ይሁን እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ባደረገው ተደጋጋሚ ግፊት ክሱ በአሁኑ ወቅት መዝገብ ተከፍቶለት፣ የዳኝነት ክፍያ ተከፍሎ በቀጣይ ሀሙስ ሚያዝያ 9/2006ዓ/ም ክሱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሃብሄር ችሎት ላይ መታየት እንደሚጀምር ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ በጉዳዩ ላይ አቋም ወስዶበት ከሰላማዊ ሰልፉም ባሻገር ዜጎቹ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱና ካሳ እንዲሰጣቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እስካሁንም ድረስ በዜጎች ላይ በሚደርሰው ችግር ከጎናቸው ሆኖ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡›› ያሉት አቶ ብርሃኑ ፓርቲው ኢትዮጵያውያኑ በመፈናቀሉ ሂደት በደረሰባቸው ችግር ልጆቻቸው የታመሙባቸውን ለህክምና እንዲሁም ለመጓጓዣም ፓርቲው እገዛ ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም ዜጎቹ ፍትህ እስኪያገኙ ድረስ ከጎናቸው እንደሚሆኑ አሳውቀዋል፡፡
በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸው ትክክል ነው ወይ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ‹‹አሁንም ማፈናቀሉ ቀጥሏል፡፡ አሁንም ዜጎች እየተፈናቀሉ ስለመሆኑ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡ አሁንም ሰልፉን የጠራንበት ምክንያት ይህ የማፈናቀል ህገወጥ ድርጊት ባለመቆሙ ነው፡፡ እኛ እየከሰስን ያለነው ባለፈው የመፈናቀል ህገወጥ ተግባር በተፈጸመባቸው ላይ ነው፡፡ የቡለን ወረዳ ቀኑን ጠቅሶ ‹‹ስለምትፈናቀሉ ልቀቁ!›› ያለበትን ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያዎች በመረጃነት ይዘናል፡፡ ይህ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ማንሳት ደግሞ ዋነኛው ስራችን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም ‹‹አሁን ይህ ድርጊት ከወረዳና ከክልሎች አልፎ የመንግስት ፖሊሲ ወደመሆን በመሸጋገሩ በተደራጀና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መታገል አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡›› ብለዋል፡፡ የሰልፉ አላማም በኢህአዴግ የፖሊሲ ችግር ላይ መሆኑን የገለጹት የህዝብ ግንኙነቱ ‹‹ኢህአዴግ መሬት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ንብረት ነው፡፡›› በሚል ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር መብታቸውን ስለገደበና በዚህ የተሳሳተ ፖሊሲ ኢትዮጵያ እንደ አገር ትልቅ ችግር እየገጠማት በመሆኑ ችግሩ ከሚደርስባቸው ዜጎች ጎን በመሆንና ሌላውን ህዝብ በማንቀሳቀስ ኢህአዴግ ሃገር የማስተዳደር አቅምም ሆነ ችሎታ እንደሌለው በማጋለጥ ስልጣኑን እንዲለቅ ግፊት ለማድረግ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ለነገረ ኢትዮጵያ አስታውቀዋል፡፡ የክሱን ሂደትም ሚዲያውያና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲከታተሉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
Source: Negere Ethiopia
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11866/
No comments:
Post a Comment