FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Monday, February 10, 2014

ጉራማይሌ ፖለቲካ ክፍል 2 (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

ባለፈው ሳምንት በተቃርኖ የተሞላ ጉራማይሌ ፖለቲካችንን በማስረጃ አስደግፎ ማየቱን ጀምረን፣ ቀሪውን በይደር ማቆየታችን ይታወሳልና እንዲህ እንቀጥላለን…

…የጎንደር ፕሮግራሜን ከጨረስኩ በኋላ ለስድስት ቀናት ያህል በባሕር ዳር ከተማ አሳልፌ ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም ያገጠመኝን ለፖለቲካዊ ፈገግታ የሚሆን ጉራማይሌ ክስተትን በአዲስ መስመር ላካፍላችሁ፡፡Journalist Temasegan Dasaleg
እንደሚታወቀው ጥር 17 እና 18 የአፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዓመታዊ መደበኛ ስበሰባቸውን በባሕር ዳር ከተማ አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹ ሚኒስትሮችም በከተማዋ የተገኙት በዋዜማው (ጥር 16) ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ በየመቶ ሜትሩ ባለው ፍተሻ እና ‹በዚህ ማለፍ አይቻልም› በሚል እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ ወታደሮች ክልከላ የተነሳ ከቦታ ቦታ መዘዋወሩ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም፡፡
በአናቱም ከአዲስ አበባም ሆነ ከጎንደር ወደ ባሕር ዳር የሚገባ ማንኛውም ሰው፣ ተደጋጋሚና ጠበቅ ያለ ትዕግስት አስጨራሽ ፍተሻን ማለፍ ግዴታው ነበር፡፡ በተወሰነ የሰዓታት ልዩነትም መላ ከተማዋንና ዙሪያዋን በሚያጓራ ድምፁ እያናወፀ፣ በአየር እየተሸከረከረ የሚቃኝ የጦር ጄት ተመልክቻለሁ፡፡ በግምትም በየአስር ሜትር ዕርቀት ላይ የፌደራልና የክልሉ ፖሊሶች ለጥበቃ ከመመደባቸውም አልፎ ጣታቸውን ቃታ ላይ አሳርፈው ሲታዩ፣ ከተማዋ ከሰዓታት በፊት ከባዕድ ወራሪ ጦር ነፃ የወጣች እንጂ፣ አፍሪካውያን ባለሥልጣናት የሚሰበሰቡባት በመሆኗ ካልታሰበ አደጋ ለመከላከል የተደረገ ጥበቃ ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል፡፡
በርግጥ ይህ ሁሉ የቅድመ-ጥንቃቄ ሽር-ጉድ ሀገሪቱ አልሸባብን ከመሰለ ልምድና አቅም ያለው የሽብርተኛ ቡድን ጋር ከገባችበት ግጭት አኳያ ብዙም የተጋነነ ላይሆን ይችላል፡፡ የጉዳዩ ግርምቢጥነትም (ጉራማይሌነትም) ይህ አይደለም፤ ከምሽቱ ገጠመኜ ጋር የተያያዘ እንጂ፡፡ ይኸውም ይህ ሁሉ የፀጥታ ጥበቃ የተደረገላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሀኖም እና ሚኒስትር ዴኤታው ብርሃነ ክርስቶስን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት፣ ባለቤትነቱ የታዋቂዋ አርቲስት አምሳለ ምትኬ በሆነው የጭፈራ ቤት በመክተም፤ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነው አሸሼ ገዳሜአቸውን እያቀለጡ ውድቅት ሌሊቱ እስኪጋመስ ድረስ ማሳለፋቸው ነው፡፡
በዚህ ጊዜም በከተማዋ ቅጥር ከባድ ፍርሃት ያነገሰው ያ ሁሉ የጥበቃ ጋጋታ አልነበረም፤ እንዲያ በአይናቸው ብቻ አፈር ከድሜ የሚደባልቁት የደህንነት ሰራተኞችም የሉም፤ ‹ወዴት ነህ? ቁም! ተቀመጥ!› የሚልም የለም፡፡ እየተመለከትኩት ያለሁት ትዕይንት፣ በተንጣለለው ግዙፍ አዳራሽ አርቲስቷ በተስረቅራቂ ድምጿ የጥላሁን ገሰሰን ዜማ ‹‹አንቺ ከቶ ግዴለሽም፣ ስለፍቅር አይገባሽም…››ን ስታቀነቅን፣ ክቡራን ሚኒስትሮችም ጉሮሯቸው እስኪዘጋ፣ ትከሻቸውን እያርገፈገፉ ‹‹አንቺ ከቶ…››ን ተቀብለው የሚያዳምቁበትን ፈንጠዝያ ብቻ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ (ከሚኒስትሮቹ የግል ነፃነት አኳያ) እንደማይመለከተኝ አውቃለሁ፤ በትርፍ ሰዓታቸውም እንዳሻቸው የመሆን መብት እንዳላቸው አምናለሁ፡፡ ግና ጉዳዩን እዚህ ጋ ለማንሳት የተገደድኩበት ገፊ-ምክንያት ያንን ሁሉ የሀገር ሀብት በማፍሰስ በተዋጊ ጄት እገዛ ጭምር ደህንነታቸው ሲጠበቅ ከማዋሉ ጋር ስለሚያያዝ ብቻ ነው፤ እንዲህ ከአፍ እስከገደፉ በታዳሚ በተጨናነቀ ጭፈራ ቤት ዘና ብለው ለማሳለፍ የሚያስችል የተረጋጋ ፀጥታ ካለ፣ ስለምንድር ነው ያ ሁሉ ጥበቃና የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት መገደብ ያስፈለገው? እዚህም እዚያም ተሯሩጠው የዕለት ጉርሳቸውን የሚያሟሉ ለፍቶ አዳሪዎችንስ ሰርተው እንዳይበሉ መከልከሉ ምን የሚሉት አስተዳደራዊ ዘይቤ ነው? (በርግጥ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ እንዳሌለ አውቃለሁ፤ ምክንያቱም ‹‹ነፃ አውጪ››ው ኢህአዴግ፣ ሀገሬን ‹17 ዓመት ታግዬባታለሁና፣ ሃምሳ ዓመት እንዳሻኝ የመፈንጨት መብት አለኝ› የሚልባት መቀለጃው ካደረገ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ እናም እንዲህ አይነቱን የጉራማይሌ ፖለቲካ ገፅታ መመልከቱ ያልተጠበቀ ሊሆን አይችልም)
ባለሐብት ወይስ ሰላይ?
በባህር ዳር ውስጥ ስሙ ተደጋግሞ ወደ ጆሮዬ የደረሰ የጎረቤት ሀገር ሰው፣ ሌላው የጉራማይሌ ፖለቲካው ማሳያ ነው፡፡ ይህ አሽራፍ የተባለ ሱዳናዊ ባለሃብት፣ በከተማዋ መረቡን ከዘረጋ አስር ዓመት እንዳለፈው ይነገራል፤ ‹‹እሰማራባቸዋለሁ›› ብሎ የነበረው የኢንቨስትመንት ዘርፎችም፡- ከመንግስት የገዛው የምግብ ዘይት ፋብሪካውን ጨምሮ ራሱ ባስገነባቸው የስጋ፣ የዶሮ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ፣ የወተት ተዋፆኦ፣ ፍሌበር ወተር እና ከሱዳን የሚመጣ ጋዝ ማሸግን የሚያካትት ነበር፡፡ እንዲሁም በቡሬ-ወለጋ መንገድ አካባቢ የግራናይት እምነበረድ ማምረቻ እከፍታለሁ ብሎ መሬት ወስዷል፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ የሚጠቀስ የጀመረው ሥራ እንደሌለ ሰምቻለሁ፡፡
በግቢው ውስጥ ጥቂት ሰራተኞች ውር ውር ከማለታቸው በቀር በተደጋጋሚ የሚታየው ክስተትም፣ አንድ በየሳምንቱ ሙሉውን ሰው የጫነ አውቶብስ ከካርቱም ባህር ዳር የመመላለሱ ምስጢር ነው፤ አውቶብሱ ምንጊዜም አዳዲስ ሰዎችን ይዞ ይመጣል፣ ለሳምንት ያህል የከረሙትን ደግሞ አሳፍሮ ይመለሳል፤ ይህ ሂደት ሳይቋረጥ ዛሬም ድረስ ሲደጋገም ተስተውሏል፡፡
የሚመጡት እንግዶችም አልፎ አልፎ ጀንበር ስትጠልቅ የምሽት ክለቦችንና በዚያ የሚገኙ እህቶቻችንን ሲያሳድዱ ከመመልከት በቀር፣ ለምን ስራ ወደ ባህር ዳር እንደሚመጡ እንኳንስ የአካባቢው ነዋሪ ቀርቶ፣ የክልሉ አስተዳዳሪዎችም ቢሆኑ ያወቁት አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩን በቅርብ ከተከታተሉ የመረጃ ምንጬ እንደተረዳሁት ከሆነ ደግሞ፣ ሰዎቹ በስለላ ስራ ላይ የተሰማሩ ሳይሆኑ እንደማይቀር ነው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እና ዩክሬን ጭምር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እንዳፈሰሰ የሚነገርለት ባለሐብቱ አሽራፍ፣ ከኢህአዴግ ጋር ከትጥቅ ትግሉ ዘመን የጀመረ ወዳጅነት እንዳለው ቢታወቅም፣ ኩነቱ ጉራማይሌ የሚሆንብን ግን የዜግነት ጉዳይን ስናነሳ ነው፤ ምክንያቱም በውሃ ቀጠነ ሰበብ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን የሚያስጨንቀው ስርዓት፣ ለሱዳናዊው ከበርቴ ወደርየለሽ ትዕግስት ከማሳየቱም በላይ ገበናውን አሳልፎ መስጠቱን መታዘብ ይቻላልና ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከአባይ ውሃ ጋር በተያያዘም ሆነ ‹ወደ ሱዳን ሊካለሉ ነው› የሚባሉ መሬቶችን በተመለከተ የካርቱም መንግስት ወኪል እንደሆነ መረጃ አለን የሚሉ ሰዎችም አጋጥመውኛል፡፡
መቼም በታሪካችን የኢህአዴግን ያህል በብሔራዊ ስሜትና በሀገራዊ ጥቅም ደንታ ቢስ የሆነ ስርዓት ታይቶ አይታወቅም፡፡ ዳሩ ቀድሞውንስ እንዲህ ተዋርዶ ሕዝብን ከሚያሳንስ ስብስብ ምን የተሻለ ነገር መጠበቅ ይገባል?
በብአዴን ማን ይወክላል?
በዘመነ ኢህአዴግ ከታሪክ ተጠያቂነት በፍፁም ሊያመልጡ ከማይችሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ብአዴን እና ኦህዴድ በግንባር ቀደምትነት ይሰለፋሉ፡፡ ሁለቱም ‹እንወክለዋለን› በሚሉት ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ክህደት ለመፈፀማቸው፣ ደርዘን ያለፉ ድርሳናትን ማዘጋጀት እንደሚቻል እናውቃለን፡፡ አልፎ ተርፎም ህወሓትን ከመሰለ የማፍያ ቡድን ጋር ግንባር ፈጥረው ‹‹ወከልነው›› የሚሉትን የማህብረሰብ ክፍል ህልውና ማድቀቃቸው እውነት ነው፡፡ በርግጥ ምንም እንኳ የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ የጣለ ከፋፋይ ፖለቲካን ጨምሮ ሕዝብ እና ትውልድ የሚሉ ነገሮችን ቅርጫት ውስጥ የመጣል አባዜ ቢጠናወተውም፣ ህወሓት ከቅጥረኞቹ ይልቅ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ቁመና እና መሬት የወረደ አጀንዳ ይዞ የተነሳ መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው፡፡
በዚህ ቁጣ እንድናገር ያደረገኝ ሰሞነኛ ምክንያት ከአንድ የብአዴን ከፍተኛ ካድሬ ነውረኛነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ሰው የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አለምነው መኮንን ሲሆን፣ ኢህአዴግን የተቀላቀለው በተወለደበት ሰሜን ወሎ በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ ከመንግስት ለውጥ በኋላም ረዝም ላለ ጊዜ በዛው በሰሜን ወሎ ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር በኢህዴን /ብአዴን/ ተጠሪነት ሰርቷል፤ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን ማግኘቱን ተከትሎም በክልሉ አስተዳደር ስር ባለው በምፃረ ቃል ‹‹SRAR›› ተብሎ በሚጠራው (በእርሻና መልሶ ማቋቋም ላይ በሚያተኩር) ተቋም በአንድ ክፍል ኃላፊነት አገልግሏል፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ ደግሞ የክልሉ የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ እንደነበር ይታወሳል፤ ቀጥሎም የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሰርቷል፤ ከ2004 ዓ.ም
መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ቢሮ ኃላፊ ነው (በነገራችን ላይ በአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሶስት ናቸው፤ ከአለምነው በተጨማሪ ብናልፍ አንዱአለም እና ዶ/ር አምባቸው የተባሉ ተሿሚዎችም አሉ) የሆነው ሆኖ ይህ ሰው ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር በተዘጋጀ አንድ ስብሰባ ላይ የተናገረውን አስነዋሪ ነገር፣ ረዥም ዕድሜ ለኢሳት ይሁንና ጭው ባለ ድንጋጤ ተውጬ አድምጬዋለሁ፤ ግና ተሳዳቢው የክልሉ አስተዳዳሪ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ የንግግሩ ይዘት ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ይጠቃለላል፡-
‹‹….የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው፣ ከሌላው ጋር መኖርን መልመድ አለበት፡፡ …የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክህተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ፣ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደድ ምክንያት ሆኖታል። ….በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው። ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም፡፡ …ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት። ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም። …ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው። ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው። ያንን ምግብ እየተመገበ ያቅራራል።››
በእውነቱ ይህንን የተናገረው ፋሽስቱ ዱቼ ሞሶሎኒ አሊያም ሶማሊያዊው መሀመድ ዜያድባሬ ቢሆን ኖሮ፣ ቅኝ-ግዛት ያማለለው የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ አድርጎ ማለፍ ይቻል ነበር፤ ግን የዚህ ልብ ሰባሪ ቃላት ባለቤት የክልሉ አስተዳደሪ አለምነው መኮንን ነው፡፡ ዳሩ እርሱስ ቢሆን ማንን እየሰማ አደገና ነው! ምክንያቱም የቀደሙት የብአዴን ሰዎች የወከሉትን ዘውግ ሲረግሙና ሲያንቋሽሹ መታዘባችን የትላንት ክስተት ነው፡፡ የታምራት ላይኔን ‹ሽርጣም ሲልህ የኖረውን ይሄን ነፍጠኛ አሁን ጊዜው ያንተ ነውና በለው› የሚለውን ሐረር ላይ የተሰማ እልቅቲ ነጋሪ አዋጅ ጨምሮ፤ የተፈራ ዋልዋ ‹አማራው በባዶ እግሩ እየሄደ፣ ስንዴ በሩ ላይ አስጥቶ በባዶ ሆዱ የሚፉልል ትምክህተኛ ነው› እስከሚለው ድረስ ያሉ በአደባባይ የተሰሙ ስድቦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ምሳሌ ለማድረግ፣ እዚህ ሳምንት ድረስ በሬዲዮ ፋና እየተተረከ ያለ አንድ የጥላቻና ዘረኝነት አቀንቃኝ የሆነ መፅሀፍን ልጠቀስ (በነገራችን ላይ እንዲህ አይነቱን ለእርስ በእርስ ግጭት መነሾ የሚሆን፣ በክፋት፣ በተንኮል፣ በክበረ-ነክ ጭብጥ የተሞላን መፅሀፍ ርዕስ እዚህ ጋ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንምና አልፈዋለሁ)፡፡ ይህንን መፅሀፍ ደረሲው ዳንኤል ግዛው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያዘጋጀው ሲሆን፣ ወደ አማርኛ የመለሰው የብአዴን ታጋይና የበረከት ስምኦን ባለቤት ወንድም የሆነው መዝሙር ፈንቴ ነው፡፡
በርግጥ በምስጋና ገፁ ላይ እንደተጠቀሰው፣ እንዲተረጉመው ያዘዘውና መፀሀፉን የሰጠው ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ነፃነትና ክብር በዱር-በገደል ታግያለሁ የሚለን ራሱ በረከት ስሞኦን ነው፤ ውለታውንም እንዲህ ሲል ገልፆለታል፡-
‹‹…የምተረጉማቸውን እያንዳንዳቸውን ገፆች ከስር ከስር እየተከታተለ ያነባቸውና ያበረታታኝ ነበር፡፡ ያስጀመረኝ እሱ፣ ያስጨረሰኝም እሱ ነበርና ለአቶ በረከት ስምኦን ያለኝ ምስጋና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡››
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ‹‹አስተማሪ፣ አስገራሚና መሳጭ›› ሲል በፃፈው የጀርባ ገፅ አስተያየት፤ ይህንን እንቶ ፈንቶ እና አንድ ብሔርን ለይቶ የሚያጠቃ ውጉዝ ድርሳን ከፍቅር እስከ መቃብር ጋር በአቻነት አስከማስመሰል ታብዮአል፡፡ ህላዊ ዮሴፍም ረቂቁን በማንበብና በማረም ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳደረገ ተርጓሚው ተናግሯል፤ በአናቱም መዝሙር ፈንቴ መፅሀፉን ከመተርጎሙ በፊት በ‹‹ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ›› ፋብሪካ ውጪው ተሸፍኖለት (የማሳተሚያ ዋጋውንም የቻለው ሼክ መሀመድ አላሙዲ ነው) አደረኩት በሚለው ጉዞ፣ አማራ ረግጦ፣ ቀጥቅጦ፣ ከሰው በታች ዝቅ አድርጎ፣ መሬታቸውን በመንጠቅ አሽከር አድረጎ… እንደገዛቸው የተተረከላቸው የማንጃ እና ማኛ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሚገኙበት ደቡብ ኢትዮጵያ ሄዶ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረጉን ከነገረን አኳያ (የእንግሊዘኛውን ቅጂ ማግኘት አልቻልኩም) መፀሀፉ ቃል በቃል የተተረጎመ ነው ብሎ መቀበሉ ይቸግራል፡፡ ራሱም ቢሆን የፃሀፊው ተደራሲያኖች አሜሪካውያን መሆናቸውን ጠቅሶ ‹‹አቀራረቡን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ›› ማለቱን ስናስተውል ከተርጓሚነትም ወሰን ተሻግሮ ተጉዟል ብለን እንድናምን ከመገፋታችንም በላይ፣ እነበረከት ስምኦን በአማራው ላይ ያላቸውን ያደረ ጥላቻ ለማንፀባረቅ የተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል ብለን ለመጠርጠር እንገደዳለን፡፡
እንግዲህ ብአዴን ማለት፣ ከጉምቱ መሪዎቹ ጀምሮ የክልሉን ነዋሪ ‹‹ቀጣይ ነፃ አውጪያችሁ ነኝ›› የሚለውን ነውረኛውን አለምነው መኮንን ጨምሮ፣ ይህን መሰል በተዋረደ ስብዕና የሚበየኑ ምስኪን ፍጥረቶች የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ታዲያ፤ ለዚህ ሁሉ ሰቅጣጭ ሁኔታ፣ የክልሉ ነዋሪ የሆነው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዝምታ ምን ድረስ ይሆን? የሚለው ይመስለኛል፡፡
መልክዓ-ሌንጮ
ሌላኛው ሰሞነኛ ጉራማይሌ የፖለቲካችን ገፅ አንጋፋውን የኦሮሞ ልሂቅ ሌንጮ ለታን የተመለከተው ርዕሰ-ጉዳይ ነው፡፡ ኦነግን በመመስረትም ሆነ ፖለቲካዊ ቁመና ይዞ ህልው እንዲሆን ከዮሀንስ ለታ በላይ ማንም የለፋ እንደሌለ ይነገራል፤ ዮሀንስ ከጓዶቹ ጋር ተባብሮ ድርጅቱን ሲመሰርት ካነገበው አጀንዳ አኳያ ያለውን ተዛምዶ ገልፆ ባይነግረንም፣ ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት ይታወቅበት የነበረውን መጠሪያ ስሙን ‹ሌንጮ› በሚል ቀይሮታል፡፡
ኦነግ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የሻዕቢያ እና የህወሓትን ያህል ባይሆንም ያለፈውን ስርዓት ለመቀየር የጠመንጃ ትግል አድርጓል፡፡ ከዚህም አኳያ ይመስለኛል የመንግስቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ግብዓተ-መሬት መፈፀሙ የቀናት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ በታመነበት ወቅት በሀገረ እንግሊዝ፣ ሰሞኑን ‹ባድመን ለኤርትራ ስጡ› እያለ በሚወተውተን ኸርማን ኮህን አርቃቂነት በተዘጋጀው የለንደኑ ኮንፍረንስ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር የተቃውሞውን ፖለቲካ ወክሎ እንዲገኝ የተደረገው፡፡ ኋላም የታመነው ደርሶ አገዛዙ ሲወድቅ ኦነግም የሽግግር መንግስቱ መስራች አባል ሆኖ የመተዳደሪያ ቻርተሩን ዋነኛ አዕምዶች (የመሬት የመንግስት ባለቤትነት፣ የመገንጠል መብት እና ቋንቋ ተኮሩን ፌደራሊዝም) ከማርቀቅ ባለፈ እስከ 1984 ዓ.ም የመጨረሻ ወራት ድረስ የሥልጣን ተቋዳሽ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ባደረሰበት ጫናና ግፊት ሥልጣኑን ለቆ ተመልሶ ወደ በረሃ መግባቱ አይዘነጋም፡፡
ግና! ይህችን ለብዙ አስርታት በታጋዮቹ ስትማተር የነበረችውን የኦነግ የመኸር አንዲት ዓመትን ተከትሎ፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ መውረድ የጀመረው የመከራና የዕልቂት መዓት ዛሬም ድረስ አላባራም፡፡ እስከዚህች ቀንም እልፍ አእላፍ ንፁሃኖች በኦሮሞነታቸው ብቻ አስከፊውን የቃሊቲ ማጎሪያ ጨምሮ በተለያዩ ገሀነም-መሰል እስር ቤቶች የምድር ፍዳቸውን እየተቀበሉ ነው፡፡ በደርግ ዘመን የኤርትራ ነዋሪዎችን ‹‹ሻዕቢያ››! በማለት በአደባባይ ገድሎ መሄዱ ቀላል የነበረውን ያህል፣ ኢህአዴግም ሃያ ሁለቱን ዓመታት ሙሉ በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ላይ ተመሳሳዩን ታሪክ ደግሞታል፡፡ የነገይቱን ኢትዮጵያ ህልውና በሚያጠይቅ ሁኔታም በግዙፉ ቃሊቲ ‹የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው› እስኪባል ድረስ ያለ አሳማኝ ክስ እያነቀ ግቢውን እንዲያጥለቀልቁት አድርጓል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ሰበብ የእነሌንጮ ለታ ድርጅት መሆኑ አይካድም፡፡
ኦነግ ከ1980ዎቹ መጨረሻ ወዲህ ለስርዓቱ አስጊ እንዳልነበር እና ይዞታውን ከባሌ ወደ አስመራ እና ሚኒሶታ ማዘዋወሩን፣ በስሙ ለተፈፀመው ዕልቂት ቀማሪና አዛዡ ህወሓትም ሆነ አስፈፃሚው ኦህዴድ ጠንቅቀው የሚያውቁት ቢሆንም፤ ‹‹በስመ-ኦነግ›› ከሚፈነዱና ከሚከሽፉ ፈንጂዎች ጋር እያያዙ የክልሉን ተወላጆች የጥቃት ኢላማ ማድረጉ መደበኛ መንግስታዊ ስራ ከሆነ ሁለት አስርታት ተቆጥረዋል፡፡ የዚህ መነሾም የህወሓት ኦሮምኛ ተናጋሪ ክንፍ ከሆነው ኦህዴድ ይልቅ፣ በኃይል የተገፋው ኦነግ በብዙሀኑ ልብ ማደሩ ያነበረው ፍርሃት አንዱ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ኦህኮ እና ኦፌዴን (ባለፈው ዓመት ‹‹ኦፌኮ›› በሚል ስያሜ መዋህዳቸው ይታወሳል) ያላቸውን ቅቡልነት መጨፍለቅን ያሰላ ይመስለኛል፡፡
በዚህ የተቀነባበረ ጥቃትም ብዙዎች ለህልፈት፣ እልፍ አእላፍቶች ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፤ ቤተሰብ ተበትኗል፤ ህፃናት ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀርተዋል፡፡ እርግጥ ይሄ ጉራማይሌ አይደለም፤ አያሌ ማስረጃ ሊቀርብበት የሚችል ተጨባጭ እውነታ እንጂ፡፡ በአናቱም ይብዛም ይነስ የቀድሞ የኦነግ መስራችና የአመራር አባሉ ሌንጮ ለታ፣ ለዚህ ሁሉ ስቃይና መከራ የድርሻውን ያህል የታሪክ ተወቃሽ (ተጠያቂ) መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡
የሆነው ሆኖ በሌንጮ ኦነግ ስም ለተገደሉት ገዳዮቻቸው ለፍረድ ሳይቀርቡ፣ የታሰሩት ሳይፈቱ፣ የተሰደዱት ሳይመለሱ፣ የፈረሱ ጎጆዎች ሳይቀለሱ፣ ሌላው ቀርቶ ከኢትዮጵያም አልፎ ከኬኒያ ‹ኦነግ› እያሉ አፍነው በመውሰድ ለእስር መዳረጉ (በቅርቡ በወህኒ ቤት ሕይወቱ ያለፈውን ኢንጂነር ተስፋዬ ጨመዳን እናስታውሳለን) ዛሬም ቀጥሎ እያለ ኦቦ ሌንጮ ለታ ‹‹የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር›› የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት መስርቶ፣ ለሚቀጥለው ምርጫ እያሟሟቀ ከመሆኑም በላይ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ታሪክ እንደሚሰራ የተናገረውን ማድመጣችንን ነው ለጉራማይሌ ፖለቲካ ማሳያ ያደረኩት (ሌንጮ ኦዴግን ከመሰረተ ጀምሮ ላለፉት በርካታ ወራት ‹‹ገብተን እንታገላለን›› ማለቱን ስንሰማ ከርመናል) በተያያዘም ሰውየው የኖርዌይ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ መሆኑን ስንጨምር፣ በአንድ ወቅት ራሱም ‹‹እዚህ ኖርዌይ ቁጭ ብዬ ምን እሰራለሁ?›› እንዳለው የአማካሪነቱን ከፍተኛ ደሞዝ ጭምር ትቶ ለመምጣት መወሰኑ፣ ቀጣይ ሚናው ላይ ያለውን የመተማመን ልክ ማየት እንችላለን፡፡ ርግጥ ሌንጮ ከ40 ዓመታት በፊትም የቅርብ ዘመዱ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለታሪክ ትምህርት ወደ ጀርመን ለመሄድ አዲስ አበባ ላይ በተገናኙበት ጊዜ ‹አንተ ታሪክ ተማር፤ እኛ ደግሞ ታሪክ ሰርተን እንጠብቅሀለን› ማለቱ አይዘነጋም፡፡ ዛሬም ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላቶች ስለታሪክ መጨነቁን ያመላክታሉ፡፡ ይሁንና ሌንጮ ‹ታሪክ መስራት› የሚለው የእነአባዱላ ገመዳን አይነት ወዶ-ገብት ከሆነ ሀፍረቱ ለሁላችንም መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኦሮሚያን ለመደለል ሌንጮን በዝውውር የማምጣቱ ሥራ የተጀመረው በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን ነው፤ የዊክሊክስ ዘገባም እንደጠቆመው፣ መለስ ዜናው ‹‹ሌንጮ ማድረግ ያለበት እኔን ለማግኘት መሞከር ብቻ ነው፤ ይህን ደግሞ እንዴት ማድረግ እንዳለበት ያውቃል›› ማለቱን አስነብቦናል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ባዘጋጀው፣ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕገ-መንግስታዊነት ጉዳይ ላይ በተካሄደ ኮንፈረንስ፣ የቀረበውን የሌንጮ ለታን ጥናታዊ ፁሁፍ መከራከሪያዎችን በማብራራት ተጠምዶ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ እንደነበረ ስናስታውስ፣ በሌንጮ የመምጣት ድርድር ውሳኔ ውስጥ የፕ/ሩን (የመንግስትን) የሰነበተ ሚና እንድንገምት እንገደዳለን፡፡ እርሱም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊንፊኔ ላይ የታየው በ2004 ዓ.ም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ደግሞ የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ኖርዌይ እጅ እንዳለበት ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር መጀመሪያ ሳምንት ሌንጮና አባዱላ ገመዳ አሜሪካን ሀገር በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፈው የነበረ መሆኑም የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡
ኢህአዴግ ስጋት ላይ ከጣሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ግለስብን ገንጥሎ ማማለልን ተክኖበታል፤ ከሶስት ዓመት በፊት መለክት ተንፍቶለት ወዶ የገባው አባቢያ አባጆቢር (ከኦነግ መስራቾቹ አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ለእንግሊዘኛው ‹‹ዘ-ሪፖርተር›› ጋዜጣ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ፣ የድርጅቱ የመጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ስለመገንጠል የሚያወራውን አንቀፅ በወቅቱ ተቃውሜ ነበር ማለቱ ይታወሳል) ዛሬ ድምፁ አይሰማም፡፡ ከኦብነግ ጋርም ተደረሰ በተባለ ስምምነት የመጡትን ግለሰቦች፣ ድርጅታቸው አሁንም አፈመዝ ካለመድፋቱ አኳያ ስናየው ጨዋታው ዕቃቃ እንደነበር ይገባናል፡፡ በዚህ ሰሞን ደግሞ ዶ/ር መራራ ጉዲና ከፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጋር ሊወያይ ወደ ጀርመን አምርቷል፤ ሌንጮ ለታም አዳዲስ አባላትን ሊመለምል እዛው ጀርመን ይገኛል (ሁለቱ ጉምቱ የኦሮሞ ልሂቃኖች ተገናኝተው ይሆን?) በርግጥ ሌንጮ የጀርመን ቆይታውን ሲጨርስ፣ በሆላንድ ያቀደውን ተመሳሳይ መረሃ ግብር አከናውኖ በይፋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ለጉዳዩ ከሚቀርቡ የመረጃ ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡
ይሁንና እዚህ ጋ የሚነሳው ጥያቄ ሌንጮ ወደ ሀገሩ ለምን መጣ? የሚል አይደለም፤ እነበቀለ ገርባን የመሳሰሉ ፍፁም ሰላማዊ እና እጃቸው በንፁሀን ደም ያልጨቀየ ፖለቲከኞችን መታገስ ያልቻለ ስርዓት፣ ለሌንጮ የሚሆን ይቅር ባይነትን ከወዴት አገኘ? የሚል ነው፤ ሁለት አርፍተ ነገር የተናገረ ሁሉ ተለቃቅሞ እየታሰረ ሌንጮ ምን ተማምኖ መጣ? በኦሮሚያ ላይ የነገሡት እነአፄ አባዱላና ኩማ ደመቅሳስ ቢሆኑ ከሌንጮ አዲሱ ድርጅት ተነፃፅሮ የሚነሳባቸውን የቅቡልነት መገዳደር ለመጋፈጥ እንዴት ፍቃደኛ ሆኑ? ምናልባት መተካካት የሚባለው ይህ ይሆን እንዴ? ወይስ መረራ ጉዲና ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ በቁመቱ ልክ ሥልጣን ይገባዋል!›› እንዲል፣ ሌንጮ ለታም በራሱ ቁመት የተቀነበበ ሥልጣን ቃል ተገብቶለት ይሆን? …የእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ ዛሬም በሙት መንፈስና በታመመ ሰው እንድትመራ በተፈረደባት ኦሮሚያ ላይ በቀጣይ ከሚኖረው ፖለቲካዊ አሰላለፍ ጋር መጋመዱ አይቀሬ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚህ ባለፈ ‹‹ጀግናው›› ኢህአዴግ የሌንጮ ድርጅትን ኦፌኮን ወይም አንድነትን እንደመሳሰሉ ፓርቲዎች ነፃ ተቃዋሚ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ይፈቅድለታል ብሎ ማሰቡ እጅግ በጣም የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ኦቦ ሌንጮ ከሳምንታት በፊት ለጀርመን ድምፅ ራዲዮ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ላይ፣ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ ስለመወሰኑ ሲጠየቅ ‹‹ፖለቲካ በምርጫ በመሳተፍ ብቻ አይወሰንም፤ ሕዝቡን ማስተማርና ማንቃቱም አንዱ መንገድ ነው›› የሚል መንፈስ የያዘ መልስ ሰጥቷል፡፡ የሆነው ሆኖ ሌንጮ ለምርጫ ቅስቀሳ አሊያም ለንቃተ ህሊና ስብከት ፊቱን ወደ ኦሮሚያ ከማዞሩ አስቀድሞ የሚከተለው ጥያቄ ተጋፋጭ ተግዳሮት እንደሚሆንበት ይታሰባል፡- በሽግግር መንግስቱ ወቅት ሥልጣን ላይ የነበርክበትን ጊዜ ተከትሎ አንተን እና ኦነግን አምነው ከቤታቸው የወጡ ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ አባቶቻችንን የት ጥለሀቸው መጣህ? ሰማዕታቶቻችንንስ በማን ስም እንዘክራቸው? … Akka dhufaa jirtu barree carraa garii (sihaaqunamu)
http://ecadforum.com/Amharic/archives/10943/

No comments:

Post a Comment