የኢትዮጵያው አዋጅ ትርጓሜና ክፍተቶቹ
መንግስታት በተለያየ መልኩ ትርጉመው ያቀረቡትን ሽብርተኝነት ለመዋጋት በሚል ህግ ያወጣሉ፡፡ በእርግጥ በአዲስ መልክ በሽብር ላይ የታወጀው ዘመቻ በአሜሪካ ግፊት የመጣ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 አሜሪካ ከደረሰባት የሽብር ጥቃት በኋላ “war on terror” እንዲሁም “counter terrorism” የተሰኙ ዘመቻዎችን ነድፋ ተንቀሳቅሳለች፡፡ አሜሪካ ወዳጅም ሆነ የቀዩ ባላንጣዎቿን ሳይቀር ደልላም ሆነ ተማጽና የጀመረችው ይህ “ጸረ ሽብር ዘመቻ” መንግስታት በየ አገራቸው የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁ አፋኝ “የጸረ ሽብር” ዘመቻ እንዲያወጡ እድል ሰጣቸው፡፡ አሜሪካ የሰብአዊ መብት ይጥሳሉ እያለች ስትወቅሳቸው የነበሩ ስርዓቶች ሳይቀሩ የተደላደለ የዴሞክራሲያዊ መሰረት ባልተጣለበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን የሚደፈጥጡ አዋጆች አጽድቀው ሲተገብሩ ከሀያሏ አገር የገጠማቸው ወቀሳና ግፊት ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተቃራኒው አልቃይዳንና ቅርንጫፎቹ አሊያም ተያያዥ አሸባሪና አክራሪ የምትላቸውን ሁሉ እንዲያድኑ ወታደራዊ ድጋፍን አጋብሰዋል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ከኒዮርኩ ጥቃት በኋላ አጋጣሚውን ከተጠቀሙት መንግስታት መካከል አንዱ ነው፡፡
አሜሪካ መራሹ ከሆነው በተጨማሪ በተለይም የምዕራባዊያን አገራት የደረሰባቸውን አደጋም አስከትለው ህጎችን አውጥተው ተግብረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ጸረ ሽብር ህጎች መንግስታት ራሳቸው ያጸደቋቸውን ህጎች ሳይቀር ጥሰው ሽብርተኝነት ያሉንት ወንጀል እንከላከላለን የሚልባቸው ህግጋቶች ናቸው፡፡ በተለይ ዴሞክራሲ ባልተጠናከረባቸው አገራት እነዚህ ህጎች አምባገነኖች በአገራቸው ህዝብ ላይ ያሹትን እንዲፈጽሙ እና ህጉን ተገን አድርገው ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ምክንያት እየሆነላቸው ይገኛል፡፡
የአዋጁ አውድ
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሚገኙት የተለያዩ የሽብር ትርጉሞች የሚተረጎሙት በዝርዝር ተግባራት (ግድያ፣ ጠለፍ፣ እገታ፣ በመሳሰሉት ድርጊቶችና) እና ከተፈጸሙት ድርጊቶች በስተጀርባ አሉ የሚባሉት (አብዛኛዎቹ መንግስታት ራሳቸው ከጥቅማቸው አንጻር የሚተረጉሟቸው ናቸው) በዓላማና ፍላጎትን በማጣመር ነው፡ ፡ የኢትዮጵያ የጸረ ሽብር አዋጅ ትርጓሜም ይህንኑ መንገድ የተከተለ ነው፡፡ አዋጅ 652/2001 በድርጊት በኩል ሽብርተኝነትን ሲተረጉም፡-
- ሰውን የገደለ ወይንም በአካሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ
- የህብረተሰቡን ወይንም የህብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይንም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ እንደሆነ
- እገታ ወይንም ጠለፋ የፈጸመ እንደሆነ
- በንብረት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ
- በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይንም የባህል ቅርስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ
- ማንኛውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ ወይንም ያበላሸ እንደሆነ ወይንም
- ከላይ የተጠቀሱትን ለመፈጸም የዛተ እንደሆነ በሽብርተኝነት እንደሚወነጀል ይገልጻል፡፡ ለጥፋቱም ከ15 አመት ጀምሮ የእድሜ ልክ ብሎም የሞት ቅጣት እንደሚያስወስንበት አስቀምጧል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት መካከል አብዛኛዎቹ ዝርዝሮች ህጉ ተወሰደባቸው ከሚባሉት የዴሞክራሲያዊ አገራት ጸረ ሽብር ህግ ያልተካተቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል “ማንኛውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ ወይንም ያበላሸ” የሚለው በሰላማዊ እምብይተኝነት ጊዜ የሚፈጸምና በሌሎች አገራት ሽብርተኝነት ቀርቶ ተራ ወንጀል ስምም አያስከስስም፡፡
ዝርዝሮቹ በቂ ባለመሆናቸው ትርጉሙን ለማጠናከር ዓላማና ፍላጎት የግድ መጨመር ነበረበት፡፡ በመሆኑም አዋጁ ከላይ የተጠቀሱት ተግባራት ሽብርተኝነት ሊፈርጅ የሚችለው “ማንኛውም ሰው ወይንም ቡድን የፖለቲካ፣ የሀይማኖት ወይንም የአይዲዮሎጃዊ አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰብን ወይንም የህብረተሰብን ክፍል ለማስፈራራት ወይንም የአገሪቱን የፖለቲካዊ፣ ህገ-መንግስታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይንም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይንም ለማፍረስ” የሚል አላማና ፍላጎት ይጨምርበታል፡፡ ይህ የሽብር ትርጉሙን ከተራ ወንጀልነት ወደ ሽብርተኝነት የሚቀይረው አብይ ክፍል ሲሆን መንግስታትም በዋነኛ ካርድነት ይጠቀሙበታል፡፡ በተለይ በአገራችን የተደላደለ ፖለቲካዊ ስርዓት ባለመፈጠሩ ምክንያት አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መሆናቸው አልቀረም፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግስትን የተቆጣጠረው ፓርቲ ጥቃቅን ጉዳዮቹን ወደ “ሽብርተኝነት” ለመቀየር የሚያስፈልጉ ዓላማዎች ጋር በማገናኘት የሰላማዊ ትግሉን እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች “በሽብር” ስም እየፈረጃቸው ይገኛል፡፡
ኢቲቪ ታህሳስ 19 ባስተላለፈው ዶክመንተሪ አቶ መለስ ዜናዊ ስለ አዋጁ ዴሞክራሲያውነት ሲናገሩ አሳይቷል፡፡ አቶ መለስ አዋጁን በቀጥታ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከእንግሊዝና ከአሜሪካ ቃል በቃል የወሰዱት ቃል ቢቀይሩ ይተቹናል በማለት እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አቶ መለስ አዋጁ ከእነዚህ አገራት ቃል በቃል ስለተቃዳ ብቻ ምንም እንከን የማይወጣለት ብለውታል፡፡ ይህን የአቶ መለስ ንግግር የተጠቀሙበት አሁንም የኢህአዴግ አቋም (ማሳመኛ) ቢሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረትና ከእንግሊዝ የተለየ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያላት አገር እንደመሆኗ ለራሷ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ህግ እንደሚያስፈልጋት ጥርጥር የለውም፡፡ ኢህአዴግ በውል የማይተረጉማቸው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስት” ከአውሮፓ ህብረት፣አሜሪካና እንግሊዝ ኒዮ ሌብራሊዝም ይልቅ ከአገራችን (ከአፍሪካ) ነባራዊ ሁኔታ ተጣጥሞ የተቀረጸ መሆኑን ሲናገሩ ኖረዋል፡፡ የአውሮፓውያን ፖሊሲ ለአውሮፓውያን እንጅ ከአውሮፓ የተለየ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሰረት ላላቸው አፍሪካውያን እንደማይጠቅም “AFRICAN DEVELOPMENT: DEAD ENDS AND NEW BEGINNINGS” በሚለው ጽሁፋቸው ሊያስረዱ ሞክረዋል፡፡ ገና በመግቢያውም “የእኔ መከራከሪያ ኒዮ ሌብራሊዝም ያለቀለትና በአፍሪካ ህዳሴ ሊያመጣ የማይችል በመሆኑ የአፍሪካን ህዳሴ ለማምጣት ሌላ ስርዓት ያስፈልጋል የሚል ነው” ይላሉ፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ ከምዕራባዊያን የተለዩ በመሆናቸው ከአውሮፓውያኑ የተለየ ስርዓት ካስፈለጋቸው የጸረ ሽብር ህጉንስ ለምን በቀጥታ መገልበጥ አስፈለገ? ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት፣ የግለሰብ ነጻነት፣ የመሬት ህግ፣ ኢኮኖሚውን ለግል ባለሃብት የማስተላለፍ ለምን እንደ ጸረ ሽብር ህጉ አቶ መለስ ሰለጠኑ ከሚሏቸው ምዕራባዊያን በቀጥታ አልተገለበጡም? የሚሉት ጥያቄዎች ሊያስረዱ የሚችሉት የጸረ ሽብር ህጉ በመልካም ተሞክሮነት ተገልብጦ መጠቀሚያ መሆኑን ብቻ ነው፡፡
ኢህአዴግ ያመነው ስህተት
ይህ ጸረ ሽብር አዋጅ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉበት እየተተቸ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ቀዳሚው ከህጋዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ትርጉሙ ማመዘኑ ነው፡፡ አንድነት የጸረ ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ ለሶስት ወር ባደረገው የድምጽ ማሰባሰብ ሂደት የተደናገጠው ኢህአዴግ ከወራት በፊት በአዋጁ ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር ክርክር ማድረጉ ይታወሳል፡ ፡ በክርክሩ ወቅት ተቃዋሚዎችና ገዥው ፓርቲ የተስማሙበት ብቸኛው ነጥብ ቢኖር አዋጁ ከህጋዊ ይልቅ የፖለቲካ ትርጓሜ የተሰጠው መሆኑን ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በህገ- መንግስቱ መሰረት ህግ ሊተረጎም የሚገባው በህግ አካላት እንጅ ፖለቲካዊ ሚናን በሚጫዎተው እንዲያውም የአንድ ፓርቲ አባላት በሞሉት ፓርላማ አይደለም በሚል ተከራክረዋል፡፡ በአንጻሩ ኢህአዴግ ሽብርተኝነት ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ሊነጻጸር የማይችልና አንገብጋቢ በመሆኑ ፓርላማ ሊያጸድቀው የግድ መሆኑን በመጥቀስ ፖለቲካ ትርጓሜ እንደተሰጠው አምኗል፡፡ በጸረ ሽብር ህጉ መግቢያ ላይም ‹‹በስራ ላይ ያሉት (ህገ መንግስቱን ጨምሮ) የሀገሪቱ ህጎች በበቂ ሁኔታ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ባለመሆናቸው ጠንካራ የህግ አቅም መፍጠር በማስፈለጉ ነው በሚል አዋጁ ከህገ መንግስቱ የተለየ (የጣሰ) መሆኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአንደበቱ ተናግሯቶታል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 25(1) “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት አቅራቢነት አንድን ድርጅት በሽብርተኝነት የመሰየም እና የሽብርተኝነቱን ስያሜን የመሻር ስልጣን ይኖረዋል፡፡” ሲልም “ሽብርተኝነት” ከትርጉሙ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ፖለቲካዊ እንጅ ህጋዊ ማዕቀፍን የተከተለ እንዳልሆነ ያስረግጣል፡፡
ከኢትዮጵያውያን በተቃራኒ በሌሎች አገራት መንግስታት ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የሚከራከሩት ህጉ ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶታል አልተሰጠውም በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ፖለቲካዊ ትርጓሜ የተሰጠው “ህግ” ከህግነት ይልቅ መጠቀሚያ በመሆኑ ሲሆን ኢህአዴግ ግን የጸረ ሽብር አዋጁ ፖለቲካዊ ትርጉም እንደተሰጠው አምኗል፡፡ በዚህ ረገድ ኢህአዴግ የጸረ ሽብር ህጉን ለራሱ ጥቅም የተጠቀመ መሆኑን ያመነ ብቸኛው ፓርቲ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የፖለቲካ ትርጉሙና አተገባበሩም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎችና ህገ-መንግስቱ ህዝብንም ሆነ የአገር ድህንነትን ለመጠበቅ የሚደረግ የትኛውም የመንግስት እርምጃዎች የዜጎችን የመደራጀት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና ሚስጥራቸውን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ቢያስቀምጡም የጸረ ሽብር አዋጁ እነዚህን ጨምሮ አብዛኛዎቹን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በፖለቲካዊ አውዱ ጨፍልቋቸዋል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ አዋጁ ህገ መንግስቱን የማይጥስ፣ ህጋዊ ትርጓሜ እንጅ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ያልተሰጠው (ለፖለቲካ ጥቀም የማይውል ነው) ሲል ይደመጣል፡፡
የጸረ ሽብር አዋጁ በፖለቲካዊ ትርጉምና አተገባበሩ ሁሉንም ነገር ከብሄራዊ ደህንነት ጋር ማገናኘቱ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ሽብርተኝነት ዋነኛው የደህንነት ትኩረታቸው በሆኑት አገራት ሳይቀር ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና ብሄራዊ ደህንነት አብረው እርስ በእርሳቸው በማይጋጩበት አሊያም መጠቀሚያ በማይሆኑበት መንገድ ተግባር ላይ ይውላሉ፡፡ ‹‹ሽብርን›› መዋጋት ለዜጎች ደህንነት ነውና የዜጎችን ነጻነት የሚነፍግ ተግባር ራሱ ሽብር ከመሆን አያልፍም፡፡ አንዳንዴ ለዜጎች ለራሳቸው እንዲሁም ለአገሪቱ ሲባልም ነጻነታቸው ለደህንነት በሚያመች መልኩ ይቃኛል፡ ፡ በመንግስታት ቅቡልነትና ባህሪ መካከል ያለው ትርጉምና አተገባበር የተለያየ ቢሆንም ሁለቱን በተገቢውመንገድ የማጣጣም ሀላፊነት የሚወስደው ደግሞት መንግስት ነው፡፡
በህዝብ ይሁንታ ስልጣን ላይ ወጥተው ህዝብን የሚያስተዳድሩ መንግስታት አዋጁን የዜጎችንና ብሄራዊ ደህንነትን በማጣጣምና ለማስጠበቅ ይጠቀሙበታል፡፡ በተቃራኒው አምባገነን መንግስታት የጸረ ሽብር ህግ የተፈቀዱና ሰላማዊ የፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በመቀፍደድ ለራሳቸው ስልጣን ማራዘሚያ በመሳሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ “ARTICLE 19″ የተሰኘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ነጻ ሀሳብና የመረጃ ነጻነት የሚከራከር ተቋም “COMMENT on Anti-Terrorism Proclamation, 2009, of Ethiopia” በሚል ጥናቱ የኢትዮጵያው ጸረ ሽብር አዋጅ የህዝብንም ሆነ የብሄራዊ ደህንነትን የማያስጠብቅ የኢህአዴግ መሳሪያ መሆኑን ይደመድማል፡፡ በተቃራኒው አዋጁ ተጠቅሞ ከብሄራዊ ደህንነት ጋር በማይጋጭ መልኩ ለዜጎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መቆም የነበረበት መንግስት ፖለቲካዊ ትርጉም የሰጠውን አዋጅ ተጠቅሞ መሰረታዊ መብቶቻቸውን እየጨፈለቀ እንደሚገኝ ይከሳል፡፡
የትርጉም ግልጽነት
አካላት ህግን ከራሳቸው ጥቅም አንጻር እንደፈለጉ እንዲጠመዝዙ ከሚያችላቸው አጋጣሚ አንዱና ዋነኛው ህጉ የሚኖረው የግልጽነት ችግር ነው፡፡ የግልጽነት ችግር በተለይም ጉዳዩን ለራሱ ጥቅም ለመጠምዘዝ ለሚችለው የበላይነት ያለው አካል መጠቀሚያ ሲሆን አቅም (ወቅታዊ ስልጣን) የሌላቸው ግልጽነት በጎደለው ህግ ተጎጅዎች ይሆናሉ፡ ፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያ መቼም ቢሆን የህይወት ስምምነት ውልን አይረሱትም፡፡ ጣሊያንኛውና አማርኛው በተምታታና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የተጻፈው ውል በብዙ መልኩ ሀይሉ የነበራቸው ጣሊያኖች በፈለጉት መልኩ እንዲጠመዝዙት ሲያስችላቸው ኢትዮጵያውያኑ ደግሞ ተጎጅዎች ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ “የጸረ ሽብር” አዋጅ ከህይወት ስምምነት የሚለየው ውሉ በኢትዮጵያ መንግስትና በአገሪቱ ህዝቦች መካከል፤ እንዲሁም የትርጉሙ ችግር ከቋንቋ ይልቅ አድበስብሶ የማለፍና ወደሚፈልጉት ለማስጠጋት አመች መሆኑ ብቻ ነው፡፡ አዋጁ ከመጠን በላይ ሰፊና ግልጽነት የሚጎድለው ነው፡፡ ከላይ በዝርዝሩ እንዳየነው በርካታ ተራ ወንጀል እንኳን የማይሆኑ የሰላማዊ ትግል አካላትን ጭምር በትርጉሙ አካቷል፡፡ ተራ ወንጀልነት በሌላ ህግ ሊታዩ የሚችሉትን ተግባራትም ከበስተጀርባቸው የራሱን ዓላማና ትርጓሜ በመጨመር ወደሚፈልፈው “የሽብር” አይነት ይቀይራቸዋል፡፡ አዋጁ “ንብረት”፣ “በሽብርተኝነት የተገኘ ንብረት”፣ “እገታ ወይንም ጠለፋ”፣ “ማነሳሳት”፣ “የህዝብ አገልግሎት”፣ “መንግስት”፣ “ፍርድ ቤት”፣ “ፖሊስ”፣ “ሰው” የሚሉትን ተራ ቃላት በግልጽ ደግሞ ደጋግሞ በተረጎመበት “ሽብርተኝነት” የሚለውን ተግባር ግን ግልጽነት እንደጎደለው በአከራካሪነት እንደተሞላ አልፎታል፡፡ ይህም የሆነው አሸባሪነት በግልጽነት ከሚተረጎም ይልቅ በድፍኑ ለመግዢያ መሳሪያነት ስለሚያገለግለው ነው፡፡
ከምንም በላይ አዋጁ በሰላማዊ ትግል፣ ሽብር፣ የትጥቅ ትግልና ተራ ወንጀል መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለይቶ ለማወቅ አለማስቀመጡ አዋጁንም ስልጣን ላይ ያሉት ለጥቅማቸው የሚጠመዝዙት የዘመኑ የህይወት ውል ያደርገዋል፡፡ በአንቀጽ 3(6) ማንኛውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ ወይንም ያበላሸ እንደሆነ ይላል፡፡ ይሁንና እነዚህ ተግባራት በሰላማዊ እምብይተኝነት ላይ የተለመዱ ስልቶች በመሆናቸው ከሽብርተኝነት ይልቅ ለሰላማዊ ትግል አካል ናቸው፡፡ ይሁንና ከ1997 አብዛኛዎቹ ተግባራት ሲተገበሩ ያየው አሊያም ሊተገሩ ሲሉ ፈርቶ በሀይል ያስቆመው ኢህአዴግ ወደ ሽብር አስጠግቷቸዋል፡፡ አዋጁ በሰላማዊ ትግል፣ ሽብር፣ የትጥቅ ትግልና ተራ ወንጀል ላይ ግልጽነት ቢኖረው እና ከፖለቲካዊ ይልቅ ህጋዊ ትርጉም ቢሰጠው ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጃቸው የአገራችን ድርጅቶች እና አልቃይዳ መካከል በአንድ አውድ ውስጥ ሊቀመጡ እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለጸረ ሽብር አዋጅ መሰረት የሆነችው አሜሪካ የኢትዮጵያ ፓርላማ መካከል ያለውን ልዩነት መግለጽ ተገቢ ነው፡፡ ኢህአዴግ በበላይነት የሚመራው ፓርላማ የኢትዮጵያዎቹ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም አልቃይዳና አልሻባብ በአንድ አውድ አጭቋቸዋል፡፡ በተቃራኒው አሜሪካ የኢትዮጵያዎቹና አልቃይዳ እጅጉን የተለያዩ መሆናቸው ለማመን የሚያስችላት ህጋዊ ማዕቀፍን የተላበሰ “ጸረ ሽብር ህግ” በማጽደቋ ኢህአዴግ ለሚያሳድዳቸው መጠለያ ሆናለች፡፡
መንግስታት ዜጎች፣ ቡድኖችንን በምርመራ፣ በእስራትና በመሳሰሉት ህዝቦችን በርዕዮታዊ፣ ሀይማኖታዊና ፖለቲካዊ አቋማቸው ከመፈረጅ ይድኑ ዘንድ የጸረ ሽብር ህጉን ግልጽ በሆነ መንገድ ሊተረጉሙ ይገባቸዋል፡፡ በሽብርተኝነት ምክንያት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለህዝብም ሆነ ለአገር ደህነነት ሲባል እንዲወሰን ግድ የሚለው ሀሳብን የመግለጽ መብት ርዕዮታለማዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ወይንም የተደራጀ ወንጀልን በማራመድ በመንግስትና ባለስልጣናት እንዲሁም በህዝብ ላይ “ሽብር” ይፈጥራል በሚል ነው፡፡
የጸረ ሽብር ህጉ ሽብርተኝነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉትን ፈርጇል፡፡ ሆኖም ህጉ እንዲህ አከራካሪና ፖለቲካዊ አላማ በያዘበት ሁኔታ በአንቀጽ 6 ሽብርተኝነትን ስለማበረታታት፣ አንቀጽ 7 በሽብርተኝ ድርጅት ውስጥ ስለመሳተፍ፣ በአንቀጽ 8 ለሽብርተኝነት ድርጊት መፈጸሚያነት እንዲውል ንብረት መያዝ ወይም መጠቀም፣ በአንቀጽ 9 በሽብርተኝነት ድርጊት የተገኘን ንብረት ስለመያዝና መገልገል፣በአንቀጽ 10 ምስክር ማባበል ወይንም ማስፈራራትና ማስረጃ ማጥፋት፣ በአንቀጽ 11 በሀሰት የሽብርተኝነትን ድርጊት ስለማስፋፋት፣ በአንቀጽ 12 የሽብርተኝነት ድርጊቶችን አለማስታወቅ የሚሉት ከህጋዊ መሰረት ይልቅ አወዛጋቢና በህዝብ ላይ አሉታዊ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡
የሽብርተኝነትን ጉዳይ የሚከታተሉ ተቋማት ውስጥ (1) አቃቢ ህግና ፖሊስ፣ (2) የደህንነት ሰራተኞች፣ (3) የጸረ ሽብር አስተባባሪ ኮሚቴ፣ (4) በሽብርተኝነት ወንጀል የዳኝነት ስልጣን በሚል ሲቀመጥ ዳኞች በአራተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጡት፡፡ ምንም እንኳ ዳኝነቱም በገዥው መንግስት ቁጥጥር ስር የወደቀ ቢሆንም መጀመሪያ ሽብርተኝነትን ደህንት፣ የጸረ ሽብር አስተባባሪ ኮሚቴ የመሳሰሉት ከገዥው ፓርቲ ጋር ልዩነት የሌላቸው አካላት ስለ ሽብርተኝነት ቀድመው የመወሰን አቅም አላቸው ማለት ነው፡ ፡ ይህም የሚያሳየው ገዥው ፓርቲ ከተጽዕኖው ያልወጣውን ፍርድ ቤትም ቢሆን የደህንነትና የጸረ ሽብር ግብረ ኃይልን ያህል “አላማየን ያስፈጽምልኛል!” ብሎ እንደማያምነው ነው፡፡ ጌታቸው ሺፈራው (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)
http://www.goolgule.com/the-mystery-terrorism/
No comments:
Post a Comment