(እዮብ ከበደ ኖርዌይ)
በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጭቆና፣ ስቃይ እና መከራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካደረጉት ምክንያቶች መካክል አንዱ፣ የወያኔ መንግስት ከምዕራባዊያን የሚያገኘው ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ሙገሳ ትልቅ ቦታ ይይዛል። ከነዚህ መንግስታት የሚያገኘው ድጋፍ እና ሙገሳ ምክንያት የማን አለብኝነት ስሜት ስርዓቱ እንዲሰማውና የኢዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቡ ላይ እንዲንያሰራፉ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ስርዓቱም ከነችግሩ ለረዥም ጊዜ በስልጣን እንዲቆይ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የምዕራባዊያን ድጋፍ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። እነዚህ ሀገራት የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ብቻ ትኩረት በመስጠታቸው ላለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በጭቆና ውስጥ እንዲያሳልፍ አድረገውታል። የሀገሪቱ መልካምድር\ጅኦግራፍያዊ አቀማመጥ፣ የመንግስት ለምዕራባዊያን ፍላጎት አጎብዳጅነት እና ሃገሪቱ በአካባቢው ብሎም በአፍሪካ ፖለቲካ ያላት ማእከላዊ ስፍራ የለጋሽ ሀገራትን ትኩረት ሊስብ ችሏል። በዚህ ምክንያት ምዕራባዊያን የወያኔ ስርዓትን አቅፈውና ደግፈው በመያያዛቸው ህዝቡ ከዚህ አስከፊ ስርዓት ነጻ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል አስቸጋሪ አድርጎታል።
የወያኔ መንግስት በህዝብ ላይ እያደረሰ ካለው ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች እና የስርዓቱ ልዩ መለያ ባህርያት መካከል በዋናነት፣ በሀይል ህዝቦችን ለዘመናት ከሚኖሩበት መሬት ማፈናቀል እና መሬታቸውንም በርካሽ በኢንቨስትመንት ስም መቸብቸብ፤ የጸረ-ሽብር ህግ በማውጣት የፖለቲካ አመራሮችን እና ጋዜጠኞችን ማፈን፤ ከፍተኛ ሙስና እነዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት የስልክ እና የኢንተርኔት ክትትል እና ጠለፋ ማድረግ ተጠቃሽ ናቸው። የምዕራባዊያን በወያኔ ላይ ያላቸው ቸልተኝነትና ለዘብተኛ አቋም መንግስት የማናለብኝነት ስሜት እንዲሰማውና በህዝብ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃና ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑና ስፋቱን እየጨመረ በመሄድ የሀገሪቱን ብሎም የአካባቢውን መጻይ ዕድል አሳሳቢ አድርጎታል።
ከምዕራባዊያን የሚገኝ እረዳታ በመጠቀም ብዙ የአፍሪካ መንግስታት አምባገነናዊ ስርዓትን በሰፊዊ የማጠናከራቸው ሁኔታ አዲስ ነገር አይደለም። ከሰሞኑም የወጣው የHuman Rights Watch ሪፖርት እንዳመለከተው መንግስት ህዝቡን እንዴት ጠፍንጎ እና ጨቁኖ እንደያዘው ምናልባት ለውጭ ማህበረሰብ አዲስ ነገር ሊመስል ቢችልም ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን አዲስ አይደለም። በተለያዩ ወቅቶች የተቃዋሚ ሓይሎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲገልጹት የቆዩት ጉዳይ ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ መጠቆም የሚገባን፤ ወቅታዊ ሪፖርቶችን በተከታታይ በማቅረብ፣ ሰፋ ያለ ማብራሪያና መረጃወችን የሚያቀርበውን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት( Human Right Watch) ማመስገን ይገባናል።
ድርጅቱ ከጥቂት ድርጅቶች መካከል አምባገነናዊ ስርዓቶችን በማጋለጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስለ ወያኔ ፍጹም አምባገነናዊ ስርዓት ሲነገር ቢቆይም ሰሞኑን የወጣው የ Human Rights Watch ሪፖርትም የዚህን ስርዓት አስከፊነትና ከምእራባዊያን ከሚያገኘው ዳጎስ ያለ የገንዘብ ድጋፍ ዘመናዊ የስለላና የክትትል ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት ስርዓቱ ፍጹም አምባገነናዊ እንደሆን አመላክቷል። በረቀቀ እና ጊዜውን በጠበቁ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረጋ ባለው ጭቆና የምዕራባዊያን ሀገራት እና ድርጅቶች በተዘዋዋሪ ተሳታፊና ተባባሪ አድርጓቸዋል። በመሆኑም የ Human Rights Watch ሪፖርት እንደሚያመልክተው የምዕራባዊያን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ለጨቋኝ ስርዓት ተባባሪ በመሆናቸው ሊጠየቁ እንደሚገባ በማሳሰብ ቴክኖሎጂውን የሚያቀርቡ፣ የሚሸጡ፣ እና አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የቴክኖሎጂ ውጤታቸው ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተግባር በተደጋጋሚ ክስ የሚቀርብባቸው እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ላሉ መንግስታት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መቆጣጠር እንዳለባቸው ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ለጋሽ አገራት በአመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በውጭ እርዳታ መልክ ድጋፍ ያገኛል። ይህ ከፍተኛ ድጋፍ በአግባቡ ለልማት ቢውል በደሃው ህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ቀላል አይደለም። ነገር ግን አምባገነናዊው መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ከመጠቀም አልፎ ህዝቡን ለማፈን፣ ለመጨቆን እና ለመሰለል እንዲረዳው ዘመናዊ እና የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማስገባት ይህን ድጋፍ ያውለዋል። ድጋፉን ለሚሰጡት ምዕራባዊያን ግን ይህ ድርጊት ከእይታቸው የተሰወረ አይደለም።የ Human Right Watch እና የተላያዩ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ጋዜጠኞች፣ ዳኞች፣ ምሁራን፣ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተሰደዋል። እነዚህንም መረጃዎች ለጋሽ አገራት አንብበዋል፤ የጉዳዩንም ክብደት ከማንም በተሻለ ሁኔታ ያውቃሉ። ነገር ግን ምዕራባዊያን በጉዳዮ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ወይም ተጽዕኖ ለማሳደር ለዘብተኛ መሆናቸው ሳያንስ በአሳፋሪ ሁኔታ ጉዳዩን አይተው እንዳላዩ በመሆንና የመንግስትን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው በማቀንቀን የበሰበሰው ስርዓት በህዝቡ ላይ እንዲንሰራፋ አድረጎታል።
በተጨማሪም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በህይወት እያሉ የምዕራባዊያንን ፍላጎት በማስቀደም በሰላ ምላሳቸው የምዕራባዊያንን ቀልብ መሳብና ማማለል ችለው ነበር። የለጋሽ ድርጅቶች ቡድን (The Donors Assistance Group) እንደሚያመለክተው የወያኔ መንግስትን በተመለከተ በተከታታይ የሚወጡትን ሪፖርቶች መርምሮ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጉዳዩን ወደጎን በመተው ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር የለት ተለት ተግባራቸውን መቀጠል እንደሚመርጡ አመልክቷል። ከዚህ በፊት ካለን ልምድ እንደምንረዳው ለጋሽ ድርጅቶች ወይም ሀገራት ከወያኔ መንግስት ጋር ፊት ለፉት ከመላተም ይልቅ ከገለልተኛ ወገኖች እንደ ከ Human Right Watch የሚወጡ ሪፖረቶችን ውድቅ ማድረግን ይመረጣሉ። ከተቻለም የራሳቸውን ሪፖርት በማዘጋጀት በመንግስት ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ የሚያጠናክር መረጃ እንዳላገኙ በመግለጽ ጉዳዩን ያለዝባሉ ወይም ከገለልተኝ ወገኖች የሚወጡ ሪፖረቶች የተፋለስ ድምዳሜ እንዳላቸው በመጥቀስ መሬት ያልያዙና እውነታውን እንደማያሳይ ማመልከት ይመርጣሉ። ይህ ሁኔታ እነዚህ የውጭ ሀገራትና ድርጅቶች ምን ያህል ለሰፊው ህዝብ መብት እና ጥቅም ደንታ እንደሌላቸው ያመላክታል።
የምዕራባዊያን ከአምባገነናዊ ስርዓት ጋር ያላቸው አጋርነት እና ቁርኝት በኢትዮጵያ ወይም በአፍሪካ ብቻ የተወሰነ ክስተት ሳይሆን በተለያዩ አገሮችም የሚስተዋል ነው። ምዕራባዊያን ለምን ይህን ድጋፍ እንደሚያደረጉ ሲገልጹ፤ እረዳታ መስጠት ብናቆም ዞሮ ዞሮ ተጎጂው ድሃው ህብረተሰብ ስለሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ ባለው ስርዓት አማካኝነት እርዳታ መስጠቱን መቀጠል እንደሚመረጡ ይናገራሉ። ይህ አስተሳሰብ ለጋሽ ሀገራት ለሰብአዊ መብት ክብር እና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ባይተዋር እንደሆኑ ያሳያል። ለሚሰጡት እርዳታ ቁጥጥርና ክትትል ተአማኒነትና ግልጽ ያሰራር ስርዓት በመዘርጋት የሚሰጡትን ገንዘብ ላልተፈለገ አላማና ፍጆታ ሲውል እርዳታውን ማቆም የሚቻልበትን መንገድ የሚጠፋቸው አይመስለንም።
መንግስትም ማንኛውንም አማራጮች የሚዘጋ ከሆነም ከነጭራሹ እረዳታውን በማቆም ጠንከር ያለ ተጽዕኖ መፍጠር ይችሉ ነበር። እረዳታ ብናቆም ደሃዉ ህብረተሰብ ይጎዳል የሚባለው ምክንያት አጥጋቢ መነሻ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰቡ ከእርዳታው ተጠቃሚ እየሆነ አይደለምና። ስለሆነም ማነኛውም ምዕራባዊ አገር ለአምባገነናዊ መንግስት የሚሰጡትን እርዳታ ለማቆም ዝግጁ ባለመሆናቸው የሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ አላማውን ስቶ በተቃራኒው ንጹሃንን ህዝቦች ለማፈን እና ለመጨቆን ትልቅ መሳሪ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል።
ጸሃፊውን ለማግኘት ከፈለጉ eyobekebede1@gmail.com ይጠቀሙ።
http://www.goolgule.com/the-west-who-are-supporting-the-regime/
No comments:
Post a Comment