ብሩክ ሲሳይ (አዲስ አበባ)
ያለወትሮዬ ሴንትራል ሆቴል ቁጭ ብያለሁ ከጎኔ ሁለት ሽማግሌዎች ተቀምጠዋል ብቻዬን በመሆኔ እና የሽማግሌዎች ወግ ስለምወድ እነዚህ ሁለት አዛውንቶች የሚያወሩት ወሬ ላይ ጆሮዬን ጥያለሁ፤ ከአገራችን ፖለቲካ ጀምሮ እስከ ልጅነት ህይወታቸው እና ሌሎችም ብዙ ነገሮችን እያነሱ ያወራሉ። ከወሬያቸው እንደተረዳሁት አንደኛው አዛውንት ከአሜሪካ ቨርጂኒያ ለእረፍት የመጡ ዲያስፖራ ናቸው ሌላኛው ደግሞ በኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃወች ያገለገሉ እና ኢህአዴግ መጥጦ መጥጦ የወረወራቸው አዛውንት ናቸው። ወሬያቸው ግሏል ግንቦት 7 እና የግብፅ እና የሻብያ ተላላኪዎች፣ የጨረቃ ቤቶች፣ የመተማ እና የሱዳን ጠረፍ መሬቶች፣ መለስ ዜናዊ፣ ብርሀኑ ነጋ፣ ሟች ጳጳስ ጳውሎስ፣ አልማ፣ የዲያስፖራው አክራሪነት ወዘተ አይነት ነገሮች እየተወሩ ነው። ጋባዥ ስለሆኑ ነው መሰለኝ ብዙ የሚያወሩት ዲያስፖራው አዛውንት ናቸው ተጋባዥ አዛውንት ደግሞ ራሳቸውን በመነቅነቅ ድጋፍ ይሰጣሉ።
የጨረቃ ቤት መፍረስ ትክክል ነው አሉ ዲያስፖራው ብዙ ማብራሪያ በመስጠት ፣ ያኛው አዛውንት ደግሞ የተዋጠላቸው አይመስልም ወደ እኔ ዞሩ እኔ ደግሞ ያልሰማሁ ይመስል ሞባይሌን መነካካት ያዝኩኝ ግን ጆሮየም ልቤም ወሬው ላይ ነው። አዛውንቱ ዲያስፖራ የሚናገሩት በሙሉ ያበሽቃል ብቻ ግን እኔ እያዳመጥኩኝ ነው፤ በመቀጠል አልማ አሜሪካ ላይ ገቢ ማሰባሰቢያ ሲያደርግ ቶምቦላ እንደገዙ (ያኔ ደመቀ መኮነን፣ ህላዊ ዮሴፍ፣ ካሳ ተክለብርሀን ወዘተ ሲዋረዱ ማለት ነው)፣ ለአማራ ልማት ብር እንደለገሱ፣ አቡነ መርቀርዮስ የሚባሉት ጳጳስ መለስ ዜናዊ እና አቡነ ጳውሎስ የሞቱት በህዝብ እንባ እና በእግዚአብሄር ቁጣ ነው ብለዋል፣ ወደ ኤርትራም ሶስት ጊዜ በመሄድ አርበኞች ግንባርን አበራትተዋል የአሜሪካን ምዕምናንም ገንዘብ እየዘረፉ ነው በማለት ከላይ ከታች አብጠለጠሉ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንንም እንደ ኢራቅ ሊያደርጉን ነው አሏቸው፣ ሰ’ማያዊ ፓርቲዎችንም እነሱ ከእንጦጦ መጥተው ስለ መተማ መሬት ምና አገባቸው እና መንግሥት ያልሰጠውን መሬት ለሱዳን ሰጠ ብለው በውሸት አመፅ ሊያስነሱ የሚፈልጉት እያሉ ሲቀጥሉ አላስችለኝ አለ አቁነጠነጠኝ አፌን በላኝ እኚህ የሽማግሌ ወራዳ አናደዱኝ ከዚያም “ይቅርታ አድርጉልኝ በወሪያችሁ ጣልቃ ገባሁ” በማለት
“የመተማ እና ሌሎች የሱዳን አዋሳኝ መሬቶች እንዳልተሰጡ በምን አወቁ?” አልኳቸው እሳቸው ሲመልሱ
“መንግስት አልሰጠሁም እያለ ነው፣ ጠ/ሚኒስተሩ በቴሌቪዥን ውሸት ነው ብለዋል ይሄን የሚያወሩት ተቃዋሚዎች ናቸው በውሸት ህዝብን ሊያሳምፁ ነው” አሉኝ እኔ ደግሞ ጥያቄየን ቀጠልኩ
“መንግስት መሬት ቢሰጥስ በአደባባይ ሰጥቻለሁ ብሎ የሚያወራ ይመስልወታል? እንዴትስ መንግስትን እና የመንግስት ሜዲያን ያምናሉ? የኛ መንግስት ባለስልጣናት እና ሜዲያዎች እኮ መለስ ዜናዊ መሞቱ እየታወቀ የአዲስ አመት ዘመን መለወጫ ይመጣል የሚሉ ናቸው፣ የባድመ እና ዛላንበሳ መሬቶች በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኝነት ለኤርትራ ተወስኖ እያለ ነገር ግን የኛ መንግስት በውሸት ለኢትዮጵያ ነው የተወሰነው በማለት ህዝብን ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስወጣ ነው፣ በ97 ምርጫ የ14 አመት ህፃን ገድለው ባንክ ሊዘርፍ ሲል ነው የተገደለው የሚል መንግስት፣ ሜዲያ እና ማፍያ ባለስልጣናት እንዴት ያምናሉ? ከፈለጉ ደግሞ መሬቱ በሱዳን መንግስት የተወሰደበት ተማሪየን ላገናኘወት እችላለሁ………”
ሰውየው ትንሽ ረጋ አሉ እና “በድንበር አካባቢ ችግር ሊኖር ይችላል ነገር ግን ከግብፅ እና ሻብእያ ጋር በመላላክ እነ ግንቦት 7 እና ብርሀኑ ነጋ ኢሳትን በመጠቀም የሚያናፍሱት ወሬ ነው” አሉኝ። እኔም
“ለምንድን ነው ብርሀኑ ነጋ እና ግንቦት 7 ከሻቢያ ጋር የሚሰሩት?” ብዬ ስጠየቃቸው። እሳቸውም
“ብር ነዋ ሆዳም ስለሆኑ በግብፅ በኩል ገንዘብ ለማግኘት ነው” አሉኝ። እኔም
“ይህ ዶ/ር ብርሀኑ የሚባሉ ሰውየ አገር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ባለሀብት ናቸው፣ ቤተሰቦቻቸውም እንደዚያው ናቸው። ታዲያ ይሄን ሰው ብር ፈልገው ነው ማለት አይከብድም ወይ? ደግሞስ ብር ቢፈልጉ ይህ ሰውየ ከኢህአዴግ ጋር ተሞዳሙደው አገሪቱን መዝረፍ ያቅታቸዋል ብለው ነው? ህሊናን ሽጦ ከዚህ መንግስት ጋር ተሞዳምዶ ሀገር መዝረፍ እኮ በጣም ቀላል ነገር ነው ምናልባት ለእርሰዎ ከብዶዎት ካልሆነ?” ስላቸው መልሳቸውን ወደ ምክር በማዞር
“እናንተ ወጣቶች እየተሸወዳችሁ ነው፣ በዚህ እድሚያችሁ መስራት፣ መማር፣ ገንዘብ መያዝ ነው ያለባችሁ እዚያ አሜሪካ ሁሉም ስራ ላይ ነው ታች ላይ የሚለው፣ እንደ እኛ ጊዜ አትሸወዱ እየው ሀገሪቱ እያደገች ነው በዚህ እድል መጠቀም አለባችሁ” አሉኝ እኔ ደግሞ ቀጠልኩኝ
“እርሰዎ ከአሜሪካ መጥተው የነፃ መሬት ከመንግስት ተበርክቶለዎት ለንግድ ቤት የሚሆን ህንፃ እየሰሩ ነው። እኔ ግን ህዝቤን እያገለገልኩ ለቤት መስሪያ የምትሆን ቁራጭ መሬት መንግስት ነፍጎኛል፣ ይህች አገራችን ለልጆቿ በቀላሉ የምታበረክተው ነገር ቢኖር መሬት ነበር ነገር ግን ይህንን ቀላሉን ነገር ተነፍገናል። ታዲያ የእርሰዎ ሀገር ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ለእኔ አገሬ ናት ማለት እችላለሁን? ኢትዮጵያ ውስጥ በሀገሬ ያለኝ መብት ከአንድ ሱዳናዊ ወይም ህንዳዊ ግለሰብ ያነሰ ነው” ስላቸው “ተሳስተሀል መሬት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም ለዜጋው ለውጭ ሰዎች እየተሰጠ ነው ግን እኛ ሰነፎች ስለሆነ እና መስራት ስለማንወድ መሬቱን አንጠቀምበትም” አሉኝ። እኔም በመቀጠል
እርሰዎ ዕድሜዎ እየገፋ ነው፣ ከዚያ ላይ ሃይማኖት አለዎት እንደው ቢያንስ እንኳን በአይንዎት እያዩ ያሉትን ነገር እንዴት እንዳላዩ ይሆናሉ፣ ውስጠዎ ምን እያሰበ እንደሆነ እረዳዋለሁኝ እውነታውን በልበዎ ያውቁታል ነገር ግን እንደ እርሰዎ አይነት ሽማግሌ ሆኖ ያውም መረጃ በቀላሉ ከሚገኝበት አሜሪካ ተቀምጠው በዚህ ደረጃ ማሰብዎ ይገርመኛል” አልኩኝ።
ሌላ ተጋባዥ የእሳቸው ጓደኛ መጣ እና በሰላምታ ምክንያት ክርክሩ ተቋረጠ እኔም ተነስቸ ሄድኩኝ። ነገር ግን እስካሁን በህይወቴ እንደዚህ አይነት አይነ ደረቅ ሆዳም ሽማግሌ አጋጥሞኝ አያውቅም። ያውም እኮ እድሜው ወደ 70 አካባቢ ይሆናል። አገር ሲዘቅጥ እንደዚህ ነው በሞት አፋፍ ላይ ተቀምጠው እውነትን የፈሩ የሚያናድዱ ሽማግሌ ናቸው።
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11780/
No comments:
Post a Comment