FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Tuesday, April 1, 2014

ኢህአዴግ የአፍሪካ ቀንድ ስጋት?

አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች

eprdf and the usa


ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ብቸኛ ተዋናይና ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን የሾመው ኢህአዴግ ለቀጠናው ስጋት እንደሚሆን ተጠቆመ። አልሸባብንና አልቃይዳን ከምንጩ እናጠፋለን በሚል ስትራቴጂ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ሰምጣ የነበረችው አሜሪካ ከጉድጓዱ ለመውጣት ወስናለች። ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑትና የሚቀበሉትን መሪ በድፍረት አደባባይ የማውጣት ሃላፊነቱ “አገር ወዳድ” በሚሉ ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጫንቃ ላይ ነው።
ህወሃት ያቋቋማቸው ጥቃቅን መንግስታት ከህዝብ ይልቅ ለህወሃት የወደፊት እቅድ ታማኝ በመሆን መጓዛቸው ከቀን ወደቅን የፈጠረው ስሜት ኢህአዴግን እየበላው እንደሆነ የጠቆሙ የዜናው ምንጮች፣ ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪቃ የሰላም አባት ሊሆን ቀርቶ የራሱንም ችግር መፍታት ወደማይችልበት የቁርሾ ማሳ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህወሃት “በነጻ አውጪነት” ያሰላውና፣ ይህንኑ ዓላማውን በፈለገበት ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያመቸው ዘንድ በየክልሉ ለጣጥፎ ያቋቋማቸውን ፓርቲዎች ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ በድንገት ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሰላሙ መናጋቱ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ “የጓድ መለስን ውርስና ራዕይ ያለማዛነፍ እናስቀጥላለን” እያለ አገሪቱን በደቦ እንድተመራ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አቶ መለስ በጓዶቻቸው ቋንቋ “ተሰው” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ተቸግሮ ነበር። ደህንነቱን፣ መከላከያውን፣ ፖሊስና ዋንኛ የአገሪቱን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘው ህወሃት በቀጥታ አሜሪካ ባደረገችው ጫና ሳይወድ በግዱ አቶ ሃይለማርያምን በጠ/ሚኒስትርነት ለመሰየም ተገደደ። የስልጣን ክፍተቱን በተመለከተ አቻ ድርጅቶችና ህወሃት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር “ምደባ” በሚል ኢትዮጵያ በደቦ የሚመሯት አራት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሰየሙላት።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት እንዳሉት አሜሪካ ስጋት የገባት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር። መለስ እንዳለፉ ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁኔታውን በመገምገም ስራ የጀመረችው አሜሪካ አሁን አሁን በህወሃት ስትራቴጂ የተሰራው ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ዋንኛ የችግር ምንጭ ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየመከሩበትና የመፍትሔ ስትራቴጂ እየነደፉ ነው።
“We cannot afford to lose Ethiopia” አሜሪካ ኢትዮጵያን ልታጣት አይገባም በማለት ለጎልጉል የዋሽንግቶን ዘጋቢ የተናገሩት የዲፕሎማት ምንጭ “የአሜሪካን ባለስልጣናት ኢህአዴግን በተመለከተ የሚጠቀሙት ቃልና የድምጻቸው ቃና ተቀይሯል” ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመላክተዋል።
በዋሽንግቶን የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ኢህአዴግን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ስብሰባ መቀመጣቸው ታውቋል። አዲስ አበባም ተወካይ በመላክ ከሚመለከታቸው ባለስልጣናት ጋር በግል እየተነጋገሩ ነው። በያዝነው ሳምንትም ለተመሳሳይ ስራ አዲስ አበባ የተጓዙ አሉ። እንደ ዲፕሎማቱ ገለጻ የህወሃት ሰዎች ውስጣዊ ችግር እንዳለ አይቀበሉም። በግል ያነጋገሯቸው የሌሎች ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ግን ኢህአዴግ ውስጡ አለመረጋጋትና ስጋት የተሞላው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ችግር ቢፈጠር ለማረጋጋት አስቸጋሪ እንደሚሆን፣ ህዝቡ በተለይ በህወሃቶች ላይ የሚያሳየው ጥላቻ እየተካረረ መምጣቱ፣ በአገሪቱ የሚፈጸመው ያልተመጣጠነ የሃብት ስርጭት፣ አፈናውና ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ ተግባራት ተዳምረው ህዝቡን ክፉኛ ማስቀየሙ ያልታሰበ ችግር ሊቀሰቅስ እንደሚችል አሜሪካ መገንዘቧን ያወሱት ዲፕሎማት፣ “ህወሀቶች የቀጠናው የሰላም ምንጮች ስለመሆናቸው ለራሳቸው ምስክርነት ለመስጠት ቢሞክሩም በተግባር የሚታየው ግልባጩ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላይ የተተከለው የጎሳ አገዛዝ እንደሆነ ያመለከቱት እኚሁ ዲፕሎማት “በጎሳ አስተሳሰብ የተዋቀረው ኢህአዴግ ችግሩ ከገነፈለ ሊቆጣጠረው የሚችል ባለስልጣንና መሪ የለውም። አስተዳዳራዊ ማዕከላዊነት አይታይበትም። በግል የሚወስን ባለስልጣንና ርምጃ የሚወስድ አካል የለውም” ሲሉ የስጋቱን ግዝፈት ያሳያሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሩ ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰቡ አዳጋች እንደማይሆን ይጠቁማሉ። አያይዘውም “አሜሪካ ቸል ብላ ስትመለከተው የነበረውን ጉዳይ አጽንኦት ብትሰጠው አይገርምም” ብለዋል። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው ለራሷ ስትል እንደሆነ ያልሸሸጉት ዲፕሎማት አንድ ጥያቄም ጠይቀዋል። “እናንተስ ለራሳችሁ ስትሉ ምን እየሰራችሁ ነው?” ከረጅም ፈገግታ ጋር።
አልቃይዳን ከምንጩ ማድረቅ በሚለው የመለስ ስትራቴጂ ለኢህአዴግ ግብር ስታስገባ የነበረችው አሜሪካ ግብሯን ስትገብር የኖረችው በፔንታጎን ወታደራዊ ውሳኔ መሰረት ነበር። ኢህአዴግም ግብሩ እንዳይቆምበት በአዲስ አበባ ታክሲ ላይና ህዝብ በሚያዘወትርባቸው ቦታዎች ፈንጂ በማፈንዳት ሲጫወተው የነበረውን ድራማ ዊኪሊክስ (ሹልክ ዓምድ) አምባሳደር ያማማቶን ጠቅሶ ማጋለጡ አይዘነጋም። በዚሁ መነሻ ይመስላል ኢህአዴግ የቀድሞውን ጨዋታ የመጫወት እድሉ እንዳከተመ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ባደባባይ የመለስን ስብዕና በመዝለፍ ባልተለመደ መልኩ ተናግረው ነበር።
ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ዲፕሎማት “እናንተስ” በሚል ለሰነዘሩት ጥያቄ ማብራሪያ ተጠይቀው “እኔ ኢትዮጵያዊ ብሆን አገሬን አስቀድማለሁ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ አማራጭ ማጣቷንም እንደ አንድ ችግር አንስተዋል።
በዲፕሎማቱ አስተያየት ላይ ገለልተኛ ወገኖችን አነጋግረናል። ያሰባሰባንቸው አስተያየቶች “አሜሪካ እዚህ ደረጃ ከደረሰች፣ ኢህአዴግም በዚህ ደረጃ ከተመደበ ተቃዋሚዎች የግል ጉዳያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ውሳኔ በመተው ለመጪው ትውልድና ለአገር ሲሉ ከመቧደን በሽታ ሊፈወሱ ይገባል” የሚል ይገኝበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀናጅቶ መበተን፣ ተደራጅቶ መፍረክረክ፣ ተደላድለው መስለል በተለያዩ ወቅቶች ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርገዋል። የሚፎካከሩትን ፓርቲ ትተው እርስ በርሳቸው ለተራ ጉዳይ ሲሻኮቱ ዓመታት አሳልፈዋል። በዚህም የተነሳ “አማራጭ የለም” በሚል ኢህአዴግን ማንገስ ግድ እንደሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን አስተሳሰብ ሰብረው አገር መምራት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ህብረት መፍጠር ይገባቸዋል። ይህም ካልሆነ የርስ በርስ ውዝግባቸውን ማቆምና የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት ላይ ማተኮር ግዳጃቸው ይሆናል” ብለዋል።
ምሁራን ከተደበቁበት ሊወጡ እንደሚገቡም ያሳሰቡ አሉ። አገር የመምራት፣ በህዝብ የመታመን፣ የህዝብን ይሁንታ ማግኘት እንችላለን የሚሉ ከፊት ለፊት፣ አሁን ከፊት ያለውን ችግር በመጥረግ የወደፊቷን ኢትዮጵያ በመገንባትና መጪውን ትውልድ በማዳኑ ስራ አጋዥ ሃይል ለመሆን መወሰን እንደሚገባቸው በመግለጽ ጥሪ አቅርበዋል። ከሁሉም በላይ ግን “አሁን ካለው ህዝብን ካገለለ ዘመናዊ የመሳፍንት ስርዓት ኢትዮጵያንና ህዝቧን ማሻገር የሚችል ሞገሰ ሙሉ፣ ቅን፣ ከጥላቻ የጸዳ፣ ከሥልጣን ይልቅ የወደፊቷን ኢትዮጵያ አሻግሮ መመልከት የሚችል መሪ ወደ ፊት ወጥቶ በግልጽ ለህዝብ የሚተዋወቅበትን መንገድ የማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረገጾች፣ ሬዲዮኖች አገር ወዳድ የመገናኛ አውታሮች አጀንዳ አድርገው ሊወያዩበት ይገባል” የሚለው አስተያየት ሚዛኑን የደፋ ሆኗል።
http://www.goolgule.com/eprdf-a-source-of-instability-to-east-africa/

No comments:

Post a Comment