FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Saturday, October 19, 2013

በልማት “ማሳበብ” ከልማታዊ መንግስት አይጠበቅም!

በመንግስት “ሳንባ” መተንፈስ ለ“ቲቢ” ያጋልጣል

ፖለቲካዊ ወጋችንን የምንጀምረው በቀልድ ነው፡፡ ግዴለም ባትስቁም አልቀየማችሁም፡፡ ፈገግ ካላችሁ መች አነሰኝ! (ኑሮ “ሃርድ” ሲሆን ሳቅም ይገግማል አሉ) ይልቅስ ሳልረሳው ቀልዱን ቶሎ ልንገራችሁ፡፡ - ፡፡ አንድ የሰው አገር ሰው (ፀጉረ ልውጥ ማለቴ አይደለም!) ከጅቡቲ እየተጫኑ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡትን የመኪኖች መዓት በትዝብት ሲመለከት ይቆይና እነዚህ ሁሉ መኪኖች የት ነው የሚገቡት?” ሲል ይጠይቃል፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊም (መሬት ይቅለላቸውና!) “የሌሎቹን አላውቅም…አይሱዙ ግን ገደል ነው የሚገባው” አሉ (አሉ ነው!) 
በነገራችሁ ላይ… በመዲናዋ የሚርመሰመሰው የመኪና ብዛት እኮ ከነዋሪው እኩል ሊሆን ትንሽ ነው የቀረው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን ባለሀብቱም ሆነ ሌላው ትንሽ ገንዘብ እጁ ላይ ከተረፈው ዝም ብሎ መኪና የሚያስጭን ነው የሚመስለኝ። (ጀት ለማስጫን አቅም የለችማ!?) እናላችሁ… የመዲናዋ ተሽከርካሪዎች ከህዝቡ በልጠው መፈናፈኛ ከማጣታችን በፊት “አራርቆ መግዛት” የሚል ፖሊሲ ቢቀረጽ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ (“አራርቆ መውለድ” እንደሚባለው) ትራፊክ ፖሊስና መንገድ ትራንስፖርት ጥናት አላደረጉ ይሆናል እንጂ የመኪና አደጋ እንዲህ ህዝብ የሚፈጀው የተሽከርካሪው ቁጥር ያለቅጥ በዝቶ ሊሆን ይችላል እኮ! (“የመኪና ምጣኔ” ሳያስፈልገን አይቀርም!)
እኔ የምላችሁ…ባለፈው ሳምንት የኢቴቪ “ዓይናችን” ፕሮግራም ላይ ከመንጃ ፈቃድ አወጣጥና የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ት/ቤቶች አሰራር ጋር በተገናኘ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የሰጡትን ምላሽ ሰምታችሁልኛል? ሃላፊዋ የተናገሩትን በአማርኛ ተርጉሞ ለነገረኝ (የገባው ካለ ማለቴ ነው) ወሮታውን እከፍላለሁ፡፡
ቆይ ግን ኢህአዴግ ሌላ ቋንቋ ጀመረ እንዴ? (የደበቀን የትግል ሜዳ ቋንቋ ካለው ብዬ እኮ ነው!) ሃቁን ልንገራችሁ አይደል….ሴትየዋ ከተናገሩት ውስጥ በትክክል የገባኝ “ኪራይ ሰብሳቢነት” የምትለዋ ቃል ብቻ ናት፡፡ እሱም የገባኝ ቃሏን ስለደጋገሟት ነው፡፡ ከ10 ጊዜ በላይ እኮ “ኪራይ ሰብሳቢ” የምትለዋን ቃል ጠቅሰዋል፡፡ (አጋነንኩት እንዴ?)
በነገራችሁ ላይ… “ዓይናችን” ፕሮግራም በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ት/ቤቶች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች የሚያጋልጥ (በአራዳ ቋንቋ “አቧራ የሚያስነሳ”) ዘገባ ባቀረበ ጥቂት ቀናት ውስጥ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጡ ናቸው ከተባሉት ማሰልጠኛዎች መካከል 40 ያህል ት/ቤቶች ሰሞኑን ተዘግተዋል፡፡ (እንኳን ማሰልጠኛ የአሜሪካ መንግስትም Shut down ተደርጓል!)፡፡
እናንተዬ… ፕሬዚዳንት ኦባማ ያመጡት የጤና ዋስትና ሽፋን (Obamacare) ጉድ አፈላ እኮ! እንግዲህ በአሜሪካ እንደኛ አገር አንድ አውራ ፓርቲ ሳይሆን ሁለት አውራ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡ ዲሞክራትና ሪፐብሊካን፡፡ (በአሜሪካ ሰማይ ሁለት ፀሐይ መውጣት ይፈቀድለታል ማለት ነው!) እናላችሁ …ባለፈው ሳምንት የመንግስት ባጀት እንዲፀድቅ በኮንግረስ ሲቀርብ ሪፐብሊካኖቹ ስውር ደባ ፈፀሙ ተባለ፡፡ “የጤና ዋስትና ሽፋን ፖሊሲው ካልተሰረዘ ባጀቱን አናፀድቅም” ብለው ገገሙ፡፡ ሁለቱ የአሜሪካ አውራ ፓርቲዎች እልህ ውስጥ በመገባባታቸውም የበጀቱ ጉዳይ ሳይፀድቅ ቀረ፡፡ በዚህም የተነሳ የአሜሪካ ፌደራል መንግስት ተቋማት በሙሉ ካለፈው ማክሰኞ ተሲያት በኋላ ተዘጉ - ከመከላከያና የፖሊስ ሃይል በስተቀር፡፡ ስሙ ደሞ “Government Shut down” ይባላል። እናላችሁ… ባጀቱ እስኪፀድቅ ድረስ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ የፌደራሉ መንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ላይከፈላቸው ይችላል ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ የመንግስት መ/ቤቶች በር ላይም “የፌደራል መንግስቱ ስራ ስላቆመ አገልግሎት አንሰጥም” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል፡፡ ዋሺንግተን በሚገኝ አንድ ፓርክ በር ላይ የተለጠፈው ማስታወቂያ “Because of The Federal Government Shut down All National parks are closed” ይላል፡፡ ወደ አሜሪካ!…የማታሰማን ጉድ የለም እኮ! (መንግስት የሚዘጋበት አገር!) እኔን ከሁሉም የገረመኝ ግን ምን መሰላችሁ? የመንግስት መ/ቤቶች በሙሉ ተዘግተው ህይወት መቀጠሉ! በነገራችሁ ላይ… የዛሬ 17 ዓመትም በክሊንተን ዘመን ለ28 ቀን ገደማ የአሜሪካ ፌደራል መንግስት ስራ አቁሞ ነበር፡፡ እስቲ አስቡት…እኛ አገር እንኳን 28 ቀን ሁለት ቀን “ልማታዊ መንግስታችን” ስራ ቢያቆም የሚፈጠረውን ምስቅልቅል
ለነገሩ…የእኛ አገር አንዳንድ የመንግስት ተቋማት እኮ እንኳን ተዘግተው ሳይዘጉም የተዘጉ ያህል ናቸው፡፡ (አሁን ለምሳሌ መብራት ሃይል አልተዘጋም ብሎ የሚከራከረኝ አለ?) አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ተከርችመው የዕለት ተዕለት ህይወት የማይስተጓጐለው ህዝቡ በመንግስት ሳንባ ሳይሆን በራሱ ሳንባ ስለሚተነፍስ ነው ይላሉ፡፡ “እኛ ግን መንግስት ድንገት shut down” አብረን shut down እንሆናለን፤ ምክንያቱም የምንተነፍሰው በመንግስት ሳንባ ነዋ!” ሲሉ ይተነትናሉ - ባለሙያዎቹ፡፡ (እንዴ የራሳችን ሳንባ የት ሄዶ ነው?)
ይኸውላችሁ… በአሜሪካ የመንግስት መ/ቤቶች ተዘግተዋል ቢባልም መሰረታዊ አገልግሎቶች እኮ አይቋረጡም፡፡ ለምን መሰላችሁ… እንደኛ አገር “የምትታለብ ላም” ምናምን አይሰራማ! መብራት፣ ውሃ፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌ፣ ባንክ ወዘተ ሁሉም በግሉ ዘርፍ ስር ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስትም በራሱ ሳንባ፣ ህዝብም በራሱ ሳንባ ይተነፍሳሉ ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው ግን… እኛ አገር ህዝብና መንግስት በአንድ ሳንባ ሲተነፍሱ የጤና ችግር አያስከትልም እንዴ? መንግስት አያድርስበትና በቲቢ ከተጠቃ እኮ የአበሻ ዘር አብሮ ማለቁን ነው፡፡ (ጤና ጥበቃ እያለ?) “በአውብቶስ ስትሄዱ መስኮት በመክፈት ቲቢን ተከላከሉ” ማለት ብቻውን እኮ አይበቃም (በአንድ ሳንባ መተንፈስስ?) እባካችሁ ለኢቴቪ “ጤናዎ በቤትዎ” ፕሮግራም እቺን ጥያቄ ጠይቁልኝ። (ወሮታውን እንደተለመደው እከፍላለሁ!)
አንድ ዘወትር ከመንግስት ሹመኞችና ከኢህአዴግ ካድሬዎች አፍ የማትጠፋ አባባል አለች። (ፕሮፖጋንዳ ልትሆን አንድ ሃሙስ የቀራት!) “ወጣቱ ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ መሆን አለበት” ትላለች፡፡ እውነት ለመናገር… አባባሏ እኮ እንከን የማይወጣላት ወርቅ አባባል ናት፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? በመንግስት ሳንባ እየተነፈሱ የራስን ሥራ መፍጠር ከባድ ነው፡፡ (የመተንፈስ ነፃነት ይቀድማል ወይስ ሥራ መፍጠር?) እናም መንግስት “ሥራ ፍጠሩ” የሚለው ከአንጀቱ ከሆነ በራሳችን ሳንባ የመተንፈስ ተፈጥሮአዊ፣ ሰብአዊና ጤናዊ መብታችንን ያስከብርልን (ያክብርልን ማለቴ ነው!) በነገራችሁ ላይ …ይሄ የመብት ጥያቄ ወደው በመንግስት ሳንባ የሚተነፍሱ ወገኖችን (“በአንድ ሳንባ እንተንፍስ” ባዮችን) አይመለከትም፡፡ ያለፍላጐታቸው ተገደው በመንግስት ሳንባ የሚጠቀሙትን ብቻ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በመንግስት ሳንባ በመተንፈስ የመብት ጥሰት የተፈፀመባችሁ ወገኖች …በቅርቡ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል፡፡ (መስተዳድሩ ከፈቀደ ማለት ነው!)
አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለምንድነው መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለትንሹም ለትልቁም ልማቱን “ሰበብ” ማድረግ የጀመረው? (ይሄ ከልማታዊ መንግስት አይጠበቅም!) ተቃዋሚዎች ለሰላማዊ ሰልፍ ቦታ ሲጠይቁ፣ ከጃንሜዳ ሌላ ቦታ የለም ብሎ በልማቱ ማሳበብ አይደንቅም? (ጦቢያ በቦታ ትታማለች?)
ጠዋትና ማታ ለሚያሰቃየን የትራንስፖርት እጥረት መፍትሔ ከመሻት ይልቅ በልማት ማሳበብ ምን ይባላል? ለመብራት መቆራረጥ፣ ለውሃ መጥፋትና ለኔትዎርክ መንቀራፈፍ አሁንም ሰበቡ የፈረደበት “ልማት” ሆኗል፡፡
ትንሽ ከታገስነው ደግሞ አንድ ቀን፣ የህዝቡን ቅሬታና እሮሮ ለመስማትም “ልማት ላይ ስለሆንን ፋታ የለንም” ይለን ይሆናል፡፡ (ልማት ጆሮ ይደፍናል እንዴ?) የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ግን ጆሮ የሚደፍነው ሌላ ነው ባይ ናቸው) (ቃል በቃል ሳይሆን ሃሳባቸውን ነው) “የስልጣን ቁጥር በጨመረ መጠን ጆሮ መስማቱን ይቀንሳል” ብለዋል፡፡ እናላችሁ…ትክክለኛ ልማታዊ መንግስት ልማቱን በማናቸውም ሁኔታ ሰበብ አያደርግም ለማለት ያህል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “አገሪቱን ለማልማት 30 እና 40 ዓመት በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ” ማለትም ልማቱን ማርከስ ነው ይላሉ - የልማት ኤክስፐርቶች፡፡ (ገዢ ፓርቲ ብቻ ነው የሚያለማው ያለው ማነው?
በነገራችሁ ላይ… ኢህአዴግም በመንግስት ሳንባ ከመተንፈስ እንዲላቀቅ እንታገላለን፡፡ (ባለውለታችን እኮ ነው!)
ማሳሰቢያ
በመንግስት ሳንባ መተንፈስ “ጥገኝነት” ለተባለ ቫይረስ እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ይጠቁማሉ!

No comments:

Post a Comment