አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
የእሪታ ቀን በሚል መሪቃል በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስመልክቶ በተለይም ከተማዋን ወደ ማህበራዊ ቀውስ እየመሯት የሆኑትን የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍ ህዝቡ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ መጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ለማካሄድ ያቀደውን ሕዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ አስመልክቶ በህዝብ መገናኛ ብዙሃን ይፋ ካደረግንበት ቀን ጀምሮ የሚጠበቅብንን ህጋዊ የማሣወቅ ሥራዎችን ስንሠራ የቆየን መሆኑና መድረስ ለሚገባው አካል ሁሉ በተገቢው ሁኔታ ማሳወቃችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ጥሪው ለሕዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከተው የሠላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል በህግ የተቋቋመበትን ኃላፊነት በመዘንጋት ለጠየቅነው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ህግ በመተላለፍ ክልከላ አዘል ደብዳቤ ልኳል፡፡ ሆኖም የአንድነት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል የላከው ደብዳቤ በአዋጅ ከተደነገገ ህግ ጋር የሚጣረስና የዜጎችን መብት የሚያፍን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአንድነት ምክር ቤት ግንዛቤ በመያዝ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በማውጣት ለመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
የአቋም መግለጫው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሠላማዊ ሠልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ፓርቲያችን መጋቢት 15 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ላስገባለት የሠላማዊ ሠልፍ እውቅና መጠየቂያ ደብዳቤ መጋቢት 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በሠጠው ምላሽ የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄውን አለመቀበሉን ማሳታወቁንና ለዚህ ደብዳቤ የላክንለትን መልስ አልቀበልም በማለት የወጣ ነው፡፡
1. የሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍሉ ለሚቀርብለት የሠላማዊ ሠልፍ የእውቅና ጥያቄ ህገ መንገሥቱንና አዋጅን በሚቃረን መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ቢሆንም በማን አለብኝነት አዋጁን በጣሰ መልኩ ምላሽ መስጠቱን አልተቀበልነውም፡፡
2. ህዝብን በተለይም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች እንዲያገለግል ኃላፊነት የተሰጠው አካል ህጋዊ እውቅና ካገኘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚቀርብለትን ደብዳቤ አልቀበልም ማለቱም ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ግለሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ወስነናል፡፡
3. ለህግና ህገ መንግሥታዊነት ጥብቅና ለመቆም ቃል የገቡት የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች ህግን አክብሮ እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ፓርቲያችን ጎን እንዲቆሙ እንጠይቃለን፡፡
4. አዋጁን ያፀደቀው ፖርላማ ለሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄያችን የተሰጠን ምላሽ ህገ ወጥ መሆኑን እንዲመለከት አባሪ በማድረግ ለላክንለት ደበዳቤ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
5. ለመጋቢት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓም የጠራነው ‹‹የእሪታ ቀን›› ሠላማዊ ሠልፍ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የቀረበ በመሆኑና በህገ ወጥ አሰራር ሊታጠፍ ስለማይችል ምክር ቤታችን ሙሉ እውቅና ሰጥቶታል፡፡
6. በሠላማዊ ሠልፍ ለሚደርስ ማናቸውም አይነት ኪሳራዎች፣ ጉዳቶችና መጉላላቶች ተጠያቂው ህጋዊ ቢሮ ይዞ ህገ ወጥ አሰራር የሚከተለው አካል መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
7. አሁን የገጠመን የመሠረታዊ አገልግሎቶች ችግር የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ ችግር የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ የገጠመውን ስቃይ እሪ በማለት እንዲያሰማ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መድረኩን ያዘጋጀ ስለሆነ ጥያቄያችሁን ለመንግሥት እንድታስተላልፉ የአዲስ አበባ አንድነት ም/ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የቅስቀሳ ስራ ከዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ የሚጀመር መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ የዘመቻ ስራ ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ከወዲሁ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ ውጭ በቅስቀሳው ስራላይ ለሚገጥመን ህገወጥ ችግር መንግሥት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ እንገልፃለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓም
አዲስ አበባ
አዲስ አበባ
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11657/
No comments:
Post a Comment