ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ምሁራን መፍለቂያ ለመሆኗ አለም ይመሰክርላታል፡፡ አንቱ የተባሉ ምሁራንን በማፍራት ለዓለም አበርክታለች፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአለም ካሉ ታላላቅ ዩንቨርስቲዎች እና የምርምር ተቋማት እስከ አመራነት ድረስ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን በተሰማሩበት ስራ መስክ የሚያስመዘግቡት ውጤት እና በስራቸው ተሸላሚ መሆን ላነሳነው ሀሳብ ማጠናከሪያነት ያገለግለናል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው ግን ሀገራችን ከእነዚህ ውድ ልጆቿ ተገቢውን ዋጋ አለማግኘቷ ነው፡፡ ሀገራችን የወላድ መካን እየሆነች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ የሚቀነባበር ሴራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ምሁራን መፍለቂያ ብትሆንም ቅሉ በተከታታይ ስልጣኑን የጨበጡት ጭፍን አንባገነኖች በሚያራምዱት አግላይ ምሁር ፖሊሲ ምክንያት እውቀታችሁን እና ገንዘባችሁን በምትወዷት ሀገራችሁ ኢንቨስት አድታደርጉ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው የስደትን መራራ ጽዋ እንድትጨልጡ ተገዳችኋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ ባለፉት 10 አመታት በተቃዋሚዎች መዳከም የሚያታግል ኃይል አጥታችሁ እንደቆያችሁም እናምናለን፡፡
ፓርቲያችን ሰማያዊ እያንዳንዱ ዲያስፖራ ሀገር ቤት ያለውን ዜጋ ያክል የኢትዮጵያዊነት መብት አለው ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ይረጋገጥ ዘንድም አጥብቆ ይታገላል፡፡ በተለያየ ሁኔታና ወቅት አንባገነኖችን በሀገር ውስጥ እንደታገላችሁ እናምናለን፡፡ ለዚህ ትግላችሁና ለከፈላችሁት ዋጋም እውቅና እንሰጣለን፡፡ በስርዓቶቹ ጨካኝ ዱላ እና ሰቆቃ ብዛት ውድ ሀገራችሁን ትታችሁ የሥደትን ኑሮ ትገፉ ዘንድ ቢበየንባችሁም ስለ ኢትዮጵያ ከመብሰልሰል እንዳልዳናችሁና ሀሳባችሁ ሀገር ቤት ስለ መሆኑ መስካሪ አያሻም፡፡
ውድ የሀገራችን ልጆች እናንተ የሰው ሀገር በምታለሙበት በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ኢትዮጵያ የጉልበት ሰራተኛ ሳይቀር ከቻይናና ከህንድ በከፍተኛ ክፍያ እያስመጣች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ስለ መሆኑ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ እንደ ማርዳት ያለ ነው፡፡ ይህ በእውነት ለአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንደ እግር እሳት ያንገበግባል፡፡ ልማታዊ መንግስት ነኝ በሚል የቃላት ጋጋታ ብቻ ከድሃው ወገናችሁ በሚሰበስበው ገንዘብ የሰከረው ጉልበታም መንግስት ዴሞክራሲና ልማት አንድ ላይ አብረው አይሄዱም በሚል ማሳሳቻ በየጊዜው ጉልበቱን እያፈረጠመ የሄደው በአብዛኛው እናንተ ከምትኖሩበት ከምዕራባውያን ሀገራት በሚቀበለው እርዳታ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡
ዳያስፖራው በነጻነት መኖር ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያውቀዋል፡፡ ነጻ ሆኖ መስራት ለሀገር ልማት ግንባታ ያለውን ጠቀሜታም ሀገር ቤት ካለው ህዝብ በተሻለ ሁኔታ ይገነዘባል፡፡ ድህነትና አንባገነንነት ባመጣው ጦስ ኢትዮጵያዊ ክብራችን ተገፎ በየ በረሃው ዜጎቻችን እንደ እንስሳት ሲታረዱ፣ እህቶቻንን በቡድን ሲደፈሩ፣ ወገኖቻችን ልብና ኩላሊታቸው ወጥቶ ለገበያ ሲውል እንደማየት ያለ ዘግናኝ ተግባር ምን አለ?!! ይህ ህገ ወጥ ተግባር ሊፈጸምባቸው አይገባም ብላችሁ ያሳያችሁት ለወገን መቆርቆር ይበል የሚያስብልና ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለን እናምናለን፡፡
በተለይ የሳውዲ መንግስት በዜጎቻችን ላይ የወሰደባቸውን ህገ ወጥ ተግባር ለማውገዝ ያደረጋችሁትን ርብርብና ለሀገራችን በአንድ ሆ ብላችሁ መቆማችንሁን በድጋሚ እያመሰገንን አንባገነኑን ኢህአዴግ ለመታገል በሚደረገው ትግል አጋራነታችሁን ስለምንገነዘብ ከጎናችን በመሆን ለምታሳዩት ውጣ ውረድ እውቅና እንሰጣለን፡፡ ከዚህ በፊት ያሳያችሁትን የትግል ቁርጠኝነት እንደምትደግሙት በማመን ያላችሁን የገንዘብ አቅም፣ የእውቀትና የተሰሚነት ሚና በመጠቀም የአንባገነኑን ስርዓት አፈና በማጋለጥ ከጎናችን እንድትሰለፉ ስንል እንጠይቃለን፡፡ ዳያስፖራው ያለውን የኢኮኖሚ ነጻነት፣ የሚዲያ ነጻነትና፣ ሀገር ቤት ካለው ጋር ሲነጻጸር ያለው የለሻለ የትምህርት ደረጃና ልምድ፣ እንዲሁም በእርዳታ ሰጭ ሀገራት ያለው የተሰሚነት አቅም ተጠቅሞ ሀገር ቤት ያለውን ትግል በማገዝ ነጻ የምንወጣበትን ቀን ሊያፋጥን እንደሚገባ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
ፓርቲያችን የህግ የበላይነትን ለማስፈን ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጋ ያሳተፈ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ዘርፈ ብዙ ትግል ውስጥ ደግሞ ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ‹‹የተነጠቁ መብቶቻችን እናስመልስ›› በሚል መሪ ቃል ታላቅና ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሂዳል፡፡ በመሆኑም ይህን ሁሉን አቀፍ የሆነ ሰላማዊ ትግል በሞራል፣ በእውቀትና በምክር፣ እንዲሁም በገንዘብ በማገዝ የትግሉ አጋር ትሆኑ ዘንድ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
ከአገራችሁ እርቃችሁ የምትኖሩ በመሆናችሁ አዲስ አበባ ውስጥ አብራችሁን ባትቀሰቅሱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ባትወጡና ባትታሰሩም መረጃውን ለዓለም ህዝብ በማድረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወታችሁ ቆይታችኋል፡፡ በዚህ ሰልፍም አገር ቤት ለሚኖሩ ቤተሰብ፣ ጓደኛ እንዲሁም ሌላው ህዝብ በስልክ፣ በማህበራዊ ድህረ ገጽና የተለያዩ መልዕክት ማስተላለፊያዎች በመጠቀም ህዝቡን የማነቃቃት አቅምና አጋጣሚ ተጠቅማችሁ በትግል ጉዟችን ተሳታፊ እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ኑ ራሳችንን ነጻ በማውጣት የአገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11945/
No comments:
Post a Comment