የሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ-ምህረት የመጀመሪያ ወር ተጠናቅቋል፤ አዳዲስ ክስተቶችም ታይተዋል፤ ያለፉት አስራ ሁለት ዓመታትን በጃንሆይ ቤተ-መንግስት ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ በኦህዴዱ ሙላቱ ተሾመ መተካታቸው አንዱ ነው፡፡ አባይ ፀሀዬና ዶ/ር ካሱ ኢላላም ከበረከት ስምዖንና ኩማ ደመቅሳ በተጨማሪ በሚኒስትር ማዕረግ የኃ/ማሪያም ደሳለኝ ‹‹የፖሊሲና ጥናት ምርምር›› አማካሪ ሆነው መሾማቸው ሌላው ነው (በነገራችን ላይ ሹመቱን እንደተለመደው አይቶ ችላ ብሎ ለማለፍ የማያስችሉ ሶስት ምክንያቶች አሉ፤ የመጀመሪያው በሀገሪቱ ለአንድ የሥራ መደብ አራት ሚንስትር ተሹሞ አለማወቁ ሲሆን፤ ሌላው ተሿሚዎቹ፣ ኢህአዴግን ከመሰረቱት አራት ፓርቲዎች በኮታ የተወጣጡ መሆናቸው ነው፡፡ ሳልሳዊውና አስገራሚው ደግሞ ሰዎቹ ፖለቲከኞች እንጂ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ምሁራን አለመሆናቸው ነው)
እነዚህ ሁሉ በግልፅ የሚታወቁ የዓመቱ መጀመሪያ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለስርዓቱ ቅርበት ካላቸው ምንጮቼ ባገኘሁት መረጃ መሠረት፣ በቅርቡ ‹ሚዲያ›ን እና ‹የይቅርታ ስነስርዓት›ን የተመለከቱ አዳዲስ አዋጆች በተወካዮች ም/ቤት ለመፅደቅ ተዘጋጅተዋል፡፡ በተለይም ‹ሚዲያው›ን የሚመለከተው አዲሱ ህግ፣ ከአምስት ዓመት በፊት ተግባር ላይ የዋለውን የ‹‹ፕሬስ አዋጁ››ን የአፋና ጉልበት ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ፣ የነበረው አንፃራዊ ጭላንጭል ጭራሽ ሊዳፈን እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ‹‹የይቅርታ አዋጁ››ም ቢሆን ጥቂት የአገዛዙ ጉምቱ ባለስልጣናት ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላትና አንዳንድ የግል ጋዜጠኞች ብንታሰርም በይቅርታ እንፈታለን በሚል ግንባሩን እየተፈታተኑ ነው›› ሲሉ ደጋግመው መደመጣቸውን፣ ከአዲሱ ‹‹የይቅርታ አሰጣጥ እና አፈፃፀም ሥነ-ሥርአት አዋጅ›› ጋር ካያያዝነው፣ አንቀፆቹ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ መገመቱ ብዙ ከባድ አይሆንም፡፡
ለማንኛውም ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጉልበታም በመሆን ቀጣዩን ምርጫ በስኬት ለማለፍ፣ በያዝነው ዓመት የተለያዩ አፋኝ ህጎችን በማውጣት ፓርቲዎቹን የማዳከም ስራ ለመስራት በተለየ መልኩ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡ በአናቱም ኃ/ማርያም ደሳለኝ-ከመንግስት፣ ከፓርቲውና ከውስን የግል ጋዜጠኞች፤ ደመቀ መኮንን-ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ሽመልስ ከማል -ከኢዜአ ጋር ያደረጓቸው ቃለ-መጠይቆችም ይህንን መረጃ የሚያጠናክር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ተጠየቅም አገዛዙ በቀጣይ ሊኖረው የሚችለውን ባህሪ እና ‹አምስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ›ን አስቀድሞ ለማሸነፍ እየቀመረ ያለውን ሴራ መጠቆም ነው፡፡
የባለስልጣናቱ አንደበት
ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያምና ምክትሉ ደመቀ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ላይ፣ በስሱም ቢሆን ከጀርባቸው ያደፈጡትን አንጋፋ ታጋዮች ቀጣይ ‹‹የፖለቲካ ሴራ›› (Political Conspiracy) አርድተውናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሁለቱ መሪዎች በዋናነት እንዲያተኩሩ የተደረገው በአራት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በግንባሩ ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩን መካድ፣ አመቱን ሙሉ ‹የመለስ ራዕይ› እየተባለ የተዘመረለትን ‹እሳት ማጥፊያ› ፕሮፓጋንዳ ማስተባበል፣ የሙስና ክሱን ሂደትና ውጤት መሸፋፈን እንዲሁም ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ማስፈራራት የሚሉ ናቸው፡፡ በአዲስ መስመርም እነዚህን አራት አጀንዳዎች ነጣጥለን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ክፍፍሉን በተመለከተ
ከመለስ ህልፈት ማግስት አንስቶ በግንባሩ ግልፅ ክፍፍል መከሰቱ የአደባባይ ሀቅ ቢሆንም፣ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ‹‹ፓርቲዎ ውስጥ ክፍፍል አለ ይባላል፤ የኃይል አሰላለፍ እየተጠበቀ ነው የሚኬደው የሚባሉ አሉባልታዎች ይሰማሉ፣ የፓርቲዎ ጤናስ እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት፡-
‹‹በፓርቲዬ ውስጥ ክፍፍል አለ የሚለው ጥያቄ የምኞት ነው፤ ብዙ ምኞቶች ሲሰሙ ነበር፤ ምኞት አይከለከልም፡፡ ስለዚህም ምኞት ይኖራል የሚል ሃሳብ ከማቅረብ በዘለለ እውነት ስለሌለው ምኞት ነው ብሎ ማለፍ ነው›› በማለት አስተባብሎ ሲያበቃ፤ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ተገልብጦ ‹‹አሁን በቅርቡ እንደደረስንበት አንዳንድ ጊዜ በየቦታው ደባ የሚሰሩ ጥቂት የመሥሪያ ቤት ሰራተኞች አሉ›› ብሎ የራሱ ሰዎች በመንግስቱ ላይ እያሴሩበት እንደሆነ በመግለፅ ከላይኛው ንግግሩ ጋር መጣረሱ፣ በርግጥም የተጠቀሰው ችግር መኖሩን ለመረዳት አያዳግትም፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተም ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ አጠንክሮ ጠይቆት ያስተባበለበት መንፈስም ለመሸሸግ የፈለገው ጉዳይ እንዳለ የሚያሳብቅ ይመስላል፡፡
‹‹አንድ ግልፅ መሆን ያለበት እንደ አቶ መለስ ያለ ታላቅ መሪ፣ ታግሎ የሚታገል ጠንካራ መሪን ማጣት ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ጉድለቱ እንዲሁ ዝም ተብሎ እዚያና እዚህ በዘመቻ የሚሞላ ጉዳይ አይደለም፡፡ …ስለዚህም ሁለት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ኃላፊዎችን በመሰየም ክላስተር እንዲያስተባብሩ ማድረግ ያለመተማመን መገለጫ አይደለም፡፡››
የሁለቱ ሚኒስትሮችን ያልተጠበቀ ቃለ-መጠየቅ መግፍኤ ለመረዳት በተለይ ደመቀ መኮንን ለቀረቡለት ጥያቄዎች የሰጠውን ምላሾች በጥልቅ መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ተከስቶ የነበረውን መከፋፈልም ሆነ ‹ፓርቲው በጥቂት የህወሓትና የብአዴን ታጋዮች ነው
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የሚሽከረከረው› መባሉን ለማስተባበል የሄደበት መንገድ፣ ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ የሚከራከርባቸውን እምነቶቹን ጭምር እስከመናድ የደረሰ ነውና፡፡ ወይም እንዲንድ ታዝዟል ያስብላል (በነገራችን ላይ ከምንጮቼ ባገኘሁት መረጃ እነአባይ ፀሀዬና በረከት ስምዖንም ከመጋረጃው ጀርባ የሚሰራ ኃይል መኖሩን ማስተባበል ይፈልጋሉ፡፡ በተለይም ‹‹በነፃነት እንዲሰሩ አመቻቹላቸው›› እያሉ የሚወተውቷቸውን ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ማሳመኑ ከባድ ሥራ እንደሆነባቸው ሰምቻለሁ፡፡
የሰሞኑ የቃለ-መጠይቅ ጋጋታም ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣም ለደመቀ መኮንን ያቀረባቸው ጥያቄዎች ከቀደመው ታሪኩ አኳያ ሲመዘን የግል እምነቱ አለመሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡ ‹‹ጋዜጣው እስከአሁን ያልነበረውን ‹የኤዲቶሪያል ነፃነት› ዛሬ አግኝቶ ነው ሰውየውን እንዲህ ያፋጠጠው›› የሚል ተከራካሪ ካልቀረበ ማለቴ ነው፡፡ ምናልባትም ጉዳዩን በሌላ አውድ እንየው ከተባለ ደግሞ የሚያያዘው፣ የድርጅቱ አመራሮች አልፎ አልፎ ህዝብ ዘንድ የደረሱ እውነታዎችን፣ በራሳቸው ጋዜጠኞች እንዲጠየቁ በማድረግ ለማስተባበል ከሚሞክሩበት የቆየ ልማዳቸው ጋር ብቻ ነው፡፡ በመስከረም 22፣ 23 እና 24 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው የ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በተስተናገደው የደመቀ መኮንን ቃለ-መጠይቅ ላይ የተነሱትን ጥያቄዎች ብንመለከት ይህንኑ ያረጋግጡልናል፡፡ ‹‹ፓርቲው በጥቂት ሰዎች ስር ስለመውደቁ፣ ከመንግስት ኃላፊነት የተነሱ ባለስልጣናት በፓርቲው ውስጥ ስራ-አስፈፃሚ ሆነው ስለመቀጠላቸው፣ መተካካቱ የቦታ መቀያየር ብቻ ስለመሆኑ፣ ሥራ የማይሰሩ ደካማ መሆናቸውን በተወካዮች ም/ቤት ጭምር የተረጋገጠባቸው ከፍተኛ አመራሮች ዛሬም በኃላፊነት ቦታ ላይ ስለመቀመጣቸው፣ በብልሹ አሰራር /በሙስና/ የተጠየቁ ባለስልጣናት ጥቂት ብቻ መሆናቸው፣ በአቅም ማነስ የሚነሱ ኃላፊዎች ወይ ከነበሩበት የተሻለ አሊያም ተመጣጣኝ በሆነ ደረጃ ስለመመደባቸው፣ አንድ ጊዜ የላይኛውን የስልጣን እርከን የተቆናጠጠ ባለስልጣን ከፓርቲው ቁልፍ አመራሮች ጋር ካልተጋጨ በቀር አቅም ባይኖረውም እንደማይሻር፣ ለፓርቲው መስራቾችና እስከአሁንም ወሳኝ ለሆኑት አመራሮች ታማኝ የሆነ ኃላፊ ምንም አይነት ድክመትና ወንጀል ቢፈፅምም በስልጣን መቆየት መቻሉን፣ የሁለቱ ተጨማሪ ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች ሹመት በአራቱ የብሔር ድርጅቶች መካከል ያለውን አለመተማመን ስለማሳየቱ፣ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል አለመሆናቸውን፣ መለስ በሃያ ሁለት የሥልጣን ዓመታቱ ተተኪ ማፍራት አለመቻሉን፣ ‹የመለስ ራዕይ› የሚባል ነገር አለመኖሩን…›› እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ባልተለመደ ድፍረት የጠየቀው መንግስታዊው ዕድሜ ጠገብ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ነው)
ቃለ-መጠየቁ ከእነዚህ በተጨማሪም ቀጣዩን የኢህአዴግ አቅጣጫ አመላክቷል፡፡ የሆነው ሆኖ ክፍፍሉንና ከጀርባ ሆነው ያሽከረክራሉ የሚባሉትን አንጋፋ የአመራር አባላት አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ከሰጠው ምላሽ ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡-
‹‹ፓርቲው አንድ ሰው፣ ሁለት ሰው፣ ሶስት ሰው እጅ ጠምዝዞ ‹ይሄን አድርጉ› በሚል አንዳችም ጉዳይ የሚያስፈፅምበት አይደለም፡፡ …ኢህአዴግ በጥቂቶች የሚመራ ድርጅት አይደለም፡፡ …ጥቂት ግለሰቦችን በተለየ ሁኔታ የሚያይ፣ በእነርሱም ስር የሚሆን አይደለም፡፡ የጥቂቶች ነው የሚለው ከእውነት የራቀ ነው፡፡ …ማንም በራሱ ተቆጥሮ በተሠጠው ሥራ ሊወስን፣ ሊመራና ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡ በድርጅታዊ ዲሲፒሊንና አሰራር፣ የግልና የጋራ አሰራር በሚዛን ተቀምጦ በንቅናቄ የሚመራ እንጂ በግለሰቦች አይደለም የሚለው ቢሰመርበት ጥሩ ነው፡፡››
በርግጥ ይህንን ያነበበ ‹‹ሰውየው ስለየትኛው ኢህአዴግ ነው የሚያወራው?›› ቢል ላይፈረድበት ይችላል፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱ የታሪክ ንባብም ሆነ የቀድሞዎቹ ስዬ አብርሃ፣ አለምሰገድ ገ/አምላክ፣ አውዓሎም ወልዱ፣ ገብሩ አስራት፣ አረጋሽ አዳነ፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ሀሰን አሊ፣ አልማዝ መኩን የመሳሰሉት የአመራር አባላት የነገሩን ‹ድርጅቱ በጣት በሚቆጠሩ ሰዎች ፍቃድ የሚያድር› መሆኑን ነው፡፡ ለነገሩ ራሱ ደመቀም ቢሆን ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ለመግባት ህወሓት በር ዘግቶ ብቻውን መምከሩንም ሆነ የግንባሩን አባል ድርጅቶች ነፃነት እንዳሻው መጋፋቱን አምኖ መቀበል ባይፈልግ እንኳን፣ በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ከሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጎንደር መሬት ላይ የተላለፈው ውሳኔ በምን መልኩ እንደነበረ ሊክደው አይችልም (በነገራችን ላይ በወቅቱ የአማራ ክልል አስተዳዳሪው አያሌው ጎበዜ ምክትል የነበረ በመሆኑ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጎንደርና ትግራይ አካባቢ፣ የሚወራበትን ውንጀል በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)
የሰውየው መከራከሪያ ግን እውነት አለመሆኑን ‹ፍትህ›ና ‹ልዕልና› ጋዜጦች፤ ‹አዲስ ታይምስ›ና ‹ፋክት› መፅሄትን ጨምሮ የምዕራብ ሀገራት ብዙሃን መገናኛ እና ድርጅቱን በቅርብ የተከታተሉ ምሁራን በተለያየ ጊዜ ማስረጃ በማጣቀስ ደጋግመው ስላቀረቡ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልገዋል ብዬ አላስብምና ወደ ቀጣዩ ጉዳያችን አልፋለሁ፡፡
‹‹መተካካት›› ሲባል…
በአንድ ወቅት አቶ መለስ ብዙ ብሎለት የነበረው የመተካካት ዕቅድ ‹‹ቦታ ከመቀያየር ያለፈ አዲስ ፊት አላመጣም›› መባሉን በተመለከተ፣ ደመቀ መኮንን የሰጠውን ምላሽ፣ ከተለያየ አውድ ካየነው ከላይ የተጠቀሰውን ክፍፍል በሌላ በኩል ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም መለስ በህይወት በነበረበት ዘመን ጉዳዩን አስመልክቶ የነገረን ‹መተካካቱ ከላይ ያሉትን ነባር የአመራር አባላት፣ በየተራ በጡረታ በማሰናበት አዲሱን ትውልድ (አዲስ ፊት) ወደመሪነት ማምጣት ነው› የሚል እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ደመቀ መኮንን ደግሞ በግልባጩ እንዲህ ይላል፡-
‹‹አዲስ ፊት ሲባል የማናውቀው ሰው ከጨረቃ ይምጣ? የሚመራው እኮ አገር ነው፡፡ አንድ ሰው አንድ ቦታ ላይ ሆኖ ሥራውን እየተወጣ፣ ሌላውንም እያበቃ ሥርዓቱ መቀጠል አለበት፡፡ በጣም የሚታወቅ ህዝባዊ አገልግሎት ላይ ያለ ሰው፣ ከያዘው ኃላፊነት ሌላ፣ በሌላ ጊዜ ሌላ ተክቶ ሊቀርብ ይችላል፡፡ አዲስ ፊት የለም፤ የማናውቃቸው ሰዎች ይምጡ ማለት፣ ሀገር የሙከራ ቦታ ይሁን ማለት ነው፡፡››
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ የሚደክመው በረከት ስምዖን፣ አባይ ፀሀዬ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ሽፈራው ጃርሶ፣ ካሱ ኢላላ፣ ሙላቱ ተሾመን… የመሳሰሉ አንጋፋ መሪዎች ከዚህ ቀደም ለአባላቶቻቸው የገቡትን ቃል ጠብቀው በክብር ከመሰናበት ይልቅ ስልጣን መቀያየራቸውን ለማስተባበል ይመስለኛል፤ በርግጥ ጉዳዩን ከለጠጥነው ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአንጋፋዎቹ መካከልም ሊሆን ይችላል እያለን ይሆናል፡፡ ይሁንና ሰውየው ያስተባበለበት መንገድ ግን በውስጡ ካለው እውነታ ጋር የተቃረነ በሚመስል መልኩ
የመተካካቱ አንድምታ የተቀየረው በመካከል የተፈጠረውን የኃይል ልዩነት አርግቦ፣ ስርዓቱ ከገጠመው መንገራገጭ ወጥቶ በሁለት እግሩ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንዲቀጥል ለማስቻል መሆኑን ፍንጭ ይሰጣል፡፡
‹‹መተካካት ግለሰብን አይደለም የሚተካው፤ የስርዓት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ነው!››
ይህ ሁናቴ በደንብ የሚፍታታው አቦይ ስብሃት ነጋ በተለይ ህወሓት ውስጥ የተካሄደው መተካካት ከተፈጠረው ልዩነት ጋር ተያይዞ መሆኑን ለ‹‹ውራይና›› መፅሄት የሰጡትን ቃለ-መጠየቅ ስናነብ ነው፡-
‹‹ጉባኤው ከማዕከላዊ ኮሚቴ ለተሰናበቱ ሰዎች ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው፣ አሰራር ለምን እነሱን በሌሎች መተካት እንዳስፈለገ፣ ተራ በተራ እየጠቀሰ አስተያየት (ማብራሪያ) መስጠት ነበረበት፡፡ ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከተሰናባቾቹ መካከል ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ መቆየት (መቀጠል) የሚገባቸው በተገኙ ነበር፡፡ ከተመረጡት ውስጥ ደግሞ መሰናበት (በሌላ መተካት) የሚኖርባቸው ሊገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ አካሄዱ ስህተት ስለሆነ ውጤቱም እንደዚያው ሊሆን ችሏል፡፡ እነማን መሰናበት፣ እነማን መቆየት እንደነበረባቸው በዝርዝር ስም ጠርቼ መናገር እችል ነበር፡፡ ግን ምንም ለውጥ ስለማያመጣ ስም መዘርዘሩ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡››
የ‹‹ራዕዩ›› ጉዳይ…
በፋክት መፅሄት ቁጥር 5 ላይ ኢህአዴግ ‹የመለስ ራዕይ› እያለ ይደሰኩርለት የነበረውን አጀንዳ በወራት ጊዜ ውስጥ ገልብጦ በማጠቋቆር ሊቀየረው መዘጋጀቱ ተጠቅሶ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በደመቀ መኮንን ቃለ-መጠይቅ ላይም፣ መለስ ሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ተገምግሞ መንግስታዊ ተቋማትንና የልማት ዕቅዶችን በአግባቡ መከታተልና መቆጣጠር አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
‹‹ያለፉት ዓመታት ሥራዎቻችንን ስንገመግም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ብዙ ሥራ ተሸክመው ይሰሩ በነበረበት ዋና ዋና የልማት ሥራዎቻችን ላይ በማተኮር አንዳንድ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የልማት መስኮችን በሚፈለገው ደረጃ ያለመፈተሽ፣ በዝርዝር ዕቅድ ግምገማና ድጋፍ ያለማድረግ ክፍተቶች እንደነበሩ እንደ ችግር በጋራ ያገኘናቸው ነጥቦች አሉ፡፡››
እንዲያ ሀገር-ምድሩ ‹ካልዘመረለት ተደፍረናል!› ሲሉለት የነበረው ‹‹የመለስ ራዕይ››ም ቢሆን የኢህአዴግ እንጂ የመለስ አለመሆኑን እየነገሩን ነው፡፡ አቶ ደመቀም፣ መለስ የነበረው ‹‹ራዕይ›› ሳይሆን ኃላፊነት ነው ወደ ማለቱ አዘንብሏል፡፡
‹‹ይሄን የዕድገት መንገድ ከኢህአዴግ አባላትና ከመሪዎቹ ጋር በመሆን በግንባር ቀደምነት የመሪነት ቁልፍ ሚና የተጫወቱ መሪ ናቸው፡፡››
በጥቅሉ በወቅታዊው የድርጅቱ ፖለቲካዊ አተያይ ‹‹የመለስ ራዕይ›› የሚለው ሀረግ ከየት እንደመጣ የተተነተነበትን አውድ ለመረዳት ከጋዜጣው ላይ አንድ ተጨማሪ ጥያቄና መልስ እንደወረደ ልጥቀስ፡-
‹‹አዲስ ዘመን፡- በየዘርፉ ራዕያቸው ተብለው የሚነገሩት መልእክቶችና መሪ ቃሎች ጋር በተያያዘ የተለጠፈባቸው ራዕይ እንዳለ ነው የሚነገረው፤ አገሪቱን ከመሩበት 22 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ምናልባት አንድ ጊዜ በንግግር መሀል የተናገሯት ወይም ለጋዜጠኞች የሰጡት ምላሽ ራዕይ ተደርጎ እየቀረበ ነው ስለሚባለውስ?
‹‹አቶ ደመቀ፡- እነዚያ መልዕክቶች ያንን ራዕይ የሚገልፁ፣ የሚያስታውሱ ምልዕክቶች ናቸው፡፡ ከማንኛውም ጉዳይ ጋር የተያያዙ መልዕክቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚያ ያንን ትልቁን ራዕይ የሚመግቡ መልዕክቶች እንደሆኑ አድርጎ መመልከት ይቻላል፡፡››
ይኸው ነው፤ በቃ፡፡ መለስ ራዕዩን በጥሩ ቋንቋ ከመግለፅ ባለፈ የብቻው የሆነ ነገር የለውም፡፡ በክፍፍሉ ወቅት ከ‹አዲስ አበባው-ህወሓት› ጎን የተሰለፉት አቦይ ስብሃት ነጋ በጉባኤ፣ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዲሁም አርከበ እቁባይ በህወሓት ጉባኤ ላይ የመለስ ‹ራዕይ› የሚባል ነገር አለመኖሩን በመግለፅ፣ በወቅቱ በአሰላለፍ የተመሳሰሉት ‹የመቀሌው-ህወሓት› እና ብአዴን በ‹ራዕይ› ስም ኃይል የማጠናከር እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ለመተቸትና ለማደናቀፍ መሞከራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ሁናቴም ልዩነቱ ከተገለፀባቸው ምልክቶች አንዱ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ሌላው እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ጉዳይ በዚህ ዓመት በዚሁ መፅሄት ላይ ‹‹አዲሱ የኢህአዴግ አሰላለፍ›› በሚል ርዕስ የቀረበው ፅሁፍም ‹‹የመለስ ራዕይ››ን የማይቀበለው ቡድን እያሸነፈ በመምጣቱ፣ የእነ አዜብ-አባይ ወልዱ ህወሓትን አዳክሞ፣ የእነ በረከት-ብአዴንን ከጎኑ ማሰለፍ መቻሉን የተተነተነበትን ጉዳይ የሚያጠናክር መሆኑን ነው፡፡
የሆነው ሆኖ አሁን መለስን የሚያመልኩት ሄደዋል፤ በቦታውም እርሱ የሚያርቃቸው፣ እነርሱም ይፈሩት የነበረ ተተክተዋል፡፡ እናም በህልፈቱ ማግስት ድጋፍ ማሰባሰቢያ እና ኃይል ማጠናከሪያ ከመሆን አልፎ ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ሰማይ የሚያከንፍ፣ መና የሚያዘንብ ተደርጎ የነበረውን ‹‹የመለስ ራዕይ›› ታሪክ በማድረጋቸው፣ አርቀው መስቀል ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ አነጋገር በፋውንዴሽኑ አጥር ክልል ተወስኖ ይቀመጥ ዘንድ በይነዋል (በነገራችን ላይ ይህን ጉዳይ በዚህ ደረጃ ያነሳሁት የስርዓቱ መሪዎች ‹‹እንመራዋለን›› የሚሉትን ህዝብ በአደባባይ ሲዋሹ ቅንጣት ያህል ሀፍረት እንደማይሰማቸው ለማሳየት እንጂ፣ በግሌ መለስም ሆነ ጓደኞቹ ለስልጣናቸው ካልሆነ በቀር ሀገር የሚጠቅም ራዕይ አላቸው ብዬ አላምንም)
የ‹‹ሙስና››ውን ክስ ሂደት መሸፋፈን:
የእነ መላኩ ፈንቴን እስር ተከትሎ ‹‹ሙስና›› ዋነኛ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያምም ‹ጉዳዩን ራሴ እከታተለዋለሁ› የምትል ፉከራ ብጤም ሞካክራው ነበር (ቀደም ሲል በዚሁ መፅሄት የ‹ሙስና›ው ክስ በፖለቲካው የኃይል አሰላለፍ ላይ የበላይነትን ለመጨበጥ በአዲስ አበባው ህወሓት የተመዘዘ ‹‹ካርድ›› እንደሆነ መገለፁ ይታወሳል)
ባለሥልጣናቱ የታሰሩ ሰሞን ‹‹የመለስ ራዕይ›› ገና አልከሸፈም ነበርና ‹‹የፀረ-ሙስና ኮሚሽን›› ኮሚሽነር አሊ ሱለይማንም ጉዳዩን አቶ መለስ ራሱ ጀምሮት ለሁለት ዓመት ያህል ሲከታተለው ከቆየ በኋላ፣ በመጨረሻ ህይወቱ እንዳለፈ እያለቃቀሰ ነግሮን ነበር፡፡
ይሁንና
ከእስራ አምስት ቀን በፊት ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ባደረገው ቃለ-መጠይቅ፣ የታሰሩትን ሰዎች አስመልክቶ ከጊዜ ቀጠሮ ያለፈ ቁርጥ ያለ ነገር አለመኖሩ፣ በሌሎች ላይ ስጋት ስለመፍጠሩ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ‹ገድሉ›ን ከመለስ ወደራሱ (ከኋላው ወደአሉ ሰዎች) መልሶታል፡፡
‹‹በቅርቡ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ለማቃለል በሙስና የተጠረጠሩ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችና በሙስና ተግባሩ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተጠያቂ የሚሆኑበት ስርዓት ተዘርግቶ የመንግስት አካል የሆነው የፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ክስ መስርቷል፡፡››
ጥያቄውም ይህ ነው፡፡ ‹‹የአሊ ሱሊማንን ‹መለስ የጀመረው…› መግለጫንስ ምን እናድርገው?››
…ደመቀ መኮንንም ‹‹እዚያም እዚያም ከኃላፊነት የማውረድ፣ በሕግ የመጠየቅና ሕጋዊ እርምጃዎች ደረጃቸውን ጠብቀው ይቀጥላሉ›› ቢልም በመሬት ያለው ተጨባጭ እውነታ ግን የሚያሳየው ሙስና የተዘጋ አጀንዳ መሆኑን ነው፡፡ የ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የፊት ገፆችም ‹‹ሚኒስትር እገሌ…››፣ ‹‹ዳይሬክተር እገሌ… በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ›› ከሚል ዜና በብርሃን ፍጥነት ‹‹በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 10 የዲዛይንና ግንባታ ፍቃድ ጽ/ቤት፣ የግንባታና ዕድሳት ባለሙያ የነበረችው ግለሰብ መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም አራት ሺ ብር ጉቦ ስትቀበል በፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ተያዘች›› ወደሚል ቧልት ተቀይረዋል፡፡
አቦይ ስብሃት ነጋ ከላይ በጠቀስኩት መፅሄት የሙስናውን ጨዋታ የገለፁት እንዲህ በማለት ነበር፡-
‹‹አሁንም ድረስ ያልተፈቱ የአካሄድ (የአሰራር) ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ‹ሙስና አለ› ብትል፣ ሙስና በስርዓቱ ላይ በሚያደርሰው አደጋ ላይ ከማተኮር ይልቅ ‹አንተስ ከሙሰኛነት ነፃ ነህ ወይ?› በማለት ዋናው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልሱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ አሁንም ቢሆን ይህንን የከፋ ድርጅታዊ ጉዳይ (ችግር) በመጋረጃ ሸፋፍኖ ለማለፍ ‹ስብሃት ለምን በጊዜው ጉባኤው ላይ አላቀረበውም ነበር› የሚሉ አይጠፉም የሚል ግምት አለኝ፡፡ በበኩሌ ይህ ነገር በሌላ ላይ ጊዜው ሲደርስ የሚነሳ ይሆናል ነው የምለው:፡››
በርግጥ የአቦይ ወቀሳ እውነት ነው፡፡ ይሁንና ጉዳዩን በጉባኤው ላይ ያላነሱበት ምክንያት ‹‹በሌላ ላይ ጊዜው ሲደርስ የሚነሳ ይሆናል›› በሚል እንደሆነ ለመናገር መሞከራቸው ግን የክፍለ ዘመኑ አስቂኝ ቀልድ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም፤ ባይሆን ‹‹አንተስ ከሙሰኛነት ነፃ ነህ ወይ?› ይሉኛል ብዬ ተውኩት›› ቢሉን፣ ቢያንስ ለግልፅነታቸው ባርኔጣ እናነሳ ነበር፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የኢህአዴግ ሰዎችን የሙስና ወንጀል በህግ የሚያስጠይቅ ከሆነ አቦይ ስብሃት ከፊት መስመር መሰለፋቸው አይቀርምና፡፡ ሌላው ቀርቶ አርከበ እቁባይ ለጊዜው ገለል እንዲል (ከሀገር እንዲወጣ) የተደረገው ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የመረጃ ምንጮቼ ነግረውኛል፡፡ አርከብ፣ አቦይን ጨምሮ ከታሰሩት ባለሀብቶች ውስጥ ጥቂቶቹ በስጋ ዝምድናና በጋብቻ የተሳሰሩት የመሆኑ ጉዳይ ይመስለኛል ‹ማዕበሉ እስኪረጋ› ከዕይታ እንዲርቅ የተደረገበት ምስጥር፡፡ በተቀረ አርከበ ሀገር ጥሎ ኮበለለ፣ ኢህአዴግን ከዳ… ጂኒ ቁልቋል የሚሉት የፒያሳ ወሬዎች፣ አንድም ወቅታዊውን የኢህአዴግ አሰላለፍ ካለመረዳት ሊሆን ይችላል፤ አሊያም የጉዳዩ ባለቤቶች ስራዬ ብለው የተሳሳተ መረጃ በሚያስተላልፉበት በተለመደው ሰርጥ ያሰራጩት ማስቀየሻ ነው የሚሆነው፤ አርከበ የሄደው አቦይ እንዳሉት ‹‹አንተስ ከሙስና ነፃ ነህን?›› የማለቱ አቅም ያላቸውን አጉረምራሚ ሰዎችን ለማለዘብ ነው፡፡ ምናልባት የመቀሌው ህወሓት አሸንፎ ቢሆን ኖሮ እውነትም አርከበ ከቃሊቲ ይልቅ አሜሪካ ይሻለዋል ማለታችን አይቀርም ነበር፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በእጁ ላይ ካቴና ለማጥለቅ አያመነቱም፡፡ ግና! የሆነው በተገላቢጦሹ ነው፡፡ …ማን ነበር ‹‹አባቱ ዳኛ…›› ያለው? (በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የሙስና አዋጁንም በዚሁ ዓመት የማሻሻል ዕቅድ አለው፡፡)
የአፈናው ዝግጅት:
ስርዓቱ በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገው አምስተኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫን ከወዲሁ ‹የቤት ስራን በማጠናቀቅ› ካልተዘጋጀንበት፣ ያልተጠበቀ አደጋ ሊያመጣብን ይችላል ወደሚል ጠርዝ የተገፋው አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ በተለያየ ጊዜ በጠሩት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኘው ህዝብ ቁጥር አሳስቦት ብቻ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ያለ መለስ ዜናዊ የሚጋፈጠው የመጀመሪያው ምርጫ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ እንደሚታወሰው አቶ መለስ ሁሉንም የሥልጣን ምንጮች ጠቅልሎ የያዘ ‹ጠንካራ ሰው› (Strong Man) በመሆኑ፣ በእንዲህ አይነት ወቅት የሚመጡ ድንገቴ አደጋዎችን ለመቋቋም ብዙም ሲቸገር አይስተዋልም ነበር፡፡ ይሁንና በቀጣዩ ምርጫ አንድም በድርጅቱ ውስጥ የእርሱ አይነት ተተኪ ሰው አለመኖሩ፣ ሁለትም ምንም እንኳ ከህልፈቱ በኋላ የተፈጠረው ልዩነት በአንፃራዊነት የተረጋጋ ቢመስልም፣ ለሌላ ዙር የክፍፍል አደጋ አለመጋለጡ አስተማማኝ ባለመሆኑ ስጋት መፍጠሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአናቱም ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የተከሰተው አለመግባት እና በማህበረ ቅዱሳን ላይ ተፅእኖ ለማድረግ የመሞከሩ ጨዋታም ለተቀናቃኞች ያልተጠበቀ ኃይል ሊሆን የሚችልበት ዕድል ቢፈጥርስ የሚል ስጋት አለ፡፡
የባለሥልጣናቱ በአደባባይ የማስፈራራት መግፍኤም ይኸው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም በቃለ-መጠይቁ ላይ ተቃዋሚዎችን (አንድነትና ሰማያዊን) እና የሀይማኖት ማህበራትን ለማስፈራራት ከሰባት ጊዜ በላይ የመለስን ‹‹ቀይ መስመር›› አገላለፅ ተጠቅሞበታል፡፡ በተለይም ሁለቱ ፓርቲዎች የያዙት በሠላማዊ ሠልፍ ተፅዕኖ የመፍጠር መንገድ ተከታዮቻቸውን እያበዛ እና የፈዘዘውን የፖለቲካ ተሳትፎ እያነቃቃው መሆኑን ግንባሩ ጠንቅቆ የተረዳው ይመስለኛል፡፡ በኃ/ማሪያምም በኩል ያስተላለፈው መልዕክትም ቀጣዩን የፖለቲካ ሴራ አመላካች ነው፡-
‹‹መታወቅ ያለበት አንድ ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚጠየቅ ከሆነ፣ እኛም አንድ ቦታ ስንደርስ ‹ለዚህ ጥያቄ ብዙ ጊዜ መልስ ሰጥተናል፤ ጥያቄው ይህ ከሆነ የሠልፍ ትርጉም ምንድነው?› ብለን የምናቆምበት ደረጃ እንደርሳለን፡፡ ምክንያቱም ሠልፍ ለዘላለም የሚካሄድበት ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡››
በተመሳሳይ መልኩ የሃይማኖት ማህበራት የሚያነሱትን የመብት ጥያቄም ወዴት ሊገፋው እንደሚችል ጥቁምታ ሰጥቷል፡-
‹‹የሀይማኖት ግብንም አክራሪዎች በምድር ላይ ሊሰሩ የሚፈልጉትን ግብ ሁለቱን የሚያምታቱ ሰዎች አሉ፤ የሌላውን ግብ በምድራዊ ዓለማዊ ማሳካት ስለማይቻል፣ እነዚህ ፖለቲከኞች ይዘዋቸው እንዳይነጉዱ፣ ከህዝብ እንዲነጠሉ ምክር ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ የሚታወቁ ስላሉ፡፡ በተለይ ወጣቶች፣ ከወጣቶችም ወጣት ሴቶች በአሁኑ ወቅት በዚህ ውስጥ ተሳትፈው የሚጓዙ እንዳሉ በግልፅ ይታወቃሉ፡፡ መንግስት በዚህ ደረጃ ለእነዚህ አካላት መልዕክት ማስተላለፉ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡››
የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን በሚንስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚመራው ሽመልስ ከማልም ከ‹‹ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)›› ጋር ያደረገውና ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም በታተመው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ላይ በወጣው ቃለ-ምልልስ እንደተለመደው ጉዳዩን በተመለከተ ጠንከር ያለ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ለማስተላለፍ የፈለገ (የታዘዘ) መስሎ አግኝቸዋለሁ፡-
‹‹አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጉን እናሰርዛለን፣ ሕጉ ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ነው ብለው በአደባባይ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰሙ የሚታዩና በተዘዋዋሪ መንገድ ከሽብርተኞች ጋር ለሽብርተኞች የሞራል ድጋፍ ሲሰጡና ሲቸሩ የምናያቸው አንዳንድ ወገኖች ሳያውቁ፣ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በቀና መንገድ ተሳስተው ነው የሚል ግምት ሊኖር የሚገባው አይመስለኝም፡፡
እነዚህ ወገኖች አውቀው ነው ይህንን ሥራ የሚሰሩት፤ በስሌት ነው ይህን የሚከናውኑት፡፡››
በእርግጥም የስርዓቱ የሴራ ቀማሪዎች ‹‹አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ የፈጠሩት መነቃቃት፣ በጊዜ ካልተቋጨ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ‹ባልታወቀ ስፍራ የተኛ ሰይጣን ቀስቅሶ፣ ድንገቴ ማዕበል ሊያስነሳ ይችላል›› የሚለው ትንተናቸው ይመስለኛል ቀድሞም የጠበበውን ምህዳር ይበልጥ ለማጥበብ (ለመድፈን) ከወዲሁ እላይ-ታች እንዲሉ ያስገደዳቸው፡፡
እንደ መውጫ:
ስርዓቱ በብዙ መልኩ ያለ ስኬት ከሃያ ሁለት ዓመታት በላይ መጓዙ እርግጥ ነው፡፡ በተቃውሞ ሰፈርም ይህንን ሁናቴ ለመለወጥ አብዛኛውን ዓመታት የበረዶ ያህል ቢቀዘቅዝም፣ አልፎ አልፎ እየጋመ ለውጥ ለማምጣት ያደረገው ሙከራ፣ አገዛዙ ካከማቸው ኃይል ጋር ባለመስተካከሉ ደጋግሞ መምከን አሳዛኝ ዕድል ፈንታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት የተያዘው ዕቅድም ከቀድሞ በባሰ መልኩ፣ ለመደራጀት የሚውተረተረውን ኃይልም ሆነ ተበታትኖና ተከፋፍሎም ቢሆን ለውጥ የሚጠይቀውን ህዝብ በተለያየ መንገድ ማቀዝቀዝ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ጉዳዩን በደንታቢስነት ማየቱ ይህ እውን ሆኖ የ2002ቱ የምርጫ ድል፣ በ2007 ዓ.ምም ይደግም ዘንድ ፍቃድ የመስጠት ያህል ነው የምለው፡፡
አሁንም አረፈደም፡፡ ነገር ግን ፈረንጅኛው እንደሚለው ‹‹እውነቱ ግድግዳው ላይ ተፅፏል›› የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ለውጥ ፈላጊ ዜጎች… ስርዓቱ ለህዝብ ፍላጎት ይገዛ ዘንድ ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ (በሰላማዊ ትግል ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ) አማራጮችን ከመተግበር ውጪ ጠረጴዛው ላይ የተቀመጠ ተጨማሪ ‹የዕድል ቁጥር› አለመኖሩን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡