ግፍ ከበዛበት ወህኒ የአክብሮት ስላምታየ ይድረሳችሁ! (ነብዩ ሲራክ፣ ከሳውዲ አረብያ ውህኒ ቤት)
እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ለአፍታ ያህል እድሉን አግኝቼ ወህኒ የመውረዴን እውነታ ላስረዳችሁ ግድ አለኝ ። ዛሬ አስረግጨ የምነግራችሁ ወህኒ የመውረዴ ምክንያት ሚስጥር ግማሽ እድሜዬን ህግና ስርአቷን አክብሬ የኖርኩባትን የሳውዲ አረቢያን ህግ ተላልፌ አይደለም! የስደተኛው ጉዳይ ያገባኛል በሚል የማቀርበው መረጃ ቅበላዬ የማይመቻቸው ፣ ያመማቸው ከተሴረውና እየተሴረ ካለው እገታ ጀርባ ስለመኖራቸው አልጠራጠርም ። … ዛሬ በዚህ ዙሪያ ብዙ አልልም!
አላወቁትም እንጅ ክፉዎች ጠቅመውኛል ፣ ያላየሁትን እንዳይ አድርገውኛል። መንገዱ የከፋ ቢሆንም በወሰዱኝ መንገድ ተመርቼ እሰማው የነበረውን የወገኖቼ የወህኒ የከፋ ኑሮና ህመም ፣ በተቆርቋሪ ጠያቂ ማጣት ፣ በፍትህ መነፈግ እየሆኑ ያሉትን ከመስማት ማየት ማመን ነውና በአካል ማየት ችያለሁ !
ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት በግፍ ለተደበደበው፣ ሁለት አይኑን ላጣውና “አይሆኑ ከሚሆን ቢሞት ይሻላል” ተብሎ የፎቶ መረጃው ሳይቀር በእጀ የገባውን ወጣት ምንዱብ የወህኒ ህይወትን ተጨባጭ ታሪክ ከአይን እማኞች ቃርሜያለሁ! እሱም ያለው ከታሰርኩበት የቅርብ ርቀት ነው ።… አትጠራጠሩ አገኘውም ይሆናል !
በዚህ የጭንቅ ሰአት ከእኔና ከቤተሰቦቼ ጎን ሆናችሁ አለኝታነታችሁን ለገለጻችሁልኝ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው ! ዛሬ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ አንገባም ። በመላ አለም የምትገኙ ወገኖቼ ያሳያችሁኝ ድጋፍና መቆርቆር ከጨለማው ቤት ደርሶኝ ጽናት አጎናጽፎኝ ሰንብቷል። ይህም በአረብ ሃገር ስደተኛ ዙሪያ ሳቀርበው ለነበረው መረጃ ያገኘሁት ክብርና ሞገስ ሆኖ መከራውን አስረስቶኛል: ) ምስጋናዬ አይለያችሁ!
ወገኖቸ ወዳጆች ፣ ዛሬ ሰላም መሆኔን ብቻ ተረዱ ብየ እንጅ በሰፊው ስለሚሆነው አቅም በፈቀደ መጠን እናወራለን ! ዝምታው ከናፈቅኳቸው ልጆቸ ፣ ከቤተሰቦቸና ከእናንተ ጋር የሚያደርሰው መንገድ ውል እንዲይዝ የሚደረገው ሙከራ ውል እንዲይዝ የሚተጉ ወገኖችን ሂደት ላለማደናቀፍ ብቻ ለመረጋጋት ሲባል ብቻ ነው !
በጨለመው የሳውዲ ወህኒም ይነጋል ፣ በንጋቱ ጮራ ታግዘን የምናወጋው የማለዳ ወግ ናፍቆኛል: ) ይህን ለማድረግ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ደግሞ ልቤ ብርቱ ነው …
ሰላም ለሁላችሁ !
ነቢዩ ሲራክ
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት
ከአንዱ የሳውዲ ወህኒ ቤት
http://ecadforum.com/Amharic/archives/11664/
No comments:
Post a Comment