና ሊፈተሽ የሚገባ አብይ ብሔራዊ ጉዳይ ነው።
ጤፋችን በመሰረቱ የማንነታችን መግለጫ፣ ረሃብን ተዋጊ – ብሄራዊ ጦራችን ነው፤ ድንበር አስከባሪያችን ነዉ። “የዕለት እንጀራችንን አታሳጣን” እያልን ለፈጣሪ ቢያንስ በቀን አንዴ፣ ከሆነልንም ሶስቴ የምንጸልይለት የጤናችን ምሰሶ ነው፤ ከሚያመጣው ዶላር ይልቅ የሚያስታግሰው የሚሊዮን ረሃብተኛ ሆድ ሚዛን የደፋ ነው፤ በየሶስትና አራት ዓመቱ አንገት አስደፊና ብሄራዊ ውርደት የሆነውን የልመና እጅ ከመዘርጋት የሚያድን ነው። ለእኛ ለዜጎቿ ምርቱ ከቡናና ከወርቃችንም በላይ ነው፤የሱስ ማርኪያ ወይም ሠርግና በዓል እየተጠበቀ ብቅ የሚል ማጌጫ አይደለም፤ ሳይተርፈን ቡናና ወርቅ ለውጭ ገበያ ብንልክ በሕብረተሰባችን ማህበራዊ ህይወት ውስጥ የሚያመጣው ቀውስ የለም፣የሚበጅ እንጂ። ሳይተርፈን የጤፍ ዘርን በጥሬውም ሆነ በእንጀራ ለውጭ ገበያ መስደድ ግን ሀገራዊ ጥቃት ነው። እኛነታችንን ሳያስከብር ከሀገር እንዳይወጣ፣ ለባዕዳን ሲሳያ እንዳይሆን በያለንበት ዘብ ልንቆምለት ያስፈልጋል፤ የመስኩ ባለሙያዎች ከምርምር ጣቢያችው ወደ ህብረተስቡ መድረክ ወጣ ብለው ስለ ጤፍ ልዩ ባህርይ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሊነግሩንና ጥብቅና ሊቆሙ ይገባል፤ የጤፍ ምርት ያለበትን የምርታማነት ደረጃ ሊተነትኑልን ፣ ለውጭ ምንዛሪ የመዋልን ብሄራዊ ጠቀሜታና ጉዳት ግንዛቤ ሊያስጨብጡን ያሻል፤ብሄራዊ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ከመከላከሉ ላይ ኢትዮጵያዊ ሃይላችንን ማሳረፉ ላለውና ለመጪው ትውልድ ባለውለታ ያደርገናል።
በመሰረቱ ፣ የጤፍ ዘርን ህለውና የተፈታተነ የክተት ጥሪ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ በደርግ ዘመነ መንግስት የገበሬው የጤፍ ማሳ ምርታማነታቸው ከፍ ባሉ አዝዕርቶች እንዲተካ የሚያደርግና በመንግስት የተደገፈ “ጥናት” ቀርቦ ለአፈጻጸሙ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክልሎች ሸብ-ረብ ተብሎ ነበር። ጥናቱ ምርታማዎቹ በቆሎ፣ ስነዴና ድንች ምርታማ ያልሆነውን የጤፍ ዘር ቢተኩ፣ የሀገሪቱን ዓመታዊ የምርት እጥርት ከመሸፈን አለፈው ለመጪው አመት የሚሻገር ምርት ለማከመቸት እንደሚቻል ያስረገጠ ነበር። ተግባራዊነቱ ከአንድ ዓመት አልተሻገረም። በይዘቱ ከዛሬው ጥሪ ቢለይም በገበሬው ኑሮና በጤፍ ህልውና ላይ ጥሎት የነበረው አደጋ ተመሳሳይ ተፅእኖ ነበረው። ውሳኔውንም ሆነ አፈጻፀሙን የተቃወሙ ጥቂት ወገኖች ነበሩ፤ መድረኩም ወቅቱም ባለመፍቀዱ አልተደመጡም። ውሳኔው ከማዕከል ወጥቶ ወደ ገጠሩ – ከገበሬው ማሳ አመራ፤ ገበሬው ጤፉን ወደ ጓዳው መልሶ፣ እንደታዘዘው ማሳውን በምርታማዎቹ በቆሎና ድንች አርመሰመሰው። መሰብሰብ ከሚችለው በላይ ማረስ ልምዱም ባህሉም ያልነበረው ገበሬ አቅሙና ጎተራው የሚችለውን ያህል ሰብስቦ የቀረውን ከማሳው ላይ ተወው፤ ወድሞ ቀረ። በጎተራ ያከማቸው ስንዴም በነቀዝ ተጠቃ፤ በቆሎና ድንች የከተሜውን ገበያ ቢያጥለቀልቀውም ዋጋው በመውደቁ ገበሬውን ከኪሳራ ዳረገው፤በአርሲና ባሌ በሰፊው የታረሰው የመንግስት እርሻ ምርትም ለተመሳሳይ አደጋ ተጋለጠ፤ አቅምን ያላገናዘበ ውሳኔ፣ በበቂ ጊዜ፣ ገንዘብ ባለሙያ ያልተደገፈ ምርትና ምርታማነትን የማሳደጉ ዘመቻ አባዜ፣ ለሌላ አስከፊ ችግር ገበሬውንም፣ ሸማቹንም መንግስትንም ጭምር አጋልጦ አለፈ።
ከስህተት ያለመማር ባህል የተፀናወታቸው ገዥዎቻችን በመጪው የዕቅድ አመትም መሰረታዊ ችግሩን ባልፈታና ስሙን ብቻ በቀየረ እቅድ እንዲቀጥል ተቃጥቶ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ጥቂት ቆራጥ የሆኑ የጤፍ ምርት ተመራማሪዎች ድምጸ-አልባ የነበረውን የገበሬውን ድምጽ ከፍ አርገው በማስተጋባታቸውና በቁጥር ከሁለት ያልበለጡ የጊዜው ባለስልጣናትን ግንዛቤ ሊያገኙ በመቻላቸው፣ ከገበሬው ጉያ ተደብቆ የሰነበተው የጤፍ ዘር በግላጭ ወጥቶ ከማሳው ሊመለስ በቃ። ዛሬ ኢትዮጵያናችን እነዚያን የመሰሉ ለገንዘብና ለግል ስልጣን ያላደሩ ተመራማሪዎቿንና የመንግስት ሃላፊዎቿን በባትሪ የምትፈልግበት ወቅት ላይ ነች። አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የዚህ ፁሁፍ አቅራቢ ለማረጋገጥ መረጃ ባይኖረውም፣ በዚያን ወቅት በጤፍ ዘርና ምርታማነት ጥናትና ምርምር ዙሪያ ከተሰለፉት ሳይንቲስቶቻችን መሀከል እነ ዶ/ር ሰይፉ ከተማና ባልደረቦቻቸው ለአብነት የሚጠቀሱ የሀገሪቱ ባለውለታ ናቸው። ዶ/ር ሰይፉ የጤፍ ዘር ለዘመናት አላነዳች የቴክኖሎጂና የመንግስት ድጋፍ የመቆየት ሚስጥርን አበክሮ የሚገልጽ የምርምር ስራ (Tef ፤ Eragrostis tef , 1993) ለተነባቢነት አብቅተዋል፤ በዚያ ጥናታዊ ስራቸው ገበሬዉን ጭምር እማኝ በማድረግ እንደነገሩን፣ የጤፍ ዘር ከማንኛውም ምርት በተሻለ ድርቅንም ሆነ ከባድ ዝናብን የመቋቋም ልዩ ባህርይ የገበሬውን ቀልብ የሳበ ነው።
ጤፍ በምግብነቱ እንዲህ እንደዛሬው የሀብታሙ አልነበረም፤ ደሀው ችግር ሲጋፈጠው እየደበቀ፣ እየቆጠበ የሚበላው ሳር ነበረ። የዘሩን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ደሀውም ሀብታሙም ገበሬ በእጅጉ ከተረዱት በሗላ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበሉት እዚህ ለመድረስ በቅቷል። በተዘራበት ማሳ እንደ ስንዴና በቆሎ በዝናም እጥረትም ሆነ ብዛት ወድሞ አይቀርም፤ ገበሬውን አመድ አፋሽ አያደርግም፤ የጠበቀውን ያህል ባያገኝም ለዘር ያህል አያሳጣውም። በጎተራ ሲከማች እንደተቀሩት ምርቶች በነቀዝ አይደፈርም፣ ጭዱ የእንስሳቱ ተወዳጅ ምግብ፣ የጎጆው ግድግዳ ማገር መመረጊያ ነው። በገቢ ምንጭነቱም አንጀት አራሽ ነው። የጤፍ ዘር የሸማቹም ልዩ ወዳጅ ነው፤ በረከት ያለው እህል ነው፤ ግማሽ ኩንታል ጤፍ ከወፍጮ ቤት ወስዶ ሙሉ ኩንታል ዱቄት ተሸክሞ የሚመለስበት ነው፤ ለዚህም ነው ሸማቹ የዋጋ ውድነቱን አጠብቆ የሚያማርር። በምግብነቱም ቢሆን ተወዳጅና ሁለገብ ነው፤ ችግር ከመጣ አለማባያ፣ አለዚያም በወተት ተምጎ ፣ በሚጥምጣ ተረምዶ ይበላል። ማባያዎቹ ሳይደመሩ የጤፍ ዘር በራሱ አይነታቸውና መጠናቸው የተለያዩ በርካታ ለሰውነታችን ጤና ግንባታ የሚረዱ ንጥረነገሮችን(ፕሮቲን፣ አይረን፣ ካልስየም፤ ፋይበር እና የተለያዩ ቫይታሚኖችን) አዝሎ የሚገኝ ነው። ዜናው ከምዕራቡ ዓለም የወሬ ማሰራጫ ጣቢያ ካልመጣ ጆሯችን አልሰማ ብሎ እንጂ፣ አዲስ አይደለም። የደብረዘይቱ የግብርና ምርምር ሳይንቲስቶቻችን የዛሬ 25 ዓመት አስረግጠው ነግረውን ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ተመራማሪዎች ይህን የጤፍ ዘር ባላቸው ውስን አቅም ምርታማ ለማደረግ ጥረታቸው የመቀጠሉ ተቀዳሚ ምክንያት ለምዕራባውያን የጤፍ ብስኩትና ትኩስ እንጀራ ለመሸጥ አልነበረም፤ አይደለመም። ዋና ግባቸው በሚሊዮን የሚቆጠረው የሀገሪቱ ጤፍ አምራች ገበሬ ለዘመናት ከያዘው አድካሚ አሰራር ተላቆና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆኖ ምርቱን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለበላተኛው እንዲያቀርብ ማስቻል ነው። በሀገር ውስጥ ምርቱን የማስተዋወቅ ስራ ሳይሆን፣ ምርቱ የያዘው ንጥረ-ነገር ምን ያህል ለጤናችን አስፈላጊ እንደሆነ አግባብ በላቸው ተቋማት በኩል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት ነው።
በጥናታዊ ጹሁፋቸው፣ የጤፍ ተመራማሪው ዶ/ር ሰይፉ እንደሚነግሩን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤፍ ምርቱ ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ምርምር የተጀመረው እንደ አውሮጳ አቆጣጠር በ 1950 ዎቹ መጨረሻ ግድም ሲሆን፣ የመጀማሪያው ኢትዮጵያዊው የጤፍ ሳይንቲስት ዶ/ር መላክ-ሃይለ መንገሻ ይባላሉ። እኒህ ሙሁር ስለጤፍ ዘር ባህሪ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ጀምሮ በግብርና ኮሌጆችና የእርሻ ምርምር ጣቢያዎች ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ምርምሩ እንዲቀጥል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል። በመቀጠለም ሌላው ሳይንቲስት ዶ/ር ታረቀ በርሄ የተሰኙ በጤፍ ምርት ምርምር ሂደት ግኝቱ እጅግ አስቸጋሪ የሆነውንና በምርታማነቱ ልዩ ሚና የሚጫወተውን የጤፍ ባህርይ (The Pollination Habit of Tef) ግኝት በተጨባጭ በማሳየት በሙያ አጋሮቻቸው አድናቆትን ያተረፉ የመስኩ ባልደረባ ናቸው። በእነዚህ ግኝቶች ላይ በመንተራሰ ዶ/ር ሰይፉና ባልደረቦቻቸው በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል በጀመሩት የናሙና እርሻ፣ በሄክታር 8 እና 9 ኩንታል ላይ የቆመው የጤፍ ምርት ከ 20 ኩንታል በላይ ለማምረት የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ሊያስመዘግቡ በቅተዋል። ይህ ድንቅና ተስፋ ፈንጣቂ ውጤት፣ ዛሬ ስለደረሰበት ሁኔታ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት የዚህ ፁሁፍ አቅራቢ ምቹ ሁኔታ ባይኖረውም ፣ ከተጨባጩ የሀገሪቱ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው የምርታማንቱ ማነቆ አሁንም ድረስ እነዳልተፈታ ነው፤ በአብዛኛው ገበሬ ማሳ ላይ የጤፍ ምርትና ምርታማነት ባለህበት እርገጥ ላይ ነው። በየክልሉ በደብቅና በገሀድ የረሀብ አለንጋ እየተቀጣ ያለው ህብረተሰብም በእማኝነቱ የሚያወለዳ አይደለም።
በሌላ በኩል – የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት – የጤፍ ምርት ከሀገር ውጭም በአሜሪካ፣በካናዳ፣ በአውሮጳ፣ በአውስትራሊያና በአፍሪካም ጭምር ለማብቀል ጥረቱ ተይዟል፤ በኢትዮጵያ አየርና አፈር የሚበቅለውን የጤፍ ዘር ሊተካ ባይችልም፣ ለጤፍ ምርታችን የሚበጁ ሁለት እገዛዎችን ለማድረግ ዕደሉ የሰፋ ነው። የመጀመሪያው፣ የጤፍን ምርታማነት ለማሳደግ ከበቃ፣ ለግብርናቸው የተጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ በጥንቃቄ አጢኖ ለሀገራችን ጤፍ ምርታማነት በአጋዥነት ለማሰለፍ መቻሉ ነው። ሁለተኛው፣ የሀገሪቱን የምግብ ፍላጎት ሳያሟላ፣ ባልተመጣጠነ ዋጋ ከደሃው ገበሬ ተዘርፎና ከበላተኛው አፍ ተነጠቆ ወደ ውጭ በቀላሉ እየወጣ ያለውን ጤፍ ጊዚያዊ እፎይታ ለማሰጠት አቅሙ መኖሩ ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥቂት ባለጊዜ ባለስልጣናትንና ነጋዴዎችን ኪስ ከመሙላት ባለፈ ብሔራዊ ፋይዳ እነደሌለው በይፋ የሚነገረለት ይህ የሀገሪቱ ጤፍ፣ ለውጭ ገበያ እንዳይውል ጥሪ የመደረጉ አንዱም መልዕክት የሀገር ቤቱን ጤፍ ለሃገር ፤የውጭውን ለውጭ የሚል ነው። በዋና ዋና ያሜሪካ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆቻቸው ከሀገር ቤት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭምር ተጭኖ የሚመጣውን ትኩስ እንጀራና ጥሬ ጤፍ ሸማቹ እንዳይገዛ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፤ በተሳታፊ ነጋዼዎችም ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ግፊት እያደረጉ ነው፤ ምላሹ ግን አጥጋቢ ሆኖ አይታይም። ምዕራባውያኑ ጤፍን እንደ ጣሊያኑ ፒሳ እስከሚለምዱት ድረስ እኛ በውጭው አለም ነዋሪ የሆንን ዜጎቿ የፈረጠመ ክንድ አለን፤ ከደሀው አፍ ተነጥቆ ማዕዳችንን እያጣበበ ያለውን የኢትዮጵያ እንጀራ – የጤፍ ዘር – ለማስቆም ትግሉን መቀላቀል ይጠበቅብናል፤ የይቁም ጥሪውም ቅዱስ ጥሪ በመሆኑ፤ ከጎናቸው ልንቆም ያስፈልጋል።
ጤናማውን ኦርጋኒክ ጤፍ ወደ ባዕድ ሃገር ሰደን በኬሚካል ያበደውንና ለበሽታ መራቢያነት ምቹ የሆነውን የባዕድ እህል ወደ ሀገር ከማስገባት ፣ ወይም የጤፍን ኦርጋኒካዊ ይዘት ለሚያቃውሱ ባዕዳን ነጋዴዎችና ሳይንቲስቶቻቸው አጋልጠን ከመስጠት፤ ልንድን የምንችለው፣ ዜጎቿ በአንድ ሆነን ለምርቱ ደህንነትና ምርታማነት ዘብ ስንቆም ብቻ ነው።ሀገሪቱ ወጣት የጤፍ ሳይንቲስቶች በጥራትና በብዛት እንድታፈራ ፣ የምርምርና ጥናት ዘርፉ ሀገራዊና አለም ዓቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝና፤ በቂ የመዋዕለ ነዋይ ፈሰስ ለዘርፉ እንዲደረግለት የሚደረጉ ተከታታይ ጥረቶች ለጤፍ ምርታችን አይነተኛ ለውጥ መምጣት መሠረት የሚጥሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትሄድ የሚያስቸላት ነው። ይህን ለመሆን ካበቃን፣ ከክረሰቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የገበሬው ችግር ደራሽና አለኝታ ሆኖ እዛሬ ድረስ እስተንፋሱ የቆየው የጤፍ ዘራችን፣ ምርታማነቱ ከፍ ብሎና ከጥቂቶች ማዕድ ወጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ በሚሊዮን ህዘብ ማዕድ በመደበኛም ሆነ በአማራጭ ምግብነት የምናስተናግድበት ይሆናል። ከተጠነከረም፣ ሀገሪቱ ለጤፍ ምርት በሚውል መጠነ-ሰፊ መሬት የታደለች በመሆኗ፤ ዛሬ ከኢትዮጵያ አይውጣ እያልን የምንጮህለት ጤፍ – ያኔ ለውጭ ገበያ ጭምር በመዋል- ቡናና ወርቃችን ተደምረው ከሚያገቡት የውጭ ምንዛሪ በተሻለ ገቢ አስገኚና የሀገሪቱ የልማት ገንቢ ሆኖ እንደሚቀጠል ተስፋችን በእጅጉ የፀና ነው።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10987/

No comments:

Post a Comment