በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሚመራው መንግስት ከናቅፋ እስከ ጉና ተራራ ያሉ ምሽጎቻቸውን ከሰማይ በጦር አይሮፕላን፣ ከምድር እሳት በሚያዘንቡ ቢ.ኤሞችና መድፎች ሳያቋርጥ ቢደበድብም፤ በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ከቀን ወደ ቀን ግዛታቸውን እያሰፉ የተጠናከሩት ‹‹ወንበዴዎች›› ራስ ምታት ሆነውበታል፡፡ የኤርትራ ‹‹ነጻ አውጪ›› ቤዝ-አምባው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለጥቃት የመጋለጥ እድሉ አናሳ በሆነው የሳህል በረሃ በመሆኑ አብዛኛው የአመራር አባል መሸሸጊያው አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የወያኔ መሪዎች ምሽጋቸው እንደ ሳህል ምቹ ባለመሆኑ፤ በርካታ ክፉ ቀናትን ያሳለፉት በተራራማ አካባቢዎች በሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ገዳማት ውስጥ ተደብቀው እንደሆነና ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሲፈልጉም የመነኮሳቱን አልባሳት ይጠቀሙ እንደነበረ በትግሉ ዙሪያ የተዘጋጁ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በተለይም ታጋይ መለስ ዜናዊ፣ አባይ ፀሀዬ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋን…. የመሳሰሉ የአመራር አባላት የገዳማቱ ቤተኛ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነገርም አንድ ታሪክ አለ፤ የመንግስት ፀጥታ ሰራተኞች ሁለት የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች በትግራይ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ተመሳስለው መሸሸጋቸው መረጃ ይደርሳቸውና በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮችን በመላክ ዙሪያ ከበባ ያደርጋሉ፡፡ ይሁንና መደበቂያ በመስጠት የረዷቸው መነኮሳት ሁለቱን ታጋዮች ‹‹ወይባ›› በመባል የሚታወቀውን ረጅሙን ቀሚሳቸውን አልብሰው እና ቆብ አስደፍተው ከአካባቢው በማሸሽ ይታደጉዋቸዋል፡፡ የታሪኩ ባለቤት መለስ ዜናዊ እና አባይ ፀሀዬ ነበሩ፡፡ በርግጥ እነዚህ የ‹‹ወንበዴ›› መሪዎች ‹በእንዲህ አይነቱ ከመርፌ አይን እጅግ በጠበበ ዕድል ህይወታችን ከሞት መንጋጋ ተርፎ ኮለኔል መንግሥቱን በጓሮ በር ወደ ዜምባብዌ ሸኝተን በትረ-መንግሥቱን ለመጨበጥና ለሃያ ምናምን ዓመታት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር አንቀጥቅጠን ለመግዛት እንበቃለን› የሚል ጠንካራ እምነትና የእርግጠኝነት ስሜት በወቅቱ ነበራቸው ብሎ ማሰብ ለእነርሱም ቢሆን እጅግ አዳጋች ይመስለኛል፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡
‹‹ማሕበረ-ቅዱሳን››
መለስ ዜናዊና ጓዶቹ በለስ ቀንቷቸው ባልጠበቁት ፍጥነት የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር እየተቆጣጠሩ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሲያፋጥኑ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ሰብሳቢበት፣ በደህንነት ሠራተኞች እና የኢሠፓ ካድሬዎች ገፋፊነት ትምህርታቸውን አቋርጠው ለወታደራዊ ስልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴና የጦር ማሰልጠኛ ከተቱ፤ ዩኒቨርሲቲውም ተዘጋ፡፡
…ከመላው ዘማቾቹ አስራ ሁለት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ፣ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ‹ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን› በመሄድ፣ ከመዓቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በፀሎት መማፀን የህይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት፣ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹ማህበረ ሚካኤል› ብለው የሰየሙትን የፅዋ ማህበር መሠረቱ፡፡ …ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1977 ዓ.ም በ‹ፓዊ መተከል› ዞን የተደረገውን ‹የመልሶ ማቋቋም› ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የፅዋ ማህበራት ጋር በመዋሀድ የዛሬውን ‹ማህበረ-ቅዱሳን› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነብይነት ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment