FREE ALL POLITICAL PRISONERS

FREE ALL POLITICAL PRISONERS
FREE ALL POLITICAL PRISONERS

Sunday, October 6, 2013

የምርትና የሕዝብ እድገት እሽቅድድም

መሬት የማነው? ክፍል ሁለት ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

farmer1


እአአ በ1798 (ከሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት በፊት) መምሬ ቶማስ ሮበርት ማልቱስ የሚባል የ32 ዓመት የብሪታንያ ቄስ የዘመኑን የነገረ ንዋይ አስተሳሰብ የለወጠ አዲስ ሀሳብን የያዘ መጽሐፍ አሳተመ፤  ሀሳቡ በጣም ግልጽ ነበረ፤ የሰው ልጆች ቁጥር እድገት መጠኑ እያጠፈ የሚሄድ ነው፤  የሕዝብ ቁጥር 1፣ 2፣ 4፣ 8፣ 16፣ 32፣ 64፣ 128፣  እያለ የሚጨምር ነው፤ ከእርሻ የሚገኘው ምርት ደግሞ የእድገቱ መጠን አያጥፍም፤ 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7፣ 8፣ 9፣ 10፣ እያለ የሚሄድ ነው፤  የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ በሌላ መንገድ ካየነው የበላተኞች ቁጥር እያጠፈ ሲያድግ የምግቡ አቅርቦት የሚያድገው ግን በጣም በዝግተኛ ፍጥነት ነው፤ የሚል ነው፤  እንግዲህ የሕዝብ ቁጥርና የምርት አቅርቦት እኩል መጓዝ ሲገባቸው የሕዝቡ ቁጥር እየቀደመ ስለሚገኝ፣ መምሬ ማልቱስ የደረሰበት መደምደሚያ የሕዝቡን ቁጥር ለመቀነስ በሰው ልጆች መሀከል በሽታ፣ ችጋርና ጦርነት የማይቀሩ ይሆናሉ፤ ችጋር፣ ጦርነትና ሌሎችም አደጋዎች በሕዝቦች ላይ እየደረሱ የሕዝብ ቁጥርና የምርት እድገት በሚያደርጉት መሽቀዳደም መሀከል ሚዛንን ይጠብቃሉ።
መምሬ ማልቱስ በነበረበት ዘመን ላይ ሆኖ ከሃምሳና መቶ ዓመታት በኋላ እውቀትና (ሳይንስ) የእውቀት ጥበብ የሚያስከትሉትን መሠረታዊ የአስተሳሰብ፣ የአሠራርና የኑሮ ለውጥ ለመገንዘብ አልቻለም፤ እንዴት ብሎ? በመምሬ ማልቱስ ዘመን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው ምርት አምስት ኩንታል ብቻ ቢሆን በኋላ ግን በአንድ ሄክታር ላይ በእውቀትና በእውቀት ጥበብ ኃይል ምርቱን ከእጥፍም በላይ ማምረት የሚቻልበት ዘመን መጣ፤ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የተለያዩ የእርሻ ዘዴዎች የእርሻውን ሥራ ቀልጣፋና ምርታማ አደረጉት፤ በዚህም ምክንያት የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ ብዙ ሰዎች ይነቅፉት ጀመር፤ ሆኖም የመምሬ ማልቱስን ሀሳብ ዛሬም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ጊዜ አልሻረውም፡፡
ከመሠረት ለመጀመር — አንድ አገር መሬት አለው፤ ሕዝብ አለው፤ መሬትም ሆነ ሕዝብ በጥሬአቸው ከቆሙ የመምሬ ማልቱስ ትንተና መደምደሚያ መሬቱ ከሚችለው በላይ የሆነውን ሕዝብ ችጋር፣ በሽታና ጦርነት ያነሣዋል፤ መሬትና ሕዝብ ብቻ አገርን አያቆሙም፤ በሕዝብ መሀከል ያለውን ግንኙነት፣ እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ጋር ያለውን አብሮ የመኖር ትስስር ሕግና ሥርዓት እንዲኖረው ያስፈልጋል፤ የመሬትም ሀብት አጠቃቀም በእኩልነትና በፍትሐዊነት ዘዴ ለመደልደል ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋል፤ እንግዲህ ሕዝቡ ኑሮውን በሕግና በሥርዓት ለመምራት አንድ መንግሥት የሚባል እንደእድር ያለ ድርጅትን ይፈጥራል፤ እያንዳንዱ ሰው በግሉ የኑሮ ጣጣ ተወጥሮ በሚራወጥበት ጊዜ መንግሥት የሚባለው ድርጅት ለጠቅላላው ማኅበረሰብ የሚበጀውን ይሠራል።
በእያንዳንዱ ሰው የኑሮ ግዴታ መሬቱ ያለማቋረጥ በጥቅም ላይ እየዋለ በግጦሽና በእርሻ፣ በሌሎችም ምክንያቶች እየተጎዳ ይሄዳል፤ በዚህም የተነሣ መሬቱ የሚሰጠው ጥቅም በያመቱ ይቀንሳል፤ የመሬቱ መደህየት ከሕዝብ መደህየት ቀድሞ ይመጣል ማለት ነው፤ እንግዲህ መንግሥቶች የሚቋቋሙት እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ ከተፈጠረም ብዙ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነው፤ በኢትዮጵያ ስለኢትዮጵያ የሚፈበረከው የአሐዝ መረጃ ወይም ስታቲስቲክስ አስተማማኝ ነው ባይባልም አማራጭ ባለመኖሩ ልንጠቀምበት እንገደዳለን፤ ለምሳሌ በ2004 ዓ.ም. የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት የታረሰው መሬት 13 690 119 ሄክታር ነበር ይባላል፤ የስታቲስቲክስ መሥሪያ ቤት ገበሬዎች ሳይሆን ባለይዞታ የሚላቸው 14 747 439 ይሆናሉ፤ ይህንን ቁጥር በአምስት ስናባዛው (በአንድ የገጠር ቤተሰብ በአማካይ አባሎች) 73 737 195 ይሆናል፤ ይህንን ቁጥር ከ2007 የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ጋር ማስተያየቱ ያስተምራል፤ ከዚያም በላይ አንዳንዶቹ ቁጥሮች በሌላ ቦታ አይደገሙም፤ ወይም መልካቸውን ለውጠው ይቀርባሉ።
ለጊዜው ግን ለያዝነው ርእስ የሚከተሉትን አሐዞች እንመልከት፤ በመጀመሪያው ሰንጠረጅ ባለይዞታ የተባሉት ገበሬዎችና የታረሰው መሬት (በሄክታር) በሦስት ዓመት ውስጥ ያሳዩትን ለውጥ ለማሳየት ይሞክራል፤ ሠንጠረጅ ሁለት ደግሞ የእርሻ ምርት (እህል፣ ጥራጥሬና የቅባት ዘር) ከገበሬው ቁጥር ጋር ለማነጻጸር ይሞክራል፤ ኢትዮጵያ የተአምር አገር መሆንዋን ተንተርሶ የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት የእርሻ መሬቱንም በ2004 ዓ.ም. ትንሽ አሳድጎታል፤ አይቻልም ማለት አይደለም፤ በመስኖና በእርከን የእርሻውን መሬት መጨመር ይቻላል።
ሠንጠረጅ አንድ
የታረሰ መሬትና (በሄክታርየገበሬዎች ቁጥር 2002-2004 .
ዓ.ም.
ባለይዞታ
እድገት ከመቶ
መሬት (ሄክታር)
ካለፈው ዓመት እድገት ከመቶ
አማካይ ድርሻ
መሬት ለባለይዞታ(ሄክ)
2002
13439174
100.0
12953636
100.0
0.96
2003
14789071
110.0
13358883
103.13
0.90
2004
14747439
109.7
13690119
105.69
0.93
ምንጭ የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት ድረ-ገጽ
ዋናው ነጥብ ግን የስታቲስቲክስ ጽ/ቤት የፈለገውን ያሀል ቢጠማዘዝም እውነቱን እምብዛም ሊለውጠው አልቻለም፤ የቁጥር ነገር ወዲያ ቢሉት አራት፣ ወዲህ ቢሉት አራት ሆነና በአማካይ የአንድ ገበሬ እርሻ አንድ ሄክታር እንደማይሞላ መሸሸግ አልተቻለም፤ በእርሻ መሬቱ ላይ ያለው ጭነት በጣም ከፍተኛ ነው፤ እውነተኛውን የሕዝብ ቁጥር ብናውቅ ደግሞ ጭነቱ ምን ያህል የበለጠ እንደሆነ እንረዳ ነበር፤ የዓለም ባንክና የአሜሪካው ዓለም-አቀፍ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀጥር በአሁኑ ጊዜ ከዘጠና ሚልዮን በላይ ያደርሱታል፤ በአገር ውስጥ የሚነገረው ቁጥር ግን በሰባና በሰማንያ መሀከል ነው፤ የዛሬ ሠላሳ አምስትና አርባ ዓመት ግድም በደቡብ (በተለይ በከምባታና ሀድያ፣ በወላይታና በሲዳሞ፣ በደራሳ) የሕዝብ ቁጥር የሚፈነዳ እንደሆነ ተናግሬ ነበር፤ በትግራይና በወሎም፣ በሰሜን ሸዋም በመሬቱ ላይ ያለው ጭነት ከባድ ነው።
ሠንጠረጅ ሁለት
የእርሻ ምርትና (አህል፣ጥራጥሬና የቅባት) የገበሬዎች ድርሻ
ዓ.ም.ምርት ኩንታል ካለፈው ዓመት እድገት ከመቶየባለይዞታ ቁጥርየባለይዞታ/የዓመት ድርሻ ኩንታልየአንድ ሰው የወር ድርሻ ኪሎ
2002
180758897
100.0
13439174
13.45
22.25
2003
203485288
112.57
14789071
13.76
22.92
2004
218569429
120.92
14747439
14.82
24.67
ባለይዞታ ምናልባት በአማካይ አምስት ሰዎችን ያካትታል፤ ነፍስወከፍ እያንዳንዱን ሰው ይመለከታል።
በእነዚህ ሁለት ሠንጠረጆች ላይ በግርድፍ (መረጃው ነው ግርድፍ!) የሚታየውን እውነት መሸሽግ አይቻልም፤ በወር 25 ኪሎ እህል ከችጋር  አለመውጣትን ያሳያል፤ መሬት ተትረፍርፎ ሠራተኛ ሕዝብ የጠፋበት አገር አንዳልሆነም ይታያል፤ ታዲያ ለህንድና ለቻይና፣ ለሌሎችም መሬት በችሮታም ሆነ በሽያጭ የምንሸጥበት ምክንያት ዕብሪት ከወለደው እብደት ሌላ ምን ሊኖር ይችላል?
መሬት የማን ነው? ክፍል አንድ – ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

No comments:

Post a Comment